ከጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ፤ (አሜሪካ)
ጥቅምት 14/2010
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በፌስ ቡክ (Facebook) ገፄ ላይ፤ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ ያውጅ የሚል ሃሳብ አቅርቤ ነበር። ይህንን ካልኩ ጥቂት ሳምንታት ቢያልፉም፤ በዶ/እ አብይ አስተዳደር በኩል፤ በስርዓተ አልበኞች ላይ ጥርስ ያለው እርምጃ ባለመወሰዱ፤ የዜጎችን የመኖር ዋስትና የሚፈታተን ሕገ ወጥነት በብዙ የሃገሪቱ አካባቢዎች እየታየ ነው። በአሁኑ ወቅት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሥርዓተ አልበኝነት እየባሰበት በመምጣቱ እና፤ በተለይም ደግሞ፤ በቅርቡ በዶ/ር አብይ አስተዳደር ላይ ተቃጥቶ የነበረው “መፈንቅለ መንግሥት” ይህንን ሃሳቤን የበለጠ እንዳጠናክር አድርጎኛል። ብዙውን ጊዜ ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲነገር፤ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ፤ ለረጅም ዓመታት በአምባገነኖች መዳፍ ስር ለነበሩ ሕዝቦች፤ የሚፈጥረው ስሜት እና ትዝታ መጥፎ እንደሆነ ይገባኛል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መጥፎ እና አደገኛ ጎን ያለውን ያክል፤ ሕግን እና ሥርዓትን በተከተለ ሁኔታ አዋጁ ከተተገበረ፤ ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ እንደሚችል ከሌሎች ሃገራት ልምዶች መገንዘብ ይቻላል። እዚህ እኔ በምኖርበት ሃገር፤ በተለያዩ ክፍለ ሃገራት፤ አደጋ በሚፈጠርበት እና ባንድ ጊዜ የበርካታ ዜጎችን ንብረት እና ሕይወት የሚጎዳ ነገር ሲከሰት፤ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ፤ ወታደር ወይም የክፍለ ሃገሩን ብሔራዊ ዘብ (National Guard) በክፍለ ሃገሩ በማሰማራት፤ ጸጥታ ያስከብራል፤ የዜጎችን ሕይወት እና ንብረትም ይጠብቃል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ፤ በተወሰነ ደረጃ፤ የዜጎችን፤ የድርጅቶችን እና የንግድ ተቋማትን መብት እና ነፃነት ይገድባል። ይህ ገደብ ግን በሕዝብ እና በተቋማት ቅሬታ የማይፈጥረው፤ በአዋጁ፤ የሕዝቡን እና የተቋማቱን፤ መብት እና ግዴታ ምን እንደሆነ በግልጽ በማሳወቅ እና ሕጋዊ በሆነ መንገድ ሲከናወን ነው። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ አንዳንድ በሃገሪቱ ሕገ መንግስት ውስጥ የተቀመጡ የመብት ሕግጋት መጣሳቸው አይቀሬ ቢሆንም፤ የእነዚህ መብቶች ለጊዜው መሸርሸር አስፈላጊነት እና ለሃገሪቱ ዘላቂ ሰላም የሚኖረው አንድምታ በግልጽ በማስገንዘብ ሕዝቡ እንዲተባበር ማድረግ ይቻላል። ለምሳሌ፤ ሕግ ጥሰዋል ተብለው የሚጠረጠሩ ሰዎችን ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ ማሰር፤ የሰዎችን መኖርያ ቤት እና የንግድ ተቋማትን ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ መፈተሽ፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሊደረጉ የሚችሉ ድርጊቶች መሆናቸውን፤ ለሕዝብ በማስገንዘብ፤ ሊነሱ የሚችሉ ቅሬታዎችን ማለዘብ ይቻላል። በአለም አቀፍ መስፈርትም ሆነ፤ በአለም አቀፍ ሕግጋት፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈላጊ የሚሆንበት ወቅት አለ። በተለይም፤ የሃገር ፀጥታና ሰላም አደጋ ላይ የመውደቅ አዝማምያ ሲታይ፤ በሃገር ውስጥ ወይም ከውጭ ሃይሎች፤ የሚነሳ ጦርነት ወይም ግጭት ሲኖር፤ የሕዝብ ዓመጽ፤ ወይም ማህበረሰቡን ወደ ቀውስ የሚያመራ ነገር እና ሃገሪቱን የማያረጋጋ ነገር ሲከሰት፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ ተገቢ ይሆናል።
ምንም እንኳን ከሚያዚያ 2010 ጀምሮ፤ በዶ/ር አብይ አሕመድ የሚመራው መንግሥት፤ በፍቅር እና በመቻቻል፤ ሁሉም የሚያምንበትን የፖለቲካ መስመር በሰላማዊ መንገድ እንዲያራምድ መድረኩ ቢፈጠርም እና፤ የጋዜጠኞች እና የሕዝብ መገናኛ ዘዴዎች መብት እንዲከበር ቢደረግም፤ የተለያየ የፖለቲካ ፍላጎት እና ምኞት ያላቸው ኃይሎች፤ እድሉን በበጎ መልኩ ከመጠቀም ይልቅ፤ ከሃገር ጥቅም ይልቅ የራሳቸውን ጠባብ አላማ እና ፍላጎት ከግብ ለማድረስ በተጉ ሰዎች እና፤ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ፤ የእነዚህን እኩይ ኃይሎች ዓላማ ለማስፈፀም መሳርያ የሆኑ ወጣቶች፤ በሃገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች፤ እራሳቸውን ከሕግ በላይ በማድረግ፤ የተለያዩ ወንጀሎች በመፈፀም ላይ ይገኛሉ። የተጀመረውን ለውጥም ለመቀልበስ ከፍተኛ ሴራ እየተሴረ ለመሆኑም፤ በቅርቡ የታጠቁ ወታደሮች፤ ከሕግ ውጭ፤ ያለምንም ከልካይ፤ ወደ ቤተ መንግስት ያደረጉት ጉዞ አመላካች ነው። በብዙ ዜጎች ተስፋ ተሰንቆለት የነበረው ይህ ለውጥ፤ አሁን፤ ዜጎችን ተስፋ እያስቆረጠ ለመሆኑ ነጋሪ የሚያሻው አይደለም። ዛሬ በሐረር፤ በወለጋ፤ በአርባ ምንጭ፤ በትግራይ ክልል፤ በአማራ ክልል፤ እንዲሁም በአዲስ አበባ የምናያቸው ሕገ ወጥ ተግባሮች፤ ዜጎች፤ እዚህ አገር መንግሥት አለ ወይ? ወይም እዚህ አገር ስንት መንግሥት ነው ያለው? ብለው እንዲጠይቁ አስገድዷል። ሌላው ቀርቶ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ባለፈው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር፤ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት አንፀባርቀዋል። ብዙዎቻችን፤ ወደ ለውጥ ለመሄድ ሽግግር ላይ እንዳለን ብናምንም፤ ወደ ምን ዓይነት ለውጥ እየሄድን እንደሆነ ግን ግልጽ አይደለም። በዚህ ፀሃፍ እምነት፤ “መርከቧ፤ በሚናወጠው ማእበል ካፒቴኗን ልታጣ ትችላለች” ብሎ ይሰጋል። ምንም እንኳን ዶ/ር አብይ፤ በበጎ እይታ ሁሉንም “በፍቅር ዓይን ለማየት ቢሞክሩም” ሁሉም ሰው ግን ፍቅር ተቀባይ አለመሆኑን እያየን ነው። “ፍቅር ያልገዛውን ኃይል ይገዛዋል እንዲሉ” የዜጎችን ኑሮ ለማረጋጋት፤ እየጠፋ ያለውን ሕይወት እና ንብረት ለመታደግ፤ እንዲሁም የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ከግብ ለማድረስ፤ ግልጽ እና የአጭር ጊዜ ግብ ያለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ አስፈላጊ ነው። ይህ የሽግግር ጊዜ አስተዳደር፤ በየአካባቢው የሚነሳውን “እሳት” ለማጥፋት፤ እንደ እሳት አደጋ እዚህም እዛም በመሮጥ ጊዜውን እና አቅሙን ማባከን አይገባውም። በተረጋጋ ሁኔታ የለውጡን ሂደት ከግብ ለማድረስ፤ መጀመርያ ሃገሪቱን እና ሕዝቡን ማረጋጋት ያስፈልጋል። በየአካባቢው ወስላታ ጡንቸኞች እየተነሱ፤ አካባቢውን እየተቆጣጠሩ ሕዝብ የሚያሸብሩ ከሆነ፤ ስርዓተ አልበኝነት መጠናከሩ እና፤ ሃገሪቱ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት እንደምትሄድ ለማወቅ ጠንቋይ መሆን አያስፈልግም። የሶማልያ መበታተንም ሆነ፤ የሩዋንዳ ግጭት በአንድ ሌሊት አልተፈጠሩም። ዛሬ አንዳንድ የኢትዮጵያ አካባቢዎች፤ ሶማልያን እየመሰሉ መምጣታቸው፤ ነጋሪ አያሻውም። ፍቅር ባልገዛቸው፤ የራሳቸውን እኩይ ዓላማ በሕዝብ ላይ ለመጫን በሚፈልጉ ሃይሎች፤ ሃገሪቱ ቀውስ ውስጥ እየገባች በመሆኑ እና፤ ለዶ/ር አብይ አስተዳደር ንቀት እያሳዩ በመሆናቸው፤ ካሮቱ እንዳልጣማቸው በመጥፎ ተግባራቸው ለሚያሳዩን ዜጎች፤ በትሩን ከማሳየት ውጭ አማራጭ የሚኖር አይመስለኝም።
ለዚህም ነው፤ ከመዘግየታችን በፊት፤ መንግስት በአስቸኳይ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያውጅ የምለው። ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ ግልጽ የሆነ መመርያ ያለው፤ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት የሚያከብር፤ ሆኖም በተወሰነ ደረጃ የሚገድብ መሆን አለበት። ከሚገደበው መብት አንዱ የሕዝብ መገናኛ ዘዴዎች ስራ መሆን አለበት። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፤ ማንም የሕዝብ ግንኙነት ተቋም፤ የብሔርም ሆነ የሃይማኖት ግጭቶችን የሚሰብክ፤ ጥላቻን የሚሰብክ እንዳይሆን መደንገግ አለበት። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ሕግ የሚጥሱ ዜጎችም ሆኑ ተቋማት እንዴት እና በምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚቀጡ በግልጽ በአዋጁ ሊቀመጥ ይገባዋል። ወታደሩ፤ የፊደራል ፖሊስ፤ የክልል ፖሊስ፤ ፍርድ ቤቶች እና ሌሎች የመንግስት ተቋማት፤ በዜህ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ የሚኖራቸው ሚና፤ ሃላፊነት እና ግዴታ በግልጽ መቀመጥም ይኖርበታል። ሥልጣናቸውን በመጠቀም፤ ዜጎችን ያለአግባብ የሚያንግላቱ የመንግስት አካላት ተጠያቂ ሊሆኑ የሚችሉበትንም መዋቅር እና አሰራር በግልጽ መቀመጥ አለበት።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፤ የሚገድበው የዜጎች መብት ምን እንደሆነ በግልጽ ለሕዝብ መነገር ይኖርበታል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፤ የዓለም አቀፍ ሕግጋትን በማይጥስ መልኩ መዋቀር እና ስራውንም መስራት አለበት። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፤ የሚወሰዱ ማንኛቸውም እርምጃዎች፤ ለሕዝብ ግልጽ መደረገ አለበት። በክልል እና በፌደራል መንግስታት መካከል ስራዎችን የሚያዋቅር፤ ከሁሉም አካላት የተውጣጣ የጋራ ኮሚሽንም ያስፈልጋል። ሃገር ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ በአስቸኳይ ጊዘ አዋጁ ወቅት እንዴት መንቀሳቀስ እንዳለባቸው፤ ሕዝባዊ ስብሰባ ሲጠሩ በምን መልኩ ፈቃድ መጠየቅ እንዳለባቸው፤ መመርያም ይሰጥ። ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች፤ አባላቶቻቸው እና ደጋፊዎቻቸው፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ሕግ እንዲያከብሩ መመሪያ በመስጠት እና በማስተማር እንዲተባበሩም ሊነገራቸው ይገባል። የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ የሕዝብ ግንኙነት ተቋማት፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ከጣሱ የሚወሰድባቸው እርምጃ ምን እንደሆነ በማያሻማ ሁኔታ መቀመጥ አለበት። በዜጎችም ሆነ በማናቸውም ተቋማት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ለጥፋቱ ተመጣጣኝ ሊሆን ይገባዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመጠቀም፤ ሕግ አስከባሪው አካል፤ ተገቢ ባልሆነ ሁኔታና ከሕግ ውጪ የዜጎችን ሕይወት እንዳያጠፋ እና፤ የአካል ጉዳት እንዳያደርስ ጥብቅ መመርያ ሊሰጥ ይገባል፤ ሕግ የሚጥሱ ሕግ አስከባሪ ኃይሎች ላይም እርምጃ እንደሚወሰድ መገለጽ አለበት። ሕግ በመጣስ ተጠርጥረው የሚታሰሩ ሁሉ፤ ሕገ መንግስቱ ላይ የተቀመጠው መብታቸው ሙሉ በሙሉ መከበር አለበት።
እንደ እኔ እምነት፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፤ አሁን ያለውን እና እያደገ የመጣውን ስርዓተ አልበኝነት ለመቆጣጠር ከማስቻሉ በተጨማሪም፤ የተጀመረው ለውጥ ሳይደናቀፍ፤ በተረጋጋ ሁኔታ ከተፈለገው ግብ የሚያደርስ አስፈላጊ የሆነ አገልጋይ መሳርያ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ቡድናቸው፤ እንደ እሳት አደጋ፤ ሁከት በተፈጠረ ቁጥር፤ ለሁከቱ ምላሽ ለመስጠት ከመሮጥ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፤ ሁከቱ ከመነሳቱ በፊት፤ ሁከት አጋጅ የሆነ፤ ሥራቸውን የሚያቀልላቸው አጋዥ ሃይል ይሆናቸዋል። አሁን ሃገሪቱ ባለችበት ሁኔታ ከቀጠልን እና፤ በየመንደሩ፤ “ትናንሽ ወስላታ ንጉሶች” እንዲፈረጥሙ እድል ከተሰጣቸው፤ የሃገራችን እጣ ፋንታ ከአንድ ቀውስ ወደ ሌላ ቀውስ መሸጋገር ይሆናል ብዬ እሰጋለሁ። ሃገር ውስጥ ያሉ ጽንፈኛና አደገኛ ሃይሎች ብቻ ሳይሆኑ፤ የኢትዮጵያን መዳከም የሚሹ የውጭ ሃይላትም ይህንን የሽግግር ወቅት የውዥንብር አጋጣሚ በመጠቀም፤ በሃገራችን ላይ አደጋ ለመፍጠር አሰፍስፈው እንደሚጠብቁ ከግምት መግባት አለበት። የአስኳይ ጊዜ አዋጁ፤ ጊዜ ሳይጠፋ፤ በአስቸኳይ እንዲታወጅ እና በስራ ላይ እንዲውል፤ ዜጎች የበኩላቸውን ጉትጎታ እንዲያደርጉ በትህትና እጠይቃለሁ። መንግሥት ተቀዳሚ ሃላፊነቱ የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ በመሆኑ፤ በተለያዩ አካባቢዎች ያለውን ሕገ ወጥነት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊቆጣጠረው ይገባል።
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም።
ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።