spot_img
Tuesday, October 3, 2023
Homeነፃ አስተያየትሕዝቡ፤ ከመሪዎቹ እውነት እንዲነገረው ይጠብቃል (ከጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ)

ሕዝቡ፤ ከመሪዎቹ እውነት እንዲነገረው ይጠብቃል (ከጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ)

advertisement

ከጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ
(መጋቢት 8 2011 (03/17/2019))

“እውነት ጫማዋን እስክታጠልቅ ድረስ፤ ውሸት ግማሽ ዓለምን ያዳርሳል” ማርክ ትዌን

በጌዴኦ ሕዝብ ላይ ለደረሰው የጠኔ ግፍ እና የሕይወት ህልፈት፤ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ መራሹ መንግሥት ከተጠያቂነት ሊያመልጥ የሚችልበት ምንም ዓይነት መንገድ የለም። ምንም ዓይነት፤ ሃሰት፤ ምንም ዓይነት ሰበብ፤ የተሰራውን ጥፋት ሊሸፍነውም አይችልም። ይህችን ጽሁፍ እንድጭር ያደረግኝ፤ በፌስ ቡክ ገፄ ላይ “በጌዴኦ ሕዝብ ላይ ለደረሰው ግፍ፤ ዶ/ር አብይም/ አቶ ለማም፤ የደቡብ ክልልም ሊወገዙ፤ እኛም ተጠያቂ ልንሆን ይገባል።” በሚል ርዕስ ስር አጭር ጽሁፍ ከለጠፍኩ በኋላ፤ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ እና ከሰላም ሚኒስትር ቢሮ የተሰጠውን መግለጫ እጅግ ስላሳዘነኝ ነው። አንድ የሃገር መሪ፤ በሃገር ውስጥ፤ ተቀባይነቱ ሊቀጥል የሚችለው እና የሕዝቡን ልብ ማሸነፍ የሚችለው፤ በሥራው ላይ ለሚያጋጥሙት መሰናክሎች እና ችግሮች፤ እንዲሁም፤ የራሱን ድክመቶች፤ በመገንዘብ፤ ለሕዝብ እውነቱን ሲናገር ብቻ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰለቸው እና ከጫንቃው ላይ አሽቀንጥሮ መጣል የሚፈልገው፤ ውሸት የሚናገሩ መሪዎችን እና የማይሆን ሰበብ እየሰጡ፤ ድክመታቸውን ለመሸፈን የሚጥሩ ገዥዎችን እና መሪዎችን ነው።

እኔ እንደማምነው፤ ዶ/ር አብይ፤ ብዙ መልካም ነገሮችን በአጭር ጊዜ ሰርተዋል፤ ብዙ ሲደክሙም እያይሁ ነው። የፖለቲካ ባህላችንን ለመለወጥ የሚያደርጉት ትግል እና እየሰሩ ያለው በጎ ሥራ ሊያስመሰግናቸው እና ሊያስወድሳቸውም ይገባል። ይህቺን ሃገር ወደ ተሻለ የፖለቲካ ሥርዓት ለማሸጋገር፤ ሃላፊነቱን ሲቀበሉ፤ ‘ሁሌም እውነቱን እነግራችኋላሁ፤ ምንም የምደብቀው ነገር የለም’ ሲሉም ቃል ገብተዋል። ይህ ከአንድ የሃገር መሪ የሚጠበቅ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያውያን ለዓመታት፤ ከመሪዎቻችን የምንጠብቀው አመለካከት ስለነበር፤ በሃገራችን አዲስ የፖለቲካ አየር ለመንፈሱም ምልክት ሆኖ ቆይቷል። እንዲህ ዓይነት ንግግሮችንም፤ ከቀድሞው የአሜሪካን መንግስት ፕሬዝዳንት፤ ባራክ ኦባማም ሰምተን ነበር። ግን የሰማነው እና በተግባር ያየነው ተመሳሳይ አልሆነም። ፖለቲከኞች የሥልጣን መንበር ላይ ሲቀመጡ፤ ለምን ውሸት እንደሚቀናቸው አላውቅም፤ ከወንበሩ ጋር የሚመጣ በሽታም ሊሆን ይችላል። ለሕዝብ ግን፤ እውነትን እንደመሰማት፤ ነፍሱን የሚያድስ ነገር ያለ አይመስለኝም። አንዳንዴ፤ እውነቱን መናገር መሪር ሊሆን ይችላል፤ ዋጋም ሊያስከፍል ይችል ይሆናል። ግን ውሸት ተነግሮ፤ ውሸትነቱ ቆይቶም ሲጋለጥ፤ የበለጠ መሪር፤ ይሆናል፤ የበለጠም ዋጋ ያስከፍላል።

በእኔ አመለካከት፤ በጌደኦ ሕዝብ ላይ የደረሰው የጠኔ ጥቃት፤ ምንም ዓይነት ሰብብ ሊሸፍነው የማይችል ጥፋት ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ እና የሰላም ሚኒስትሯ የሰጡት መግለጫ፤ ወኃ የማይቋጥር ሰበብ ብቻ ሳይሆን፤ ውሸት ነው። የመከላከያ ሰራዊቱን እና የፌደራል ፖሊሱን አቅም፤ እንኳን እኛ ዓለም ያውቀዋል። በጌዴኦ አካባቢ ያሉ ቀማተኞችን፤ የመከላከያ ሰራዊቱም ይሁን የፌደራል ፖሊስ ሊቆጣጠር አልቻለም ከተባልን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህግ አስከባሪውን እና የመከላከያውን ተቋም፤ የመምራት እና የማዘዝ አቅም አጥተዋል ብዬ ለመደምደም እገደዳለሁ። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ፤ ትላንት በፌደራል መንግሥቱ የተሰጠው መግለጫ፤ በማያሻማ መልኩ ያስተላለፈው መልዕክት፤ የፌደራል መንግስቱ ደካማ መሆኑን ነው። አንድን ጥፋት ለመሸፈን፤ የተሰራ ሌላ ስህተት። የፌደራል መንግስቱ፤ ቀማተኞችን በአንዲት ትንሽ አካባቢ ለመቆጣጠር ባለመቻሌ፤ ለተፈናቃይ እና በጠኔ ለተጠቁ ዜጎች፤ እህል ማቅረብ አልቻልኩም ወይም ያቀረብኩት የእርዳታ እህል በቀማኞች ተነጥቀዋል ካለ፤ ትልቁን ሃገር ተቆጣጥሬ ሕግ አስከብራለሁ እንዴት ሊል ይችላል? በተለያየ መልኩ የፌደራል መንግስቱን እየተፈታተኑ ላሉ ጽንፈኛ ሃይሎችስ የሚያስተላልፈው መልዕክት ምንድን ነው? የፌደራል ፖሊስ እና የመከላከያውን አቅም ለሚያውቅ ሕዝብ፤ በፌደራል መንግስቱ የተሰጠው “የመቀነቴ አደናቀፈኝ” ሰበብ በምንም መልኩ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም። ስለዚህ፤ ዶ/ር አብይ እራሳቸው፤ የፌደራል መንግሥቱ ያለውን አቅም አስተባብሮ መስራት ያለበትን ስራ ባለመሰራቱ ለተፈናቀለው እና በጠኔ ለተጠቃው የጌዴኦ ሕዝብ በፋጣኝ እና በበቂ ሁኔታ እንዳልደረሰለት በመግለጽ፤ ሕዝቡን ይቅርታ መጠየቅ እና በድጋሚ እንደዚህ ዓይነት ነገር እንደማይፈጠር ቃል መግባት አለባቸው። በዚህ ጉዳይም ሃላፊነታቸውን ያልተወጡ የመንግሥት ባለሥልጣናት ካሉ፤ ባለስልጣናቱ፤ ሊገሰፁ እና ለጥፋታቸውም ተመጣታኝ እርምጃ ሊወሰድ፤ ከከፋም ከሥልጣናቸው እንዲነሱ ሊደረግ ይገባል። ከዚህ በተጨማሪ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ የፌደራል መንግሥቱ፤ ከቤቱ ተፈናቅሎ፤ በጠኔ እየተጠቃ ላለው የጌዴኦ ሕዝብ፤ በአስቸኳይ እና በተገቢ ሁኔታ ስላልደረሰለት፤ ተገቢ የወቀሳ ውሳኔ ማስተላለፍ ይገባዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ጠርቶ በዚህ ጉዳይ ላይ ሊያነጋግር ይገባዋል።

ሃገሪቱ የሽግግር ወቅት ላይ በመሆንዋ፤ ብዙ ጉደለቶች እየታዩ በዝምታ እየታለፉ ነው። የመንግሥት ባለሥልጣናት ግን፤ ለሕዝብ ሲዋሹ እየሰማን፤ በዓይናችን የምናየውን ነገር፤ እንዳናምን ሲነገርን፤ በዝምታ የምናልፍበት ሕሊና ሊኖረን አይገባም። እኔ በበኩሌ፤ የምደግፈውም ሆነ የምተቸው፤ ግለሰብን አይደለም ሥራውን ነው። አንድ ሰው ጥሩ ሲስራ ሊወደስ፤ ሲያጠፋ ደግሞ ሊወቀስ ይገባዋል። ከምንም በላይ፤ ሕዝቡ መሪዎቹ እውነት እንዲነግሩት ይፈልጋል። የሚፈልገው፤ መሪዎቹ ፍፁም እንዲሆኑ አይደለም፤ የሚጠብቀው፤ ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ይሆናልም ብሎ አይደለም፤ ከምንም ነገር በላይ ግን መሪዎቹ እውነት እንዲነግሩት ይፈልጋል። ሕዝብ ያውቃል፤ እውነትና ውሸት የመለየት ብቃት አለው። ሕዝቡን መናቅ ዋጋ ያስከፍላል። እንኳን አሁን፤ መረጃ፤ በድምጽ ፍጥነት በሚራባበት ጊዜ ይቅር እና፤ ሬድዮ በዳንቴል ተሸፍኖ ይደመጥ በነበረበት ጊዜ እንኳን፤ ሕዝብ መረጃ አግኝቶ፤ እውነትና ውሸቷን ይለይ ነበር። ስለዚህ፤ አትዋሹን፤ ሥራችሁን ሥሩ፤ የማትችሉት ነገር ካለ ለሕዝብ ንገሩ፤ ሃገራችን የኢኮኖሚ ደሃ ናት፤ ይገባኛል። “የልጆች ደሃ” ግን አይደለችም። የፌደራል መንግስቱ አቅሙ ውስን ሊሆን ይችላል፤ ዛሬ እንደትላንቱ አይደለም፤ ሕዝቡን አስተባብሮ አስፈላጊ እርዳታ ለማድረስ ይቻላል። የፈረንጆችን ስንዴ የምንጠብቅበት ጊዜ ሊያልፍ የሚችለው፤ ተባብረን ሕዝባችንን እንድንረዳ ጥሪ የሚያቀርብልን እውነተኛ መሪ ሲኖረን ነው። ያ ካልሆነ፤ ከጠኔ፤ ከለማኝነት አንድንም። ዛሬም እንደትላንቱ መታወቂያችን ጠኔ አይሁን። ይኽው እጅግ የማከብረው፤ አርቲስት ታማኝ በየነ ለኢትዮጵያ ልጆች ባደረገው ጥሪ፤ በአጭር ጊዜ የተሰጠውን ምላሽ አይተናል፤ ይህ በአውሮፓ እና በሰሜን አሜሪካ ከሚገኘው ኢትዮጵያዊ በትንሹ የተሰጠ ምላሽ ነው። ማርክ ትዌን እንዳለው፤ ውሸት ተፈናጣር ዓለምን ታዳርስ ይሆናል፤ እውነት ጫማውን ለማጥለቅ ጊዜ ቢፈጅበትም፤ ማራቶኑን ግን ማሸነፉ አይቀርም። እውነት ንገሩን፤ አስተባብሩን፤ የመፍትሔው አካል አድረጉን፤ እያንዳንዱ ዜጋ ሃላፊነቱን እንዲወጣ፤ ብቃት ያለው እና የሚመጥን አመራር ስጡን። በሃገራችንም “እውነት ትቀጥን ይሆናል እንጂ አትሰበርም” ይባላል። ስለዚህ እውነቱን ንገሩን፤ ቢጎዳንም፤ እንቀበለዋለን። ውሸቱ የበለጠ ይጎዳናል፤ ውሸት ስትናገሩ፤ ለወድፊትም እንዳናምናችሁ ያደርገናል። ይህ ደግሞ ሃገራችን ልትሸከመው የማትችል ውድቀት ያመጣብናል። ልብ ያለው ልብ ይበል።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ይባርክ።

____
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
13,723FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here