spot_img
Wednesday, June 12, 2024
Homeነፃ አስተያየትነገረ-ወልቃይት - ክፍል ፪ (በመስከረም አበራ)

ነገረ-ወልቃይት – ክፍል ፪ (በመስከረም አበራ)

(በመስከረም አበራ)
ኅዳር 21 ፤ 2018 ዓ.ም.

Meskerem Abera መስከረም አበራ
መስከረም አበራ
የሃገራችን የፖለቲካ ችግር መሰረቱ የብሄረሰቦች ጭቆና እንደሆነ የሚያምነው ኢህአዴግ ለዚህ መፍትሄ ብሎ ያቀረበው ሃገሪቱን በዘውግ ፌደራሊዝም ከፍሎ ማስተዳደርን ነው፡፡እስከ መገንጠል የደረሰ የብሄረሰቦች መብት የሰጠው ህገ-መንግስት የዘውግ ፌደራሊዝምን ምርጫው አድርጓል፡፡ይህ የሆነው የሃገሪቱን ብሄረሰቦች ተከባብረው እንዲኖሩ የሚያስችል ስለሆነ ለሃገሪቱ ህልውና ሁነኛ መፍትሄ ነው በሚል እሳቤ ነው፡፡ ሆኖም ውጤቱ እንደ ታሰበው ሃገር ያረጋጋ፣በዘውጎች መካከል የታሰበውን ያህል ሰላም ያመጣ አይደለም፡፡ምናልባትም ውጤቱ በተቃራኒው ሳይሆን አይቀርም፡፡በሃገራችን ጎሳን መሰረት ያደረገ ግጭት፣መፈናቀል፣ዘር ማጥፋት፣ደም መፋሰስን ያስከተለ የማንነት ጥያቄ የተከሰተው ይሄው ሃገር ያረጋጋል የተባለው የዘውግ ፌደራሊዝም በስራ ላይ ከዋለ በኋላ ነው፡፡

የዘውግ ፌደራሊዝሙን ተከትሎ ከሚነሱ ጥያቄዎች አንዱ የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ ነው፡፡የወልቃይት ጉዳይ ከማንነት ጥያቄ ባለፈ ከኢኮኖሚያዊ እስከ ስነ-ልቦናዊ ጉዳዮችን የያዘ ውስብስብ ጥያቄ ነው፡፡ስለዚህ ችግሩን ለመፍታት የሚደረገው እርምጃ ሁሉ የጉዳዩን ክብደት እና ውስብስቦሽ ከግምት ያስገባ መሆን አለበት፡፡ ህወሃት የወልቃይትን ችግር ሲቀምም መፍትሄ እንዳይኖረው አድርጎ ነው፡፡ስለዚህ የወልቃይትን ችግር ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ችግር ፈጣሪው ህወሃት ጉዳዩ እንዲሄድ በሚፈልግበት መንገድ ተኪዶ ሊሆን አይችልም፡፡የወልቃይትን ጉዳይ ለመፍታት ሃይል እና መጠፋፋት አማራጭ ሆነው መቅረብ የለባቸውም፡፡ እንዲህ ያለው አካሄድ የችግሩ እንጅ የመፍትሄው አካል አይሆንም፡፡

ሁነኛ መፍትሄ ለመፈለግ የወልቃይት ችግር መቼ?እንዴት?በማን? እና ለምን? ተፈጠረ የሚለውን ነገር በመፈተሽ መጀመር ያስፈልጋል፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች በመመርመር የሚነሳ ሁነኛ የመፍትሄ እርምጃ በቀጥታ የሚያመራው የወልቃይት ነገር ተወሳስቦ ወደታሰረበት ወደ ሽግግሩ ዘመን ወቅት ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ስለወልቃይር ችግር ጥብቀት ባነሳሁበት ፅሁፍ የሽግግር ዘመኑ እንዴት ለወልቃይት ችግር መነሻ እንደሆነ እና ይህ ችግር እንዴት ከህገ-መንግስቱ ጋር በጥብቅ እንደታሰረ ለማሳየት ሞክሬያለሁ፡፡ በሽግግሩ ወቅት ህወሃት በወልቃይት ላይ ጤናማ ያልሆነ የስነ-ህዝብ ለውጥ አድርጓል፡፡እጅግ የተጣደፈ እና ሰውሰራሽ የህዝብ ስብጥር ለውጡን ያደረገው የፈለገውን ሰው በቦታው በማስፈር ብቻ አልነበረም፡፡ ይልቅስ በአካባቢው ነባር ሰዎች ላይ ዘር እየለየ የመግደል፣የማፈናቀል እና ማንነትን የማስካድ ጉልበታዊ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡

ህወሃት ይህን ያደረገው ከጫካ ጀምሮ በነበረው ትግራይን ከሱዳን ጋር ጎረቤት የመድረግ እቅድ እንደነበረ የድርጅቱ መስራች ዶ/ር አረጋይ በርሄ ተናግረዋል፡፡ ሌላው ተጨማሪ ጉዳይ ልምላሜ ለሚያጥራት ትግራይ ለም መሬት የማምጣት ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ሲሆን ስነልቦናዊ ነገርም አያጣውም፡፡በሽግግር ወቅቱ ደርግን የጣለው ህወሃት በከፍተኛ የአሸናፊነት ስነ-ልቦና ሰክሮ ነበር፡፡እንደ አንድ ዘረኛ ድርጅት አሸናፊነት ቦታ ላይ ቆሞ መጀመሪያ ሊያደርግ የሚችለው ነገር ደግሞ ታገልኩላት ለሚለው የትግራይ ብሄር ይጠቅማል የተባለውን ነገር ሁሉ ማድረግ ነው፡፡ከዚህ አንዱ የትግራይን ንዑስ ግዛት በመስፋፋት ወደ ግዙፍነት መቀየር ነው፡፡ጨቋኝ እና ትምክህተኛ እያለ ሲያክፋፋው ከነበረው የአማራ ግዛት ላይ መሬት ወስዶ ለትግራይ መስጠት ደግሞ የአሸናፊነቱን ስሜት ጣፋጭ ከማድረጉም በላይ ለአማራው ሞቶ መቀበር ምልክት ተደርጎ ታይቷል፡፡የህወሃት ሰዎች “አማራውን ገድለን ቀብረነዋል” ሲሉ የኖሩበት አንዱ ምክንያት(ብቸኛው ባይሆንም) ወልቃይት ላይ ያደረጉትን ሲያደርጉ “ሃይ” የሚል ስለጠፋ ነው፡፡

ከዚህ የምንረዳው የወልቃይት ጥያቄ የማንነት ብቻ ሳይሆን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል፣የዲሞግራፊ፣የኢኮኖሚ፣የህግ የበላይት(የተጠያቂነት) እና የስነ-ልቦና ጉዳዮችን ሁሉ ሰብስቦ የያዘ መሆኑን ነው፡፡ስለዚህ የማንነትን ጉዳይ ብቻ አጉልቶ የሚያወጣው የወልቃይትን ጉዳይ የሚከታተለው ኮሚቴም ሆነ ነገሩ ያመለከተኛል ባይ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ጥያቄውን ማቅረብ ያለበት ከዚሁ አንፃር መሆን አለበት፡፡ እናም ከስሙ ጀምሮ “የወልቃይት የማንነት ጥያቄ አስተባባሪ” የሚለውን አጠራር መቀየር አለበት፡፡ ኮሚቴው በዚህ መጠሪያ መቀጠሉ “ሪፈረንደም ይደረግና የህዝቦቹ ትግሬ/አማራነት ይለይ” የሚለውን የህወሃት ክርክር የማጠናከር አስተዋፅኦ ከማድረጉም በላይ የወልቃይትን ፈርጀ-ብዙ ችግር ደፍጥጦ ከችግሩ አንዱ ብቻ በሆነው የማንነት ጥያቄ ላይ ብቻ ያንጠለጥለዋል፡፡ ይህ የሚበጀው ደግሞ ያደረገውን እያወቀ “ነገሩ በሪፈረንደም ይለቅ” ለሚለው ህወሃት ብቻ ነው፡፡

የወልቃይት ጉዳይ ከላይ በተጠቀሱት ፈርጀ ብዙ ጥያቄዎች አንፃር ከታየ ቀዳሚ ሆኖ የሚመጣው የህወሃት ባለስልጣናት ከጫካ ጀምሮ ያቀዱትን ከሱዳን ጋር የመዋሰን፣አማራን የማንበርከክ ፣ትግራይን ታላቅ የማድረግ ዕቅድ ለማሳካት በሰው ልጆች ሰብዓዊ መብት ላይ ያደረጉትን ወንጀል በተጨባጭ ማስረጃ አጠናቅሮ ለሃገር አቀፍም ሆነ ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ማቅረብ እና ነገሩን በነሱ ደረጃ እንዲከታተሉት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡የሰብዓዊ መብት ጥሰት በህግ ይርጋ የሌለው ወንጀለ ስለሆነ የተፈፀመበት ዘመን ቢርቅም ወንጀለኞቹ ለህግ መቅረባቸውን የሚያግድ ነገር የለም፡፡ይህ በዋናነት የኮሚቴው ስራ ቢሆንም የሁሉም ሰብዓዊነት የሚሰማው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ድርሻ መሆን አለበት፡፡

የሰብዓዊ መብት ጥሰቱን የማጣራቱ ስራ ለጉዳዩ ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመስጠት የሚረዳ ነገር ይዞ ይመጣል፡፡ ይኸውም “ህወሃቶች በሽግግር ወቅቱም ሆነ ከዛ ወዲህ በወልቃይት ህዝብ ላይ ያደረጉትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲያደርጉ ምን አስገደዳቸው?” የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጥ እውነተኛ መልስ የችግሩ ራስ፣ የመፍትሄውም ጭራ ነው፡፡ መልሱ የሚሆነው የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ የተካሄደው ህወሃት ትግሬ እንድትሆን የፈለጋት ወልቃይት ከሽግግሩ ወቅት በፊት በነበራት ተፈጥሯዊ የህዝብ ስብጥር ትግሬ ሆና ወደትግራይ ለመካለል የሚያስችል ትግሬነት ስላልነበራት ነበር፡፡ስለዚህ ወልቃይትን ትግሬ ለማድረግ ትግሬን በጥድፊያ ከተከዜ ማዶ እያመጡ ከማስፈሩ በተጨማሪ ለወልቃይት ቀደምት አማራነት ምልክት የሆኑ አማሮችን ከአካባቢው በእስር፣በግድያ ፣በማፈናቀል መቀነስ ወይ ማጥፋት አስፈልጓል፡፡

ከክቡሩ የሰው ልጅ ሰብዓዊ መብት የበለጠ ምንም ነገር የለምና በወልቃይት ጉዳይ ከሚነሳው ኢኮኖሚያዊ እና የድንበር ጉዳይ በፊት መመርመር ያለበት በቦታው የተፈፀመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ጉዳይ ለማጣራት ገለልተኝን እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ በስራው ብዙ ልምድ ያካበቱ እንደ “Genocide watch”, “Human rights watch” ያሉ ድርጅቶችም መጋበዝ አለባቸው፡፡የነዚህ ድርጅቶች ሪፖርት ብቻውን ወንጀለኞችን ፍርድቤት ለማቅረብ በቂ ስለማይሆን መንግስትም የራሱን ኮሚሽን አቋቁሞ ነገሩን ማጣራት አለበት፡፡ዘላቂ መፍትሄ ሊያመጣ የሚችለው እንዲህ ካለው ከስር ከመሰረት ችግሩን ከመመርመር በሚነሳ እርምጃ እንጅ ከችግሩ ወገብ ተነስቶ፣ህወሃት ችግሩን ሲፈጥር በጓዘበት መንገድ ተጉዞ “በህገ-መንግስታዊ መንገድ ይፈታ” በሚለው ፍርደ-ገምድል መንገድ አይመስለኝም፡፡

“የወልቃይት ጉዳይ በህገ-መግስታዊ መንገድ ካልተፈታ እንዴት ይፈታ?” የሚል ጥያቄ መከተሉ አይቀርም፡፡ ይህን ጥያቄ በተመለከተ የማቀርበው ነገር እኔ በግል ይበጃል ብየ የማስበውን እይታየን ለማጋራት እንጅ የመጨረሻ መልስ ለመስጠት አይደለም፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው ችግሩን ለመፍታት የሚደረገው እርምጃ መጀመር ያለበት በቦታው ለረዥም ዘመን የተፈፀመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት መርምሮ ወንጀለኛን ተጠያቂ በማድረግ ላይ መሆን አለበት፡፡ሌሎቹ ቀጥየ የማነሳቸው የቢሆን መፍትሄዎች የሚሰሩት ይህ ከተደረገ ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም በደሉ ተገልጦ ሳይወራ/ሳይካስ፣እውነት ሳይወጣ ተሸፋፍኖ ከቀረ ሁለት አደገኛ መዘዞች ይኖሩታል፡፡አንደኛው የሰብዓዊ መብት ጥሰጥን የመሰለ ክፉ ወንጀል የሰራን ሰው ዝም ብሎ ማለፍ የተጠያቂነትን እና የህግ የበላይነትን ጉዳይ ድርድር ውስጥ ማስገባት ከመሆኑም በላይ ወንጀለኛን ማበረታታት ነው፡፡ ለዚህ ነው በወልቃይት ህዝብ ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳደረጉ በሃገሬው ህዝብ ዘንድ የሚወራላቸው የህወሃት ባለስልጣናት ያለ ምንም መሸማቀቅ የወልቃት ህዝብ ጉዳይ ለማዳፈን የሚሰሩት፡፡ ሁለተኛው መዘዝ ተበዳዩ ህዝብ ቂሙን እንዳይረሳ ስለሚያደርግ ዋናውን ችግር በመሸፋፋን የተፈለገውን የሰላም መፍትሄ ማምጣት ፈፅሞ አይቻልም፡፡

የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ጉዳይ ተበዳዮችን በሚያረካ ሁኔታ በዓለም አቀፍም ሆነ በአገር አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ታይቶ እልባት ከተሰጠው በኃላ ወደ ፖለቲካዊ መፍትሄዎቹ መምጣት ይቻላል፡፡ዘላቂ ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመስጠት ደግሞ የትግራይ እና የአማራ ህዝብ/ልሂቃን ዘንድ ከእልኽኝነት ይልቅ የሚዛናዊነት እና ሆደ ሰፊነት አካሄድን መምረጥ አለባቸው፡፡በመንግስት በኩልም ከችግሩን ውስብስብነት የተነሳ እውነትን ከመሸሽ ይልች የችግሩን ብልት አውጥቶ መለሃኛ ውሳኔ ማሳለፍ አለበት፡፡ቀድሞ የሰብዓዊ መብት ወንጀሎችን ማጣራቱ እና ተጠያቂነትን ማረጋገጡ ለዚህ ጉልበት የሚሰጥ እርምጃ ነው፡፡ፖለቲካዊ መፍትሄ ሲሰጥ ከላይ እንደተጠቀሰው ችግሩ ከማንነት አልፎ የዲሞግራፊ ጉዳይ እንደሆነም በአማራም ሆነ በትግራይ ህዝቦች ዘንድ መረዳት እንዲኖር ያስፈልጋል፡፡ የችግሩ ዘላቂ ፖለቲካዊ መፍትሄ የዘውግ ፌደራሊዝምን መቀየር ነው፡፡ ይህ ግን በአጭር ጊዜ ሊሆን የሚችል አይደለም፡፡ አሁን በወልቃይት ምክንያት በትግራይ እና አማራ ልሂቃን መሃከል የተፈጠረውን እያደር የሚካረር ፍጥጫ ደግሞ አፋጣኝ መፍትሄ ያሻዋል፡፡ ይህን መፍትሄ ለማዋለድ በሁለቱ ህዝቦች ዘንድ ማስተዋል የተሞላበት አካሄድ ያስፈልጋል፡፡

ህወሃት ስልጣ እንደያዘ በመኪና እያጫነ ወደ ወልቃይት ያመጣቸው ትጥቅ-ሰቀል ወታደሮቹም ሆኑ ሲቪል የትግራይ ተወላጆች በአሁኑ ወቅት ሲመጡ በነበሩበት ቁጥር ላይ የሚገኙ አይደሉም፤እጅግ ተባዝተዋል፡፡ ወልደው እዛው ምድር ላይ ያሳደጉ ሰዎች ናቸው፡፡ እዛው ምድር ላይ ተወልዶ ያደገን ሰው ደግሞ “ዛሬ ተነስና ወደ መድረሻህ ድረስ” ማለት ከህወሃት አለመሻል ነው፡፡ እዚህ ላይ አብሮ መታየት ያለበት አንድ ህዝብ ነቅሎ ሌላውን የመትከሉ ሴራ ተጀምሮ እስኪጨረስ የተከወነው በህወሃት እንጅ “የተሻለ ህይወት ላመጣላችሁ ነው” ሲባሉ በመኪናተሳፍረው በመጡ እንጀራ ፈላጊ ግለሰቦች እንዳልሆነ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ በአካባቢው የሰፈሩ ሰዎች ህወሃትን እንደ አጉራሽ አይተው በወልቃይት ህዝብ ላይ በሚያደርገው ግፍ ላይ የመተባበር አዝማሚያ አሳይተው ከሆነም አካሄዳቸው ስህተት እንደነበረ አሁን እየሆነ ካለው ነገር መረዳታቸው አይቀርም፡፡ህወሃት የሃገሪቱን ህዝቦች ድህነት እና እንጀራ ፈላጊነት ተጠቅሞ ሲያባላ እንደኖረ ማስተዋል አለብን፡፡ ይህን ያደረጉ የህወሃት ሰዎች በህግ ቅጣት እስካገኙ ድረስ ነገሩን አርግቦ በአንድ ሃገር ልጅነት መንፈስ መተያየት ያስፈልጋል፡፡

“አብሮ መኖሩ የመሆነውስ እንዴት ባለ መዋቅር ውስጥ ነው?” የሚለውም ሌላ አስቸጋሪ ጥያቄ ነው፡፡የወልቃይትን ህዝብ ሲገድለው፣ ሲያሳድደው፣ማንነቱን ጨፍልቆ “በትግርኛ አልቅስ” ሲለው በኖረው የትግራይ ክልል መስተዳድር ስር ተዳደር ማለት እየፈጩ ጥሬ መሆን ነው፡፡በአንፃሩ ወልቃይትን እንኳን ትግሬ ለማስመሰል ከትግራይ ተነቅሎ የመጣን ህዝብ በአማራ ክልል ስር ተዳደር ማለትም አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህ የወልቃይት ጉዳይ ሌላ መሃለኛ መፍትሄ ሊሆኑ የሚችሉ አማራጮችን ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ በግሌ አንድ መፍትሄ የሚመስለኝ አካባቢውን በፌደራ መንግስት ስር የሚተዳደር ልዩ ዞን አድርጎ በህወሃት እና አዴፓ ጥምር አስተዳደር እንዲተዳደር ማድረግ ነው፡፡ የሃረሬን ክልል ኦዴፓ እና ሃብሊ እያስተዳደሩት ስለሚገኙ ይህ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ይህን ለማድረግ ግን የአዴፓ እና የህወሃት ባለስልጣናት ከገቡበት የውድድር፣የንትርክ እና እልኸኝነት መንፈስ ወጥተው ለሁለቱ ክልል ህዝቦች የተረጋጋ መፍትሄ የማምጣት ስክነት ላይ መድረስ አለባቸው፡፡

ሰላማዊ መፍትሄ ይምጣ ከተባለ እልኽኝነቱ ባስ የሚልበት ህወሃት አዴፓ በወልቃይትም ሆነ በራያ ጉዳይ ትንፍሽ እንዳይል የሚፈልገውን ነገር መተው አለበት፡፡በነዚህ ህዝቦች ላይ የቀድሞውን ብአዴንን በጠመንጃው አስገድዶ የሰራውን ሆዱ እያወቀ አዴፓ “አማራነንና በስርህ እንተዳደር” የሚሉ ሰዎችን ጉዳይ እየሰማ ዝም ይበል ማለት ብአዴን ተቀይሮ አዴፓ እንደሆነ፤ህወሃትም የቀድሞው ህወሃት እንዳልሆነ መረዳት አለመፈለግ ነው፡፡ ብአዴን አዴፓ ሆነ ሲባል የፓርቲውን መጠሪያ ሆሄያት ቀያየረ ማለት ብቻ አይደለም፡፡ ይልቅስ በብአዴንነቱ ዘመን ለህወሃት በማደግደጉ ሳቢያ ‘አይንህ ላፈር’ የሚለው የአማራ ህዝብ አሁን በተለይ በወልቃይት ጉዳይ ከሞላ ጎደል አብሮት እንደሆነ ህወሃት ማወቅ አለበት፡፡ ህዝብን የያዘ እንደሚያሸንፍ ደግሞ ለህወሃት ዛሬ ካልገባው መቼም አይገባውም፡፡ ሰላማዊ መፍትሄ የማይወደው ህወሃት ‘እኔም ህዝብን ይዣለሁና ይዋጣልን’ የሚል ከሆነ “ይሞክረው” ባይባልም እንደማያስኬደው ግን ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

አዴፓ እና ህወሃት ተስማምተው አካባቢውን ለማስተዳደር መጣጣሙ ካልሆነላቸው ሁለተኛው አማራጭ የሚሆነው የፌደራሉ መንግስት ልዩ ዞን የሆነውን የአካባቢውን አስተዳደር እንዲረከብ ማድረግ ነው፡፡ የፌደራሉ መንግስት አስተዳደሩን ከተረከበ በኋላ በአካባቢው ዘልቆ ከህወሃትም ከአዴፓም ያልሆኑ ነገር ግን ከሁለቱም ብሄሮች የተውጣጡ ብቃት ያላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች በህዝቡ ተመርጠው እንዲያስተዳድሩ ማድረግ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ የተለየ እና የተሻለ ሁለቱን ህዝቦች በሰላም የሚያኖር ውጥረቱንም የሚያረግብ ሃሳብ ያለው ዜጋ ሁሉ የታየውን ቢሰነዝር ደግሞ የተሸለ አማራጭ ላይ ለመድረስ ይቻላል፡፡
___
ለአስተያየት meskiduye99@gmail.com

ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም።
ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here