spot_img
Sunday, July 21, 2024
Homeነፃ አስተያየትየአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ሕገ መንግሥታዊ ነው (ጥበበ ሳᎀኤል ፈረንጅ -አሜሪካ)

የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ሕገ መንግሥታዊ ነው (ጥበበ ሳᎀኤል ፈረንጅ -አሜሪካ)

ጥበበ ሳᎀኤል ፈረንጅ (አሜሪካ)
12/21/2018 (ታህሳስ 12 2011)

“Sometimes we find ourselves walking through life blindfolded, and we try to deny that we’re the ones who securely tied the knot.”
Jodi Picoult

ከላይ የተፃፈው ከአሚሪካዊት ደራሲዋ የጆሲ ፒኮልት ብሂል በግርድፉ ሲተረጎም እንዲህ ይላል። “አንዳንዴ፤ በሕይወት ውስጥ አይናችንን በጨርቅ አስረን እራሳችንን ስናውር፤ ጨርቁን አጥበቀን የቋጠርነው እኛ መሆናችንን ደግሞ እንክዳለን።”

ይህ ጥቅስ በመጠኑም ቢሆን፤ ሰሞኑን የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ኮሚሽን አዋጁን (ከዚህ በኋላ የኮሚሽኑ አዋጅ እየተባለ ይጠቀሳል) አስመልክቶ፤ በተለይም በሕወሃት አመራር እና በደጋፊዎቹ፤ እንዲሁም “ምሁር” በሚል ታርጋ በየቴሌቪዥን መስኮቱ እየቀረቡ፤ እጅግ አስቂኝ፤ ግን አሳዛኝ አስተያየት የሚሰጡትን ሰዎች ይገልፃል። ከዚህ ቀደም “ሕገ መንግሥቱን የጣሰው ማን ነው?” በሚለው ጽሁፌ የሕወሃት አመራሮች እና ደጋፊዎቻቸው፤ ሰለ ሕገ መንግሥቱ “ሲከራከሩ”፤ እንዲሁ በድፍኑ መሆኑን እና፤ ስለ ሕገ መንግሥቱ የሚያነሱት ክርክር ጭብጥ አልባ መሆኑን አሳይቻለሁ። ዛሬም ከዚሁ ወገን የምንሰማው የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ነው የሚሉት፤ ግልብ ከሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብ እንጂ በጭብጥ ያልተመሰረተ መሆኑን አሳያለሁ። ለዚህም እንዲረዳን፤ የኮሚሽኑ ዓላማ ምን እንደሆነ በግልጽ ያስቀመጠውን አዋጅ ቁጥር 4 እና 5 የሚለውን እጠቅሳለሁ። በተለይም ቁጥር 5 ከንዑስ 1-8 ያሉት አንቀጾች፤ የኮምሽኑን ሥልጣን በግልጽ አስቀምጧል። ከሁሉም በላይ ሊሰመርበት የሚገባው፤ ይህ ኮሚሽን፤ ውሣኔ ሰጪ አካል አለመሆኑን አዋጁ በማያሻማ ሁኔታ ማስቀመጡን ነው ከዛ ቀጥዬ አዋጁን የሚቃውሙትን ሰዎች “የተቃውሞ ሃሳብ” በመጥቀስ መሰረተ ቢስነቱን አሳያለሁ።

ቁጥር 4 እና 5 የአዋጁ ድንጋጌ እንደሚከተለው ነው።

4. የኮሚሽኑ ዓላማ ኮሚሽኑ አሳታፊ፣ ግልጽ፣ አካታችና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ከአስተዳደር ወሰኖች፣ ራስን በራስ ማስተዳደር እና ከማንነት ጋር የተያይዙ ግጭቶችንና መንስኤያቸውን በመተንተን የመፍትሄ ሃሳቦችን ለህዝብ፣ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለአስፈጻሚው አካል ማቅረብ ነው።

5. የኮሚሽኑ ሥልጣንና ተግባር ኮሚሽኑ የሚከተሉት ስልጣንና ተግባራት ይኖሩታል፡-1/ ከአስተዳደራዊ ወሰኖች አከላለል፣ ራስን በራስ ማስተዳደር እንዲሁም ከማንነት ጥያቄ ጋር የተገናኙ ማናቸውንም ችግሮችንና ግጭቶችን በጥናት ለይቶ አማራጭ የመፍትሄ ሃሳቦችን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ሪፖርት ያቀርባል2/ በህዝቦች እኩልነትና ፈቃድ ላይ የተመሰረት አንድነት ስር እንዲሰድና እንዲዳብር ለማድረግ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃዎች ማሻሻያ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክረ ሃሳቦችን ያቀርባል3/ አስተዳደራዊ ወሰኖች በቀጣይነት የሚወሰኑበትንና የሚለወጡበትን መንገድ በተመለከት አግባብነት ያላቸውን ህገ-መንግስታዊ መርህዎች ያገናዘበ፣ ግልጽና ቀልጣፋ ስርዓት ወይም የህግ ማሻሻያ እንዲዘረጋ ጥናት በማድረግ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እና ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክረ ሃሳብ ያቀርባል4/ ጎልተው የወጡና በፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በፌዴራል መንግስት የሚመሩለትን የአስተዳደራዊ ወሰን ውዝግቦችን መርምሮ የውሳኔ ሃሳብ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀርባል5/ ከአስተዳደራዊ ወሰኖች ጋር በተያያዘ የተነሱ ግጭቶች ተፈተው፣ በአጎራባች ክልሎች መሃከል ያለው መልካም ግንኙነት የሚታደስበትና የሚጠናከርበትን መንገድ ያመቻቻል፤6/ በቀጣይነት አስተዳደራዊ ወሰኖች የግጭት መንስዔ እንዳይሆኑ ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች አስመልክቶ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እና ለሀዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክረ ሃሳብ ያቀርባል7/ አስተዳደራዊ ወሰኖችና አካባቢያቸው አስተማማኝ ሰላም የሰፈነባቸው የልማትና የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሂድባቸው እንዲሆኑ አስተዳደራዊ ወሰኖችን የተመለከተ የፖሊሲ ማእቀፍ ያመነጫል፤8/ የአስተዳደር ወሰን ጉዳዮችን በተመለከት የህዝብ አስተያየት ይሰበስባል፤” (ድምቀት እና ሰረዝ የተጨመረ።)

እስካሁን ካነበብኳቸው እና ከሰማኋቸው ቃለ መጠይቆች፤ ኮሚሽኑ የተቋቋመበት አዋጅ ሕገ መንግስቱን ይፃረራል ብለው የሚሟገቱት ሃይሎች፤ ከሕገ መንግሥቱ የጠቀሷቸው ሁለት አንቀፆች፤ አንቀጽ 9ን እና አንቀጽ 39 ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም በሃገሪቱ ጦርነት ያስነሳል፤ሕዝብ ያልመከረበት ነው፤ የትግራይን ሕዝብ ለመጉዳት ነው፤ እና በጣም ገራሚ የሆነው ደግሞ፤ በብሔር ብሔረሰቦች በኩል የተነሳ የማንነት ጥያቄ አሁን የለም፤ የሚሉ መሰረተ ቢስ መከራከርያዎችም አንስተዋል። በመጀመርያ የተጠቀሱትን አንቀጾች እንመልከት።

አንቀጽ 9 የሚያወሳው ስለ- የሕገ መንግሥት የበላይነት ነው፤የሚለውም እንደሚከተለው ነው።

“ሕገ መንግሥቱ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ ነው። ማንኛውም ሕግ ልማዳዊ አሠራር፣ እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም።” አንቀጽ 9 የሚለው ይህ ሲሆን፤ የኮሚሽኑ አዋጅ ከዚህ አንቀጽ ጋር እንዴት እንደሚጋጭ ግልጽ አይደለም። ይህንን አንቀጽ ይዞ ለመከራከር፤ በመጀመርያ ደረጃ፤ አዋጁ እራሱ ሕገ መንግስቱን የጣሰ መሆኑን ማስረዳት ያስፈልጋል። አዋጁ የትኛውን የሕገ መንግስት አንቀጽ ነው ይሚፃረረው? የሚል ጥያቄ መነሳት እና መልስ ማግኘት አልበት። አዋጁ፤ አንቀጽ 39ን ስለሚጻረረ፤ አንቀጽ 9 አዋጁን ውድቅ ያደርገዋል ከሆነ ክርክሩ፤ አንቀጽ 39 ደግሞ ምን እንደሚል ማየት ነው። የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 39 የሚከተለውን ይላል።

“አንቀጽ 39 – የብሔሮች ብሔረሰቦች ሕዝቦች መብት

1. ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከመገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው፡፡

2. ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ በቋንቋው የመናገር፣ የመጻፍ፣ ቋንቋውን የማሳደግ፣ እና ባሕሉን የመግለጽ፣ የማዳበርና የማስፋፋት እንዲሁም ታሪኩን የመንከባከብ መብት አለው፡፡

3. ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ ራሱን የማስተዳደር ሙሉ መብት አለው። ይህ መብት ብሔሩ፣ ብሔረሰቡ፣ ሕዝቡ በሰፈረበት መልክዓ ምድር ራሱን የሚያስተዳድርበት መንግሥታዊ ተቋማት የማቋቋም እንዲሁም በክልልና በፌዴራል አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት መብትን ያጠቃልላል፡፡

4. የብሔር፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብት ከሥራ ላይ የሚውለው፤

ሀ) የመገንጠል ጥያቄ በብሔር፣ በብሔረሰቡ ወይም በሕዝቡ የሕግ አውጪ ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ የድምፅ ድጋፍ ተቀባይነት ማግኘቱ ሲረጋገጥ፤
ለ) የፌዴራሉ መንግሥት የብሔር፣ የብሔረሰቡ ወይም የሕዝቡ ምክር ቤት ውሳኔ በደረሰው በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለጠያቂው ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ሕዝበ ውሳኔ ሲያደራጅ፤
ሐ) የመገንጠሉ ጥያቄ በሕዝብ ውሳኔው በአብላጫ ድምፅ ሲደገፍ፤
መ) የፌዴራል መንግሥት መገንጠሉን ለመረጠው ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ምክር ቤት ሥልጣኑን ሲያስረክብ፤
ሠ) በሕግ በሚወሰነው መሠረት የንብረት ክፍፍል ሲደረግ ነው፡፡”

ማንም ማሰብ የሚችል ሰው እንደሚገነዘበው የኮሚሽኑ አዋጅ ከአንቀጽ 39 ጋር የሚጣረዝበት አንድም ነገር የለውም። እንደውም፤ የኮሚሽኑ መቋቋም፤ ለአንቀጽ 39 ድጋፍ የሚሰጥ እና በጥናት የተደገፈ የምክር ሃሳብ ለፌደራል መንግስት የሚያቀርብ ተቋም ነው። ይህም ግጭቶችን ይቀንሳል እንጂ እንዴት ግጭት ሊያባብስ እንደሚችል ግራ ያጋባል። ስለዚህ የኮሚሽኑ አዋጅ ሕገ መንግስቱን ይፃረራል የሚሉ ሰዎች ወሃ የሚቋጥር ሕገ መንግስታዊ መከራከርያ ነጥብ የላቸውም። እንደውም ሕገ መንግስቱ፤ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕግ አርቅቆ የማስፀደቅ ሥልጣን ስለሚሰጠው፤ ምክር ቤቱ የተከተለው ሕገ መንግሥቱን ነው። ሕገ መንግስቱ በግልጽ ያስቀመጣቸው ድንጋጌዎችም፤ የኮሚሽኑ መቋቋም አዋጅ ላይ ለተነሱት አንዳንድ የተቃውሞ ነጥቦች የማያሻማ መልስ ይሰጣል። ለምሣሌ፤ ሕዝብ ያልተውያየበት ነው የሚለው ውኃ የማይቋጥር ሃሳብ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 8 መልስ ያገኛል። በተለይ ንዑስ አንቀጽ 3 በማያሻማ መልኩ፤ ሕዝቡ ሕግ ላይ ውይይት የሚያደርገው፤ በተወካዮቹ አማካኝነት መሆኑን ይገልፃል። “የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ስራቸው ሕዝቡን ወክሎ መምከር፤ መከራከር እና ሕግ መደንገግ ነው። ስለዚህ የሕዝብ ተወካዮች ተወያዩበት ማለት፤ ሕዝቡ ተወያየበት ማለት ነው። በየትም ሃገር፤ ሕግ አውጪው አካል ሁሉንም ነገር ለሕዝብ እያወያየ አይወስንም። በእርግጥ እንዳስፈላጊነቱ ሕግ አውጪ አካል ሕዝቡን የሚያወያይባቸው ጉዳዮች አሉ፤ ይህንንም የሚወስነው ምክር ቤቱ ነው። አንቀጽ 8 ከቁጥር 1 እስከ 3 እንዲህ ይላል።

1.“የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው፡፡

2.ይህ ሕገ መንግሥት የሉዓላዊነታቸው መግለጫ ነው፡፡

3.“ሉዓላዊነታቸውም የሚገለጸው በዚህ ሕገ መንግሥት መሠረት በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካይነት ይሆናል፡፡” (ስርዝና ድምቀት የተጨመረ።)

ከዚህ በተጨማሪ፤ የአከላለል ለውጦችን በተመለከተ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 48 ለፌደራል መንግስት የሚሰጠው ሥልጣን አለ። አንቀጽ 48 እንዲህ ይላል።

“የአከላለል ለውጦች

1. የክልሎችን ወሰን በሚመለከት ጥያቄ የተነሳ እንደሆነ ጉዳዩ በሚመለከታቸው ክልሎች ስምምነት ይፈጸማል። የሚመለከታቸው ክልሎች መስማማት ካልቻሉ የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት የሕዝብን አሰፋፈርና ፍላጎት መሠረት በማድረግ ይወሰናል፡፡

2. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት የቀረበ ጉዳይ ከሁለት ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በፌዴሬሽኑ ምክር ቤት የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጥበታል፡፡”

አንቀጽ 48ን በጥሞና ከተመለከትን፤ የኮሚሽኑ መመስረት፤ የፌዴሬሽኑን ምክር ቤት እጅግ የሚጠቅም ሆኖ እናገኘዋለን። ፌዴሬሽኑ የክልል ጉዳዮችን ወሰን በተመለከተ፤ በጥናት እና በመረጃ የተደገፈ ውሳኔ እንዲወስን ይረደዋል። ምክንያቱም የኮምሽኑ አላማ፤ በከፊል፤ ጥናት ማድረግ፤ ሃሳብ ማመንጨት፤ የሕዝብ ሃሳብ መሰብሰብ ናቸው እና። ከዚህ ሌላም የኮምሽኑ አዋጅ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 50 ንኡስ ቁጥር 3 የተደገፈ ነው።

አንቀጽ 50 (3) እንዲህ ይላል፡-

“የፌዴራሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን አካል የፌዴራሉ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። ተጠሪነቱም ለሀገሪቱ ሕዝብ ነው። የክልል ከፍተኛ የሥልጣን አካል የክልሉ ምክር ቤት ነው፤ ተጠሪነቱም ለወከለው ክልል ሕዝብ ነው፡፡” ከዚህ በተጨማሪ የሕገ መንግስቱ ቁጥር 54 የምክር ቤቱ አባላት የመላው ሕዝብ ተወካዮች ናቸው ሲል አረጋግጧል፡፡ ስለዚህ ሕዝብ ያልተወያየበት ነው የሚለው፤ የአዋጁ ተቃዋሚዎች መከራከርያ ሃሳብ የወደቀ ሃሳብ ነው።

ስለሕግ አጸዳደቅ የሚደነግገው አንቀጽ 57፤ ለምክር ቤቱ ሕግ እንዲያወጣ ሥልጣን የሰጠው ሲሆን፤ አንቀጽ 59 ደግሞ “በዚህ ሕገ መንግሥት በግልጽ በተለይ ካልተደነገገ በስተቀር ማናቸውም ውሳኔዎች የሚተላለፉት በምክር ቤቱ አባላት የአብላጫ ድምፅ ነው።” ሲል ምክር ቤቱ በአብላጫ ያሰለፈው ሕግ የሃገሪቱ ሕግ እንደሚሆን አስምሮበታል። የኮሚሽኑ አዋጅ ተቃዋሚዎች፤ አንዱ መከራከርያቸው አዋጁ የትግራይን ክልል ለመጉዳት ነው የሚል ነው፤ ግን፤ የትግራይን ክልል እንዴት እንደሚጎዳ ያቀረቡት ምንም ጭብጥ የለም። ችግሮች እንዳይነሱ ጥናት የሚያደርግ፤ ግጭቶች ከተነሱ በኋላም ግጭቶችን በሰላም ለመፍታት ጥናት የሚያደርግ እና የመፍትሔ ሃሳቦችን ለፌደራል መንግስቱ የሚያቀርብ ተቋም፤ እንዴት ትግራይን ሊጎዳ እንደሚችል ምንም ግልጽ አይደለም። የሚያሳዝነው እና የሚያሳፍረው፤ ግን በአሁኑ ስዓት በኢትዮጵያ የሚደረጉ ማናቸውም በጎ ነገሮች የማይዋጣለት እና፤ የሕዳሴውን ጉዞ ለማደናቀፍ ታጥቆ የተነሳው ጽንፈኛ ቡድን፤ የትግራይን ሕዝብ ከወንድሞቹ ጋር ለማጋጨት የማይቆፍረው ድንጋይ አለመኖሩ ነው። እነዚህ ለሕዝብ ምንም ደንታ የሌላቸው፤ ግን በሕዝብ ስም የሚነግዱ ሃይሎች፤ ስለግል ጥቅማቸው ከመጨነቅ ይልቅ ሃገርን እና ሕዝብን ቢያስቀድሙ፤ ካለአስፈላጊ ቀውሶች እንድናለን። እሳት፤ ጫሪውንም አብሮ እንደሚበላ የሚያስረዳ መካሪ ያስፈልጋቸዋል። እንደውም ይህን አዋጅ በቅንንነት ካዩት፤ የኮሚሽኑ አዋጅ የትግራይን ክልል በብዙ መልኩ የሚጠቅም ነው። ለምሣሌ በወልቃይት ጠገዴ፤ በቅማንት፤ በራያ እና መሰል ሕዝቦች የተነሱ የማንነት ጥያቄዎች አሉ። እነዚህን ጥያቄዎች፤ በጥናት እና በሰላማዊ መንገድ መፍታት ነው የሚበጀው ወይንስ በጥይት? ሰላም ለሚፈልግ ሃይል መልሱ ግልጽ ይመስለኛል።

ሌላው በጣም የሚያሳዝነው እና የሚያሳፍረው፤ ጠዋት ጠዋት ከእንቅልፋቸው ሲነሱ፤ በሃገር ውስጥ በየአካባቢው ያሉ ግጭቶችን እያነፈነፉ በየማህበራዊ ገፃቸው የሚለጥፉልን ሰዎች፤ “አሁን መች የማንነት ጥያቄ ተነሳና ነው ኮምሽኑ የሚያስፈልገው?” የሚለው ክርክራቸው ነው። ምናልባት፤ ከሁለት ዓመታት በላይ የፈጀው የወልቃይት ጠገዴ ጥያቄ እና ያስነሳው ግጭት ለእነዚህ ሰዎች ተዘንግቷቸው ይሆን? ራያ ውስጥ በማንነት ጥያቄ ምክንያት የሚቀጠፈው ሕይወት፤ የሰው ሕይወት አልመሰላቸው ይሆን? ከመቸውም በላይ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ “የማንነት ጥያቄ” ሃገሪቱን እያተራመሰ ለመሆኑ፤ በድሎት አልጋ ላይ መቀሌ ለተኙት ሹማምንት፤ ይህ ጠፍቷቸው ይሆን? ነገሩ “አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም” ዓይነት ነው። እነሱ ባኮረፉ ቁጥር የሚመዟትን ሕገ መንግስት እራሳቸው ቢያከብሩ እና እራሳቸው የሕግ ተገዢ ቢሆኑ፤ መቀሌ ላይ አላስፈላጊ ሕዝበ ተእይንት ባላስፈለገ ነበር። ይህንን ምስኪን ለፍቶ አዳሪ ሕዝብ እያስገደዱ ሰላማዊ ሰልፍ ከማሰወጣት፤ እራሳቸው ያፀደቁትን፤ ግን አንብበው የማያውቁትን ሕገ መንግሥት ቢፈትሹ፤ የሚበጀው ለራሳቸው ነው።

ሕጉን የመቃወም መብታቸው የተከበረ ነው፤ ግን ሕጉን በመቃወም ስም እያሳዩ ያሉት ባህሪ እና ሸፍጥ የትም አያደርስም። በተለይ የጦርነት ታምቡር ጉሸማቸው፤ ሊያሳፍራቸው ይገባል። በእርግጥ ሕገ መንግስቱን አንብበው የተረዱ ሰዎች ቢሆኑ፤ የኮምሽኑ አዋጅ ሕገ መንግስቱን ጥሷል ብለው፤ በአቋማቸው ከተማመኑ እና ሕገ መንግሥታዊ መከራከርያ ካላቸው፤ አንቀጽ 62 መፍትሔ ይሆናቸዋል። የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62 በማያሻማ ሁኔታ እንደሚያሰቀምጠው፤ የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ሥልጣን አለው፡፡ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔን የማደራጀት ሥልጣን አለው። የኮምሽኑ ተቃዋሚዎች፤ ተቃውሟቸውን ሕጋዊ እና ተገቢ በሆነ ሁኔታ መሟገት ሲችሉ፤ እየሄዱበት ያለው መንገድ ግን እራሳቸውን የሚያጠፋ ነው። ሕግ ይከበር እያሉ ሌትና ቀን እያላዘኑ፤ ምክር ቤቱ ያወጣው ሕግ ትግራይ ውስጥ ተግባራዊ አይሆንም ብሎ መፎከር እንዴት ሕግን መከተል እና ሕግ ማክበር ሊሆን ይችላል።

የትግራይ ቲቪ “ምሁራን” በሚል ታርጋ ለጥፎ ካነጋገራቸው እጅግ አስቂኝ ከነበሩት አስተያየቶች ቀልቤን የሳበው፤ ይህንን ሕግ በአለም አቀፍ ፍርድ ቤትም ተከራክረን እናሰርዘዋለን የሚለው ነው። ይህ ምሁር ሕገ መንግስቱ የሃገሪቱ የበላይ ሕግ መሆኑን ከሆነ የተማረው፤ የውጭ ሃይል በምን ተአምር፤ ወይም በየትኛው አሰራር ነው ጣልቃ ሊገባ የሚችለው? በኮምሽኑ መቋቋም ላይ የሚነሱ ተቃውሞዎች፤ ሊከበሩ እና ሊታዩ ይገባቸዋል። የኮምሽኑ አዋጅ ተቃዋሚዎችም ተቃውሟቸውን በጭብጥ ሃሳብ ላይ የተመሰረተ ያድርጉ፤ ሕገ መንግሥታዊውን አሰራር ይከተሉ፤ ሕጋዊ መንገድ ተከትለው ካሸነፉ ሃሳባቸው ይከበር፤ ከተሸነፉም ሕግ ያክብሩ። ግን፤ በትግራይ ሕዝብ ስም አይነግዱ፤ የትግራይ ሕዝብ ላይ ዘመቻ እንዳለ አድርገው አይሰበኩ፤ የጦርነት ታምቡር አይጎሽሙ፤ መጥፊያቸውንም አይደግሱ።
____
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም።
ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here