spot_img
Tuesday, June 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትየእስክንድር ነጋ ስሕተት፤ እውነት የጎደለው “የምሁራኑ” ደብዳቤ እና “የጋዜጠኞች” የአድማ ፖለቲካ፡፡

የእስክንድር ነጋ ስሕተት፤ እውነት የጎደለው “የምሁራኑ” ደብዳቤ እና “የጋዜጠኞች” የአድማ ፖለቲካ፡፡

ከጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ፤ (03/28/2019) 19/07/ 2011

የመጀመርያው ክፍል፤

“….ሳታሸንፍ አሁን አደራ – ባለአደራ እንደሚባለው ዓይነት ጨዋታ የምትጫወት ከሆነ ግን ግልጽ የሆነ ጦርነት ውስጥ እንገባለን ማለት ነው። ይህ መታወቅ አለበት። ምክንያቱም፤ ለምሳሌ አዲስ አበባ ውስጥ የሆነ ሺ ሰው ሰብስቦ ባለአደራ ካለ፤ ኦሮምያም፤ በቃ ይህ ኦዲዲ የሚባል የእኛ መንግሥት አይደለም ፍላጎታችን ይህ አይደለም ባለ አደራ ነው፤ ተገንጥልናል ካለ፤ ኢትዮጵያ አትኖርም።” ዶ/ር ዓብይ አሕመድ ድምቀት የተጨመረ)

ይህ ከጥቂት ቀናት በፊት ዶ/ር ዓብይ አሕመድ የተናገሩት ነው። ይህንን ተከትሎ፤ በአንዳንድ የፖለቲካ ሃይሎች እየተነስ ያለው የፖለቲካ ጡዘት፤ ሰሞኑን የሕዝብ መገናኛ አውታሮችን ተቆጣጥሯል። ከዚህም አልፎ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር 42 የሚሆኑ “ምሁራንን” አስቆጥቶ፤ “ምሁራኑ ውድ ጊዜያቸውን ሰውተው” ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡ ከዛም አልፎ፤ “ጋዜጠኞች” ለእስክንድር ነጋ አጋርነታቸውን ለመግለጽ፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ትችት ከመሰንዘር አልፈው፤ ወደ ማስፈራራት፤ የስም ማጥፋት እና ዛቻም የገቡ አሉ። ይህ አሳዛኝ፤ አሳፋሪ እና፤ አላስፈላጊ የፖለቲካ ቁማር፤ የሰከነ አዕምሮ ባላቸው እና አርቀው በሚያዩ አስተዋይ ዜጎች፤ ሊተች እና ሊወገዝ ይገባዋል።

የሚያሳዝነው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የተናገሩትን፤ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ፤ በማጣመም እና፤ ከታሰበለት ዓላማ ውጭ በመተርጎም፤ የሚፈልጓትን ብቻ መዘው አውጥተው፤ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስክንድር ነጋ ላይ ማስፈራርያ ሰነዘሩ” የሚል፤ ለጊዜያዊ ጥቅም የሚመስላቸውን ርዕስ እያጮሁ ስናይ፤ በፊት ስናከብራቸው የነበሩ ሰዎች፤ ዛሬ የመከነ አስተሳሰባቸውን ሲያሳዩን ለመታዘብ ተገደናል። ወደ “ምሁራኑ እና” “ጋዜጠኞቹ” ዛቻ ላይ አስተያየት ከመስጠቴ በፊት፤ ከእስክንድር ስህተት ልጀምር። ይህ ለውይይቱ ጭብጥ ይሆናል። ዊልየም አለን ዋይት የተባለ አሜሪካዊ ጋዜጠኛ፤ “ጭብጥ ሚዛናዊ እና ትክክል ሆኖ ከቀረበ፤ እውነት እራሷን በጽናት ታቆማለች” ይላል። ስለዚህ፤ ለዚህ ሁሉ የፖለቲካ አቧራ መነሻ ወደ ሆነው ጭብጥ እንሂድ።

እስክንድር ነጋ “በዚህ በሽግግር ወቅት ትልቅ ስህተት የተሰራው አዲስ አበባ ላይ ነው፤ አዲስ አበባ ላይ ካንቲባ ሲሾም፤ የሕዝቡን አመለካከት የሚወክል ስው ነው ተብሎ የታመነበት መሆን አለበት፤ ኦሮምያ አዲስ አበባ ውስጥ ልዩ ጥቅም አላት የሚለውን የኦሮሞ ድርጅቶች የሚያራምዱት አቋም አለ፤ ሁሉም የኦሮሞ ድርጅቶች የሚያራምዱት አቋም ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ የአዲስ አበባ ሕዝብ አለ፤ ኦሮምያ በአዲስ አበባ ውስጥ ምንም ትቅም ሊሰጣት አይገባም የሚል አለ፡፡ ፌደራል መንግስቱ ለአዲስ አበባ ሰው የሚሾምላት ከሆነ የማእዘን ድንጋይ መሆን ያለበት ይሄ ነው”፡፡ ሲል በፈረንጆቹ አቆጣጠር የካቲት 4 ከኢቢኤስ ጋር ባደረግው ቃለ ምልልስ ሃሳቡን ገልጽዋል፡፡ በጥቅሉ፤ እስክንድር፤ ኢንጂነር ታከለ ለአዲስ አበባ መሾም አልነበረባቸውም፤ ምክንያቱም፤ ኦሮምያ በአዲስ አበባ ላይ ጥቅም አላት የሚለውን ስለሚቀበሉ የሚል ነው። የእስክንድር ከጭብጥ ጋር የሚጋጨው ስህተት እዚህ ላይ ይጀምራል። እስክንድር እንዳለው፤ “ኦሮምያ በአዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም አላት” የሚለውን ሁሉም የኦሮሞ ድርጅቶች ይቀበሉታል የሚለው፤ እውነት ቢሆንም፤ ሁሉንም እውንት ግን አይገልፀውም። አሁን ባለው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ድንጋጌ መሰረት፤ ማንም ይሁን ማን፤ ከየትም ይምጣ፤ አዲስ አበባ ላይ የሚሾም ማንም ባለሥልጣን ‘ለሕገ መንግስቱ ተገዢ ሆኜ አገልገላለሁ’ በሎ የሚምል በመሆኑ፤ ኦሮምያ፤ አዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም አላት የሚለውን ሳይቀበል የከተማዋ ሹም ሊሆን አይችልም። እስክንድር ይህን ጭብጥ ለማየትም ሆነ ለመቀበል ባለመፈለጉ፤ መፍትሄ ነው ወደሚለው የራሱን “መንግሥት የማቋቋም” ሂደት ጀምሯል፡፡

የእስክንድር ተጨማሪ ስህተት፤ የእራሱን የግል እምነት እና፤ ትቂት በአካባቢው ያሉትን ሰዎች አመለካከት፤ እንደ ብዙሃኑ የአዲስ አበባ ሕዝብ እምነት አድርጎ የገለፀበት ሁኔታ ነው። በእሱ አካባቢ ያሉ ሰዎች፤ “ኦሮምያ አዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም አላት” የሚለውን ስለሚቃውሙ ብቻ፤ አብዛኛው ሰው ይህንን ይደግፋል ብሎ መደምደም እራሱን የቻለ ስህተት ነው። ይህን ሃሳብ ምን ያክል ሰው እንደሚደግፍው እና እንድሚቃወመው፤ እስክንድር ያደረግው ጥናት እንዳለ የገለፀው ነገር የለም፡፡ የዜና አውታራትም በተገቢው ሥራቸውን ሰርተው ያደረጉት ጥናት የለም፤ እስክንድርን ያውያየ ጋዜጠኛም ይህን መጠየቅ ሲገባው አልጠየቀም። አንዳንዴ ተጽእኖ ፈጣሪ ነን ብለው የሚያምኑ ሰዎች፤ የራሳቸውን እምነት እንደ “አብዛኛው ሰው እምነት” አድርገው ሲገልፁ፤ ሃሳብቸው ከጅምሩ የሚነሳበት ቀመር የተሳሳተ ይሆናል። አዲስ አበባ ውስጥ ካለው እድሜው ከ18 ኣመት በልይ ከሆነው ከ ሚልዮን ገደማ Hዝብ ውስጥ ምን ያክሉ ነው የእስክንድርን ሃሳብ የሚደግፈው? ይህንን የሚያውቅ ያለ አይመስለኝም፡፡

እኔ እንድሚገባኝ፤ በተቃዋሚው ጎራ የነበርም ሆነ አሁንም ተቃዋሚ ይሆነ፤ ገዥው ፓርቲ እና፤ ከዛም አልፎ ሕዝቡ ዘንድ ያለው መግባባት፤ ሕገ መንግስትን በተመለከተ በሕዝብ ውይይት ማሻሻያ እስኪደረግ ድረስ፤ ሃገሪቱ የምትተዳደርበት አሁን ባለው ሕገ መንግስት ነው። በመሬት ላይ ያለው እውነታ ይህ ከሆነ፤ እስክንድር እና የሱ ተሟጋቾች፤ የሃገሪቱን ሕገ መንግሥት አንቀጽ 49 ቁጥር 5ን በምን ሥልጣናቸው ነው የሚሰርዙት? ሃገሪቱን ወደ ሽግግር የምንወስዳት፤ አሁን ያለውን ሕገ መንግሥት ተመርኩዘን ከሆነ፤ የአዲስ አበባም ጉዳይ መቀጠል ያለበት በዚሁ ሕግ ነው። አንቀጽ 49 ቁጥር 5 በማያሻማ ሁኔታ ኦሮምያ በአዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም አላት ይላል፤ ያ ጥቅም ግን ምን እንደሚሆን በሕግ በዝርዝር ይደነገጋል ይላል። ይህ ሕወሃት የተከለው የሚፈነዳ የጊዜ ቦምብ ለመሆኑ ማንም አስተዋይ ሰው ይገነዘበዋል ብዬ አምናለሁ። አሁን ግን፤ ሰላማዊ በሆነ መንገድ፤ ሃገራችንን ወደ ዲሞክራሲያዊ ስልተ ስርዓት ለማሸጋገር፤ ይህንኑ ሕገ መንግስት ነው፡፡ ሕግ መንግሥቱ ብዙ አነጋግሪ ጉዳዮች ስላሉት እና፤ በሕገ መንግሥት ዙሪያም ውይይት የሚያስፈልግ በመሆኑ፤ አንቀጽ 49 ቁጥር 5 ለውይይት መቅረብ ያለበት ያን ጊዜ ነው። አሁን ሕዝብ የመረጠው ቋሚ መንግሥት ሳይኖር፤ በሕገ መንግሥቱ ዙሪያ ንትርክ መፍጠር ፋይዳ የለውም፡፡ ሕገ መንግስቱንም ሊቀይር፤ ሊይሳተካክል፤ ወይም እንዳለ ይቆይ ብሎ ሊወስን የሚችለው፤ ጥቂት አክቲቪስት እና ፖለቲከኛ ሳይሆን፤ የሕዝብ ድምጽ ነው፡፡ ዲሞክራሲ ስንል፤ የአብላጫውን የሕዝብ ድምጽ ተቀብሎ፤ ያንን አክብሮ መኖር ነው።

ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 49 በተጨማሪ፤ የአዲስ አበባ የመጀመርያው ቻርተርም ሆነ የተሻሻለው ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/1995 እና አዋጅ ቁጥር 1094/2010፤ የአዲስ አበባ አስተዳደር እንዴት እንደሚዋቀር እና እንዴት እንደሚተዳደር በግልጽ አስቀምጧል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ፤ ማንም ሃይል፤ አዲስ አበባን፤ በሕግ የራሱ ሊያደርግ የሚችልበት ምንም መንገድ የለም፡፡ ይህንን ጽሁፍ እያዘጋጀሁ በነበረበት ጊዜም፤ አቶ ለማ መገርሳ በማያሻማ ሁኔታ እንደገለፁት፤ ኦሮሞ አዲስ አበባን የመቆጣጠር ፍላጎት የለውም፤ የእነ እስክንድርም ሥጋት “ኦሮሞ አዲስ አበባን ሊቆጣጠር ነው” የሚል ለመሆኑ፤ ሕልም ፈቺ አያስፈልገውም። ታከለ ኡማ፤ ምን ሰሩ ከማለት ይልቅ፤ ዘራቸው ምንድ ነው ብሎ መጠየቅ፤ በተለይ “የአንድነት ሃይል ነን” ከሚል ጎራ መሰማቱ፤ አሳፋሪ ያደርገዋል። በእርግጠኝነት መናገር የምችለው፤ ታከለ ኡማ ከጎጃም፤ ወይም ከጎንደር መጥተው ቢሆን፤ እንደዚህ ዓይነት ተቃውሞ አይገጥማቸውም ነበር። ታከለ ኡማ አሿሿማቸው ሕገ መንግሥታዊ አይደለም የሚለው ክርክርም ውኃ አይቋጥርም። የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 49፤ 5 ቁጥሮች አሉት፡፡ አንቀጽ 49 ቁጥር 2 “የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን ይኖረዋል፡፡ ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል” ይላል፡፡ የአዲስ አበባ የአስተዳድር የሕግ ዝርዝር የተደነገገው “ በአዲስ አበባ ቻርተር” ነው፡፡ ይህም ተደጋጋሚ ማሻሻያ ተደርጎበታል። ይህን ተከትሎ፤ የፌደራል መንግስቱ “የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት” የአዲስ አበባን የምክትል ከንቲባ አመራረጥን በአዋጅ ቁጥር 1094/2010 ሰኔ 30 2010 ሲያፀድቅ እንዲህ ሲል አሻሽሎታል፤ አንቀጽ 1094/2010 ቁጥር 3 “ምክትል ከንቲባው ከምክር ቤት አባላት ውስጥ ወይም ከምክር ቤት አባላት ውጭ የሚሾም ሆኖ የሥራ ዘመኑ የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን ይሆናል”፡፡ ስለዚህ የኢንጂነር ታከለ ሹመት “ሕገ መንግሥታዊ ነው”። እኝህን ሰው በጎ ሲሰሩ መደገፍ፤ ሲያጠፉ መተቸት ተገቢ ሆኖ ሳለ፤ የዘር ሃረጋቸውን በመምዘዝ የተጀመረው ሥም ማጥፋት እጅግ አሳፋሪ ነው። ሊገታም ይገባዋል።

በእኔ እምነት፤ ሁለተኛው እና ለዚህ ሁሉ ፍትጊያ ምክንያት የሆነው፤ የእስክንድር ስሕተት የራሱን “ምክር ቤት” ማቋቋሙ ነው። ኦሮምያ በአዲስ አበባ ላይ ጥቅም አላት የሚለው ነገር ከሕገ መንግሥቱ መውጣት አለበት የሚል ውይይት ማንሳት ተገቢ ነው። እስክንድር የራሱ ጋዜጣ ስላለው እና በተለያዩ ሚድያዎች የመቅረብ እድልም ስላለው፤ የሃሳብ ፍጭት መፍጠር ይችላል። ትላንት ጃዋር “ሁለት መንግሥት አለ” ሲል ያወገዙ ሁሉ፤ አሁን አዲስ አበባ ላይ ባለ አደራ በሚል ሥም “አማራጭ መንግሥት” ሲያቋቁሙ ደጋፊ ሆኖ መቅረብ፤ “በአንድ እራስ ሁለት ምላስ” ዓይነት ነገር ይሆናል። እስክንድር የራሱን መንግሥት አቁቋመ ትላለህ፤ የትኛውን መንግሥት ነው ብለው የጠየቁ አሉ። “ባለአደራ ምክር ቤት” ተብሎ በአንድ የግል ዜጋ ሲቁቋም የራስን “መንግስት” ማቋቋም ማለት እንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? እንዲህ አይነት ነገር፤ በየትኛውም ሃገር ተቀባይነት የለውም። እንዲህ ዓይነት “የለሰለሰ መፈንቅለ መንግሥት” ኢ-ዲሞክራሲያዊ እና በሃገር ላይ ትልቅ አደጋ የሚፈጥር ነው። ዛሬ እስክንድር ነጋ ያቋቋመው ዓይነት ምክር ቤት፤ ነገ እንደ ተስቦ በሽታ ተባዝቶ፤ በየቦታው “ምክር ቤት” የሚል ነገር መቁቋሙ አይቀርም። እውነት እንነጋገር እና፤ ጃዋር “ባለአደራ ምክር ቤት” ብሎ ቢመሰረት፤ ስንቶቻችን ነን ዝም የምንለው? ነገ ሲዳሞ ላይ፤ ኦሮምያ ላይ፤ አማራ ክልል ላይ፤ ወይም ሌላ ቦታ ሲበራከት፤ በምን ሞራልስ ነው ትክክል አይደለም ልንል የምንችለው? ጃዋር ሁለት መንግሥት አለ ብሎ ከተናገረው፤ እስክንድር ያቋቋመው “ባለአደራ መንግስት” ለኢትጵያ አንድነት ስጋት ነው፡፡ ይህንን ካልተረዳን፤ የሃገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ አልተገነዘብንም ማለት ነው፡፡

ይህንን ተከትሎ 42 “ምሁራን” ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የፃፉት ደብዳቤ አስገራሚ እና አንካሳ እውነትን የያዘ ነው። ምሁራኑ እስክንድር ላይ ማስፈራርያ ተሰንዝሯል ያሉት፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሃሳብ በተቆረጠ መልኩ በመረዳት፤ ወይም፤ ለራሱ የፖለቲካ ቁማር ሲል፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ቆርጦ በየሚድያው በሚያቀርበው ጽንፈኛ ሃይል ተወናብደው ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ጦርነት ውስጥ እንገባለን” ያሉት ከእስክንድር ነጋ ጋር እንዳልሆነ የንግግራቸው ሙሉ ቃል ያስረዳል። እንዲህ ዓይነት “ባለ አደራ” የሚል “ጨዋታ” በየአካባቢው ከተነሳ “ጦርነት ውስጥ እንገባለን ሲሉ፤ ሃገሪቱ ጦርነት ውስጥ ትገባለች የሚለውን ለማስረገጥ ነው። ይህን ለመረዳት ግን የሮኬት ሳይንቲስት መሆን አያስፈልግም። ከላይ ሙሉ ቃሉን እንደጠቀስኩት፤ አዲስ አበባም ባለአደራ ካለ፤ ኦሮምያም ባለአደራ ካለ፤ እንዲሁም ሌላውም በዚህ ከቀጠለ፤ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት እንዘፈቃለን ነው። ይህ ደግሞ ሃቅ ነው። በየአካባቢው የራሱን ጥቅም ብቻ የሚያስጠብቅ ትንንሽ መንግስታት መስርተን፤ ሃገር በሰላም ትኖራለች ብሎ ማሰብ ቅዠት ነው። ለዚህም ይመስላል ምሁራኑ በደብዳቤያቸው ሙሉውን እውነት ለመናገር ያልደፈሩት። “ምሁራኖቻችን” በደብዳቤያቸው፤ “ባለአደራ” ለተባለው ምክር ቤትም ድጋፍ የሚሰጥ ነገር አላስነበቡነም፤ “ከስጋው ፆመኛ ነኝ ከመረቁ አውጡልኝ ዓይነት ነው ደብዳቤያቸው። ኢሳት የተባለው የዜና አውታር፤ የምሁራኖቹን ደብዳቤ ይዘት ሲዘግብ “እስክንድር ነጋ ከሚመለከታቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጋር ሆኖ ያደረገው ሰላማዊና ጨዋነት የተሞላበት ውይይትና አቤቱታ ያስመሰግነዋል እንጅ አድናቂዎቹንና ደጋፊዎቹን የሚያስወቅስ ጉዳይ አይደለም ሲሉ ምሁራኑ ድጋፋቸውን ገልጸውለታል፡፡” ይላል፤ ምሁራኖቹ፤ እስክንድር ባለ አደራ ምክር ቤት ማቋቋሙ ልክ ነው ሲሉ ግን አይደመጡም፡፡ እስክንድርም ሆነ ማንም ዜጋ ማንንም ሰብስቦ ያማወያየት መብት አለው፤ “የራሱን መንግስት” የማቋቋም ግን ምንም መብት የለውም፡፡

ከዋናው ቁም ነገር እና የውይይቱ ማዕከል መሆን ከሚገባው ነገር ወጥተው፤ ምሁራኖቹ፤ የምናውቀውን ነገር ነው የሰበኩን፡፡ እስክንድር ዋጋ ከፍሏል፤ የብዙ አለም አቀፍ ተቋማትም ተሸላሚ ነው፡፡ እኔም በግሌ የማደንቀው ሲሆን “እምባሽን ላብሰው” በሚለ የግጥም መደብሌ ውስጥ ከተካተቱት ግጥሞች አንዱ “የብዕር ጦረኛው” በሚል ርዕስ ለእስክንድር ነጋ የፃፍኩት ነው፡፡ የቅንጅት አመራሮች፤ እስክንድ፤ ሌሎች ጋዜጠኞች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የግንቦት 1997 ምርጫን ተከትሎ በግፍ በታሰሩበት ወቅት፤ አዲስ አበባ ሆኜ አሳትመው በነበር ጋዜጣ፤ በመጀመርያው እትማችን ርዕስ አንቀጽ፤ የቅንጅት አመራሮች እና እንደ እስክንድር በግፍ የታሰሩ ዜጎች ከእስር እንዲፈቱ በመጠየቃችን፤ ከፍተኛ ወከባም ደርሶብኛል፤ ጋዜጣችንም እድሚዋ አጭር እንድሆን ከሆነበት ምክንያት አንዱ ነበር። እስክንድርም ሆነ ማንም ዋጋ የከፈለ ዜጋ ልክ ሲሰራ ሊወደስ፤ ሲያጠፋ ደግሞ ሊወቀስ ይገባዋል። የደቡብ አፍሪካዋ ዊኒ ማንዴላ፤ ለፀረ አፓርታይድ ትግል ያበረከተቸውን እና የከፈለችውን መስዋዕትነት ያክል፤ ባጠፋቸው ጥፋት፤ በባልዋ፤ በፓርቲዋ እና በሕዝቡ ውግዘትም ወቀሳም ደርሶባታል። ትላንት “ለሃገር የሰራኽው ውለታ፤ ዛሬ እንድታጠፋ ፈቃድ ይሰጠሃል” የሚል አስተሳሰብ ለማንም አይበጅም። እንደ ኢሳት ዘገባ ምሁራኑ በደብዳቤያቸው “ይህም ሆኖ ግን በዶክተር አብይ አህመድ መንግስት ብቻ የተፈናቀሉት ከሶስት ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ ቀያቸው እንዲመለሱና ተመልሰው እንዲቋቋሙ ሳይደረግ ሌሎች በብዙ ሺህ የሚገመቱ ወገኖቻችን ለተመሳሳይ አደጋ መጋለጣቸው እጅግ በጣም አሳስቦናል ነው ያሉት።” ይላል። እንዲህ ዓይነት አሳፋሪ የፖለቲካ ቁማር፤ በምሁራኖቻችን ሲታይ የመጀመርያው አይደለም። “እስክንድር ሲነካ” ነው እንዴ ለምሁራኖቻችን የወገን መፈናቀል የታያቸው? ምነው በጎንደር በሺህ የሚቆጠር ዜጋ ሲፈናቀል ድምፃቸውን አልሰማን፤ ጽንፈኛ የሆኑ የአማራ ወጣቶች፤ የትግራይን ሕዝብ ወኃና ምግብ ሲያግዱበት ድምፃቸውን አልሰማን? በኦሮምያ፤ በሶማልያ፤ በደቡብ እና በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍል ይህ ሁሉ ቀወስ ሲከተል፤ ምነው እነዚህ ምሁራኖች ተጠራርተው ለዚህች ሃር ቀውስ መፍትሔ እንፈልግ አላሉ? ምነው ለተራበው፤ ለተፈናቀለው ሕዝብ፤ ህዝቡን አስተባብረን ገንዘብ እናሰባሰብ ሲል አልሰማን? ሥራ ፈቶ፤ ሙሉ ሥራውን ሰላማዊ ሰልፍ ያደረገውን ወጣት፤ ሥራ ሊፈጠርለት የሚችልበትን መንገድ፤ ሙያ ሊያሻሽልበት የሚችልበትን መንገድ እናጥና እንጠቁም አላሉ። ስንቶቻቸው ናቸው ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ፤ በየቦታው ችግር ለሚፈጥረው ወጣት፣ ምክር እና ተግሳጽ በጽሁፍ ወይም በቪድዮ ያስተላለፉት? ስንቶቹስ ናቸው ወደ ሃገር ሄደው ሙያቸውን፤ እውቀትና ልምዳቸውን በዘርፋቸው ላለው ዜጋ ያጋሩ? የኢትዮጵያውያን የሂሳብ ባለሙያዎች ማህበር በአሜሪካ በኢትዮጵያ ለሙያ አጋሮቹ የሰጠውን ዓይነት ሴሚናርስ እነዚህ ምሁራን ለመስጠት ያደረጉት ሙከራ አለ?

በሰሜን አሜሪካ ተሽከርካሪ ወንበር ላይ ተቀምጦ፤ ሃገር ውስጥ “እሳት ላይ ተጥደው፤ ይህን ሕዝብ ከእርስ በእርስ ግጭት ለማዳን” የሚተጉ ሰዎችን ሥራ ማቃለል ፍፁም ተገቢ አይደለም” ለእነዚህ ሰዎች፤ እስክንድር እንዴት ከሃገር ሊበልጥባቸው እንደቻለ ሊገባኝ አልቻለም። ምሁራኖቹ በጽሁፋቸው “እስክንድር ነጋን እና በብዙ ሚሊየን የሚቆጠሩ ወዳጆቹን እንዲሁም አድናቂዎቹንና ደጋፊዎቹን ማስፈራራትና መዛት ተገቢ አይደለም” ይላሉ፤ እስክንድር ላይም ሆነ ደጋፊዎቹ ላይ ደረሰ ለሚሉት ዛቻና ማስፈራርያ ግን፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር አጣመው ከመረዳት በስተቀር ምንም ጭብጥ የላቸውም። እነዚህ ምሁራኖች፤ በዚህ አንካሳ እውነትን ባዘለ ደብዳቤ እና በተዛባ አመለካከታቸውም “በቅርቡ በአዲስ አበባ የተከሰተው አለመግባባት ለሁሉም አስደንጋጭ የሆነና የባለቤትነት ጥያቄውም የሁሉም ኢትዮጵያውያን እንጅ የእስክንድርና የደጋፊዎቹ ብቻ አይደለም” ይላሉ፤ ይህ ፍጹም አሳፋሪ ነው። በመጀመርያ ደረጃ፤ በአዲስ አበባ የተነሳው ያልተገባ ፍትጊያ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰው፤ በጃዋር እና በእስክንድር “የብሽሽቅ ፖለቲካ” እንጂ፤ የአዲስ አበባ ጉዳይ በሕግ የተደነገገ ነው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄም አይደለም። ይህንንም ሕግ ለመቀየር ጊዜው አሁን አይደለም። ዋሽንግተን ዲስ የኔነው ስላልክ የሚሆን ይመስልሃል? አዲስ አበባ “የኔ ነው” ስላልክ ያንተ አይሆንም፡፡ አዲስ አበባ የእኔ ነው ስትልስ ምን ማለት ነው? እነዚህ ምሁራን በተፈጠረው አለመግባባት ሸምጋይ መሆን ሲገባቸው፤ በእሳቱ ላይ ጋዝ ሲጨምሩ ማየት፤ ያሳፍራል፡፡ ምሁራኑ በደብዳቤያቸው፤ አንድ ጊዜ እንኳን፤ ስለ ባለአደራው ምክር ቤት አላነሱም፡፡ ለምን? ሃገርን ሊበትን የሚችለው በግል ተነስቶ “የራሱን መንግሥት የሚያቁቁም” ዜጋን በዝምታ ማየት እና መደገፍ እንጂ፤ እሱን ተሳስተሃል ተው ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ ምሁራኑ ራሳቸውን ቢገመግሙ እና ለእውነት ቢቆሙ፤ እንዲሁም በሙያቸው እና በትምህርታቸው፤ ሃገሪቱ ትክክለኛ አቅጣጫ ልትይዝ የምትችልበትን መንገድ ቢያመላክቱ ነው የሚበጀው፡፡ ለፖለቲካ ትርፍ እና “ለቲፎዞ” ተብሎ፤ ሃገሪቱ አላስፈላጊ በሆነ ጉዳይ ንትርክ ውስጥ ስትገባ፤ የንትርኩ አካል በመሆን የሚጎዱት ሃገሪቱን ነው፤ ይህ በማያሻማ ሁኔታ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

በዚህ የሽግግር ወቅት እና፤ በተለይም በአዲስ አበባ ጉዳይ በአድመኛ ጋዜጠኖች እና “አክቲቪስት ጋዜጠኞች” እያየን ያለነው አሳፋሪ እና አሳዛኝ ድርጊት ነው፡፡ አንዳንዶቹም እራሳቸውን “ኢትዮጵያዊነትን ሰፋሪ” አድርገው መሾማቸውን በሚጭሯቸው “ስላቆች” ማየታችን፤ ትላንት ከነበርንበት የመጠላለፍ የፖለቲካ ባሕል አለመወጣታችንን ይጠቁማል፡፡ ትላንት በያዳግም ሁኔታ ሞግተን፤ ከዋና የፖለቲካ መስመር ያስወጣነው ጽንፈኛ አመለካከት እንደገና እያንሰራራ ነው፡፡ ይህን በተመለከተ በቀጣዩ በሰፊው እፅፍበታለሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ግን፤ ለጋዜጠኝነት ሙያው ተገዝቶ፤ ዶ/ር አብይን በተመለከተ ለተነሳው የስም ማጥፋት ዘመቻ፤ ሚዛናዊ አስተያየቱን እና ክሁሉም በላይ ደግሞ እውነቱን ለሕዝብ ይፋ ያደረገውን ጋዜጠኛ አበበ ገላውን ላመሰግን እወዳለሁ።

ይቀጥላል፤

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንን እና ሕዝቦቿን ይባርክ፡፡

__
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here