ከጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ
ጥር 19/2011 (01/27/2019)
በታህሳስ 2011 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋምያ ረቂቅ አዋጅ፤ አላስፈላጊ የፖለቲካ አቧራ ከማስነሳቱም በላይ፤ በጥር 16 ቀን 2011 ዓ.ም የትግራይ ክልላዊ መንግስት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ ተገቢ እና ሕጋዊ ባልሆነ አካሄድ፤ ይህን ረቂቅ አዋጅ እንደሚቃወም በሙሉ ድምጽ ማጽደቁ፤ ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርገዋል። የዚህን ኮሚሽን ማቋቋምያ ረቂቅ አዋጅ በተመለከተም “የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ሕገ-መንግሥታዊ ነው” በሚል ርዕስ በታህሳስ 12 ቀን 2011 ዓ.ም. የፃፍኩት መጣጥፍ፤ በተለያዩ ድኅረ ገጾች ታትሞ ለንባብ በቅቷል። ይህንን ምላሽ እንድጽፍ ያነሳሳኝ፤ በጥር 5 ቀን 2011 ዓ.ም. “እኔ የምለው” በሚል አምድ ስር በሪፖርተር ጋዜጣ ሜጀር ጄነራል አበበ ተክለሃይማኖት “የማንነትና የድንበር ኮሚሽን ኢሕገ መንግሥታዊና አደገኛ ነው” በሚል ርእስ ስር የፃፉትን ካነበብኩ በኋላ ነው። ምንም እንኳን ጄነራሉ፤ በፃፉት መጣጥፍ ሥር፤ ከጭብጥ ጋር የሚጣረዙ እና፤ ከፃፉት ርዕስ ጋር ምን ግንኙነት የሌለው “የኢሕአዲግን የሥልጣን አያያዝ እና የብሔር ጥያቄ” ትርከት ከራሳቸው እይታ ሃተታ ጽፈዋል። ጄነራል አበበ፤ የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋምያ ረቂቅ አዋጅ፤ ኢሕገ መንግሥታዊ ነው በሚለው ጽሁፋቸው፤ የሕገ መንግሥቱ የትኛው አንቀጽ እንደተጣሰ የጠቀሱት ምንም ነገር የለም። ጄነራሉ ስለፃፉት “የሥልጣን አያያዝ እና የብሔር ጥያቄ ትርከት” ላይ ምላሽ መሰጠት ወቅቱ ስላልሆነ እና፤ ከዚህ ርዕስ ጋር ምንም ግንኙነት ስለሌለው፤ በእሱ ላይ ሃሳብ አልሰጥም።
ሆኖም፤ ጄነራል አበበ የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋምያ ረቂቅ አዋጅ “ኢሕገ መንግሥታዊ እና አደገኛ” ነው ያሉትን ሃሳብ እንድተችበት ይፈቀድልኝ። ጄነራሉ፤ ለጽሁፋቸው ርእስ ትኩረት የሰጡበትን ሃሳብ ሲጀምሩ“ሕገ መንግሥቱ የማንነትና የድንበርን ጉዳይ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንጂ፣ ለተወካዮች ምክር ቤትና ለሥራ አስፈጻሚው ሥልጣን አልሰጠም፡፡ ማንነትና ድንበርን የሚመለከት አንድ አንቀጽ በተወካዮች ምክር ቤትም ሆነ በሥራ አስፈጻሚው ሥልጣንና ተግባር ውስጥ የለም”ሲሉ ይጀምራሉ። ይህ ከጅምሩ ስህተት የሆነ የመነሻ ሃሳብ ነው። ሕገ መንግስቱ፤ የማንነትና የክልሎችን የድንበር ጉዳይ፤ እንዲወስን ለፌደሬሽን ምክር ቤት ሥልጣን ይስጥ እንጂ፤ በሕገ መንግስቱ የትኛውም አንቀጽ ላይ፤ ስለማንነት እና ስለክልሎች የድንበር ጉዳይ፤ የሚያጠናም ይሁን ሃሳብ የሚያቀርብ ተቋም አይቋቋም የሚል የለውም። ከዚህ በተጨማሪ፤ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 77 ቁጥር 2 የመንግስትን ተቋማት አደረጃጀት በተመለከተ ረቂቅ አዋጅ እንዲያቀርብ ሥልጣን የተሰጠው፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው። የሚኒስትሮች ምክር ቤት የመንግስትን ተቋማት አደረጃጀት እና አወቃቀር በተመለከተ ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲያቀርብ በተሰጠው ሥልጣን መሰረት ነው፤ በኅዳር 7 ቀን 2011 ዓ.ም.”“የብሄራዊ እርቀ ሰላም እና የማንነትና የወሰን ኮሚሽኖች” እንዲቋቋም ውሳኔ ያሳለፈው እና ረቂቅ አዋጁ እንዲፀድቅ ለፌደራሉ የሕዝብ ተወካዮች መንግስት ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበው። በዚህም መሰረት፤ የህገ መንግስቱ አንቀጽ 55 ለፌደራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጠው ሥልጣን ፤ የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋምያ ረቂቅ አዋጅ በድምጽ ብልጫ ፀደቀ። ተገቢ እና ሕጋዊ አሰራሩም ይኽው ነው። ነገር ግን፤ ጄነራል አበበ ያለምንም ጭብጥ፤ ረቂቅ አዋጁ ኢሕገ መንግሥታዊ ነው ሲሉ ይከራከራሉ። ጄነራሉ የሳቱት ነገር፤ የፊደሬሽን ምክር ቤት በአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ላይ ውሳኔ የመሰጠት ሕገ መንግሥታዊ ስልጣን ሲኖረው፤ የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ደግሞ ምንም ዓይነት ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን አልተሰጠውም። ሃቁ እና ትክክለኛ የአሰራር ሂደቱ ይህ ሆኖ ሳለ፤ የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋምያ ረቂቅ አዋጁን ኢሕገ መግሥታዊ ሊያደርገው የሚችለው ምንድን ነው? ጄነራል አበበ የተጣሰው አዋጅም ሆነ ሕገ መንግስታዊ አንቀጽ ይህ ነው የሚል ጭብጥ ሊያቀርቡ አልቻሉም።
ጄነራል አበበ ጽሁፋቸውን በመቀጠል “የተወካዮች ምክር ቤት ሕግ የማውጣት ሥልጣን ስላለው አዋጁ ኢሕገ መንግሥታዊ ሊሆን አይችልም ብለው የሚከራከሩ አሉ፡፡ ውኃ የሚቋጥር አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ባስቀመጠው ሥልጣንና ተግባር የተገደበ ነው፡፡ እንኳን የፌዴራሉ መንግሥት ቅርንጫፎች ሥልጣንና ተግባር የሚሸረሽር ሕግ ሊያወጣ፣ ለክልሎች በተሰጠው ሥልጣን እንኳን ሕግ ለማውጣት አይችልም።” ሲሉ ለመከራከር ይሞክራሉ፤ ይህ አመለካከት የራሳቸውን ሃሳብ ብቻ የሚያንፀባርቅ እንጂ፤ ምንም መከራከርያ ጭብጥ የለውም። በእርግጥ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕገ መንግስቱን የሚፃረር ሕግ ለማውጣት አይችልም፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚያወጣው ሕግ ግን፤ ሕገ መንግስታዊ ካልሆነ፤ አይደለም ብሎ መወሰን የሚችለው፤ ህገ መንግስቱን የመተርጎም ሥልጣን የተሰጠው የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ነው። ጄነራል አበበ በጭብጥ ሊያስረዱን ያልቻሉት ግን፤ በዚህ ረቂቅ አዋጅ፤ የትኛው የሕገ መንግስት አንቀጽ እንደተጣሰ ነው። የራስ ሃሳብ ብቻውን (opinion) ጭብጥ (fact) ሊሆን አይችልም።
ጄነራል አበበ ቀጥለው በሚያነሱት መከራከርያ እንዲህ ይላሉ “ሁለተኛው ክርክር አጥንቶ ለውሳኔ ለፌደሬሽን ምክር ቤት በሚያቀርብ ስለሆነ ምን ችግር አለው? የሚል ነው፡፡ የሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔን ገድሎ ወይም እንደሌለ ተቀጥሮ በቀጥታ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ለውሳኔ መላኩ ፀረ ሕገ መንግሥት ነው፡፡ ሕገ መንግሥታችን የዚያን ጉባዔ ሥልጣን፣ ተግባርና አወቃቀር ግልጽ በሆነ መንገድ አስቀምጦታል፡፡ ጉባዔው 11 አባላት ይኖሩታል ይላል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት የጉባዔው ሰብሳቢና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ምክትል ሰብሳቢ ሲሆኑ፣ በተቀመጠው መሥፈርት መሠረት ስድስቱ በተወካዮች ምክር ቤት እንደሚመረጡና ፌዴሬሽን ምክር ቤት በሦስት አባላት እንዲወከል ተደርጓል፡፡ ከሥራ አስፈጻሚው በስተቀር ሦስቱ የፌዴራል ተቋማት የሚወከሉበት ጉባዔ መሆኑ ነው፡፡ በጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚመራ ሕገ መንግሥታዊ ተቋም ሳይንሳዊ ሳይሆን፣ በሌላ ኮሚሽን እንዴት ነው ሳይንሳዊ የሚሆነው? የኮሚሽኑ መቋቋም አንዱን ሕገ መንግሥታዊ ተቋም እንደሌለ ስለሚቆጥርና ስለሚያኮላሽ ነው ኢሕገ መንግሥታዊ ነው የምንለው፡፡ ለተወካዮች ምክር ቤት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ በምክር ቤት አፈ ጉባዔ ይሆናል ብሎ ሕግ እንደማውጣት እኮ ነው!” (መስመር እና ድምቀት የተጨመረ)።የመጀመርያ ጥያቄ ሊሆን የሚገባው፤ የሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮችአጣሪ ጉባዔን እና የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋምያ ረቂቅ አዋጅ ምን አገናኛቸው? የሚል ነው። የሕገ መንግስታዊ አጣሪ ጉባኤ በሕገ መንግስቱ የተሰጠው ሥልጣን፤ ሕገ መንግስቱን የመተርጎም እና፤ ሕገ መንግስቱን የሚጻረረ ሕግ ወጥቷል ብሎ አቤቱታ የሚያቀርብ ካለ፤ ያንን ሕግ መርምሮ ውሳኔ መሰጠት ነው። የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ደግሞ ሕገ መንግስቱን በመተርጎምም ሆነ ሕገ መንግስቱን በተመለከተ የሚሰራው ምንም ስራ የለም። በረቂቅ አዋጁ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው፤ ኮሚሽኑ የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ጥያቄን በተመለከተ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ጥናቶችን የሚያቀርብ፤ ከሕዝብ አስተያየት የሚሰበሰብ፤ አስፈላጊ ሲሆንም የመፍትሔ ሃሳቦችን የሚያቀርብ ነው። ኮሚሽኑ ሕግ አውጪ፤ ሕግ ተርጓሚ፤ ወይም ውሳኔ ሰጪ አካል አይደለም። ስለዚህ፤ ጄነራሉ፤ ግልጽ ያልሆነላቸው ነገር ያለ ይመስለኛል። በህግ ተርጓሚ አካል እና በክልሎች መካከል ግጭቶች እንዳይነሱ፤ ወይም ግጭቶች ከተነሱ ግጭቶችን ለማብረድ ጥናት የሚያጠና አካል እንዴት አንድ ሊሆኑ ይችላሉ? ይህ ለጄነራሉ ግልጽ የሆነላቸው አልመሰለኝም። ምናልባትም፤ ጄኔራል አበበ የኮምሽኑን ሃላፊነት እና በአዋጁ የተሰጠውን ሥልጣን በጥሞና አላነበቡት ይሆናል። ከመቃወማቸው በፊት ግን፤ በቅጡ አንብበው ይረዱት እላለሁ። እኔ እንደሚገባኝ፤ እንደውም የፊዴሬሽን ምክር ቤቱን ተግባር እና ሥልጣን የሚደነግገው አንቀጽ 62 ቁጥር 5 የፌደሬሽን ምክር ቤቱ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር በጣምራ በመስራት ስልጣኑን ያከናውናል ይላል። ይህም ሕገ መንግስቱ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ከተወካዮች ምክር ቤት ጋር አብሮ እንዲሰራ የሚደነግግ ነው። ስለዚህ፤ የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን፤ የክልል ወሰኖችንም ሆን የማንነት ጥያቄን አስመልክቶ፤ ለተወካዮች ምክር ቤትም ሆነ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያቀርበው የመፍትሔ ሃሳብ፤ ለፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ውሳኔ አሰጣጥ ግብዓት የሚሆን ሃሳብ ያቀርባል እንጂ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱን ሥራ የሚሰራ ባለመሆኑ፤ ከዚህ ምክር ቤት ጋር ሊፃረር የሚችልበት ምንም መንገድ የለም። ጄነራል አበበ “የኮሚሽኑ መቋቋም አንዱን ሕገ መንግሥታዊ ተቋም እንደሌለ ስለሚቆጥርና ስለሚያኮላሽ ነው ኢሕገ መንግሥታዊ ነው የምንለው፡፡ ለተወካዮች ምክር ቤት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ በምክር ቤት አፈ ጉባዔ ይሆናል ብሎ ሕግ እንደማውጣት እኮ ነው!”ቢሉም፤ ይህ እንዴት ሊሆን እንደሚችል ግን አያስረዱም። በሕገ መንግስቱ ውሳኔ የማስተላለፍ ሥልጣን የተሰጠው ሃይል፤ ለመፍትሔ ጥናት እና ሃሳብ በሚያቀርብ ተቋም፤ እንዴት ሥልጣኑ ሊገፋ ይችላል? ጥናት የሚያጠና እና የሕዝብ ሃሳብ የመሰብሰብ ስልጣን እና ሃላፊነት የተሰጠው ተቋም፤ በህገ መንግስቱ ውሳኔ የመወሰን ሥልጣን ከተሰጠው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጋር እንዴትስ ሊነፃፃር ይችላል? ይህ በጄነራል አበበ ጽሁፍ ነጥሮ ጥርት ባለ መንገድ አልወጣም። ስለዚህ፤ ይህ ሃሳብ፤ ኮሚሽኑ ኢሕገ መንግሥታዊ ነው ብሎ የሚከራከርበት መቆምያ እግር የለውም።
በእርግጥ የአከላለል ለውጦችን በተመለከተ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 48 ለፌዴሬሽኑ ምክር ቤት የሚሰጠው ሥልጣን አለ። አንቀጽ 48 እንዲህ ይላል። “የአከላለል ለውጦች
1. የክልሎችን ወሰን በሚመለከት ጥያቄ የተነሳ እንደሆነ ጉዳዩ በሚመለከታቸው ክልሎች ስምምነት ይፈጸማል። የሚመለከታቸው ክልሎች መስማማት ካልቻሉ የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት የሕዝብን አሰፋፈርና ፍላጎት መሠረት በማድረግ ይወሰናል፡፡
2. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት የቀረበ ጉዳይ ከሁለት ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በፌዴሬሽኑ ምክር ቤት የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጥበታል፡፡”
አንቀጽ 48ን በጥሞና ከተመለከትን፤ የኮሚሽኑ መመስረት፤ የፌዴሬሽኑን ምክር ቤት እጅግ የሚጠቅም ሆኖ እናገኘዋለን። የክልል ጉዳዮችን ወሰን በተመለከተ፤ ኮሚሽኑ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ፤ በጥናት እና በመረጃ የተደገፈ ውሳኔ እንዲወስን ይረደዋል። ምክንያቱም የኮምሽኑ አላማ፤ በከፊል፤ ጥናት ማድረግ፤ ሃሳብ ማመንጨት፤ የሕዝብ ሃሳብ መሰብሰብ ናቸው እና። ለዚህም ነው ረቂቅ አዋጁ የፌዴሬሽኑን ምክር ቤት የሚንድ ወይም የሚተካ አይደለም የምለው። ምንም እንኳን ጄነራል አበበ ጭብጥ የሌላቸው ሌሎች ነጥቦችን ያነሱ ቢሆንም፤ ከላይ የገለጽኳቸው፤ የጄነራሉን ሃሳብ ይሞግታሉ ብዬ አምናለህ።
እግረ መንገዴን የትግራይ ክልል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔን በተመለከተ ጥቂት ልበል። የክልሉ ምክር ቤት፤ በሙሉ ድምጽ የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጥያቄ ረቂቅ አዋጅን ውድቅ እንዳደረገው ገልጽዋል። በተለይ፤ ነጋ ጠባ ሕገ መንግሥት ይከበር እያለ ከሚጮኽ የክልል መንግስት፤ ይህን “ኢሕገ መንግስታዊ” አካሄድ ማየት አስገራሚ ነው። የክልል መንግስት፤ በየትኛው ሕገ መንግሥታዊ አንቀጽ ነው፤ የፌደራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአብላጫ ድምጽ ያጸደቀውን፤ በክልሉ ምክር ቤት አልቀበልም የሚለው? የሕገ መንግስቱ አንቀስ 9 በግልጽ እንደሚያሳየው “ሕገ መንግሥቱ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ ነው። ማንኛውም ሕግ ልማዳዊ አሠራር፣ እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም።” የሚል ሲሆን፤ አንድን ሕግ፤ ሕገ መንግሥታዊ ነው ወይም አይደለም የሚለውን፤ ለመመርመርም ሆነ ለመወሰን፤ ሕገ መንግሥቱ ሥልጣን እና ሃላፊነት የሰጠው ለፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ነው። በዚህም አሰራር፤ የትግራይ ክልል፤ የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ኮምሽኑ መቋቋም ሕግ መንግስታዊ አይደለም ካለ፤ የሚቀጥለው ስራው ሊሆን የሚገባው፤ ለፌዴሬሽኑ ምክር ቤት በተወካዮቹ በኩል አቤቱታ ማቅረብ ነው። እየሆነ ያለው ግን ሕጋዊ አካሄድ ሳይሆን፤ የፌደራል መንግስቱን የሚንቅ ሕገ ወጥነት ነው። ይህም፤ የትግራይ ክልላዊ መንግስት፤”የበቀል ፖለቲካ” ላይ እንደተጠመደ ያሳብቅበታል። የትግራይ ክልል ምክር ቤት ባስተላለፈው ውሳኔ “አዋጁ የፌዴራል መንግስት በክልሎች ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የክልላዊ አስተዳደር መብትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስልጣንን እንዲጋፋ የሚያደርግ ነው” ብሏል። ይህ ጄነራል አበበ ካቀረቡት ውኃ ከማይቋጥር ክርክር ጋር ተመሳሳይ ነው።
የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 59 በግልጽ እንዳስቀመጠው “በዚህ ሕገ መንግሥት በግልጽ በተለይ ካልተደነገገ በስተቀር ማናቸውም ውሳኔዎች የሚተላለፉት በምክር ቤቱ አባላት የአብላጫ ድምፅ ነው።” ሲል ምክር ቤቱ በአብላጫ ያሳለፈው ሕግ፤ የሃገሪቱ ሕግ እንደሚሆን አስምሮበታል። የኮሚሽኑ አዋጅ ተቃዋሚዎች፤ አንዱ መከራከርያቸው እና የትግራይ ክልል መንግስትም ከሁለት ቀናት በፊት የኮምሽኑን መቋቋም ተቃውሞ ያሳለፈው ውሳኔ፤ አዋጁ የትግራይን ክልል ለመጉዳት ነው ከሚል መሰረት የለሽ ሃሳብ ለመሆኑ፤ የማህበራዊ ሚድያዎችን ክርክር ማየት ይበቃል። ተከራራካሪዎቹ ግን፤ ይህ ረቂቅ አዋጅ፤ የትግራይን ክልል እንዴት እንደሚጎዳ ያቀረቡት ምንም ጭብጥ የለም። ችግሮች እንዳይነሱ ጥናት የሚያደርግ፤ ግጭቶች ከተነሱ በኋላም ግጭቶችን በሰላም ለመፍታት ጥናት የሚያደርግ እና የመፍትሔ ሃሳቦችን ለፌደራል መንግስቱ የሚያቀርብ ተቋም፤ እንዴት ትግራይን ሊጎዳ እንደሚችል ምንም ግልጽ አይደለም።
በመጨረሻም ይህን ልበል። ሕግ ስለምንወደው ብቻ የምንከተለው አይደለም። የማንፈልገው እና የማንወደው ሕግ ሲኖር፤ ያንን ሕግ ለመቀየር ልንሄድባቸው የሚገቡ አሰራሮች አሉ። ይህ አሰራር መንገዱ እስካልተዘጋ ድረስ ልንከተለው ይገባል። ምንም እንኳን አሁን እየተሰራበት ያለው ሕገ መንግስት፤ በአንድ የፖለቲካ ድርጅት ረቅቆ እና በዚሁ ድርጅት ፍላጎት እና አካሄድ የፀደቀ ቢሆንም፤ በሃገራችን ሰላማዊ የአስተዳደር ሽግግር በመሻት አሁን ያለውን ሕገ መንግስት በመጠቀም ነው፤ ያለ ሁከት ለውጡን ማስቀጠል የምንችለው። በመሆኑም፤ ሁሉም ይህንን ሕገ መንግስት ተከትሎ ሊሰራ ይገባዋል። የትግራይ ክልል ሕጉ ካልተስማማው፤ አቤቱታውን ለፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ያቅርብ እና ይሟገት። የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ሕገ መንግስት ተጥሷል ካለ፤ ሌሎቻችን ውሳኔውን በፀጋ እንቀበል። የፌደሬሽን ምክር ቤቱ ሕገ መንግሥት አልተጣሰም ካለ፤ የትግራይ ክልል መንግስት፤ ለሕግ ይገዛ። በአንድ በኩል ሕግ መንግሥት ይከበር እያሉ ላንቃቸው እስኪበጠስ የሚጮሁ ሰዎች፤ እራሳቸው ሕግ ሲጥሱ እያየን ነው። ይህ አካሄድ ለማንም አይጠቅምም። ስለፈለግነው ብቻ በሃገራችን የሕግ በላይነት አይኖርም፤ የሕግ የበላይነት እንዲኖር፤ ከሊቅ እስከ ደቂቅ የሕግ ተገዢ ሊሆን ይገባዋል።
_____
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።