አገልግሎት ያቋረጡ 18 ሚሊየን ሲም ካርዶች በአዲስ መልክ ለገበያ ሊቀርቡ ነው

EthioTelecom_simcard

ቦርከና
ኅዳር 24, 2011 ዓ.ም.

የመቀበልም ሆነ የመደወል አገልግሎት ያቋረጡ 18 ሚሊየን ሲም ካርዶች በአዲስ መልክ ለገበያ ሊቀርቡ መሆኑን ኢትዮ ቴሌኮም አስታዉቋል።አሁን ላይ ኩባንያው ያስቀመጣቸውን ደረጃዎች በሙሉ ጨርሰው አገልግሎት መስጠት ያቆሙ የሞባይል ቁጥሮች 18 ሚሊየን ደርሰዋል።

አርትስ እንደዘገበው ኩባንያው እነዚህን ቁጥሮች ለገበያ የሚያውላቸው ደንበኞቼ የተሰጣቸውን ጊዜ ገደብ ባለመጠቀማቸውና አገልግሎት መጠቀም ካቆሙ ከረጅም ጊዜ በላይ የቆዩ በመሆናቸው ነው ብሏል።

አንድ የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኛ አዲስ የሞባይል ሲም ካርድ ቁጥር ካወጣ በኋላ ተደጋጋሚ አየር ሰዓት የሚሞላ ከሆነ ሳይሞላ መስመሩ ሳይዘጋ ለ120 ቀናት ይቆይ የነበረ ሲሆን፥ በ120 ቀናት ውስጥ ከሞላም አገልግሎት እንደሚቀጥል ይታወቃል።

ከ120 ቀናት በኋላ ግን የሞባይል አገልግሎቱ መደወል ሳይችል ከሌላ ወገን ጥሪዎችንና መልዕክቶችን እያስተናገደ ለ330 ቀናት ይቆይ እንደነበረም ነው የተገለጸው።በእነዚህ ቀናት ውስጥ የአየር ሰዓት የማይሞላ ከሆነ ግን መስመሩ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት የሚያቋርጥ ይሆናል። እነዚህ የሞባይል ቁጥሮች ሀብት ስለሆኑ ለአዳዲስ ደንበኞች በአዲስ መለያ ለመስጠት ዳግም ገበያ ላይ በቅርቡ ለገበያ ይውላል ።

ከአሁን በፊት አንድ ደንበኛ አዲስ የሞባይል ቁጥር አውጥቶ አየር ሰዓት መሙላት ካቆመና መስመሩ መወደልም ሆነ መቀበል ካቆመበት ቀን ጀምሮ፥ በሶስት ዓመት ውስጥ ያን ቁጥር ወደ ኩባንያው ቅርንጫፎች በመጓዝ ዳግም ማውጣት ይቻል ነበር።ይህ የቆይታ ጊዜ በአሁኑ ሰዓት ወደ አንድ አመት ዝቅ ማለቱን ኩባንያው ገልጻል ።

ኢትዮ ቴሌኮም አሁን ላይ ያሉት ደንበኞች የሚጠቀሙት አብዛኛዎቹ የድምፅ አገልግሎት ቢሆንም፥ የኢንተርኔት አገልግሎትን አሁን ካለበት ደረጃ ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር የተለያዩ እቅዶችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑም ታውቋል።

በፍሬህይወት ዮሃንስ
_____
ወቅታዊ እና ሚዛናዊ መረጃን ለማግኘት ቦርከናን በፌስ ቡክ ላይክ ያድርጉ።

Published
Categorized as ዜና

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *