(በመስከረም አበራ)
መጋቢት 23 ቀን 2011 ዓ .ም.
ህወሃት በአምሳሉ ጠፍጥፎ ሰርቶ እስትንፋስ “እፍ” ያለባቸው የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ካድሬዎች የእውቀት ራስ ህወሃት ብቻ ይመስላቸዋል፤እርሱ ከሄደበት መንገድ ውጭም ፖለቲካ የሚዘወር አይመስላቸውም፡፡የኢትዮጵያ ህዝብ ወዝውዞ ወዝውዞ ያዛለውን ፈጣሪ ጌታቸውን ህወሃትን ገፍትረው ለመጣል የደፈሩት የህዝብን ክንድ ተማምነው ነበር፡፡ህወሃት ከወደቀ በኋላ ስልጣን ላይ የተሰየመው ኦዴፓ ጌታው ህወሃት አይንህ ላፈር የተባለበትን ነገር ሁሉ እየደገመ ያለው ከህወሃት ውጭ አስተማሪ፣ከመለስ ዜናዊ ጥራዞች ውጭ ንባብ፣እንደው ባጠቃላይ ከህወሃት ውጭ “ትምህርት ቤት” ስለማያውቅ ነው፡፡
ብዙ ህዝብ እንወክላለን የሚሉትን የኦህዴድ ካድሬዎችን ጨምሮ ሁሉንም የኢህደዴግ ድርጅት ሰዎችን ሲዘውር የኖረው ህወሃት እንደ እውቀት ጥግ ሲያዩት ለኖሩት ለአገልጋዮቹ ሲያስተምር የኖረው አንዴ ስልጣን ላይ ከተቀመጡ እንዴት ይሉኝታ ቢስ ብልሹ ዘረኛ መሆን እንደሚቻል ነው፡፡በእህወሃት እግር ስር ቁጭ ብለው ዘረኝነት፣እብሪት፣ሃሰት፣ሼር እና ዘረፋ ሲማሩ ከነበሩ አንዱ(ኦዴፓ) በለስ ቀንቶት ስልጣን ላይ ሲወጣ እየደገመ ያለው ብቸኛው መምህሩ ህወሃት ሲያደርግ የኖረውን ነው፡፡
የተለየ ነገር ቢኖር ኦዴፓ የእበልጣለሁ ባይነቱን ስሜት እንደ ህወሃት ጊዜ ወስዶ ረጋ ባለመንገድ ማስኬድ አለመቻሉ ነው፡፡የአዴፓ ለበላይነት መራወጥ ከፍተኛ ፖለቲካዊ መንቀዥቀዥ የታየበት፣በይሉኝታ ቢስነቱም ህወሃትን ሊያስናፍቅ የሚቃጣው ነው፡፡ይህ ኦዴፓን በአራስ ቤት እንደሚሞት ህፃን እድሜውን ሊያሳጥር የሚችለው አካሄድ ሁሉን ነገር ለእኔ በሚለው በዚህ ፅሁፍ ሁኔታ “የኬኛ ፖለቲካ” እያልኩ በምገልፀው እጅግ ብልሃት በጎደለው አካሄዱ ይታጀባል፡፡እየጎመራ የመጣው የኬኛ ፖለቲካ አዝማሚያ ለሁሉም ዜጋ እጅግ አደገኛ ነገር ይዞ ስለሚመጣ መገለጫዎቹን መመርመሩ አስፈላጊ ነውና ወደዛው ልለፍ፡፡
የ”ባንክ እና ታንክ” ቁጥጥር
የኦህዴድ መምህር ከህወሃት ለ27ዓታት የኢትዮጵያን ሁለመና በመሀል እጁ ይዞ የኖረው በክላሹ እና ከህዝብ በሚዘርፈው ገንዘብ ነበር፡፡ከህወሃት ውጭ ዓለምም፣ አስተማሪም፣ንባብም የሌላቸው የኦህዴድ ካድሬዎችም በለስላሳ ምላሳቸው የሚሉትን ብለው ህዝቡን ወከክ ካደረጉ በኋላ መንግስታቸው የፀና ሲመስላቸው ያደረጉት ባንኩን እና ታንኩን መቆጣጠር ነው፡፡ህወሃት ኢፈርትን የመሰለ የዘረፋ ኢምፓየር የገነባው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን እየዘረፈ ነበር፡፡የአሁኑ ንጉስ ኦዴፓም ተመሳሳዩን ለማድረግ የጎጡን ሰዎች ከአዋሽ ባንክ አምጥቶ በንግድ ባንክ ቁንጮ የአስፈፃሚነት ቦታዎች ከኮለኮለ እነሆ አንድ ወር ተጠጋው፡፡
ባንኩን መቆጣጠር የገዥውን ጎጥ ሰዎች እየመረጡ ቱጃር ለማድረግ አመች ነገር ነው፡፡ዘመድ ሰብሰብ ብሎ ባለስልጣን በሆነበት ባንክ ያለማስያዣም ቢሆን የብድር አግልግሎት ይቀላጠፋል፣በንግድ መሃል ኪሳራ ከመጣም “ክፈሉ” የሚል ግዳጅ የለም “የተበላሸ ብድር” ተብሎ እዳው ወደኢትዮጵያ ህዝብ ይዞራል፡፡የዘመድ በየባንኩ መኮልኮል የሚበጀው የራስን ጎጥ ለመጥቀም ብቻ አይደለም “የትምክህተኛን” ወይም የሌላን ዘር አድጋለሁ ባይ ነጋዴ ለማቀጨጭም ነው፡፡ሁሌም በልዩ ሁኔታ ተጠቃሚ ካለ በልዩ ሁኔታ ተጎጅ አለ፡፡የራስን ጎጥ በልዩ ሁኔታ ተጠቃሚ ማድረግ እና ሌሎችን የበይ ተመልካች ማድረግ ደግሞ ለጎጥ ፖለቲከኛ ትልቁ ስኬቱ ነው!
ኦዴፓ እንደ ዝንጀሮ ልጅ(የዝንጀሮ ጎረምሳ ማደጉን የሚያረጋግጠው እግሩን ከአባቱ እግር ጋር እለካ ነው ከሚባለው አባባል ጋር በሚዛመድ መልኩ) እድገቱን የሚለካው እግሩን በህወሃት ዱካ እየለካ ለመሆኑ ማስረጃው በሃገር መከላከያ ሰራዊት ውስጥ የጎጡን ሰዎች የሰገሰገበት እጅግ አደገኛ አካሄድ ነው፡፡በህዝብ ሞኝነት እርግጠኛ የሆኑት ጠ/ሚኒስትሩም ይህንኑ የጎጣቸውን ሰዎች ማህበር ከሁሉም አብልጠው የሚመኩበት ኢትዮጵያዊ ተቋም እንዳደረጉት ደንቀፍ ሳያደርጋቸው ተናግረዋል፡፡አርአያው ህወሃት የሆነ ሰው ሲዋሽ በምቾት ነው!ዋናው ጥያቄ ግን መከላከያን የአንድ ጎጥ ጎሬ ማድረግ ያስፈለገው ለምንድን ነው የሚለው ነገር ነው፡፡መልሱም ቀላል ነው-አፈንጋጭን በሰደፍ እየነረቱ መንግስትን ለማፅናት፡፡
በዚህ ላይ የኦሮሚያ ልዩ ሃይል ዋና ማዘዣ አዲስ አበባ እንዲከትም አዲሱ ጌታ ኦህዴድ አዟል፡፡ይህን ተከትሎ ሶስት ሽህ አዳዲስ የኦሮሚያ ልዩ ሃይል ፖሊሶችም አዲስ አበባ እንዲከትሙ ተደርጓል፡፡ይህ የአንድ ዘር የወታደር ጉልበት መጠናከር የኦህዴድን አንደበት ቀይሮታል፡፡ ሰላምን በመስበክ የሰነበቱት ጠ/ሚ አብይ የኬኛ ነገር የተነካካባቸው ሲመስላቸው ቅልጥ ያለ ጦርነት ውስጥ እንደሚገቡ ከሰሞኑ ቆጣ ብለው እየተናገሩ ነው፡፡ይህ የአንደበት ለውጥ የመጣው ጦርነቱን የሚመራው ቤተ-ዘመድ መሆኑን ጠ/ሚው የሰሩትን ሰርተው ስላስተማመኑ ነው፡፡
ከዚህ የምንረዳው የኬኛ ፖለቲካ የተንተራሰው የፈጠራ ታሪክን እና የህገ-መንግስትን ተረክ ብቻ ሳይሆን የወታደር ጉልበትንም ደጀን እንዳደረገ፣በታንክም እንደሚታገዝ ነው፡፡ጠ/ሚው ከጦርነት ማስፈራሪያቸው አስከትለው የሱሉልታን እና ሆለታን ስም የጠሩት አዲስ አበባን የከበበውን ባለ ሜንጫ ቄሮ እንደ ተጨማሪ ማስፈራሪያ መጠቀማቸው ነው፡፡እነዚህን አካባቢዎች የሚመሩት ደግሞ የለውጥ አመራር የተባሉ ልሙጥ ዘረኞች መሆናቸው መረሳት የለበትም፡፡
የለውጥ አመራሮች- የንቅል ካድሬዎች ምትክ
ኦህዴድ ከህወሃት የተለየ ለመምሰል በሚሞክርበት ዘመን ፓርቲው “የለማ ቡድን” የተባሉ የለውጥ አመራሮችን መፍጠሩን ሲያወራ ከርሟል፡፡እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን ሲገልጡ ደግሞ የለገጣፎዋ አረመኔ አፈናቃይ ወ/ሮ ሃቢባ ሲራጅን፣ግራ የገባቸውን ተፈናቃዮች ሰብስባ ስትመፃደቅ የሰነበተችዋን የክልሉን ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወ/ሮ ጠይባ አህመድን፣ከጎኗ ተሰይሞ በሰው ቁስል እንጨት ሲሰድ የከረመውን አቶ አዲሱ አረጋን አይነት ሰዎች ናቸው፡፡ሌላዋ ግልፅ ዘረኛ እና እብሪተኛ የለውጥ አመራር ተብየ ደግሞ “በአርባ ሽዎች የሚቆጠሩ ሰዎን ባላፈናቅል ጣቴ ነው አንገቴ ይቆረጥ” ስትል በአደባባይ የምትናገር ወ/ሮ ሮዛ የተባለችው የሱሉልታ ከንቲባ ነች፡፡ ይህች ሴትዮ ቤታቸው እንደሚፈርስ ተነግሯቸው ሰማይ ምድር የዞረባቸውን ሰዎች ሰብስባ የኦሮሞ ቤት ተቀባ ማለት ይፈርሳል ማለት እንዳልሆነ እና ኦሮሞዎች የባዕዳንን ጦርነት መዋጋታቸውን እንዲያቆሙ ኮራ ብላ በአደባባይ የምትናገር ናዚ ነች፡፡እነዚህ የለውጥ አመራር የተባሉ ሰዎች የሚያስፈፅሙት አብይ እና ለማ በሌሉበት ብቻቸውን ያቀዱትን ዕቅድ እንዳልሆነ ግልፅ ነው፡፡
ዕቅዱ እስከ ክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ድረስ እውቅና እንዳለው ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ ወ/ሮ ጠይባ እና አቶ አዲሱ ተፈናቃዮችን ሰብስበው የሚናገሩት እብሪት የተሞለ ንግግር ምስክር ነው፡፡ ለማ እና አብይም የእቅዱ አካል እንደሆኑ የሚጠራጠር ካለ እነዚህ የለውጥ አመራር ተብየ ዘረኞች የተሾሙት በማን ነው? የስራ ሪፖርታቸውን የሚያቀርቡትስ ለማን ነው? ብሎ ራሱን ይጠይቅ፡፡ከሁሉም በላይ አብይ እና ለማ በአዲስ አበባ ዙሪያ ለሚደረጉ የግፍ መፈናቀሎች ያሳዩት አልሰማሁም የሚል የፌዝ መልስ እና የምንግዴ ዝምታ፣አፈናቃይ ባለስልጣናቱም እስካሁን በስልጣናቸው ላይ መቀመጣቸው የለማ ቡድን የሚያስፈፅመው ለማ ያቀደውን እንደሆነ ምስክር ናቸው፡፡
እነዚህ አደገኛ የዘረኝነት አዝማሚያ የተሸከሙ የኦህዴድ የለውጥ አመራር ተብየዎች ህወሃት ከትግራይ ገጠራማ አካባቢዎች አምጥቶ አዲስ አበባ ይሰገስጋቸው የነበሩ፣ህወሃት ካዘዛቸው ምንም ከማድረግ ወደኋላ የማይሉ በተለምዶ ንቅል ካድሬ የሚባሉትን አይነት ናቸው፡፡ እንደ ህወሃት ንቅል ካድሬዎች ሁሉ የኦህዴድ የለውጥ አመራር ተብየዎች ከሚመሩት እና ከሚያፈናቀሉት ህዝብ ጋር አንዳች የቆየ ትስስር የሌላቸው ከኦሮሚያ ክልል ሌላ አካባቢዎች መጥተው የተሾሙ እንደሆኑ ነው ተጎጅዎች የሚነገሩት፡፡
እነዚህ ንቅል የለውጥ አመራሮች ከሌላ የኦሮሚያ ቦታ(ምናልባትም ገጠራማ ቦታዎች) መጥተው አዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ከተሞችን እንዲመሩ የተደረገው የከተሜን ከዘር ትስስር የራቀ አኗኗር ስለማይረዱ በማፈናቀሉ ላይ ወደ ኋላየማይሉ መሆናቸው በለማ ቡድን ስለተፈለገ ነው፡፡ለዚህ ማስረጃው ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ ወ/ሮ ጠይባ ሃሰን አቶ አዲሱ አረጋን አስከትላ ለገጣፎ ተገኝታ ወ/ሮ ሃቢባ ያደረገችው አረመኔያዊ ማፈናቀል እንዴት ህጋዊ እንደሆነ ለተጎጅዎቹ ለራሳቸው ልታስረዳ የተሟሟተችበት መንገድ ነው፡፡
እንደዚህ ከላይኛው አመራር ጥብቅና የሚቆምላቸው ንቅል የለውጥ አመራሮች የከተማ ሰው እንዴት እንደሚኖር የማያውቁ፣ጥሩ ፖለቲከኛ ማለት ጭፍን ዘረኛ የሚመስላቸው፣ብልጣብልጦቹ አለቆቻቸው የኬኛ ፖለቲካን የመሰለ አደገኛ መርዝ ጭነው ፈተው የለቀቋቸው የእውቀት ድሆች ናቸው፡፡ብልጦቹ የላይኞቹ አመራሮች ደግሞ የሚያምን ሞኝ ካገኙ ይህን የሚያደርጉት ከነሱ ቁጥጥር ውጭ የወጡ አክራሪ ዘረኞች እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡በዚህ መንገድ ከኦሮሙማ አላማቸውም ሳይናጠቡ ከህዝብ ድጋፍም ሳይጎድሉ ለመጓዝ ይሞክራሉ፡፡ ይህ እስከየት እንደሚያስኬዳቸው የሚታይ ይሆናል፡፡
ኢትዮጵያን ከኦሮሚያ ማስወጣት፤ኦሮሚያን ወደ ኢትዮጵያ ማስገባት
የኦህዴድ ንቅል የለውጥ አመራሮች የኦሮሙማ አጀንዳቸውን የሚያሳኩበት የኬኛ ፖለቲካ ዋናው አላማው ኦሮሚያን የኦሮሞዎች ብቻ ማድረግ ነው፡፡ ኦሮሚያ የኦሮሞዎች ብቻ የምትሆነው ደግሞ በለገጣፎ እና በሱሉልታ እንደተደረገው ዘር እየለዩ ኦሮሞ ያልሆነውን ህዝብ አፈናቅሎ ከኦሮሚያ ምድር በማስወጣት ነው፡፡ መፈናቀሉ ዘር የለየ እንደሆነ የለገጣፎዋ ወ/ሮ ሃቢባም ሆነች የሱሉልታዋ ወ/ሮ ሮዛ በገዛ አንደበታቸው የተናገሩት ነው፡፡አሁን በዚህ ሰዓት ደግሞ በአርሲ እና በባሌ የተለያዩ ቦታዎች ኦሮሞ ያልሆኑ ሰዎች በተለይ አማሮች ሃገራቸውን ለቀውላቸው እንዲወጡ የሚያሳስብ እና የሚያስፈራራ ወረቀት በየ”ባዕዳኑ” በር ላይ እየተለጠፈ እንደሆነ እማኞች እየተናገሩ ነው፡፡እነዚህ ሰዎች ከአርሲ እና ባሌ እንዲወጡ የተጠየቁት እንደ ሱሉልታ እና ለገጠፎዎች ህገወጥ ቤት ሰርታችኋል የሚል አስመሳይ ምክንያት እንኳን ሳይነገራቸው ነው፡፡ ከዚህ የምንረዳው የኬኛ ፖለቲካ መዳረሻው ኦሮሚያን ከኢትዮጵያ ማፅዳት እንደሆነ ነው፡፡
ኦሮሚያ የኦሮሞ ነች ብሎ ሰፊ እና ለም ክልልን ለኬኛ ፖለቲከኞች ብቻ የሸለመው የህወሃት ህገ-መንግስት ይህ ክልል ኦሮሞ ወደ ኢትዮጵያ ከመፍለሱ በፊት ህዝብ እንደነበረበት ለኬኛ ፖለቲከኞች አላስረዳቸውም፡፡ከህወሃት የሚያልፍ እውቀት ያለ የማይመስላቸው የኬኛ ፖለቲከኞች ደግሞ ኦሮሚያ የኦሮሞ ነች የሚለውን የህወሃት ተረክ ንጥር ሃቅ፣የማይጠየቅ እውነት አድርገው ተቀብለው ሃገርን እግር በራስ የሚያደርግ ስህተት እየሰሩ ነው፡፡
አሮሚያን ለኦሮሞ ብቻ የሚሉት የኬኛ ፖለቲከኞች በአንድ በኩል ኢትዮጵያን ከኦሮሚያ እሰከማስወጣት የደረሰ የቂል ሙከራ ሲያደርጉ በሌላ በኩል ኦሮሚያን ኢትዮጵያ ላይ ለማንሰራፋት የፌደራል ስልጣኑን ወረውታል፡፡ከሲቪል እስከ ወታደራዊ ስልጣን፤ከሚዲያ እስከ የፍትህ አካላት የፌደራል መንግስቱ ስልጣን በእጃቸው ነው፡፡የመንግስት ሚዲያው ኦህዴዶች ለኦሮሙማ አላማቸው የማይፈልጉትን አጀንዳ የሚያራምድ ሁነት አይዘግብም፤ለምሳሌ የአዲስ አበባ ህዝብ በባልደራስ ተሰብስቦ ዘረኝነት እና ስልጣን ተጋግዘው ካመጡበት አደጋ ራሱን ለመከላከል የሚያደርገውን ትግል መንግስት የሚቆጣጠራቸው ሚዲያዎች በስህተት አልዘገቡም፡፡ ኦህዴድ ህገ-መንግስቱን ጥሶ በማያስተዳድረው ግዛት ውስጥ ያለችው አዲስ አበባ ከተማ “የግል ንብረቴ ነች” የሚል ህገ-ወጥ መግለጫ ሲያወጣ ጠቅላይ አቃቤ ህግ በወንጀል ያልጠየቀው መስሪያ ቤቱ በኦህዴድ ስለሚዘወር ነው፡፡አዲስ አበባ ነዋሪዎቿ ላልሆኑ ሰዎች በገፍ መታወቂ ስታድል የአዲስ አበባ ምክር ቤት ድምፁን ያጠፋው ተጠሪነቱ (ስለ አዲስ አበባ የሚጠይቅ ጦርነት ይነሳበታል እያሉ ማስፈራራት ለጀመሩት) ለኦህዴዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ስለሆነ ነው፡፡
የኬኛ ፖለቲካ መዘዘዞች
ከላይ የተጠቀሱ እና ባለፈው ሳምንት ለመጠቆም የሞከርኳቸውን አስቻይ ሁኔታዎችን ተጠቅሞ ክፉኛ እየሰገረ ያለው የኬኛ ፖለቲካ ፈረስ ልጓም ካልገባለት በርካታ መዘዞችን ይዞ የሚመጣ ነገር ነው፡፡ እነዚህ መዘዞች የወዲያው(Immediate) እና የረዥም ጊዜ(Long t erm)ተብለው በሰፊው ለሁለት ሊከፈሉ ይችላሉ፡፡ የኬኛ ፖለቲካ የወዲያው ጥፋቶች መታየት ጀምረዋል፡፡ ከነዚህ ጥፋቶች አንዱ የህዝቦች መሞት፣መፈናቀል፣ መዘረፍ፣ፍትህ ማጣት ነው፡፡
የጌዲኦ ተፈናቃይ ህዝቦች ስቃይ፣የለገጣፎ ተፈናቃዮች፣በሱሉልታ መፈናቀል የተደገሰላቸው በአስር ሽህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች፣በቄለም ወለጋ የሚኖሩ አማሮች፣በአርሲ እና ባሌ በስጋት የሚኖሩ ኦሮሞ ያልሆኑ ህዝቦች ስጋት እና እንግልት አንዱ የኬኛ ፖለቲካ መዘዝ ነው፡፡ የኬኛ ፖለቲካ ብዙ ያልተነገረለት ግፍ የተከሰተው በቡርጅ እና በኮይራ ህዝቦች ላይ ነው፡፡ እነዚህ የደቡብ ህዝቦች ከኦሮሚያ ክልል ጋር ስለሚጎራበቱ በአገረማርያ(ቡሌ ሆራ) እና አጎራባች የኦሮሚያ መሬቶችም ይኖራሉ፡፡በተለይ በጤፍ አምራችነታቸው በአጠቃላይ በጠንካራ አራሽነታቸው ይታወቃሉ፡፡
በዚህ ምክንያት “መሬታችንን ለቃችሁ ውጡ” እየተባሉ መንገላታት ከጀመሩ አንድ አመት አልፏቸዋል፡፡ ከአንድ አመት በላይ መንገድ ተዘግቶባቸው ለቅንጦት ቀርቶ ቢታመሙ፣ወላድ ምጥ ቢይዛት ሆስፒታል የሚደርሱበት መንገድ የላቸውም፡፡በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ ቡርጅ እና ኮይራዎች “ባለመሬት ነኝ” ባዮቹ ካድሬዎች የፈለጉትን ቢያደርጓቸው አቤት የሚሉበት አካል የለም፡፡አንድ ከአካባቢው የመጣ ኦሮሞ እንደሆነ ግን በድርጊቱ በጣም እንደሚያዝን የነገረኝ ልጅ ይህን ግፍ አጫውቶኛል፡፡አራት ጌዲኦዎች ታርደው ተጥለው በአይኑ እንዳየ እየዘገነነው ነግሮኛል፡፡የሃገር ባለቤት ነን ያሉ የኦሮሞ ጎረምሶች በቀን በብርሃን የቡርጅዎች ቤት ጣራ ላይ ወጥተው ቆርቆሮ ነቅለው ሲወስዱ ባለቤቶቹ ቡርጅዎች ቆመው ከማየት ውጭ አማራጭ እንደሌላቸው፤ይህንንም ሲያደርጉ እንዳየ እያዘነ ነግሮኛል፡፡”ይሄ ቡርጅ፣ኮይራ፣ጌዲኦ ላይ ለምን ተደረገ?”ብሎ መጠየቅ አንድ ነገር ሆኖ በቡርጅ ፣ኮይራ እና ጌዲኦ ተወስኖ ይቀራል ብሎ ማሰብ ግን ሞኝነት ነው፡፡ዝም ከተባለ ነገ አዲስ አበባ ይመጣል፤እየመጣም ነው፡፡
ይህ የህዝቦች መፈናቀል፣የባለ ጊዜ ነኝ ባዮች ስርዓት አልበኝነት በራሱ እጅግ አደገኛ ነገር ሆኖ ሳለ ለሌሎች ክልሎች ጎረምሶችም አርአያነትን ሊያመጣ ይችላል፡፡ይህ ደግሞ በተጨባጭ በደቡብ ክልል ዋና ከተማ በአዋሳ፣በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባህርዳር የታየ ነው፡፡ባለ ጊዜ ነኝ ባይ ስርዓት አልበኛ ምንም ሲደረግ ያላየ የሌላ ክልል ጎረምሳም ዘሩን የበላይ ለማድረግ “ሌሎች” በሚላቸው ላይ ተመሳሳዩን እያደረገ ሲሄድ ሃገራችንን መልሰን ላናገኛት እንችላለን፡፡
ነገሩን ከሃገር መፍረስ በመለስ እንየው ከተባለም ሃገሪቱን ለከፋ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ቀውስ ይዳርጋትል፡፡ሲንፏቅ የኖረው ኢኮኖሚያችን ጨርሶ እንዲሞት ያደርጋል፡፡የኢኮኖሚ ችግር ደግሞ ዘረኝነት የለኮሰውን የፖለቲካ እሳት ይብስ ያነደዋል፤ስርዓት አልበኝነቱን ያጎነዋል፡፡ይህ ሁሉ ተደማምሮ በሃገር ተስፋ መቁረጡን ያባብሳል፡፡ስደት መፍትሄ ይሆናል፤ የባህር ራት መሆኑ ከነበረው ብሶ ይቀጥላል፡፡ኢትዮጵያዊነት የሚኖር ከሆነም እንደ ውሻ በየቦታው ወድቆ ከመቅረት፣በየባዕድ ሃገር በረሃ ከማለቅ ውርደት ጋር ተጋምዶ ይቀጥላል፡፡
በኬኛ ፖለቲካ ምክንያት በህዝብ እና በመንግስት መሃል ወርዶ የነበረው እርቅ ይከስማል፤ጠብ እና ክርክር ከአንድ አመት እረፍት በኋላ ወደቦታው ይመለሳል፤እየተመለሰም ነው፡፡በዚህ ሳቢያ ከዲያስፖራው ይመጣ የነበረው የውጭ ምንዛሬ ይመናመናል፤እንደ ቀድሞው በዘመቻ የሚታገድበት ጊዜም ሩቅ አይመስለኝም፡፡ሃገር ውስጥ ያለው ዜጋ ስራውን እንዳያከናውን የፖለቲካ አለመረጋጋቱ እግር ብረት ሆኖ ይቀይደዋል፡፡የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ ያገሪቱን ኢኮኖሚ ከድጥ ወደ ማጥ ይከተዋል፡፡ይህ የኬኛ ፖለቲካ የወዲያው ተፅዕኖ የሚያመጣው ተራዛሚ ውጤት ይሆናል፡፡ ይህ ተራዛሚ ውጤት ሃገሪቱን መልሶ ወደ አለመተማመን ፖለቲካ፣ ወደተስፋ መቁረጥ እና በኋላቀር ኢ-ዲሞክራሲያዊ ሁኔታ ወደመመራት ልማዷ ይከታታል፡፡ተከባብሮ ተማምኖ መኖር ይጠፋል፡፡መብለጥን እንጅ እኩልነትን እንደ መፍትሄ የማያየው የዘር ፖለቲካ መጨረሻው ሃገር ማፍረስ ነው፡፡ በሰለጠነ ዘመን፣በነቃ ህዝብ ላይ የበላይ ሆኖ መኖርን ማሰብ፣በልብ ሌላ ይዞ በአፍ ሌላ እያወሩ ሰውን ለማመሞኘት የሚደረግ ሩጫ ሄዶ ሄዶ ኢትዮጵያን እንደይጎዝላቪያ “ነበረች” ወደ ምትባልበት ተረት ሊቀይራት ይችላል፡፡
የኬኛ ፖለቲከኞች ሁሉን ለእኔ በማለታቸው የገፉት ይህን ሁሉ ስለማያውቁ አይደለም፡፡ይልቅስ የያዛቸው የዘረኝነት አባዜ ኢትዮጵያ ፈርሳ ኦሮሚያ ልታብብ እንደምትችል ስለሚነግራቸው ነው፡፡ይህ እጅግ ስህተት ቢሆንም ተገፍቶበታል፡፡ልጓም ያልገባለት ምኞታቸው የኢትዮጵያዊነት አንድያ አምባ የሆነችውን አዲስ አበባን የአንድ ጎጥ ንብረት ለማድረግ እስከመሞከር ሄዷል፡፡ይህ ሳይታፈርበት በመግለጫ እስከመነገር ደርሷል፡፡ይህን ህገ-ወጥ እና ዘረኛ መግለጫ ፈርመው ያፀደቁት ባለ ብዙ መልኩ ጠ/ሚ አብይ ሳምንት ቆይተው ደግሞ “አዲስ አበባ የኢትዮጵያዊ ሁሉነች” ማለት ጀምረዋል፡፡ይህ ኢህአዴጋዊ ተንኮል ያለበት ንግግር ነው፡፡አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ንግግራቸው እውቅና እየሰጡ ያሉት ከኬኛ ፖለቲካቸው ጋር የማይጋጨውን የአዲስ አበባን የፌደራል ከተማ የመሆን ነጠላ ማንነት ብቻ ነው፡፡ሁለተኛውን እና እያጨቃጨቀ ያለውን፣ለኬኛ ፖለቲካቸውም ጋሬጣ የሚሆነውን አዲስ አበባ የኗሪዎቿ የመሆኗን ሃቅ ሊናገሩት አልደፈሩም፡፡
አዲስ አበባን በትክክል እና በተሟላ ሁኔታ የሚገልፃት ራሷን በራሷ የማስተዳደር መብት ያላት ከተማ እንዲሁም የሁሉም ኢትዮጵያዊ መዲና የመሆኗ መንታ ማንነት ነው፡፡ራሷን በራሷ የምታስተዳድር የኗሪዎቿ ከተማ መሆኗን መግለፅ ከተማዋን በማስተዳደሩ በኩል ለኦሮሞ ከፈጣሪ የተሰጠችነች ከሚለው የኬኛ ፖለቲካ ጋር ስለሚጣረስ አብይ በዘዴ አድበስብሰውት አልፈዋል፡፡ይህ ማደናገሪያ ነው፡፡እውነተኛው በመግለጫ ተነግሮናል፡፡መግለጫውን ተረድቶ ሃገርን ከጥፋት ለማዳን የሚደረገውን ማድረግ ወይም የማደናገሪያውን ማደንዘዣ ተወግቶ ሃገር ሲጠፋ ማየት የሰሚው ምርጫ ነው፡፡
የኬኛ ፖለቲካ በአዲስ አበባ ላይ ያለውን አላማ እንዲያሳካ እና ከተማዋን እንዲቆጣጠር መፍቀድ ለማንም ኢትዮጵያዊ የሚሆንለት ነገር አይደለም፡፡በአዲስ አበባ ዙሪያ ያለውም አብይ እንዳት የሱሉልታ እና የሆለታ ኦሮሞ ብቻ አይደለም፡፡ በቅርብ ርቀት ደብረብርሃን እና ቡታጅራም አሉ፡፡አዲስ አበባን የመሰለች የኢትዮጵያዊነት ምልክት ለመታደግ ሰመራም፣ጅጅጋም፣ባህርዳርም፣ድሬዳዋም፣አርባምንጭም፣ሆሳዕናም፣ወላይታ ሶዶም፣ዱረሜም፣አሶሳም፣ደብረማርቆስም ሩቅ አይደሉም፡፡በሰለጠነ ዘመን የሃገር ሩቅ የለም! በቅርብ ያለሁ እኔነኝና አርፋችሁ ተቀመጡ የሚለው ቂልነት የማያጣው ሃሳብ ይልቅስ ከተማዋን የእልቂት አምባ ያደርጋታል፡፡
አዲስ አበባ ስትታመስ የምናጣው ብዙ ነው፡፡አዲስ አበባችን ከኒውዮርክ እና ጄኔብ ቀጥላ የአለም አቀፍ ድርጅቶች መዲና በመሆን ሶስተኛዋ ዓለም አቀፍ ከተማ ነች፡፡ይህ ክብራችን ነበር! ከሁሉም በላይ አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና ነች፤ ይህ የሆነው እኛ በዘር መባላቱ አዳርሶን በሰራነው ስራ አይደለም- በነጋ በጠባ የምንረግማቸው አባቶቻችን ሞተው ባመጡልን ክብር የተገኘ እንጅ!የኬኛ ፖለቲካ ዝቅታ እንዲህ ላለው ለአዲስ አበባ ዓለማቀፋዊ ግዝፈት የማይመጥን የኦሮሙማ ጠባብ ጥብቆ ሊያለብስ የሚንገታገት ነው፡፡ግዙፏ፣አለማቀፏ አዲስ አበባ በዚህ ጠባብ ጥብቆ ለመግባት ትልቅነቷ አይፈቅድላትም፡፡
በጠባቡ ጥብቆው እንድትገባ የሚደረገው አሽቆልቋይ ትግል አዲስ አበባን እጅግ ያዉካታል፤መረጋቷን ይነጥቃታል፡፡ባልተረጋጋ ከተማ ለመኖር የሚፈቅድ ዓለም ዓቀፍ ተቋም ደግሞ አይኖርም፡፡ሁሉም አንዳንድ እያለ በኬኛ ፖለቲካ የምትታመሰውን አዲስ አበበን እየለቀቀ ይሄዳል፡፡ይሄኔ የአፍሪካ መዲናነት ምን እንደሆነ ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ይህን ክብር ለማግኘት ሌት ተቀን ሲሰሩ የኖሩ የአፍሪካ ሃገራት መባላታችንን ጠቅሰው የአፍሪካ መዲናነት ወደሚመጥነው ከተማ እንዲያቀና ይከራከራሉ፡፡ያኔ ምን እንደምናወራ አላውቅም!የሜንጫ እና የዱላ ትርኢት በሚታይበት፣በገዛ ጠ/ሚኒስትር ጦርነት በሚታወጅበት ከተማ መኖር አለባችሁ ብሎ ማስገደድ ይቻላል? ላስገድድ ቢባልስ ማን ይሰማል? ስለዚህ የኬኛ ፖለቲካ በዚህ ከቀጠለ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫነታችንን ሊነጥቀን ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ታሪካዊ፣ዲፕሎማሲያዊ፣ኢኮኖሚያዊም ሆነ ስነ-ልቦናዊ ውርደት ያመጣል፡፡ከዚህ ውርደት ለመዳን ኦህዴድ ሃይ መባል አለበት፡፡እንዴት? ለሚለው ሌላ ቀጠሮ ልያዝ::
___
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።