
ፎቶ : ኢብኮ
ቦርከና
ኅዳር 14 2011 ዓ.ም.
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትላንት ባካሄደው ስብሰባ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ እንዲሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእጩነት ያቀረቧቸውን ብርቱካን ሚዴቅሳን ሹመት አጽቋል።
ሹመቱ በአብላጫ ድምጽ በአራት ተቃውሞ እና በሶስት ድምጽ ተአቅቦ ነው የጸደቀው።
የአንድነት ለዲሞክራሲ እና ለፍትህ ተቃዋሚ ፓርቲ (በአሁኑ አጠራር ተፎካካሪ) መሪ የነበሩት ብርቱካን ሚዴቅሳ በፖለቲካ አመለካከታቸው ያለ አግባብ ታስረው ኢሰብዓዊ የሆነ ድርጊት እንደተፈጸመባቸው የሚታወስ ሲሆን ከተፈቱም በኋላ በስደት በአሜሪካን ሃገር ለሰባት ዓመታት ቆይተው በቅርቡ በመንግስት ግብዣ ወደ ሃገራቸው ተመልሰዋል።
አሜሪካን ሃገር በነበራቸው ቆይታ በሃርቫርድ ዮኒቨርሲቲ በፖሊሲ እና ህዝብ አስተዳደር ትምህርት የማስትሬት ዲግሪ ያገኙ ሲሆን ፤ “ናሺናል ኢንዶውመንት ፎር ዲሞክራሲ” በሚባለው የአሜሪካ ድርጂት በፊሎሺፕነት የተለያዮ ጥናቶችን እንዳካሄዱ የአሜሪካ ቆይታ ታሪካቸው ያስረዳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ብርቱካን ሚዴቅሳ ምርጫ ቦርድን ነጻ ፤ ተዓማኒ እና ገለልተኛ ተቋም በማድረግ በ አዲስ መልክ ለማዋቀር የታሰበውን ለውጥ ያሳካሉ ብለው ያምናሉ ፤ ብዙ ኢትዮጵያውያንም ተመሳሳይ እይታ አላቸው።
በሌላ በኩል እንደ ጃዋር ሞሃመድ ያሉ የአክራሪ ኦሮሞ ብሄርተኛ “አክቲቪስቶች” የብርቱካንን መመረጥ አግባብ አይደለም በሚል በማህበራዊ ድረ ገጽ የተቃውሞ ዘመቻ የሚመስል ነገር አስነስተዋል።