spot_img
Wednesday, April 17, 2024
Homeነፃ አስተያየትአዋቂ ሲጠፋ ታዋቂ ይበዛል! (ከአዲስ አበባ )

አዋቂ ሲጠፋ ታዋቂ ይበዛል! (ከአዲስ አበባ )

መጋቢት 8 2011 ዓ.ም.

ሀገራችን አያሌ ታዋቂነትን በሚሹ የመንደር አለቆች እየታመሰች ትገኛለች፡፡ የመንደር አለቆቹ የራሳቸው የሆነ የትግል መነሻ የሌላቸው ከሆዳቸው ውጪ የሚታገሉለት ህዝብ የሌላቸውና የሚታገሉበት ዕውቀት የነሳቸው ስለመሆናቸው በተጨባጭ የሚታዩ ሰው ሰራሽ ሰብዓዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ማሳያ ናቸው፡፡ በጊዚያዊ ጥቅም እና በሴራ ማንነታቸው ከልጅነት እስከ እርጅና ዘመናቸው ታንፀው ባደጉ ኢምንት ሰብዓዊ ፍጥረቶች ብቻ እየተነዱ በወገናቸው የግፍ ግፍ ይፈፅማሉ፣ ሀገራቸውን ወደ መጨረሻው ጥፋት ይመራሉ፡፡ በተዳፈነው የነጮች ክፋት ተቃኝተው መጨረሻቸውን ሳያውቁ በራዕይ የሚኖረውን የፍቅር ህዝብ ፍቅር አሳጥተው ሳይተማመን እንዲኖር ለማድረግ ሲውተረተሩ ይታያል፡፡ ለመሆኑ መጨረሻቸው ምንድን ነው? ሀገራቸውስ የት ነው? በነተበ ፖለቲካቸው በወርቅ የተቀባ ንግግራቸውን እያወሩ ህዝቡን በመዝረፍ በድህነት እንዲቀጥል ማድረግ? ይህ ደግሞ ዕድሜ ለእነሱው ላስተማሩን ብልጠት የማይቻል ነው፡፡ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ወገኖቻችን በአራቱም አቅጣጫ በረሃብ ያልቃሉ፣ ከቀያቸው ይሰናበታሉ፣ እርስ በርስ ይተላለቃሉ፣ በመኖርና ባለመኖር መካከል ሆነው ይታገላሉ፡፡ በዚህ ሁሉ ሰቆቃ የሚያገኙት ፋይዳ የሚያሳዝን ቢሆንም የፈለጉትን ስልጣን እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ግን በብቸኝነት እንደማይጠቀሙበት ታግዘው እንኳን ቢነገራቸው መስሚያ የላቸውም፡፡ ይህ ሁሉ ሰቆቃ ዋጋ የሚከፍሉበትና የነፃነት መውጫ በር ያለው መሆኑን በውል መረዳት ይገባል፡፡ በአዳዲስ ትርክቶች አዲስ ባለታሪክ ለመሆን አሉታዊ ቀደምት ታሪኮችን በማራገብ ከአወንታዊ ታሪኮቻችን መማር ሲገባ ባልተገባና አስነዋሪ ድርጊቶች ፍፁማዊ ታሪክ ለመገንባት መዳዳት የአስተሳሰብ ልህቀት ደረጃቸውን ያሳያል፡፡ ኢትዮጵያ ያለእኛ ካልሆነ እንደ ሀገር ትጠፋለች በሚል የቃልና የተግባር እኩይ ተልዕኮ ለጊዜውም ቢሆን ሀገራችን ብትቸገርና ቢነግሩንም ሳይቻላቸው ሲቀር ደግሞ የእኛ እና ኬኛ በሚሉ ግልገል መልዕክተኞቻቸው የጥፋት ምዕራፋቸውን ቀጥለውበታል፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ ዕውነትና ዓለም የሚያውቀው ብሎም በተጨባጭ የሆነ ነው፡፡ ታሪክ አልባ ሀገር ስለሌለ በጭፍን የምንክደው አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የተሰራችው፣ የተመሰረተችው ወይም የተቆረቆረችው በአማራው ነው፡፡ አማራው ደግሞ በእምነቱና በስነልቦናው እውነተኛውን መደመር ስለሚሻ ፣ አንድነትን፣ ኢትዮጵያዊነትን ስለሚያቀነቅን፣ወዘተ ምክንያት እንደ ብሄር ለማጥፋት የገሃድም ሆነ የስውር ደባ በመፍጠር በርካታ ጥፋት ተደርጎበታል፡፡ እምነቱም የስነ ባህሪው መታነፅ ምክንያት በመሆኑ በእምነቱም የተፈፀመውን ሁሉ በሰው ልጅ አንደበት የማይገለፅና ለአፀፋው ባለቤት ያለው በመሆኑ መተው ይበጃል፡፡ ግፍና በደሉን በዝርዝር መተረክ ለታላቁ የአማራ ህዝብ የሚጠቅመው ባለመሆኑ መተው ሳይሻል አይቀርም፡፡ ዳሩ የታሪክ መሰረት ለሌለው ጎሳ የሀገር ታሪክ ባለቤትነቱና ዕንግድነቱ ሲሰጠው አይዋጥለት ይሆናል፡፡ ጥያቄያቸውን ጣራ ላይ በመስቀል የማገሩን እኩሌታ በድርድር ለማግኘት የግርግር ከንቱ ስትራቴጅ ሲፈጥሩ እንደቂል ያሰቡትን ህዝብ ጠንቅቀው ያወቁት አይመስልም፡፡ ለማንኛውም ቀጣይ የሀገራችን ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል? መፍትሄውስ ምንድን ነው?

ምንም እንኳን በማንነት/በዘር/በብሄር ፖለቲካ ከረቀቀ ሴራ ጋር ለሀገራችን የዘሩብንን መርዝ መንቀል መሰረታዊ ጉዳይ ቢሆንም ትዕግስት እና ዕውቀት የሚያስፈልገው ነው፡፡ ሆኖም ግን ለጊዜውም ቢሆን የሀገራችን ዕጣ ፈንታ በወቅቱ መንግስት እጅ ላይ ነው፡፡ የለውጥ ሀይሉ በውስጡ የነበረበትን ርዕዮተ ዓለም ተገንዝቦና ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለ በመሰለ መልኩ ህዝቡን ከጭቆና፣ ከስቃይ እና ከባርነት ነፃ አውጥቶ ህዝብ የሚፈልገውንና ስሜቱን የሆነለትን የለውጥ ሀይልነቱን በውጭ እና በሀገር ውስጥ ከፍተኛ ቅቡልነትን አስገኝቶ ነበር፡፡ ሆኖም ግን የለውጥ ሀይሉ ከፍተኛ የሆነ ስህተት በአደባባይ ሲሰራ ይስተዋላል፡፡ መንግስት እንደ አገባቡ መጓዝ ያዳገተው ሆኗል፡፡ ለምን?

የለውጥ ሀይሉ ምርጫ ምንድን ነው?

የለውጥ ሃይሉ ባልተጠበቀና ባልተገመተ መልኩ ያለምንም ልፋት፣ መስዋዕትነት፣ ጦርነትና ግጭት በቀላሉ የህዝብን ቀልብ ሊስብ በሚችል ተናፋቂ የህዝብ ፍላጎት መግቢያ ንግግር የሳጥናኤልን ስልጣን ተረክቧል፡፡ ንግግሩ የተረከበውን ስልጣን ተግባር ሊተገብር ሳይሆን የንግግሩን ሊሆን እንደሚችል ግምት ተወሰደ፣እምነትም ተሰጠው፡፡ የውጭ መንግስታትም ድጋፍ በምንም ስሌት ሊታሰብ በማይቻልበት መንገድ ተደረገለት፡፡ የእነ አሜሪካ ስውር እጅ የተለመደ ፍላጎቱን ተግባራዊ አደረገ፡፡የሌሎችም አለሁ ባይነት ቀጠለ፡፡ የውስጥ እሳታችንን ለማዳፈን በሚመስል መልኩ ዳር ዳሩን ዙረቱን ተያያዝነው፣ የውጭ ዲፕሎማሲያዊ ስራችን ይሁንታ ተቸረው፡፡ የዕድሜ ልክ ታጋዮቻችን በአንድ ሌሊት ወደ ቀያቸው እንዲገቡ ተደረገ፡፡ አቻ የማይገኝለት ወንጀል መስራታቸውን በጋራ ስምምነት በሚመስል መልኩ ህግ የጣሱ መሆኑ ይፋ ተደረገ- ያ ሁሉ ወንጀል ከዘገየ የታወቀ፣ በድንገት የተገኘ እንደሆነ ሁሉ በሩ ከተከፈተ በኋላ ከሀገር ውስጥ እና ውጪ ህግ በላይ መሆናቸውም ተነገረን፡፡ምንም ይሁን ምን ለህዝብ የገጠመ ንግግር ያደረገ መሪ በመገኘቱ የዋሁ ወገን ይሁን አለ፡፡

አሁን የለውጥ ሀይሉ የህወሃትን ዕድሜ ለማራዘም ቃል የገባ ይመስላል፡፡ልክ እንደ ዝግመተ ለውጥ ቲዎሪ ህወሃት ስታረጅና ስትጠላ ሊታመን በሚችል ድራማ ፍች የተፈፀመ መሰለ፡፡ የለውጥ ቡድኑ ከውሉ ውጭ የተጓዘ ቢመስልም የዋናውን አጀንዳ ሳይነካ ህወሃትን የኢኮኖሚዊ እና ፖለቲካዊ ኪሳራ አደረሰባት፣ እንዳትሰራራ አድርጎ ጣላት፡፡ በዚህ ሁኔታ የለውጥ ሀይሉ ወደ ኋላ መመለስ የሚቻል አይመስልም፡፡ መመለስ ቢያስብም መስዋዕትነቱ የመጨረሻው ይሆናል፡፡ ታዲያ የለውጥ ሃይሉ ያገኘውን ዕድል መጠቀም ለምን አልፈለገም? ምንስ ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ይኖረው ይሆን?ፍላጎቱስ ምንድን ነው?

መሪው የነበረበትና ያደገበትን ርዕዮተ ዓለም ፍላጎት ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ የእናቱ ልጅ ታላቁ በኦነግ እስከተገደለበት ድረስም ያደገበትን ህብረተሰብ ፍላጎት አይዘነጋም፡፡ ነገር ግን የጥቂት ቡድኖች ፖለቲካ በቤቱ ሰላም ሲያሳጣው ሌላ የአፀፋ ርምጃ ሊያስወስድ የሚያስችለው ቡድን ተቀላቀለ፣ በለጋ ጭንቅላቱ ተጠመቀ፡፡ በጎልማሳነት ዕድሜው ሰብዓዊ ማንነቱ ሲመለስ የህዝቡንና የወገኑን ፍላጎት አንፀባረቀ፡፡ ይህም ውሸት አልነበረም ፣ አይመስልምም ነበር፡፡ በአንፃሩ በጥንቃቄ የመለመሉትን የውጭ መንግስታት ፍላጎትና አቅም ያውቃል፡፡ከህወሃት ያልተለየው ሲ.አይ. ኤ ጠልፎ እንደያዘው ቢያውቅም ለኢትዮጵያውያን ቃል የገባውንና ህዝብ የፈለገውን ማድረግ ቢፈልግም እንኳን የሚያስችለው ምቹ ሁኔታ ስለሌለው በንፅፅር የተገኘውን ነፃነት እንደ ውለታና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ብቻ ማቀንቀን ተጀመረ፡፡ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ህዝባዊ ድጋፍ ቢኖርም የብሄር ማንነትን የሚያቀነቅኑ ጥቂት የማንነት ቀውስ በሚታይባቸው ቁንፅል ምሁሮችና የሰፈር አለቆች ግለሰባዊ የስልጣን እና የጥቅም ፍላጎት በመሳብ አጣብቂኝ የገባ ይመስላል፡፡ምን አልባትም አቋሙ የፀና ቢሆን እንኳን ባለው የፖለቲካ ምህዳር ሜዳ ውጭ እንዲሆን ከድርጅቱ ሊሰናበት ስለሚችል ወይም እንደ ዘመኑ ፋሽን በፍላጎቱ ስንብት ቢጠይቅና በዓለም አቀፍ ተቋማት ተቀጥሮ ለመስራት ከሀገር ሊወጣ ስለሚቻል የማንነት ፖለቲካ ዕድሜውና ቀጣይነት ከህወሃት ጋር በተደረገው ስምምነት መሰረት ይፀናል፡፡ የህወሃትም ዋነኛ አከርካሪ ያገግማል ማለት ነው፡፡ ዋናው ቁም ነገር ብሄረሰቦች ያላቸው ልዩነት ተጠብቆ በፍቅር መኖር ለኢትዮጵያዊያን አስተማሪ አያስፈልጋቸውም፡፡ ችግሩ በሰፋ ልዩነትና የተንኮል ትርክትና ሴራ የታነፀ ከንቱ አሰተሳሰብ መፈጠሩ ነው፡፡ ስለሆነም የለውጥ ቡድኑ ያገኘውን ዕድል ተጠቅሞ ሀገራዊ ታሪክ መስራት ሳይሆን አጋጣሚውን ተጠቅሞ የተራነት ድርሻውን መከወን ፈለገ፣ የቁማር ፖለቲካነቱን ፣የማፍያዎችን ተማሪነቱን ማረጋገጥ ጀመረ፡፡ ወገኑንም ሆነ እራሱን ወደማይወጣበት ማጥ ውስጥ ገባ፡፡ እሄንም ጊዜ የሚመልሰው ይሆናል፡፡

በተመሳሳይ ግን የለውጥ ቡድን አመራሩ በመናበብ ልክ እንደ አባቱ ድርጅት ወደ ዋሻዉ በመግባት የዘረመል ፖለቲካውን እያቀነቀነ እንደ ጎረቤት ኤርትራ ተከልሎ ይኖራል፣ ኢትዮጵያን ይገነጣጥላል፡፡ ከማንነት ቀውስ በሽታው ተላቆ ይኖራል፡፡ የወጣበትን ማህበረሰብ ስነ ልቦና ይሰብራል፣ያሳዝናል፡፡ የመጨረሻ ምርጫውም ይህው ነው፡፡ የሚያሳዝነው ግን ኢትዮጵያ እንደዚህ መሆን እንደማትችል አለማወቁ ነው፡፡ ድንቄም ፖለቲከኛ!

የለውጥ ሀይሉ የምርጫውን መፋጠን ለምን ፈለገው? ከላይ እንደተጠቀሰው የታነፀበትን የማንነት ፖለቲካ ለማስቀጠልና ቃሉን ለመጠበቅ ትኩስ ድንቹን ለቀጣዩ ፓርቲ አቀብሎና ግራ አጋብቶ ወደ ዋሻው ሊገባና ከደሙ ነፃ ነኝ ለማለት እንዲመቸው ይመስላል፡፡ ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ በምንም ምክንያት ኢህአዴግን እንደማይመርጠው ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ነው፡፡ እስከዚያው ግን የዋሻውን ማህበረሰብ ተቀባይነት ለማግኘት የማህበረሰቡን የምጣኔ ጥቅም ያመቻቸ በመምሰል ላይ ይገኛል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የማንነት ፖለቲካ እንዲቀጥል የሚሰሩትን ድራማዎች ማጤን ያስፈልጋል፡፡ በዋናነትም አዲስ አበባ እና በዙሪያዋ የሚደረጉ ስራዎች በአንድ በኩል ክልላዊና ድርጅታዊ አመኔታና ይሁንታ ለማግኘት ሲሆን በሌላ መልኩ ከድርጊቱ ጋር በተያያዘ ህወሃት ብለን ነበር ሰሚ አጣን! በማለት የትግራይን ህዝብ ተቀባይነት ለማግኘት፣ በአማራ በኩል ደግሞ አዴፓ ዜጎቼ ለምን ተነኩ በማለት ሲያወግዝና አዲሱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ቆራጥ አፀፋ ሲወሰድ የዜግነት ፖለቲካው ጦዞ ለቀጣይ ምርጫ አዴፓ ከማንነት ፖለቲካ አቀንቃኙ አብን ጋር ተመጣጣኝና ተፎካካሪ እንዲሆንና ድምፅ እንዲያገኝ ለማድረግ፣የኦዴፓም ህዝብ የዘረመል ፖለቲካው ሲቀጣጠል ኦዴፓ ወይም ሞት እንዲባልለት በአጠቃላይም የብሄር ፖለቲካው በድርድርና ድርድር ብቻ ተቃኝቶ ሀቅና ዕውነታው ጠፍቶ እንደተፈለገ በጥቂት ጀሌዎች ብቻ የሚቃኝና የሚነዳ ልፍስፍስ ብሔረሰብ በመፍጠርና ሀገራችን ለጥቂቶች ምቾት ብቻ የምትሆን ሀገር በሚያደርገው ፖለቲካ እየተቃኘች በተለመደ የወሬ ብቻ ፖለቲካ በድህነት እንድትቀጥል ማድረግ ነው – ዓላማው፡፡ ለዚህ ደግሞ ህወሃት በየክልሉ የራሳቸው የትግል ታሪክ የሌላቸውን የህወሃት ብቻ ትርክት የተጫነባቸውን ጥቂት የብሄረሰቦችን ኢሊቶች ፍላጎት ለችግሩ መጦዝ አስተዋፅኦ መዘንጋት የለበንም፡፡

መፍትሄው ምንድን ነው?

መፍትሄው ጊዜ ሳይሰጡና ሳይዘናጉ መደራጀት ነው፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ፣ ሁሉም ብሄር ከዚህ በኋላ በአንድ ብሄረሰብ ስውር ስትራቴጅና የሀይል የበላይነት ቁጥጥር ስር መግባት የለበትም፡፡ በስነልቦናው እራሱን የቻለና ማንም እንደፈለገ የቡድን ጥቅሙንና ፍላጎቱን እንዲጭንበት መፍቀድ የለበትም፡፡ ከአለፈው መማር ያለበትም እሄን ነው፡፡ይህ ከሆነ ኢትዮጵያዊነቱን ሲፈልግ እውነተኛውን የመደመር ስሌት በመሳሳብ ያለሰባኪ ይተገብራል ማለት ነው፡፡ የሴራ ፖለቲካ በተካኑ ከንቱ ፖለቲከኞች ከመታመስም ይድናል፡፡ ብሔረሰቦች ሲጠናከሩ ክልሎቻቸውንና ህዝቦቻቸውን ለመለወጥና ለመከላከል ብቃት ይኖራቸዋል፡፡ ከፌዴራል ተፅዕኖ ይወጣሉ፡፡አሉታዊ ችግር ቢፈጠርባቸውም ሳይለማመጡ ይፋለማሉ፣ህግ ያስከብራሉ፣ወዘተ፡፡ በተመሳሳይ ከጎረቤት ክልሎች ጋር በተፈጥሯዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮችና ጥቅሞች ላይ ይሳሳባሉ፡፡ በራሳቸው ለመቆም የማስችሏቸው በርካታና አስገዳጅ ጉዳዮች ስለሚፈጠሩ ሰብዓዊነታቸውን እያስቀደሙ የቀደመ ኢትዮጵያዊነታቸውን በዕምነት ይቀበላሉ፡፡ በሂደትም በርካታ ክልሎች የአንድነት ጠቀሜታዊ አስተሳሰባቸው ሳይበረዝ ይረዱታል፣ ግንባርም ይፈጥራሉ፡፡ ይህ ሲሆን ፖለቲካ እና የፖለቲከኞች የፍላጎት አጀንዳ በደረጃው የሚታየው ከላይ ከተዘረዘሩት ጉዳዮች በታች ይሆናል፡፡ ፖለቲከኞችም እንደፈለጉት የሚጋግሯት ሀገር አትኖርም፣ የሚነዳ ህዝብም አይፈጠርም፡፡ ስለሆነም ሁሉም ብሄሮች ኢትዮጵያ የምንላትን ሀገር ወደ ጎን በማድረግ ቅድሚያ ለማንነት ህልውና መደራጀትና መስራት ይጠበቅብናል፣ ምረጫውም እሄው ነው፡፡ ያኔ ተመሳሳይ ወፎችን አንድ ላይ ሲበሩ መለየትና በትክክል ማወቅ ይቀላል፡፡ ዜጎችም እርስ በርስ በጥርጣሬ ከመተያየትም ይታደጋሉ፡፡ እዚህ ላይ የማንነት ፖለቲካን በሀገራችን የዘሩት የሴራ ፖለቲከኞች ሊደሰቱ እንደሚችሉ ይገመታል፡፡ ሆኖም ግን እነሱ ያቦኩትና የሚጋግሩት ብሄር እንጅ በማንነቱ የጠነከረ፣ ለማንም የማይታለል፣የማይገዛ፣ወዘተ ብሄር ስለማይፈልጉ ሌላ የተንኮል ርዕዮተ ዓለም እስኪያጠኑ ዕድሜ ስለማይኖራቸው ሀገራችን ሰላሟን ታገኛለች የፀሀፊው እምነት ነው፡፡ ስለዚህ በተለይም አማራው ለኢትዮጵያዊነታችን እና ለታሪካችን መቀጠል ሚናህ ከፍተኛ በመሆንህ የሌሎችን ብሄሮች ጥቅምና ፍላጎት ባገናዘበ በመሰረት እንድትታነፅና በህቡዕ እንድትደራጅ መልዕክታችን ነው፡፡ በፖለቲካው እና በትግል የተፈተነው ህዝብህ በቀላሉ የማይታለል ቢሆንም በስነልቦናው የተሰራበትን ተንኮል ገንብተህ ከፖለቲካው ጎን ለጎን በዋናነት በክልልህ ልማትና ዕድገት በቅድሚያ ልትሰራበት አደራችን ነው፡፡ ሁልጊዜ በጦርነት አውድማ ጊዜህ እያለፈ በሂደት ታሪክህን ለማጥፋት ትንኮሳ ሊደርስብህ ስለሚችል ህዝብህን ማደራጀት ጊዜ የማይሰጠው ነው፡፡ የነበረ ታሪክህ ህያው የሚሆነው በጥላቻ ፖለቲካ ተተብትበህ ዘላለም በሽንፈት እንድትኖር ስለሚፈለግ በውል ለልማት እና ለመከላከል መደራጀት ካልቻልክ ሀገራችን አደጋ ላይ ትጥላለህ፡፡ አሁን ቅድሚያ አማራነትህን የምታቀነቅንበትና የምታስቀድምበት ጊዜ ነው፡፡ ለህዝብህ ህልውናም ስትል በፍጥነት አድርገው፡፡ ኢትዮጵያ ያኔ ትመለሳለች፣ ያኔ ብሄረሰቦች ፍቅርህ ይገባቸዋል፡፡ ታውቃለህ በአማራነትህ የሚደረገው የጥፋት ርብርብ ለታሪክ ሽሚያ ብቻ አይደለም- የመኖርህ እውነተኛ ታሪክ ስጋታቸው እንጅ! ስለዚህ በተገኘው የተለየ ፓርቲ ለጊዜውም ቢሆን በፍጥነት መደራጀት ያስፈልጋል፡፡ የአማራ ህዝብ ሆይ! የህወሃት አጃቢዎች አሁንም ለይቶላቸው ያልጠፉ በመሆኑና ለጥፋት ተግባርህን ለማበላሸት ስለሚሻሙብህ ከኢህአዴግ መርህ እና መዋቅር ለአንዴም ለመጨረሻ ጊዜ መለያየት አለብህ፡፡ ለሌሎች ጊዜ አትስጥ!

እያዩ ማዘን
ከአዲስ አበባ
__
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here