ቦርከና
ኅዳር 23, 2011 ዓ.ም.
የኢፌዲሪ የብሄራዊ የጸጥታ ምክር ቤት በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የሚስተዋሉትን የጸጥታ ችግሮች በመፍታት የህግ የበላይነትን ለማስከበር ክልሎቹ የፌዴራል መንግስት የጸጥታ አካላት በህገ መንግስቱ መሰረት ጣልቃ ገብተው ችግሩን እንዲያረጋጉ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ ምክር ቤቱ የጸጥታ አካላቱ በአካባቢው ተሰማርተው የህግ የበላይነት እንዲያስከብሩ፣ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቤትና ንብረታቸው በመመለስና በማቋቋም ሰላም እንዲያሰፍኑ በክልሉ እንዲሰማሩ ወሰነ።
የብሄራዊ የጸጥታ ምክር ቤት “የህግ የበላይነት በማረጋገጥ አስተማማኝ ሰላምን በማስፈን የህዝብ ደህንነትን ማስከበር የመንግስት ቀዳሚ ተግባር ነው! ህገ ወጦችን ወደ ህግ የማቅረቡ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል!” በሚል ርዕስ መግለጫ ማውጣቱን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ይፋ አድርጓል።
በዚሁ መግለጫው እንዳስታወቀው፤ የመንግስት ቀዳሚ ተግባር የህዝቦችን ደህንነት መጠበቅና የህግ የበላይነትን ማስከበር በመሆኑ በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የታዩትን የጸጥታ ችግሮች በመፍታት ሰላምን በማስከበርና የዜጎችን ህይወት በመታደግ የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ የፌዴራል መንግስት የጸጥታ አካላት በአካባቢው የማረጋጋት ተግባራትን በማከናወን በአካባቢው ያለውን ማንኛውንም ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎች በመቆጣጠር ተጠርጣሪዎችን ወደ ህግ እንደሚያቀርቡ ኢዜአ(የኢትዮጵያ የዜና አገልግሎት) ዘግቧል፡፡
መንግስት የህግ የበላይነትንና የህዝቦችን ደህንነት ለማረጋገጥ የጀመረውን ተግባር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በሃላፊነት እንደሚወጣ አመልክቶ፤ ተግባሩ በሌሎች ክልሎችም ተግባራዊ እንዲሆን ህዝቡ ከመንግስት ጎን በመቆም ለውጡን እውን ለማድረግ የማይተካ ሚናውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ምክር ቤቱ ጥሪውን አስተላልፏል።
በፍሬህይወት ዮሃንስ
__
ወቅታዊ እና ሚዛናዊ መረጃን ለማግኘት ቦርከናን በፌስ ቡክ ላይክ ያድርጉ።