
ቦርከና
ጥር 15 2011 ዓ.ም.
የሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ቀኝ እጂ እንደነበሩ የሚነገርላቸው አቶ በረከት ስምዖን በዛሬው እለት በአዲስ አበባ በመኖሪያ ቤታቸው በቁጥጥር ስር አንደዋሉ ተሰምቷል፡፡
አቶ በረከት ስልጣን ያለ አግባብ በመጠቀም የሙስና ወንጀል (በአሁኑ መንግስት አስተሳሰብ የሌብነት ወንጀል) ፈጽመዋል በሚል ነው የተያዙት፡፡
የአማራ ክልል የጸረ ሙስና ኮሚሽን ባለስልጣን በአቶ ዝግአለ ገበየሁ በኩል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አቶ በረከት ጥፋተኛ ተብለው የተጠረጠሩት በክልሉ መንግስት በሚተዳደረው ጥረት የተባለ ድርጂት በተደረገ የኦዲት ምርመራ ድርጂቱን ለኪሳራ ዳርገዋል በተባሉ ጉዳዮች ላይ አስተሳሰብ አመንጪ ( ማስተር ማይንድ) ናችው በማለት ነበራቸው ያለውን ሚና አብራርቷል፡፡ አቶ ዝግአለ ጉዳዮን በድርጂቱ ስር ባሉ አምስት ኩባንያዎች የተደረጉ የአክሲዮን ግዢ እና ሽያጭ የአዋጪነት ጥናት ሳይደረግ በዘፈቀደ ተፈጽመው ድርጂቱ ለኪሳራ ተዳርጓል በሚልም ክሱን አብራርተዋል፡፡
አቶ በረከት የድርጂቱ የቦርድ አባል ሲሆን የድርጂቱ ስራ አስኪያጂ የነበሩት አቶ ታደሰ ካሳም በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ታውቋል፡፡ አቶ በረከት በአዲስ አበባ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ወደ አማራ ክልል እንደተወሰዱም ተሰምቷል ፤ በዚያው ክልል ክስ እንደሚመሰረትባቸውም ታውቋል፡፡
በአብይ አህመድ የተመራው ለውጥ ከመጣ ጀምሮ አቶ በረከት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩበት አሁን አዴፖ የተባለው ድርጂት ባደረጋቸው ስብሰባዎች ለደህንንቴ እስጋለሁ በሚል ሳይገኙ መቅረታቸው የሚታወስ ሲሆን ፤ ባለፉት ጥቂት ወራት ብዙውን ጊዜያቸውን በትግራይ እንዳሳለፉ ይታወቃል፡፡
ዛሬ በአዲስ አበባ በቁጥጥር ስር ሲውሉ የአማራ ክልል ጸጥታ አካላት ሊይዙኝ አይገባም በሚል ላለመታሰር በመሞከራቸው የፌደራል ፖሊስ ጣልቃ እንደገባም ተሰምቷል፡፡
ህብረተሰቡ በማህበራዊ ሚዲያ እና መገናኛ አውታሮች የአቶ በረከትን መታሰር አስመልክቶ የተለያዮ አስተያየቶችን እየሰጠ ነው ፤
አቶ በረከት ስምዖን ከስርቆት በላይ በኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ በደረሱ በሰብአዊ መብት ጥሰቶች በዋና ተዋናይነት ጭምር ሊጠየቁ ይገባል የሚለው አስተያየት ጎልቶ የወጣ ቢሆንም ፤ በምንም ጉዳይ ይጠየቁ ነገር ግን ያለፈውን ስርዐት ችግሮች ላለማስቀጠል ሲባል የፍርድ ሂደታቸው በህግ ብቻ እንዲሆን ፤ ሂደቱ ፍትሃዊ እንዲሆን እና ለአቶ በረከት ደህንነት ጥበቃ እንዲደረግ የሚያስታውሱ አስተያየቶችም ተስተውለዋል፡፡
___
ወቅታዊ እና ሚዛናዊ መረጃን ለማግኘት ቦርከናን በፌስ ቡክ ላይክ ያድርጉ።