spot_img
Tuesday, June 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትየሀገራችን ሽግግር ውጣ ውረዶችና ጊዜን መሻገር የሚገባው የፖለቲካ ቅኝት (አክሊሉ ወንድአፈረው)

የሀገራችን ሽግግር ውጣ ውረዶችና ጊዜን መሻገር የሚገባው የፖለቲካ ቅኝት (አክሊሉ ወንድአፈረው)

አክሊሉ ወንድአፈረው
ethioandenet@bell.net
ታህሳስ 26፣ 2011 (ጃንዋሪ 4፣ 2019)

ባለፉት ስምንት ወራት ውስጥ የሕዝባችን መራራ ትግል በተገኘው የለውጥ ጅማሮ ፀረ-ዴሞክራሲ፣ አፋኝና ከፋፋይ የነበረውን ህወሓት-መራሹን አገዛዝ በማፈራረስ አዲስ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማዋለድ ከፍተኛ ትንቅንቅ የሚታይበት ወቅት ሆኗል።

ይህ ጽሁፍ በለውጥ ሂደቱ የሚታዩትን ሁለት ገጽታዎች ማለትም፣ በአንድ በኩል የማፍረስ በሌላ በኩል ደግሞ የመገንባት ሂደቶችን ይዳስሳል። ጽሁፉ የማፍረስና የመገንባት ሂደቶችን ሲል የሥርዓቱን ብቻ ሳይሆን የተቃዋሚውንም ጎራ አጋዥነት ወይም አደናቀቃፊነት የሚመረምር ነው።

የሽግግር ሂደቱ በአጭር ጊዜ ውጤታማ እንዲሆን ከትላንቱ አስተሳሰብና አካሄድ መላቀቅ አልፎም ጊዜ ተሻጋሪ የሆነ የፖለቲካ መስመርና ራዕይን ማራመድ የሚገባው በሁሉም በኩል በተሰለፉው የፖለቲካ (ገዥው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚ/ተፎካካሪ) ድርጅቶች ጭምር ነው።

ጊዜና ሁኔታ ሲቀየር፣ ጊዜ ያለፈበት አመለካከትና የይገባኛል አጀንዳን አንግቦ መጓዝ አላስፈላጊ በሆነ ቦታ ጉልበት፣ ሀብትና ንብረት እንዲባክን ያደርጋል፣ ለዴሞክራሲያዊ ሽግግርም እውን መሆንም ታላቅ እንቅፋትን ይደቅናል።

ከለውጡ ጋር እኩል መራመድ ያቃተው “መሪ ፓርቲ” (ህወሓት) የጋረጣቸው አደጋዎች

በሀገራችን ውስጥ ለሚካሄድው የለውጥ ሂደት ትልቅ እንቅፋት ሆኖ የሚገኘው ለ28 ዓመታት ብቸኛው አውራ ፓርቲ ነኝ እያለ ራሱን ሲያታልል የኖረውና አሁንም ሕዝብ የሚፈልገውን ለውጥ በግድም በውድም ለመቀልበስ ተግቶ እየሠራ የሚገኘው ህወሓትና በእርሱ የፖለቲካ ምህዋር ዙሪያ የሚገኙ ግለሰቦች በዋናነት የሚታዩ ናቸው።

ህወሓት በዶ/ር አብይ ወደ ሥልጣን መምጣት የተከሰተውን ለውጥ ከመጀመሪያ ጀምሮ ሲቃወም እንደነበር ይታወሳል። የፖለቲካ እስረኞችን ሙሉ በሙሉ መፈታት፣ በሀገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ እንቅቀስቃሴ ታግደው የነበሩ ድርጅቶች እንዲመለሱ መደረጉን…ወዘተ እንደሚቃወም በግልጽ የአቋም መግለጫዎች በማውጣትና በተለያየ ደረጃ በሚገኙ ባለሥልጣናቱ (ዶ/ር ደብረጽዮን፣ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ አቶ አባይ ጸሀየ፣ አቦይ ስብሀት…ወዘተ) ተደጋግሞ ተናግሯል።

የለውጥ እንቅስቃሴውን ለማገት ያደረጋቸው ተደጋጋሚ ሙከራዎች አልሳካ ሲሉት ህወሓት ወደ ትግራይ አፈግፍጎ የሚካሄደው ለውጥ የትግራይን ሕዝብ ለመጉዳት፣ ለማዋረድና ለማጥቃት እንደተደረገ ሤራ አስመስሎ በማቅረብ የትግራይን ሕዝብ ጥላ መከታ በማድረግ የለውጡን ሂደት ለማደናቀፍ፣ ከተጠያቂነትም ለማምለጥ ሙከራውን እንደቀጠለ ነው።
ህወሓት በአሳሳች ፕሮፓጋንዳ የሕዝብን ትኩረት መቀየር ይቻላል በሚል እሳቤ ስሜትን የሚኮረኩሩና በዚህ የለውጥ ሂደት አልፎ አልፎ የተከሰቱ ስህተቶችን በማራገብ፣ የትግራይን ሕዝብ በብሄረተኛ ስሜት በማነሳሳት አሁንም ለውጡን ለማደናቀፍ ይፋ የሆነ ቅስቀሳ ሲያካሂድ ይታያል።

የህወሓት ለውጥ አደናቃፊነት በክልሉ ብቻ የተገታ አይደለም። በተለያዩ ክልሎች ቀደም ሲል የነበረውን ሀገራዊና መንግሥታዊ መዋቅርን በመጠቀም ግጭቶችን ይተንኩሳል፣ አስፈላጊ ሲሆንም ያቀጣጥላል፣ ያባብሳል። ከነዚህም ውስጥ በቤነሻንጉል፣ በሱማሌና በኦሮሚያ፣ በቅማንትና አማራ መካከል የታዩ ግጭቶች ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው።

ይህ የህወሓት የአደናቃፊነት ተግባር በቅርበት ሲታይ እየተጠናከረ ሳይሆን እየተዳከመ የሚሄድባቸው ሁኔታዎች እጅግ ሰፊ ናቸው። ሁኔታው በጥንቃቄ ከተያዘም ሤራው ሁሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊከሽፍ የሚችልበት ምክንያትና መንገድ እጅግ ሰፊ ነው። ከነዚህም ውስጥ የሚከተሉትን መሠረታዊ ጉዳዮች ማየት ይቻላል።

በትግራይ ሕዝብ የነፃነት ፍላጎትና በህወሓት መጠነ-ሰፊ የጭካኔ አገዛዝ መሀል ያለ ቅራኔ

ለሃያ ስምንት ዓመታት እንደ ሰሜን ኮርያና የቀድሞዋ አልባንያ የትግራይ ሕዝብ በአንድ ፓርቲ ብቻ ነው የሚገዛው። በየጊዜው “ምርጫ” እየተባለ በተካሄደው ቀልድ ድምጹን ሰጠ አልሰጠ ዋጋ አልነበረውም። በትግራይ ምድር “መሪ ድርጅቱ” ህወሓት ነው፣ መወዳደርም፣ መግዛትም የሚፈቀድለት፣ የፖለቲካ አማራጭ አጀንዳም መቅረብ የሚቻለውም በዚሁ ድርጅት ብቻ ነው። ህወሓት ራሱን እንደ አንድ አማራጭ ሳይሆን ከትግራይ ህዝብ ጋር አንድ እንደሆነ አካል፣ እንደ ብቸኛ አማራጭ በማቅረብ “የትግራይ ሕዝብና ህወሓት አንድ ናቸው” በሚል ትርክት ሕዝቡን ሌላ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚያዊና የማኅበራዊ ፖሊሲዎች አማራጭ እንዳይቀርብለት አፍኖት ኖሯል።

ይህንን የአምባገነን ተግባሩን የተቃወሙት ሁሉ (አቶ ገብሩ አስራት፣ ወ/ሮ አረጋሽ፣ አቶ ሰየና ቤተሰቡ፣ አብርሃ ደስታ፣ አቶ አስገደ፣ አቶ ተወልደ…ወዘተ)፣ ከሥራ እንዲባረሩ፣ እንዲሰቃዩና እንዲዋረዱ፣ በህመምና በረሀብ እንዲቀጡ ተደርጓል። ከህወሓት በተፃራሪ የቆሙ ድርጅቶችንም በፍጹም ሥር እንዳይሰዱ አባሎቻቸውን በማሠር፣ በማሳደድ በመግደል…ወዘተ ለማዳከም ጥሯል።

በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች በተቃዋሚነት ተጠርጥረው መዳረሻቸው ጠፍቷል፣ ዜሮ ስድስት በሚሏቸው አሰቃቂ እስር ቤቶች ተሰቃይተዋል። ሰዎች በቁም ተቀብረዋል፣ ተደብድበው አካለ ስንኩል ሆነዋል።

ይህን ጭካኔ በትግራይ ውስጥ በሰፊው የሚታወቅ፣ ግን በአደባባይ ገና በበቂና በሰፊው ያልተነገረ ድርጊት ነው። ይህን ግፍ የሚረሳ የትግራይ ተወላጅ ይሁንም አይሁንም አይገኝም። ስለዚህም ይዋል ይደር እንጂ የዚህ ግፍ ሰለባ የሆነው ሕዝብ በተለይ የትግራይ ተወላጅ በህወሓት ላይ እንደሚነሳበት በእርግጠኛነት መናገር ይቻላል። በትግራይ ውስጥ በህወሓት ላይ የሚነሳው ተቃውሞ እየጠነከረ ሲሄድም ደግሞ የለውጥ አደናቃፊነት ብቃቱ እየደከመ ይሄዳል።

በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች ዴሞክራሲና ፍትህ ሲከበር በትግራይ ፀረ-ዴሞክራሲ አገዛዝ ሊቆም የሚችልበት መሠረትም ይናዳል።

ህወሓት ለ28 ዓመታት በሥልጣን ላይ የቆየው ዴሞክራሲን አፍኖና የጭቆና አገዛዙን በመላ ሀገሪቱ አስፍኖ ነው።

ባለፉት ስምንት ወራት ግን በሀገር አቀፍ ደረጃ ህወሓት ሥልጣኑን አጥቶ በጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ የሚመራ መንግሥት ሃላፊነቱን ተረክቧል። በዚህ አኳያም ከትግራይ ውጭ ባሉት የሀገራችን ክፍሎች እጅግ ፈጣን የዴሞክራሲ መሠረት እየተጣለ ሕዝቡም መሠረታዊ መብቱን ያለፍራቻና ያለጭንቅ ተግባረዊ ለማድረግ እየጣረ ይገኛል። ህወሓት በሚቆጣጠረው የትግራይ ክልል ግን ካስመሳይ ፕሮፓጋንዳ የዘለለ ለውጥ አልታየበትም።

ላለፉት 28 ዓመታት እንደታየው ህወሓት በትግራይም ይሁን በመላ ኢትዮጵያ ለሚከሰቱ ችግሮች ዋነኛ ምንጭ የድርጅቱ ፖሊሲዎችና ፖሊሲዎቹን ለመተግበር የሚወስዳቸው እርምጃዎች መሆናቸውን ባለመቀበል ከውጭ የሚሰነዘር “ሤራ” አድርጎ ስለሚመለከት ራሱን ለማደስና ሕዝብ በሚፈልገው ቁመና መጠን ለመዘመን አልቻለም።

በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ዴሞክራሲ ሥር እየሰደደና የሕዝብ ነፃነትም እየጎለበተ ሲሄድ በትግራይ ውስጥ ሥልጣኑንም ሀብቱንም አንቆ የያዘው ህወሓት ጥንካሬውን ጠብቆ መቀጠል አይችልም። ሕዝብም ከክልሉ ወጣ ሲል የሚያጣጥመውን መብቱን ትግራይ ክልል ሲደርስ መከልከሉን እሺ ብሎ ወይም በፍርሃት ታሥሮ የሚቀጥልበት ሁኔታ እየመነመነ ነው የሚመጣው። የሰብዓዊና ዴሞካራሲያዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ መከበር የሁሉም ኢትዮጵአዊ መብት ስለሆነም ህወሓት የትግራይን ሕዝብ እየረገጠ መቀጠሉንም ማዕከላዊው መንግሥትም አይፈቅድም። እነዚህ ሁሉ ጫናዎች የህወሓትን የአምባገነን ጎራ መፍረክረክ ያፋጥነዋል። በቀጣይነት የለውጥ እንቅፋት የመሆን አቅሙንም ይበልጥ ያዳክመዋል።

ህወሓት በጥቅማ-ጥቅም የተነሳ ተከታዮችን በዙሪያው ለመሰብሰብ የሚያሰችለው አቅም እየደከመ መምጣት

ሦስተኛውና ሌላው ትልቅ ጉዳይ ላለፉት 28 ዓመታት ህወሓት በዙሪያው ግለሰቦችንም ሆነ ስብስቦችን በአብዛኛው ማሰባሰብ የቻለው በሹመት፣ በገንዘብና የተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎችን ለደጋፊዎቹ ማስገኘት የሚያሰችለው ቁመና ስለነበረው ነበር። ህወሓትን መቅረብ፣ ከህወሓት ጋር መወዳጀት የሚያስገኘው ልዩ ጥቅም ሰፊ ነበር። ቋሚ ሥራ፣ መጠነ-ሰፊ ሥልጣን፣ ለባለሥልጣኖችና ውሳኔ ሰጪ አካሎች ልዩ ቀረቤታ፣ ሰፊ ሀብትና ንብረት…ወዘተ ያስገኝ ነበር። ይህ ሁሉ ከሕግ ውጭና ሕዝብን በማሰቃየት ሲፈጸም የነበረ ተግባር እነሆ መጨረሻው ላይ ደርሷል።

በሚሰምጥ መርከብ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ሊያድናቸው የሚችል ኃይል አጠገባቸው እንዳለ ሲያውቁ ለመዳን ይጥራሉ እንጂ ባሉበት ሆነው አብረው አይሰምጡም። አብሮ መስመጥ የሰውን ልጅ ምክንታዊነት (rational and logical decision making) አስተሳሰብን (አመክኖያዊ ውሳኔ አሰጣጥን) ይጻረራል።

እርግጥ ነው ህወሓት አሁንም ሊያግደረድረው የሚያሰችለው የተወሰነ የገንዘብም ሆነ የሰው ኃይል እንዲሁም የፖለቲካ ግንኙነት አቅም ሊኖረው ይችላል። ሆኖም ግን አሁን ባለው ሁኔታ ህወሓትን መወዳጀት የሚያጓጓ አይደለም። እንዲያውም ከህወሓት ጋር መቧደን (መቀራረብ) በየዕለቱ አክሳሪ (Liability) እየሆነ ነው የመጣው። ይህ በመሆኑም የህወሓትን ጎራ የሚርቀው ሕዝብ እየበዛ በመሄዱ የህወሓት ወዳጆች ካምፕ እየተደረመሰ እንጂ እየተጠናከረ ሊሄድ አይችልም። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚገኝ ድርጅት ደግሞ በሕዝብ የተደገፈ ለውጥን የማደናቀፍ ችሎታው ከዕለት ወደ ዕለት እየኮሰመነ እንጂ እየጎለበተ አይሄድም።

ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም ምክንያቶች ከለውጡ ጋር እኩል መሄድ ያልቻለው “መሪ ፓርቲ” (ህወሓት) የጋረጣቸው አደጋዎች በሁለት መልክ ፍጻሜ ሊያገኙ ይችላሉ። ህወሓት ሃቁን ተረድቶ ከገባበት ቀውስ በመውጣት በሀገራችን ውስጥ የተጀመረው የዴሞክራሲው ለውጥን በሰላማዊ መንገድ በትግራይም ለማጠናከር ከለውጥ አራማጅ ኃይሎች ጋር ተባብሮ መሥራት አንደኛው ነው። ይህ ሂደት ለትግራይ ሕዝብም ይሁን ለመላው ኢትዮጵያ ታላቅ ጠቀሜታ ያለው ይሆናል። አላስፈላጊና አውዳሚ ግጭትን አስወግዶ የቂም በቀልን አዙሪት በመስበር የጭቆናን ቀንበር አሽቀንጥሮ በመጣል፣ ወንድማማችነት፣ እኩልነትና ፍትኅ የሰፈነባት የጋራ ሀገራችንን ለመገንባት ትልቅ ዕድል ይሰጠዋል።

ሌላው አማራጭ ህወሓት የእብደት እርምጃ ወስዶ ሀገራችንና ሕዝባችን በደም እንዲታጠቡ ማድረግ ከተሳካለትም ሀገር መበተን እስከሚደርስ ጠርዝ የሚወስድ እርምጃን መውሰድ ነው። አዎ፣ ዛሬ ባለው ሁኔታ የእብደቱ እርምጃና የሀገር መበተን አደጋ ዝቅተኛ ነው ሊባል ይቻላል። ሆኖም ህወሓት ቢያንስ ከላይ የተጠቀሰውን ሊሞክር እንደሚችል መገንዘብ ተገቢ ነው። ተግባረዊ ሆነም አልሆነም ሊፈጠር እንደሚችል አንድ እውነታ በመቃኘት “ቢሆንስ” በሚል እሳቤ መንግሥት ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ሌሎች ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ሁሉ፣ ምን መደረግ እንዳለበት መመካከር፣ በበቂ ጥናት ላይ የተመረኮዘ የአደጋ መቀነሻ (ማምከኛ) ዕቅድን የለውጡን ሂደት ሳያናጋ ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ተቃዋሚ/ተፎካካሪ ኃይሎች የጋረጧቸው አደጋዎች

በህወሓት በኩል የተጋረጡ አደጋዎች እንዳሉ ሁሉ በተቃዋሚ/ተፎካካሪ ድርጅቶች ጎራም የሚስተዋሉ እጅግ አሳሳቢ ችግሮች አሉ። እነዚህን ችግሮች በሦስት ዋና ዋና ሃሳቦች ዙሪያ አጠቃሎ መመልከት ይቻላል።

የለውጡ ዋና አንቀሳቃሽ “እኔ ነኝ” ከሚል አመለካከት የሚመነጭ ችግር

በሀገራችን ውስጥ ለ28 ዓመታት በሥልጣን መድረኩ በዋናነት የሚታወቀውን ህወሓትን በማስወገድና በምትኩም የለውጥ ኃይሉ ወደ ሥልጣን እንዲመጣ በተደረገው ትግል ውስጥ ማን ምን ሚና ነበረው? በሚለው ጉዳይ ዙሪያ የተለያዩ አመለካከቶች ሲሰነዘሩ ይታያል።

እነዚህ አመለካከቶችና ትንተናዎች ካጠቃላይ አመለካከት አልፈው ወደ ትርክትነትና “እውነታው ይኸ ነው” ብሎ ለማሰጨበጥ ወደሚደረግ ጥረት ተሸጋግረው ይታያሉ። ይህ ክስተት በአብዛኛው በለውጥ አራማጆች (activists) የሚራመድ ሲሆን በአንዳንድ የፖለቲካ ድረጅቶችም በተደጋጋሚ ሲነገር ይሰማል።

ይህ ትርክት በተራ ትንተና ብቻ የሚያቆም ወይም እንደ ታሪክ ሽሚያ ብቻ የሚታይ ሳይሆን እያንዳንዱ ድርጅትና የለውጥ አራማጆች (activists) ጡንቻውን የሚያሳይበት፣ አልፎ ተርፎም በሀገራችን ለውጥ ለእያንዳንዱ ድርጅት ወይም የለውጥ አራማጆች (activists) የሚኖረው ቦታ ምን መሆን እንዳለበት በድፍረት የሚነገርበት ተዋረድ (highrarchy) ያለው አቀራረብ ሆኖም ሲቀርብ ይታያል። ባለፉት ጥቂት ወራት “እኛ ባመጣነው ለውጥ”ና በከፈልነው መስዋዕትነት“…ወዘተ የሚሉ አመለካከቶችና የባለቤትነት ስሜት የተጠናወታቸው አባባሎች ተደጋግመው ሲሰነዘሩ ይሰማል።

ይህ ብቻ አይደለም፣ በአንዳንድ ክፍሎች የሚቀርበው ትርክት “መንግሥትን በማንኛውም ሰዓት ለመገልበጥ የሚያሰችል ብቃት እንዳላቸውና ካሁን በፊትም ይህን ያላደረጉት የተለያዩ ጉዳዮችን እሳቤ ውስጥ አስገብተው ( ለሕዝብ ብለው እንጂ) ቤተ መንግሥቱን ሳይቀር በ24 ሰዓት መቆጣጠር ይችሉ እንደነበር፣ አስፈላጊ ከሆነም የተወሰነውን የሀገር ክፍል መገንጠል ይችሉ እንደነበረ በልበ ሙሉነት ሲናገሩ ይደመጣል። ከዚህ አልፎም “ቲም ለማ” እየተባለ የሚጠራውን የለውጥ ኃይልም ቢሆን (እነዶ/ር አብይን፣ አቶ ለማን፣ አቶ ደመቀን አቶ ገዱን) እነርሱ ፈቅደውላቸው፣ በነርሱ ጥበብና ስሌት ወደፊት እንደመጡና ሥልጣን እንደያዙ አስመስለው ሲናገሩ ተደምጧል።

ከላይ የተጠቀሰው አመለካከት የተወሰነ እውነትንት ቢኖረውም እንደሚተረከው ዓይነት ንጉሥ የማንገሥና ሀገር የማፈራረስ ኃይል ግን እንኳንስ በአንድ የፖለቲካ ተሳታፊዎች ስብስብ (activists) ወይም በአንድ የፖለቲካ ድርጅት ይቅርና ከዚያ በላይ በሆኑ ኃይሎችም ቢሆን በብቸኝነት የተቀነባበረና የተመራ እንዳልነበረና የለውጡ ሂደቱም ሙሉ በሙሉ በሂሳብ ስሌት መሰል ቀመር የተከሰተ ሂደት እንዳልነበረ ማሳየት ይቻላል።

አዎ፣ ያለፉት ሦስት ዓመታት ፀረ-ህወሓት/ኢህአዴግ ትግሉ እጅግ ተፋፍሞ በቀጣይነት ሲካሄድ ብዙ የኅብረተሰብ ክፍሎችም (በተለይም ወጣቱ) የተሳተፉበት ነበር። ይህ ወቅት የለውጡ ሚዛን ወደ ተቃዋሚው ክፍል ያጋደለበትና በቀጣይም የተቃውሞው ጎራ የበላይነቱን ይዞ የቀጠለበት ነበር። ይህ ትግልና ግፊት በተለይም በኦሮሚያ፣ በአማራና በተለያዩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክፍሎች (ኮንሶ፣ አርባምንጭ…ወዘተ) እጅግ ተጠናክሮ አገዛዙን ያሰጨነቀ ትግል የታየበት እንደነበረ ይታወቃል። በዚህ ሂደት ውስጥ ካጠቃላዩ ህዝብ ጋር የተለያዩ የለውጥ አራማጆችም (activists) ሆኑ ድርጅቶች የተጫወቱትን ታላቅ ሚና በመቀበል እያንዳንዱ ታጋይ ማህበረሰብ፣ ግለሰብም ሆነ ድርጅት ላደረጉት ትግል ክብርን መስጠት አድናቆትን ማሳየት ተገቢ ነው።

ውሃ የሚፈላው በ100 ዲግሪ ሙቀት ላይ ሲደርስ ነው ሲባል፣ ድንገት ከዜሮ ተስፈንጦሮ 100 ዲግሪ ይደርሳል ማለት አይደለም። አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት… እያለ ሙቀቱ እየጨመረ መፍለቅለቁና መትነኑ የሚታየው 100 ዲግሪ ሲደርስ ነው። 20 ዲግሪ ካልደረሰ መፍላት አይችልም፣ 60 ዲግሪ ካልደረሰ ወደ መቶ ዲግሪ ሊሽጋገር አይችልም። የለውጥ ሂደትም እንደዚሁ ነው።

ቀደም ያሉ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ሳይኖሩ የመጨረሻው ዓመታት ትግል ብቻውን ለውጡን ሊያስከትል ባልቻለ ነበር። ከስምንት ወር ፊት በተከሰተው ለውጥ ዋዜማ ከፍተኛ ድምፅ ያሰሙ አንዳንድ ግለሰቦችና ድርጀቶች እንዲሁም የህወሓትን አገዛዝ ተቀባይነት ሙሉ ለሙሉ ራቁቱን ያስቀረውና ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ባህሪውንም በማያጠራጥር ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ ያሳየው የ1997 የሕዝብ አመፅ ወቅት የነበራቸው ቦታ የጎላ እንዳልነበረና፡ አንዳንድ ድርጅቶች ደግሞ ያን የሕዝብ መነሳሳት ተቀባይነት እንዳያገኝ በይፋ ቅስቀሳ ማድረጋቸው የማይረሳ የታሪካችን አካል ነው። ከምርጫ 97 በፊት የነበረውን ጊዜ ስንመለከት ደግሞ ከመጀመሪያው ጀምሮ የህወሀትን አፍራሽና ከፋፋይ አካሄድ ተረድተው እነማን ህይወታቸውን ገብረው የህዝብን ትግል እንዳቀጣጠሉ እነማን ደግሞ ከስርአቱ ጋር አብረው ተሰልፈው እንደነበር ታሪክ መዝግቦታል። ይህ ሁሉ የሚያሳየው በትግሉ ውስጥ በተለያየ ጊዜ የየራሳቸውን ገንቢም አፍራሽም ፣ ታላቅም መጠነኛም ሚና የተጫወቱ ግለሰቦችም ድርጅቶችም ሲቀያየሩ እንደነበር ነው።

ለዚህ ነው የህወሓት የበላይነት የተወገደው ሕዝባችን ለ27 ዓመታት በተለያየ መልክ ታላቅ መስዋዕትነትን በመክፈል ባደረገው ትግል እንጂ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ብቻ በተካሄደ ትግል አይዶለም የሚባለው።

ያለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ትግል ደግሞ ባብዛኛው ወጣቱን ማእከል ያደረገ እጅግ ሰፊ የኅብረተሰቡ ክፍል፣ ሙስሊሙም ክርስቲያኑም፣ ፣ ከሰላማዊ ትግል እስከ መሣሪያ ያነሱ ወገኖች፣ ከከተሜው እስከ ገጠር ነዋሪው፣ በእርሻ ከሚተዳደረው እስከ አርብቶ አደሩ፣ ፊት ለፊት ከተጋፈጠው ውስጥ ውስጡን ተቃዋሚውን መረጃ በማቀበል…ወዘተ ሲያግዝ እስከነበረው፣ በሀገር ውስጥ በይፋ ይንቀሳቀሱ ከነበሩት በህቡዕ ይታገሉ እስከነበሩትና በውጪው ዓለም የተለያየ ተጽዕኖ ለማድረስ የተንቀሳቀሱ ኃይሎች፣ የተደራጁ ወይም በግል ይንቀሳቀሱ የነበሩ፣ ምሁራን፣ ደራሲያን፣ የኪነት ሰዎች፣ የመገናኛ ብዙሃን አዘጋጆች…ወዘተ ትግል ድምር ውጤት መሆኑን መገንዘብ ፣ተገቢ ነው።

የመጨረሻዋን ሚዛን ደፊ (tipping point) ሁኔታ ለማምጣት ቀደም ሲል የተደረጉ ትግሎች ሁሉ የነበራቸውን አስተዋጽዖ መገንዘብ አስፈላጊ ነው። ይህ ሲሆን እኔ ያመጣሁት ለውጥ ከሚለው አስተሳሰብ በመውጣት የብዙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የብዙ ዓመታት ተከታታይ ትግል ድምር ያሰገኛው ለውጥ ነው ወደሚለው ሰፊ አመለካከት ያሸጋግራል።
የትግሉ ባለቤት ከሁሉም የሀገራችን ሕዝብ የተውጣጣ ለውጥ ፈላጊ ኃይል አድርገን ስንመለከት ደግሞ ተጠቃሚውም በእኩል ደረጃ ሁሉም ኢትዮጵያዊ መሆን እንደሚገባው እንቀበላለን። ከተወሰነ ማኅበረሰብ አልፈንም የሀገሪቱን ሕዝብ ያማከለና በእኩልነት የሚያሳትፍ አካሄድና የፖለቲካ ራዕይ ተግባራዊ ለማድረግም እንችላለን።

እያንዳንዱ ለውጥ አራማጅም (activists) ሆነ የፖለቲካ ድርጅት የአንበሳውን ድርሻ ከፍዬ እዚህ ያደረስኩኳችሁ በዋናነት እኔ ነኝ” በሚል አስተሳሰብ ከጀምረ፣ የሚያሳድርበት ስሜት “ዋነኛው የለውጥ ባለቤት እኔ ነኝ” የሚል ራሰን ከሌላው ከፍ አድርጎ የመመልከት ሲሆን የሚወስደውም እርምጃ ባብዛናው በወደፊቱ የሀገራችን አቅጣጫ ላይ እኔ የምለው (የኔ አመለካከት) ዋናውን ቦታ መያዝ ይገባዋል” ከሚል ቅኝት ጋር የተያያዘ ነው።

ይህ ትርክትና እሳቤ ዛሬ በአንዳንድ ተቃዋሚዎችና በለውጥ አራማጆች (activists) መሀል ትልቅ ቦታ ይዞ ይታያል። ይህም በመሆኑ እያንዳንዱ ድርጅትና ቡድን ለራሱ በሚሰጠው ግምት መሠረት ከሌላው የተለየ የይገባኛል ስሜቱ ጎልቶ እንዲታይ አድርጓል። አንዳንድ ጊዜም ሀገሪቱ የምትመራው በማን እንደሆነ ግራ እስከማጋባት የሚያደርስ ሁኔታ ራስን በሀገሪቱ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ሰጭ አድርጎ የማቅረብ ሁኔታ ይስተዋላል።

ይህ በይፋ ከሚታይባቸው ሁኔታወች ውስጥ አንዱ በተደጋጋሚ የሚነሳውን ” ጎላ ጎላ ያሉ ድርጅቶች” “ “ዋና ዋና አካላት ች” ተሰባስበው መንግስት ይመስርቱ የሚለው በተቃዋሚ/ በተፎካካሪ ድርጅቶች መሀል የደረጃ ክፍፍልን የሚያሳየው ሀሳብ ነው።

ህወሓት የደርግን ሥርዓት ለመደምሰስ እርሱና የትግራይ ሕዝብ ባደረጉት ትግል ብቻ የተፈጸመ ተግባር አድርጎ ሲተርክ እንደነበረው፣ ሁሉ ዛሬ ደግሞ በሌላ ትርክት ወጥመድ ውስጥ መውደቅ ተመሳሳይ አደጋን ይጋብዛል። ወደስልጣን የሚወስደው ጎዳና ጉልበትን መሰረት ያደረገ ነው የሚል መልእክት ያሰተላልፋል። ተፎካካሪዎች መተማመናቸው እንዲቀንስ፣ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችም ሙሉ በሙሉ ልብ ለልብ ተቀራርበው የጋራ አጀንዳ እንዳይቀርጹ መሰናክል ሆኗል።

ይህ ትርክት ከመጀመሪያውም በተፋለሰ አመክንዮ (logic) ላይ የተገነባ ብቻ ሳይሆን በኅብረተሰብ መሀል ደረጃን በማውጣት ሁሉም በጋራ የሚያሰተሳስረው ጉዳይ ላይ ከማተኮር ይልቅ የግል ቡድንን ታላቅነት በማጉላት ላይ እንዲያተኩር የሚያበረታታ ለቀጣይ አለመተማመንና ለግጭት መሠረት የሚጥልም ጭምር ሆኗል።

ብዙወች እንደሚስማሙት አምባገነኖችን የታገልነው ሌላ ንጉስ ለማንገስ፣ የተወሰኑ ምርጦች በህይወታችን ላይ ውሳኔ እንዲጡበት፣ ወይም ሌላ ሳይሆን ሁላችንንም በእኩልነት ሊያሳትፍ የሚችል ስርአትን ገና ከጅምሩ ጀምሮ በሁሉም ተሳትፎ ለመመስረትና ለመገንባት ነው።

ቀደምት ነገስታት “እኛ ለህዝባችን የሰጠነው ህገመንግስት ይሉ እንደነበረው” አሁንም “እኛ ያመጣንላችሁ ለውጥ” የሚለው ትርክት ህዝብን ከማግለል የተለየ ጠቀሜታ የለውም። ይህን አስቸጋሪ ሁኔታ ለማሻሻል ተቃዋሚውም ሆነ የለውጥ አራማጆች (activists) ይህ ትርክት ጊዜ ሳይወስድ እንዲስተካከል ማድረግ ይኖርባቸዋል።

ለተጨባጭ ሁኔታዎች የምንሰጠው ትርጓሜ የበላይነትን የሚያንጸባርቅ ከሆነ ስሜታችንም ሆነ ተግባራችን ከዚህ አይርቅም። ትርጓሜ አሰጣጣችን በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ሲሆን ግን ስለሁሉም ዜጎች የሚኖረን ስሜትም ሆነ በተግባር የምናሳየው እንቅስቃሴ ይህንኑ የሚያንጸባርቅ ይሆናል። አመለካከታችን (አስተሳሰባችን)፣ ስሜታችናና ተግባራችን እጅግ የተያያዙ ጉዳዮች ናቸውና።

የሽግግሩ መሪነት ለኔ ይገባኛል የሚለው አስተሳሰብ

ከላይ እንደተጠቀሰው “የለውጡ አንቀሳቃሽ፣ የለውጡ መሪና በሕዝብም ተቀባይነት ያለኝ እኔ ነኝ” የሚለው አስተሳሰብ የሚያሰከትለው፣ ለውጡን ያመጣሁትም ሆነ ተከታይም ልምዱም ያለኝ እኔ ስለሆንኩ የሽግግሩን ሂደት እኔ መምራት አለብኝ ወደሚል መደምደሚያ ለመሸጋገር የሚኖረው እጅግ አጭር ጉዞ ነው።

ይህ ሁኔታ በአሁኑ ሰዓት በተቃዋሚው ጎራ በተለይም በኦሮሚያ ክልል ጎልቶ ይታያል። ይህ ከሚገለጥባቸው ሁኔታዎች አንዱ በኦነግና በመንግሥት በኩል የኦነግን ተዋጊዎች ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጋር የማዋሀድን ጉዳይ በሚመለከት የሚታየው ውጥረት ነው።

ኦነግ በኦሮሞ ሕዝብ ውስጥ ያለኝ ድጋፍ ከፍተኛ ነው፣ ለውጡ እዚህ እንዲደርስ የተጫወትኩት ቀጥተኛም ሆን በለውጥ አራማጆች (activists) በኩል ያደረግኩት ቀጥተኛ ያልሆነ አስተዋጽዖ ትልቁን ድርሻ ይይዛል ብሎ እንደሚያምን ወደ ሀገር ከመግባቱም በፊትም ሆነ ከገባ በኋላ በሰጣቸው ቃለ ምልልሶችና መግለጫዎች ላይ ታይቷል። በተለይ በለውጥ አራማጆች (activists) በኩል የሚታየውን ለመገንዘብ ብዙ ርቀት መሄድ የሚጠይቅ አይደለም።

በአቶ ዳውድ ኢብሳ ተደጋግሞ ሲገለጽ እንደተሰማው፣ በጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ ዕዝ ሥር የሚገኘው ሠራዊት የአንድ ድርጅት ሠራዊት እንጂ የሀገሪቱ ሠራዊት ነው ብሎ ኦነግ አያምንም። ስለዚህም የኦነግ ሠራዊትም ሆነ የአሁኑ የሀገሪቱ ሠራዊት ወደ ኢትዮጵያ ሠራዊትነት እንዲለወጡ አጠቃላይ የሠራዊት አወቃቀር ለውጥ (reform) ሥራ መሠራት አለበት ይላል። ኦነግ የሠራዊት መቀላቀል ሲል ሙሉ በሙሉ የሀገሪቱን ሠራዊት በአዲስ መልክ ስለማዋቀር ተግባር እንጂ ተዋጊዎቹ ካለው ሠራዊት ጋር ስለሚቀላቀሉበት ሂደት ብቻ ማለቱ አይደለም።

ኦነግ ይህን ሲል የሀገሪቱን የመከላከያ ኃይል የዕዝ (ኮማንድ) አወቃቀር ኢህአዴግ ጋር በመደራደር ሊቀየር ወይም ሊስተካከል የሚቻልበትን ሁኔታ፣ እነማን ሠራዊቱን ይምሩት በሚለው ላይም ድርድር ማድረግን…ወዘተ ሁሉ ያጠቃለለ ተግባር ውስጥ መግባት አለብኝ ማለቱ ነው።

ኦነግ የራሱን ሠራዊት አሁን ወዳለው ቋሚ ሠራዊት የመጠቃለል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱን ሠራዊት አጠቃላይ ቁመና በተመለከተ ውሳኔ ለመስጠት ልዩ የይገባኛል ጥያቄ ማቅረቡና ይህንንም እውን ለማስደረግ እስከ መሣሪያ ግጭት መሄዱ ደግሞ በሀገራችን ፖለቲካ ውስጥ ይገባኛል የሚለውን ቦታ (ከሌሎች የኦሮሞም ይሁን ሀገራዊ ድርጅቶች ተነጥሎ) አመላካች ነው። ወይም ደግሞ የኔን ሀሳብ ለማሳክት እኔ ካልሆንኩ ሌሎች ያበላሹታል ወይም መስመር ያስቱታል በሚል እምነት መጉደል የተነሳ ሊሆን ይችላል”

ያም ሆነ ይህ፣ በአሁኑ ሰዓት እየተካሄደ ላለው ሀገራዊ ለውጥ ከታላላቅ ተግዳሮቶቹ አንዱ እንደሆነና በብዙ ሕዝብ ዘንድ አለመረጋጋትን እንዳስከተለ ከተለያዩ የሕዝብ አሰተያየቶች መገንዘብ ይቻላል። ይህ ደግሞ ከረዥም ጊዜ የመከፋፈል ሂደት በኋላ ወደ አንድ ጎራ መሰባሰብ በጀመረው የሕዝብ ትግል ላይ ታላቅ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል። የለውጡ ቀጥተኛ ተጠቃሚ መሆን የሚገባው ህዝብም መሰረታዊ ሰላሙም ሆነ ልማቱ እጅግ የሚጎዳበት ድባብ እንዲሰፍን ያደርጋል።

ለውጡን ለማደናቀፍ ሌት ተቀን የሚንቀሳቀሰው ህወሓትም ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ ቅራኔውን ለማስፋት ኦነግንና ሌሎች ለውጥ አደናቃፊ ኃይሎችን ለመቀስቀስ ሰፊ የፐሮፓጋንዳ ሥራ ሊሠራ እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ኦነግንና ኦሮሚኛ ተናጋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን በለውጥ ኃይሉ ላይ እንዲያምጹ ይፋ የማበረታታት ሥራ ሲከናወን ይታያል።
https://www.facebook.com/kalitipress/videos/1828785233899533/UzpfSTU5Nzc0MzU3NToxMDE1NjEyNjE2OTQ5MzU3Ng/

መጪውን ምርጫ ለማሸነፍ ከወዲሁ የሚደረግ ሩጫ ያሰከተለው ውጥረት

በአንድ በኩል ለውጥ ፈላጊው የነዶ/ር አብይ መንግሥት ከአሁን በኋላ በኢትዮጵያ ውስጥ ሥልጣን በሕዝብ ድምፅ እንጂ በማጭበርበር፣ ኮሮጆ በመገልበጥ…ወዘተ እንደማይገኝ ለማድረግ ጠንክረው እንደሚሠሩ ደጋግመው ተናግረዋል። በሌላ በኩል ደግሞ በስደት የቆዩም ሆኑ በህቡዕ ይንቀሳቀሱ የነበሩ ተቃዋሚ/ተፎካካሪ ድርጅቶች በይፋና በሕጋዊነት መሥራት መጀመር፣ እጅግ ያልተለመዱ ክስተቶችን እንድንመለከት አድርጎል።

ከነዚህ ክስተቶች መሀል ሰላምና መረጋጋትም ሆነ በወደፊቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ ታላቅ ተግዳሮትን ሊያሰከትሉ ከሚችሉት ውስጥ የሚከተሉትን እንመልከት።

ሀ) በተቃዋሚ ቀስቃሽነት ወይም አስተባባሪነት በቀጥታም ሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ ተጽዕኖ መንግሥታዊ፣ የቀበሌና የወረዳ አስተዳደር አካሎችን በማፍረስ (ከሥልጣን እንዲለቁ በማድረግ) በአካአቢው በሚንቀሳቀሱ የለውጥ አራማጆች (activists) ወይም ድርጅቶች በሾሟቸው አስተዳዳሪዎችን መተካት።

ይህ አካሄድ የለውጥ ሀይሉ የሚመራውን መንግስት መግዛት እንዳቃተውና ፍላጎቱንም ማስፈጸም እንደማይችል አድርጎ በህዝብ ስነ ልቦና ክብርን ከማሳጣት አልፎ በሀገራችን ውስጥ በሕግ ማስተዳደር ይበልጥ እንዲሸረሸርና፣ ጉልበት ያለው ሁሉ እንደፈለገ የሚፈነጭበት ሁኔታ እንዲፈጠር ይበልጥ የሚያበረታታ ነው። የዚህ ሁኔታ መስፋፋት መጠነ-ሰፊና ውስብስብ ምስቅልቅልን (በልማትም ሆነ በቀጣይ ሰላም አንጻር) ሊጋብዝ የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው።

ለ) ሌላው እጅግ አሳሳቢው ጉዳይ ደግሞ በተለያዩ ተቃዋሚዎች/ተፎካካሪወች “የኔ” በሚሏቸው አካባቢዎች ውስጥ ሌሎች ተፎካካሪ ድርጅቶች እንዳይንቀሳቀሱ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ ተጽዕኖ በማሳደር “አካባቢያቸውን” ከሌሎች አማራጭ አመለካከቶች “የፀዳ“ የማድረግ ተግባር ነው። ይህ ተግባር የተለያዩ ድርጅቶች በነፃ እንዳይንቀሳቀሱ ከማስፈራራት፣ የሌሎች ድርጅቶችት ደጋፊዎች ተብለው የተጠረጠሩትን ማገት፣ መደብደብ፣ ስብሰባ እንዳያካሂዱ በባለሥልጣናት በኩል በቀጥታ ማስከልከልን፣ የተተያዩ ድርጅቶችም ሆኑ ነጻ ጋዜጦች ባካባቢው እንዳይስራጩ ማድረግንና ሌሎችንም ያካትታል። እነዚህ ሁሉ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች (ለምሳሌ በአሰላ፣ በሻሰመኔ፣ በሰሜን ምዕራብ ጎጃም…ወዘተ) የተከሰቱ እውነታዎች ናቸው።

ተመሳሳይ ስልትን በመጠቀም፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ለራሱ ጥቅም አዋለ በማለት ተቃዋሚው ህወሓት/ኢህአዴግን ሲከስ እንዳልኖረ ሁሉ አሁን ገና ሥልጣን ሳይዝ የተፈጠሩ ክፍተቶችን በመጠቀም የዚህ ዓይነት ፀረ-ዴሞክራሲና ሥልጣንን በጉልበት የመያዝና አማራጭን የማፈን እርምጃ ማየት እጅግ የሚረብሽና አንዳንዱን ተቃዋሚ ለዴሞክራሲ ያለውን ታማኝነት ከወዲሁ በጥርጣሬ እንዲታይ የሚያደርግ ተግባር ነው።

ይህ ሁኔታ በሀገራችን ዴሞክራሲን ለመገንባት ትልቅ አደጋን የሚጋርጥ ሲሆን ከፍተኛ ግጭትን ሊጋብዝ፣ የሕዝብንም አንድነት ሊቦረቡር የሚችል አደጋ ነው።። ምርጫ እየተቃረበ ሲሄድ ይህ ተቃዋሚ-ሠራሽ አደጋ ማንም አሸናፊ የማይሆንበት የዘርፈ-ብዙ ችግሮች መሠረት ሊሆን እንደሚችል ቀድሞ መገንዘብ ተገቢ ነው። ይህን አደጋ ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ ወይም ለመቀነስ የመፍትሄው ቁልፍ በዋናነት በተቃዋሚው እጅ ይገኛል።

ለማጠቃለል

የሀገራችን የሽግግር ሂደት ከሁለት አቅጣጫዎች ታላላቅ ተግዳሮቶች ገጥመውታል። እንዚህን ተግዳሮቶች መሻገር ለምንፈልገው የእኩልነትና የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ሕገ-መንግሥታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት መሠረታዊ ጉዳይ ነው።

ሽግግሩ አንዱ የበላይ ሌላው የበታች፣ የተወሰነው ክፍል የበኩር ልጅ ሌላው የእንጀራ ልጅ ተደርጎ የሚታይበት ሥርዓት አክትሞ ሁሉም የኢትዮ.ጵያ ልጆች በእኩልነት የሚታዩበት፣ ያለአድልዖ የሚዳኙበት ሥርዓትን ለመፍጠር እንጂ ያለፈውን ለመድገም እንዳልሆነ ከግንዛቤያችን እንዳይርቅ ማድረግ አስፈላጊ ነው።

ይህ የሽግግር ሂደት የሚፈለገውን መሠረታዊ ውጤት እንዲያሰገኝ ሁሉም የተደራጀ ኃይሎች እና ዜጎች ሁሉ ታላቅ ኃላፊነት አለባቸው። በዚህ እንቅፋት በበዛበት የሽግግር ሂደት ውስጥ የአጭር ጊዜ ድልን ለመጨበጥ በማተኮር ተቃዋሚው በሚፈጥረው ተጨማሪ ማደናቀፊያ በሰላማዊ መንገድ የሥልጣን ሽግግር መደረግ የሚችልበትን መሠረታዊና ተቋማዊ ለውጥ እንዳያሰናክለው አርቆ ማሰብና በጥንቃቄ መራመድ ይገባዋል። ተቃዋሚው ራሱ በሚወሰደው አላስፈላጊ ትንኮሳና በሚቀሰቅሰው ግጭት የራሱ ትርክት ሰለባና አስረኛ እንዳይሆን አርቆ ማሰብ ይኖርበታል።

በትክክል መገንዘብ የሚገባው በሀገራችን የፖለቲካ ሽግግር ሂደት እያንዳንዱ ድርጅት ይገባኛል ብሎ የሚለውን ሳይሆን፣ ሁሉም ድርጅቶች (ገዥውን አካል ጨምሮ)ና ዜጎች መሠረታዊ መብታቸው ተከብሮ በሕግ ፊት እኩልነታቸው ተረጋግጦ ከማንም በላይም ሆነ በታች ሳይሆኑ የሚንቀሳቀሱበትን፣ በሕዝብ ነፃ ፍላጎትና ምርጫ ብቻ ወደ ሥልጣን የሚወጡበትና ከሥልጣንም የሚወርዱበትን ሥርዓት መመሥረትና መገንባት፣ ለሁሉም ዜጋ የግልም ሆነ የቡድን መብት ቋሚ የመብት መረጋገጫ ሊሆን እንደሚችል ነው። ከዚህ ውጭ በጉልበትም ሆነ በሌላ ተጽዕኖ የሚደረግ የግል ፍላጎትን የማስከበር ጥረት ዘላቂነት እንደማይኖረው በህወሓት አዛዥነትና በጥቂት ምርጦች አጃቢነት ተደርጎ ከነበረው የከሸፈ “ሽግግር” መማር ይቻላል።

የዘመናት ትግል ተካሂዶ የብዙ ሰማዕታት ደም ተገብሮበት፣ እዚህ የደረሰው ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እንዳይከሽፍና ወደ ግቡ እንዲደርስ ሁሉም ኃላፊነት የተሞላው ተግባር ማካሄድ ይጠበቅበታል። የለውጥ ኃይሉ ብቻውን ሽግግሩን ሊሸከም አይችልም፣ የተቃዋሚው ገንቢ ሚና ለዚህ ሂደት ውጤታማነት ወሳኝ ነው።

__
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም።
ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here