spot_img
Friday, July 19, 2024
Homeነፃ አስተያየትየጎሳ አከላለልና የጎሳ ፖለቲካ ከኢትዮጵያ መወገድ ያለበት፤ አሳማኝ ምክንያቶች (ዶ/ር አበራ...

የጎሳ አከላለልና የጎሳ ፖለቲካ ከኢትዮጵያ መወገድ ያለበት፤ አሳማኝ ምክንያቶች (ዶ/ር አበራ ቱጂ)

ዶ/ር አበራ ቱጂ
ታህሳስ 13 2011 ዓ.ም.

በ PDF ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐቢይ ስልጣን ከያዙ ጀምሮ በኢትዮጵያ የተስፋ ጎህ ቀዷል። አዲሱም አመራር አበራታች ጥረት እያደረገ ነው። ያም ሆኖ ግን በአገሪቱ በጎሳ ክልል መካከል እየተፈጠረ ያለው ችግር ሁሉንም የአገሪቱን ክፍል እያዳራሰ ነው። በጎሳ መካከል የሚፈጠረው ችግር የአገሪቱን ዜጎች በእጂጉ የሚያሳስብ ጉዳይ ሆኗል። በኢትዮጵያ ወደ 2.5 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ በአገሩ ውስጥ ተፈናቅሏል። በራሱ አገር በኢትዮጵያ ውስጥ ስደተኛ ሆኗል። ብዙዎች በዚህ ግጭት ሞተዋል። ብዙዎች የመከራ ኑሮ እየገፋ ነው። ንጹህ ዜጋ በህዝብ ተከቦ በቪድዮ እየተቀረጸ ሲገደልና ሲሰቀል እስከማየት ደርሰናል። የጎሳ ፖለቲካ ዜጎችን እየበላ እያደገና አገር ለማጥፋት እየተዘጋጀ ነው።

የዚህ የአገራችን ችግር ስረ-መሰረቱ ህውሃት-ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ላይ የፈጠረው፣ ሆን ተብሎ የተተከለ፣ ስርዓታዊና ህገ መንግሥታዊ መሰረት ያለዉ የጎሳ ወይም የዘር መድሎ ፖሊሲ ነው። ኢትዮጵያ ከገባችበት የፖለቲካ አዘቅት የምትወጣዉ ይህን የጎሳ ፖለቲካና በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ከፋፍይና አድሏዊ አከላለል አስወግዳ፣ በምትኩም የዜግነት ፖለቲካና ሁሉንም በዕኩልነት የሚዳኝበት የህግ የበላይነት ስትመሰርትና በተግባር ስታዉል ብቻ ነው። ይህም ሲባል የጎሳ አደረጃጀት በኢትዮጵያ ያመጣዉ ቀዉስ በተግባርና በተጨባጭ ስለታየ ነዉ። በአለማችን የመጨረሻ ድሃ ከሚባሉት አገሮች መካካል ያለችዉ ኢትዮጵያ፣ በሰላምና በአንድናቷ እንድትኖር፣ ብዙ ጊዜ በማይሰጠዉና ቀስፎ ከያዛት ድህነት ላይ ታተኩር ዘንድ፣ ይህን የጎሳ ፖለቲካና ግጭት ከስር መሰረቱ ማስወገድ ለጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐቢይ አስተዳደርና ለኢትዮጵያ ህዝብ የመጀመሪያዉ ስራ ሊሆን ይገባል። አገሪቱ በአንድነቷ እንድትቀጠልና የህዝብ እርስ በዕርስ ጦርነት እንዳይነሳ፣ በሩዋንዳ ያየነዉ በኢትዮጵያ እንዳይደገም፣ ከዚህ የበለጠ ቅድሚያ የሚሰጠዉ ጉዳይ የለም። በዶ/ር ዐቢይ የሚመራዉ የለዉጥ ሃይልም፣ በቅርብ ጊዜ ታሪክ ባልታየ ደረጃ፣ ከፍተኛ የህዝብ ተቀባይነትና ተወዳጅነት ስላለዉ፣ ይህንም የጎሳ ፖለቲካ ለማስወገድ ግንባር ቀደም ሚና ሊኖረዉ ይገባል። ይህንም ለማድረግ የኢትዮጵያ የህዝብ ድጋፍ አለዉ።

በአንድ ወቅት የተባይ ማጥፊያ ነዉ፣ ለችግርም መፍትሄ ነው ተብሎ በመንግስት መመሪያ የተረጨ ኬሚካል ምድሩንና አየሩን ከመረዘዉ፣ ዉሃዉን ከበከለው፣ ጠቃሚ ተክሎችን የሚያጠፋ ከሆነ፣ መንግስት ምን ማድረግ አለበት? መጀመሪያ መደረግ ያለበት፣ ይህን መርዘኛ ኬሚካል በጥቅም ላይ እንዳይዉል በአዋጅ ወይንም በህግ ማገድ ነው። ቀጥሎ መደረግ ያለበት፣ ምንም እንኳ ስራዉ አዳጋች ቢሆንም፣ ጤናማ አገርና ህዝብ እንዲኖር ሲባል፣ የተበከለዉን አካባቢ በተለያዩ በተፈተኑ ዘዴወች ማጽዳትና አካባቢዉን ወደ ጤናማ ይዞታዉ መመለስ ነው። ከዚህ ሌላ አማራጭ የለም፣ ምክንያቱም ምድራችን አንድ ብቻ ናትና።

የአሁኑ የኢትዮጵያ ሁኔታ በዚህ ይመሰላል። ህዉሃት ወደስልጣን ሲወጣ፣ ከኦነግ ጋር በመሆን ኢትዮጵያን በጎሳ የሚከፋፍለዉን ህገ መንግስትና የጎሳ አከላለል አዉጥተው የአገሪቱ መታዳደሪያ አደረጉ። በዚህም መሰረት ለሃያ ሰባት ዓመታት በአገሪቱ ዉስጥ ጥላቻ ተነዛ። በአሜሪካ ፎርቹን 500 ተብለዉ ከሚታውቁት ኢኮኖሚዉን ከሚመሩት ታላላቆቹ ድርጂቶች፣ ወደ ግማሽ የሚጠጉት የተመሰረቱት ከዉጭ በመጡ ሰዎች ወይንም በእነርሱ ልጆች ነው። አገሩ ፈጠራንና ስራን እንጂ ጎሳን ወይንም የመጡበትን አገር ባለማየቱ ነዉ ሃያል ሆኖ የቀጠለዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ ግን ዜጎች ከአንድ ክልል ሄደዉ በሌላ ክልል እንዳይሰሩ ተደረገ። ኢትዮጵያዊያን በተሰደዱባቸዉና ወላጆቻቸዉ ባልገነቧቸዉ ምዕራባዊያን አገሮች ለፖለቲካ ስልጣን በሚወዳደሩበት ዘመን፣ የአንድ ጥቁር ኬኒያዊ ልጅ የአሜሪካ ፕሬዘደንት ሲሆን አይተን፣ ኢትዮጵያዊያን ግን በአገራቸዉ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰዉ የመሥራት ተፈጥሯዊ መብታቸው ተነፈገ። ከወሊሶ ሂዶ ወልቂጤ ወይንም ከወልቂጤ ሂዶ ወሊሶ ስራ ማግኘት ጭራሽ የማይታሰብ ሆነ፡፡ ክፍፍሉ በሁሉም ዘርፍ ሆኖ በቤተሰብ ደረጃ ደረሰ። የባህልን ትሥሥር በማወቅ ከሌላ አካባቢ ከመጡ ወገኖቻቸው ጋር ለመተዋወቅ ሊረዱ የሚገባቸዉ የከፍተኛ ትምርት ቤቶች ሳይቀር የጎሳ ክፍፍል ማሰልጠኛና የጠብ ሜዳዎች ሆኑ። የተማሪዎች ማደሪያ አመዳደብና፣ የተማሪዎች ማህበር አደረጃጀት ሳይቅር በጎሳ የተከፋፈለ ሆነ።

የመንግስት ሰራተኞች በተወለዱበት አካባቢ እንዲወሰኑ ተደረገ። ይህም የሃሳብ ብዝሃነት እንዳይኖርና፣ አዲስና የተሻለ ሃሳብ በስራ ላይ እንዳይዉል አደረገ። ዜጎች ከሌላዉ የአገሪቱ ክፍል ከመጣዉ ወገናቸዉ ጋር እንዳይተዋወቁ ሆን ተብሎ መጋረጃ ተደረገባቸዉ። የመንግስትም ዋናዉ ስራ ህዝብን በጎሳ መለያየትና ማጠር ሆነ። በተጨማሪም ዜጎች የተለየና አማራጭ ሃስብ ማመንጨት እንዳይችሉ የሚያደነዝዝ የህዉሃት ፖለቲካ ሰበካ ተደረገባቸው። ዜጎች ዕውነተኛ መረጃ አያገኙም፣ የተነገራቸውን ብቻ መቀበልና የታዘዙትን መከተል ባህላቸው እንዲሆን ተደረገ። አዲስ በሬ ወለደ ታሪክ በመፍጠር፣ አንዱ በሌላው ላይ ጥላቻና ጥርጣሬ እንዲኖረው ተደረገ። ለዚህ የትግራዩን የመምህር ገበረኪዳን ደስታን ታሪክ ትንተና ማየት ይበቃል።

በአጭሩ ኢትዮጵያ የብሔረሰቦች እስር ቤት ናት በማለት እንቅስቃሴያቸውን የጀመሩት የስድሳወቹ የተማሪ ፖለቲከኞችና ህዉሃት፣ የአሁኗን ኢትዮጵያ ጎሳዎች በየጉሪያቸው ተከፋፍለው የታሰሩባት ወህኒ ቤት አደረጓት። አሁን በኢትዮጵያ የምናየው የጎሳ ግጭት የዚህ የኢሃዲግ የመንግሥት ህገ-መንግስታዊ ከፋፋይ ሥርዓት ውጤት ነዉ። በወያኔ በተደረገዉ የረጂም ጊዜ አዕምሮ አጠባ (brain wash) የተነሳ ወይንም በፍርሃት፣ ብዙዎች ይህን አፍጥጦ የመጣ ሃቅ መረዳት እየቸገራቸዉ ነው። ይህ አስከፊ የዜጎች ዕርስ በዕርስ መገዳደል መቆም አለበት። ብዙ ሰዉ በግልጽ ያልተገነዘበዉ ነገር ቢኖር፣ ህዉሃት ይህን ስርዓት የፈጠረዉ፣ ህዝቡን በጎሳ ከፋፍሎና ደካማ አሻንጉሊት የጎሳ መሪዎችን በማስቀመጥ፣ የአገሪቱን ሃብትና መሬት ለመዝረፍና ለመሸጥ መሆኑን ነው። ከኢኮኖሚያዊ ምክንያቱ በተጨማሪ፣ በህይወት ለመኖር ስንል፣ ይህ የሚያጫርሰን የጎሳ ክፍፍል አስተዳደር መቅረት አለበት። ለዚህም የሚከተሉት ዝርዝር አሳማኝ ምክንያቶች አሉ።

በማናዉቀዉ ፅንሰ-ሃሳብ እየተጋደልን ነው፤ በኢትዮጵያ ህገ መንግሥት ብሔር ብሄረሰቦች ህዝብ የሚለው ፅንሰ-ሃሳብና ትርጉሙ በውል ተለይቶ አይታውቅም፡፡ ፅንሰ-ሃሳቡም ለኢትዮጵያ አግባብ የለውም፡፡ ብሔር ብሔረሰብና ህዝቦች የሚለው ምን ለማለት እንደሆነ ለብዙው ኢትዮጵያዊ ቀርቶ ህግ አውጭ ነን ብለዉ ፓርላማ ዉስጥ የሚቀመጡት፣ ህግ አስፈጻሚ ነን የሚሉት ባለስልጣናት፣ የቃላቱን ወይንም ጽንሰ ሃሳቦቹን ትርጉም አያውቋቸውም። ስለዚህ ማነው ብሔር፣ ማነው ብሔረሰብ፣ ማነው ህዝብ የሚለው በትክክል አይታወቅም። ስለዚህ ኢትዮጵያዊያን ትርጉሙ ባልገባን ባዕድ ቃላት እርስ በዕርስ ተከፋፍለን እየተጋደልን ነው። ይህ በብሔር ብሔረሰብ ህዝብ የሚለው ከስታሊን ዘመን ፖለቲከኞች፣ አገራቸዉን ባግባቡ ያላወቁ በአስራ ዘጠኝ ስድሳዎቹ ወጣት የተማሪ ፖለቲከኞች የተኮረጀና ለእኛ አገር ፍፁም አግባብነት የሌለው ባዕድ ነገር ነው እያጋደለን ያለዉ።

ያልነበረንና የማይኖርን ወሰን ለመፍጠር ሲባል ህዝብን ማጋደል፤ እነዚህ ብሔር ብሔረሰብ ህዝብ ተብለው በቋንቋ የተከፋፈሉ ክልሎች መካከል የማያሻማና ግልፅ ወሰንና የመለያ መስመር ለማድረግ የማይቻል ነዉ። የጎሳ የሃሳብ መስመሩ ያለው በወያኔ-ኢሃዲግ ፖለቲከኞች አዕምሮ እንጂ፣ በህዝቡና በመሬት ላይ የለም። ይህን በወያኔዎች የቅዠት ምናብ ያለ የጎሳ የሃሳብ መስመር በህዝቡ ወስጥ ለማስመር ሲባል ህዝብ ወደማይቆም ብጥብጥና ግጭት እየገባ ነው። ለምሳሌ የኦሮሞ ክልል አልቆ የጉራጌ ዞን የሚጀምረው በትክክል ድንበሩ ወይንም መስመሩ የት ላይ ነው? በመካከል ሁለቱንም ቋንቋ የሚናገሩ የተሳሰሩ ዜጎች የሉም ወይ? በሱማሌና ኦሮሞ፣ በአማራና ትግሬ፣ እንዲሁም በሌሎችም መካካል ህዝቡን የጎሳ ፖለቲከኞች እንደፈለጉት መከፋፈል ባለመቻሉ ግጭቱ ይቅጥላል። የግጭቱ ምክንያት የማይለያይንና የተወሃደን ህዝብ ለመለያየት በሚደረግ ዋጋቢስ ትግል ነው።

የትኛዉ ቦታ ነው ለማን የሚሰጠው፣ በምንስ መሰረት? በደም ወይም DNA ምርመራ ነው? በሚናገረው ቋንቋ ነው? በህዝብ ብዛት ነዉ? በታሪካዊ ይዞታ ነው? ያስ ከሆነ ወደኋላ እስከመቼ ያለዉን ታሪክ ነዉ የምናየዉ? ቦታዉ በተሰየመበት ቋንቋ ነው? ለምሳሌ አሁን የቅማንት ነዉ፣ የአማራ ነው እየተባሉ ሰዎች የሚሞቱባቸው ቀበሌዎች ጉባይ፣ ሌንጫ፣ መቃ ይባላሉ። በቦታ ስም ካየን ኦሮምኛ ይመስላሉ። የቦታ ስም የተሰየመበትን ቋንቋ ካየን አንዳንድ የኦሮሞ የጎሳ ፖለቲከኞች ቅኝ ገዥ ናቸዉ የሚሏቸዉ፣ እቴጌ ጣይቱ ብጡል አዲስ አበባን የቆረቆሩት፣ የኦሮሞዉ የራስ ጉግሳ የልጅ ልጅ ልጅ ሲሆኑ፣ ባለቤታቸዉ አጼ ሚኒሊክ ከጣያሊያኖች ጋር ታሪካዊዉን ዉለታ የተፈራረሙበት ቦታ ደግሞ ከጢጣ አልፎ መርሳ ሳንደርስ ዉጫሌ ላይ ነዉ። ትንሽ ኦሮምኛ ለሚችል ሰዉ እንዲህ ያሉ የቦታ ስሞች በተለያዩ በሰሜኑ የአገራችን ክፍሎች መኖራቸዉን ሲሰማ፣ ምንም እንኳ ታሪክ ባያዉቅ፣ እንዴት ነዉ “የመቶ ዓመትን ታሪክ” ተብሎ የተነገረዉን ተቀብሎ የሚነዳዉ? በሌላ በኩል ደግሞ አዲስ አበባ የኦሮም ብቻ ናት ሌላው መጤ ነው የሚሉት ጎሰኖች በ1450 አካባቢ በዚያዉ በአዲስ አበባ አካባቢ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ከተማ እንደነበር ያለዉን የአርኪዮሎጂ መረጃ ማየት አይፈልጉም። የጎሳ ፖለቲከኞች ይህን ትሥሥራችንን የሚያሳየዉን ሃቅ ግን መመርመርና ማጥናት አይፈልጉም። የተነገራቸዉን “የመቶ ዓመት ታሪክ” ይዘዉ ያላዝናሉ እንጂ።

ሁሉም የጎሳ ፖሊቲከኞች አንድ ትልቁንና የሚያግባባቸዉን ካርታ በመያዝ፣ ታላቋን ኢትዮጵያን የራሳቸዉ በማድረግ ፋንታ፣ የግላቸዉን ትንንሽን የሚያጋጩ ካርታዎችን በኪሳቸዉ ይዘዉ ንግስናቸዉን እየጠበቁ ነው። ግጭቱ በቋንቋ ተለያይቶ ብቻ ሳይሆን በመንደርም እየሆነና የማይቆም ነው። በደቡብ አካባቢ የማይቆም የሚመስል የክልል፣ የወረዳና የራስ አስተዳደር ጥያቄ እየተነሳ ነዉ። ምንድን ነዉ መመዘኛዉ? ኢትዮጵያ የጎሳ ፖለቲካ መሞከሪያ ቤተ-ሙከራ (laboratory) ሆናለች። በድንቁርና ሙከራዉን በሚያክሂዱ “ተመራማሪወች” የቤተ-ሙከራዉ መሳሪያወችና እቃዎች እየተቃጣጠሉ ነው። አሁን የምንፈራዉ አጠቃላይ ቤተ ሙከራው እንዳይቃጠልና እንዳይወድም ነዉ። በዚህ በክልል ድንበር የተነሳ እስከአሁን ያለቁት ወገኖቻችን፣ የተፈናቀሉት ዜጎች በቂ ትምህርት አይሰጠንሞይ? መቼ ነዉ የራሳችን ጉዶች የፈጠሩት መከራ የሚበቃን? ኢትዮጵያዊያን ምን አደነዘዘን?

አንድ ክልል ለተወሰኑ የህብረተሰብ አካል ሲሰጥ፣ በሌላ አባባል ሌላው የህብረተሰብ ክፍል የዚያ አካል አይደለም ማለት ነው። ይህም “የኔ የብቻዬ ነው” ለማለት ነዉ። የአማራ ክልል ለአማራ ነው ማለት፣ በሌላ አባባል፣ የትግሬው አይደለም፣ የኦሮሞው አይደለም፣ የጉራጌው አይደለም ማለት ነዉ። ስለዚህ አከላለሉ፣ የአንተ ነው ተብሎ ለአንድ ጎሳ ሲሰጥ፣ ሌላውን በዚህ ቦታ አያገባህም፣ ይህ አካባቢ የኔ እንጂ የአንተ አይደለም ማለት ሲሆን፣ ህገ-መንግስታዊ የሆነ ፍፁም አግላይ የሆነ፡ አሰራር ነው። በየትም አለም ዜጎቹን እንዲህ የሚያገልና የሚከፋፍል ህግ የለም። ለምሳሌ በህንድ በማንነት ፖለቲካ አደረጃጅት አገር አፍራሽ መሆኑን የተረዳው የህንድ የመጨረሻዉ ፍርድ ቤት፣ የማንነት ፖለቲካ እንቅስቃሴ ህገ ወጥ እንደሆነ በይኗል፣ አግዷል።የጎሳ አከላለል፣ የኢትዮጵያ ህዝብ የዉጭ ጠላት ቢመጣበት እንኳ ተግባብቶና ተባብሮ አገሩን መከላከል እንዳይችልና፣ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የተሸረበ ስልታዊ (strategic) ደባ ነው።

የቡድን ጥያቄ የዜጋን መብት በማክበር ይፈታል። የጎሳ ፖለቲካ፣ ግለሰቦች የሃሳብ የበላይነት ማግኘት ሲያቅታቸው፣ ወደ ስልጣን ለመዉጣት የሚጠቀሙበት አቋራጭ መንገድ ነው። የግለሰብ መሰርታዊ መብቱ ከተከበረ፣ ያማይከበር የቡድን መብት የለም። በየትኛዉም የአገሪቱ ክፍሎች፣ በክልል ወይም ጎሳ ሳይወሰን፣ ዜጎች በአፍ መፍቻ በቋንቋቸው መማር፣ በቋንቋቸው መጠቀም፣ መዳኘት፣ የመስራት፣ ሃብት የማፍራት፣ መሪያቸዉን የመመረጥ፣ ሃሳብቸዉን የመግለጽና የመደራጀት መብታቸው ያለምንም ገደብ ሊከበርላቸው ይገባል። ይህን ለማደረግ የግድ የጎሳ አደረጃጀት ወይም ክልል አያስፈልግም። ለአንዱ መብት ለመታገል፣ የዚያ ሰዉ ጎሳ አባል መሆን አያስፈልግም፣ ዜጋ መሆን ብቻ ይበቃል። ጎንደር ዉስጥ ያለ አንድ ኦሮምኛ ተናገሪ፣ የምችለው ቋንቋ ኦሮምኛ ብቻ ነዉ፣ በኦሮምኛ ልዳኝ ይገባኛል ካለ፣ አስተርጓሚ ሊመደብለት ይገባል። ይህን ለማደረግ የግድ የጎሳ ክልል አያስፈልግም። ይህ በየትኛዉም የገራችን ክፍል የዜጎች ሁሉ መብት ሊሆን ይገባል።

በጎሳ ግጭት የማይነካና የማይጎዳ ክልል ወይንም የህበረተሰብ ክፍል አይኖርም። ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ ያየነው ይህን ነዉ። የጎሳ ፖለቲካ መሃንዲስ ነን የሚሉት ግለሰቦች፣ ሌላዉ መጤ፣ ሰፋሪ፣ ቤት የለሽ፣ ነዉ እናባርረዋለን፣ የሚሉት ሳይቀር ራሳቸዉ ባጠመዱት ወጥመድ እየገቡ ነው። ኦሮሞ ከሶማሊ፣ጉጂ ከጌዶ፣ ቤኒሻንጉ ከኦሮም፣ ኦሮሞ ከአማራ፣ ሲዳማ ከወላይታ፣ አማራ ከቅማንት፣ አማራ ከትግሬ፣ ብዙ ቦታ ማቆሚያው የማይታወቅ ግጭት ተነስቷል። ይህ ችግር ወደ እኔ አይመጣም ብሎ ተዝናንቶ የሚቀመጥ የህብረተሰብ ክፍል የለም። በዚህ ከቀጠለ የጊዜ ጉዳይ ሆኖ እንጂ ሁሉንም ያዳርሳል። ስለዚህ ይህ ሁኔታ አንዱ ወገን አባራሪ ሆኖ ሌላው ተባራሪ፣ አንዱ አገር ሲመሰርት ሌላዉ አገር የሚፈርስበት ከስተት አይደለም፣ የዕርስ በዕርስ መተላላቅ እንጅ። አንዱ ወገን ሲጠቃ ሌላዉም አልሞት ባይ ተጋዳይ ሆኖ ራሱን ያዘጋጃል፣ በምላሹም ጥፋት ያደርሳል። እየገደለ ይሞታል። በነሩዋንዳ፣ የመን፣ ሶሪያ የደረሰው እልቂት በኛ ላይ ካልደረሰ አንማርም ብሎ እልቂትን መጋበዝ ከድንቁርናም አልፎ ደደብነት ነው።

በጎሳ ስም ማጥፋት እንጂ ተጠያቂ ጎሳ አይኖርም። በጎሳ ፖለቲካ መሪወች በጎሳ ስም በግለሰብ ላይ ጥፋት ይፈጸማሉ እንጂ ተጠያቂ የሚሆን ወይንም ሃላፊነት የሚወስድ ጎሳ ወይም ቡድን ግን አይኖርም፣ ሊኖርም አይገባም። በህግ አግባብ በማይጠየቅ ቡድን ስም፣ ግለሰቦች ወንጀል የሚፈጽሙበት አሰራር ነዉ። ግለሰቦች በቡድን ስም ሃይል የሚያገኙበት ነገር ግን ጥፋቱን በህግ ወደማይጠየቅ ጎሳ የሚያላክኩበት፣ በወንጀላቸዉ ሲጠየቁም ጎሳችን ወደሚሉት ቡድን ሂደዉ የሚደበቁበት ሀገወጥነት ነዉ።

የጎሳ አከላለሉ፣ አሁን እንዳለ እንዲቀጥል ቢደረግ እንኳ፣ አገሪቱን ወደ ኢኮኖሚያዊ አዘቅጠት ከዚያም ወደ ማህበራዊ ቀውስ ይወስዳታል። በየትም አገር ለዕድገት አስፈላጊ የሆኑ መሰረታዊ ነገሮች አሉ። አንዱና የመጀመሪያው የህግ የበላይነት ነው። ሌላው የንብረት ባለቤትነት መብት ሲሆን፣ ስራን፣ ችሎታን፣ ፈጠራንና፣ ተወዳዳሪነትንና የሚያበረታታ ነጻ ገበያ ነው። ይህም የሰዉን ሃብት በነጻነት ማንቀሳቀስ ይጨምራል። እዲሁም እነዚህን በስርዓትና በህግ የሚያስከበር ህጋዊ ተቋማት ሊኖሩ ይገባል። ማንም አካባቢ ሆነ ግለሰብ በራሱ ብቻ ምሉዕ እይደለም። አንዳችን ለአንዳችን እናስፈልጋለን። ነገር ግን ማንም ቢሆን ያለውን ሀብትና ዕዉቀት አውጥቶ ወይንም ሙያውን ተጠቅሞና ተቀናጅቶ ለመሥራት የህይወትና የንብረት ዋስትና ያስፈልገዋል።

በአሁኑ የኢትዮጵያ ሁኔታ ሰዎች ካደጉበት አካባቢ በግፍ እየተባረሩ፣ ምን አይነት ሰዉ ነው ህይወቱን ለአደጋ እየሰጠ አገርን አልምቶ ራሱንም የሚጠቅመው? ከምንም በላይ ከግዚአብሄር ቀጥሎ ሃይል ያለውን የሰው አዕምሮ አልምቶና እንደተፈላጊነቱ አዘዋዉሮ መጠቅም ካልተቻለ፣ ከድህነት መዉጣት አይቻልም። አደጉ የሚባሉት የአለማችን አገሮች እዚህ የደረሱት በቆዳ ስፋታቸው አይደለም፣ በተፈጥሮ ሃብታቸዉም አይደለም፣ የሰው ሃብታቸዉን አልምተው አስተምረዉና ይበልጥ ምርታማና ዉጤታማ በሚሆነብት ቦታ አሰማርተዉ፣ ያለዉን የማምረትና የመፍጠር ችሎታ በመጠቀማቸዉ እንጂ። የምጣኔ ሃብት እድገት ምንጩ ከሰዉ ልጅ አዕምሮ ነው። ትርጉም ያለዉ የኢኮኖሚ ለውጥ ያመጣዉ ፈጠራ innovation ነዉ። ለዚህም አሜርካንን፣ ጀርመንን፣ ጃፓንንና ቻይናን የመሳሰሉትን አገሮች ማየት ይበቃል።

ዜጎች ለዓመታት ለፍተው ላባቸዉን አንጠፍጥፈው ያፈሩትን ንብረት በሚቀሙበት አገር፣ ንብረታቸው በጎሰኞች በሚቃጠልበት አገር፣ የውጭ አገር ባለሃብት ቀርቶ፣ ኢትዮጵያዊያን ያላቸውን ሀብት ያሸሹ እንደሁ እንጂ በልማት ላይ አያውሉትም። ምንም እንኳ እንድ አንዶች ቢኖሩም፣ ያገኙትን የተፈጥሮ ሃብት አራቁተውና በክለዉ፣ የኢትዮጵያን ባንኮች ዕዳ ላይ ጥለው፣ ዘርፈው ለመውጣት ካልሆነ፣ በአገሪቱ ሰላም ተማምነው ያላቸዉን ሃብት አፍስሠዉ ዘላቂ ልማት አያመጡም። ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሰዉን ልጅ ስራ እየተሻማ ባለበት ዘመን፣ በተራ ጉልበት ስራ ላይ በሚመሰረቱ የቻይና ፋብሪካዎችም ላይ መተማመንም አይቻልም። በቴክኖልጂ (robotics, 3D printing, artificial inteligence) ምርታማነታቸዉን ሲያሳድጉና በጥቂት ሰዎች ብቻ ማምረት ሲችሉ፣ ስራዉን ወደ አገራቸዉ ይመልሱታልና። በህዝብ ልማትና ምርታማነት ላይ ያልተመረኮዘ ዕድገት ዘላቂነት የለዉም፡፡ ወያኔ የፈጠረዉ የጎሳ ሥርዓት፣ ሰው በችሎታውና ዕውቀቱ ወይም የሥራ አፈፃፀሙ የሚለካበት ሳይሆን በጎሳ ፖለቲካ ታማኝነቱ ነዉ። ይህም ወጣቱን በአቋራጭ ሀገወጥ ሃብት ፈላጊ እንጂ የዕዉቀት ፍላጎት እንዳይኖረው አድርጓል፡፡

አንዲት አዋሳ ተወልዳ ያደገች ወጣት የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን አጠናቃ ሥራ እያፈለገች ያጋጠማትን የገለፀችው ልብ የሚነካ ነበር። አንድ አጎቷን ይህን ጠየቀቸው። አጎቴ፣ እኛ ምንድን ነን? አጎቷም ምን ማለትሽ ነው ይላታል፡ እሷም ዘራችን ምንድን ነው? አለች፣ አጎቷም በመገረም ዘሯ የተቀላቀለ መሆኑንና በቀላሉ ኢትዮጵያዊ መሆናቸዉን አብራራላት። እሷ ግን ሥራ ለማግኘት ዘር ይመረጣል። የተወለድኩት እዚህ፡ ነው። ነገር ግን አንቺ የዚህ ክልል ዘር አይደለሽም እያሉ ስራ ሊቀጥሩኝ አልቻሉም ብላ ወጣቷ በሃዘን ተናገረች። ከአገራችን በድህነት ወደኋላ ከመቅረት በተጨማሪ፡ ህውሃቶች ህዝቡን በጎሳ ከፋፍለው በፈጠሩት ስርዓት ሰው የሙያ ችሎተው ሳይሆን ዘሩ ታይቶ ሥራ የሚቀጠርበት አገር ሁኗል። በዚህ ሁኔታ ያደገ ወጣት ለአገሩ ምን አይነት በጎ አመለካከት ሊኖረዉ ይችላል?

አገራችን ያላትን የሰው ሃይል ማልማት እትችልም። ያላትንም የለማ ህዝብ በሚያስፈልግበት ቦታ መጠቀም አልቻለችም። ወደ 105 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ያላትና 80 በመቶ ወጣት በሆነበት አገር፣ ወጣቱን በሥራ ማሰማራት ዋነኛ ጉዳይ መሆን ሲገባው፣ በጎሳ ፖለቲካ ላይ በማተኮረ ሰውን ሠርቶ እንዳይበላ ማድረግ በወገን ላይ የሚፈፀም ወንጀል ነው። በአንድ አካባቢ ሰልጥነው የተቀመጡ ሥራ አጥ ወጣቶች ሲኖሩ በሌላ አካባቢ ደግሞ ህዝቡ ባለሙያ አጥቶ በችግር ይሰቃያል። ይህም የጎሳ ፖለቲካ ያመጠው ጣጣ ነው።አገራችን ካለባት አጠቃላይ ድህነት በከፋ የገጠሩ አካባቢ ከፍተኛ የተማረ የሰው ሃይል እጥረትና ችግር አለበት። በከተማዎች አካባቢ የተጠራቀመው የሰው ሃይል ራቅ ወዳለዉ የአገሪቱ ገጠር ክፍል ሄደ፡እንዳይሠራ፣ እንዳያለማ፣ የሰዉ ህይወት እንዳያድንና፣ አገሩንም እንዳያዉቅ፣ ይህ የጎሳ ክፍፍል መስናክል ሆኗል። በአገሪቱ ገበሬው ያመረተውን ምርት በማዕከላዊ ገበያ መሸጥ ባለመቻሉና የስርጭት ችግር በመኖሩ ነው በአገራችን የምግብ እህል እጥረት የሚፈጠረው ተብሎ፣ የገበያ ልውውጥ ማዕከል (የኢትዮጵያ ምርት ገበያ) ያቋቋመዉ መንግሥት፣ ለዕድገት ፍጹም አስፈላጊ የሆኑትን የተማሩ ወጣቶች ግን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሄደው መሥራት እንዳይችሉ አድርጓል።

የጎሳ ፖለቲካና ግጭትና ዘረኛ ቅስቀሳ በህዝብ መካከል የሚይረሳ የታሪክ ጠባሳ ጥሎ ያልፋል። ይህም ለወደፊት የአገሪቱን አንድነት አደጋ ላይ ይጥላል። የዘሬ ጥፋት የነገ ታሪካዊ ችግር ይሆናል።

ዘመኑ ከአንድ ክፍለ ዓለም ሌላው ክፍለ ዓለም መረጃ በቅፅበት የሚደርሰበት፣ የአገር ድንበሮች የሰውን እንቅስቃሴ የማይገድቡበት ዘመን ነው። የተፈጥሮ ሃብትም ቢሆን የልዩነትና የግጭት ምንጭ መሆን የለበትም። እያንዳንዱ አካባቢ የራሱ የሆነ የተፈጥሮ ሃብት አለው። አንዱ ነዳጅ፡ ሲኖረው ሌላው እብነበረድ ሊኖረው ይችላል፣ አንዱ ደግሞ ለም የእርሻ መሬት ሊኖረው ይችላል፤ ሌላዉ ሲሚንቶን ማምረት የሚያስችል ሃብት ሲኖረዉ፣ ሌላዉ የዉሃ ሃብት ይኖረዋል። ስለዚህ ሁሉም ዋጋ አለው ሁሉም ለአገራችንና ለህዝባችን ያስፈልጋል። ዘመኑ በጎሳ ታጥሮ የምንኖርበት አይደለም። የሚያዋጣዉና ሃይል የሚኖረን የጎሳን አጥር አስወግደን ስንተባበርና ሁላችንም በችሎታችን ስናበረክት ነው።

ኢትዮጵያ የጎሳ መብት የግለሰብን ወይንም የዜጋን መብት ያጠፋባት አገር ሆናልች። ኢትዮጵያ ዜጋ የሌላት የጎስ ስብስብ ተደርጋለች። ስለዚህ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግስት ተቀዳሚ ስራዉ ይህን የጎሳ አደረጃጀትና ፖለቲካ ማስወገድና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያለአድሎ የሚይስተናግድ የዜግነት ፖለቲካን ማስፈን ነው።

ይህንም ማድረግ ይቻል ዘንድ ኢትዮጵያዊያን ረጋ ብለንና ምክንያታዊ፣ ገንቢና ሰላማዊ ወይይት በማድረግ፣ ችግሩን ከስር መሰረቱ በመመርመር፣ ካለፈዉ ስህተት በመማር፣ የወደፊት አቅጣጫችንን ራሳችን መንደፍ አለብን። ሃላፊነቱን ለተወሰኑ የጎሳ መሪወች መተዉ የለብንም። ሁላችንም እኩል ሃላፊነት አለብን። የኢትዮጵያ ምሁራን ፈረንጆች ከጻፉት የመማሪያ መጽሃፍ ዕዉቀት (textbook knowledge) በዘለለ፣ የአብዛኛዉን የአገራችንን ህዝብ ኑሮና ችግር ከተለያየ ዘርፍ ቀርቦ በማጥናት ለአገራችን ሁኔታ የሚስማማ አገር በቀል የመፍትሄ ሃሳብ ሊያቀርቡ ይገባል። የኢትዮጵያ ህግ አዉጭወች፣ አገሪቱን ወደዚህ ደረጃ ያደረሱትን ከፋፍይና አግላይ ህጎች በማስወገድ፣ ሁሉም ዜጋ በእኩልነት የትም የአገሪቱ ክፍል በነጻነት የሚኖርበት ስርነቀል ህግ ሊያወጡ ይገባል። እንዲዚሁም የኢትዮጵያ ጦር ሃይል፣ የአገሪቱን ዳር ድንበርና የአገር አንድነትና የአገር ዉስጥ ሰላም ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን አዉቆ፣ የተጣለበት ሃላፊነት በንቃት ሊወጣ ይገባል። የኢትዮጵያ የፖለቲካ መሪወችና ባለድርሻወች፣ የአገሪቱን ስልታዊ (strategic) ጥቅም፣ ለጊዚያዊና የአጭር ጊዜ የፖለቲካ ድል መስዋዕት ሳያደርጉ፣ ለዘላቂ ሰላምና ዕድገት መሰረት በሆነው የዜግነት መብትና ፖለቲካ ላይ ሊያተኩሩ ይገባል።
__
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም።
ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

1 COMMENT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here