spot_img
Tuesday, June 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትየዶክተር አቢይና የኢትዮጵያ ፅኑ ጠላቶች - ሁሉም ሊያውቀው የሚገባ! (ይኄይስ አእምሮ)

የዶክተር አቢይና የኢትዮጵያ ፅኑ ጠላቶች – ሁሉም ሊያውቀው የሚገባ! (ይኄይስ አእምሮ)

ይኄይስ አእምሮ
ጥር 21 2011 ዓ.ም.

ሰላም ውድ አንባቢያን!

ሀገራችንን ከከበቧት ውስብስብ ችግሮች አንጻር ብዙ ከሚጨነቁ ዜጎች መካከል አንዱ ነኝ፡፡ እንደለመደብን በዝምታ ተውጠን በአርምሞ የፈጣሪን ተዓምራዊ ሥራ በጉጉት የምንጠብቅ ብዙ ዜጎች ብንኖርም አንዳንዴ የሚያስጨንቁንን የምንተነፍስ አንጠፋምና ዝም ብዬ ዝም ከምል ከምታዘባቸው መጥፎ ነገሮች መካከል አንድ ሁለቱን ያህል አሁን ባጭሩ ልናገር ወደድኩ፡፡

አስቀድሜ ግን ዓመት ሊሞላው ከሦስት ያነሱ ወራት በቀሩት አዲሱ ለውጥ እጅግ የምደሰት መሆኔን መግለጽ ይገባኛል፡፡ ይህ ለውጥ በሰዎች ፍላጎትና በልመና ወይም በወያኔ ቸርነት የተገኘ ሣይሆን ከአገዛዙ ውስጥም ከአገዛዙ ውጪም ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለበት ነው፡፡ በዚህ ለውጥ ምክንያት ያገኘናቸውን ወርቃማ ዕድሎች መጥቀሱ ጊዜ ማባከን ነው፡፡ በተጨማሪም ያገኘናቸውን ድሎችና በረከቶች ማንኳሰስ የበሉበትን ወጪት እንደመስበር ወይም ያጎረሰን እጅ እንደመንከስ ነው፡፡ “በትንሹ ያላመሰገነ በትልቁም አያመሰግንም” በሚለው ሥነ ቃል የሚገለጽ አይደለም ያገኘነው እፎይታ፡፡ ከዚያ በእጅጉ ይበልጣል፡፡ ወያኔን የሚያውቅና በሥርዓቱ ያለፈ ዜጋ ይህንን ለውጥ “ብልጥ ልጅ እየበላ ያለቅሳል” በሚለው ብሂልም ለመግለጽ አይደፍርም – ከዚህም በላይ ነውና፡፡ ወደ ተናጋሪ እንስሳነት እኮ ተለውጠን ነበር፡፡ የአሁኑ ሥነ ልቦናዊ ችግራችን እኮ “ወደዚያ ዓይነቱ ስቃይ እንመለስ ይሆን?” የሚለው እንጂ አሁንማ ጌታ ይመስገን – ቢያንስ ገልብጦ … የሚገርፈን የለም፡፡ ወያኔ? እንዴ! በላዔሰብዕ ምን አጠፋ?

ለዚህ ያበቁንን በትግሉ የተሰው የሁሉም ጎሣዎች አባላትና የአሁኑ መንግሥት አመራሮች – ንጹሓኑን እንጂ የበግ ለምድ የለበሱትን ተኩላዎች አይደለም – ሁሉንም በፈጣሪ ስም ባመሰግን “አመስጋኝ አማሳኝ” እንደማልባል ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ሀገራችንና ማኅበረሰባችን ከሞቱበት ነፍስ ዘርተው መነቃቃት የጀመሩት በዚህ ለውጥ አማካይነት ነው፡፡ ይህን ለውጥ አለማወደስ በውነቱ ትልቅ ስህተት ይመስለኛል፤ የምሥጋናንና የእርካታን መነሻና መድረሻ አለማወቅም ነው፡፡ እንከኖችን እየነቀሱ ወደፊት እንዴት እንደሚሻሻሉ መጠቆም ግን አግባብ ነው፡፡ አነሳሴም ለዚህ ነውና፡፡ እውነትን መናገር ሊያሽኮረምም ወይም ሊያግደረድር አይገባም – ዋናው ነገር “እውነቱ በርግጥም እውነት ነው ወይ?” ነው፡፡ እውነትን ብቻ ከተነጋገርን ታዲያ በዚህና በዚያ ምክንያት ሳንፈራረጅና ሳንጠላላ እየተራረምንና እየተማማርን በአንድ ሀገራዊ የጋራ ዓላማ መጓዝ ነው የሚገባን፡፡ ሌላው ሁሉ ትርፍ ነው፡፡

ከዓመት ገደማ በፊት ቲቪ ስከፍት የጦር ኃይሉ ማለትም የመከላከያው ጄኔራልና አዛዥ፣ የየክፍል አለቆች ከሞላ ጎደል ሁሉም፣ የትምህርት ባለሥልጣናት፣ የዲፕሎማሲው ዘርፍ ባለሥልጣናት፣ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ባለሥልጣናት፣ የደኅንነትና ፀጥታ ባለሥልጣናት፣ የንግዱ መስክ ባለሥልጣናት፣ የቀበሌ – የከፍተኛና የማዘጋጃ ቤት ሹሞች፣ የጉምሩክ ባለሥልጣናት፣ የሕንፃና ግንባታዎች ባለቤቶች፣ ሰጭ ነሽዎች፣ የሜቴክ ሠራተኞች፣ የአየር መንገድ ሠራተኞች፣ … በአብዛኛው እነሐጎስና አብረኸት ነበሩ – ሊያልፍ ዓለም አንወሻሽም፡፡ የሚቀጥሩት ትግሬ ጠፍቶ ከሌሎች ጎሣዎች ለመናጆነት ያህልና ለይምሰል ቢቀጠሩም ወያኔዎች በፈለጉ ጊዜ የሚያባርሯቸውና በሁለተኛ ዜጋነት እንደዕቃ የሚቆጠሩ ነበሩ፤ ተራ ማይማን ጽዳትና ዘበኛ ትግሬ የሚያንቆራጥጠው አማራ ሚኒስትርና የድርጅት ሥራ አስኪያጅ ቢኖር እንደ አንደኛ ደረጃ ሳይሆን በኢንጂነር ዶክተር ቅጣው እጅጉ አገላለጽ እንደሰባተኛ ዜጋ የሚቆጠር በገዛ የጋራ ሀገሩ መፃተኛ ሆኖ የሚኖር ነበር፡፡ የለዬልን አሽከርና ገረድ አድርገውን እንደከረሙ የአደባባይ ምሥጢር ነው – ሊያውም ከግድያቸውና ከስቃያቸው ተርፈን በትልቁ እስር ቤት – በዞን ዘጠኝ – ውስጥ ከነበርን፡፡

ያ አዝማሚያ ተቀይሮ ወደ ኢትዮጵያዊነት የጋራ ማዕከል ልንመለስ ነው ብዬ ስጠብቅ አሁንና ሰሞኑን ደግሞ የዱሮው ቅኝት በሌላ ተመሳሳይ አሠራር እየተለወጠ እንዳለ ታዘብኩ – “አሣራችን ለካንስ ገና ነው!” ብዬም አዘንኩ – ያውም በከፍተኛ ፍጥነት፡፡ እናም የማስተውላቸው የኃላፊዎችና የባለ ሥልጣናት ስሞች ከሐጎስና ከአብረኸት ወደ ጫላና ጫልቱ በብርሃን ፍጥነት እየተቀየሩ ነው፡፡ ይህን ነገር እንደችግር የማየው “እባብን ያዬ በልጥ በረዬ” ወይም “የአበራሽን ጠባሳ ያዬ በእሳት አይጫወትም” እንዲሉ ሆኖብኝ በወያኔው የግፍ አገዛዝ የደረሰብን መከራና ስቃይ እየተንኳተተ መጥቶ በሌላ ተረኛ ያሣለፍነው ምስቅልቅል ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሕይወት እንዳይደገምብን ፈርቼ እንጂ ፈይሣም ሆነ ረጋሣ ወይም ፍትዊም ሆነ ግደይ ዝንታለማቸውን ሥልጣን ወንበር ላይ ቢጎለቱ ደንታየ አይደለም – እኔ ራሴም ፈይሣ ልሁን ግደይ ወይም ስንሻው በቅጡ የማላውቅ አንዲት ኢትዮጵያን ብቻ እንዳስብ አድርጎ አስተዳደግ የበደለኝ ከባሕር የወጣሁ ዓሣ ነኝ፡፡ ግና ይህ አካሄድ እንዳልበጀንና እንደማይበጀንም ከተሞክሮኣችን መረዳት አያቅተኝም፡፡ ሰሚ ከተገኘ ከጦዙ ወር-ተራዊ ስሜቶች እንውጣና ብዙ ሳይመሽብን በአፋጣኝ ወደ ትክክለኛው መስመር መግባት ይኖርብናል፡፡ አንዱን በጥላቻ እየመረዙ ሌላውን በፍቅር እያቀረቡ የአንዲት ሀገር እኩል ዜጎች መባባል አይቻልም፤ ቢባባሉም እንኳን ከአንገት በላይና ከቀልድ ፍጆታነት አያልፍም፡፡ እነአቢይ ያስቡበት፡፡ አቢይን በሰውኛ አቅሜ አውቀዋለሁ ብዬ አስባለሁ – ይህን አሠራርም ይደግፈዋል ብዬ ማመን ይቸግረኛል፤ እየሰማና እያወቀ ዝም ካለ ግን መዘዙ ወደራሱና ወደ ትውልደ-ትውልዱ ይተላለፋል፡፡ በሌላ በኩል ግን እርሱ አንድ ነውና ከሥር ያሉት ነገር እያበላሹ በስሙ መጥፎ ሥራ በመሥራት ጥርስ ውስጥ እንዳያስገቡትና እንዳያስረግሙት መጠንቀቅ ይገባዋል – ከእርግማን ሌላ፣ ሌላ የተሻለ መሣሪያ ለጊዜው የለንማ! ይህንን መሰል የሕዝብ ብሶት የምታነቡና አቢይን የምትቀርቡት ወገኖቼ ጠጋ ብላችሁ “ኧረ እንዲህም እኮ እየተባለ ነው!” ብትሉት ክፋት የለውም፡፡ የዱሮ ነገሥታት ያደርጉትና ይጠቀሙበትም ነበር፡፡ መካሪ በግድ ከሰማይ እንዲወርድ አይጠበቅም፤ እግዚአብሔር እንኳንስ ሰውን ሣር ቅጠልንና ዓለቶችን እያናገረ ልበድፍን ነገሥታትን ይመክርና ያስመክር ነበር፡፡

የሚታየው ነገር ቀድሞም በታሳቢነት የተያዘና በስትራቴጂ ተቀምጦ የሚሠራበት እውነት ከሆነ ይህ ክስተት የዶ/ር አቢይ መውደቂያ ውስጣዊ ግን ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ስህተት እንደሚሆን ለማወቅ ብዙ መመራመር አያስፈልግም፡፡ አንድን ቁስል አፍረጥርጦ መግልን በማውጣት በተገቢው መንገድ ማከም እንጂ እንደነገሩ አከምን ብለው ከነመግሉና ከነቆሻሻው በፋሻ ቢጠቀልሉት እስከመቆረጥና ከዚያም አልፎ እስከመሞት ለሚያደርስ አደጋ ያጋልጣል፡፡ እናም ይህ የምናገረው ወልጋዳ አካሄድ ሳያመረቅዝ አሁኑኑ ይታሰብበት፡፡ ከመሸ በኋላ መፍትሔ ከማፈላለግ በጊዜ መስተካከል ከዳግም ድቀት ያድነናል፡፡

በሥነ ጽሑፍ ትምህርት nemesis የሚሉት ነገር አለ፡፡ አንድ አካል ሲፈጠር በውስጡ አጥፊውንም ይዞ እንደሚፈጠር የሚጠቁም ጽንሰ ሃሳባዊና ምናባዊ ንግርት ነው፡፡ በሕይወታችንም ውስጥ ይህ እውነት በግልጽ አለ፡፡ አንድ ሰው ከሁለት ነገሮች ጋር ይወለዳል – ከሕይወትና ከሞት ጋር፡፡ አንዱ በአንዱ ውስጥ እንደየሁኔታው በገሃድም ይሁን በድብቅ ይኖራል፡፡ የማታ ማታ ግን በፊት ገናና የነበረው ይወድቅና ተደብቆ የነበረው ይወጣል፡፡ በዚህ ሂደት የጊዜ ጉዳይ አለ፡፡ የጊዜው መርዘም ማጠሩ በኃያላኑ ተቃርኖዎች ትግል የሚወሰን ነው፡፡ እንዳማሩ መሞትን ለመታደል ታዲያ ዕውቀትና ጥበብን መላበስ ያስፈልጋል፡፡ መቼ? አሁን፡፡

ዶ/ር አቢይን ከፍ ሲል የጠቀስኩት ችግር ክፉኛ እየተፈታተነው እንደሆነ መገንዘብ ቀላል ነው፡፡ በውጭ ሀገር ቃል የተገባለት ገንዘብ እስካሁን የሚያረካ ያልሆነው – ለአብነት- ሰው አይናገረው እንጂ አዲሱን ለውጥ ከማመንና ካለማመን ጉዳይ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ በነሐጎስና በነጫላ መካከል በሚደረግ ፍትጊያ ውስጥ ገንዘቡንም ሆነ ሕይወቱን መገበር የሚፈቅድ አይኖርም፡፡ እስኪጠራ መጠበቅን የሚመርጠው ወገን ብዙ ነው፤ ዛሬ ሰው ነቅቷል፡፡ በቀላሉ አይታለልም፡፡ የዝንብን ልጃ-ገረድነትም በሉት ጠንጋራነት በሚያውቅ ማኅበረሰብ ውስጥ፣ አገር ቤት የምትሠራዋ አንዲት ነገር በሴከንዶች ውስጥ ዓለምን በምታዳርስበት ሁኔታ ሰዎችን በማራኪ ቃላት ብቻ “እመኑኝ” ብሎ ለማሳመን መሞከር ከባድ ነው – ተግባር ከቃላት በላይ ነውና፡፡ ለዚያም ነው በእስካሁኑ ሁኔታ ከቃል ባለፈ ተጨባጭ ነገር ሊታይ ያልቻለው፡፡ እንጂ የሀገር ቤቱ ነገር ፈር ቢይዝ – ምራቅን የሚያስውጥ ስብከትም ሆነ ዲስኩር ሳያስፈልግ – ኢትዮጵያን በዕውቀትም በገንዘብም እንደገና አፍርሶ የሚሠራት እምቅ ኃይል በውጭ እንዳለ በበኩሌ አምናለሁ፡፡ እነጫላና ሐጎስ ሌላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊንቁት አይገባም፡፡ መናቅ አደጋ አለው፡፡ አማራው ብዙ ነው፡፡ ሶማሌው ብዙ ነው፡፡ ደቡቡ ብዙ ነው፡፡ ዝኆን ነኝ ብሎ ሣርን መናቅ እንደማይገባ ትልቅ ነኝ ብሎ ትንሽ ወይም ጥቂት የሚመስሉ ግን እኩል መብት ያላቸው ዜጎችን በዐይን ቂጥ ማየት የከፋ አደጋ አለው – ጉንዳን እንኳን በአቅሟ ትጎዳለች – ሱሪ ታስወልቅ የለ እንዴ? በለውጡ ሂደት መረጋጋትና ሰላም የጠፋውም ለዚህ ነው፡፡ መጽሐፉ “ቆሜያለሁ ብሎ የሚያስብ ይጠንቀቅ” የሚለው ቆሜያለሁ ብሎ የሚኩራራ አወዳደቁ ላያምር እንደሚችል ለመጠቆም ነው፡፡ ውስጣዊውን ዐይናችንን – ሦስተኛውን ዐይን – ስድስኛውን የስሜት ሕዋስ – የዘጋነውን የኅሊና ችሎት በቶሎ እንክፈትና በትግስት ሁሉንም እንመርምር፡፡ ከዚያ የችግሮቻችን ሁሉ ቁልፍ በቀላሉ ይገኛል፡፡ ዋና ችግራችን አንዳችን ለሌላኛችን ጆሮ አለመስጠታችን ነው፡፡

ሌላው የአቢይና የኢትዮጵያ ችግር ለውጡ ከጫፍ እንጂ ከአንገት ጀምሮ ወደታች ስላልዘለቀ ነው – የአደባባይ ምሥጢርን ለመናገር እማኝ መጥቀስ አያሻኝም፡፡ በሙስና የጨቀዬ ቢሮክራሲ ይዘህ ሥር ነቀል ለውጥን ማምጣት አትችልም ወይም ጊዜና ትግስትን እንዲሁም ከፍተኛ መስዋዕትነትን ስለሚፈልግ በፈለግኸው ፍጥነት እውን አታደርገውም፡፡ አንድ ለውጥ ደጋፊ ኃይልና ለውጡን የሚቀበል የሚንከባከብም ሰፊ ማኅበረሰብኣዊ መደላድል ያስፈልገዋል፡፡ እኛ ግን በብዙ አቅጣጫ የተመታን ሕዝብ ነን፡፡ ወያኔ ባሳረፈብን ዱላ ተቀጥቅጠን አይሆኑ ሆነናል – ዘረኝነቱን፣ ከቤተ መንግሥት እስከ ቤተ አምልኮ የዘለቀውን የጥፋትና የሙስና ዝቅጠት፣ የትምህርት ሥርዓት መላሸቅ፣ የሞራልና የባህል ገመዶች መበጣጠስ፣ የሀገር ፍቅር መጥፋት፣ ገብጋባነት፣ ራስ ወዳድነት፣ … እነዚህንና ሌሎቹንም የውድቀት መገለጫዎች እናስባቸው፡፡ መቼ ይጠገናሉ? ማን ይጠግናቸዋል? እንዴት ብለን ወደ ጤናማ ስብዕና እንመለስ? እነማንን አይተው ልጆቻችን ጥሩ ዜጎች ይሁኑ? ሌብነትና ውሸት፣ ማጭበርበርና በአቋራጭ መክበር እንዴት ልጓም ይበጅላቸው? ይጨንቃል፡፡ ስለዚህ ጤናማ ዜጎችንና ጤናማ ማኅበረሰብን ለመፍጠር ራሱ ገና ብዙ ትግልና ጥረት ይጠብቀናል፡፡ ሻጥሩ በየፈርጁ ነው፤ ጎሠኝነቱ እስካንገት ነው፤ ብልሹ አሠራሩ እስከጥግ ነው፤ ማይምነቱና ካለሙያና ካለችሎታ ትልልቅ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ሳይቀር መመደቡ እስከጫፍ ነው፡፡ ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ወገኖች በሀሰት የግዢ ዲግሪ እየተንበሸበሹ መሥሪያ ቤቱን ሁሉ በሚያጥለቀልቁበትና እግራቸው የመ/ቤቱን ደጃፍ ከመርገጡ አንገታቸውን ወደ ሙስና በሚያሰጉበት ሁኔታ ሀገርን በለውጥ ማዕበል ማስጓዝ ከባድ ፈተና ነው፡፡ ጥራት በሁሉም ደረጃ ድርድር ውስጥ ገብቶ ስቃይ ላይ ነው፡፡ አንገትህን የሚያስደፋ እንጂ ደረትህን የሚያስነፋ አንድም ሀገራዊ ነገር አታይም – አጋንኜው ይሆናል፡፡ ግን ከእውነቱ ብዙም የምርቅ አይመስለኝም፡፡

ጨረስኩ፡፡ ዶ/ር አቢይ ግን ይወቅበት፡፡ የነብርን ጭራ/ጅራት ይዟል፡፡ ነብሩ ደግሞ በጠባዩም በመልኩም ዥንጉርጉር ነው፤ እንደነብር ያለ ኃይለኛ ዥንጉርጉር ፍጡርን መያዝ አስቸጋሪ ቢሆንም ፈጣሪ ከረዳው ከገባንበት አዘቅት በቶሎ እንወጣ ይሆናል፡፡
___
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here