spot_img
Thursday, May 30, 2024
Homeነፃ አስተያየትየስቃይ ገፈት የሚጋተው የጌዲኦ ተፈናቃይ ህዝብ (በመስከረም አበራ)

የስቃይ ገፈት የሚጋተው የጌዲኦ ተፈናቃይ ህዝብ (በመስከረም አበራ)

በመስከረም አበራ

የካቲት 30 2011 ዓ.ም.

ቋንቋን መሰረት ያደረገው የጎሳ ፌደራሊዝም አስከፊ ገፆቹ ብዙ ናቸው፡፡በመሰረታዊነት የሰውን ልጅ በጎሳው ከልሎ ማስተዳደር ከሰውልጆች ተፈጥሯዊ መስተጋብር የማይገጥም አካሄድ ነው፡፡የሰው ልጅ መሬት ጠበበኝ ብሎ ሽቅብ ወደ ጠፈር በሚምዘገዘግበት በዚህ የሰለጠነ ዘመን ቋንቋን መሰረት ያደረገ ክልል ከልሎ አንዱን የክልል ባለቤት ሌላውን ባይተዋር የሚያደርግ አስተዳደር መዘርጋት ከዘመን መጣላት ነው፡፡አሁን ዓለማችን ያለችበት ሁለንተናዊ እድገት እትብት በተቀበረበት አካባቢ ብቻ የሚያስቀምጥ ያህል ቀላል አይደለም፡፡የእኛ ሃገር ፖለቲካ ደግሞ እትብቱ የተቀበረበትን መሬት እያየ እዛው ላልተቀመጠ ሰው የመከራ ገፈት የሚግት ነው፡፡ ዕትብቱ በተቀበረበት ሃገር እየኖረ ያለውም ቢሆን የወላጆቹ፣የሰባት ጉልበቱ እትብት የተቀበረበት ቦታ ሌላ ከሆነ የጎሳ ፖለቲካ ወለድ ስቃዩ አያልፈውም፡፡

እንዲህ ያለው ለወሬ የማይመች ህሙም ፖለቲካዊ መስተጋብር አጀማመሩ ጨቋኝ እየተባለ ባልበላው የሚብጠለጠለውን የአማራ ህዝብ ከሃገሪቱ ዳርቻ ለማሳደድ ተብሎ የተቀመረ የህወሃት፣የሻዕብያ እና የኦነግ ቀመር ነበር፡፡ይህ ደማቅ ውሸት እውነት ተደርገ በመለስ ዜናዊ እና አሽከሮቹ አፍ ሲነዛ ስለኖረ ተቀባይነት አግኝቶ ኖሯል፡፡ የጎሳ ፖለቲካው እና ፌደራሊዝሙ ሲፈጠር የታቀደለትን አማራውን እያደኑ የማሳደዱ ስራ ለረዥም ዘመን በተሳካ ሁኔታ ሲሰራበት ቆይቷል፡፡ሆኖም እሳትን ሃላፊነት በማይሰማው ሁኔታ ካያያዙት በኋላ አካሄዱን የሚወስነው ራሱ እሳቱ ነውና ከባለቤቱ ቁጥጥር ውጭ ሆኖ ያገኘውን ሊበላ ይችላል፡፡የሃገራችን የዘር ፖለቲካም እንዲያ ነው!አማራውን ለመብላት ተብሎ ነደደ ውሎ አድሮ ግን ‘አማራው በአንድ ላይ ሲጨቁናቸው የኖሩ ናቸው’ የተባሉ ዘሮችምን እርስ በርስ እያናከሰ ይገኛል፡፡የጌዲኦ እና የጉጅ ህዝቦች ለሌላ የነደደው የጎሳ ፖለቲካ እሳት እየለበለባቸው ያሉ ህዝቦች ናቸው፡፡

የጌዲኦ እና የጉጅ ህዝቦች ለረዥም ዘመን አብረው የኖሩ፣ እኩል በእኩል በሆነ ሁኔታ ኦሮምኛም ኤዲኦኛም የሚናገሩ ህዝቦች ናቸው፡፡ሁለቱን ህዝቦች በሚናገሩት ቋንቋ “ጉዲኦ” እና “ጉጅ” ብሎ መለየት አስቸጋሪ እንደሆነ በህዝቦቹ ላይ ጥናት ያደረጉ ምሁራን ፅፈዋል፡፡በተለይ በጉጅ እና በጌዲኦ ድንበር አካባቢ “ጌዲኦ” በሚል የሚጠራ ሰው “የጉጅ ኦሮሞ” ከሚባለው ሰው ባልተናነሰ ኦሮምኛን የሚያቀላጥፍ ነው፤ጉጅውም እንደዛው ጌዲኦኛን አቀላጥፎ ያወራል፡፡በዚህ ምክንያት ህዝቦቹን ለይቶ በአንድ ክልል መከለል አስቸጋሪ ነው፡፡ በታሪክም ቢሆን ጦር አዋቂዎች እና ሃይለኞች ተደርው የሚወሰዱት የጉጅ ኦሮሞዎች እንደነሱው ኦሮሞ ከሆኑት ቦረናዎች፣አርሲዎች እና ሲዳማዎች ጋር በተለያየ ምክንያት የመጋጨት ታሪክ ያላቸው ሲሆኑ ከጌዲኦዎች ጋር ግን የስምምነት እና የትብብር ታሪክ እንዳላቸው ነው ጥናቶች የሚያሳዩት፡፡

የጦር አዋቂነታቸው የሚነገርላቸው ጉጅዎች ከጌዲኦ ጋር የስምምነት ታሪክ ሊኖራቸው የቻለው አንድም ጌዲኦዎች እህል አምራች፣ጉጅዎች ደግሞ ከብት አርቢ በመሆናቸው በምርት ልውውጥ ተደጋግፈው የሚኖሩ በመሆኑ፣ሁለትም ጌዲኦዎች እምብዛም የጦረኝነት ባህል ስለሌላቸው በግብርና ላይ የሚያተኩሩ ህዝቦች በመሆናቸው ጌዲኦዎችን መውጋት በጉጅዎች ዘንድ ተቀባይነት ያለው ተግባር ስላልሆነ፣ ሶስትም ‘በጌዲኦ እና በጉጅ ቀደምት አባቶች ዘንድ በሁለቱ ህዝቦች መሃል መጋደል እንዳይኖር የተደረገ መሃላ አለ፤ይህን መተላለፍ እርግማን ያመጣል’ ተብሎ የሚታመን እምነት ስላለ እንደሆነ አሰበ ረጋሳ “Ethnicity and Inter-ethnic Relations: the ‘Ethiopian Experiment’ and the case of the Guji and Gedeo” በሚል ርዕስ የሰራው ጥናት ያመለክታል፡፡እነዚህን ኢኮኖሚያዊ እና ባህላዊ እሳቤዎች ተላልፎ አንዳንዴ በሁለቱ ህዝቦች መሃከል ግጭት ቢከሰት እንኳን “ጎንዶሮ” በሚባው በሁለቱም ህዝቦች እኩል በሚሰራበት የይቅርታ እና እርቅ ባህል አማካይነት ሰላም ሲወርድ እንደኖረ ይሄው ጥናት ያስረዳል፡፡

እንደዚህ በሰላም የኖሩ ህዝቦች ዛሬ ለመጋደል እና ለመፈናቀል/ማፈናቀል ያበቃቸው ምንድን ነው? የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡የአሁኑ ቋንቋን መሰረት ያደረገው ፌደራሊዝም ስራ ላይ ከመዋሉ በፊት የጌዲኦ እና ጉጅ ህዝቦች የሲዳሞ ክፍለሃገር በሚባለው አከላለል ውስጥ አብረው ተከልለው ይተዳደሩ ነበር፡፡ሆኖም የጎሳ ፌደራሊዝም ስራ ላይ ሲውል ጉጅዎቹ ወደ ኦሮሚያ ክልል፣ጌዲኦዎቹ ደግሞ በደቡብ ክልል ውስጥ እንዲተዳደሩ ሆነ፡፡እነዚህ ህዝቦች ግን እንደማንኛውም አብሮ እንደኖረ ህዝብ የተቀላቀሉ ስለሆኑ በጌዲኦ እና ጉጅ መሃከል መስመር አውጥቶ፣ በተለያዩ ክልሎች ውስጥ ማካለሉ እጅግ አስቸጋሪ ነገር ፈጠረ፡፡በዚህ ምክንያት ብዙ ጉጅዎች በደቡብ ክልል ወደሚገኘው ወደ ጌዲኦ ዞን ፣በርካታ ጌዲኦዎች ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ወደሚገኘው ምዕራብ ጉጅ ዞን እንዲካለሉ ሆነ፡፡

በዚህ አከላለል ጉጅዎች በተለይ ‘በርካታ መሬቶች ወደ ጌዲኦ ተካለውብናልና ራሳችንን በራሳችን የማስተዳደር መብታችንን ተነፍገናል፤ያለ አግባብ በጌዲኦ ዞን ስር እንድንተዳደር በመደረጋችን ማንነታችን ተጨፍልቋል፣የትምህርት፣የስራ እና የስልጣን እድል ከጌዲኦዎች እኩል እያገኘን አይደለም’ የሚል ቅሬታ ለመንግስት ያቀርባሉ፡፡ጌዲኦዎች በበኩላቸው በርካታ መሬታችን ያለ አግባብ ወደ ኦሮሚያ ክልል ጉጅ ዞን ተካሏል፣እስከ ቡሌ ሆራ(ሃገረ ማርያም) ድረስ ያለው መሬት ይባናል የሚል ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ ይሄው ንትርክ ወደ ግጭት አድጎ በ1987 ዓም ላይ በሁለቱ ብሄረሰቦች መሃከል2000-3000 ሰዎችን ህይወት የቀጠፈ ትልቅ መጋደል አስከትሎ ነበር ይላል ከላይ የተጠቀሰው የአሰበ ረጋሳ ጥናት፡፡

ይህን መጋደል ለማስቆም በኦህዴድ የሚመራው ኦሮሚያ ክልል እና በደኢህዴን የሚመራው ደቡብ ክልል ከፌደራሉ መንግስት ጋር በመተባበር በአከራካሪዎቹ ስድስት ወረዳዎች ላይ ህዝበ-ውሳኔ እንዲደረግ ሆነ፡፡በህዝበ ውሳኔው መሰረት አራት ወረዳዎች እዛው ጌዲኦ ዞን ውስጥ እንዲረጉ ሲሆን ቀሪዎቹ ሁለቱ ወረዳዎች ወደ ኦሮሚያ ክልል ጉጅ ዞን እንዲካለሉ ተደረገ፡፡ ሆኖም መፍትሄ ያመጣል የተባለው ሪፈረንደም ጌዲኦዎቹንም ሆነ ጉጅዎቹን ሊያስደስት የሚችል አልሆነም፡፡’የፌደራሉ መንግስት በብሄር ፌደራሊዝሙ ብዙ ግዛታችንን ለጌዲኦዎች ሰጥቶብናል’ ብለው የሚያስቡት ጉጅዎቹ ‘ሪፈረንደሙን የመራው መንግስት ለጌዲኦዎች ያደላል’ ብለው ያስባሉ፡፡በዚህ ላይ ከስድስቱ አራቱ ተመልሰው ወደ ጌዲኦ ዞን መካለላቸው ቅሬታቸውን አባብሶታል፡፡ጌዲኦዎች በበኩላቸው ‘በሪፈረንደሙ ለጉጅዎች የተሰጠው ሁለት ወረዳ መሬት ያለአግባብ የሄደ ለእኛ የሚገባ ነው’ ብለው ያስባሉ፡፡

በዚህምክንያት ሪፈረንደሙ የታሰበውን ሰላም ሳያመጣ ቀረ፡፡አካባቢውም በሁለቱ ብሄረሰቦች በሚነሳ ግጭት ውጥረት እንዲቀጥል ሆነ፡፡ውጥረቱ ተባብሶ በ1990 የበርካታ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈ ላይ ሌላ ግጭት ተቀሰቀሰ፤የበርካታ ሰዎች ህይወት አለፈ፡፡የፌደራል መንግስቱ ተከታታይ ስብሰባዎችን እና ባህላዊ የእርቅ ስነ-ስርዓቶችን ቢያከናውንም በሁለቱ ህዝቦች መካከል የቀደመ ሰላማቸውን መመለስ አልተቻለም፡፡ከሪፈረንደም እስከ ጎንዶሮ ድረስ የሚያደርገው ሙከራ ሁሉ ያልተሳካለት ህወሃት መራሹ ፌደራል መንግስት መላ ሲጠፋው እንደሚያደርገው የጉጅዎች እንቅስቃሴ በኦነግ የሚደገፍ ነው እያለ ሰዎችን ማሰር ጀመረ፡፡እስሩ በጉጅ ኦሮሞዎች ዘንድ የሃይማኖት መሪ ተደርጎ የሚታመንበትን አባ ቃሉ እስከማሰር ደረሰ፡፡የታሰሩት አባ ቃሉ እስርቤት ህይወታቸው ማለፉ የጉጅ ኦሮሞዎችን ቁጣ አባባሰው፡፡መንግስትም በመላ-ቢስ እስሩ እና የጉልበት አካሄዱ ቀጠለበ፡፡

የመንግስት ጉልበት የበረታባቸው ጉጅዎች መንግስት የሚያንገላታቸው ለጌዲኦዎች አግዞ እንደሆነ መገንዘብ ጀመሩ፡፡መንግስትም የጉጅዎቹን እንቅስቃሴ ከኦነግ ጋር አያይዞ በጭካኔው ቀጠለበት፡፡ይህ የመንግስት ብስልት የጎደለው አካሄድ በጌዲኦ እና ጉጅ ታጋዮች መካከል ያለውን መቃቃር እያባባሰው ሄደ፡፡በዚህ መሃከል በሁለቱም ዞኖች ውስጥ የሚኖረው የጉዲኦም ሆነ የጉጅ ህዝብ እንግልት ውስጥ ወደቀ፡፡በተለይ በጉጅ ዞን የሚኖሩ ጌዲኦዎች ህይወታቸውን አደጋ ላይ በሚጥል መጥፎ ሁኔታ ውስጥ መኖር ጀመሩ፡፡

ነገሮችን ከማሻሻል ይልቅ በማባሱ የጉልበተኝነት አካሄድ ሲሄድ የኖረው ህወሃት ከማዕከላዊ ስልጣ ወርዶ ኦዴፓ ስልጣን ሲይዝ፣ኦነግ ደግሞ በአካባቢው መንቀሳቀስ ሲጀምር በጉጅዎቹ በኩል እንቅስቃሴው እየተፋፋመ ሄደ፡፡ኦነግ በአካባቢው የሚንቀሳቀስ መሆኑ ደግሞ በጉጅ ዞን ለሚኖሩ ጌዲኦዎች እጅግ አደገኛ ሁኔታ ፈጠረ፡፡አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ወደ ስምንት መቶ ሽህ የሚደርሱ ጌዲኦዎች ጉጅ ዞንን ለቀው ወደጌዲኦ ዞን እንዲፈናቀሉ ሆነ፡፡የተፈናቃዩ ብዛት የረድኤት ድርጅቶችን ጉልበት ፈተነ፡፡ህፃናት በክረምት ከቤታቸው ወጥተው በአሳዛኝ ሁኔታ ሜዳ ላይ ፈሰሱ፣ከትምህርት ገበታቸው ተፈናቀሉ፣ሴቶች፣አዛውንቶች በማያውቁት ሰበብ ከቤታቸው ወጥተው ሜዳላይ ወደቁ፡፡የዚህ ሁሉ ምክንያቱ ባለፈው የህዝብ ቆጠራ መሰረት በምዕራብ ጉጅ ዞን 14% የሚሆነው ሰው ጌዲኦ ሆኖ በመገኘቱ ውለው አድረው ከተባዙ መሬቱ የእኛ ነው የሚል ጥያቄ ያመጣሉ የሚል እሳቤ ከጉጅዎቹ ዘንድ በመነሳቱ ነው፡፡ይህ ከጎሳ ፌደራሊዝሙ ያገኘነው አስከፊ ቱርፋት ነው ንፁሃንን ከቤታቸው አውጥቶ እያንገላታ ያለው!

መፈናቀሉ ከአንድ አመት በፊት ሲጀመር ስምንት መቶ ሽህ የሚደርሰው የጌዲኦ ተፈናቃዮች ቁጥር አሁን ወደ 1.4 ሚሊዮን እየተጠጋ እንደሆነ “irinnews.org” የተባለው ድረ-ገፅ “Etheiopia’s Neglected Crisis: No easy way home for doubly displaced Gedeos” በሚል ርዕስ ከቀናት በፊት ባወጣው ፅሁፍ አስነብቧል፡፡ ይህ ቁጥር ሃገራችንን በሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች ብዛት ከዓለም አንደኛ ያደርጋታል፡፡የድረ-ገፁ ዘገባ ተፈናቃዮቹ ከአንድ አመት ለዘለለ ጊዜ ከቤታቸው ወጥተው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሊያዙበት ይገባል ብሎ ካወጣው መስፈርት እጅግ በወረደ ሁኔታ እየኖሩ፣ህፃናት በምግብ እጥረት እና በሽታ እየተሰቃዩ እንደሆነ ያትታል፡፡

እንደ ዘገባው አራት በአራት በሆነች ድንኳ ውስጥ የአራት አባወራ ወደ ሰላሳ የሚጠጉ በተሰቦች ተፋፍገው ይኖራሉ፡፡በዚህ ላይ የረድኤት ድርጅቶች ገብተው እነዚህን ወገኖች እንዳይታደጉ መንግስት በምዕራብ ጉጅ ዞን አድርጎ ወደ ተፈናቃዮቹ የሚወስደውን መንገድ ጠርቅሞ ዘግቷል፡፡በዚህ ምክንያት ህፃናት፣አረጋዊያን ሴቶች እና ሌሎች ተፈናቃዮች ኮሌራን በመሰለ ተላላፊ በሽታዎች፣በምግብ እጥረት፣በውሃ እጦት እየተሰቃዩ እና ማንም ሳያውቅላቸው እያለቁ እንደሆነ ጋዜጠኛው ያነጋጋራቸው የዓለም አቀፍ ረድኤት ድርጅት ሰራተኞች ተናግረዋል፡፡መንግስት ወደ ተፈናቃዮቹ የሚወስደውን መንገድ ለረድኤት ድርጅቶች የዘጋው ተፈናቃዮቹን ወደ ነበሩበት ወደ ምዕራብ ጉጅ ዞን እንዲመለሱ ለማስገደድ ነው ይላሉ የረድኤት ሰራተኞቹ፡፡ተፈናቃዮቹ ደግሞ ከአንድም አራት ጊዜ በኦሮሚያ ክልል ጉጅ ዞን ወደሚገኘው ቀያቸው ለመመለስ ሞክረው በታጣቂ ቡድኖች እና ዘረኛ ጎረምሶች በደረሰባቸው ህይወትን አደጋላይ የሚጥል ማስፈራራት እና ዘረፋ ምክንያት ወደ ጌዲኦ ዞን መልሰው መላልሰው ለመፍለስ ተገደዋል፡፡

ጋዜጠኛው ያነጋገራቸው ተፈናቃዮች እንደሚሉት የመንግስትን ቃል አምነው እና አክብረው ተወልደው አድገው ወደኖሩበት የጉጅ ዞን ቀያቸው ሲመለሱ በተመለሱበት ቀን ማግስት ማታ በቡድን ሆነው የሚመጡ ታጣቂዎች እና ስለታማ ነገር የያዙ ጎረምሶች ይዘውት የመጡትን ነገር ሁሉ ተዘርፈው፣ቀየውን ለቀው እንዲሄዱ ጥብቅ ማስፈራሪያ እንደተነገራቸው ይገልፃሉ፡፡በዚህ ሁኔታ ከአንድም አራት ጊዜ ስለተመላለሱ ጉጅ ዞን መሄድ እንደሚያፈራቸው እና እንደማይፈልጉ አበክረው ገልፀዋል፡፡ ሆኖም መንግስት የተፈናቃዮቹን ደህንነት በአስተማማኝ ደረጃ ባላስጠበቀበት ሁኔታም ሰዎቹ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ይፈልጋል ብቻ ሳይሆን ያስገድዳል፡፡መንግስት የተፈናቃዮቹን መመለስ የሚፈልገው በቅርቡ አደርገዋለሁ ለሚለው ህዝብ ቆጠራ በቀያቸው እንዲገኙ ነው፡፡በተጨማሪም “ተፈናቃዮቹ አሁን ተመልሰው ሚያመርቱትን መሬት ለመጭው ክረምት ለእርሻ ካላዘጋጁ በሚቀጥለው አመት ተረጅ እንዳይሆኑ ስጋት ስላለን ነው” ይላሉ የአደጋ መከላከል ኮሚሽነሩ አቶ ምትኩ ካሳ ለድረ-ገፁ በሰጡት መልስ፡፡በሞት ሰቀቀን እና በከፍተኛ የስነልቦና አለመረጋጋት ላይ የቆየ ህዝብ እንዴት አምራች ሊሆን እንደሚችል ተናጋሪው ባለስልጣ ብቻ ናቸው የሚያውቁት፡፡

ይህ የመንግስት ምክንያት እጅግ አሳዛኝም ሰብዓዊነት የጎደለውም ነው፡፡በመጀመሪያ ነገር እነዚህ ተፈናቃዮች አንድ አመት ሙሉ ሲንገላቱ እንደ መንግስት ስቃያቸውን በሚመጥን ሁኔታ ትኩረት አልተሰጣቸውም፡፡ አንድ የተደረገ ነገር ቢኖር የሰላም ሚኒስትር የተባሉት ወ/ሮ ሙፈሪያት ከሚል አምና ተፈናቃዮቹን መጎብኘታቸው ነበር፡፡የሚኒስትሯ ጉብኝት “ከተፈናቃዮቹ ውስጥ 90%ን ወደቀያቸው መልሰን እያቋቋምን ነው” የሚል የውሸት ሪፖርት ከማዥጎድጎድ ውጭ ያመጣው ነገር የለም፡፡እንዴውም ወ/ሮ ሙፈሪያት ራሳቸው ተፈናቃዮቹ ወደቀያቸው እስካልተመለሱ ድረስ የረድዔት እርዳታ እንዳይደርሳቸው መንገድ መዘጋት እንዳለበት ማዘዛቸውን ነው ከላይ የተጠቀሰው ድረ-ገፅ ያስነበበው፡፡

ተፈናቃዮች ወደቀያቸው ከተመለሱ ህይወታቸው አደጋ ላይ መሆኑን ከአንድም ሶስት አራት ጊዜ በተግባር ተመላሰው አረጋግጠው እየተናገሩ በግድ ካልተመለሱ የረድኤት አቅርቦት እንዳይደረግላቸው የማዘዝ ጭካኔ መንግስትነትን ቀርቶ ተራ ሰውነትን አይመጥንም፡፡ችግር ባይሆንበት ማንም ከቤቱ ወጥቶ ሜዳላይ የመሰጣት እና በረሃብ የማለቅ ፍላጎት የለውም፡፡ ሰዎቹ የኖሩበትን መንደር የፈሩት ያዩትን አይተው ነው፡፡በጉጅ ዞን ኦነግ ከነጠመንጃው እንደሚንጎራደድ እየታወቀ፣መንግስት ራሱ በቴሌቭዥኑ “ይህን ያህል ወረዳ በኦነግ ቁጥጥር ስር ነው” እያለ እየተናገረ ምስኪን ሰዎችን ወደሞት ሂዱ ካልሆነ እዚህ በረሃብ ሌላ ሞት ይጠብቃችኋል ማለት በጣም አሳዛኝ አረመኔነት ነው፡፡

የሰው ልጅ ተፈናቃይም ቢሆን ክብር ያለው፣በምርጫው መኖር ያለበት ፍጡር ነው፡፡የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ሲመለሱ ህይወታቸውን አደጋ ላይ የሚጥል ስጋት ሳይኖራቸው፣በግድ ሳይሆን ወደው፣መመለሳቸው ሌላ መፈናቀል እንደማያስከትል ተረጋግጦ፣ሰብዓዊ ክብራቸውን ባስጠበቀ ሁኔታ መሆን እንዳለበት ደነግጋል፡፡ይህ ቀርቶ ባዕዳን ረጅዎች ለሰዎቹ የእለት ጉርስ ሚደርስበትን ነገር ሲጠይቁ የራስን ወገን በረሃብ ለመግደል መጨከን በጣም አሳዛኝ ነገር ነው፡፡

ከመንግስት በተጨማሪ የኢትዮጵያ ህዝብም ከሱማሌ ክልል ለተፈናቀሉ፣ከአዲስ አበባ ዙሪያ ለሚፈናቀሉ ወገኖቹ የሚያሳየውን የወገንተኝነት መቆርቆር በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩት የጌዲኦ ተፈናቃዮችም ማሳየት አለበት፡፡ችግራቸውን በተለያዩ ሚዲያዎች ማንሳት አለበት፤በፍጥነት ወደተረጋጋ ኑሯቸው የሚመለሱበት መንገድም የሚገኘው ለነገሩ ትኩረት ሰጥቶ በመነጋገር ነው፡፡እነዚህ ሰዎች በየማህበራዊ ድረ-ገፁ ብቅ እያለ ወደቀ ሲባል ተሰበረ የሚል ዘረኛ አክቲቪስት ስለሌላቸው ሰማይ ሙሉ ችግራቸው እንደቀላል ነገር መቆጠር የለበትም፡፡እነዚህ ተፈናቃዮች ለሁላችንም ወገን የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ናቸውና ሰብዓዊነት የሚሰማው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ብሶታቸውን ሊያስተጋባላቸው ያስፈልጋል፡፡
___
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here