spot_img
Wednesday, June 12, 2024
Homeነፃ አስተያየትየኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ ሕዝቦች አይደለንም። (ከጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ -አሜሪካ)

የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ ሕዝቦች አይደለንም። (ከጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ -አሜሪካ)

ከጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ (አሜሪካ)
ጥቅምት 23 ቀን 2011 (11/02/2018)

“ቃላቶች ነገሮች እንዲሆኑ የማድረግ ኃይል አላቸው” ይላል እውቁ አሜሪካው ፀሃፊ ፍሬድሪክ ብዩክነር። ቃላቶች፤ ሃሳባችንን የምንገልጽልበት ትልቁ ተሰጦዋችን በመሆናቸው፤ የምንጽፋችው ወይም የምንናገራቸው ነገሮች፤ ከፍተኛ ጉልበት አላቸው። የቃላቶቻችን አቅም ደግሞ’ በማህበረሰባችን ውስጥ ባለን ቦታ ከፍ እና ዝቅ ሊል ይችላል። ብዙውን ጊዜ እንደሚነገረው፤ በአመራር ላይ ያሉ ሰዎች የሚናገሯቸው ወይም የሚጽፏቸው፤ በህዝቡ ዘንድ፤ ከሌላው የማህበረሰብ አባል በተለየ ከበድ ያለ ተጽእኖ ይኖራቸዋል። የቃላቶችን ሃይል በመጠቀም፤ ያለፉት 27 ዓመታት፤ በህዝባችን መሃከል ክፍፍሎችን በመፍጠር ገዥው ፓርቲ፤ የጥቂት ሰዎችን እና ቡድኖችን ዓላማ ሲያራምድ ቆይቷል። ሕዝቡ፤ ከገዥው ፓርቲ የሚሰነዘሩ ቃላቶችን ጥቅም እና ጉዳት ባለመረዳት እና፤ ቃላቶቹ የሚፈጥሩትን ስሜት ካለመገንዘብ፤ ሳይጠይቅ እንደተነገረው እያስተጋባቸው ይገኛል። ኪራይ ሰብሳቢ፤ ሙስና፤ ብሔርተኛ፤ ጽንፈኛ፤ ወዘተ የሚሉት ቃላቶች፤ ዛሬ በየእለቱ የምንጠቀምባቸው ቃላቶች ናቸው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ “የቀን ጅቦች” ቄሮ፤ ፋኖ፤ ዘርማ እያልን፤ ቀን በቀን እንናገራለን እንጽፋለን። አንዳንዶቹ ቃላቶች፤ ምንም የአሥተሳሰብ ተጽእኖ ባያደርጉም፤ አንዳንዶቹን ለበጎ፤ አንዳንዶቹን ደግሞ ሌሎችን ለመጉዳት እንጠቀምባቸዋልን። ላለፉት 27 ዓመታት ገዥዎቻችን የኢትዮጵያዊነት ስሜትን ለመሸርሸር ብዙ ሰርተዋል። በመሃላችን ግጭት፤ ጥርጣሬ፤ እና አለመተማመን እንዲኖር የተጠቀሙባቸው ቃላት፤ ዛሬም፤ በመደበኛ የቀን ተቀን ኑሮአችን፤ እንዲሁም በሕዝብ ግንኙነት አካላት የምንጠቀምባቸው በመሆናቸው፤ በሕዝባችን ውስጥ ሥር ሰደዋል።

ገዥው ፓርቲ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ “አንድ” አይደለም የሚል ስሜት ለመፍጠር ከተጠቀመባቸው ቃላቶች አንዱ፤ ለዘመናት ስንጠቀምብት የነበረውን፤ “የኢትዮጵያ ሕዝብ” የሚሉትን፤ የሃገር መሪዎችን ሕዝብ ሲጠቀምባቸው የነበሩትን ቃላቶች “የኢትዮጵያ ሕዝቦች” ወደ ሚለው በመቀየር ነው። እነዚህ ቃላቶች፤ በኢትዮጵያ “ሕገ መንግስትም” የተካተቱት ያለምክንያት አይደለም፤ ሕዝብን ለመከፋፍለ ታስቦ እና ታቅዶ እንጂ። ዛሬም፤ ይህ የተለያዩ በሃገር አመራር ላይ ባሉ ባለስልጣናት እና የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎች እየተጠቀሙበት ይገኛል። ሕዝብ የሚለው ወደ ሕዝቦች የተቀየረበት ዋና ምክንያት፤ ብሔርተኝነትን ለማጎልበት እና ኢትዮጵያዊነትን ለማሳነስ ሆን ብሎ የታቀደበት ነው። በተወሰነ ደረጃም ይህ ዓላም ግቡን መቶ በተለያየ አቅጣጫ እየተተራመስን እንገኛለን። የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሚለውን የሚያቀነቅኑ ሃይሎች፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ስብስብ መሆኑን ለማሳየት ነው መንግስት ይህንን የሚጠቀመው የሚል፤ አስቂኝ ግን አደገኛ የሆነ አመለካከት ያንፀባርቃሉ። ይህን አመለካከታቸውን እንደ እውነት ከተቀበልነው፤ የትግራይ ሕዝብ ወደ ሕዝቦች፤ የኦሮሞ ሕዝብም ወደ ሕዝቦች፤ የአማራም ሕዝብ ወደ ሕዝቦች መቀየር ይኖርበታል። እኔ በበኩሌ፤ እስካሁን ድረስ፤ የኦሮሞ፤ የትግራይ፤ የአማራ፤ የአፋር ወዘተ ሕዝቦች ሲባል ሰምቼ አላውቅም። ከሌላው ሁሉ በተለየ መልኩ፤ የደቡብ ሕዝብ ነው፤ “የደቡብ ሕዝቦች” የሚለው ታርጋ የተለጠፈበት። የዚህም ምክንያት፤ የደቡብ ክልል አስተዳደር የተፈጠረው ከተለያዩ ብሔር/ብሄረሰቦች መሆኑን ለመጠቆም እና አንድ ተዋጽኦ ያለው “ክልል” አለመሆኑን ለማሳየት ነው። ሁለት ወዶ አይሆንም እና፤ ያለው አማራጭ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማለት፤ ወይም ደግሞ ሌሎቹን ሕዝቦች ማለት ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ፤ በተለያዩ ብሔር/ብሄረሰቦች የተገነባች ሃገር ስትሆን፤ የተለያዩ ብሔር/ብሄረሰቦች ደግሞ የተገነቡት ከተለያየ ጎሳ/ነገድ/ብሄረሰብ ነው። እንዳብራር ይፈቀድልኝ።

መባል ያለበት፤ የኢትዮጵያ ሕዝቦች እንጂ፤ ሕዝብ አይደለም ከተባለ፤ በተመሳሳይ መልኩ ደግሞ የትግራይ ሕዝቦች እንጂ ሕዝብ መባል የለበትም። ትግራይን፤ ትግራይ ያደረጋት አንድ ወጥ ሕዝብ አይደለም፤ ትግራይ፤ የአድዋ፤ የአጋመ፤ የውቅሮ፤ የኢሮብ፤ የአዲግራት፤ ወዘተ ሕዝቦች ክልል ናት፤ ኦሮሞም እንዲሁ፤ የወለጋ፤ የጂማ፤ የአርሲ፤ የቦረና፤ የየጁ፤ የአምቦ፤ ወዘተ ሕዝቦች ክልል ነው። የአማራን፤ የአፋርን፤ የሶማሌን፤ እና ሌሎች አካባቢዎችን ካየን፤ አንድ ወጥ የሆነ ማንም የለም፤ የአጋመ እና የአድዋ፤ ባህል፤ የአነጋገር ዘይቤም ሆነ ሌላ እሴቱ አንዱ ከሌላው በመጠኑም ቢሆን ይለያያል። በተመሳስይ መልኩ፤ የአርሲው፤ ኦሮምኛ ከወለጋው ኦሮምኛ የሚለይባቸው፤ እንዲሁም አንዳቸው ከአንዳቸው ለየት የሚሉበት ባህላዊ እና ማህበራዊ አኑኗር እሴቶችም አሏቸው። ስለዚህ፤ እነዚህ ብሔር/ብሔረሰቦች ካላቸው ልዩነቶች አንፃር፤ ልዩነታቸውን ለማጉላት ከተፈለገ፤ ሕዝብ ስይሆን ሕዝቦች ሊባሉ ይገባል። ሆኖም፤ የ1980ዎቹ የሃገራችን የፖለቲካ ገዥዎች እና ልሂቃን፤ በየብሔረሰቡ ያለውን ልዩነት በማጥበብ፤ በአንድ ብሔር/ብሔረሰብ ውስጥ ጠንካራ ስሜት እንዲፈጠር፤ የኢትዮጵያውያኖችን ልዩነት በማጉላት ደግሞ፤ ኢትዮጵያዊነትን ለማመንመን የተጠቀሙበት ስልት ነው።

ዛሬ፤ ኢትዮጵያዊ ስሜትን ለመግደል ሲያሴሩ ከነበሩ ገዥዎቻችን ተላቀን፤ ኢትዮጵያዊነትን ወደሚያቀነቅኑ የሃገር መሪዎች የተሽጋገርን በመሆኑ፤ በተለይም በመንግሥት ደረጃ የሚነገሩ፤ ኢትዮጵያዊነትን አደብዣዥ ቃላቶችም ሊለወጡ እና፤ ሊስተካከሉ ይገባቸዋል። ኢትዮጵያ፤ በአለማችን እንዳሉ በርካታ ሀገራት፤ በተለያዩ ብሔር/ብሔረሰቦች የተገነባች ነች። የዛሬይቱን አሜሪካንን የገነቡት፤ ከሌሎች በተጨመአሪ፤ ከአየርላንድ፤ ከጣልያን፤ ከእንግሊዝ፤ ከስፔን፤ ከጀርመን፤ ከኢስያ፤ ከመካክለኛው ምስራቅ፤ ከሩስያ እና ከአፍሪካ የመጡ ሕዝቦች ናቸው፤ የእነዚህን ሕዝቦች ልዩነት የታወቀ በመሆኑ ማብራርቱ አስፈላጊ አይደለም። ሆኖም፤ “የአሜሪካ ሕዝቦች” የሚሉ መሪዎች፤ አሜሪካ አልነበሯትም። አሜሪካን እንደ ሃገር ስትገነባ፤ 13 የተለያዩ ግዛቶች ናቸው “የተባበሩ የአሜሪካን መንግስታትን” የአሜሪካን ፊደራላዊ መንግስት ያቋቋሙት። ሕገ መንግስታቸውም ሲጀምር፤ “እኛ የተባበሩት የአሜሪካን መንግስታት ሕዝብ” እንጂ ሕዝቦች አይልም። ይህ የሆነብትም ምክንያት፤ እያንዳንዱ ግዛት (State) የራሱ የሆነ አስተዳደራዊ መንግስት ቢኖረውም፤ እንደ ሃገር ግን አንድ ሕዝብ መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ ለማስቀመጥ ነው። እነዚህ፤ የ18ኛው ክፍለ ዘመን “አሜሪካዊ ፖለቲከኞች”፤ ከእኛዎቹ 21ኛ ክፍለ ዘመን ፖለቲከኞች መጥቀው የሄዱ እና የሃገር አንድነት ጥቅሙ የገባቸው መሆኑ ሊያስደምመን ይገባል። የእኛዎቹ ሳይገባቸው ቀርቶ ሳይሆን፤ በተንኮል የታመሙ ጽንፈኞች በመሆናቸውም ሊሆን ይችላል፤ ከአንድነታችን ይልቅ፤ ልዩነታችንን በማጉላት እና ጥላቻን በመስበክ፤ ብሔርተኝነትን የፖለቲካ ምሶሷቸው ያደረጉት።

በተደጋጋሚ፤ በሃገራችን ከተከሰቱት ሁነቶች የምረዳው፤ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ባሉት እና ለዘመናት በተሳሰረበት የተለያዩ እሴቶቹ በመድመቅ እንደ አንድ ሕዝብ፤ ተፋቅሮ እና ተባብሮ መኖር የሚፈልግ ሕዝብ ነው። ዶ/ር አብይ አሕመድ፤ የሰፊውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፍ እና ፍቅር ያገኙት፤ ከምንም በላይ፤ ኢትዮጵያዊነትን በማስቀደማቸው እና፤ ኢትዮጵያዊነትን ልንኮራባት የሚገባ ታላቅ ሃገር፤ የትልቅ ሕዝብ ሃገር መሆንዋንም በመመስከራቸው ነው ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም። የአሁኖቹ መሪዎች፤ ይህ ላለፉት 27 ዓመታት “ኢትዮጵያን እንመራለን” እያሉ፤ ኢትዮጵያ የሚለውን ሥም እንኳን ለመጥራት ከሚሰቀጥጣቸው እና ኢትዮጵያዊነት ላይ ከዘመቱ ገዥዎቻችንም ፍፁም የተለዩ በመሆናቸው ነው፤ ሕዝቡ አክብሮቱን እና ፍቅሩን የቸራቸው። የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በተለያዩ ብሔር/ብሔረሰቦች ያሸበረቀ፤ በታሪኩ፤ በብዙ ኢትዮጵያዊነት እሴት፤ እና በደም የተሳሰረ አንድ ሕዝብ ነው፤ ስለዚህም “የኢትዮጵያ ሕዝብ” እንጂ ሕዝቦች ሊባል አይገባውም። ቃላት ብዙ ስሜቶችን የመፍጠር አቅም ብቻ ሳይሆን፤ ስነ ልቦናችንንም የመማረክ ከፍተኛ አቅም አላቸው። ኢትዮጵያዊ ስነልቦና ለማዳበር እና የደበዘዘውንም ለማድመቅ፤ ቃላቶችን መርጠን መጠቀም አለብን። ስለዚህ የቀደምቱ የ27 ዓመታት ገዥዎቻችን፤ ኢትዮጵያዊነትን ለማደብዘዝ እና፤ ልዩነታችንን ለማጉላት፤ ወይም አንድ ሕዝብ አለምሆናችንን ሊነግሩን የተጠቀሙበት የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሚሉት ቃላቶች፤ “የኢትዮጵያ ሕዝብ” በሚሉት ተገቢ ቃላቶች ይተካ። እኛ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ፤ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አይደለንም።
__
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም።
ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here