(በመስከረም አበራ)
ጥር 15 2011 ዓ. ም.
ህወሃት አንጉቶ የጋገረው ኢህዴን ፈጣሪው ህወሃት ሁን ያውን ሁሉ እየሆነ ሰላሳ አምስት የታዛዥነት ዘመናትን አሳልፏል፡፡ኢህዴን መነሻው የወቅቱን የሃገራችንን ፖለቲካ ቀልብ ስቦ ከነበረው ኢህኣፓ ነው፡፡ኢህአፓ ደግሞ ህወሃቶች ማኒፌስቶ እንኳን ሳይፅፉ ታጋይ ነን የሚሉ ልሙጥ ፖለቲካኞች መሆናቸውን እየጠቀሰ ከመናቅ አልፎ ሲዘባበትባቸው የነበረው ፓርቲ ነው፡፡ነገሮች ተገለባብጠው የተናቀው ህወሃት በሃገራችን ፖለቲካ ላይ ጌታ መሆኑን አስረግጦ ጭራሽ አሽከር የሚያምረው ኋላቀር ጌታ ሆኖ ቁጭ አለ፡፡ህወሃት በሃገራችን የሰፈነው የዘር ፖለቲካ የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ ቁጭ ሲል አሽከሮቹ ደግሞ የየክልላቸውን የዘር ቆጠራ ፖለቲካ የሚያስተናብሩ፣ጆሯቸውን ከጌታቸው ከህወሃት ንግግር ለአፍታ አንስተው ለህዝባቸው የማያውሱ ከፊል መስማት ተሳነው ሆነው ብዙ ዘመን ኖረዋል፡፡በዚህ አሽከርነቱ እንከን የማይወጣለት የቀድሞው ኢህዴን፣የትናንቱ ብአዴን ነው፡፡
ኢህዴን ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ ሆኖ ሳለ ለአንድ ዘር ቆሜያለሁ ለሚለው ህወሃት አሽከር ሆኖ መታዘዙ ነውር መስሎት የሚያውቅ አይደለም፡፡ጭራሽ እንደ ጌታ ለማጎንበስ ሲል ከኢህዴንነቱ ተኮማትሮ “ብአዴን ነኝ” ሲል ለአንድ ዘር በመቆሙ ጌታውን መስሎ ቁጭ አለ፡፡በብአዴንነት ዘመኑ ታዲያ ጌታው ህወሃት ጥርስ የነከሰበትን የአማራ ሕዝብ በእሾህ ለበቅ ሲገርፍ አንገቱን ደፍቶ የኖረ ወገንተኝነቱ ለጌታው ህወሃት ብቻ የሆነ ስብስብ ነበር፡፡ይህን ጠንቅቆ የሚያውቀው የአማራ ክልል ህዝብም ብአዴንን እና ህወሃትን አንድ እና ያው ብሎ መድቧቸው ራሱን ነፃ የማውጣቱ ትግል ከሁለቱም ጋር እንደሆነ አምኖ ትግሉን በዚሁ መሰረት አስኬደ፡፡ሆኖም በመለወጡ ተስፋ የተቆረጠበት ብአዴን እንደ አላዛር ባለ ሁኔታ ከፖለቲካ ሞቱ ተነስቶ፣የህዝብን ትግል ተገን አድርጎ ጌታውን ማንጓጠጥ ጀመረ፡፡
ብአዴን እና ሌላው የረዥም ዘመን አሽከር ኦህዴድ እንደ ሰው እምቢ ማለት በጀመሩ አፍታም ሳይቆይ የጌታ ጉልበት መብረክረክ ጀመረ፡፡ጌትነቱም አከተመ፤ወንበሩም በትናንት አገልጋዮች ተያዘ፡፡የአገልጋች ስም ተቀየረ፡፡ዛሬ የህወሃትን መንበር የሚሸከሙት ብአዴን እና ኦህዴድ የሉም፤ህወሃትም ከዙፋኑ ውርዶ መለስተኛ አስተዳዳሪ ሆኖ መቀሌ ከትሟል፡፡ሆኖም ህወሃት እግሩ ከወንበር ይውረድ እንጅ ልቡ ዛሬም ጌትነቱን እንጅ መለስተኛ አስተዳዳሪነቱን የተቀበለው አይመስልም፣ራሱን አግዝፎ የሚያይበት መነፅርም፣የቀድሞው እበልጣለሁ እና ከኔ በላይ ብልጥ ላሳር ባይ ስነልቦናውም የተቀየረ አይመስልም፡፡ዛሬም በአድራጊ ፈጣሪነቱ ዘመን በሰፊ እጁ ያፈሰውን ሁሉ እንደልቡ መቆርጠም ይፈልጋል፡፡
ጠመንጃውን ተመርኩዞ ከአማራ ክልል ያፈሰውን ለም መሬት ዛሬም ተዝናንቶ አርሶ፣ ምርት ማፈስ ይፈልጋል፡፡ይህን ፍላጎቱን አደባባይ ወጥቶ ሲናገር “የአማራ ህዝብ ከትግራይ ህዝብ ጠብ የለውም፣እኔም ከገዱ ጠብ የለኝም እንደውም ጓዶች ነን” ይላል በርዕስ መተዳድሩ በዶ/ር ደብረፅዮን አፍ፡፡ከትናንት በስቲያ በሽማግሌዎች ፊት ይቅር ለእግዜር እንባባል ብለው የተሰየሙት የአማራ ክልል እና የትግራይ ክልል መሪዎች ጋዜጣዊ መግለጫ ባሉት ዲስኩራቸው ብዙ ማድበስበስ እና እልፍ ማስመለሎችን ሲያዘንቡ አምሽተዋል፡፡ትልቅ ችግር መደንቀሩ ሳይጠፋቸው ምንም ችግር እንደሌለ ሲቀላምዱ ሰሚን ያሰለቻሉ፡፡የተለመደውን መፍትሄ አልቦ፣እውቀት አልቦ፣መስህብ የለሽ የካድሬ ንግግራቸውን ግተውን ወርደዋል፡፡
የትግራይ ህዝብ እና የአማራ ህዝብ አልተጣላም የሚለው ከካድሬዎቹ አልፎ የሌሎቻችንም የንግግር ማሳመሪያ እየሆነ የመጣው የማድበስበስ ፈሊጥ በሁለቱ ክልሎች ላይ ላንዣበበው ትልቅ ችግር መፍትሄ ቢሆን ኖሮ እሰየው ነበር፡፡ ለመሆኑ ሁለቱ ባለስልጣናት እስኪያቅረን እንደነገሩን የትግራይ እና የአማራ ህዝብ ካልጣላ፣ክልሉን የሚመሩት ሰዎችም ጓዶች ከሆኑ ሽምግልናውን ምን አመጣው ሊባል ነው? ነው ወይስ ዶ/ር ደብረፅዮን መቀለዴ ብለው እንደ ተናገሩት ሽማግሌዎቹ እና ደብረፅዮን ስለተዋደዱ ነው እየተገናኙ የሚሸማገሉት?ማድበስበስ ምን ያህል ያስኬዳል? የቱን ችግር ይፈታል?
ሽማግሌ ተብየዎቹስ በምን አላማ ሊያሸማግሉ እንደተነሱ፣ከሽምግልናው ምን መፍትሄ እንደሚጠበቅ ወይም የተሳካ ነገር ካለ ከመቀሌ ባህርዳር፣ ከባህርዳር አዲስ አበባ የሚንከራተተው ሽምግልናቸው ትርፍ ምን እንደሆነ ለህዝብ ግልፅ የማያደርጉበት ሽምግልና ለማን ምን ትርጉም ይኖረዋል ብለው ነው የሚደክሙት?ከዚህ በፊት የሽምግልናቸው ልዕልና የት ድረስ ቁልቁል እንደሚምዘገዘግ የታዩ ሰዎች እንዲህ በሽፍንፍን የሚያደርጉት ቀርቶ በግልፅ የሚያደርጉት እንቅስቃሴም በህዝብ ዘንድ እንዴት በአጥርጣሬ እንደሚታይ አለማወቃቸው ትልቁ ችግራቸው ነው፡፡
በፖለቲከኞቹ በኩል ያለው ማድበስበስ እና ማስመሰል ኢህአዴግ የሚባል ፓርቲ ከእውነት ጋር ክፉኛ የተጣላ እንደሆነ አመላካች ነው፡፡ሁለቱም መሪዎች ነገ ዛሬ ሳይባል ተፍረጥርጦ ውይይት ሊደረግበት የሚገባ አንገብጋቢ ችግር ታቅፈው የሚመሩትን ህዝብ እየጠቀሱ ጥርስ ያበቀለ ህፃን ሳይቀር የሚያውቀውን ጠቅላላ እውነት ሲደጋግሙ መዋላቸው ለዚህ ምስክር ነው፡፡አንዱ ተደራዳሪ “የእንትን ህዝብ ከሰላም ስለሚጠቀም አጥብቆ ሰላም ይፈልጋል እና ቀድሞ ጥይት አይተኩስም”ሲል፤ሌላው በኦሪት ዘመን የተደረገውን እያነሳ “የኔ አካባቢ ህዝብ እነ እንቶኔ ከእንትን ሃገር ሲመጡ አስጠልሎ ነበር አሁን ግን ተፈናቀለ ይህም ሆኖ ችግሩን ይሸከማል እንጅ ጥይት አይተኩስም” ይላል፡፡ቀድሞ ነገር ከሰላም የማይጠቀም ህዝብ የለም፡፡ሲቀጥል የአመፅ ልብ ይዞ፣በእበልጣለሁ ባይነት ታጅሎ በኦሪት ዘመን አንድ ደግ ንጉስ ያደረጉት እንግዳ ተቀባይነት ደጋግመው ቢያወሩት ለዚህ ዘመን ችግር መፍትሄ አይሆንም፡፡የደጉ ንጉስ ስራ የሚወክለው ራሳቸውን እንጅ ዘራፊውን እና ገራፊውን ህወሃትን አይደለም፡፡የህወሃት ተጨባጭ ማንነት ሌላ ነው፡፡
ህወሃት ህዝብን በጊንጥ የሚገርፍ፣በዘረፋው እና በግፉ ሃገር ከመመረሩ የተነሳ “ሆ!” ብሎ ወጥቶ ከወንበሩ የፈጠፈጠው የአረመኔዎች ስብስብ ነው፡፡ህወሃትነትን የመሰለ ደም የተነከረ ሸማ የለበሰ ሰው የደጉን ንጉስ ስራ እየጠራ ሌላውን ህዝብን ባፈናቃይነት መክሰስ ትልቅ ግብዝነት ነው፡፡ማን በማን ላይ እንዴት ያለ አሰቃቂ ወንጀል እንደሰራ፣ማን አቡክቶ የጋገረውእብሪት እና ዘረኝነት ወለድ ችግር በአጎራባች ህዝቦች መሃከል የእልቂት ዳመና እንዲያንዣብብ እንዳደረገ፣መሬቱን እና ማንነቱን ተቀምቶ በመፈናቀሉ፣በመገደሉ፣በመሳደዱ፣በስውር እና ግልፅ እስርቤት አሳር መከራ በማየቱ በኩል ማን የሚብስ ብሶት እንዳለው የሁሉም ሆድ ያውቀዋል-ሽማግሌ ተብየዎቹም ጭምር፡፡ሆዳቸው ሲያውቅ እንሸማገል ብለው የተሰየሙት ሹማምንትም ጉዳያቸው ከቄስ መነኩሴ ሽምግልና አለፍ ያለ የህግ የበላይነት፣የተጠያቂነት፣የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የመሳለሉ ስልጣን፣እብሪት እና ጠመንጃ መራሽ ችግሮች ጥርቅም እንደሆነ አሳምረው ያውቁታል፡፡
ፖለቲከኞቹም ሆኑ ሽማግሌዎቹ ሆዳቸው ሲያውቅ ሽምግልና ያስቀመጣቸው ምንድን ነው የሚለውን ነገር መመርመር ያስፈልጋል፡፡እንደሚታወቀው ሽምግልናው የተደረገው የኢህአዴግ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ ሊደረግ ቀናት ሲቀረው ነው፡፡በዚህ ስብሰባ ላይ ደግሞ በተካረረ መነቋቆር የቆዩት የአዴፓ እና ህወሃት ሹማምንት ሊገኙ ነው፡፡እነዚህ ሰዎች የችግሩን ስር በማይነቅለው የቄስ መነኩሴ ሽምግልና መሸማገላቸው ምናልባትም ለስብሰባው ሲገናኙ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በሚያስቸግር አምባጓሮ ውስጥ እንዳይገቡ ለማለሳለስ ይሆናል እንጅ ውስብስቡ የአማራ እና ትግራይ ክልል ችግር በምናውቃቸው በነፓስተር ዳንኤል ገ/ስላሴ ሽምግልና እልባት ያገኛል ተብሎ አይደለም፡፡የጋዜጣዊ መግለጫው ፍሬ ከርስኪነት ለዚህ እሳቤ ምስክር ነው፡፡
በተረፈ ሽምግልናን ለምን እንደሚጠቀም ከሚታወቀው ህወሃት ጋር በቄስ መነኩሴ ተሸማግዩ ፖለቲካዊ ችግሮችን በቤተ-ዘመድ “አንተም ተው አንተም ተው” እፈታለሁ ማለት የችግሩን መጠንም ሆነ ችግሩን ማድበስበሱ የሚያስከትለውን አደጋ አለመረዳት ነው፡፡ህወሃት ሽምግልናን የሚጠቀመው ለብልጣብልጥ አላማው ማስፈፃሚ ብቻ እንደሆነ ካለፈው መማር ያስፈልጋል፡፡ይህ የሚሆነው ደግሞ ህወሃት በቀድሞው የአዛዥ ናዛዥነቱ ወንበር ላይ ቢሆን ነበር፡፡አሁን ዘመን ተቀይሯል፡፡ስለዚህ ለህወሃት ሽምግልና እንደወትሮው የልቡን የሚያደርስለት፣አዘናግቶ የሚመታበት የጊዜ መግዣ፣ጣላትን ማደንዘዣ በስተመጨረሻም እንዳይነሳ አድርጎ መቅበሪያ መሰሪ ትዕንት አይደለም፡፡
ዶ/ር ደብረፅዮን ችግሮችን በሽምግልና ከመፍታት ይልቅ ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ይመርጡ እንደ ነበር ቁጭት ባዘለ የተሸናፊነት ድምፀት በንግግራቸው መጀመሪያ በገደምዳሜ ተናግረዋል፡፡ሽምግልና የዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ቡራኬ ቢሆን ነበር የህወሃት ፍላጎት፡፡ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በተባለው ህወሃትን የአሸናፊነት ማዕከል ላይ በሚያስቀምጠው ፈረስ ላይ ተጭኖ ያልመጣ መፍትሄ ሁሉ ለህወሃት አይጥመውም ብቻ ሳይሆን ያሳዝነዋል፡፡ዶ/ር ደብረፅዮን ለሽማግሌዎቹ “ሳመሰግናችሁ እያዘንኩ ነው” ያሉትም ለዚህ ነው፡፡ደብረፅዮንን ያሳዘናቸው “የፓርቲ እሴት መሸርሸር” ሲሉ የገለፁት የብአዴን ወደ አዴፓ መቀየር፣የታዛዥን ወደ እኩልነት ተርታ መምጣት የሚወክለውን የፓለቲካ መናወጥ ነው፡፡
ብአዴን ወደ አዴፓ የመቀየሩ ነገር የስም ለውጥ ብቻ አይደለም፡፡ወትሮ ህወሃት ያለውን ነጥቆ እየበረረ፣በህዝቡ ኪሳራ የአዛዡን ፍላጎት ያስጠብቅ የነበረው ብአዴን ዛሬ ስም ከምግባር ተቀይሯል፡፡ጌታ ቀይሯል-ህወሃትን በሚያስተዳድረው ህዝብ፡፡አቶ ገዱ በሽምግልናው ፍፃሜ ከዶ/ር ደብረፅዮን ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በተደጋጋሚ”እኔ እዚህም እዛም ስሄድ የማወራው ተመሳሳይ ነገር ነው….ከዚህ ውጭ ብሄድ ህዝብ አይፈቅድልኝም” ያሉት ነገር ትርጉሙ የድሮው አይደለሁም፤ጌታየም ተቀይሯል ማለት ነው፡፡
ይህን መራራ እውነት መቀበል የማይፈልገው ህወሃት ታዲያ የአዴፓን ከህዝብ የመወገን ወደ በጎ የመለወጥ ነገር “የድርጅታችን እሴት መሸርሸር” እና “የእኛ ስራችንን አለመስራት” ሲሉ በቁጭት ይጠቅሱታል፡፡ሁልጊዜ አሸናፊነትን እና እበልጣለሁ ባይነትን ሰንቆ የሚነሳው ህወሃት የሚያስበው እንዲህ ነው፡፡ህወሃት ሲያሾረው በኖረው ኢህአዴግ የድርጅት እሴት ተከበረ የሚባለው የግንባሩ አባል እና አጋር ድርጅትቶች ሹማምንት በየተሾሙበት ክልልላቸው ህወሃት ሊኖረው የሚችለውን አምሮት ማሳካት ነው-መሬት ካማረው መሬት፣ንግድ ካማረው ገበያ፣ዝርፊያም ካማረው ህጋዊ፣አስተዳደራዊ እና ፖለቲካዊ ሽፋን መስጠት፡፡
አሁን ይህ ነባር የቤታቤት ደምብ የለም፡፡ህወሃት ማዘዝ አቁሟል፡፡የቀድሞ ታዛዦቹም ማሸብሸብ ትተው የቀድሞ አዘዣቸውን በትከሻቸው ከማየት አልፈው ወንበር ነጥቀው፤ከማእከል አባረው ጠረፍ አስይዘውታል፡፡የቀድሞው የህወሃት ማዘዝ እና የአጋር/አባል ፓርቲዎች መታዘዝ እንደወትሮው አለመቀጠሉ ነው በዶ/ር ደብረፅዮን ንግግር ውስጥ”…እኛ ስራችንን መስራት ባለመቻላችን ነው ይህ ሁሉ የመጣው” ተብሎ የተገለፀው፡፡
በሽታውን የደበቀ መድሃኒት ከወዴት ይማስለታል?
በአጠቃላይ የሽምግልናው ማሳረጊ ተብሎ በተሰጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ከህወሃትም ሆነ ከአዴፓ በኩል በችግሩ ዙሪያ ከመዞር እና ከማድበስበስ በቀር በችግሩ ላይ የቆመ ሃሳብ አልተሰነዘረም፡፡እንደውም ንግግራቸው ሲጠቃለል በአማራ እና በትግራይ ሕዝብ ዘንድም ሆነ በህወሃት እና በአዴፓ መሃከል ምንም አይነት ችግር እንደሌለ ነው የተገለፀው፡፡ይህን የሚለው መቀሌ ላይ ሰልፍ ጠርቶ በትግራይ ሕዝብ ላይ ትልቅ ስጋት እንዳለ ለህዝብ የሚናገረው ህወሃት ነው፡፡መቀሌ ላይ የትግራይ ህዝብ በትልቅ አደጋ ውስጥ በመሆኑ የተነሳ ለማንኛውም ነገር መዘጋጀት እንዳለበት ያወሩት ዶ/ር ደብረፅዮን ሂልተን ሆቴል ላይ “ጓዴ” ካሏቸው አቶ ገዱ አጠገብ ተምጠው የሚያወሩት ደግሞ ገብስ ገብሱን ነው፡፡
እንደውም በተለመደው ህወሃታዊ ብልጣብልጥነት የጎንደር ህዝብ ሲሞት፣ሲሰደድ፣ሲገረፍ፣ሲፈናቀል የኖረለትን የድንበር ጥያቄ፣ማንነት የመነጠቅ ጉዳይ በምድር ላይ የሌለ ጉዳይ እንደሆነ፣አቶ ገዱ እና እሳቸውም እንደ አጋጣሚ በሽማግሌዎች ፊት ተገኙ እንጅ በሁለቱ ክልሎች መካከል ኮሽታም እንደማይሰማ እንዲህ ሲሉ ገለፁ “ሁለታችን ስለተጠራን እንጅ የተለየ ግጭት የለንም፤ሊያበጣብጡን የሚፈልጉ አሉ፤የወሰን ችግር የለብንም ፣የመሬት ነገር አጀንዳችን መሆን የለበትም፤በቦታ የምንጋጭ አይሆንም;አልተጋጨንም…”፡፡የዚህ አባባል ትርጉም፣አላማ እና ፖለቲካዊ ጥቅም የኢህአዴግ ካድሬ ሆኖ ለማያውቅ ሰው ሊገባው አይችልም፡፡
እንዲህ በሽታውን ሽምጥጥ አድርጎ የሚክድ ሰው ከነበሽታው አፈር ከመግባት በቀር ምን መፍትሄ ይፈለግለታል፡፡የሽምግልናውም ሆነ የጋዜጣዊ መግለጫው ያስፈለገበትን ዋና ጉዳይ፣እሳቸው ራሳቸው በዛች ቅፅበት እዛ ቦታ ተገኝተው እንዲያወሩ ያደረጋቸውን ዋና ነገር የለም ሲሉ ከካዱ ሰውየ ጋር ተነጋግሮ ለመግባባት፣መፍትሄም ለማምጣት የመላዕክት ቋንቋ ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡
ሌላው አስገራሚ ጉዳይ ፖለቲካ እና ሰላም ሁለት የተለያዩ ነገሮች ተደርገው የቀረቡበት የዶ/ር ደብረፅዮን ንግግር ነው፡፡”ፖለቲካውን ለብቻ ሰላሙን ለብቻ … ፖለቲካው ሊቆይ ይችላል ሰላሙ ግን ጊዜ አይሰጥም ፤ይቆይ ፖለቲካው ሰላም ይቅደም…..” ይላሉ ፖለቲካ አዋቂ ነኝ ብለው ሃያ ሰባት አመት በሃገሪቱ ፖለቲካ ዋና ዋና ቦታ ላይ የኖሩት ዶ/ር ደብረፅዮን፡፡ፖለቲካው ባልተረጋጋበት ሃገር እንዴት ያለ ሰላም እንደሚጠበቅ የሚያውቁት ደብረፅዮን ብቻ ናቸው፡፡ እውነት ለመናገር ይህን የሰውየውን ንግግር ስሰማ በሁነኛ እጅ ላይ ወድቆ በማያውቀው የሃገሬ ፖለቲካ አዝኛለሁ፡፡ኢህአዴግ በከፍተኛ የአሳቢ ጭንቅላት ድርቅ የተመታ ፓርቲ መሆኑ ድሮም የሚታወቅ ቢሆንም ይህ ንግግር ደግሞ ይህንኑ የሚያጠናክር ነገር ነው፡፡የሃገራችን ችግር በኢህአዴግ ካድሬዎች የመፈታቱ ነገር አጠያያቂ የሚሆነውም በዚሁ በፓርቲው ሰዎች የእውቀት ጠብ ነው፡፡ ከእውቀትም ከእውነትም ተጣልቶ ምን መፍትሄ ሊመጣ እንደሚችል ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡
__
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።