spot_img
Thursday, May 30, 2024
Homeነፃ አስተያየትበአዲስ አበባ ጉዳይ ከመካረርና ከመጋጨት ሁሉም አሸናፊ ሊሆን የሚችልበት መፍትሔ ማግኘት ይሻላል...

በአዲስ አበባ ጉዳይ ከመካረርና ከመጋጨት ሁሉም አሸናፊ ሊሆን የሚችልበት መፍትሔ ማግኘት ይሻላል (ከብርሃኑ ጉተማ ባልቻ)

ከብርሃኑ ጉተማ ባልቻ
የካቲት 29 2011 ዓ.ም.

Berhanu Gutema _ Addis Ababa
ከብርሃኑ ጉተማ ባልቻ
የአዲስ አበባ ነገር የሕዝቡን አብሮ የመኖር መንፈስ እየገዘገዘ ያለ ኃይለኛ ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። እሳቱ ውስጥ ለውስጥ እየጋመ ያለና አንድ ቀን ሊፈነዳ እንደሚችል እሳተ ገሞራ አስቦ ሰላማዊ መፍትሔ ለማግኘት መሞከር የግድ ይላል። የአዲስ አበባ ጉዳይ በአዲስ አበባ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን አጠቃላይ አገሪቱን ወደ አደገኛ ትርምስ የሚከት ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ይህንን ያንዣበበ መከራን በሰላም ለመወጣት አዲስ አበባ እና አካባቢው ከሃያ አምስት አመት በኃላ ምን ሊመስል ይገባዋል የሚለውን ማሰብ የተሻለ መፍትሔ ሊያመጣ ይችላል። አዲስ አበባ በከተማው የሚኖረውን የኢትዮጵያዊ መብት ሳይጣስ፤ የአካባቢውን አርሶ አደር ሕይወትና ቋንቋ ሳይደፈጥጥ፤ እንዲሁም ጎረቤቱ ከሆነው የኦሮሚያ ክልል ጋር የሚኖረውን መልካም ግንኙነት በማዳበር ለሁሉም ጠቃሚ ሊሆን የሚችል መፍትሔ ማግኘት ይቻላል።

በሰላም አብሮ ለመኖር ከታሰበ አዲስ አበባ ውስጥ የሚኖረው ከአምስት ሚሉዮን የሚበልጥ ኢትዮጵያዊ በራሱ አገሩ ውስጥ እንደሚኖር መረዳትና የከተማውንም የወደፊት እድገት እንደ አገሪቱ ርዕሰ ከተማነትንና የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ ከተማነትን ግምት ውስጥ አስገብቶ ማየት እና አዲስ አበባን በመቶ ኪሎ ሜትር ዙሪያ ከቦ ከሚኖረው የኦሮሞ ሕዝብ ጋርም ሊያስማማ የሚችል መፍትሔ ያስፈልጋል። የት ይደርሳሉ? ምን ያመጣሉ? የሚል የግጭትና የኃይል ፖለቲካ መንገድ ለአዲስ አበባም ሆነ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር መፍትሔ አያመጣም። የድሮውን ይዞ ወይም አሁን ላይ ብቻ ተቸንክሮ ከመቅረት ወደፊት ሊሆን የሚችለውን ለማየት መሞከር መፍትሔ ሊያመጣ ይችላል። የከተሞች መስፋፋት የማይቀር ክስተት ነው። አዲስ አበባ ከአሁን በኃላ ወደ ላይ እንጂ ወደ ጎን መስፋት አይገባውም የሚለውም አስተሳሰብም ዝም ብሎ ለፖለቲካ ሲባል የሚነገር እንጂ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል አስተሳሰብ አይደለም። በዩኤን ግምት መሠረት በ2050 ወደ ሰባ በመቶ የሚጠጋ የአለማችን ሕዝብ በከተሞች ይኖራል። በተለይም በታዳጊ አገሮች ውስጥ የከተሞች እድገት በጣም ከፍተኛ ይሆናል። የአዲስ አበባንም ሁኔታ በዚህ እይታ ማየት ይገባል። የአዲስ አበባ ሕዝብ በየሃያ አምስት አመቱ በእጥፍ ይጨምራል። ስለዚህ አዲስ አበባ የግድ መስፋት ይኖርበታል። ከተማው በፓለቲካ መካረር ምክንያት መስፋፋቷ ተገድቦ ታፍኖ መሰቃየትና መታነቅ አይገባውም። በከተማው መስፋትም ምክንያት ደግሞ በዙሪያው የሚገኘው አርሶ አደር ሕይወት መመሰቃቀልና ቋንቋው መጨፍለቅ የለበትም። እየታነቀ ዝም ብሎ የሚቀበል እንደማይኖር ሁሉ፤ እየተጨፈለቀም ዝም ብሎ የሚቀበል አይኖርም።

ይሄ ከተማው የኛ ነው ፖለቲካ የሚያቀራርብ መፍትሔ አያመጣም። አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆና በዙሪያዋ የነበረውን የኦሮሞ አርሶ አደር ያለበቂ ካሣ እያፈናቀለች ከአራቱም ማእዘን በመጣ ሕዝብ የተገነባች ከተማ በመሆኗ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የጋራ ንብረት ናት። የከተማው ነዋሪም በዴሞክራሲያዊ አሰራር የራሱን በራስ የማስተዳደር መብት ሊጠበቅለት ይገባል። በተጨማሪም ባለፈው ሃያ ስምንት አመታት የግፍና የዘረፋ አገዛዝ ምክንያት እንኳን በየክልሉ የነበሩ ሹመኞች የክልላችን ነባር ተወላጅ አይደለም በሚል በየክልላቸው በሚኖረው ኢትዮጵያዊ ላይ ሲያደርሱ የነበረው የግፍ አስተዳደር የሚረሳ አይደለም። በዚህ አስተደዳር ተማሮ ለእራሱና ለቤተሰቡ ይሻላል በሚል ጓዙን ጠቅልሎ ለዘመናት ወልዶና ከብዶ የኖረበትን ቦታ ሳይወድ በግዱ ጥሎ አዲስ አበባ መኖርያው ያደረገ ኢትዮጵያዊ በጣም ብዙ ነው። ዛሬ ይህን ሕዝብ አገሩ የኔ ነው ያንተ አይደለም ቢባል ያው ለዘመናት ከኖረበት ቦታ ያፈናቀለው ፖለቲካ እንደገና ሲመጣበት የሞት ሽረት ትግል ያደርጋል እንጂ ከዚ በኃላ የት ለመሄድ የሚያስብ ይመስለናል? በአንፃሩ ደግሞ አዲስ አበባ ስትሰፋ ለዘመናት ከኖረበት መሬቱ በግፍ እየተፈናቀለ ቤተሰቡን በትኖ ስድተኛ የሆነውን አርሶ አደርና የአርሶ አደር ቤተሰብ በአዲስ አበባ ጉዳይ ምንም አያገባህም ብንለው ዝም ብሎ የሚቀበል አይሆንም። ስለዚህ ጉዳዩን ከስሜታዊነ በራቀ መንገድ አይቶ ፍትህና ሰላም በሚያመጣ መንገድ መፍትሔ መፈለግ ያስፈልጋል።

የከተማ አንዱ ትልቁ ተግባር የገጠሩን ሕዝብ በሂደት ከተሜ እያደረገ ዘመናዊነትንና እድገትን ማስፋፋት ሲሆን በአቅራቢያው የሚገኘውን የገጠር ማኅበረሰብንም በማካተት ነው። በአቅራቢያው የሚገኘውን የገጠር ማኅበረሰብ ደግሞ ከተሜ ለመሆን ቋንቋውን የግድ መለወጥ ባይገደድ የተሻለ ይሆናል። እስከተቻለ ድረስና ለአገር ግንባታና ለሰላም የሚበጅ ከሆነ ቋንቋውን ሳይተው ከተሜ ሊሆን የሚችልበት ዘዴ መፈልጉ ይሻላል። ቶሎ ዘመናዊና ከተሜ ለመሆንም ሆነ ለኢኮኖሚ ጠቀሜታ ቋንቋ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋልና። ስለዚህ አማርኛ ተናጋሪውንም ሆነ ኦሮምኛ ተናጋሪውን በሚጠቅም ሁኔት መፍትሔ ማግኘት ይቻላል። በአገራችን የሚታየውን አጥባቂ ብሔርተኛነትንም ሊቀንስ ይችላል። ብሔርተኝነት እየጠነከረ የሚመጣበት አንዱ ምክንያት የመጨፍለቅና የመገለል ፍራቻና ጥርጣሬ ነው። ይህንን ፍራቻና ጥርጣሬ መቀነስ ከተቻለ ብሔርተኝነትም እየለዘበ ሊመጣ ይችላል። በአለም ላይ በብሔርና በብሔረሰቦች ግጭት ለአርባ አመት ተመራማሪ የሆኑትና በብዙ አገሮች የደረሱትን የብሔርና የቡድን ግጭቶችን የመረመሩት ታዋቂ አሜሪካዊ ምሁር ፕሮፌሰር ዶናልድ ኤል ሆሮዊትዝ እንደተገነዘቡት የመጨፍለቅና የመገለል ፍራቻና ጥርጣሬን የሚቀንሱ የፖሊሲ እርምጃዎች ብሔርተኝነት እንዳለዘቡና እንደሚያለዝቡም በደንብ አስምረውበታል ። ስለዚህ አስቸጋሪና ከባድም ቢሆን መቼም ቢሆን ከመጨራረስ የሚሻል መፍትሔ መፈለግ ይሻላል።

በአገራችን የከተሞቻችንን እድገት ሁኔታ ያየን እንደሆነ ለበርካታ አሥርተ አመታት ስንተገብረው የነበረው የአገር ግንባታ መርህን የሚያንፀባርቁ ናቸው። በሰሜን ኢትዮጵያና በደቡብ ኢትዮጵያ ያሉ ከተሞች ለየት ያሉ ባህሪያት አላቸው። በተለይ በአማራና በትግራይ አካባቢ ያሉት ከተሞች በዙሪያቸው የከበባቸውን የገጠር ነዋሪ አፍ መፍቻ ቋንቋ የሚናገሩ ሲሆን በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በሱማሌ፣ አፋር የመሳሰሉት አካባቢዎች የተመሠረቱት ከተሞች ግን በዙሪያቸውን የከበባቸውን የገጠር ነዋሪ አፍ መፍቻ ቋንቋ በዋናነት የሚናገሩ አይደሉም። በዚህም ምክንያት በአማራና በትግራይ አካባቢ ያሉት ከተሞች በዙሪያው የሚኖረውን ገጠሬ የአፍ መፍቻ ቋንቋውን ሳይለቅ ከተሜ እያደረጉ ስለሚያድጉ ከከበባቸው የገጠር ነዋሪ ጋር ብዙም የጠላትነት ስሜት ሊያዳብሩ አይችሉም። በተቃራኒው በኦሮሚያና በደቡብ በሚገኙ ከተሞች የከበባቸው የገጠር ሕዝብ ከተሜ ለመሆን አፍ መፍቻ ቋንቋውን የግድ መለወጥ ስለሚገባው ይህ የራሱ የሆነ የኢኮኖሚ የፖለቲካና የማህበራዊ ተፅእኖና ልዩነት ይፈጥራል። ቋንቋ መቻል የከተማን ባህልን ለመማር የተሻለ እድል ይፈጥራል። በተቃራኒው ግን ከአማራና ከትግራይ ውጭ ያሉ ከተሞች የአካባቢውን የገጠር ሕዝብ ቋንቋ ስለማይናገሩ በአካባቢው ያለው የገጠር ሕዝብ ከተሜ ለመሆን ከፈለገ የገጠሬ ባህሉን ብቻ ሳይሆን ቋንቋውንም እየተወ ከተሜ ለመሆን ትልቅ ድካም ያለበት ነው። ቋንቋ ሳይገባህ የከተማ ባህል መማር ደግሞ እጅግ አስቸጋሪ ነው። ድርብ መከራ የሚባለው ይህ ነው። ይህ ደግሞ በሥራም በማህበራዊም ሆነ በኢኮኖሚ እድገት ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ሊያመጣ ይችላል።

የከተማውን ቋንቋ በሚገባ የማይናገር ደሃ የገጠር ሰው በከተማ ውስጥ መለስተኛ ሙያ የሚጠይቅ እንደ አስተናጋጅነት የመሳሰሉ ሥራ እንኳን ለማግኘት ትልቅ ፈተና ስለሚሆንበት በአብዛኛው በጉልበት ሥራ መሰማራት ገዴታው ይሆኗል። ይህ እንግዲህ በቀጣይ በማህበረሰቡ ላይ የሚያሳድረው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖ እጅግ የከፋ ነው። ለዚህም ነው የቋንቋ ጉዳይ ኢትዮጵያ ውስጥ የሞት ሽረት ጉዳይ የሚሆነው። አንዱን አካባቢ ጠቅሞ አብዛኛውን የሚጎዳ መሆን የሌለበት። ከተሜ ለመሆንም ለመሠልጠንም ቋንቋ መሠረት ነው። የከበባቸውን የገጠር ሕዝብ ቋንቋ የማይናገሩ ከተሞች ለአካባቢያቸው ሕዝብ አስቸጋሪ ይሆናሉ። ዘመናዊነትና ትምህርት እየተሰፋፋ የሰብዓዊ መብታና የፖለቲካ እውቀት እየጨመረ ሲመጣ የእራሴን አፍ መፍቻ ቋንቋ እየተናገርኩ ከተሜ መሆን ለምን አልችልም ብሎ መጠየቅ የማይቀር በመሆኑ በአሁኑ ወቅት እዚ ደረጃ ላይ የደረሰ ጠንካራ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ተፈጥረዋል። ለወደፊትም ወቅቱንና እድገቱን ጠብቆ እንደዚህ አይነት ጥያቄዎች ሊጠየቁ እንደሚችሉ መገንዘብ ይበጃል። የሕብረተሰብ እድገት ባለበት ሆኖ የሚቀር አይደለም። ስለዚህ ጥያቄዎቹ ከፍተኛ የፖለቲካ ጥያቄ ላይ ሲደርሱ መፍትሔ ለማግኘት መሞከር ለሁሉም ይበጃል።

የአገራችንም አንዱ ትልቁ የፖለቲካ ቅርቃር የአዲስ አበባ ጉዳይ ነውና ይህንን የፖለቲካ ቅርቃር መፍትሔ ለመፈለግ አዲስ አበባ ወደ ጎን ሲሰፋ ሁለት ከተሞች አዲስ አበባ እና ፊንፊኔ እየሆነ አማርኛና በኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ እየሆኑ አንዲያድጉ ማድረግ ይቻላል። በአንደኛው አቅጣጫ በአብዛኛው አማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሆኖ ሲሰፋ በአዲስ አበባ ከተማ የአስተዳደር የሚተዳደር ሲሆን በሌላው አቅጣጫ ደግሞ በአብዛኛው የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ እየሆነ የሚያድግና በኦሮሚያ ክልል መስተዳደር ስር ያለ ፊንፊኔ በመመሥረት ሁለት ጎን ለጎን አማርኛና ኦሮምኛ ተናጋሪ የሆኑ እህት ከተሞችን ማለም ይሻላል። አማርኛና ኦሮምኛ ተናጋሪ ሲባል በከተሞቹም የሚነገሩት ቋንቋ ሁለት ብቻ ይሆናሉ ለማለት ሳይሆን ወይንም የሚኖሩበት የሁለቱ ቋንቋ ተናጋሪዎች ብቻ ናቸው ለማለት ሳይሆን የከተሞቹ ዋና የሥራ ቋንቋን ለማመልከት እንጂ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ይመቸኛል ብሎ ለመኖር በሚፈልገው ከተማ የመኖር የዜግነቱ መብት ነው።

Addis Ababa _ Ethiopia

በአንደኛው አቅጣጫ በሚኖረው የፊንፊኔ ከተማ በአብዛኛው ኦሮምኛ ተናጋሪ እየሆነ በሚሰፋበት አቅጣጫ ያለው የኦሮሞ አርሶ አደር ምርጫው ተጠብቆ ቋንቋውን መጣል ሳይገደድ ሕይወቱ ሳይመሰቃቀልና የሚከፈለው ካሳ የአርሶ አደሩንና የቤተሰቡን የወደፊት ሕይወት በጥልቀትና በቀጣይነት በማየት የከተማው ነዋሪ የሚሆነበትን መንገድ የሚያመቻች ጥሩ ሕግና ፓሊሲ መቅረፅ ይቻላል። እንደዚሁ በሁለተኛው አቅጣጫ አዲስ አበባ በአብዛኛው አማርኛ ተናጋሪ እየሆነ በሚሰፋበት አቅጣጫ የሚገኘው የኦሮሞ አርሶ አደር ደግሞ ምርጫው ተጠብቆለት ቋንቋውን ሳይለቅ ወደ ከተማ ሕይወት መቀየር ከመረጠ ኦሮምኛ ተናጋሪ እየሆነ በሚሰፋው ፊንፊኔ አቅጣጫ በኩል እንዲኖር በማመቻቸት ሕይወቱ ሳይመሰቃቀልና የሚከፈለውም ካሳ የአርሶ አደሩንና የቤተሰቡን የወደፊት ሕይወት በጥልቀትና በቀጣይነት በማየት ቋንቋውን ሳይተው የከተማው ነዋሪ የሚሆነበትን መንገድ የሚያመቻች ጥሩ ሕግና ፓሊሲ መቅረፅ ይቻላል። በአብዛኛው አማርኛ ወይም ኦሮምኛ ተናጋሪ ቢሆንም ሌላ ቋንቋ ተናጋሪዎችም በሁለቱም በኩል የመኖር መብታቸው የተጠበቀ ነው።

ከመካረርና ከመፈራራት ወጥቶ ሊያስማሙ የሚችሉ መፍትሔዎችን መፈለግ ይሻላል። የኔ መንገድ ካልሆነ ሞቼ እገኛለው የሚለው መንገድ አሸናፊ የማይኖርበት የግጭትና የድህነት መንገድ ነው። የድህነታችንም ዋናው ምክንያት ልዩነቶቻችንን የሚያቻችልና የሚያስማማ መፍትሔ ማግኘት አቅቶን ለሃምሳ አመታት የተከተልነው የግጭትና የኃይል ፖለቲካ መንገድ ነው። በአንዱ ቦታ ኃይልና አቅም አለኝና የፈለኩትን ማድረግ እችላለው አይነት አካሄድ ሌላውም ኃይልና አቅም ባለው ቦታ የፈለገውን እንዲያድርግ በማበረታት አገሪቷን ከፍተኛ ግጭት ውስጥ ይከታል። ምንም ጥርጥር የለውም የእልክና የወኔ ፖለቲካ ህወሃትን ለማሸነፍ ትልቅ እርዳታ አድርጓል። ዴሞክራሲንና ሰላምን ለማምጣት ግን ብዙም አይጠቅምም። ዴሞክራሲ የሚመሠረተው በሰከነ ውይይት በድርድርና በሕዝብ ድምፅ ብቻ ነው። ሰላሳ ሚልዮን ሕዝብ በአደገኛ ድህነት ውስጥ በሚኖርበት አገር፤ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የጐዳና ላይ ተዳዳሪ ልጆችና ሕፃናት ባሉበት አገር፤ ሥራ አጥነት በሚልዮኖች የሚቆጠረውን ወጣት ወደ ተስፋ መቁረጥ ደረጃ እየወሰደው ባለበት አገር የግጭትና የኃይል ፖለቲካ ማራመድ በእሳት እንደ መጫወት ነው።

በተጨማሪም ጥርጣሬና ፍራቻ ሳይወገድ አሁን የትኛውንም ቋንቋ ቢሆን የሥራ ቋንቋ ተብሎ በመንግስት ታውጆ ሕዝብ ላይ ቢጫን ጥላቻንና መከፋፈልን ይበልጥ ያስፋፋ ይሆን እንጂ አመርቂ ጠቀሜታ አይኖረውም። በኢትዮጵይ ደግሞ የቋንቋ ጉዳይ ትልቅ የፖለቲካ ጉዳይ ነው። አማርኛ ተናጋሪ የሚመቸውና የሚፈልገውን ሁሉም ይመቸዋል ወይም ይፈልገዋል ማለት አይደለም። ከኤርትራ ችግር ጀምሮ እስካሁን ድረስ የቋንቋ ጉዳይ እጅግ አከራካሪ የፖለቲካ ጥያቄ ነውና አሳንሶ ማየት በፍፁም ተገቢ አይደለም። ከቋንቋችንን ይልቅ አማርኛ ማስቀደም ይሻለናል የሚሉት መብታቸው እንደሆነ ሁሉ፤ ከአማርኛ ይልቅ የራሳችንን ቋንቋን እናስቀድማለን የሚሉትም መብት እንዳላቸው ማወቅ ይገባል። ነገር ግን ጥርጣሬንና የመጨፍለቅ ፍርሃት ከተወገድ ሕዝቡ ሌሎች ቋንቋዎችን በፍላጐቱ ለመማር የሚችልበት ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ። ስለዚህ ጥርጣሬንና የመጨፍልቅ ፍራቻ ሊቀንሱ የሚችሉ ስምምነቶችና ፖሊሲዎች ማግኘት ዋናው ትልቁ ተግባር ቢሆን ይበጃል። ጥርጣሬንና ፍራቻ ከተወገደ አማርኛና ኦሮምኛ በአዲስ አበባ እና በፊንፊኔ ላይ ያለ ብዙ ችግር እየተደባለቁ የሚያድጉበት ሁኔታ ይፈጠራል። በሂደትም ተቻችሎ የሚኖር አገራዊ አንድነቱ የጠበቀ የተቆራኘ ማኅበረሰብ ለማጐልበት ይጠቅማል። በመከባበር ከተጠቀምንበትና ካለማነው አገሩ ሰፊና ለሁላችንም በጣም በቂ ነው። የአዲስ አበባ የመሬትና የቤት ዋጋ ውድነት ካደጉ አገሮች ምርጥ ከተሞች በላይ እየሆነ የመጣው ተስማምተን ሁላንችንንም በሚጠቅም መልኩ ያለንን ሀብት መጠቀም ባለመቻላችን ነው። የሚሻለንንና የሚያዋጣን የመከባበርና የሰላም መንገድ ብቻ ነው።

ለአስተያየቶ በዚህ ይፃፉ: berhanugbalcha@gmail.com
___
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here