- Advertisement -

ቦርከና
ጥቅምት 20 ፤ 2011 ዓ.ም.
በደርግ መንግስት በትምህርት ሚኒስቴርነት እና በውጭ ጉዳዮ ሚኒስትርነት ያገለገሉት ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ ከሰላሳ ሁለት ዓመታት የስደት ቆይታ በኋላ ከትናንት በስቲያ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል፡፡
እ.ኤ.አ አቆጣጠር በ 1986 ዓ.ም. የስራ መልቀቂያቸውን ከኒውዮርክ ለኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም መንግስት ከላኩ ጊዜ ጀምሮ ኑሮአቸውን በአሜሪካን ሃገር አድርገው ቆይተዋል፡፡
አሁን የ76 ዓመት አዛውንት የሆኑት ኮሎኔል ጎሹ የደርግ መንግስት በወደቀ ማግስት ኢትዮጵያን ከህወሓት አገዛዝ ለመታደግ በተደረገው ጥረት የመድህን ፖርቲን በመምራት አስተዋጾ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡
ከዚያ በኋላ ለረዢም ጊዜ በፖለቲካ ጉዳይ በአደባባይ ድምጻቸውን ሳያሰሙ የቆዮት ጉምቱ ፖለቲከኛ በቅርቡ የአብይ አህመድ መንግስት የወሰዳቸውን የለውጥ ርምጃዎች በማድነቅ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲደግፈው የቪዲዮመልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል፡፡
የአሁኑ አመጣጣቸው ዘመድ ለመጠየቅ እና በኢትዮጵያ ውስጥ እየታዩ ያሉትን ለውጦች ለመደገፍ እንደሆነ የሚናገሩት ጎሹ ምንም አይነት የስልጣን ፍላጎት እንደሌላቸው ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡