አክሊሉ ወንድአፈረው (የግል አስተያየት)
ethioandenet@bell.net
የካቲት 16፣2011 ( ፌበርዋሪ 23፣ 2019)
በሀገራችን በኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረው ለውጥ ቁልፍ በሆኑ ጥያቄወች ላይ ምላሽ እየሰጠ የሚጓዝባቸው ሂደቶች በሰፊው ይስተዋላሉ። የፖለቲከ ምህዳሩን ከማስፋት (ሊበራላይዜሽን ) ወደ ዴሞክራሲያዊ መሰረት መጣል (ዴሞክራታይዜሽን) ለመሸጋጋር የተለያዩ ድንጋጌወችን ማውጣት አፋኝ ህግጋትን መሻርና ዴሞክራሲአዊ ስርአትን እውን ሊያደርጉ የሚችሉ ተቋማትንም መገንባት አሰፈላለጊ ነው።
ተቋም ሲባል ዴሞክራሲአዊ ስርአትን አውን ለማድረግ በቅርጽም በይዘትም የሚያግዙ ተቋማትን እንጂ ማንኛውንም ተቋም ማለት አይደለም። ህወሀት ኢህአዴግ ለ27 አመታት እጅግ ዘግናኝ የሆነ ግፍ የፈጸመው፣ እንድነተችንን ያዳከመውና መራራቅ ስር እንዲሰድ ያደረገው በተቋማት ተደግፎ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም።
በዚህ አንጻር በዚህ ጽሁፍ ውስጥ በቅርቡ የታወጀውን የብሄራዊ እርቅና ሰላም ኮሚሽን ምስረታ በተመለከተ የሚታዩትን አበረታች እና አሳሳቢ ገጽታወች በተወሰነ ደረጃ እዳስሳለሁ ። ይህን ጽሁፍ በማድረግም ጠንካራ ጎኖቹን ይበልጥ ለማጠናከርና ድክመቶችንም በጊዜው ለማረም ግብአት ይሆናል የሚል እምነት አለኝ። ከዚህ በተጨማሪም ለወደፊቱ በሀገራችን ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ለሚወሰዱ እርምጃወች አንዳንድ ትምህርትንም ይሰጣል ብየ ተስፋ አደርጋለሁ።
መነሻ
ሕዝባችን ያሳለፈው ሰቅጣጭና በመብት መጣስ የተሞላ ታሪክ ሁሉንም የህብረተሰባችንን ክፍል እጅግ ጎድቷል። ይህ ተደጋጋሚ የመብት ረገጣ አለመተማመንን ፣ በሀገር አለመመካትን፣ የበላይና የበታች ስሜትን ወዘተ አስፍኗል።በሀገራችን ታሪክም ሆነ በወደፊት አቅጣጫዋ ላይ ከመግባባት ይልቅ ጥልቅ ልዩነት እንዲሰፍን ሆኗል። በነዚህና ተዛማጅ በሆኑ ምክንያቶችም ሀገራችን በፖለቲካ ምስቅልቅልና በጦርነት አዙሪት ከተተበተበች እጅግ ብዙ ጊዜ ሆኗል።
በሀገራችን ውስጥ በመንግስታትና፣ በህዝብ፣ በመንግስታትና በፖለቲካ ድርጅቶች፣ በተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች መሀላ፣ በያንዳንዱ ፖለቲካ ድርጅት ውስጥ፤ በተለያዩ ማህበረሰቦች መሀል ወዘተ ግጭቶች፣ አለመተማመኖች ወዘተ እንደተከሰቱ፣ እነዚህም ግጭቶች ባግባቡ ሳይፈቱ እስካሁን እደቀጠሉ ይታወቃል።
__
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።