ምንጭ: የተባበሩት መንግስታት ድርጂት መረጃ ማዕከል
ቦርከና
ጥቅምት 13 ፤ 2011 ዓ.ም.
በነገው ዕለት የፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመን የመልቀቂያ ጥያቄ ለማጽደቅ የተጠራው የህዝብ ተወካዮች እና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች ልዮ ስብሰባ (በዚህ ዓመት ሁለተኛው ልዮ ስብሰባ መሆኑ ነው) በሚለቁት ፕሬዝዳንት ምትክ አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴን ይሾማል ተብሎ እንደሚጠበቅ በአፍቃሬ ህወሓትነት የሚታወቀው የሆን አፌይርስ ዛሬ ዘግቧል።
ዜናው እውነት ከሆነ ሳህለወርቅ ዘውዴ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ይሆናሉ ማለት ነው።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው የሁለት ልጆች እናት የሆኑት ሳህለወርቅ ዘውዴበተለያዮ የፈረንሳይኛ ቁዋንቋ ተናጋሪ የአፊሪካ ሃገራት የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን ለረዥም ዘመን አገልግለዋል።
የ አንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አዲስ አበባ በሚገኘው የሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት እና የዮኒቨርስቲ ትምህርታቸውን በፈረንሳይ ሀገር ሞንተፔለ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ያጠኑት በዚያው በፈረንሳይ ሃገር የኢትዮጵያ አምብሳደር በመሆንም ሰርተዋል።
እ.ኤ.አ በ2011 ደሞ በወቅቱ የተባባሩት መንግስታት ድርጂት ጸሃፊ የነበሩት ባን ኪሙን በናይሮቢ የተባበሩት መንግስታት ጽ ቤት ዋና ሃላፊ የስራ መደብ ሾመዋቸው ለዓመታት አገልግለዋል።
በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ህብረት የተባበሩት መንግስታት ድርጂት ተወካይነት እያገለገሉ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል ፤ ሆኖም ከአዲሱ ሹመታቸው ጋር በተያያዘ ኃላፊነታቸውን በፈቃዳቸው መልቀቃቸውም ተሰምቷል።
ወቅታዊ እና ሚዛናዊ መረጃን ለማግኘት ቦርከናን በፌስ ቡክ ላይክ ያድርጉ።