spot_img
Thursday, May 30, 2024
Homeነፃ አስተያየትየትግራይ ክልላዊ መንግስት መግለጫና አንድምታው። የሕወሃት የመጨረሻ እስትንፋስ፤ ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ፤ ...

የትግራይ ክልላዊ መንግስት መግለጫና አንድምታው። የሕወሃት የመጨረሻ እስትንፋስ፤ ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ፤ (ክፍል ሁለት)

ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ፤
ታህሳስ 27/2011 (01/05/2019)

“ሃሳዊ ከምሕሶቱ፤ ሰራቂ ከምስርቆቱ ይመስሎ” የትግርኛ ምሳሌ።

ሲተረጎም፡ “ውሸታም እንደ ውሸታምነቱ፤ ሌባም እንደ ሌብነቱ ይመስለዋል”

በክፍል አንድ ጽሁፌ ለማሳየት እንደሞከርኩት፤ የሕግ የበላይነትን ከማስከበር አንፃር፤ የሕወሃቱ መሪ እና የትግራይ ክለላዊ መንግስት አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት፤ ዶ/ር ደብረፅየን ገ/ሚካኤል በኅዳር 9 ቀን 2011 ዓ.ም (እኢአ) በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ‘የታገልነው እና መስዋዕትነት የከፈልነው ለሕግ የበላይነት መከበር ነው’ ማለታቸውን አዎንታዊ ገፁን ጠቁምያለሁ። ምንም እንኳን ዶ/ር ደብረጽየን፤ ሕወሃት እና የትግራይ ክልል መንግሥት ለሕግ የበላይነት ያለውን ቁርጠኝነት ቢነግሩንም፤ በዚህ ሽፋን ለማስተላለፍ የፈለጉት፤ የፌደራል መንግሥቱ፤ በትግራይ ሕዝብ ላይ የጥቃት ዘመቻ ጀምሯል የሚለውን መልዕክት መሆኑን ማንም አስተዋይ ሰው ይረዳዋል።

ዶ/ር ደብረጽዮን በመግለጫቸው፤ የጄነራል ክንፈ ዳኘው መታሰር ለምን ሰበር ዜና ሆነ ሲሉም በአግራሞት ጠይቀዋል። ሰበር ዜና የማይሆንበት ምክንያት ግን ግልጽ አይደለም፤። የእሳቸው “ህቡእ” መልእክት፤ የጄነራሉ መታሰር “ሰበር ዜና የሆነው” የትግራይ ሕዝብን ለማሸማቀቅ ነው የሚል አቧራ ለማስነሳት መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ምንም እንኳን ዛሬ መደበኛ እና ሰበር ዜናውን መለየት የማንችልበት ደረጃ ላይ ብንደርስም፤ የጄነራል ክንፈም ይሁን የማንም ከፍተኛ ባልስልጣን በወንጀል ተጠርጥሮ መታሰር ሰበር ዜና ነው። በዚህ በምንኖርበት ሃገር (አሜሪካን) የምክር ቤት አባላት፤ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት፤ ወይም የተለያዩ ትላልቅ ኩባንያዎች ባለሥልጣናት ሲታሰሩ በስበር ዜና ነው የምንሰማው። እኝህ፤ ከፍተኛ የሕዝብ ሃላፊነት ተጥሎባቸው የነበሩ እና፤ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን የነበሩ ጄነራል መታሰር፤ በሰበር ዜና መቅረቡ ስህተት ነው እንኳን ብለን ብንቀበል፤ የእሳቸው መታሰር “ከትግራይ ሕዝብ መሸማቀቅ” ጋር ምን አገናኘው? የትግራይ ሕዝብስ የሚሸማቀቅበት ምን ምክንያት አለው?

በጣም የሚያሳዝነው እና የሚያሳፍረው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፤ በሚሰጡት ትክክለኛ እና ሚዛናዊ አስተያየት የማከብራቸው፤ ጄነራል ፃድቃን ገብረትንሳኤ፤ በዚህ መቋጠርያ በሌለው “ጋሪ” ላይ መሳፈራቸው ነው። የእነ ጄነራል ፃድቃን፤ በዚህ ጎዶሎ ጋሪ ላይ መፈናጠጥ፤ አንዳንድ የትግራይ “ልሂቃን” የከፈቱት ይህ የሃሰት ዘመቻ፤ በመጠኑም ተቀባይነት እንዳገኘ ያሳያል። አብዛኛው የትግራይ ሕዝብ ግን በዚህ የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ይሸነፋል ማለት ስህተት ነው። የትግራይንም ሕዝብ አስተዋይነት ከግምት ውስጥ አለመክተት ነው። ይህንንም “የትግራይ ሕዝብ መግለጫውን በመደገፍ መሬት አንቀጥቅጥ ሰልፍ አደረገ” የሚለውን ዲስኩር ላጤነ ጤነኛ ሰው እና ሰልፉንም ለተመለከተ ግልጽ ይሆንለታል። በመጀመርያ፤ መግለጫው በትግራይ ሕዝብ ድጋፍ አገኘ የሚል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ፤ የትግራይ ሕዝብ በራሱ ፍላጎት እና አነሳሽነት፤ ያደረግው ምንም ዓይነት ሰላማዊ ሰልፍ የለም። በቅርቡ በትግራይ በተለያዩ አካባቢዎች እና በመቀሌ የተደረጉት ሰልፎች፤ በመንግስት እና በሕወሃት አቀነባብሪነት የተዘጋጀ ነው። ‘መግለጫውን ደግፈናል ብላችሁ’ “ሰላማዊ ስልፍ ውጡ ለመባሉ”፤ የትግራይ የኮምኒኬሽን ጽ/ቤት ለዜና ተቋማት ያሰራጨውን ደብዳቤ ማየት ብቻ ይበቃል። ሕዝቡ ይዞት የወጣው መፈክርም፤ በክልሉ መንግስት እና ሕወሃት ተጽፎ የተበተነ ነው። ትግራይ ውስጥ የተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ፤ በደርግ ጊዜ ሕዝቡን እያሰገደዱ ከሚደረግው ሰላማዊ ሰልፍ ፍጹም የተለየ አይደለም። ስለዚህ፤ ሰልፉም ሆነ መፈክሩም የመንግስት ነው። የትግራይ ሕዝብ፤ የክልሉ መንግስትም ሆነ ሕወሃት ለወሰደው አቋም ፈልጎ እና ወዶ ደገፈ ማለት አይቻልም። በትግራይ ሕዝብ ውስጥ ስጋት ለመፍጠር፤ የፈለገ ዓይነት ዲስኩር ትግራይ ውስጥ ቢለፈፍ፤ የትግራይ ነጋዴ፤ ዛሬም በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች፤ እየተዘዋወረ፤ ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር የሚያደርገው የንግድ ልውውጥ፤ የትግራይ ሕዝብ ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ ከፌደራል መንግስት የሚሰጋው ነገር እንደሌለ ጠቋሚ ነው።

እራሳቸውን የትግራይ ሕዝብ “አፈ ንጉሥ” አድርገው በሾሙ “አንዳንድ አክቲቪስቶች” ከአቻ ተጻራሪዎቻችው ጋር “ለመበሻሸቅ” እና፤ የህወሃት መራሹ መንግስት፤ በኦዴፓ መራሽ መንግስት በመተካቱ፤ “የበላይነታችንን አጣን” በሚል የስነልቦና ሽንፈታዊ ስሜት፤ አደገኛ መርዛቸውን እየረጩ ነው። እነዚህ አፈንጉሶች እና ከፍተኛ የሕወሃት ባለስልጣኖች፤ የፌደራል መንግሥት የትግራይን ሕዝብ ለማጥቃት ከውጭ ሃይል ጋር እየሰራ ነው ሲሉም ይከሳሉ። ይህ በዶ/ር ደብረጽየን በቀጥታ ኣይነገር እንጂ፤ ትግራይ በጠላት ተከባለች ዓይነት መልእክታቸው ከዚህ የተለየ አይደለም፤ ይህ መልእክታቸውም፤ በየማህበራዊ ድህረ ገፆች፤ እንደ ገደል ማሚቱ እያስተጋባ ነው። ይህንን በመንተራስም ይመስላል፤ ፕሮፌሰር እንድርያስ እሸቴ፤ስንትና ስንት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ተገቢ ጥያቄ ስላነሱ፤ እሳቸው ፕሬዝዳንት ሆነው ሲመሩት ከነበረው ተቋም ደጃፍ ሕይወታቸው “በፀጥታ ሃይሉ” ሲቀጠፍ ትንፍሽ ሳይሉ፤ አሁን ግን፤ በወንጀል ተጠርጣሪ የሆኑት የሕወሃት ባለስልጣኖች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ የአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ እጅ አለበት” ሲሉ መናገራቸው እጅግ አስቂኝ የሆነው። እንዲህ ዓይነት ውኃ የማይቋጥር መላምት፤ ከአቶ በረከት ስማዖንም፤ ከአቶ ስብሃት ነጋም መስማታችን ገራሚ አይደለም። ዛሬ አቶ ኢስያስ፤ እንኳን የኢትዮጵያ መንግስት ላይ፤ ገና በመንገዳገድ ባለችው ደቡብ ሱዳን ላይ እንኳን ተጸኖ ማድረግ አይችሉም። ይህ ሁሉ የሚራገበው አቧራ፤ አላማው አንድ እና አንድ ብቻ ነው። አንዳንድ የሕወሃት ባለሥልጣናት ላጠፉት ጥፋት እና ለፈፀሙት ግፍ ተጠያቂ እንዳይሆኑ የማድረግ ዘመቻ ነው።

በአንድ ወቅት፤ አምባሳደር ሥዩም መስፍን፤ ትግራይ ውስጥ፤ በአንድ ስብሰባ ላይ ሲናገሩ፤ ሕዝቡን በጣም በድለነዋል፤ ወጣቱን የተሳሳተ አቅጣጫ እንዲይዝ አድርገነዋል፤ ሕዝቡን ተንበርክከን ይቅርታ መጠየቅ አለብን ሲሉ ተደምጠዋል። ዶ/ር ደብረጽየንም፣ ባለስልጣናቱ በሙስና እንደዘቀጡ፤ በሃገሪቱ መልካም አስተዳደር እንደሌለ በአደባባይ በተደጋጋሚ ተናግረዋል። በደል ከተፈፀመ፤ በደል ፈፃሚ አለ ማለት ነው፤ ታድያ ይህ በደል ፈፃሚ አካል መጠየቅ የለበትም ማለት ነው? በደል ፈፃሚንስ መጠየቅ፤ ከትግሬነቱ፤ ከኦሮሞነቱ፤ ከአማራነቱ ጋር ምን አገናኘው? ማንም ወንጀለኛ፤ ወንጀል ሲሰራ ብሔሩን ወክሎ ወንጀል አይሰራም፤ ታድያ ተጠርጣሪዎቹ እንዲጠየቁ ማድረግ፤ ከብሔር ጋር ምን አገናኘው? እንደ ጄነራል ክንፈ ዳኘውም ሆኑ እንደ አቶ ጌታቸው አሰፋ ያሉ ተጠርጣሪዎች፤ እንኳን አንድን ብሔር፤ ቤተሰባቸውን አይወክሉም፤ ለሚጠረጠሩበት ወንጀል ተጠያቂዎቹ እንሱ እንጂ ብሔራቸው አይደለም። እነዚህ ተጠርጣሪዎች ስለተጠየቁስ ለምንድነው የትግራይ ሕዝብ የሚሸማቀቀው? ይህን አቋም የያዙ ሰዎች በጭብጥ፤ የዚህን መላምት እውነተኛነት ያሳዩን። አለበለዚያ፤ ውሸት አራጋቢነታቸውን ያቁሙ፤ ለእነሱም ሆነ፤ ቆምንለታል ለሚሉትም ሕዝብ አይበጅም።

በትግርኛ “ውሸታም እንድውሸታምነቱ፤ ሌባም እንደሌብነቱ ይመስለዋል ይባላል። ምናልባት፤ እነ ዶ/ር ደብረጽዮን፤ የሚያሰሙት ስሞታ፤ ሁሉንም ነገር በዘር መነጽር ስለሚያዩ ይሆን? ሕወሃት በትግል ላይ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ፤ ከሻእብያና ከዚያድ ባሬ የወረሰው ነገር፤ “አማራ ተኮር” ዘመቻ ማድረግ ነበር። በ1983 ሥልጣን ከያዘም በኋላ፤ በተለያዩ የመንግስት ሚድያዎች፤ ያሰራጭ የነበረው ፕሮፖጋንዳ ፀረ አማራ ነበር። ሌሎች በአማራው ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ከፍተኛ ዘመቻ አድርጓል፤ በዚህም ብዙ አሰቃቂ ግፎችን አይተናል። ምናልባትም ሕወሃት፤ ሁሉም ነገር እንደራሱ አድርጎ ስለሚመለከት ይሆናል፤ ሁሉንም ነገር ብሔር ተኮር ለማድረግ የሚሞክረው። ምንም እንኳን፤ የሕወሃት ጋሻ ጃግሬዎች ፌደራል መንግስት የትግራይ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረ ዘመቻ ጀምሯል ቢሉም፤ አንድ ተጨባጭ መረጃ ሊያቀርቡ አይችሉም። ከመንግስት የዜና አውታሮች የምንሰማው አንድም የፀረ ትግራይ ሕዝብ ዘመቻ የለም። ጠቅላይ ሚኒስትሩም፤ ጥቂት የትግራይ ተወላጆች በወንጀል ስለተጠረጠሩ፤ የትግራይ ሕዝብ መወገዝ እንደሌለበት፤ ሕዝቡ ሊጠየቅም እንደማይገባ በተደጋግሚ ተናግረዋል። ባንድም ወቅት፤ ከፍተኛ የሆነ የመንግስት ባለሥልጣን፤ የትግራይ ሕዝብ ላይ ጣት ሲጠቁም አላየንም። አሁን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ፤ ሕወሃት፤ በአማራ እና በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ካደረገው ብሔር ተኮር ጥቃት ፍፁም የተለየ ነው።

በእርግጥ በአንዳንድ አካባቢዎች፤ አንዳንድ ጽንፈኛ የሆኑ ዜጎች፤ በግልም ሆነ በቡድን፤ የትግራይ ተወላጆች ላይ በተለያየ አካባቢ ጥቃት መፈፀማቸው ይነገራል። በአማራ ክልልም “እራሳቸውን የሾሙ ወጣቶች” እህል እና አስፈላጊ ነገሮች ወደ ትግራይ እንዳይገቡ መንገድ መዝጋታቸውን እና እቃ መዝረፋቸውንም፤ በተለያዩ ዜናዎች ሰምተናል። ይህ እኩይ ድርጊት በብዙዎቻችን ተወግዟል። የአማራ ክልላዊ መንግሥትም ሆነ ፌደራል መንግስቱ እርምጃ አለመወሰዱ፤ ሁለቱንም አካላት ሊያስወቅስ ይገባል። ነገር ግን እንዲህ ዓይነት ፀያፍ ተግባር ያይነው በአማራ እና ትግራይ ክልል አዋሳኝ አካባቢ ብቻ አይደለም። ሌሎች ብሔር ብሄረሰቦችም በተመሳሳይ ሁኔታ በኦሮምያ፤ በደቡብ፤ በሃረሬ፤ በአፋር፤ በሱማሌ እና በሌሎች ክልሎች ላይ አሁንም ጥቃት እየደረሰባቸው ነው። መንግስትም በበቂ ሁኔታ እርምጃ አለመውሰዱ በብዙ አካባቢዎች አቤቱታ ይሰማል፤ መንግሥትም እየተወቀሰ ነው። ይህ ማለት እነዚህ ድርጊቶች በመንግስት ይደገፋሉ ማለት አይደለም። በትግራይ ላይ ብቻ የተነጣጠረ አለመሆኑን እና፤ በዚህ በሽግግር ወቅት ሃገራችን ያጋጠማት ፈተና ለመሆኑ ግን አጠያያቂ አይደለም። እነዚህን ነገሮች ለመፍታት ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው። ከዚህም አልፎ፤ ሕወሃት የገዥው ፓርቲ አካል እንደመሆኑ መጠን የመፍትሔ ሃሳቦችን ማቅረብ እና፤ የችግሩ አካል ከመሆን ይልቅ የመፍትሔው አካል ቢሆን ይበጃል። ነገር ግን፤ በአማራ እና በትግራይ ክልል ወሰን ላይ፤ ስሜታዊ እና ጽንፈኛ በሆኑ ወጣቶች የሚሰራውን መጥፎ ሥራ፤ ከሚገባው በላይ ለጥጦ፤ የትግራይ ሕዝብ ላይ የተነጣጠረ ጥቃት አለ፤ ትግራይ በጠላት ተከባለች የሚል ታምቡር መምታት፤ ሃላፊነት የጎደለው ብቻ ሳይሆን፤ የለውጡን ሂደት የማደናቀፍ ሙከራም ነው።

ዶ/ር ደብረጽየን በመግለጫቸው ያነሱት አስገራሚ ነገር፤ ሁሉንም እሰረኛ በምህረት ፈተን ነው አዲሱ አስተዳደር ስራ የጀመረው፤ ስለዚህ፤ ተጠርጣሪዎቹ፤ ሰሩት የተባለው ወንጀል፤ ምህረት ከመደረጉ በፊት የሰሩት ወንጀል ከሆነ፤ እንደሌላው ምህረት ሊደረግላቸው ይገባል፤ ምህረት ከተደረገ በኋላ የሰሩት ወንጀል ካለ ግን ሊጠየቁ ይገባል፤ አለበለዚያ በምህረት የተፈቱት ሁሉ ተመልሰው መታሰር አለባቸው የሚል ነው።ፈረንጆቹ “False Equivalent” የሚሉት እንዲህ ዓይነቱን ነገር ነው። በመጀመርያ ሊሰመርበት የሚገባው ነገር፤ ቀደም ሲል “በምህርት ተፈቱ” የተባሉት እሰረኞች፤ የፖለቲካ እስረኞች ነበሩ። እነሱ ምህረት ሰጪ እንጂ ምህረት ተቀባይ መሆን አልነበረባቸውም። በሃሰት የተከሰሱ፤ በፍርደ ገምድል ዳኞች የተፈረደባቸው፤ በፖሊስ እና በአቃቤ ሕግ በተፈበረከ የሃሰት መረጃ በደል የደረሰባቸው ነበሩ። ከዚህም አልፎ፤ ብዙዊቹ፤ በሚያሰቅቅ ሁኔታ የተገረፉ፤ በአካል እና በሕሊናቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው። እነዚህ እስረኞች እንደውም ካሳ የሚገባቸው ናቸው። እነዚህን የፖለቲካ እስረኞች፤ የሕዝብን ገንዘብ እና ንብረት በመመዝበር ከተጠረጠሩ እና፤ የሰውን ልጅ ሕሊና የሚሰቀጥጥ በደል ከፈፀሙ፤ ያለአግባብ ሕይወት ካጠፉ ተጠርጣሪ ወንጀለኞች ጋር እኩል ማወዳደሩ እንዴት ተገቢ ሊሆን ይችላል? ከዚህ በተጨማሪ፤ የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 28 በማያሻማ ሁኔታ እንደሚያስቀምጠው፤ ዜጎችን አላእግባብ ለአሰቃዩ፤ ለደበድቡ፤ ለገደሉ፤ እና ከፍተኛ የመብት ጥሰት ለፈፀሙ ተጠርጣሪዎች፤ ማንም ሃይል ምህርት የመስጠት መብት እንደሌለው ደንግጓል። ስለዚህ ምህረት ይደረግላቸው ማለት፤ ሕወሃት “ሕገ መንግስት ይከበር” ከሚለው ዲስኩሩ ጋር የሚጣረዝ ይሆናል።

ላለፉት 27 ዓመታት በተለይም ሕገ መንግስቱ ከፀደቀበት ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ፤ በተለይም የሕገ መንግስቱን ከአንቀጽ 14 እስከ 21 ያሉትን ድንጋጌዎች በማን አለብኝነት ሲጥሱ የነበሩ ሰዎች፤ በሕግ እንዳይጠየቁ እንቅፋት መሆን፤ ዶ.ር ደብረጽዮን፤ መስዋዕትነት የከፈልነው ለሕግ የበላይነት ነው የሚለውን ዲስኩራቸውን አልቦ (ዜሮ) ያደርገዋል። የትግራይ መስተዳድር፤ “ለሕግ የበላይነት እንደሚሰራና ሕገ መንግስቱ እንዲከበር” የበኩሉን ትግል እንደሚያደርግ ቢገልጽም፤ በተደጋጋሚ ያስመሰከረው ነገ ቢኖር፤ ሕግ እኛንም ሆነ ባልደርቦቻችንን አይነካም የሚል እና ለሕግ የበላይነት ደንታ የሌለው መሆኑን ነው።

ምንም እንኳን ዶ/ር ደብረጽየን በመግለጫቸው፤ “የእነ-ጄነራል ክንፈ መታሰር ከእኛ ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር የለውም፤ ጄነራሉም ሆኑ፤ ከደህንነት መስሪያ ቤቱ የታሰሩት ሰዎች፤ የፌደራል መንግሥቱ ቅጥር ሰራተኞች እንጂ ከትግራይ ክልል መንግሥት ጋር የሚያገናኝ ምንም ነገር የላቸውም” ቢሉም፤ በሰብዓዊ መብት ረገጣ እና ዜጎች ላይ አሰቃቂ እርምጃ በመውሰድ የተጠረጠሩትን አቶ ጌታቸው አሰፋን አሳልፎ ላለመስጠት ይህን ሁሉ የፖለቲካ አቧራ ማስነሳት ለምን አስፈለገ? ባለፈው ጽሁፌ የትግራይ ክልል መንግስት መግለጫው ላይ አዎንታዊ ነገሮችን ያካተተው፤ አሉታዊ የሆኑትን እና ዋና እና መርዛም መልእክቱንም ለማድበስበስ ይመስለኛል ብዬ ነበር። ይህንንም ከመግለጫ ባሻገር በተግባር እያየን ነው። በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎችን ላለማስረከብ፤ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ለማጋጨት፤ ሕወሃት እና የክልሉ አስተዳደር ከፍተኛ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ እያደረገ ነው። በአንፃሩ ግን፤ የዶ/ር አብይ መራሹ መንግሥት፤ እልህ አስጨራሽ በሆነ ከፍተኛ ትዕግስት፤ ሰላማዊ መፍትሔ እያፈላለገ ይገኛል።

የሕወሃት ሰዎች፤ አቶ ጌታቸውን አሳልፈው መስጠት ያልፈለጉት፤ ለትግራይ ሕዝብ በማሰብ እንዳልሆነ ግልጽ ነው።የትግራይ ሕዝብም ቢሆን፤ በሕወሃት መራሹ መንግስት ከፍተኛ በደል ተፈጽሞበታል። ዛሬም በሕወሃት የግዛት ቀንበር ውስጥ ነው ያለው። ይህንንም ባለፈው መቀሌ ዩኒቨርስቲ በተደረገው ስብሰባ ላይ፤ የሕወሃት አዛውንት መርዎችን ስድነት እና አምባገነንነት አይተናል። በአንድ ጉንጫቸው ስለዲሞክራሲ እየሰበኩ፤ በሌላው ጉንጫቸው ደግሞ የሰዎችን ሃሳብ ለማፈን ይሞግታሉ። እነዚህ አዛውንቶች፤ ለልጅ ልጆቻቸው፤ ስለሃሳብ ነፃነት ተምሳሌት መሆን ሲገባቸው፤ ከእነሱ የተለየ ሃሳብ፤ በአደባባይ እንዳይደመጥ፤ ስብሰባ ሲረብሹ ለማይት ችለናል። በአደባባይ ይህን ካደረጉ፤ በድብቅ ምን እንደሚያደርጉ ለመገመት አስቸጋሪ አይደለም። በትግራይ ውስጥ የፍርሃት ጉም እንዲሰፍን አድርገዋል፤ እነሱ ከሚያስቡት መስመር ውጭ እንዳይታሰብ፤ ትግራይ ውስጥ ከፍተኛ የስነ ልቦና ጦርነትም ከፍተዋል። የጋዜጣዊ መግለጫው አንዱ አንደምታ ይህ ነበር። ዛሬ የትግራይ ክልል መምህራን ከዶ/ር አብይ ጋር ስብሰባ እንዳይካፈሉ በክልሉ መንግሥት የተጣለባቸው እገዳ፤ የሕወሃትን ረግጦ ገዥነት እና፤ ኢዲሞክራስያዊነት ባህሪ ሌላ ምሳሌ ነው። ይህ ሁሉ እንግዲህ ለሕግ የበላይነት መስዋዕትነት ከፍያለሁ ከሚል ድርጅት የማይጠበቅ፤ ግን በተጨባጭ የሚታይ እኩይ ተግባር ነው።

ሕወሃት ግን ይህን ሁሉ ትርምስ የሚፈጥረው፤ አቶ ጌታቸው፤ የወንጀል ሚስጥሮችን እንዳያወጡ ለማገድ ነው። የእሳቸው ተባባሪዎች፤ ስጋታቸው ግልጽ ነው። እነዚህን ጥቂት የወንጀል ተጠርጣሪዎችን፤ ከሕግ ተጠያቂነት ለማዳን ግን፤ የትግራይን ሕዝብ ለምን “እሳት ላይ መጣድ” አስፈለገ? በጣም የሚያሳዝነው፤ በዝግምተኛ አእምሮ የሚያስቡት፤ እራሳቸውን የትግራይ ሕዝብ አፈንጉስ ያደረጉ አክቲቪስቶች፤ “ትግራይን እንገነጥላለን” የሚለው ነጠላ ዜማቸው፤ የማህበራዊ ድኅረ ገፆችን ማጣበቡ ነው። እነዚህ ሰዎች ከታሪክ ያልተማሩ መሆናቸው አይደንቅም። ሕወሃት ሲጠነሰስ፤ ትግራይን ለመገንጠል ሲያሴር፤ ሤራውን ውድቅ ያደረገው እና ያወገዘው የትግራይ ሕዝብ ነው። የትግራይ ሕዝብ ማን ለጥቅሙ እንደቆመለት ጠንቅቆ ያውቃል። ጄነራል ፃድቃን እንዳሉት፤ የህዳሴው ለውጥ ሲመጣ በከፍተኛ ሁኔታ የተደሰተው የትግራይ ሕዝብ ነው። አሁንም በለውጡ ደስተኛ ነው። ደስታውን እንዳይገልጽ ግን ታፍኖ ተይዟል። በአራት የቴሌቪዥን ጣብያዎች፤ በሬድዮ፤ እና በጋዜጣ ትግራይ ውስጥ የሚሰበከው፤ በጠላት ተከበሃል፤ ሊያጠፉህ ነው፤ ለጦርነት ተዘጋጅ ወዘተ የሚል ነው። ይህች ዲስኩር የሕወሃት፤ የመጨረሻ እስትንፋስ መሆኗን ሕዝቡ ጠንቅቆ ያውቃል።

ዶ/ር አረጋዊ በርሄ በቅርቡ እንደገለፁት 27% የሚሆነው የትግራይ ሕዝብ ከድህነት ወለል በታች የሚኖር ነው። በሚሊዮን የሚቆጠሩ የትግራይ ነዋሪዎች፤ ንፁህ ውሃ እንኳን አያገኙም። ይህ በሕዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለ “ወንጀል” ነው። የክልሉ አስተዳደር ለመሰረተ ልማት ትኩረት ሰጥቶ፤ ለሕዝቡ የሚበጅ ነገር ከመስራት ይልቅ፤ ገንዘቡን እና የሰው ሃይሉን፤ ለርካሽ ፕሮፖጋንዳ ማዋሉ ያሳዝናል። በቅርቡ የአሜሪካው ምክር ቤት አባል የሆኑት አሌክሳንደርያ ኮርቴዝ “ጨለማ ብርሃንን ይፈራል” ሲሉ ተናግረዋል። በሕወሃት ስር በወደቀችው ትግራይም ያለው ሁኔታ ይኽው ነው። የሕወሃት አመራር፤ የሕግን ብርሃን ፈርቶ ነው፤ ጨለማ ውስጥ የተቀመጠው። የትግራይንም ሕዝብ ወደዚህ ጨለማ የሚጋብዘው እራሱን ከብርሃን ለመከላከል እንጂ የትግራይን ሕዝብ ለመጥቀም አይደለም።

ብዙዎቻችን፤ ላለፉት በርካታ ዓመታት ብሔር ተኮር ጥቃት ስንቃወም፤ ስናወግዝ እና ስንታገል ኖረናል። ብሄር ተኮር ጥቃት በሃገራችን እንዲቀር ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሏል። በትግራይ ሕዝብ ላይም ይሁን በማንኛውም የሃገራችን ሕዝብ ላይ ብሔር ተኮር ጥቃት እንዲፈጸም አንፈቅድም። በፌደራል መንግስትም ይሁን በማንም ሃይል፤ በትግራይ ሕዝብ ላይ ዘመቻ ቢጀመር፤ ብዙው ኢትዮጵያዊ፤ ይህን እኩይ ዘመቻ ከትግራይ ሕዝብ ጋር ሆኖ ይታገለዋል። ዛሬ ዘመቻው፤ ተጠርጣሪ ወንጀለኞች ላይ ነው፤ በዙ ከኦሮሞ፤ ከአማራ፤ እና ሌላ ብሄሮች በወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ አሉ፤ አማራ፤ ኦሮሞ ወይም ሌላ ብሄር ላይ ዘመቻ ተደረገ ሲባል ግን አልሰማንም። ሕወሃት እና ጋሻና ጃግሬዎቹ የሚደሰኩሩት የሃሰት ዲስኩር፤ እንፋሎቱ እናድለቀበት ባቡር፤ “ትንፋሽ እያጠረው” እንደሆነ እያየን ነው። ሕወሃት፤ እንደ ገዢው ፓርቲ አባልነቱ፤ መጫወት የሚገባውን አዎንታዊ ሚና ካልተጫወተ እና የሽግግሩን ሂደት ካላገዘ፤ እስትንፋሱ እያጠረ እንደሚመጣ እና የምያምር አወዳደቅ እንደሚወድቅ ምንም ጥርጥር የለኝም። የትግራይ ሕዝብ ሕወሃትን ወክለኝ ብሎ አያውቅም፤ የሕወሃት ባለስልጣናት ለተጠረጠሩበት ወንጀል የሚወክሉት እራሳቸውን እንጂ የትግራይን ሕዝብ አይደለም። እያወቁ ማጥፋት፤ ከወንጀልም በላይ ወንጀል ነው። በመግለጫ ጋጋት፤ አላስፈላጊ “የጦርነት ታምቡር” በመምታት የሚፈታ ነገር የለም። “ፈሪ ፍርሃቱን ሲሸፍን ደረቱን ይነፋል” ይባላል። የሕወሃት ፉከራ የሚያሳየው፤ የወንጀል ተጠርጣሪዎችን ስጋት ነው። በዚህ የህዳሴ ጉዞ የሚሰሩ ስህተቶችን እያረምን፤ ትክክለኛውን ስራ እየደገፍን፤ ለልጅ ልጆቻችን የሚተርፍ ዘላቂ የአስተዳድር ስርአት ዘይቤ እንገንባ። “ሮም በአንድ ሌሊት አልተገነባም” ይባላል። ሃገራችን ብዙ የተወሳሰበ ችግር አለባት፤ ሁሉንም ነገር በአንዴ ማስተካከል አይቻልም። መፍትሄ ለማግኘት የሁላችንንም አስተዋጽኦና ጥረት ግን ይጠይቃል። ሁላችንም ብሔር ተኮር ጥቃትን እንታገል፤ ወንጀለኛ ብሔር እንደሌለውም እንገንዘብ። ስለዚህ የትግራይ ክልል መንግሥትም ሆነ፤ ሕወሃት፤ ቀደም ሲል ለሰራቸው ጥፋቶች ሃላፊነት ወስዶ ለህዳሴው ጉዞ አዎንታዊ ሚና ይጫወት።

መልካም ገና ለሁላችንም።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን ይባርክ።

__
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም።
ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here