spot_img
Wednesday, March 22, 2023
Homeነፃ አስተያየትአንድ አገር ታሪክ የሚሰራበት መድረክ እንጂ የጦርነት መድረክ አይደለም !! ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

አንድ አገር ታሪክ የሚሰራበት መድረክ እንጂ የጦርነት መድረክ አይደለም !! ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

- Advertisement -

ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)
ህዳር 4 ፣ 2018

መግቢያ

ያለፉትን አርባ ዓመታት በአገራችን ምድር በፖለቲካ ስም የተፈጸመውን ግፍና አገርን የማፈራረስ ድርጊት ስንመለከት በአብዛኛው የፖለቲካ ተዋናይ ነኝ ባይ መንፈስ ውስጥ የተቀረጸው አርቆ-አስተዋይነት ሳይሆን ስሜታዊ አስተሳሰብ እንደሆነ መገንዘቡ ከባድ አይሆንም። በተለይም የግዴታ ስልጣን ላይ መውጣት አለብን ብለው በደመ-ፍላት ይታገሉ የነበሩና አሁንም የሚታገሉ ኃይሎች የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል፣ በተለይም ወጣቱን በመፈክር ጋጋታና በጥላቻ መንፈስ በመመረዝ በቀላሉ ሊፋቅ የማይችል መፈራራትና ጥርጣሬ እንዲስፋፋ አድርገዋል። በተጨማሪም ለብዙ መቶ ሺህ ወጣቶች መሞት፣ መገረፍ፣ እስር ቤት መጣልና ወደ ውጭ አገር መሰደድ ምክንያት ሊሆኑ በቅተዋል። በአገራችን ምድር በህቡም ሆነ በይፋ፣ መንግስትንም ጨምሮ የፖለቲካ መድረኩን የያዙት ኃይሎች በሙሉ ፖለቲካ የሚባለውን ጽንሰ-ሃሳብ የተገነዘቡት ታሪክን መስሪያ ሳይሆን፣ መሸወጃና ማስፈራሪያ፣ እንዲሁም ተንኮልን በመሸረብ ስልጣን ላይ መወጣጫ እንደሆነ ነው። አብዛኛው ታጋይ ነኝ የሚል ኃይል ግልጽ በሆነ ፍልስፍናና የህብረተሰብ ርዕይ የሚመራ ሳይሆን የራሱን የተደበቀ ዓላማ ብቻ ተግባራዊ ለማድረግ የሚሯሯጥ ነው የሚመስለው። በመሆኑም ሁሉም በየፊናው ድርጅት ፈጠርኩ እያለ ህብረተሰብአችንን የሚያተራምስ እንጂ ኃይሉን በመሰብሰብ ለመሰረታዊና ዘላቂነት ለሚኖረው ለውጥ የጋራ ግምባር በመፍጠር የተከበረችና የምትፈራ አገር ለመገንባት አይደለም። ይህ ዐይነቱ በቡድን በቡድን እየተሰባሰቡ ወደህና ወዲያ ማለት እንዳየነውና የአገራችንም ሁኔታ እንደሚያረጋግጠው ሰብአዊነትን ለተላበሰ ነፃነትና ለዲሞክራሲ የሚደረገውን ትግል በማደናቀፍ ላይ ይገኛል። የህዝባችንን ስቃይ እያራዘመውና ህልሙን እያጨለመው እንደሆነ ነባራዊው ሁኔታ ያረጋግጣል።

በአገራችን ምድር የተፈጠረውን መወዛገብና የአገርን ህልውና መዳከም በምንመለከትበት ጊዜ መብታችንና የማንነታችን ጥያቄ ይክበር ብለው የብሄረሰብን አርማ ይዘው በተነሱ ኃይሎች ላይ ብቻ የሚሳበብ አይደለም። በአርባ ዓመት የውድቀትና የአገር መፈረካከስ ትግል ውስጥ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ በተለይም ከአማራ፣ ከትግሬ፣ ከኤርትራና ከኦሮሞ ብሄረሰብ የተውጣጡ ስልጣን ለእኛ ይገባናል ባይ ኤሊቶችና „የማርክሲዝምን ሌኒንዝምን“ አርማ አንግበው የሚታገሉ ሁሉ ዛሬ አገራችን ለደረሰችበት አደገኛ ሁኔታ በአብዛኛው መልኩ ወይም መቶ በመቶ ተጠያቂዎች ናቸው ብል የምሳሳት አይመስለኝም። እዚህ ላይ ግን መያዝ ያለበት ጉዳይ፣ ችግሩ የመነጨውና የሚመነጨው 95% ከሚሆነው የአማራ ፣ የትግሬ፣ የኤርትራና የኦሮሞ ህዝብ ሳይሆን፣ ተምሬአለሁ፣ ተገልጾልኛል፣ ስለዚህም የብሄረሰቤን መብትና የማንነት ጉዳይ ማስጠበቅ አለበኝ ከሚለው በፐርሰንት ሲለካ 5% በታች ከሚሆነው „ኤሊት“ ነው። ይህ ችግር በአገራችን ብቻ ያለ ጉዳይ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ በተለይም በላቲን፣ በማዕከለኛው አሜሪካና በአፍሪካ አገሮች ጎልቶ የሚታይ ጉዳይ ነው። ይህም ማለት በአገራችንና በሌሎች በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ውስጥ የሚታየው የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ቀውስ፣ እንዲሁም የባህልና የአካባቢ ውድመት ዋናው ምክንያት ኤሊቱ ነው ማለት ይቻላል። ወደ አገራችን ስንመጣ ከፖለቲካ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች የተነሱትና የጎሳ ጉዳይ ቀሰ በቀስ ስር እየሰደደ የመጣው በጊዜው መወሰድ ያለባቸው በሳይንስ ላይ የተመሰረቱ ፖለቲካዊ መፍትሄዎች ባለመታወቃቸውና፣ የፖለቲካና ከጎሳ ጋር የተያያዙ የመብት ጥያቄዎች ሊያስከትሉ የሚችሉትን አደጋ ግንዛቤ ውስጥ ባለማስገባት ነው። በሌላ ወገን ደግሞ የመብት ጥያቄዎችን ያነሳው ከዚህም ሆነ ከዚያኛውም ብሄረሰብ የተውጣጣው ኤሊት በፍልስፍና ሳይንስ መነጽር ሲመረመር ችግሩን ለመፍታት የሄደበት መንገድ እጀግ አደገኛና፣ እንደምናየው ችግሩን የበለጠ ውስብስብ ያደረገና በቀላሉም መፍትሄ እንዳይገኝለት በሩን የዘጋ አካሄድ ነው ማለት ይቻላል።፡

የአገራችንን ሁኔታ ጠጋ ብለን ስንመለከት እስከዛሬ ድረስ የተለያዩ መፈክሮችን ይዘው የታገሉና የሚታገሉ ጨቋኝ ከሚባለውም ሆነ ተጨቁኜአለሁ ከሚለው የህብረተሰብ ክፍልና ብሄረሰብ የተውጣጡትን ሁኔታ ስንመለከት ሁሉም የመማር ዕድል ያገኙና ዩኒቨርሲቲ መግባት የቻሉ ናቸው። ከዚያም አልፈው ስኮላርሺፕ ተፈልጎላቸው በመንግስት ወደ ውጭ አገር የተላኩ ናቸው። አብዛኛዎቹ ደግሞ በኢኮኖሚም ሆነ በማህበራዊ ስታተሱ ሻል ብሎ ከሚገኝ የህብረተሰብ ክፍል የተወለዱ ናቸው። በመሰረቱ አንድ ልጅ በኢኮኖሚያዊና በማህበራዊ ስታተሱ ሻል ካለ የህብረተሰብ ክፍል ከተወለደ አርቆ የማሰብና የማመዛዘን ኃይሉም ከፍ ያለ ነው ብለን እንገምታል። ስለሆነም ባገኘው ዕውቀትና እንክብካቤ ታሪኩንና የህብረተሰቡን ዕድገት የመረዳት ኃይሉ ከፍተኛ ይሆናል ብለን እናስባለን። ይሁንና ግንያለፉትን ሃምሳ ዓመታት የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ስንመመረምር መማርና ከተሻለ የህብረተሰብ ክፍል መውጣት የግዴታ አርቆ አስተዋይነትን ከጭንቅላት ጋር ያዋሀደ አይደለም። ይህ ማለት ግን ከላይኛው ወይም ከተሻለ የህብረተሰብ ክፍል የተውጣጣ ኤሊት በሙሉ እርኩስ ዓላማ አለው ማለት አይደለም። ጥቂቶች በአርቆ-አስተዋይነትና በአገር ወዳድነት ስሜት ለህዝባቸውና ለአገራቸው እንደታገሉና እንደተሰውም የሚታወቅ ጉዳይ ነው። የአውሮፓውን የህብረተሰብን ታሪክና የሳይንስን ዕድገት ስንመለከት ለሰው ልጅ መሻሻል ከፍተኛውን አስተዋጽዖ ያበረከቱት ከላይኛው የህብረተሰብ ከፍል የመጡና የተማሩ ሊቃውንት እንደነበሩ ማረጋገጥ ይቻላል። ሳይንሳዊ ግኝቶችና ፍልስፍናዎች በሙሉ የተፈጠሩት ከአሪስቶክራሲው የህብረተሰብ ክፍል ከመጡ ምሁራን ነው። እንደነዚህ ዐይነት ሊቃውንቶች ባይፈጠሩና ለዕውቀትም ከፍተኛውን ቦታ ባይሰጡ ኑሮ የሁላችንም እጣ እንደእንስሳ መኖር ይሆን ነበር። ወደ አገራችን ስንመጣ ግን ጉዳዩ ለየት ይላል። በፖለቲካ መድረክ ውስጥ ገብቶ ተዋናይ የሆነው ወይም ያዙኝ ልቀቁኝ የሚለው ውዝግብ ከመፍጠር ይልቅ ፈጣሪና፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዕድገትን አራማጅ መሆን በፍጹም አልቻለም። የአገራችንንም ችግር በህብረተሰብ የሳይንስ መነፅር በመመርመርና ውጣ ውረድነቱን በመገንዘብ ሳይንሳዊ መፍትሄ ሊሰጥ አልቻለም። በየጊዜው የሚያነሳቸው ጥያቄዎችና የሚያስተጋባቸው መፈክሮች ህብረተሰብአዊ ቅራኔዎችን የሚያሰፉ እንጂ በማጥበብ ህዝባችን ለአንድ ዓላማ እንዲነሳ የሚጋብዙ አይደለም። ከዚህ ስንነሳ አባዛኛውን ጊዜ ህዝባችን የሚጠይቀውና ግራ
የሚጋባው የመማር ጥቅሙ ምኑ ላይ ነው ? እያለ ነው። መማር ማለት አገርን ማፈራረስ ከሆነ ይህ ዐይነቱ ትምህርት ቢቀር ይሻላል እያለ ብሶቱን ይገልጻል። መማር ማለት ግልጽነትን መቀዳጀትና ለአንድ ችግር መፍትሄ ለማግኘት የሚረዳ ወይስ በአለው ችግር ላይ ሌላ ችግር በመፍጠር አንድን ህብረተሰብ የሚያዘበራርቅ ነው ? እያለ ጥያቄዎችን ያነሳል።

ከተማረ ሰው ወይም ምሁር ነኝ ከሚል የሚጠበቅ መሰረታዊ ነገር !

በመሰረቱ አንድ ሰው ትምህርት ቤት የሚሄደው ዕውቀትን ለመገብየት ነው። አንድ ሰው ትምህርት ከመቅሰሙ በፊት በቀላሉ ሊገባውና ሊረዳው የማይችላቸውን ነገሮች ሲማር ራሱንና ማንነቱን የበለጠ ማወቁ ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮንና የህብረተሰብንም ህግ ሊረዳ ይችላል የሚል ግንዛቤ አለ። በዚህም መሰረት የኑሮን ትርጉምና የሰው ልጅስ ለምን በዚህች ዓለም ላይ ተፈጠረ፣ ሚናውስ ምንድነው ብሎ ማውጣትና ማውረድ ይችላል ተብሎ ይታመናል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ስነ-ምግባርንና ግብረገብነትን በመማርና ከመንፈሱ ጋር በማዋሃድ ላልተማረውና ለታዳጊው ትውልድ አርአያ በመሆን ህብረተሰቡ በአንድነት ተነስቶ ታሪክን እንዲሰራ ያደርገዋል። አለኝታው በመሆን ከእርስ በእርስ ሽኩቻና ከማያሰፈልጉ ግብግቦች በመቆጠብ ተግባሩን በሙሉ ወደ ስራና ወደ ጥበብ እንዲያዘነብል በማድረግ አገሩን በጸና መሰረት ላይ እንዲገነባ መንገዱን ያሳየዋል። ባጭሩ የተማረ ሰው ላልተማረው ብርሃን ነው። ከጨለማ የሚያወጣው፣ ከማያስፈልጉ ድርጊቶች እንዲቆጠብ የሚያደረገውና፣ ችግሮች ሲፈጠሩ በውይይት መፍታት እንደሚችል ትክክለኛውንመንገድ ያሳያል ተብሎ ይገመታል።

በመሆኑም የተማረ ሰው ይጠይቃል፣ ያወጣል፣ ያወርዳል፣ ወደ ውስጥ ጭንቅላቱን ያያል፤ ወደ ውጭ ደግሞ የነገሮችን መተሳሰርና መደጋገፍ ይመለከታል። አንዱ ካለሌላው መኖር እንደማይችል በመረዳትና፣ ይህም የተፈጥሮ ህግ መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ በማስቀመጥ ታሪክን በመስራት ለመጭው ትውልድ ያስተላልፋል። በሌላ ወገን ግን የአንድ ሰው አርቆ የማሰብና ያለማሰብ፣ ታሪክን የመስራትና ያለመስራት ጉዳይ በተለያዩ ነገሮች የሚወሰን ነው። በአንድ አገር ውስጥ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የተለመዱ አሰራሮች፣ አብዛኛውን ጊዜ እንደባህል የሚወሰዱ አነጋገሮችና አሰራሮች፣ እንዲሁም ህብረተሰብአዊ ግኑኝነቶችና በምድር ላይ የሚታዩ የተዘበራረቁ ነገሮች፣ የአንድን ሰው የማሰብና ያለማሰብ ኃይል ሊወስኑ ይችላሉ። ከዚህም ባሻገር አንድ ሰው ትምህርትቤት ውስጥ የሚቀስመው ትምህርት የጭንቅላቱን መዳበርና አለመዳበር ይወስናሉ። የአንድ ሰው ንቅታ-ህሊና የዕድገት ደረጃዎች ያሉት ሲሆን፣ የንቃተ ህሊናውም ማደግ በሚያደርገው ጥረት የሚወሰን ነው። ሰውነታችን ለመንቀሳቀስና ለመስራት፣ እንዲሁም ከባድ ነገሮችን ለማንሳት ልምምድ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ጭንቅላትም እንዲዚሁ ጂምናስቲክ ያስፈልገዋል። ለአዕምሮ መዳበር አስፈላጊው ነገር ከትክክለኛው ዕውቀት ጋር መተዋወቅ ሲሆን፣ በተጨማሪም የማያቋርጥ ጥያቄ መጠየቅና ጭንቅላትን ለጥሩ ነገር ማዘጋጀትና በየጊዜው የሳይንስ፣ የፍልስፍናና ልዩ ልዩ ስነ-ጽሁፎችን ማንበብ የማሰብ አድማስን ያሰፋል። ቡድናዊ ስሜትንና ወገናዊንትን ያስወግዳል። ማንኛው ሰው በአምላክ ምስል የተፈጠረ መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባል።

ከዚህ ስንነሳ አንዳንድ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች ታሪክንና የህብረተሰብን ዕድገት በደንብ ሳያገናዝቡ የሚያናፍሷቸው አሉባልታዎች ተፈጥሮአዊ ወይንም አንድ ሰው ሲወለድ ይዞት የሚመጣው አይደለም። የችግሮቹ ምንጭ ጭንቅላት በሚገባ ስላልዳበረና አንድን ነገር ከሁሉም አቅጣጫ የማየት ኃይሉ በጣም ደካማ ስለሆነ ብቻ ነው። በተጨማሪም የጥቂት ብሄረሰቦችና የአንዳንድ ግልሰቦችም ችግር አይደለም። ስለሆነም እንደነዚህ ዐይነት ሰዎችም ሆነ ቡድኖች በንቃተ-ህሊና ማነስ ተግባራዊ የሆኑ ፖሊሲዎችንና ፖለቲካዊ ውሳኔዎችን አንድን ብሄረሰብ ለመጉዳት
እንደተወሰደ እርምጃ በመቁጠር ተጨማሪ ህብረተሰብአዊ ቅራኔ እንዲፈጠር ያደርጋሉ። እንደነዚህ ዐይነት ግልሰቦችም ሆነ ቡድኖች ደግሞ በውጭ ኃይሎች በመደገፍ ቅራኔው እንዲባባስ ያደርጋሉ። የውጭ ኃይሎችም ዋና ዓላማ አንድ ህዝብ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት እንዳይሆንና የተረጋጋ ማህበረሰብ እንዳይገነባ ለማድረግ ስለሆነ እንደነዚህ ዐይነት ግለሰቦችን በጥቅም በመግዛት የርስ በርሱ ሽኩቻው እንዲጧጧፍ የማይፈነቅሉት ዲንጋይ የለም። በዚህ መልክ አርቀው ማሰብ የማይችሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ወጣቱንና ለውጥ መጣ ብሉ የሚደናበረውን ኃይል በመቀስቀስ አንድን አገር
የታሪክ መስሪያ መድረክ ከማድረግ ይልቅ ወደ ጦር አውድማነት ይለውጡታል።

ወደ አገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመጣ ትልቁ ችግራችን የህብረተሰብአችንን ታሪክና እንደ አወዛጋቢ የሚቀርቡትን፣ የሚሰነዘሩትን ጥያቄዎችና ሃሳቦች በሳይንስና በፍልስፍና መነጽር ለማየት ጥረት አለማድረጋችን ነው። በተለይም ባለፉት አርባ ዐመታት የህብረተሰብአችንን ዕድገትና በየጊዜው የሚከሰቱትን ፖለቲካዊ ችግሮች ለመቃኘት ከሚያስችሉን ሳይንሳዊ መሰረተ-ሃሳቦች ጋር ለመተዋወቅ ጥረት ባለማድረጋችን ታሪካችንን እንደፈለገን እንተረጉመዋለን። አብዛዎቻችን ፖለቲካ የሚባለውን መሰረተ-ሃሳብ ከሌሎች ለአገር ግንባታ ከሚያስፈልጉ ዕውቀቶች ነጥለን በማውጣት
አስተሳሰባችን በተወሰነ ክልል ብቻ እንዲሽከረከር ለማድረግ በቅተናል። ፖሊቲካ ህብረተሰብአዊ ፕሮጀክት የሚሰራበት መሳሪያ መሆኑን ካለመገንዘብ የተነሳ ኃይላችንን በማያስፈልጉ ነገሮች ላይ አባክነናል። ንቃተ-ህሊናችንን በማዳበር የህብረተሰብአችንን ችግሮች በሙሉ ከሁሉም አቅጣጫ በመመርመር በዚህ ዘዴና በልዩ ዐይነት ሳይንሳዊ መሳሪያ ልንፈታው እንችላለን የሚል ሃሳብ ለማቅረብ አልቻልንም። በተወሰኑ መፈክሮችና ከታሪክና ከህብረተሰብ ህግ ጋር ሊጣጣም የማይችል በወገናዊነት ላይ ያተኮረ ትግል የሚሉትን ፈሊጥ፣ ግን ደግሞ ርዕዩና ሳይንሳዊ መሰርቱ የማይታውቅ በማካሄድና ስልጣንን ለመያዝ በመቻኮል የተወሳሰበውን የህብረተሰብአችንን ችግር ልንፈታ የምንችል መስሎን ዓለምን
አዳርሰናል። የብዙ አገሮችን መዝጊያዎች በማንኳኳት ድረሱልን እያልን እርስ በእርስ ግብግብ ውስጥ ገብተናል። ስለሆነም ከአስመራ እስከካይሮ፣ ከካርቱም እስከ ሪያድና ከዚያም እስከዋሽንገተንና ለንደን ድረስ በማምራት ችግሩ ውስብስ እንዲሆን አድርገናል። የውጭ ኃይሎች ለነፃነታችን የቆሙ ስለመሰለን እንዲከፋፍሉንና በጥርጣሬ ዐይን እንድንተያይ መንገዱን አመቻችትን ሰጥተናችዋል። በዚህ ዐይነቱ ጠባብ አመለካከትና የህብረተሰብን ጥያቄዎች በሚመለከቱ መሰረታዊ ነገሮች ላይ ከመወያየት፣ ከመከራከርና አብሮ በማጥናትና አንድ የጋራ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ
መፈክሮችንና የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን በመሰንዘር በተለይም የተወሰነውን ወጣት ማሳሳታችን ብቻ ሳይሆን ጠቅላላው ህዝባችን ግራ እንዲጋባ ለማድረግ በቅተናል። እንደሰውና እንደማህበረሰብ ተስማምቶ እንዳይኖርና ታሪክን እንዳይሰራ ለማድረግ በቅተናል።

ቀደም ብሎም ሆነ ዛሬ በመሀከላችን ያለው ችግር አንድ ዐይነት አመለካከት ወይም ፍልስፍና ይዘን ለመታገል አለመቻላችን ነው። ከአርባ ዐመት በላይ የፈጀ መላቅጥ የሌለው ትግል በኋላ ዛሬም እንደትላንትናው ጭንቅላታችን ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች ለማየት አለመቻልና ሎጂካል በሆነ መንገድ የአገራችንን የተወሳሰቡ ችግሮች ወደ ውስጥ ገባ ብሎ ለማየት አለመቻል ነው። ለዚህ ሁሉ ችግር ደግሞ ትግል የሚባለውን ዘዴ የጠነሰሱት ሰዎች አሁንም በህይወት መኖራቸውና „የየድርጅቶቻቸው“ አመራር እንደ ግል ሀብታቸው መቆጣጠራቸው ነው። እንደሚታወቀው ባለፉት አርባ ዐመታት ብዙ አገሮች በሳይንስና በቴክኖሎጂ ቀድመው ሄደዋል። ለዚህ ዐይነቱ መሰረታዊ ለውጥ ደግሞ ዋናው መሰረቱ
የአመራር ለውጥ መካሄዱ ብቻ ሳይሆን፣ የአስተሳሰብና የአሰራር ለውጥም በመደረጉ ነው። በተጨማሪም የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ለመሆን የግዴታ በአዲስ ዕውቀትም በመመራት ነው። ወደ እኛ አገር ስንመጣ ግን ድርጅት አለን የሚሉ መሪዎች የአስተሳሰብ ለውጥ ማካሄድ አለማቻላቸው ብቻ ሳይሆን፣ ለምን ዐይነት ህብረተሰብም እንደሚታገሉም በግልጽ ቋንቋ ለማስቀመጥ አለማቻላቸውና አለማወቃቸው ነው። ግልጽነት እስከሌለ ድረስና ጠብመንጃን አስቀምጦ ወደ ውጭ በመውጣት ህብረተሰብአችንን በሚመለከቱ ነገሮች ላይ ክርክርና ጥናት ለማድረግ ዝግጁነት እስከሌለ ድረስ ያሉንን ችግሮች ከማባባስ በስተቀር የምናመጣው ፋይዳ የለም።

ችግርን ከመፍጠር ወደ መፍታት መሸጋገር !

ያለፉትን አርባ ዓመታት በፖለቲካ ዙሪያ የተደረገውን ትግል የሚባለውን ነገር በምንቃኝበት ጊዜ ታሪካችን የጦርነት ታሪክ ነው ማለት ይቻላል። የምናድረገው ትግል ለፖለቲካ ነፃነት ነው ቢባልም እንደዚህ ዐይነቱ በጦርነት ላይ ያመዘነና በማቸነፍና በመሸነፍ ላይ ያተኮረ ትግል ከፖለቲካ ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም። በታሪክ እንደተረጋገጠው በስልጣን ላይ ያለን አንድን ጨቋኝ አገዛዝ ለመጣል ተብሎ የሚደረግ የርስ በርስ ጦርነት በፍጹም ነፃነትን አያቀዳጅም። በጦርነት ትግል ላይ የሚሰማሩ ድርጅቶች ጭንቅላታቸው እንዳለ በጦርነት መንፈስ ስለሚሸፈን

ሳያውቁት በግድ አምባገነናዊ ባህርይን ይለምዳሉ። በድርጅታቸው ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ክርክሮች፣ ሂሲና ግለስሂስ፣ እንዲሁም ዕውቀትን ያዘሉና ለአንድ አገር ግንባታ እጅግ ጠቃሚ የሆኑ እንደፍልስፍና፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የመሳሰሉት ቦታ ስለማይሰጣቸው ድልን ከተቀዳጁ በኋላ የአንድን አገር የተወሳሰበ ችግር ለመፍታት አይችሉም። ስልጣን ላይ በሚወጡበት ጊዜ አገርን አፍራሽ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመከተልና ራሳቸውን በማበልጸግ ሰፊውን ህዝብ ደግሞ ወደ ድህነት ዓለም ውስጥ ገፍትረው በመጣል እንዲሰቃይ ያደርጉታል። ይህን ዐይነቱን ሁኔታ ከሞዛምቢክ እስከ ዝምባብዌ፣
ከአንጎላና እስከ ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም እስከ ኤርትራ ድረስ ያየነውና የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። በሌላ ወገን ግን ሞዛምቢክና ዝምባብዌ እንዲሁም አንጎላና ደቡብ አፍሪካ ከቅኝ አገዛዝ ለመላቀቅ የተደረጉት የጦርነት ትግሎች ትክክል ናቸው።

በመሆኑም የፖለቲካ ትግል በፍልስፍና፣ በሳይንስና በቲዎሪ እስካልተደገፈ ድረስና፣ በአንድ ድርጅት ውስጥም ሆነ በተለያዩ ድርጅቶች መሀከል ዲሞክራሲያዊ ውይይትና ክርክር እስካልተካሄደ ድረስ አንድ ህዝብም ሆነ አንድ ብሄረሰብ በምንም ዐይነት ዕውነተኛ ነፃነታቸውን ሊቀዳጁ በፍጹም አይችሉም። በፍልስፍና የተደገፈ ወይም ፍልስፍናን መሰረቱ ያደረገ የፖለቲካ ትግል የተወሰኑ ሰዎችን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን በአንድ አገር ውስጥ የሚኖርን ጠቅላላውን ህዝብ የሚመለከት ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን የመጨረሻ መጨረሻ ዕውነተኛ ነፃነትን የማቀዳጀት ኃይሉ ከፍ ያለ ነው። ይህም ማለት አንድ ህዝብ ከየት እንደመጣ፣ ለምን በዚህች ዓለም እንደሚኖርና ወዴትስ እንደሚያመራ እንዲገነዘብ ስለሚያደርገው አመለካከቱን በአንድ ክልል ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ሁሉንም እንደወንድሙና እንደእህቱ በመመልከት በአንድነት በመነሳሳት ታሪክን ለመስራት ያስችለዋል።

ከዚህ ስንነሳ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ እስከዛሬ ድረስ አገራችንና ህዝባችን ችግሮችን እንዲያስተናግዱ አድርገናል። ሀዝባችን አርባ ዐመት ያህል እፎይ ብሎ የኖረበት ጊዜ የለም። ሁሉም በየፊናው ታጋይ ነኝ በማለት ህዝባችንን ሲያዋክብና ግራ ሲያጋባ ነበር፤ ዛሬም ግራ እያጋባ ነው። አንዳንድ አገሮች በሰላሳና በአርባ ዐመታት ውስጥ የቴክኖሎጂ ባለቤት በመሆን ወደ ኃያል መንግስትነት ሲያመሩ፣ እኛ ግን አሁንም እንደትላንትናው መንፈሳችንን በማዋከብና ለጦርነት በመዘጋጀት ወደ መተላለቅና አገርን ወደ መበታተን እያመራን ነው። ስልጣን ላይ ለመውጣት
የሚደረገው ትግል ደግሞ ብሄራዊ ነፃነታችንን ከሚቀናቀኑና እንድንበታተን ከሚፈልጉ የውጭ ኃይሎች ጋር በመተባበርና ከእነሱ ድጋፍ በማግኘት ነው። ሳናውቀው የራሳችንን መቃብር እየቆፈርን ነው። ነፃ እናወጣዋለን የምንለውንም ህዝብ የመጨረሻ መጨረሻ ተበታትኖ እንዲቀር መንገዱን ሁሉ እያዘጋጀን ለመሆናችን በፍጹም የሚታየን አይመስልም።

ስለሆነም ከዚህ ዐይነቱ ራስንና አገርን፣ እንዲሁም ባህልንና ታሪክን ከሚያወድም አካሄድና የጦርነት ትግል ተቆጥበን ወደ ገንቢ አስተያየት መምጣቱ ታሪካዊ ግዴታ ነው። የምንፈልገውንም ነገር በግልጽ ማስቀመጡ መፍትሄ ለመፈለግ ያመቻል። በተጨማሪም ስልጣን ከተያዘስ በኋላ አፍጠው አግጠው የሚታዩትን ድህነትን፣ የንጹህ ውሃ ማግኘትን፣ የቤት ችግርን መቅረፍ፣ ህክምናን የማግኘት ጉዳይና፣ ሌሎች መሰረታዊ ነገሮችን በመፍታት እንዴት አድርገን በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረት ማህበረሰብ እንደምንገነባ ማሳየት መቻል አለብን። ይህንን ማድረግ ስንችል ብቻ ነው ለነፃነት የሚደረገው ትግል መልክ የሚይዘው። ሃሳባችንን ግልጽ ሳናደርግና ለመወያየት ዝግጁ ሳንሆን የምናደርገው መሯሯጥ ኃይልን ማባከኑ ብቻ ሳይሆን፣ አንድ ህዝብ ረጋ ብሎ እንዳይሰራ ያግዳል። እንደሚታወቀው አንድ ህዝብ በስራ አማካይነት ብቻ ነው ብሄራዊ ሀብት ሊፈጥርና ተደስቶ ለመኖር የሚችለው። አንድ ህዝብ ከፍርሃትና ከጦርነት መንፈስ መላቀቅ ሲችል ብቻ ነው ዕውነተኛ ነፃነትንና ሁለንታዊ ዕድገትን ሊቀዳጅ የሚችለው። ስለሆነም ተማርን የምንልና ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን የምናነሳና ማብራሪያም ለመስጠት የምንሞክር ሁሉ የአገራችንን የተወሳሰቡ ችግሮችና የተደቀነብንን አደገኛ ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ታሪካዊ ግዴታችን መወጣት አለብን። መልካም ግንዛቤ !

fekadubekele@gmx.de
___
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም።
ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
12,440FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here