ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ
የካቲት 18 2011 (02/25/2019)
አባቴ ነፍሱን ይማረውና፤ ከ25 ዓመታት ገደማ በፊት “ይሰቀል”፤ “ይሰቀል” በሚል ርዕስ አንድ ቲያትር ጽፎ ለእይታ ቀርቦለታል። የቲያትሩ ዋና መልዕክት፤ የሃገራችን የፖለቲካ ባሕል፤ ሁሉንም ለውጥ፤ በነውጥ እና በአብዮት የሚፈልግ መሁኑን ለመጠቆም እና፤ “በመንጋ ዳኝነት”፤ ነገሮችን በሰከን አእምሮ ባለማየት በምንወስናቸው ውሳኔዎች ወይም በምንፈጥረው ግፊት፤ የሚወሰኑ ውሳኔዎች፤ በሃገራችን ላይ ቋሚ ጉዳት የሚያደርሱ መሆናቸውን ማሳያ ነበር። አንደበት ርቱዕ የነበርው አባቴ ለ14 ዓመታት የአልጋ ቁራኛ በነበረበት ወቅት፤ እኔ እስከማውቀው ድረስ በሙሉ አረፍተ ነገር የተናገራቸው ሁለት ነገሮች ናቸው፤ ከሁለቱ አንዱ እና፤ ሁሌም እምባ እየተናነቀው ሲናገር የነበረው “ተማሪ አጠፋ” የሚል ሁለት ቃላቶች ነበር። አባቴ ይህን ያለው፤ የ60ዎቹ ተማሪዎች፤ አፄ ኃይለሥላሴን ከስልጣን ለማውረድ በጀመሩት ነውጥ፤ ሃገራችን እስካሁን ከማትወጣበት ማጥ ውስጥ መግባትዋን በቁጭት ሲያታወሰ ነበር።
ዛሬ፤ ሃገራችን፤ ለገጠማት፤ ከፍተኛ መሰናክል እና ለደረሰባትም ከፍተኛ ጉዳት፤ የ60ዎቹን ትውልድ የሚረግመው፤ ወጣቱ ትውልድ፤ ዛሬም የራሱ ድርጊት ከ60ዎቹ ያልተለየ መሆኑ፤ ከፖለቲካ ታሪካችን፤ ገና ያልተማርን መሆናችንን ያሳብቃል። ዛሬም፤ ለውጥ የምንፈልገው በነውጥ እንጂ በዝግታ እና በማስተዋል በሚደረግ የለውጥ ጉዞ አይደለም፤ በዚህ በምንቆሰቁሰው ነውጥ ግን፤ በሃገሪቱ ላይ ልናደርስ የምንችለው ከፍተኛ ጉዳት አይታየንም። ትላንት ሕዝብን ሊያነሳሱ ይችላሉ ብለን የተጠቀምንባቸው መፈክሮች፤ እና ምክንያቶች፤ ከሃገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ይጣጣም፤ አይጣጣም ሳንረዳ፤ከጥግ እስከጥግ ስናስተጋባቸው ነበር። እነዚህ መፈክሮች፤ እና ምክንያቶች፤ ዘላቂም ሆነ ጊዜያዊ ጥቅምና ጉዳታቸው ከግንዛቤ ውስጥ ሳይገባ፤ “በአድማ ፖለቲካ” ተጠፍረው ለሕዝብ በመሰራጨታቸው፤ አንድ ብርቅዬ ትውልድ አጥተናል። እንዲህ ዓይነት ጉዳት እንደሚመጣ የገመቱ፤ ሰከን ባለ አእምሮ እንዲታሰብ እና የመልዕክቶቹ አና የመፈክሮቹን አደገኛነት ያሳሰቡ ዜጎች፤ ተወግዘዋል፤ በጥይትም ተደብድበዋል። ስድብ፤ ዛቻና፤ ዱላ የገጠማቸውን ቤቱ ይቁጠረው።
ከ44 ዓመታት ስቃይ እና ውድቀት መማር ሲገባን፤ ዛሬም፤ አንዳንድ የፖለቲካ ልሂቃኖቻችን እና “አክቲቪስቶች”፤ ሃላፊነት በጎደለው እና ፍጹም በተሳሳተ መፈክር ሌላ ነውጥ፤ ሌላ አብዮት ሲጋብዙ እያየን ነው። ተው፤ ይህ ተገቢ አይደለም የምንል ሰዎች ደግሞ፤ ውግዘቱ፤ ስድቡ እና ዛቻው አልቀረልንም። የዛሬዎቹ መፈክሮች፤ ቅርጽ እና ይዘታቸውን ይቀይሩ እንጂ፤ አላማቸው አንድ ነው፤ በነውጥ፤ ለውጥ ለማምጣት መመኘት ነው። ለውጥን በነውጥ ብቻ ለማምጣት የሚጥሩ የፖለቲካ ልሂቃን፤ እነሱ የሚፈልጉትን “ፈጣን ለውጥ” ለማግኘት፤ በሚሄዱበት የነውጥ መንገድ፤ የሚከፈለው ከፍተኛ ዋጋም ሆነ በሃገሪቱ የሚያመጣው ጥፋት እና ዘላቂ ጉዳት አይታያቸውም። ምክንያታዊ ለመሆን እና በረጋ መንፈስ፤ ችግሮች የሚሏቸውን ክስተቶች ለማመዛዘን፤ እና አማራጭ መፍትሔ ለመሻት ትግስቱ የላቸውም። ብዙዊች፤ ይህን የነውጥ መንገድ የሚከተሉት ከቀና የለውጥ ፍላጎት ቢሆንም፤ ቀናነት ብቻውን ፤ ወደምንፈልገው በጎ አቅጣጫ አልወስደንም፤ ወደፊትም አይወስደንም፤ ስለዚህ፤ ቆም ብሎ በሰከነ አእምሮ ማሰብ፤ ከነውጥ (Revolution) ይልቅ በአዝጋሚ ለውጥ (evolution) የተሻለ እና ዘላቂ ለውጥ ማግኘት የምንችልበትን መንገድ ቢተልሙ፤ በሃገራችን፤ ወደ ኋላ ተመልሰን ልናስተካክላቸው የማንችላቸውን (irreparable damage) ጉዳቶችን ከመፈጸም ያድነናል።
ወደ እዚህ ሃተታ ያስገባኝ፤ ሰሞኑን በለገጣፎ/ለገዳዲ ከተማ መስተዳድር፤ “ሕገ ወጥ” ቤቶች ገንብታችኋል በተባሉ ዜጎች ላይ የከተማው መስተዳድር የወሰደው እርምጃ ነው። ይህንን ተከትሎ፤ “የፖለቲካ ልሂቃን”፤ አክቲቪስቱ፤ እና እንደ እኔ ዓይነቱ ተራ ዜጋ፤ በየፊናው የመሰለውን በየማህበራዊ ሚዲያዎች ገጽ ላይ እየገለጸ ይገኛል። አሳዛኙ ነገር፤ አንዳንዶች፤ በሰከነ አእምሮ፤ እና የተነሳውን ችግር ጭብጡን በማየት፤ ሃሳብ ከመስጠት እና መፍትሔ ከመጠቆም ይልቅ፤ ካለምንም ጭብጥ፤ በማጋነን፤ እንዲሁም ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ሊያጋጭ የሚችሉ ሃላፊነት የጎደላቸው ነገሮችን በማራገብ ተጠምደዋል። እንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎችን በመጠበቅ እና በመጠቀም፤ ሃገሪቱ የጀመረችውን የለውጥ ጉዞ ለማደናቀፍ የሚተጉ ዜጎች መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ይህ ጽሁፍ ትኩረቱ፤ ሃላፊነት ሊሰማቸው ይገባል፤ ለሌላው አርአያ መሆን አለባቸው ተብሎ የሚታመንባቸው ሰዎች ላይ ነው። ለውጡን ለማደናቀፍ የሚፈልጉ ሰዎች አላማቸው አንድ ነው እና፤ እያወቁ የሚያጠፉ በመሆናቸው፤ እነሱን ለመምከር መሞከር፤ “ወኃ እምቦጭ” ነው የሚሆነው።
ለውይይቱ ጠቃሚ እንዲሆን፤ ከተለያዩ የዜና አውታሮች የተገኘውን መረጃ፤ ጭብጥ በማድረግ እንጀምር። የመጀመርያው እና አከራካሪ ያልሆነው ጭብጥ። ቤታቸው የፈረሰባቸው፤ እና አሁንም ቤታቸው እንዲፈርስ ውሳኔ የተወሰነባቸው የቤት ባለቤቶች፤ የመሬት ይዞታው ሕጋዊ አለመሆኑ ነው። ሕጋዊ አለመሆኑን የሚያረጋግጠው፤ የሃገሪቱ ሕግ፤ መሬት በግለሰቦች እንዳይሸጥ የሚከለክል መሆኑ ነው። ሁለተኛው ጭብጥ፤ ቤቱን ለገነቡት ሰዎች፤ ቤቱ እንደሚፈርስ፤ ከመፍረሱ ቀደም ብሎ በከተማው መስተዳድር ለነዋሪዎቹ ማስጠንቀቅያ መድረሱ ነው። እዚህ ላይ አከራካሪው ነጥብ፤ ቤቱ ለፈረሰባቸው ሰዎች እና ለመፍረስ በእቅድ ላይ ላሉ የቤት ባለቤቶች፤ የከተማው መሰተዳድር፤ ቤቱ ይፈርሳል ብሎ የነገራቸው፤ ቤቶቹ ከመፍረሳቸው ከሳምንት በፊት ነው የሚል እና፤ የከተማዋ ከንቲባ ደግሞ፤ በሃምሌ 2010 ለነዋሪውቹ ቤቱ እንደሚፈርስ ነግረናል፤ ከዛም በኋላ ደግሞ ከወር ተኩል በፊት፤ በሕዝብ መገናኛ ብዙሃን ለሕዝብ አሳውቀናል፤ የሚል ነው። የኦሮሞ ክልል አፈጉባኤ በብኩላቸው በሰጡት መግለጫ፤ በኦሮምያ ክልል 12፣000 “ሕገ ወጥ” የቤት ግንባታ መኖሩን፤ ከ6 ወር በፊት ለሁሉም ቤታቸው እንደሚፈርስ እንደተነገራቸው፤ እና ለአንዳንዶቹም፤ ቅያሬ ቦታ ቢሰጣቸው፤ ቅያሬውን አንፈልግም ማለታቸውን ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪ፤ ፋና ብሮድካስቲንግ እንደ ዘገበው፤ የከተማው ከንቲባ “ቅሬታ አቅራቢዎች የከተማ አስተዳደሩ ከመመስረቱ ሶስት አመት በፊት የከፈሉበትን የግብር ካርድ ማቅረብ እንዳልቻሉ፤ አስተዳደሩ ህጋዊነታቸውን ማረጋገጥ አልቻሉም ላላቸው ለእነዚህ ዜጎች 140 ካሬ መሬት በማዘጋጀት በማህበር ተደራጅተው እንዲሰሩ እድሉን አመቻችቶ እንደነበረና፤ ነዋሪዎቹ ግን ፍቃደኛ እንዳልነበሩ ለዚህም የከተማ አስተዳደሩ ቤቶቹ ከመፍረሳቸው ሁለት ወር በፊት ደብዳቤ እንዳደረሳቸውም” ገልጸዋል ሲል ዘግቧል። ጭብጦቹ እነዚህ ናቸው።
በዚህ ጸሃፍ እምነት፤ ቤታቸው ከፈረሰባቸው ተበዳዮችም፤ ከአስተዳደሩም በኩል መሰረታዊ ችግሮች አሉ። በመንግስት ይዞታ ላይ የተገነቡት ቤቶች፤ ሕጋዊ ናቸው ብሎ መከራከር የሚያስችል ጭብጥ እስካሁን አላየሁም። ሆኖም፤ ሕጋዊ አለመሆናቸው ብቻ ግን፤ መንግሥት የወሰደውን እርምጃ ፍትሃዊ አያደርገውም። እነዚህ ሰዎች ለዓመታት በእነዚህ ይዞታዎች ሲኖሩ፤ መንግሥት አይቷል፤ ለነዋሪዎቹ፤ የቤት ቁጥርም መታወቅያም ሰጥቷል። ለነዋሪዎቹ፤ መብራትም ሆነ የውኃ ቆጣሪ ያስገባው መንግሥት ነው። ስለዚህ መንግሥት ዛሬ “ሕገ ወጥ” ለሚለው ነገር የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል። በጉቦም ይሁን በሌላ መልክ መደረግ ያልነበረበትን ነገር ቀደም ብለው የነበሩት ባለሥልጣናት ያድርጉት፤ አሁን ያሉት ባለስልጣናት ያድርጉት፤ የከተማው እና የክልሉ መንግስት ከራሱ በኩል የተሰራውን ስህተት ግምት ውስጥ በማስገባት፤ ከነዚህ ነዋሪዎች ጋር ተደጋጋሚ ውይይት በማድረግ፤ ወደ ሌላ ቦታ የሚሄዱበትን ሁኔታ ማመቻቸት፤ ወይም ተጨማሪ ጊዜ መስጠት ነበረበት፤ ይህንን ግን አላደረግም። እነዚህ ሰዎች፤ “ሕግ ጥሰዋል የተባለው” ተጭበርብረውም ይሁን፤ በማወቅ፤ ወይም ባለማወቅ፤ የመንግሥት ይዞታ ላይ ቤት ገንብተዋል በመባላቸው ነው። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ችግሩን ላለማባባስ እና፤ በነዚህ ነዋሪዎች ላይ አላስፈላጊ የኑሮ ቀውስ ላለመፍጠር፤ በከተማው መስተዳድር በኩል፤ የተለየ እና ተጨማሪ ጥንቃቄ መደረግ ነበረበት፤ ይህ አለመሆኑ ስሕተት ነው ብሎ ይህ ፀሃፍ ያምናል። አሁንም፤ ቤታቸው ለፈረሰባቸው፤ ጊዜያዊ መጠለያ ሊያገኙ የሚችሉበትን እና፤ ቋሚ ኑሯቸውን ሊቀጥሉ የሚችሉበትን መንገድ፤ የከተማው እና የክልሉ መንግሥት፤ ከፌደራል መንግስቱ፤ ከበጎ አድራጊ ድርጅቶቸ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር መፍትሔ ያብጅላቸው። አሁን ባሉበትም ሁኔታ፤ ምግብ ማግኘት፤ ማብሰል እና መጸዳዳት የሚችሉበትም ሁኔታ ሊመቻችላቸው ይገባል። ቤታቸው ላልፈረሰ እና አሁንም ለመፍረስ እቅድ ላይ ባሉት ቤቶች ላይ እርምጃ ከመወሰዱ በፊትም፤ ለነዋሪዎቹ፤ ቢቻል ቤታቸውን ሕጋዊ የሚያደርጉበት፤ ካልተቻለ ደግሞ፤ ሌላ ተለዋጭ ቤት ሊያገኙ የሚችሉበት ሁኔታ ቢመቻች፤ ሊፈጠር የሚችለውን ማህበራዊ ቀውስ ይቀንሰዋል።
ምንም እንኳን መንግሥት ሕግ የማስከበር ሃላፊነት እና ግዴታ ቢኖርበትም፤ ሃገሪቱ ከነበረባት እና አሁንም ካለባት፤ አስቸጋሪ የአሰተዳደር ጉደለት አንፃር፤ ሕግ ማስከበሩ፤ የሕብረተሰቡን ኑሮ በማያቃውስበት ሁኔታ ቢሆን ይመረጣል። አሁን የተፈጠረውን ቀውስም ለመግታት፤ ከፌደራል መንግስት፤ ከበጎ አድራጊ ድርጅት እና ግለሰቦች፤ እንዲሁም ድጋፍ ማድረግ ከሚችሉ ባለሃብቶች ጋር ውይይት ይደረግ። የፖለቲካ አታካራው እና “ብሽሽቁ” መፍትሔ አይሆንም።
በነዋሪዎቹ በኩል ይህ ጸሃፍ የታየውን ጉድለት ለመጥቀስ፤ ነዋሪዎቹን፤ በተለያየ መልክ ማየት ያስፈልጋል ብሎ ያምናል። ሁሉንም ነዋሪዎች በአንድ መስፈርት ማየት ተገቢም ሚዛናዊም አይሆንም። በማወቅ ሕግ የጣሱ ይኖራሉ፤ በአቋራጭ ቤት ለማግኘት ብለው ሕግ የጣሱ፤ ሌላ ቤት እያላቸው፤ የሚከራይ ቤት የመንግስት ይዞታው ላይ የሰሩ፤ ተጭበርብረው ይዞታውን የገዙ እና ባለማወቅ የተሳሳቱ ናቸው ተብሎ መፈረጅ ይቻላል። እነዚህንም ለይቶ ማየት ተገቢ ይሆናል። የከተማው መንግሥት ከ6ወር በፊት እና ከሁለት ወራት በፊት ለነዋሪውቹ ቤቱ እንደሚፈርስ አሳውቄ ነበር የሚለውን ባንቀበል እና ነዋሪዎቹ ያሉትን ብንወሰድ፤ የከተማው መሰተዳድር፤ ለባለቤቶቹ ቤታቸው እንደሚፈርስ ያሳወቃቸው ከሳምንት በፊት ነው። ይህን እንደ እውነት ከተቀበልን፤ መጠየቅ ያለብን ነገር፤ በዚህ በተሰጣቸው የአንድ ሳምንት የማስጠንቀቅያ ጊዜ፤ ነዋሪዎቹ፤ አቤቱታቸውን በክልል ደረጃ ለማሰማት ምን አደረጉ? በተደጋጋሚ የሰማነው፤ ለከተማው መስተዳድር ይዞታችን ሕጋዊ ነው ብለን ነግረናል፤ መስተዳድሩ ግን ያስተናገደን በግዴለሽነት ነው የሚል ነው። ከከተማው መስተዳድር የተሰጣቸው ምላሽ አርኪ ካልሆነ መስተዳድሩን አልፈው ለበላይ አካላት ለማሳወቅ ምን አደረጉ? ተሰባስበው፤ ኮሚቴ አቋቁመው፤ ችግራቸው እንዲታይ ያደረጉት ነገር ነበር ወይ? ለሚዲያስ ቀደም ብለው አሳውቀው ነበር ወይ? ለእምባ ጠባቂው አቤቱታ አቅርበው ነበር ወይ? በፍርድ ቤትስ የከተማው መሰተዳድር ቤቶቹን እንዳያፈርስ እና ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እንዲታይ እገዳ እንዲጣል አድርገው ነበር ወይ? የሚሉ ጥያቄውችን ስናነሳ፤ እስካሁን ያለው መረጃ የሚያሳየው፤ ነዋሪዎቹ ከላይ የተጠቀሱትን ነገሮች፤ ወይም ሌላ አማራጭ አለመሞከራቸውን ነው። ከዚህ በተጨማሪ፤ መሬት ከግለስብ መግዛት ሕገ ወጥ መሆኑን እያወቁ፤መሬት መግዛታቸው እራሱን የቻለ ነዋሪውቹ የሰሩት ስሕተት ነው። ነግር ግን፤ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ፤ ነዋሪዎቹ አጥፈትዋል እና፤ ፍትሃዊ ያልሆነ “ቅጣት” ይቀጡ ማለት ግን ተገቢ አይመስለኝም። ስለዚህ እነዚህ ነዋሪዎች፤ የችግሩ አካል መሆናቸውን በመገንዘብ፤ የመፍትሔው አካል እንዲሆኑ፤ የሚመለከተው አካል፤ ሁኔታዎችን ሊያመቻችላቸው ይገባል።
ከነዚህ ሁለት አካላት በተጨማሪ፤ ችግሩ በሕዝብ ግንኙነት (በሚድያ) እና በፖለቲካው መድረክ ሰፍቶ እና ጠልቆ ይገኛል። በለገጣፎ የተነሳውን ችግር፤ የፖለቲካ ትኩሳቱ እንዲጨምር፤ የዜና አውታሮች የራሳቸውን ሃላፊነት የጎደለው ሚና ተጫውተዋል። አንድ የሚድያ አውታር፤ ትልቁ ሥራው፤ ነገሮችን በጥልቅ መርምሮ፤ እውነቱን እና ውሸቱን አንጥሮ በማውጣት፤ ለሕዝብ መረጃ መስጠት ሆኖ ሳለ፤ ወገንተኛ በሆነ መልክ ብሶት አራጋቢ በመሆን የህዝቡን ቁስል፤ ለንግድ ተጠቅሞበታል። ብሶት ማራገቡ፤ ጋዜጣ ሊያሸጥ፤ አድማጭ ሊያበረክት ይችል ይሆናል፤ ግን ሃገሪቱ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ አለማመዛዘን፤ ወይም ለሚመጣው አደጋ ግድየለሽ መሆን፤ ሃላፊነት የጎደለው ብቻ ሳይሆን፤ የጋዜጠኝነትን ሙያ የሚያራክስም ተግባር ነው። ለሕዝብ የሚሰራጩ፤ ሃላፊነት የጎደላቸው እና ሆነ ተብለው ብሶት ለማባባስ የሚሰሩ ዜናዎች፤ ሊታረሙ ይገባቸዋል። ጋዜጠኞች፤ በተቻለ አቅም እና ፍጥነት፤ ሃቁን ከሃሰት አንጥረው በመለየት፤ ትክክለኛ ጭብጥ ያለው መረጃ ለሕዝብ ሊያቀርቡ ይገባቸዋል። ከተጎጂው ሕዝብም ሆነ ከባለስልጣናቱ፤ አስፈላጊውን መረጃ በመሰብሰብ፤ የትኛው የመንግሥት አካል ጉዳዩ እንደሚመለከተውም ለሕዝብ ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል። የሆነው ግን ይህ አይደለም። ከዚህ በተጨማሪ፤ በፖለቲካ ልሂቃን እና በአክቲቪስቶች፤ የሚነሱትን ውይይቶች፤ በተገቢ ሁኔታ ማስተናገድ፤ ማስተማር፤ እና ስህተት ሲገኝ ይህንን ስህተት ማረም የዜና አውታሮች ሥራ ነው።
ለምሳሌ፤ ብዙዎች በዚህ ጉዳይ የተጠመዱ የፖለቲካ ልሂቃን፤ እና አክቲቪስቶች፤ ዶ/ር አብይን እና የፌደራል መንግስቱን ሲያወግዙ፤ በሚድያው በኩል፤ የመንግስት አወቃቀር እንዴት እንደሆነ እና፤ የልሂቃኑም ሆነ የአክቲቪስቶቹ ወቀሳ ያተኮረው የተሳሳተ የመንግሥት ተቋም እና ባለሥልጣን ላይ መሆኑን አላስተማሩም። አሁን ባለው የፌደራል ስርአት አወቃቀር፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ የፌደራል መንግሥቱ፤ የከተማው መስተዳድር ስራ ውስጥ ጣልቃ ለመግባት፤ ምንም ሕጋዊ ሥልጣን የላቸውም። ይህንን፤ ትክክለኛ የመንግስት ተቋማት የስራ እና የሥልጣን ክፍፍል፤ የዜና አውታሮቹ በመዘገብ፤ ሕዝቡ እንዲያውቅ ከማድረግ ይልቅ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩን እና የፌደራል መንግስቱን፤ በማያገባቸው ጉዳይ ላይ ለምን ጣልቃ አልገቡም የሚለውን የአክቲቪስቶች እና የፖለቲካ ልሂቃኑን አቤቱታ እና ያልተገባ ውግዘት ሲያስተጋቡ ተስተውለዋል።
ከሁሉም ደግሞ አሳዛኙ እና አሳፋሪው ድርጊት፤ ለገጣፎ የተደረገው የቤት ማፍረስ ድርጊት፤ “ዘር ማጽዳት” ነው እየተባለ ሲነገር፤ እና እንዲህ ዓይነት አደገኛ እና የሃሰት ቅስቀሳ፤ በሕዝቡ ውስጥ እንዲሰርጽ በትጋት ሲሰራ፤ ሚድያው፤ በተጨባጭ ይህንን የተሳሳተ እና አደገኛ ትርከት፤ በተገቢ ሁኔታ ከመሞገት ይልቅ፤ አንዳንዱ ሚድያ፤ ይህንኑ የሃሰት ትርከት ሲያራግብ ቆይቷል።ብዙዎች ደግሞ፤ ይህንን አደገኛ ትርከት “አላየሁም አልሰማሁም” ብለው በዚህ ጉዳይ ዝምታን ሲመርጡ ማየት፤ እጅግ ይዘገንናል። የዜና አውታሮች እና ጋዜጠኞች፤ ወገንተኛ የሆኑ አክቲቪስቶች ሊሆኑ አይገባም፤ ይህን ከሆኑ፤ ጋዜጠኞች ሳይሆኑ፤ የሚሆኑት ፕሮፖጋንዲስት ነው። ሚድያው፤ ከዚህ ስህተቱ ሊማር እና ይህንን ጉድለት ሊያስተካክል ይገባዋል። እንዲህ ዓይነት የተዛቡ እና አደገኛ አመለካከቶች፤ ልንወጥው ወደ የማንችለው ችግር ውስጥ ይከተናል። በተለያዩ የሚድያ አውታሮች እንዳየነው፤ ቤታቸው የፈረሰው፤ አማሮች፤ ብቻ አይደሉም፤ ጉራጌዊች፤ ወላይታዎች፤ ኦሮሞዎችና የሌሎችም ብሔር/ብሄረሰብ አባላትም ጭምር ናቸው። ይህ ብቻ ሳይሆን፤ ሌሎች፤ አማሮችም ሆኑ የሌላ ብሄር ብሔረሰብ አባላትን፤ የኦሮሞ ክልል መንግስትም ሆነ፤ የኦሮሞ ሕዝብ፤ ኦሮምያን ለቃችሁ ውጡ ብሎ ያስገደደበት ምንም ሁኔታ የለም፤ ሃቁ ይህ ሆኖ ሳለ፤ በአንዳንድ አክቲቪስቶች እና የፖለቲካ ልሂቃን የለገጣፎን ቤት ማፍረስ “ዘር ማጽዳት” ነው በሚል ሃሰት፤ የህዝቡን ቁስል፤ ለራሳቸው ርካሽ የሆነ የፖለቲካ ትርፍ ሲጠቀሙበት ተስተውሏል። እነዚሁ ሰዎች ናቸው፤ በተሳሳተ እና በተዛባ መንገድ፤ “ይሰቀል” “ይሰቀል” የሚመስል መፈክራችውን ያስተጋቡት እና የፖለቲካ ትኩሳቱንም ከሚገባው በላይ ያጋጋሉት። እነሱ ባነሱት የሃስት ትርከት፤ የማንወጣው፤ የእርስ በእርስ ግጭት ውስጥ ልንገባ እንችል ነበር። ደግነቱ፤ ይህ መርዝ የተረጨው፤ ፈሪሃ እግዚአብሄር ባለው ታላቅ ሕዝብ መካከል በመሆኑ፤ የመርዙ ችግኝ ምቹ መሬት ስላላገኘ፤ የጥፋት ፍሬ ሊያፈራ አልቻለም።
ሁላችንም፤ በለገጣፎ/ለገዳዲ ከተማ መስተዳድር፤ ከተከሰተው አሳዛኝ ክስተት ትምህርት ልንወስድ ይገባናል። አሁንም፤ ቤታቸው የፈረሰባቸው ሰዎች የእኛን አገዝ ይፈልጋሉ። ጣታችን እስኪቆስል፤ ውግዘት ለማዥጎድጎድ የኮምፕዩተራችን ቁልፍ ላይ የምንቀጠቅጠውን ያክል፤ የመፍትሔ ሃሳብም እናፍልቅ። እንደማመመጥ፡ ስድቡ፤ ለሌላ ጊዜ ይቆይልን፤ የትም አይሄድብንም። ስድብ፤ የሃሳብ ማመንጨት ድርቀት ነው። ሃገራችን፤ ብዙ የተወሳሰበ ችግር አለባት። የተጠመደችበትን፤ የፖለቲካ ነቀርሳ ለመፈወስ፤ ሌት ተቀን በትጋት የሚሰሩ ሰዎችን፤ በማይመለከታቸው ጉዳይ፤ “ሰው ሲያነጥስ ለምን መሃረብ አላቀርቡም ብለን አናውግዛቸው።” ለሚሰሩ ጥፋቶች፤ ተመጣጣኝ ትችት እና አስተያየት እንስጥ፤ ያለችን አንድ ሃገር ናት፤ የሁላችንንም ርህራሄ፤ የሁላችንንም በጎ አመለካከት፤ የሁላችንንም መተባበር እና መተሳሰብ ትፈልጋለች። እንኳን እይተናቆርን፤ ተባብረንም፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ የማንወጣው ብዙ ችግር አለብን።
መንግሥትም ቢሆን፤ ለሚሰሩ ስህተቶች እና የሕግ ጥሰቶች፤ ተመጣጣኝ እና፤ ማህበራዊ እና ኢኮኖምያዊ ቀውስ የማይፈጥር መፍትሔ መፈለግ አለበት። የፖለቲካ ልሂቃኑ እና አክቲቪስቶችም፤ የሚሰነዝሩት ትችት፤ ከጥፋቱ ጋር ተመጣጣኝ መሆን አለበት። ትችት ሲስነዝሩም ከአማራጭ መፍትሔ ጋር ቢሆን ይመረጣል። “ተደማጭነት አገኛለሁ” በሚል በሽታ ግን፤ የሚሰቀሉት አግባብ የሌላቸው መፈክሮች፤ እንዳወጣጣቸው፤ አወራርዳቸው ቀላል እንደማይሆን መረዳት ያስፈልጋል። ዛሬ ይሰቀል ብለው ያሰቀሉትን፤ ነገ አዲስ ሕይወት ሊዘሩለት አይችሉም። አሳሳችች ጩኸታችን፤ ልናርመው የማንችለው ስህተት ሊያሰራ እንደሚችል፤ ልብ እንበል። በተለይ ጋዜጠኞቻችን፤ እጅግ በጣም ሃላፊነት የተሞላበት ሥራ መስራት ይጠበቅባቸዋል። ልዩነት ከማስፋት እንቆጠብ፤ ትልቁ ትግል፤ ሃገራችን እንዳትፈርስ፤ ሕዝባችን ወደ የእርስ በእርስ ግጭት ውስጥ እንዳይገባ ተግቶ መስራት ነው። ከ40 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ከድህነት ወለል በታች የሚኖርባት ሃገር እንደያዝን አንዘንጋ። ሰዎችን በዘር መመዘን እናቁም፤ ዘረኝነትን እንጠየፍ። አንዳችን ሌላችን ላይ ለመረማመድ ሳይሆን፤ አንዳችን በአንዳችን ትከሻ በመደጋገፍ፤ ሃገራችን የሚኖራትን መፃኢ እድል ብሩህ እናድርግ። አለዝያ፤ እንዳለፈ ታሪካችን፤ መሰቀል የማይገባቸውን፤ “ይሰቀል” ብለን እየሰቀልን፤ ወደ ማይቀርለት ውድቀት እናመራለን።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ይጠብቅ።
___
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።