spot_img
Sunday, May 26, 2024
Homeነፃ አስተያየትአገር አወዛጋቢው የጎሣ ፖለቲካ ስለመሆኑና ስለመወጫው (ተስፋዬ ደምመላሽ)

አገር አወዛጋቢው የጎሣ ፖለቲካ ስለመሆኑና ስለመወጫው (ተስፋዬ ደምመላሽ)

ተስፋዬ ደምመላሽ
የካቲት 6 2011 ዓ.ም.

በኦሮሞ ማኅበረሰብ “ማንነት” እና “ነፃነት” ስም የሚንቀሳቀሱ መሣሪያ ያነገቡ የኦነግ ነውጠኞች ባለፈው ሰሞን በመዕራብ ወለጋ ብዙ ባንኮች ዘርፈዋል፤ የባንክ ሠራተኞችን ጁሆ አድርገው (አግተው) ጠፍተዋል። ለአለፉት ሃያ ስምንት ዓመታት ወያኔዎች በትግራይ “ነፃነት” ስም እጃቸው ያስገቡትን የኢትዮጵያ መንግሥት ኃይል በመጠቀም ታይቶ በማይታውቅ የጎሣ ሙሰኝነት መልክና መጠን የአገር ሃብት ዘርፈዋል። የወቅቱን የጎሣ ፖለቲካ ሥርዓት ጥገና ለውጥ በአድሃሪ ተቃውሞ ለመግታት፣ ቢችሉም ለመቀልበስ፣ በመቀሌ መሽገው የትግራይን ህዝብ እንደ ጁሆ ይዘዋል። እነሱ ላይ ያነጣጠረውን የኢትዮጵያ ህዝብ ውንጀላና ክስ በድፍኑ ትግሬዎች ላይ ያለመ ማስመሰሉን ተያይዘውታል። ህዝብ ለህዝብ የማጋጨቱን ሞገደኛነት ቀጥለውበታል።

በብሔር ነፃ ማውጣት ስም ኢንግዲህ የኦነግም ሆኑ የወያኔ ንኡስ ጎሠኛ ብሔርተኞችና ጀሌዎቻቸው የማያደርጉት አገር አወዛጋቢና አሰናካይ ነገር ያለ አይመስልም። እነዚህ የማይታረሙ ቀውስ አድራጊ ፈጣሪዎች የጠ/ሚንስትር አብይ አመራር የሚያቀርብላቸውን የሰላምና እርቅ ልመና ከምንም አይቆጥሩትም። እንዲያውም ልምምጡን ከአመራሩ ድክመት ወይም አስፈላጊ መንግሥታዊ እርምጃ መውሰድ ካለመፈለግ ወይም ካለመቻል ጋር ሳያያዙት አልቀሩም። ይህ አተያያቸው በበኩሉ ለቀውስ ሥራ ይበልጥ ስልሚያደፋፍራቸውና ስለሚያነሳሳቸው የጠ/ሚንስትሩ መጠንና ወሰን የሌለው ልምምጥ የተገላቢጦ የኢትዮጵያን አገራዊ ደህንነት ለአደጋ፣ ለተባባሰ ቀውስ፣ የሚያጋልጥ መሆኑን መገምት አዳጋች አይደለም።

በዚህ ጽሑፍ የሠፈሩ የፖለቲካ ጎሠኝነት ችግሮችና መወጫቸው ላይ ያተኩሩ አስተያይቶችን ያቀረብኩት ሊታረሙ የማይችሉ የኦነግ እና የሕወሓት አገር አወዛጋቢ ጽንፈኞችን በተንታኝ ክርክር ለማግባባትና ለመለወጥ በመሞከር አይደለም። ቢለወጡ እሰዬ፣ ግን ይሄ ባመዛኙ ከንቱ ሙከራ ይመስለኛል። ይልቅስ ሃሳቤን ለማካፈል የምፈልገው በጎሣ እና በፖለቲካ ጎሠኝነት መካከል ያለው ልዩነት መምታታቱን እምብዛም ለማያስተውሉ ግን ለምክንያታዊ አረዳድና መግባባት ክፍት ለሆኑ ነገደ ብዙ የኢትዮጵያ ዜጎች፣ ስብስቦች፣ የህዝብ ድርጅቶች፣ ፖለቲከኞችና ምሁራን ነው።

ለኢትዮጵያ አንድነትና ደህንነት “የጎሣ ማንነት” የፈጠረውን የማያቋርጥ ውዝግብ ለዘለቄታው እንዴት እንወጣው የሚለው ጉዳይ የሚነሳው ጉዳዩን በሚገባ ባልተረዱ ሰዎች ነው። የጎሣ ማንነቶች እንዳሉ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ህልውና እና ብልጽግና ችግሮች አይደሉም። ማንኛውም ችግር መፍትሔ ሊገኝለት ይሚችል ከሆነ፣ መጀመሪያ ምንጩን፣ ቅርጹን፣ ይዘቱንና መገለጫዎቹን በሚገባ መረዳት ራሱ የመፍትሔው ወሳኝ አካል ነው። ችግሩን በእሳቤም በገቢርም ጠጋና ገባ ብሎ መጨበጥ ማለት በመሠረቱ እንዴት እንደሚፈታም ማወቅ ማለት ነው። መፍትሔው ሌላ ምስጢር የለውም። ወሳኙ ነገር የጉዳዩ አረዳዳችን ወይም አስተሳሰባችን ጥራት፣ ብቃትና ሃቀኝነት ነው።

በሌላ በኩል፣ በፈታሽ፣ ተቺ ትንተናና ግንዛቤ ብሩህ ወይም ገሃድ ያላደረግነውን የአገር ጉዳይ ቀደም ቀድም ብለን በሆኑ ባልሆኑ ድርጅታዊ እንቅስቃሴዎች ለመቋጨት ላይ ታች ማለት “ተግባራዊ” አኪያሄድ ሆኖ ይታይ ይሆናል። በእውነቱ ግን ፍሬያማ ጥረት አይሆንም። ጥረቱ በጥቅጥቅ ጨለማ የተዋጠ ቦታ ውስጥ ሆኖ መውጫውን በዳበሳ ለማግኘት ወድያ ወዲህ እያሉ በመደናበር የመሰላል። ብርሃን ሲመጣ፣ ሰፋና ጠለቅ ያለ ዕውቀት ሲፈነጥቅ፣ ጨለማው ባንዴ ይወገዳል። በኢሕአዴግ የበላይ አድራጊ ፈጣሪነት ዛሬ እየተጠጋገነ ያለው የጎሣ ፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ መንገድ ግልጥልጥ ይላል፤ ይጠረጋል፣ አቅጣጫው ይፈካል። የሥርዓታዊ ለውጡ መነሻም መዳረሻም ይበልጥ ተከሳች ይሆናል።

በተማሪው ትግል ዘመን በተጀመረና በአብዮቱ ሂደት በተስፋፋ “ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች” በሚል አእምሮ አደንዛዥ ስታሊናዊ የፖለቲካ ዲስኩር የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነት አጨላሚና አሰናካይ ብዙ ነገር ተብሏል፤ ተደርጓልም። የጎሣ ወገንተኞችንና ስብስቦችን ከአገር በላይ ሉአላዊ የሚያደርጉ “ሕገ መንግሥት” እና “ፌደራልዊነት” የተባሉ የሚመስሉትን ያልሆኑ ማንሜናዎች ተፍጥረዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬም በዘር ተከፋፍሎ በሆኑ ባልሆኑ የዘውግ ጉረኖዎች እንደከብት ተከልሎ ይገኛል።

በተለይ አማራውማ እንደ ባህላዊ ማኅበረሰብ በነፃነት ማንንቱን ራሱ ወሳኝ የሆነበት ግዛት ባለቤት መሆኑ ቀርቶ ነባር መሬቶቹን ተነጥቋል። የሱ በተባለው “ክልል” ሌሎች አድራጊ ፈጣሪ ሆነው ቆይተዋል፤ ዛሬም በቅማንት ደጋፊነት ስም የጎንደርን አማራ ህዝብ ከመከፋፈልና እርስ በርስ ከማጋጨት አልቦዘኑም። ከአብራኩ የወጡና ከሱ ምንም ያህል የማይለዩ ትናንሽ ማኅበረሰቦችን “ማንነት” እና “ልዩነት” በመጠምዘዝ አማራውን ማኅበረሰብ ሰላሙን አሳጥተዉታል። በአገር ደርጃ ደግሞ ከሁሉም ይበልጥ ተፈናቃዪና ተስቃዪ አስደርገውታል። ይህ ታላቅ ማኅበረሰብ ትዕግሥቱ ተሟጦ አልቆበት ህልውናውን ለማትረፍ ማንነቱን በአካባባዊም በአገራዊም ወርድና ስፋቱ አደራጅቶ መንቀሳቀስ ተገዷል።

ለብዙ ወራት ሲደረግ በነበረው ለውጥ ሳቢያ አገራችንን የተጠናወታት የጎሣ ፖለቲካ ችግር በገሃድ ፀረ አማራና ፀር አንድነት የሆነ ስታሊናዊ ቅርጽ ወይም ይዞታ አለው ማለት አይቻል ይሆናል። ሆኖም፣ በጠ/ሚንስትር አብይ አማላይ አንድነት ደጋፊ ንግግሮችም ባይሆን በጠ/ሚንስትሩ የገዢው ኢሕአዴግ ፓቲና መንግሥት መሪነት የኢትዮጵያ ክፍለ ሃገራት (የአካባቢዎች፣ የዞኖች፣ የወርዳዎችና የከተማዎች) መንግሥታዊ መስተዳደሮችና ተቋማት በአመዛኙ ከአንድ ጎሣ፣ በተለይ ከኦሮሞ፣ በፈለቁ ግለሰቦች የመያዝና የመሞላት ወይም ደግሞ በዘር የመሸንሸን አዝማሚያ እንደቀጠለ ነው። እዚህ ላይ የአዲስ አበባ እና የድሬ ደዋ ሁኔታዎች ጎልተው የሚታዩ ምሳሌዎች ናቸው። በተለይ አዲስ አበባን በሚመለከት እየተከሰተ ያለው ኩነት ለዘለቄታው አሳሳቢ ነው።

በጥቅሉ ለመናገር፣ በለውጡ ሳቢያ በየአካባቢው የመንግሥት፣ የባህል፣ የከፍተኛ ትምህርትና የሚዲያ ተቋማት በዘር ፖለቲከኞችና “አክቲቪስቶች” ምያዝ፣ እንዲሁም የማኅበረሰቦች መጋጨትና መፈናቀል፣ ተባብሰው መቀጠል የሚካድ አይደለም። እንደ አገር ከጎሣ ፖለቲካ ዞር ያልን ኢንጂ የሸሸን ወይም የራቅን አይመስልም። ይህ ሁኔታ ደግሞ በመሠረቱ ከኢሕአዴ የጎሣ ፖለቲካ ሥርዓት ቀጣይነት ጋር የተያያዘ ነው። በጠ/ሚንስትሩ ግለሰባዊ ዲስኩርም ባይሆን በኢሕአዴግ ፓርቲና መንግሥት አመራራቸው እስካሁን እየተኪያሄደ ባለው የሥርዓት ጥገና ለውጥ፣ ከአንድ ጎሠኛ-ወገንተኛ ቡድን የበላይነት ወይም አድራጊ ፈጣሪነት ወደ ሌላ ጎሠኛ ቡድን የበላይነት “እየተሸጋገርን” ይመስላል።

እንግዲህ የዛሬው አገራዊ የፖለቲካ ሥርዓት ቅየራ ንቅናቄ በመሠረቱ ይሚያነጣጥረው ምን ላይ እንደሆነ በደንብ ለይቶ ማወቁ ወሳኝ የመጀመሪያ የለውጥ እርምጃ ይመስለኛል። የዝች ጽሑፍ ዋና አላማ ለዚህ ዕውቂያ የተወሰነ አስተዋጽዎ ለማድረግ ነው። ብዙውን ጊዜ ስለ ነገዳዊና ባህላዊ ማኅበረሰቦች “ማንነት” ወይም “ራስነት” ስንናገር አውቀንም ይሁን ሳናውቅ በግብታዊ መንገድ በታሪክና በባህል የተሰጠ የጎሣ ማንነትን (ethnicityን) በእቅድ ከታነፀ ፖለቲካዊ ጎሠኝነት (political ethnicism) ጋር እንደባልቃለን። ይሄ ብዥታ የሥርዓታዊ ለውጡን እቅድ ጽንሰሃሳባዊ ጥራትና መርሃዊ ጥልቀት የሚነሳ ብቻ ሳይሆን ለውጡ በሚገባ ከመሬት እንዳይነሳ የሚያደርግም ነው።

ነገዳዊ/ባህላዊ ማኅበረሰብ ከፖለቲካ ይተልቃል፤ ምንም አይነት ፓርቲ በብቸኝነት ውይም በመኖፖል አጠቃሎ ሊወክለው አይችልም። ስለዚህ ነገድን ወይም ዘርን በጥቅሉ ከተወሰኑ ዘር ተኮር የፖለቲካ ዉከላ ድርጅቶች፣ እቅዶች፣ ህንፀቶችና ትርክቶች በግልጽ መለይቱ አስፈላጊ ነው። ይህን ማድረግ፣ አያይዞም ፖለቲካን በገደብ መያዙ፣ በአገር አድን የሥርዓት ቅየራ ትግሉ ስልታዊ ግዳጅ ብቻ ሳይሆን ከመርህ አኳያም የኢትዮጵያ ብዝሃን ማኅበረሰቦችን የተለያዩ ባህላዊ ራስን በራስ አተያዮች ማክበር ነው። አገራዊ አንድነታቸውንና ዲሞክራሲያዊ አስተዳደራቸውንም ይበልጥ ማመቻቸትና ማረጋገጥ ነው።

እንግዲህ የዛሬው የሥርዓት ለውጥ ኢላማ በጥቅሉ ወይም በድፍኑ የጎሣ ማንነት ወይም ልዩነት አይደለም ማለት ነው። እንደ አገር የገጠመን ውዝግብና ሥርዓተ አልበኝነት፣ በተለይ በያካባቢው የሕዝብ መፈናቀልና መሰቃየት፣ በቀጥታና ባንዳፍታ ከነገዶች ማንነቶች ወያም ልዩነቶች ጋር የተያያዘ አይደለም። ባመዛኙ ችግሮቻችን ከተወሰኑ ጎሣ ተኮር ወገንተኛ የፖለቲካ አመለካከቶች፣ ትርክቶች፣ አቀራረጾች፣ እቅዶችና እንቅስቃሴዊች የፈለቁ እንደሆኑ እንገነዘባለን። እነዚህ ነገሮች ደግሞ እንደ ዘር ወይም ቋንቋ ወይም የቆዳ ቀለም የማይለወጡ ሆነው በተፈጥሮ የተሰጡ አይደሉም። ይልቅስ፣ እንደ ፖለቲካ ሠራሽነታቸው፣ ቢያንስ በእምቁ ለክርክር፣ ለድርድርና ለለውጥ ክፍት ናቸው። በቅን ልቦና፣ ክፍት አእምሮና ተጨባጭ ትንተና የተደገፈ ምክንያታዊ ውይይት ተደርጎባቸው ሊሻሻሉ ወይም ውድቅ ሊደረጉ የሚችሉ ገጽታዎች ያሏቸው ናቸው።

ከዚህ አንጻር ስለ ለውጡ አኪያሄድ መዋቅራዊነት ስናገር የማንነት ፖለቲካ ያለውን ከጥሬ ዘረኝነትና ድርጅታዊ ወገንትኝነት ያለፈ ፓራዳይማዊ ውይም ሥርዓታዊ ቅርጽና ይዘት ታሳቢ በማድረግ ነው። የፖለቲካ ቅርጽና ይዘቱ፣ በተለይ በጥልቅ እንከናማ የሆነው የብሔር (የዘር) “ነፃነት” ወይም “ራስን በራስ ወሳኝነት” እቅዱ፣ የተለያዩ ነባር አብዮተኞችና ጎሠኛ ፓርቲዎች ከሞላ ጎደል የተጋሩትና ዛሬም የሚጋሩት አውታር ነው። በርዝራዡም ቢሆን ስታሊናዊ የአስተሳሰብ፣ የአነጋገርና የገቢር ልምድ ስለሚያንጸባርቀው ይህ “አብዮታዊ” የፖለቲካና ርዕዮት አውታር አንድ ዋና ነገር እንገነዘባለን። ይኸውም ጥልቅ ታሪክ ካለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሥልጣኔም ሆነ ዜግነት ላይ ከተመሠረተ ዘመናዊ ኢትዮጵያዊነት ጋር ምንም ያህል ተጣጥሞ አለማወቁን ነው።

ይህ የአብዮተኝነት ወይም ተራማጅነት ባህላችን አረዳድ በዛሬው የሥርዓት ለውጥ ጉዞ ምን አይነት አዲስ አቅጣጭ መያዝ እንደሚያስፈልገን ሊያመላክተን ይችላል። ማለትም፣ እንደተለመደው አስመሳይ ሳይሆን እውን ዲሞክራሲ በእትዮጵያ ለመገንባት ስናልም በአስተሳሰብ፣ በአነጋገርና በተግባር ከምን አይነት ነባር የፖለቲካ ባህል ተነስተን፣ ምን ምንን የለውጥ ኢላማ አድርገን፣ ወዴት ማቅናት እንዳለብን ሊያሳሳበን ይችላል። አገራዊነታችን የለውጡ መነሻም መድረሻም መሆኑን የሚያስታውሰን ነው። የተሻለ፣ ዘላቂ፣ አማራጭ የፖለቲካ ሥርዓት ለማቋቋም ያበቃንም ይሆናል።

ጎሣ የፖለቲካ ውቅር መሆን

በተማሪው ንቅናቄ ጊዜ የተጀመረውንና በተለይ በወያኔ ዘመነ አገዛዝ ተንሰራፍቶ የቀጠለውን የማንነት ፖለቲካ አወቃቀር ጠለቅ ብሎ መገንዘብ ዋና ነገር ነው ምክንያቱም ውቅሩ በእቅድና በቀጥታ በፈጠራቸው ሁኔታዎችም ሆነ በተዘዋዋሪ ተርፈ ውጤቶቹ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ላይ እስከ ዛሬ አሉታዊ ተጽእኖውን ቀጥሏል። በአንድ መንገድ ወይም በሌላ በአስሮች ሚሊዎኖች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ዜጎችን አገራዊም ይሁን አካባባዊ የለት ተለት ኑሮ በዘር ጉረኖዎች የከለለ፣ ያፈነ፣ የጨቆነ፣ ያዛባና በየጊዜው ያፈናቀለ ነው። የጎሣ መዋቅሩ በታሪክና ባህል የተሰጠ የነገድ ማንነትን ወይም ራስነትን በቅጡ ባልተብላላና ጠልቆ ባልዘመነ ፎርሙላዊ የፖለቲካ እሳቤ አወላግዶ፣ አጋኖና ከአገር አንድነት ጋር አቃርኖ ያቀደ፣ ያነፀና ያስፋፋ ነው። ስለዚህም ነው የሥርዓታዊ ለውጥ ኢላማ መሆን ያለበት።

የፖለቲካ ልምዱ በአብዮቱና በውያኔ አገዛዝ ዘመናት የደለበ ቢሆንም ቅድመ አብዮታዊ ፍልቀት አለው። በኢትዮጵያ ፀረ አንድነትና ፀር አማራ የዘር ፖለቲካ ምንጮች ወይም ግብአቶች የአብዮቱን ዘመን ቀድመው በአውሮፓ ሚሲዮኖች፣ ቅኝ ገዢዎችና እንደ ሮማን ባሮን ፕሮቸስካ ባሉ የፋሽስት ወረራ አነሳሾች የተደረጉ እንቅስቃሴዎች እንደነበሩ ታሪክ ዘግቧል። ከጥንት ጀምሮ የኢትዮጵያ አካል በነበርችው በኤርትራም በኩል ቢሆን የትግሬ ዘር ላይ ያተኮረ፣ ባመዛኙ ፀረ አማራ የነበረ፣ ተገንጣይ ብሔርተኝነት መነሾ የሆነው የጣሊያን ቅኝ አገዛዝ ቅርስ እንደነበረ ይታወቃል።

በኢትዮጵያ የባህላዊ-ብሔራዊ ሥልጣኔ እድገት፣ የዘመናዊ መንግሥት አፈጣጠርና የዓለም አቀፉ ከበርቴ ሥርዓት ተጽእኖ የተሟሉና የተመጣጠኑ ሳይሆኑ ክፍተታማና ወጣ ገባ የነበሩ መሆናቸው አገሪቱን ለኋልዮሽ ጎሠኛ ዘመነ መሳፍንት ወይም የዘርና ያካባቢ ባላባታዊነት ወረርሽኝ አመቻችተዋል። ለወረርሽኙ የአገሪቱ አብዮተኛ ተማሪዎችና ምሁራን ያስፋፉት “ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች” በሚል ስታሊናዊ የፖለቲካ ሰዋሰውና ቃላት የተዋቀረ የፖለቲካ አስተሳሰብ አንድ ዋና ምክንያት እንደነበር የሚካድ አይደለም። አስተሳሰቡ ቅድመ አብዮታዊ ፍልቀት የነበረውን ፋሺስታዊ የጎሣ ፖለቲካ እቅድ በተለየ ኮምንስትዊ አውታር መልሶ ቀርጿል። ይህን በማድረግም ለአገር መከፋፈሉ ሂደት በእቅድም ይሁን በውጤት አስከፊ አስተዎጽዎ አድርጓል።

እንግዲህ፣ ዛሬ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን እንደ አረም የዋጠው የጎሣ ፖለቲካ በፍልቀቱ ጥሬ ዘረኘነትን አልፎ በተለያዩ የፖለቲካ ኅይሎችና ወገኖች የተጠነሰሰ፣ የታነፀና የተስፋፋ እንደነበር እንረዳለን። ተራ ጎሠኝነትን ተሻግሮ የአምባገነናዊ አገዛዝ ሥርዓትና የወገንተኛ ፖለቲካ ውቅር ወይም ህንፀት እንደነበረ፣ ዛሬም እንደሆነ እንገነዘባለን። ቃል በቃል ወይም በርዕዮት እንደተተረከው፣ የፖለቲካው አላማና እቅድ የብሔር (የጎሣ) “ነፃነት”፣ “ዲሞክራሲ” እና “ራስን በራስ ወሳኝነት” ነበር፤ ነውም። ሆኖም፣ ፖለቲካው በእውን ሁሉን አድራጊ ፈጣሪ ነኝ ባይነቱ፣ እንዲሁም በሃሳብ ይዘቱና ገቢሩም ለአገራዊ አንድነትና ሉአላዊነት ብቻ ሳይሆን ለአካባቢዎች አንጻራዊ ነፃነትም ምንም ግድ የሌለው አምባገነናዊነት አንጽባርቋል።

እርግጥ ያለንበት ጊዜ ሥርዓት ጠጋኝ የፖለቲካ ለውጦችና መሻሻሎች ይታዩበታል። ሆኖም የጠ/ሚንስትር አቢይ አሕመድ አመራር ባልተጠበቀ መንገድ ከገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ውስጥ መውጣቱና የተወሰኑ ወቅታዊ የጥገና ለውጦች ማድረጉ የግድ የፖለቲካ ልምዱን ጥልቅ መዋቅራዊ ብልሹነትና አገር አሰናካይነት በሚገባ ተረድቶ ለመሠረታዊ የሥርዓት ቅየራ ተነስቷል ማለት አደለም። ዘር ተኮር ከሆነው ኢሕአዴግ የፈለቀው የጠ/ሚንስትር አብይ አመራር ጎሣን ከወገንተኛ ጎሠኝነት ለይቶ የማስቀመጥ አስፈላጊነት ታይቶታል የሚል ግድ ድምዳሜ አያስከትልም። ወይም ደግሞ በጠ/ ሚንስትሩ ዋና አላፊነት ቀጣይ የሆነው ኢሕአዴግ፣ እንደ ጎሣ ተኮር ድርጅት፣ ይህን ማድረግ የሚያስችለው የፖለቲካ ግንዛቤና ፈቃደኝነትም ሆነ አቅም አለው ማለት አደለም። እንዲያውም ድርጅቱ ራሱ በጎሣ ፖለቲካ አራማጅ ወኞች ስብስብነቱ በተጨባጭ የአገር አለመረጋጋትና ሽብር ምንጭ ስለሆነ በሥርዓታዊ ለውጡ ሂደት መፍረስ ያለበት ነው።

ከዝህ አኳያ፣ በሕወሓት-ኢሕአዴግ ዘመነ አገዛዝ፣ የጎሣ ማንነት ሁከትና ውዝግብ በተሞላበት መንገድ የወገንተኛ ፖለቲካ ዉቅር ወይም ፈጠራ የሆነባቸው የተለያዩ መሣሪያዎች ወይም ዘዴዎች ምን ምን እንደሆኑ ለይቶ ማወቁ ጠቃሚ ነው። ዘዴዎቹ ተራማጅ የተባሉ ውስንና ዝግ ትርክትን፣ ሃሳብን፣ እቅድን፣ ዲስኩርንና ድርጅታዊ ልምድን ያካትታሉ። ዝርዝር ሐተታ ውስጥ ሳንገባ እዚህ ትርክትን ባጭሩ መቃኘት ይበቃል። ሌሎቹን አወዛጋቢ የጎሣ ፖለቲካ ቅርጽ አውጪ መሣሪያዎች እዚህ በጥቅሉ የትርክት ግብአቶች ወይም ጎኖች አድርገን ልንወስዳቸውም እንችላለን።

ትርክት፣ ዘር እና ፖለቲካ

ማኅበራዊ ኑሮ እንዳለ በትርክት የተሞላ ነው። በዓለማዊና መንፈሳዊ ረድፎች ማኅበራዊ እምነቶች ተቋማትና ገቢሮች የሚጠበቁትና ቀጣይ የሚሆኑት፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ተሸጋጋሪ የሚደረጉት፣ በተረታዊ-ባህላዊ አነጋገርና ገለጻ (በstorytelling) ነው። ትርክት ጋዜጠኞች ወይም ታሪክ አጥኚዎች በሚያደጉት መልክ ዝምብሎ ተጨባጭ መርጃዎች ዘጋቢ አይደለም፤ ባህላዊ እሴቶችና ትርጉሞች ፈጣሪም ስለሆነ በቀላሉ እውነት ነው ወይስ ውሸት ተብሎ የሚፈረጅ አይደለም። ትረካ ያለፉ ገጠመኞችን፣ ድርጊቶችንና ሁኔታዎችን ትርጉም ሰጪ ብቻ ሳይሆን አያይዞም ወደፊት ተመልካች ሃሳቦችን፣ አላማዎችንና ምኞቶችን አፍላቂ ሊሆንም ይችላል።

ስለዚህ ትርክት በጥቅሉ በሰው ልጆች ኑሮ ያለ ነገር ነው፤ የተጨባጭ ማኅበራዊ፣ ባህላዊና አገራዊ ሕይወት ዋና አካል ነው። የኢትዮጵያ ነገዶች በረጅም ታሪክ ሂደት ባደረጉት ከቦታ ወደ ቦታ ዝውውር፣ ግንኙነትና የተጽዕኖ ልውውጥ መጠን የአካባባዊና አገራዊ ትርክቶችና የተያያዙ ባህሎች ከሞላ ጎደል ተጋርተዋል። በአስራ ስድስተኛው ምእተ ዓመት ኦሮሞች ከደቡብ ኢትዮጵያ፣ ቦረና፣ አካባቢ ተነስተው ወድ ሰሜን ኢትዮጵያ እስክ ወሎ ድረስ፣ ወደ ምስራቅ ደግሞ እስከ ሐረር ባደርጉት ተስፋፊ ዝውውርና ሰፈራ ከሌሎች የአገሪቱ ነገዳዊ ማኅበረሰቦች ጋር መቀየጣቸውና መሰባጠራቸው የዚህ ሁኔታ ዋና ምሳሌ ነው። ሁኔታው ለኢትዮጵያ ወደ አንድ ነገደ ብዙ አገር መለወጥ ከፍተኛ አስትዋጽዎ አድርጓል።

ሆኖም በፖለቲካዊ ገጽታው ተረታዊ አነጋገር አይነት አይነት አለው። ትርክቶች ከፖለቲካ ጋር ያላቸው ወይም ሊኖራቸው የሚችል የግንኙነት መጠንና አይነት ይለያያል። የማንነት ፖለቲካ ተረታዊ ገለጻዎች በግብታዊ መንገድ ራሳቸውን በራሳቸው አያፈልቁም። ይልቅስ፣ የተለያዩ ተራች ወገኖችና ስብስቦች (ለምሳሌ፣ ወያኔዎችና ኦነጎች) ከተወሰኑ የተጎጅነት ስሜቶች እና ብቸኛ ወገንተኝነት ተነስተው የተወሰኑ ዘር ተኮር የብሔርተኝነት እቅዶች የሚቀርጹባቸው መሣሪያዎች ናቸው።

ትርክታዊ ገለጻዎቹ ከተጨባጭ ታሪካዊ መረጃዎችና እውነታዎች ጋር ያላቸው ግንኙነትም እንዲሁ ይለያያል። አንዳንዶቹ ከእውን ታሪካዊ መሠረት ወይም ዕውቀት የጸዱ፣ ባመዛኙ ንጹህ የፖለቲካ ቀመሮችና ፈጠራዎች ናቸው። በጣም ወርደው የደናቁርት ወጎች ከመሆን የማያልፉም አሉ። አፄ ምኒልክ ጡት ቆረጡ የሚለው ወራዳ ትረታ (እና ሃውልት ግንባታ) የዚህ አይነት ተራ ፕሮፓጋንዳ ፈጠራ አንድ ምሳሌ ነው።

ነገር ግን የእውነታ ይዘታቸው አነሰም በዛም፣ በኢትዮጵያ የጎሣ ፖለቲካ ትርክቶችን ከሚያተኩሩባቸው፣ ማለትም “ብሔሮች” ወይም “ብሔረሰቦች” ብለው ርዕዮታዊ ስያሜና ምስል ከሚሰጧቸው፣ ተጨባጭ ነገዳዊና ባህላዊ ማንነቶች በግልጽ መለየት ያስፈልጋል። እዚህ ላይ የተለመደው የጎሣ ማንነት ዲስኩር ስህተት አምባገነናዊ የፖለቲካ ኮድ አዘል ትርክትን ወይም ርዕዮታዊ ስያሜን ከማኅበራዊ እውነታ ጋር ማመሳቀል ነው። በዛሬው አገራዊ የሥርዓት ለውጥ ንቅናቄ፣ ይህን መምታታት ማስወገድ ማለት ውዝግብ የሚነሱባቸውና መለወጥ ያለባቸው ነገሮች ምን ምን እንደሆኑ ያለምንም ብዥታ ጠንቅቆ መለየትና ማወቅ ማለት ነው።

በተጨባጭ ታሪካዊ ልምድ የተገነባ ኢትዮጵያዊነትና ባህላዊ ትርክቶቹ ዘመናዊ ዜግነት ላይ ከተመሠረተ አገራዊነትም ሆነ ከአካባቢዎች ራስ ገዝነት ጋር የግድ ተጋጪ አይደለም። ይልቅስ የፊተኛው ከኋለኛው ጋር ተመጋጋቢና ተደጋጋፊ ነው። ባህላዊነትና ዘመናዊነት፣ አገራዊ አንድነትና ነገዳዊ ብዝሃንነት ተወራራሽና ተደራራቢ ስለሆኑ፣ይበልጥ ሊሆኑም ስለሚችሉ፣ ግንኙነታቸው “የዜሮ ድምር” ጨዋታ አይደለም። ማለትም፣ የአንድነት ትርፍ ወይም ጥቅም የብዝሃንነት ኪሣራ ወይም ጉዳት አይደለም፤ የኢትዮጵያዊነት መሟላት የግድ የነገዳዊ ራስነት መጓደል አይሆንም። የአንዱ እሴት መለምለም የግድ የሌላው እሴት መጠውለግ አይሆንም።

ነገር ግን ኢትዮጵያ ጎሣዊ ብዝሃንነትን የምታካትት መሆኗን መቀበልና ማረጋገጥ የኢትዮጵያ አገራዊ ማንነት በአይነትና ደርጃ ከጎሣ ማኅበረሰቦች የቁጥር ድምር ያለፈና የላቀ መሆኑን መርሳት ወይም ሆን ብሎ ችላ ማለት አይደለም። በነገዳዊና ባህላዊ ብዝሃንነት የለመለመችው ኢትዮጵያ መልሳ መላ ዜጎቿንና ማኅበረሰቦቿን በወጥ የጋራ ብሔራዊ ሥልጣኔና ታላላቅ ታሪካዊና ባህላዊ ክንውኖች ያተለቀችና ያበለጸገች አገር ናት። እንዲሁም የተለያዩ ነገዳዊና አካባብዊ ማኅበረሰቦቿ ዘመን አመጣሽ፣ አገር አቀፍ፣ አብዮታዊ ልምድም በወል ተጋርተዋል፣ የአብዮቱ አመራርም ሆነ አኪያሄድ ወይም ውጤት በጀም አልበጀም።

እንግዲህ ከማኅበረሰቦች እውን ማንነቶች አንጻር የፖለቲካ ትርክቶችን በሚመለከት ዋናው ነጥብ ማንነቶች በተወሰነ መጠን ለአማራጭ የትረካ ቀረጻዎች ወይም አተርጓጎሞች ክፍት መሆናቸውና አገራዊ ክርክርና ድርድር ጋባዥነታቸው ነው። ለምሳሌ ከጥግ ያዢነት ቁርኝት ራሱን ማላቀቅ ያልቻለው ኦነግ ሙጥኝ ብሎ የያዘው ያረጀ ያፈጀ “የኦሮሞ ብሔራዊ ነፃ አውጪ” ፖለቲካ ቢያንስ በእምቁ ለጥያቄ፣ ለውይይትና ለመሠረታዊ ለውጥ ክፍት መሆኑ የሚካድ አይደለም። ሆኖም ፖለቲካው እንዳለ ይህ አይነት ተጨባጭ ክፍትነት ቢኖረውም እንደ ዳውድ ኢብሳ ያሉ ኦሮሞን ነፃ አውጭ ነን ባዮችን በምክንያታዊ ውይይት ለማግባባት መሞከር ባመዛኙ ድንጋይ ላይ ውሃ ከማፍሰስ ተለይቶ የሚታይ አይደለም።

ከጽንሱ ከኢትዮጵያ አንድነት ጋር የተቃረነው የኦነግ ዘር አክራሪ ፖለቲካዊ አነሳስና አኪያሄድ አማራጭ ያልነበረውና ዛሬም የሌለው ፍጹም የኦሮሞ ትረካ ነው የሚባል ሳይሆን ከሌሎች ዘር ተኮር የሆኑም ያልሆኑም ተቻይ የኦሮሞ ፖለቲካዊ ትረታዎች አንዱ ብቻ መሆኑ ነው። የኦሮሞ ማኅበረሰብ ታሪካዊ-ባህላዊ ማንነት ያለምንም ቀሪ ተጠቃሎ በኦነግ ወይም በሌላ የኦሮሞ ፓርቲ ትረካ ሊወሰንና ሊጣጣ አይችልም። በዚህ አይነት ወገንተኛ የጎሣ መሃንዲስነት “ራስ ውሰና” መሞከር ከጅምሩ “ነፃ ወጪ” የተባለውን ማኅበረሰብ የተገላቢጦ ለፖለቲካ ባርነት፣ በተለይ ለአንድ ፓርቲ አምባገነናዊ ጭቆና ፣ማመቻቸት ነው የሚሆነው። ሙከራው አንድን ሙሉ ማኅበረሰብ አሳንሶና አጓድሎ የፖለቲካ ድርጅት ተቀጥላና ጥገኛ ማድረግ ነው። በሕወሓትና በትግራይ ማኅበረሰብ መካከል ያለው የፖለቲካ ትረታ ግንኙነትም በዚሁ መልክ የሚታይ ነው።

ስለዚህ የኦነግ ብቻ ሳይሆን የሕወሓትና የሌሎች ጎሣ ተኮር ወገኖች ስታሊናዊ “የብሔራዊ ነፃነት” አስተሳሰብ፣ አነጋገርና ገቢር መዋቅር በተቃርኖዎች የተሞላ እንደሆነ እንገነዘባለን። እዚህ አንድ መሠረታዊ ተቃርኖውን መጠቆም ይበቃል። የኸውም፣ ፈሩን የለቀቀውና የተትረፈረፈው ፖለቲካ ወደ አገሪቱ ነገዳዊና ባህላዊ ማኅበረሰቦች ሰርጎም ሰርስሮም በመግባት ማንነታቸውን ከውስጥ ነጂና ጠምዛዥ ሆኗል። ይህ መዋቅራዊ ገጽታውና ባህሪው “ብሔሮች” ለሚላቸው የኢትዮጵያ ነገዳዊ ማኅበረሰቦች በኦፊሴላዊ ዲስኩር የሚሰጠውን “ነፃነት”፣ “ዲሞክራሲ” እና “ራስን በራስ ገዢነት” በተግባር ውድቅ አድርጓል። ይህ በጥልቅ የተዛባ፣ ቃል በቃል የሚለውን በእውን አድርጎ የማያውቅና የሚመስለውን ከሆነው ጋር ጨርሶ ያጻረረ “ተራማጅነት” በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በኤርትራም ያየነው ነው።

በፖለቲካ ዲስኩር በተገለጽ እቅድም ባይሆን በተጨባጭ ዉጤት እንግዲህ የኢሕአዴግ-ሕወሓት የጎሣ ፖለቲካ ሥርዓት የእውን ማኅበረሰቦች ነፃ አውጪ መሆኑ ቀርቶ ወኪል ሆኖ እንኳን አያውቅም፤ ሃቀኛ የውክላ ተግባርን ከጅምሩ ያገለለና የራሱ ልጥፍ ወይም ተጥላ ማኅበራዊ ይዘት የነበርው ነው። የተገላቢጦ፣ ሥርዓቱ ብቸኛና አምባገነናዊ የማንነት ቅርጽ አማሮች፣ ኦሮሞዎች፣ ትግሬዎችና ሌሎች የአገሪቱ ነገዳዊ ማኅበረሰቦች ላይ ጭኗል። የማኅበረሰቦቹ እውነተኛ አንጻራዊ ነፃነት ወይም ዲሞክራሲያዊ ራስን በራስ አስተዳዳሪነት ለዘር ተኮሩ ፈላጭ ቆራጭ ያገዛዝ ሥርዓት አላስፈላጊ የነበረ ብቻ ሳይሆን በጽንሱና መሠረቱ ሥርዓቱን ተቃራኒና (በእምቁ) አፍራሽም ነው።

የኢትዮጵያ አካባባዊና ባህላዊ ማኅበረሰቦች በብሔራዊ ራስ ወሳኝነት ስም የተጨቆኑት እንግዲህ ነፃ ማውጫቸው በተባሉ የርዕዮት፣ የዲስኩር፣ የትርክት፣ የድርጅትና የጦር መሣሪያዎች አማካኝነት ነበር። የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ መልክ ከተጫነበት ከፋፋይ፣ አጋጪና አፈናቃይ የማንነት ፖለቲካ ቀንበር ዛሬ አካቶ አልተላቀቀም። የሥርዓት ጥገናና ማሻሻያ ለውጦች የተደረጉ ቢሆንም የኢትዮጵያ ህዝብ ከስሮ አገር አክሳሪ ከሆነ የዘር ፖለቲካ ጨርሶ ነፃ አልወጣም። መናድ ያለበት ዘውግ ተኮር የኢሕአዴግ/ሕወሓት አገዛዝ መዋቅር ገና አልተናደም።

የኢትዮጵያ ነፃነት፣ ድህንነትና ልማት ለመላ ዜጎቿና ነገዳዊ ማኀበረሰቦቿ ሰላም፣ መረጋጋት፣ ራስ ገዝነትና ብልጽግና አስፈላጊ ናቸው። አገራችን በፖለቲካ በሽታ ተይዛ አካባቢዎቿ በጤና አይኖሩም። በሌላ በኩል፣ አካባቢዎቿ በሆነ ባልሆነ ብቸኛ የጎሣ ብሔርተኝነትና በአስመሳይ የዘር “ፌደራላዊነት” እየታመሱ ኢትዮጵያ ሰላምና ደህንነትም ሆነ በቅጡ የተማከለ አገራዊ መንግሥት ሊኖራት አይችልም።

ዘረኛ ብሔርተኝነት ነገዳዊ ማንነትን በጠባብ ወገንተኛ ፖለቲካ ከልሎ ያዥ በመሆኑ በከለለው ክፍለ ሃገር ኗሪ የሆኑ ከሌሎች ነገዶች የፈለቁ የአገሪቱ ዜጎችንና ማኅበእሰቦችን በዉጨኛነት የማየት፣ የማግለል፣ የማጉላላትና የማፈናቀል አዝማሚያ የነበረውና ዛሬም ያለው ነው። በሕወሓትና በኦነግ ልምድ እንደታየው አዝማሚያው ከጎሣ መሃንዲስነት ጋር የተያያዘ ጠብ ጫሪነትንና አጥቂነትን፣ ህዝብ ለህዝብ አጋጭነትን፣ ብሎም የማይረጋ የዘር ክልል አስፋፊነትን ያካትታል። ይህ ሁኔታ የተፈጠረው በቀጥታና ባንዳፍታ በትግሬ ወይም በኦሮሞ ማኅበረሰባዊ ማንነት አይደለም። ይልቅስ፣ ማንነቱን በተጫኑ የተወሰኑ ወገንተኛ የፖለቲካ ቅርጾችና አምባገነናዊ የጎሣ ብሔርተኝነቶች ነው። ስለዚህ በሥርዓት ለውጥ ትግሉ እነዚህን ምንጊዜም አገር አውዛጋቢ ጭነቶች በስልታዊ አቀራረብ ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃ ማውረድ ግድ ይላል።

ዜግነት ላይ የቆመ ‘ዲሞክራሲያዊ ‘ አገራዊነት?

ለኢትዮጵያ የፖለትካ ምህዳር በጎሣ ክልሎች መከፋፈል፣ መጣበብና መጨናነቅ መፍትሔው ነገዳዊነትን ዝምብሎ ወደ ጎን ትቶ ዜግነትን (ስቪክ ብሔራዊነትን) ብቻ የመንግሥት አደራጅ መርህ ማድረግ ለዘረኛ ፖለቲካ በሽታችን ፍቱን መድኃኒት ይመስላል። ሆኖም፣ ስቪክ ብሔራዊነት እንዲህ በቀላሉ ለነገዳዊ ማንነትም ሆነ ለታሪካዊ-ባህላዊ አገርነታችን ተተኪ ወይም አማራጭ ሊሆን አይችልም። ዘመናዊ ዜግነት እርግጥ አንድ ዋና የኢትዮጵያዊነት ምሰሶ ነው፣ ወይም መሆን አለበት። አብረዉት የሚሄዱ የስቪክ መብቶችና ግዴታዎች በታሪካችን ታይቶ በማይታዎቅ መልክና መጠን ዛሬ መረጋገጥና መከበር እንዳለባቸው ግልጽ የመስለኛል።

ይሁን እንጂ፣ ወዲያና ወዲህ እንደሚወዛወዝ የግድገዳ ስዓት ዘንግ ከአንድ ጽንፍ (ከጎሣ ፖለትካ ጥግ) ወደ ሌላ ጽንፍ (ወደ ንጹህ ዜግነት ጥግ) ባንዴ ጅው ማለት እውን አማራጫችን አይደለም። ዜግነት በጽንሰሃሳብ፣ በመርህና በገቢር ለችግራችን ቀድሞ ዝግጁ ሆኖ የቀረበልን “መፍትሔ” ሳይሆን ራሱ የፖለቲካ አስተሳሰብና ሥርዓት ለውጥ ንቅናቄ ክንውን መሆን የሚያስፈልገው ነው። በራዕይና እቅድ የለውጥ ትግሉ መነሻችን ብቻ ሳይሆን በዉጤት መድረሻችንም ነው። የኢኮኖሚ እድገትና ልማት ወይም የሥርዓት ቅየራ ቅድመ ሁኔታ ሳይሆን፣ በልማት ሳቢያ ግለሰቦች በጎሣ ክልሎች ሳይገደቡና ሳይተጓጎሉ በመላ አገሪቱ በሚያደርጉት የሥራና የኑሮ ዝውውር መዳበርና መጠናከር የሚችል ነው።

አለዚያ፣ ለአገር ከፋፍይና አሰናካይ የጎሣ ፖለቲካ በሽታችን ፈውሱ የስቪክና ፖለቲካ መብቶች “መከበር” ነው ማለት በጠና የታመመ የጎዳና ተዳዳሪ ሰውን ‘ከሕመሙ የሚያላቅቀው መድኃኒት ነው’ ከማለት ብዙ አይለይም። የሰውዬው ጣጣ የመድኃኒትእጦት ስለሆነ፣ ችግሩ ፈዋሽ ሕክምና ማግኘት ስለሆነ፣ በረቂቁ ወይም በድፍኑ ለሕመሙ መፍትሔው መድኅኒት ነው ማለቱ ተጨባጭ ትርጉም የለውም።

በተመሳሳይ መንገድ፣ የማንነት ፖለቲካን ውጥንቅጥ ጣጣዎች መወጫችን በድንብ ኖረውን የማያውቁ ስቪክና ዲሞክራሲያዊ (የዜግነት) መብቶች “መከበር” ሳይሆን ቀድሞ የነዚህ መብቶች ለዘለቄታው መቋቋም እና መኖር፣ ማለትም በተመጋጋቢ መርሃዊ፣ ተቋማዊና ተግባራዊ ደረጃዎች መቀረጽ፣ መረጋገጥና መጠናከር ነው። ያም ሆኖ በዓለም ዙሪያ የማንኛውም ህዝብ ብሔራዊ ሕይወት በዜግነት መብቶች ላይ ብቻ የተመሠረተና የተገነባ አይደለም። እንኳን እኛ ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት ያላለማን አገር ሥርዓቱን ያዳበሩ አገሮችም ከዘር ወይም ከባህል ማንነት አካቶ የተገለለ ንጹህ “ስቪክ” ብሔራዊነት ያቋቋሙ ናቸው የሚባሉ አይደሉም። እንዲ አይነት የአገር ማቅናት ወይም ግንባታ ሂደት በታሪክ ታይቶ አይታወቅም።

ሌላው ነገር ደግሞ በዘር፣ በባህል፣ በሃይማኖት ወይም በቁጥር ያነሱ ወገኖች ውስጥ የተካተቱ ግለሰቦች ለወጉ የአንድ አገር “ዜጎች” መሆናቸው በዚያ አገር ውስጥ በእውን እኩል/ሙሉ የዜግነት መብቶች ያገኛሉ ማለት አይደለም። ለምሳሌ ሃያ በመቶ ያህል የሚሆኑ የእስራኤል “ዜጎች” አይሁዶች ሳይሆኑ አረቦች ናቸው፤ ሆኖም የእስራኤል መንግሥት በግልጽ የተቋቋመው በተለይ የአይሁድ ዘር ላላቸው ግለሰቦችና ስብስቦች ነው። በሌላ በኩል፣ በእስራኤል አይሁድ መሆን ብቻ በዚያች አገር ለተሟላ እስራኤላዊ ዜግነት በቂ ምክንያት እንዳልሆነ ይታወቃል። እዚህ ላይ፣ ከኢትዮጵያ የተወሰዱ/የሄዱ አይሁዶች (ፈላሻዎች) ብዙውን ጊዜ ለእኩል እስራኤላዊ “ዜግነት” አለመብቃት በነገዳዊ ማኅበረሰቦች መካከል እኩልነት ያለመኖርን ችግር ይሚያሳይ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ የጥቁር አሜሪካዊያን ዜግነት መብቶች ብዙውን ጊዜ በዘር ምክንያት በሚገባ አለመከበርም የዚሁ የእኩልነት እጥረት ሌላ ምሳሌ ነው።

ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ፣ ዘርም ማኅበራዊ መደብም በዲስኩር ወይም በወረቀት (“በሕገ መንግሥት”) ቃል በቃል የሰፈሩ የግለሰብና የዜግነት መብቶችን በእዉን ዋጋ እንድሚያሳጧቸው፣ ፍሬ ቢስ እንድሚያደርጓቸው ዛሬም በዘመነ “ለዉጥ” የምናየው ነው። ባለፈው ሰሞን በኑሮ ደረጃቸው መለስተኛና ዝቅተኛ በሆኑ በአዲስ አበባ የአራት ኪሎ ኗሪ ኢትዮጵያዊያን ላይ የደርሰው አስከፊ ከየቤታቸው መፈናቀልና የጎዳና ተዳዳሪ መደረግ የዚህ አይነት ግዙፍ የዜጎች መብቶች ጥሰት የጎላ መገለጫ ነው። ወጣቶችና አረጋዊያን ብቻ ሳይሆኑ ህፃናት ጡት የሚያጠቡ እናቶች ላሉባቸው እነዚህ እውን ተፈናቃይ ዜጎች በፖለቲከኞችና ሊህቃን ተብዬዎች መካከል የሚደረግ “ዜግነት” ላይ ያተኮረ “ረቂቅ” ዲስኩር ፈሬ ቢስ ነው። ረቂቅነቱም ዝምብሎ በአነጋገር ቀመር ወይም ዘይቤነት እንጂ በጽንሰሃሳብና መርህ ደረጃ በጥልቀት ታሳቢ በመሆኑ አይደለም።

የኢትዮጵያን አገራዊ እድገትና ተቻይ የግለሰቦችና ዜጎች መብቶች መዳስበርን የሚመለከት አንድ ዓለም አቀፍ አዝማሚያ አለ። ይኸዉም፣ የስቪክና ፖለቲካ ነፃነቶች በታሪክ ሂደት ያሳደጉ አብዛኞች ዲሞክራሲያዊ መንግሥታት የተገነቡት ቀድመው የነበሩ አገራዊ ማንነቶች ውይም መንግሥታዊ ሥርዓቶች ላይ ተመሥርተው ነበር። ለእኩል ዜግንትና ለዲሞክራሲ መዳበር መነሻ የነበሩት አገራዊ ማንነቶች ራሳቸው በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተፈጠሩ ሳይሆኑ የረጅም ዘመናት ባህሎች፣ ልምዶች፣ ውጊያዎችና የፖለቲካ ትግሎች ውጤቶች ነበሩ። ምሳሌዎች ቢያስፈልጉ፣ከአውሮፓ የጀርመን፣ ፈረንሳይና እንግሊዝ አገሮችን ተመክሮዎች መጥቀስ ይቻላል። ዲሞክራሲያዊ ሆነም አልሆነም ዘመናዊ የፖለቲካ ብሔርተኝነት ነባር ታሪካዊ-ባህላዊ አገርነትን (ለምሳሌ፣ ቻይናዊነትን፣ ጃፓናዊነትን ወይም ኢትዮጵያዊነትን) ሊለውጥና ሊያሽሻል እንጂ ሊተካ አይችልም። ይህን ነጥብ በተለይ በኢትዮጵያ አገባቡ በግልጽ ማስቀመጥ ያስፈልጋል።

በተጨማሪ፣ ኢትዮጵያን የሚመለከት በዓለም ታሪክ የታየ ሌላ አዝማሚያም አለ። ይኸውም ቅድመ ዲሞክራሲያዊ አገርና አገራዊ መንግሥት ግንባታ የአንድን ነገድም ሆነ አካባቢ ዋና ተነሳሽነትና አድራጊነት ማንጸባረቁ ነው። ይህን ማለት ግን በተለያዩ ታሪካዊ ምክንያቶች የሆነ ማኅበረሰብ አባላት በይበልጥ የመሩት ወይም በአገር አቅኚነትና ጠባቂነት የተሳተፉበት ሂደት የሌሎችን ነገዳዊና ባህላዊ ማኅበረሰቦች አመራሮችና አባላት ተሳትፎ፣ ትብብርና አመራር ጨርሶ ያገለለ ውይም የደፈጠጠ ነበር ማለት አይደለም። ሂደቱ የተለያዩ ነገዳዊና አካባባዊ ወገኖችን ያጋጨና ያዋጋ ብቻ ሳይሆን እነዚህን ያገናኘ፣ ያቀራረበ፣ ያዛመደና ከሞላ ጎደል ያዋሃደም ነበር።

በነዚህ ነባርና ዘመናዊ ሁኔታዎች አገባብ ስናየው ነገድ ተኮር የኦሮሞ ብሔርተኝነት የሚገፉ አንዳንድ ወገኖች ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ላይ የሚያነሱት ጥያቄ ቅጥ ያጣ ሆኖ እናገኘዋለን። እነዚህ ወገኖች በመሠረቱ የሚሉት የኢትዮጵያ ታሪካዊና ዘመናዊ አንድነት ሲቋቋም በኛ “ፈቃድኛነት” ሳይሆን “በሌሎች” ወረራና ሠፈራ ስለነበረ አገሪቱ እንደ አገር መቀጠል ካለባት ውዴታችንን ባካተተ መንገድ እንደገና መፈጠር ይኖርባታል። በኢትዮጵያ ታሪካዊ-ባህላዊ ብሔራዊነት በሲቪክ ብሔራዊነት መተካት አለበት። ለአስርተ ዓመታት የጎሣ ብሔርተኝነት ርዕዮት ሲያራምዱ የነበሩት ኦነጎች መገንጠል የማይሆንላቸው ወይም የማያዋጣቸው መሆኑን የተርዱ ቢመስሉም ዛሬም ከርዕዮቱ ቁራኛ አካተው አልተላቀቁም። ምንጊዜም የሚመኙት ጥንት የነበርችና ዛሬም ያለች ኢትዮጵያን በአንድነቷ እና ሉአላዊነቷ መለወጥ ወይም ማሻሻል ሳይሆን ከዜሮ ተንስቶ “አዲስ” አገር መፍጠር ነው።

ይህ እዚህ ግባ የማይባል ኢታሪካዊም ኢምክንያታዊም ምኞት በምር የሚታይ ወይም እንደ ቁም ነገር ተቆጥሮ ለዉይይትም ሆነ ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም። ግን በምላሹ እዚህ ቀደም ብዬ ያልኩትን ደግሞ ማለት ይቻላል። ማለትም፣ የኦሮሞ ህዝብ በአስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን በተስፋፊነት ከደቡብ ኢትዮጵያ በመነሳት ወደ ማዕከላዊ፣ ሰሜናዊና ምሥራቃዊ ኢትዮጵያ ዘልቆ፣ “ወራሪ” እና “ሠፋሪ” በመሆን ከሌሎች የአገሪቱ ማኅበረሰቦች ጋር መድባለቁና መሰባጠሩን ማስታዎስ ያስፈልጋል። ኦሮሞዎች እንዲህ ሲስፋፉና ከአማሮችና ሌሎች የኢትዮጵያ ማኅበርሰቦች ጋር ሲሰባጠሩ የነዚህን ሌሎች ነገዳዊና ባህላዊ ማኅበረሰቦች “ፈቃደኝነት” ጠየቁ? በአዲስ አበባ መጀመሪያ የሠፈሩት ኦሮሞዎች ናቸው የሚለው ትርክትም ‘ሁሉ ነግር የኔ ነው፣ የኔን ብቸኛ ጎሣዊ ማንነት አመልካች ነው’ ከሚል ዘር ተኮር ቅዠት ወይም ምኞታዊ እሳቤ የተረፈ ምንም ያህል ትርጉም የለውም።

ኦሮሞዎች በታሪካዊ ዝውውራቸው፣ አሠፋፈራቸውና ስብጥራቸው ለኢትዮጵያ ነገደ ብዙ አገር መሆን ወሳኝ አስተዋጽዎ አድርገዋል። ይህን አይነት አገር ለዋጭና አዳባሪ አስተዋጽዎ ያደረገን ታላቅ ማኅበረሰብ አሳንሶ ተወራሪ ፣ የሌሎች ማኅበረሰቦች ሠፈራና ተጽዕኖ ተቀባይ፣ ብቻ አድርጎ ማየቱ በተጎጅነት ስሜት የተዋጠ ወልጋዳ የማንነት ፖለቲካ ትርክት ነው። በአፄ ምኒልክ በተመራው የኢትዮጵያ ዘመናዊ መንግሥት አፈጣጠርም እንደነራስ ጎበና፣ ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ፣ ራስ መኮንን ጉግሣና ፊታውራሪ ሃብተ ጊዎርጊስ ያሉ ታላላቅ የኦሮሞ ጦረኞችና አርበኞች ወሳኝ ተሳትፎ የዚህን የዝቅተኛነት መንፈስ የተላበሰ ፖለቲካዊ ትርክት ውስንነትና ጠማማነት የሚያሳይ አንድ ሌላ ማስረጃ ነው።

ማንነት ከወገንተኛ የጎሣ ፖለቲካ ውጭ

የቆዳ ቀለም፣ ዘር እና ሌሎች ተፈጥሯዊ ወይም ግብታዊ ገጽታዎች ምንም ያህል ሊለወጡ የማይችሉ የሰዎች መለያዎች ናቸው። ሆኖም፣ ማንም ግለሰብ ወይም ማኅበረሰብ ፈጽሞ የተለየና ብቸኛ የሆነ የታሪክ፣ የነገድ፣ የባህል፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋ፣ የአካባቢ ወይም የፖለቲካ “ማንነት” ማህተም ላንዴም ለሁሌም የታተመበት ነው ብዬ አላምንም። በኢትዮጵያ አገባብ በይበልጥ ትኩረት ለመናገር፣ ለምሳሌ የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የጉራጌ፣ የትግሬ፣ የአፋር፣ የወላይታና የጋምቤላ ማኅበረሰቦች እንደ ደሴቶች ወይም ቢላርዶ ኳሶች ራሳቸውን በራሳችው አካተው የዘጉና የከለሉ ወይም “የውሰኑ” አይደሉም። ይልቅስ ታሪካዊ ዝውውሮች፣ አገር ግንባታ፣ የጋራ የውጭ ጠላቶች ጥቃት ምከታ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኑሮ፣ እንዲሁም አገራዊ የአብዮት ልምድ በአፎካካሪነትም ሆነ በአስተባባሪነት ከሞላ ጎደል ያቀራረቧቸው፣ ያገናኟቸውና ያስተሳሰሯቸው ናቸው።

በተጨማሪ፣ ጣልቃ ገብ ዓለም አቀፍ ኃይሎችና ጥቅመኞች በኢትዮጵያ አካባባዊና ጎሣዊ ማንነቶች ቀረጻ ላይ ያሳደሩት ጎጂ ተጽዕኖ እሳቤ ውስጥ መግባት ያለበት ነው። የኢትዮጵያ ብዝሃን ዘሮች የራስነት ቅርጽ የያዙትና አገሪቱን ወደ ነገደ ብዙ ብሔራዊ ማኅበረሰብ የለወጡት፣ በድህረ አብዮቱ ሳቢያም፣ በተለይ በዘመነ ወያኔ አገዛዝ፣ የአገር ከፋፋይና አሰናካይ እቅድ መሣሪያ የሆኑት፣ ከዝውውራቸውና ከግንኙነታቸው በፊት ሳይሆን ባመዛኙ በነዚህ እንቅስቃሴዎችና ትስስሮች አማካኝነት ነው። በጥቅሉ ለመናገር፣ የኢትዮጵያ ነገዳዊና ባህላዊ ማኅበረሰቦች ማንነቶች በከፊል ተደራራቢና ተወራራሽ ለመሆን የበቁት ማኅበረሰቦቹ በተነጣጠሉ ክፍለ ሃገራት ለየብቻ ቁጭ ቁጭ ባሉ የጎሣ ጉረኖዎች ተከልለው በመኖራቸው ሳይሆን በዝዉውራቸው፣ ግጥጥማቸው፣ ተዋላጅነታቸውና አነሰም በዛ የባህሎች ልውውጣቸው እንድሆነ እንረዳለን።

ይህ ግንዛቤያችን ዛሬ እንደ አገር የተዘፈቅንበትን ለማናቸውም የኢትዮጵያ ነገዶች የማይበጅ የማንነት ፖለቲካ ውጥንቅጥ ወደኋላ ትተን እንደ አገር በአንድነት የወደፊት አኪያሄዳችንን እንደምታ ይጠቁማል። ችግሩን ማስወገድ በሚመለከት ከተለመዱ የመወጫ ንድፎች ለየት አድርጌ ለማዳበር በምፈልገው አስተሳሰብ ሁለት “መፍትሔዎች” ከአማራጭነት ዉጭ ናቸው፤ እግምት ዉስጥ የሚገቡ አይደሉም። አንደኛው፣ የሆነ ፓርቲ ወይም ስብስብን መውጫ የሌለው የፖለቲካ ዘረኝነት መንገድ በሌላ መውጫ ቢስ “ተፎካካሪ” የፖለቲካ ዘረኝነት አኪያሄድ መተካት (ለምሳሌ የሕወሓት ጎሠኛ አገዛዝ “ዙፋን” በኦነግ የጎሠኛ ኣገዛዝ የመያዝ አዝማሚያ) ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ጥልቅ ታሪክ ላይ ለተመሠረተ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባህልም ሆነ ተጨባጭ ነገዳዊ ብዝሃንነት ምንም ቦታ የሌለው ረቂቅ የዜግነት ጽንሰሃሳብና የፖለቲካ ዝመና እቅድ ነው።

የጎሣ ብሔርተኝነትን ችግር በመሠረቱ ለመወጣት አዲስ አስተያየት እንደሚያስፈልገን በማመን ባጭሩ የማቀርበው ሃሳብ መጀመሪያ የጎሣ ፖለቲካ “ቅነሳን” አስፈላጊነትና አኪያሄድ የሚጠቁም፣ ቀጥሎም የነገዳዊ ማኅበረሰብነትን ራሱን ለውጥ ተቻይነትና ተፈላጊነት የሚያመላክት ነው። ሃሳቡ እዚህ ዝርዝር ትንተና ሊሰጠው ስለማይቻል ወደፊት በዙሪያው ሊነሱ በሚችሉ ጥያቄዎችና ተጨማሪ ውይይቶች ይበልጥ ማብራሪያ ያገኝ ይሆናል።

ቀድሜ ስለ ፖለቲካ ቅነሳው ባጭሩ ይምለውን ልበል። ኢትዮጵያ ውስጥ በታሪክ ሂደትና በመኅብራዊ ኑሮ የዳበሩ ነገዳዊ ማንነቶች ከውስጣቸው በፈለቁ የተወሰኑ ወገኖች መጤ የፖለቲካ ትርክቶች፣ ዲስኩሮችና ገቢሮች ጨርሰው ሊጠቃለሉ ወይም ሊወከሉ የማይችሉ እሴታዊና ባህላዊ ፀጋዎች ባለቤቶች ናቸው ብያለሁ። አገር ብቻ ሳይሆን ነገድም ከፖለቲካ ፓርቲ እንደሚተልቅና እንደሚቀድም የምናውቀው ነገር ነው። መላ የኢትዮጵያ ነገዶች በወገንተኛ-ዘረኛ ፖለቲከኞች አላማዎችና አጀንዳዎች ጨርሰው የማይወሰኑ ታሪካዊ መለያዎች፣ ፍላጎቶችና ባሕሪያት አሏቸው።

ለምሳሌ፣ የኦሮሞን ማኅበረሰባዊ ምንነትና ጥቅም ኦነግም ሆነ ኦዴፓ በሞኖፖል ወይም በብቸኝነት መወከል አይችልም። የአማራው ማኅበረሰብ ራስነትማ በአዴፓ አመራር ከኦዴፓ ብሶ በወያኔ ሰርጎም ተሽሎክልኮም ጣልቃ ገብነት ተቦርቡሮና ተሸራርፎ ይበልጥ የተዳከመ ነው። ሰሞኑን እንደተዘገበውም፣ በቅማንትነት ስም ከባድ የጦር መሣሪያ የያዙ የወያኔ ወካይ ተዋጊዎች በጎንደር ጭልጋ አካባቢ ንጹህ ግለሰቦችን ሲፈጁ፣ ንብረት ሲያወድሙና በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሲያፈናቅሉ “የአማራ ክልል” መስተዳደር ተብየው እጣቱንም አላነሳም። ጥቃቱን ለመከላከል እርምጃ መውሰዱ ቀርቶ አጥቂዎቹን ያስታጠቀውንና ያሰለጠነውን ሕወሓትን በስሙ ጠርቶ መወንጃል ወይም መክሰስ እንኳን አልደፈረም።

ባጭሩ፣ ሕወሓት አማራን በጠላትነት ፈርጆ በፈጠረውና በጠ/ሚንስትር አብይ አገዛዝ ቀጣይ በሆነው “የአማራ ክልል” ተከላዩ ማኀበረሰብ “የራሱን ዕድል በራሱ መወሰኑ” ቀርቶ ነባር እርስት ጉልቱን ተነጥቆ፤ ዋናዉን አጥቶ፣ ባልረጋና ጨርሶ በማይረጋ ሁኔታ ላይ ይገኛል። በአካባቢም በአገር አቀፍ ደርጃም እራሱን ከጥፋት ለማዳንና እንደ ነገዳዊ ማኅበረሰብ የተነጠቀውን መሬቶቹን ለማስመለስ በሁሉም አስፈላጊ መንገድና ዘዴ መታገል ተገዷል።

በጠቅላላ እንግዲህ፣ በጠባብ ወገንተኛ ዲስኩር፣ ትርክትና ርዕዮታዊ ቀኖና እንዲሁም በተራ ዘረኝነት ድርርብ የደለበን የጎሣ ፖለቲካ ክብደት ቀንሰን፣ ይወክለዋል ከሚባልለት የነገድ ማኅበረሰብ እውን ማንነት ወይም ኑሮ ጋር ቀጥታ ግንኙነት የምናደርገው እንዴት ነው? በኔ ግምት ይህን ጥያቄ በግልጽ አንስቶ ተገቢ መልሱን ማግኘት ነገደ ብዙው የኢትዮጵያ ሕዝብ በጋራ የሚፈልገውንና የሚጠብቀውን የፖለቲካ መዋቅር ለውጥ ለማሳካት ወሳኝ ነው። የለውጡ ትግል መሠረታዊ አላማ በነባሩ ጨቋን ዘር ተኮር ሥርዓት ውስጥ የማኅበረሰቦችን ‘እኩልነት’ ማምጣት ሳይሆን ሥርዓቱን እንዳለ መቀየር ነው።

ከኢትዮጵያ ብዝሃን ነገዳዊና ባህላዊ ማኀረሰቦች እውን ማንነቶች ወይም የኑሮ ሁኔታዎች ጋር ቀጥታ ግንኙነት ማድረግ ስል ምን ማለቴ ነው? ማኅበረሰቦቹ ራሳቸው የሚገልጿቸውን ተጨባጭ ጉዳዮችና ችግሮች፣ የጋራ ጥቅሞቻቸውንና ፍላጎቶቻቸውን፣ በርዕዮታዊ ፈርጆች ወይም በወገንተኛ የፖለቲካ ምስሎች፣ ህንጸቶች፣ ኮዶችና ትርክቶች ቀደም ቀደም ብለን አንሸፍን፣ አናጥለቅልቅ ወይም አንተካ ማለቴ ነው። ፖለቲካችንን በገደብ ይዘን፣ በአዲስ ሃቀኛ አቀራረብ የህዝብ ጉዳዮችንና ብሶቶችን እንዳሉ ማስተዋልና ማዳመጥ ማለቴ ነው። ይህ ቀላል፣ አንደበታችንን በገደብ ይዘን አይንና ጆሯችንን ወለል አድርገን የመክፈት ሂደት፣ የአገር ጉዳዮች ግንዛቤያችን ላይ ሰፊና ጥልቅ ለውጥ የፈጥራል ብዬ እገምታለሁ።

በኢትዮጵያ መኅበራዊና አገራዊ ጉዳዮችን በጠቅላላ እንዲህ ስናስተውል የሆኑ ያልሆኑ ወገንተኛ ወይም ድርጅታዊ አጀንዳዎችን፣ የእሳቤ ፎርሙላዎችን፣ የመርህ ወይም የጽንሰሃሳብ አስመስሎዎችን፣ የሽንገላ ቃላት ክምችቶችንና ይዘት የለሽ የአነጋገር ዘይቤዎችን ከዲስኩራችን እንቀንሳለን፣ ብለንም እናስወግዳለን። የማንነት ፖለቲካ የአገሪቱ ነገዳዊ ማኅበረሰቦች ላይ የጫነውን ድርብርብ የርዕዮት፣ የዲስኩርና የገቢር ቅርፊት ደለል በደለል እናነሳለን። በዚህ መንገድ፣ ዋና ህዝባዊ ማንቶችን ከቦ መፈናፈኛ ከነሳቸው የተትረፈረፈና በጥልቅ ያልዘመነ የሊህቃን ፖለቲካ መወጣጫ በማላቀቅ በአንጻራዊ ነፃነት ራሳቸውን በራሳቸው መልሰው የሚያረጋገጡበትንና የሚጠበቁበትን አካባባዊም አገራዊም ሁኔታ እናመቻቻለን።

በዚህ መልክ እውን ህዝባዊና አካባባዊ ራስነት የሚገለጽበት የፖለቲካ ቅነሳ ሥራ ከመሬት ውስጥ የተቀበሩ የታሪክ ቅርሳ ቅርስ አጥኚዎች (አርኪዎሎጅስቶች) አሠራር ወይም ከሃውልት ሠሪ አርቲስቶች ቅርጽ ፈጠራ ጋር ትንሽ ይመሳሰላል። የአርኪዎሎጂ ባለሙያዎችም ሆኑ የሃውልት ቅርጽ አውጭዎች የሚያከናውኑት ሥራ የተለያዩ ግብአቶችን “ደማሪ” የሆነ ግንባታ ሳይሆን “ቀናሽ” የቁፈራ፣ የፍልፈላ፣ የፍርከሳ፣ የጠረባና የቀረፋ ሥራ ነው።

በዚህ መንገድ የማንነት ፖለቲካ ቀረፋ ወይም ምጠና ሥራ ስንሠራ ያለገንቢ ፖሊሲና ፕሮግራም በመንቀሳአቀስ ሊሆን አይችልም። ፖለቲካችን መርህና ስልት መር አይሆንም ማለት አይደለም። የጎሣ ፖለቲካ መቅረፉ አኪያሄድ የፓርቲዎችን እቅዶችና እንቅስቃሴዎች ጨርሶ የሚከላ አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም። ይልቅስ፣ አኪያሄዱ የፖለቲካ መጣኝነትና የአስተሳሰብ ሃቀኝነት አቅማችንን ለማዳበር የሚረዳን ነው የሚሆነው። ሰፋፊ ዓለም አቀፍ ሃሳቦችን (ለምሳሌ፣ ሕገ መንግሥትን እና ዲሞክራሲን) አጥብበን ወደ ብቸኛ የጎሣ ስብስቦችና ወገኖች “ራስን በራስ መወስኛ” ወይም “ነፃ ማውጪያ” ቀኖናዊ ቀመር ከማውረድ ተቆጥበን አካባባዊና አገራዊ የህዝብ መነጋገሪያ፣ መገናኛ፣ መግባቢያና መስማሚያ አውታሮች ማድረግ ያስችለናል።

እንግዲህ፣ የሃሳብ ሃቀኝነትና የፖለቲካ ምጥንነት አገራዊ መሠረት ላላቸው የዜጎችም የነገዳዊ ማኅበረሰቦችም መብቶችና ነፃነቶች ወጥ ሆነው መቋቋምና መረጋገጥ አስፈላጊ ናቸው ማለት ነው። በሌላ አባባል፣ ወገንተኛ ፖለቲካን በማሳነስ ወይም በመቀነስ ፣ ሲቻልና ሲያስፈልግም በማስወገድ፣ አገራዊም አካባባዊም ማኅበረሰብነታችንን እናተልቃለን። በተመጠነና በተገደበ ዘር ዘለል ፖለቲካ የግለሰቦችም የማኅበረሰቦችም መብቶችና ጥቅሞች ይበልጥ ሊረጋገጡና ሊጠበቁ የሚችሉባቸውን ሁኔታዎች ልንፈጥር እንችላለን።

አነሰም በዛም ግን በኢትዮጵያ የጎሣ ፖለቲካ መሠረታዊ ተቃርኖ ያለው መሆኑን ማሳየት አዳጋች አይደለም። የኢትዮጵያ ነገዳዊ ማኅረሰቦች ራሳቸው በታሪክ አጋጣሚዎችና በአገር ግንባታ ሂደት ባደረጓቸው ግንኙነቶች አማካኝነት ያዳበሯቸው በከፊል ተደራራቢና ተዛማጅ ማንነቶች ብቸኛ የዘር ክልል ከመጠበቅ ሙከራ ጋር ምንም አይግባቡም። በተስፋፊነቱም በአገር ግንባታ ተሳትፎውም ከአማራው ጋር የተሳሰረውና የተዛመደው የኦሮሞ ህዝብ ራስነት በተለይማ ከብቸኛ የጎሣ ብሔርተኝነት ክለላ ጥረት ጋር ፈጽሞ አይጣጣምም። በሕወሓት ፈላጭ ቆራጭ ፖለቲካ/አገዛዝ ታቅዶ የነበርውንና በእምቁ ተገንጣይ የሆነውን የወያኔዎች ዘር ተኮር ብሔርተኝነትም እንዲሁ ማየት ይቻላል። ወያኔዎችም ሆኑ ኦነጎች የተጓዙበት የጎሣ ፖለትካ መንገድ መውጫ የሌለው መሆኑ ዉሎ አድሮም ቢሆን ለአብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ግልጽ ሆኗል። የተመኙትና ያቀዱት “ብሔራዊነት” ወይም “ነፃነት” ከፖለቲካ ባህሪያቸውና አኪያሄዳቸው ጋር በመሠረቱ የተቃረነ ነበር፤ ዛሬም ነው።

ተቃርኖው በአንድ በኩል በሕወሓትና ኦነግ የጎሣ ብሔርተኝነት ፍላጎት ወይም ምኞት ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያ አገራዊም አካባባዊም ማኅበራዊና ባህላዊ እውነታዎች መካከል ባለ ግጭት የተወሰነ አይደለም። ከዚህ መሠረታዊ አለመግባባት ጋር የተያያዘ ሌላ ዋና ቅራኔ አለ። በነባሩ የጎሣ ፖለቲካ ሥርዓት፣ የሆነ የኢትዮጵያ ጎሠኛ ፓርቲ (እንበል ሕወሓት) እወክለዋለሁ የሚለውን ነገዳዊ ማኅረሰብ “ማንነት” ለማረጋገጥ አቅዶ ሲነሳና ሲንቀሳቀስ ራሱን ከአጎራባችም አገራዊም ማኅበራዊ ግንኙነቶችና ትስስሮች ለይቶና ነጥሎ (ከቻለም ራሱን የሌሎች ነገዳዊ ማኅበረሰቦች ገዳዮች ወሳኝና የበላይ አድራጊ ፈጣሪ አድርጎ) ይከልላል፤ በእውንም ከልሏል።

ሆኖም፣ ይሄ ፖለቲካዊ አኪያሄድ ከማንነት ጥበቃ ራሱ አኳያም ቢሆን ተቃርኖ ያንጸባርቃል። ምክንያቱም በአኪያሄዱ የሚፈጠር ተለይቶ የተከለለ የዘር ራስነት እወክለዋለሁ የሚለውን ማኅረሰብ ብቸኛ በማድረግ ማንነቱን ራሱን የሚያጠብ፣ ደህንነቱንም የሚያጓድልና ለአስጊ ሁኔታ የሚያጋልጥ ነው። የትግራይ ህዝብ ደህንነቱንና ልማቱን ለዘለቄታው የሚያረጋግጠው ራሱን ነጥሎና እንደ ከብት ከልሎ ወይም እንደ ጦር ሠራዊት መሽጎ የሕወሓትን አገር ከፋፋይና ዘራፊ እንቅስቃሴዎች በመደገፍ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። “ብሔር ነፃ አውጪ” ተብየው ፈላጭ ቆራጭ የዘር ንጠላና ክለላ አኪያሄድ የትግራይን ህዝብ ደህንነት የሚያረጋግጥ ሳይሆን በተቃራኒው ለህዝቡ ደህንነትና ነፃነት እጦት ዋና ምክንያት እንደሆነ በደንብ ዕውቅ መሆን አለበት። ዕውቂያው በጠቅላላ የኢትዮጵያ ህዝብ መሆን ያለበት ቢሆንም በሕወሓት እንደ ጁሆ ታግቶ የተያዘው በተለይ የትግራይ ማኅበረሰብ ግንዛቤ መሆኑ አስፈላጊ ነው።

የትግራይ ብቻ ሳይሆን የሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሰላም፣ መረጋጋትና ልማት ለዘለቄታው አስተማማኝ የሚሆኑት እንግዲህ በውስጣቸው የሚኖሩ ማህበረሰቦች በሚያዳብሯቸው ያልተዛቡ ጤናማ ህዝባዊ/አገራዊ ግንኙነቶች፣ ትብብሮችና ትስስሮች መሆኑ ምንም ያህል ስውር አይደለም። ነገር ግን ይህን እውነታ አልሞት ባይ ተጋዳይ ወያኔዎች ወይም ኦነጎች በሚገባ ሊያስተውሉት ይፈልጋሉ ወይም ይችላሉ ወይ? አገር አጥፍቶ ጠፊነትን በጭራሽ ታሳቢ አያደርጉም ሊባሉ የማይችሉት በተለይ ሕወሓቶች የአስተዉሎው ፍላጎትም ሆነ ችሎታ ያላቸው አይመስሉም።

በጥቅሉ ከመላ ኢትዮጵያ አንጻር ስናየው፣ በታሪካዊና ዘማናዊ የማኅበረሰቦች ዝውውሮች፣ ግንኙነቶችና ተጽዕኖ ልውውጦች ከሞላ ጎደል በዳበሩ ሁኔታዎች ውስጥ ሆኖ በጠባብና ብቸኛ የዘር ፖለቲካ ወገንተኝነት ደሴታዊ የጎሣ ማንነቶችን ጠብቆ ማቆየት መሠረታዊ ተቅርኖ ያለው ፍላጎትና እቅድ ነው። እንደ ፖለቲካ ፓራዳይም ወይም አገዛዝም ጎሠኝነት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሊሆን አይችልም። የኢሕአዴግ የጎሣ “ፌደራላዊነት” እንዳለ የሚለወጥና በተሻለ፣ አስመሳይ ሳይሆን እውን ዲሞክራሲያዊ ይዘት ባለው፣ አማራጭ የመንግሥት ሥርዓት የሚተካ እንጂ ተጠጋግኖ የሚቀጥል አይደለም።

በመጨረሻ፣ በኢትዮጵያ የዘር ፖለቲካ ችግር ዋና ምንጭ በቀጥታና ባንዳፍታ ዘር ሳይሆን ፖለቲካ ቢሆንም፣ ከመፍትሔ ፍለጋ አኳያ የጎሣን ራሱን ይዞታና ለለውጥ ክፍትነት ማጤን ይጠቅማል። በእቅድም ይሁን በውጤት፣ የስዎች የግልና የጋራ ማንነቶች ነገድን በተለያየ መልክና መጠን እንደ ግብአት ያካትታሉ፣ ወይም ሊያካትቱ ይችላሉ። ሌሎቹ የማንነት ግብአቶች ፆታን፣ሃይማኖትን፣ ባህልን፣ አካባቢን፣ አስተዳደግን፣ ሙያንና ማኅበራዊ መደብን ይጠቀልላሉ።

የሆነ ግለሰብም ሆነ ስብስብ ራስነት እንግዲህ ባመዛኙ የነዚህ የተለያዩ መገለጫዎች ሽግሽግ፣ ድርርብ ውይም ቅልቅል ውጤት ነው፣ ምንም እንኳን ባንዳንድ ሁኔታዎች አንዱ ውይም ሌላው ተጋኖ ሊወጣ ቢችልም። አነስና ጠበብ ያሉ የማንነት ኩነቶች ወይም ትርክቶች ተለቅና ሰፋ ባሉ ተዛማጅ ወይም የጋራ ትርክቶች እቅፍ ሊያዙ ይችላሉ። ለምሳሌ የአማራ ወይም የኦሮሞ ራስን በራስ አተያይና አገላለጽ በኢትዮጵያ ነገደ ብዙ አገራዊ ህላዌና ትርክት የተካተቱና በይበልጥ ተቀባይነት ሊካተቱ የሚችሉም ናቸው። ነገዳዊነት ወይም አካባባዊነት እና አገራዊነት በተለያዩ ዘርፎች እርስ በርስ ተመጋጋቢ፣ተወሳሳኝና ተደጋጋፊ መሆን ይችላሉ፤ ያስፈልጋቸዋልም።

የጎሣ ማንነት እንዳለ ለተለያየ ጎጂም በጎም ይዞታ ወይም አቀራረብ በአንጻር ክፍት ነው። ማለትም፣ ጠባብ፣ ብቸኛና አክራሪ ሆኖ ሌሎች ነገዶችን ሊያገልና ሊያጠቃ፣ ወይም ሰፋና ላላ ባለ ራስነት “ሌላውን” ሊቀበልና ሊታገስ ይችላል። ሲበዛ ወደ ኋላ ተመልካች በሆነ ተጎጅነት አጥባቂ “አልቃሻ” ስሜት ተውጦ ውዝግብና ግጭት ጫሪ ሊሆን ይችላል፣ ወይም ለዘብ ብሎ በአዲስ የተራማጅነት መንፈስ ተግባቢነትንና ተቻቻይነትን ሊያንጸባርቅ ይችል ይሆናል። ከግልጽ ፖለቲካ አኳያም ጎሣ እንዲሁ የተለያዩ ቅርጾች (አምባገነናዊ ወይም ዲሞክራሲያዊ፣ ሊበራል ወይም ወግና ልማድ አጥባቂ፣ ወደፊት ተመልካች ወይም አድሃሪ፣ ወዘተ) ሊይዝ እንድሚችል ይታውቃል። ባጭሩ፣ የዘር ማንነት ግትር ሳይሆን ለክፉም ለደጉም የተወሰነ ተለማጭነት እንዳለው እንረዳለን። ለምክንያታዊ ክርክር፣ ውይይትና ድርድር በአንጻር ክፍት እንደሆነ እንገነዘባለን።

ይህም ማለት፣ የዘር ራስነት ተነጥሎ፣ ተጋኖና ተከልሎ በመውጣት ለማንም በማይበጅ ቅርጽና ይዘት አገር አወዛጋቢ እንዳይሆን ከሌሎች የማንነት መገለጫዎች ጋር ተጣጥሞ፣ ተመጣጥኖና ተሳስሮ ሰፋና ለዘብ ባለ መልክ እንደገና እንዲገለጽ ማድረግ ይቻል ይሆናል። እዚህ ላይ ነገዳዊ ማንነትን በጥሬ የጎሣ ራስነት እና በወገንተኛ ፖለቲካ “መወሰን” ወይም እንደ ከብት በክልል ማጎር ማለት ነገድን “ነፃ” ማውጣት ወይም ማልማት ሳይሆን መጨቆን፣ ማፈን፣ ማሳነስና ማቆርቆዝ መሆኑን መረዳት ይጠቅማል።

እንግዲህ ዘር ዘለል ማኅበራዊና ባህላዊ ግንኙነቶቻቸውን ኮትኩተው በማሳደግና በማልማት የተለያዩ የኢትዮጵያ ነገዶች አካባቢዎቻቸውንና ማንነቶቻቸውንም ማበልጸግ ይችላሉ ማለት ነው። ለምሳሌ “ኦሮሞነት” የተለመዱ ባህላዊ እሴቶቹን ከዘመናዊ ጎሣ ተሻጋሪ የግለሰብ መብቶች ጋር አሸጋሽጎና አዛምዶ ሊያካትት ይችላል፤ የጋራ ነገዳዊና ባህላዊ የራስነት መገለጫዎቹን ከግለሰብነትና ዜግነት መብቶች፣ ከዘር ዘለል የፆታና የመደብ ጥቅሞች፣ ከሙያተኝነት እሴቶች፣ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ዲሞክራሲያዊ ሃሳቦች ጋር አናቦና አግባብቶ በኢትዮጵያዊነት እቅፍ የመያዝ አቅም ያለው የመስለኛል።

በኢትዮጵያ ሌሎች ነገዶችም ኢንዲሁ በላቁና የተስፋፉ ማኅበራዊ ግንኙነቶች በመግባባት፣ በመቻቻልና በመደጋገፍ ራሳቸውንና አካባቢዎቻቸውንም ኢትዮጵያ አገራቸውንም መልሰው የመገንባትና የማበልጸግ ብዙ እምቅ ችሎታ አላቸው ብዬ እገምታለሁ። ይህን የታመቀ ችሎታ እውን ለማድረ ግን ለማንም የማይበጅ፣ ከስሮ አገርና ህዝብ አክሳሪ የሆነ፣ ጠባብና ብቸና የዘር ፕለቲካን በማያዳግም መልክ ጥሎ ማለፍ ወሳኝ የመጀመሪያ እርምጃ ነው።

tesfayedemmellash@gmail.com
___
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here