ቦርከና
ጥቅምት 29 2011 ዓ ም
ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ ከሰባት ዓመታት የስደት ቆይታ በኋላ ከሰዓታት በፊት ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ እንደደረሰች የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዘገባ ያመለክታል።
በህግ ትምህርት ከአዲስ አባባ ዮኒቨርሲቲ ዲግሪዋን የወሰደችው ብርቱካን ሚዴቅሳ በፌደራል ፍርድ ቤት በዳኝነት ከማገልገሏም ባሻገር ፤ በኢትዮጵያ የተቃዋሚ ፖለቲካ በአመራር ደረጃ እንዳገለገለች ይታወቃል።
የምርጫ 97ትን ተከትሎ የቅንጂት ለአንድነት መሪዎች በታሰሩበት ሰዓት አብራ ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር ጊዜ በላይ ታስራ የተፈታች ሲሆን ፤ ኋላም ቅንጂት በመፍረሱ
ምክንያት ፍትህ ለአንድነት እና ለዲሞክራሲን ፓርቲና በማቋቋም ግንባር ቀደሚ ሚና ተጫውታለች።
ከዚሁ ፓርቲ ሃላፊነቷ ጋር በተያያዘ ለስራ ወደ አውሮፖ ተጉዛ በነበረበት ጊዜ ባደረገችው ንግግር ምክንያት በምህረት ከእስር የተፈታችበትን ሁኔታ ጥሳለች በሚል የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መንግስት እንደገና እንድትታሰር ተደርጋ ብዙ መከራ መቀበሏ ይታወሳል።በዓለም አቀፉ እና በኢትዮጵያውያን ግፊት ከእስር ከተፈታች በኋላ ወደ አሜሪካን ተሰዳ ለሰባት ዓመታት ያህል ቆይታለች።
በአሜሪካ በነበረችበት ጊዜ በሚባለው የዲሞክራሲ ተቋም ፊሎሽፕ በማግኘት ምርምር የሰራች ሲሆን በሃርቫርድ ዮኒቨርስቲም በመንግስት አስተዳደር የማስትሬት ዲግሪ አግኝታለች።
ወደ ሃገር ቤት የተመለሰችው በመንግስት ግብዣ እንደሆነ የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ትላንት ካቀረበው ዘገባ መረዳት ተችሏል ፤ እየተደረገ ባለው የለውጥ ሂደት ውስጥ በዲሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ላይ ለመሰራት ፍላጎት እንዳላትም ገልጻለች።
___
ወቅታዊ እና ሚዛናዊ መረጃን ለማግኘት ቦርከናን በፌስ ቡክ ላይክ ያድርጉ።