spot_img
Sunday, September 24, 2023
Homeነፃ አስተያየትኦቦ ለማ መገርሣ የኢትዮጵያን ሕዝብ እንዴት ቢንቀው ነው? (አሊጋዝ ይመር)

ኦቦ ለማ መገርሣ የኢትዮጵያን ሕዝብ እንዴት ቢንቀው ነው? (አሊጋዝ ይመር)

advertisement

አሊጋዝ ይመር
(aligazyimer@gmail.com)
መጋቢት 24 ቀን 2011 ዓ .ም.

እውነት የምትመረው፣ በዘረኝነት ደዌ የተመታና የኅሊና ሚዛኑ የተበላሸበት ሰው ይህን ጽሑፍ ባያነብ ይሻለዋል፡፡ አንድ ተረት አለ፡፡ አንድ አጭበርባሪ ሌባ ወደ አንድ ገበሬ ቤት ሄዶ አሳድሩኝ ይላል፡፡ እንግዳ ክቡር ነውና የዋሁ ገበሬ ያሳድረዋል፡፡ አጭበርባሪው በማለዳ ይነሣና በሸክም የሚችለውን የገበሬውን ሀብት ንብረት ሁሉ ሙልጭ አድርጎ ይዞ ይጠፋል፡፡ ገበሬው ይናደድና ያን ሌባ ለመያዝ ፈረሱን ከኮርቻው አዋድዶ ደንገላሳውን ያስነካዋል፡፡ ወደ አንድ ጫካ ሲደርስ አንድ ሰው ቁጭ ብሎ ያገኛል፡፡ ገበሬው ያንን ሰው “ወንድም አንድ ዕቃ የተሸከመ ሰው በዚህ ሲያልፍ አላየህም?” ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ ልትገምቱ እንደምትችሉት ያ ሰው ሌባው ራሱ ነበር፡፡ ገበሬው ግን አላስተዋለውም ነበርና አላወቀውም፡፡ ሰውዬው ግን አውቆት ስለነበር “እ.. እንድ ሰው በዚህ በኩል እየተሹለከለከ ሲሮጥ ቅድም ሳላየው አልቀረሁም፡፡” ይለዋል፡፡ ገበሬውም ደስ ብሎት “እንግዲያውስ መንገዱ ስለማያመች ይህን ፈረሴን እዚህ ጠብቅልኝና ሳያመልጠኝ በእግሬ ሮጬ ልያዘው፡፡” ይለዋል፡፡ ሰውየውም በደስታ እሽታውን ይገልጽለታል፡፡ ገበሬው ፈረሱን ትቶ ትንሽ ራመድ እንዳለ “ስመለስ ቦታው ቢሳሳተኝና ብንጠፋፋ ማን ብዬ ልጥራህ ወንድሜ?” ብሎ ስሙን ይጠይቀዋል፡፡ ሰውዬውም እርዚቅ ወርዶለት የማያርመው ቡልሃ ሰው በማግኘቱ ተደስቶ “ ‹የአሁኑ ይባስ› ነው ስሜ” ይለዋል፡፡ ገበሬው ልክ እንደኛ እንደኢትዮጵያውያኑ ቀን ጎድሎበት አንዴውኑ ዞሮበታልና እየሆነ ያለው ነገር ምንም ሳይገባው በተነገረው አቅጣጫ ይነጉዳል፡፡ ግን አንድም ሰው አላገኘም፡፡ ቢቸግረው ተመለሰ፡፡ ተመለሰናም በተነገረው መሠረት “የአሁኑ ይባስ! የአሁኑ ይባስ!” እያለ ቢጣራ ሌባው ለሁለተኛ ጊዜ ፈረሱንም ይዞበት ጠፋ፡፡ ገበሬውም ለሁለተኛ ጊዜ ተሞኘ፡፡ ተረቱን ትንሽ ሳላንሻፍፈው አልቀረሁም – ጠርዝ ጠርዙን ግን ይዠዋለሁ ይመስለኛል፡፡ ሕይወት እንዲህ ናት – እኛም፡፡

እንደብሂላችን ቢሆን “የሞኝ ሙርጥ ካላንድ ቀን አይበልጥ” ብለን ከዳግመኛ ሽወዳ ራሳችንን እናድን ነበር፡፡ እንደሃዲይኛ ይሁን ከምባትኛ ብሂላችን ቢሆን “የመጀመሪያው ቂጣ ቢያር ሁለተኛው አያርም” ብለን ከተደገሱልን ተከታታይ የመከራና የሀዘን ድግሶች ራሳችንን እናተርፍ ነበር፡፡ ግን የዕዳ ደብዳቤያችን የመቀደጃው ጊዜ ገና ሆነና ይሄውና የብዙዎቻችን ልጆች የሚሆኑ የትናንት ወጣቶች ለማ መገርሣና ዶ/ር ኮሎኔል አቢይ አህመድ እንኳን በተራ የቃላት ኳኳታ ጢባ ጢቤ ይጫወቱብናል – “አፈ ቅቤ ልበ ጩቤ”ዎቹ ጎልማሦች በከፍተኛ ትዕቢት ተወጥረው ሕዝብን ማገንተራቸውን ቀጥለዋል፡፡ አንዳንዴ የክርስቶስን የአነጋገር ላህይ መዋስ ደግ ነው፡- እናም እውነት እውነት እላችኋለሁ እነዚህ ወጣት አሰለጦች ዋጋቸውን ያገኛሉ፡፡ እንደቀለዱብን የሚቀሩ ከመሰላቸውና እናንት አንባቢያንም ከመሰላችሁ በእግዚአብሔር ኅልውናና በሕዝብ ዕንባ ሁላችሁም እንዳፌዛችሁ ይቆጠራል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ራሱን ባይጠቅመው ለጠላቶቹ ግን መርዝ ነው፡፡

ኢሳት የኢትዮጵያ የወቅቱ አንደበት ነው፤ ግዴላችሁም እንውደደው፡፡ አሁን አሁን ይታማበት ከነበረው ነገር እየጠዳ ይመስላል፡፡ የዛሬውን “ዕለታዊ” የሚባለውን የመረጃ ትንተናቸውን ሳዳምጥ ውስጤ በንዴት ተንቦገቦገ፡፡ እነዚህ ሁለት አስመሳይ የኦህዴድ አመራሮች ምን ያህል እንደናቁንና እንደሚጫወቱብን ሳስበው ኢትዮጵያዊ ዜግነቴ ራሱ አንገሸገሸኝ፤ ክፉኛ አስጠላኝ፡፡ የነሱ የቁጭ በሉ ተግባር ያን ያህል እንዳላናደደኝ ግን መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ ይበልጥ ያንጨረጨረኝ የነዚህን አጭበርባሪዎች የዓዞ ዕንባ እያዬ ለነሱ የሚሰግደው የሕዝብ ቁጥር አሁን ሁሉ ነገር ግልጥልጥ ብሎ በሚታይበት ወቅት እንኳን በቀላሉ የሚገመት አለመሆኑ ነው፡፡ ብዙው ሕዝብ በሰይጣናዊ መተታቸው የሚታወቁትን እዩ ጩፋንና እስራኤል ዳንሳን ዕጥፍ ድርብ በሚያስከነዱ በነዚህ ልዝብ ሰይጣኖች የአፍዝ አደንግዝ ትብታብ ሳይነሆልል አልቀረም፡፡

“እግሬን መትተው ራሴን ቢያኩኝ አይገባኝም” እየተባለ በሚተረትበት ሀገር እነዚህ አሰለጦች ቀን ቀን ራሳቸውና በወኪሎቻው አማካይነት የልባቸውን እየሠሩ ማታ ማታ ግን በሚቆጣጠሯቸው የሚዲያ አውታሮች በኩል የሚያቀረሹትን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ እየተጋትን አሁንም ለሚያስገድሉን አስመሳዮች እናጨበጭባለን፡፡ ቀን ቀን “ኢትዮጵያ ሱሴ ናት” እያሉ ማታ ማታ አዲስ አበባንና የፌዴራል ተብየውን የሥራ ቦታዎች በነገዳቸው አባሎች ሲያጥለቀልቁ ማደራቸውን እንዳንመለከት በሚነዙት የሀሰት ቱሪናፋ ራሳችንን እንደልላለን፡፡ በዚህም የበሬው ቆለጥ እንደሚወድቅላት ተስፋ በማድረግ እበሬው በረት ድረስ ስትከተል እንደዋለችው ቀበሮ ሆነን እነሱ በሚቀራመቷት የጋራ ሀገራችን ተፈናቃይና ርሀብተኛ እንሆናለን፡፡ ስለዚህ የዕንቆቅልሹ ደራሲያን እኛ ራሳችንም መሆናችንን መረዳት አለብን፡፡ “ስንኖር ኢትዮጵያዊ፣ ስንሞት ኢትዮጵያ” ማለት እንዲህ በድግምት መያዝንና የበይ ተመልካች መሆንን ካስከተለ ነገ ሌላ ቀን መሆኑን በግልጽ መተንበይ ይቻላል፡፡

ነገሩ እንዲያ ከሆነ ታዲያን ያዝ እንግዲህ፡-

1. ኢትዮጵያ በደጇ ላይ አዲስ ለውጥ ሊመጣ ሰውነቱን እያሟሟቀ ነው፡፡ ይህ ያለንበት ለውጥ አጭበርባሪዎችና ግፈኞች የሠለጠኑበት እንደመሆኑ የኢትዮጵያ ጠላቶች (የውጭዎቹም የውስጦቹም) የቀዱለት ነዳጅ እስኪያልቅ ድረስ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ሞተሩ ይሠራል፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን ነዳጁ ያልቅና ከማይችለው አለት ጋር ተላትሞ ፍጻሜውን ያገኛል፡፡ እስከዚያው ይህ መንገድ ጠራጊ የእስስቶችና የሸለምጥማጦች አገዛዝ በሲሞቅ በማንኪያ ሲቀዘቅዝ በእጅ … በአፍ ጂዶም፣ በጠበንጃም – በካሮትም በዱላም – መስቀል ከሰላጤ ሆኖ ትንሽ ጊዜ ያንገራግራል፡፡ አዳዲሶቹ መዥገሮችም ብዙም ሳያብጡና የተራበ አንጀታቸውም ሳይጠረቃ ይሰናበታሉ፡፡ የተወሰነ ችግርና ግርግር መፍጠራቸው ግን የሚጠበቅ ነው፡፡ ስለዚህ እነእስክንድር መረባቸው ውስጥ ላለመግባት ቢጠነቀቁ ጥሩ ነው፡፡

2.እመኑኝ – የኢትዮጵያ ችግር በሰልፍና በውይይት አይፈታም፡፡ በሀገራችን ውስጥ ቋንቋ ለመጋደያ እንጂ ለመግባቢያ አይሆንም፡፡ በብዙዎቻችን ላይ ሰይጣን ስለሠፈረ ተነጋግሮ መግባባት አንችልም፡፡ ለመነጋገር እንኳን ብንስማማ ሁሉም ተደራዳሪ የሚመጣው ለማሸነፍ ቆርጦ እንጂ ሰጥቶ በመቀበል አምኖ አይደለም፡፡ ያለፈ የቅርብ ጊዜ ታሪካችን የሚመሰክረው ሃቅ ጠበንጃ ነካሽነታችንን እንጂ ሃሳብ አፍላቂነታችንን አይደለምና በሃሳብ እንሸናነፋለን ማለት ከህልም ያለፈ ቅዠት ነው፡፡ ስለዚህ ከአስቂኞቹ 107 ፓርቲዎች ከነዚህም ውስጥ የአብዛኛዎቹ አመራሮች በፈረንጅኛው የቃላት አጠቃቀም vegetate ካደረጉ ጎምቱዎች በውይይትም ሆነ በድርድር የሚወጣ አንዳችም መልካም ነገር እንደማይኖር የማረዳችሁ በከፍተኛ ሀፍረት ነው፡፡ ሀገራችን አንሳ አንሳ አሁን አሁን ሰው ሳይሆን ጭንቅላት የሌለው ሰው መሳይ ሮቦት ማምረት ጀምራለች፡፡ ስለሀገር ደንታ የሌለው፣ ሆድ እንጂ ጭንቅላት ያልፈጠረበት፣ ያንገት ላይ የይምሰል ማተብ እንጂ የሚመራበት አማናዊና ልባዊ ሃይማኖት የሌለው፣ ቅጥፍጥፍ ምላስ እንጂ ኅሊና ያልተበጀለት … ከንቱ ዜጋ ፖለቲካውንና ኢኮኖሚውን፣ ሃይማኖቱንና መከላከያውን በሚዘውርበት በአሁኑ ሀገራዊ ምስቅልቅል ሁኔታ ሙሰኝነትና ዘረኝነት ተወግደው ኢትዮጵያ ወደ ቀደመ ክብሯና ትመለሳለች ማለት “ፀሐይ በደቡብ ወጥታ በሰሜን ትጠልቃለች” ብሎ እንደማሰብ ያለ ሞኝነት ነው፡፡

3.ኢትዮጵያ በኦህዲድም ሆነ በኦነግ፣ በግንቦት ሰባትም ሆነ በብአዴን ወይም እንደጉንዳን ሲርመሰመስ እንደምንናየው ባለ የጎጥና የሸጥ የፖለቲካ ቡድን ይበልጥ ትቆሳስል እንደሆነ እንጂ ከወደቀችበት አትነሳም፡፡ እነዚህ ቡድኖች ተፈጥሯዊ ሥሪታቸው ሙሉ በሙሉ ወይም በተወሰነ ደረጃም ይባል በከፊል ከጨለማው ገዢ ከባላምባራስ ዲያብሎስ በመሆኑ እነሱን ተስፋ ማድረግ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ቆንጆ ልጃገረድን እንደመጥቀስ የሚመሰል ቂልነት ነው፡፡ የሞኝ አሸናፊነት መሠረቱ ድንቁርናዊ እምቢታው ነውና እነሱ ግን ይመስላቸዋል፡፡ እንዲህ ስላቸውም ደግነቱ ንቀው ይተውኛል እንጂ ሊቆጡ ይችላሉ፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ ነፃነት ከአቅማቸው በላይ መሆኑን የምገልጽላቸው ለልፋትና ድካማቸውም በማዘን ጭምር ነው፡፡ መፍሻ የሰውነት ክፍሉን ከኦህዲድ/ኦነግ ጋር ገጥሞ በወረት ፍቅር በመጠመድ “እነአቢይን ያዬ በዐይኔ በብረቱ መጣ” በማለት የሀገራችንን ችግር ላለማየትና ላለመተቸት በጥቅም ይሁን በዓላማ ተሳስሮ ሁለንተናውን ያሣወረው ግንቦት ሰባት ካብ አይገባ ድንጋይ መሆኑንና የሚናገረውና የሚያደርገው ልክ እንደጓደኞቹ የተፈናጅራ መሆኑን በተለይ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በሚገባ አስመስክሯል፡፡ “ቂጥኛም ከውርዴ” እንዲሉ ከባለጊዜዎች ጋር መሞዳሞዱ አይሎ እፍ እፍ ፍቅር ውስጥ የገባ ይመስላል – ቢያንስ የጫጉላ ሽርሽሩ የጠላትህ ጠላቴ ተጋምዶሻዊ የወረት ፍቅር የፈጠረው ሥልታዊ መልካም ግንኙነት እስኪገባደድ ድረስ ይህ አሣፋሪ ድራማ መቀጠሉ አይቀር ይሆናል፡፡ ግም ለግም … ይባል የለም?

ከዚህ አኳያ “ክርስቶስ ለሥጋው አደላ” እንዳትሉኝ እንጂ ምናልባት አልዓዛርን በአራተኛ ቀኑ ከሞት ወደ ሕይወት የለወጠው የክርስቲያኖች ጌታና መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ የቀድሞ ኢሕዲንና ብአዴንን የአሁን አዴፓን በዐርባኛ ዓመቱ ከአሽከርነት ወደ ራሱ ጌትነት ለውጦት ነፍስ ከዘራ ሀገራችንም ተስፋዋ ሊለመልም ይችላል፡፡ ምክንያቱም በዘረኞች እጅ ውስጥ ጥቂት ሰዎችና ብዙ ገንዘብ ሲኖር አዴፓን መሰል ተስፋ ሊጣልባቸው የሚችሉ ቡድኖች እጅ ውስጥ ግን ተስፋን የሰነቀውና ከ100 ሚሊዮን በላይ የሚገመተው የኢትዮጵያ ሕዝብ በመኖሩ ነው፡፡ ፈጣሪንና የኢትዮጵያን ሕዝብ ይዞ የሚነሣ ኃይል “በፌዴራል ሥርዓታችን የምንደራደረው መቃብራችን ውስጥ ስንጋደም ብቻ ነው!” የሚሉ እንደ ዖዴፓ/ኦነግና ቢጤው የሌሊት ወፍ ግንቦት ሰባትን ከነአፈ ቃላጤዎቻቸው አደብ ማስገዛትና አማራ-ጠል መርዘኛ ምላሳቸውን ማስታገስ አይሣነውም፡፡ ወደንም ባይሆን ተገደን ለቀኑ ዕድል እንስጠው፤ ቀኑ ደግሞ ቀርቧል፡፡

“እባብ ልቡን አይቶ እግሩን ነሣው” ይባላል፡፡ ወሬና ተግባር፣ ፉከራና ዛቻ፣ የማድረግ ፍላጎትና አቅምና ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ክምር ዝናና ቁልል ገንዘብ… ምንም ማለት እንዳልሆኑ እኛ ብቻ ሣንሆን እነሱ ራሳቸውም ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ ስለዚህ ለብዙዎቹ ያው የያዙት “ሥራ”ም ሥራ ሆኖ የመከራና የፍዳ እንጀራ ስለሚበሉበት ካልሆነ በስተቀር በከንቱ ባይለፉ ይመረጣል፡፡

4. ኢትዮጵያን ከደራጎንያን የአጋንንት ቡችሎች ነጻ የሚያወጡ ኢትዮጵያውያን ተሹመዋል – አንዳች ነገር እንዲህ በል ይለኛል፡፡ እናም ቀናቸውን እየጠበቁ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ሰማያዊው ቀጭን ት’ዛዝ ሲደርሳቸው አሁን ካሉበት ይመጣሉ፡፡ እስከዚያው ግን ብዙ መማር ያለብን ነገር ስላለ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያውያን ሁሉ “ኮሌጅ” ገብተናል – ከነዮዲት ጉዲትና ከነግራኝ አህመድ የባከነ የትምህርት ሰዓት ስለነበር ወደዚህ ዘመን ተሸጋግሯል፡፡ መምህሮቻችንም እነ አቶ ፀጋየ አራርሳና ፕሮፌሰር ሕዝቅኤል ጋቢሳ፣ እነ ዶ/ር አቢይና አቶ ለማ መገርሣ… ናቸው – የአቢይ “ክላስማ” ሲ…ጥም!…፡፡ ጊዜያቸው ስለሆነ አንቅናባቸው፡፡ እንጥላቸው እስኪበጠስ “ፌዴራል፣ፌዴራል” ይበሉ – ሲጸነሱ ጀምሮ የተለከፉበትና በውርዝትናቸው ዘመንም የቆረቡበት የፀላዔ-ሠናያት ተልዕኮ ነውና፡፡ እስኪሰለቻው “ኬኛ፣ ኬኛ” ይበሉ፡፡ ቋቅ እስኪላቸው መሬትና ቤት ይዝረፉ፤ ንጹሓንንም ከየለገጣፎውና ከየሱልልታው ከየሰበታውም ያፈናቅሉ፤ በዚህስ ይበርቱልን፤ በውጤቱም የጽርሃ አርያምን ትግስት በብርቱው ይፈታተኑልን፡፡ መቼም ሀብትን ጠግቦ የሞተ የለም፡፡

የኦቦ ለማ ንግግር ግን “ጭስ” ናት አይደል? “አሁንም ኢትዮጵያ ሱሴ ናት፡፡ ዛሬ አይደለም ነገም አትጠራጠሩኝ” አለ አሉ?! “ዛሬን እንዳሞኘኋችሁ ነገም አሞኛችኋለሁ” ለማለት መፈለጉን የማይገባው የለም ብሎ አስቦ ከሆነ ተሳስቶ መሆን አለበት፡፡ (ንጉሡ “ራት ያልበላችሁ እጃችሁን አውጡ” ብለዋል – አለ አሉ አጋፋሪው፡፡ ከዚያ ያልበሉት እጃቸውን እንደችቦ ሽቅብ ዘረጉ አሉ፡፡ አጋፋሪው ቀጠለ – “ዛሬም ድገሙ ተብላችኋል”፡፡) እንኳን የዚችን ንግግር ውስጠዘ ሌላም ሥውር ስፍ እንደምናውቅ ኦቦ ሚስተር አቶ ለማ ቢረዳልኝ ደስ ይለኛል፡፡ ሀፍረትን ባወጣ መሸጥ ይሏል እንደለማና አቢይ ነው፡፡ ይልቅየስ ሁለቱ ተባብረውና ተጋግዘው የውሸትና በቃላት የመደለል “ጥበብ” ማሠልጠኛ ተቋም ቢከፍቱ ከአውሮፓና ከአሜሪካ ሳይቀር ብዙ ተማሪዎችን ሊያገኙ ይችላሉ፡፡

ለነገሩ እነሱ ምን አጠፉ? እነሱን አምኖ የሚጃጃል ገልቱ እስካገኙ ድረስ ገና ብዙ ያምታታሉ – ከፈለጉ በውሸት ዕንባ እየተነፋረቁ ጭምር፡፡ ወያኔ የኋላ ኋላ ዕዳው ለራሷም በገፍ ይተርፋታል እንጂ ለጊዜው የልብ አድራሽ ልጅ ተክታ ሄዳለች፡፡ ግን ግን ወያኔ ትክክል ልትሆን ትችል የነበረው አንድም አንድ እንኳን ትግሬ መሀል አገር ባይኖር፣ አንድም የትግሬና የአማራ መልክ የነጮችንና የጥቁሮችን ያህል ቢለያይ፣ አንድም ወያኔ-ትግሬዎች በመሀል አገር ምንም ዓይነት ሀብትና ንብረት ባያፈሩ፣ አንድም በዘረኝነት ፋፋና ሴሪፋም ጠብድሎ ሊፈርጥ የተቃረበው የጎሠኝነት ሦርያዊና የመናዊ ዕልቂት በነጃዋርና ዳውድ ኢብሣ ፊሽካው ሳይነፋ ትግሬዎች ጓዛቸውን ጠቅልለው ከሚፈራው ነገር ሁሉ ሊያመልጡ ቢችሉ…ነበር፡፡ አሁን ግን ግመል ሰርቆ አጎንብሶ እንደመሄድ ነው፡፡ እዚች ላይ የወያኔ ፎርሙላ ሁሉ ገደል ገባ፡፡ የደደቢትን ማኒፌስቶ የሚረግሙበት ጊዜ እየተቃረበ ነው፡፡ አማራን አጠፋን ብለው የፈለሰፉት “ኒኩሌር” ወደራሳቸው መዞሩ አይቀርም፡፡ አዎ፣ አንዳንድ የፈጠራ ሥራዎች ባለቤትንም ይዘው ይጠፋሉ፤ አንዳንድ የተረገሙ ጽንሶችም በእግራቸው ይመጡና ጦሳቸው ከነሱም አልፎ ለእናታቸውም ይተርፋል – እንደሕወሓት፡፡ “እዚያም ቤት እሳት አለ” ያሉት ማን ነበሩ?

ዋናው የነአቢይና ለማ ዓላማ ግን አዲስ አበባን ከኢትዮጵያውያንና ከአፍሪካውያን እንዲሁም ከዓለም ሕዝብ የጋራ ንብረትነት በዘዴና በልዩ ሥልት ቀምቶ ለሚቃዡባት የኦሮምያ ሪፓፕሊክ ምሥረታና ዋና ከተማነት ማብቃት ነው፡፡ ግን ግዴላችሁም እግዚአብሔር ይቀድማል፡፡ በርትተን እንጸልይ፡፡ “ኢትዮጵያ ሱስ ናት” – እውነትም ሱስ፤ በልጆቿ ደም ካልታጠቡ፤ልጆቿን ካላፈናቀሉ ዕንቅልፍ የማያሲዝ ሱስ! በኦሮምኛ እየተራገሙ በአማርኛ የሚያስመርቅ ሱስ፡፡ ወያኔም እንዲህ ነበረች፡፡ በትግርኛ “አማራ አህያ ነው፤ አማራ ፈሪ ነው፤ እገባበት እየገባህ እያሳደድክ በለው” በማለት በሀሽሽ ለሚነዱ ጦረኞቿ በወኪቶኪው ትለፍፍና በበረሃ ሬዲዮኗ ደግሞ በነሴኩቱሬና ሐመልማል በአማርኛ “ጀግናው የአማራ ሕዝብ ለኢሕአዴግ ትግል ስኬት አሥር አህዮችንና ሃምሣ በጎችን አበረከተ” ታስብል ነበር፡፡ ታሪኮች ይደጋገማሉ፤ ይመሳሰላሉም፡፡ ሁሉም ማለፉ ግን ደግ ነው፤ አሁን ያልፍና ቅድም ይሆናል፤ ትናንት አልፎ ዛሬ፣ ዛሬም አልፎ ነገ እንደሚሆነው ሁሉ፡፡ የምለው ሁሉ እውነት ነው፡፡ ዘር ለማጋጨት ቅብጥርሴ የምትይ የወያኔ አቦካቶ ሁላ እንዲህ ማለት አሁን አይደለም፡፡ ደግሞም የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደዘር ፍጅት አይገባም፡፡ ጠላቱን ያውቃል፡፡ “ድብድቡ ሲጀመር” ቡጢዎች ሁሉ ወዴት እንደሚያቀጣጩ ከአሁኑ በግልጽ ይታወቃልና በሌሎች ሀገራት እንደሆነው በሀገራችንም ይሆናል ብለን ብዙም አንፍራ፡፡ “ሳለ ፈጣሪ አሟጠሽ ጋግሪ” ብሏል ያገሬ ገበሬ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ መሠሪዎች ባጠመዱለት ፈንጂ የሚረማመድ ሞኝ ሕዝብ ቢሆን ኖሮ ፆሙ ሳይገባ ባለፈው ሰሞን እንክት አድርጌ የበላኋቸውን የጫልቱና ሙሉቀን፣ የአብረኸትና ስንሻው እንዲሁም የፈይሣና የአምለሰት ድል ያሉ የሠርግ ሥነ ሥርዓቶች እውን አይሆኑም ነበር፡፡ እኛ እኮ የተለዬን ነን፡፡ ጠላቶቻችን የእግር እሳት የሆነባቸው ደግሞ ይህ ከዓለማችን ሕዝብ የተለዬ ጠባያችን ነው፡፡ “በለው! ተላለቁልህ!” ብለው ጥጋቸውን በመያዝ በደስታ ጮቤ ከመርገጣቸው አንድ እንሆንና ሮሚዮና ዡሌትን በሚያስንቅ ሁኔታ ተፋቅረን አንጀታቸውን እናሳርራለን፡፡ እነሱም አይተኙልንም፡፡ ሌላ ዘዴ ሲቀይሱና እንደገና ሊያባሉን ሲዘምቱብንና ሲያዘምቱብን ያንንም እናከሽፍባቸዋለን፡፡ ግሩም ሕዝብ ግን በጊዜ ሂደት ኅልውናው እየተሸረሸረ ያለ ሕዝብ፡፡ እናም የውኃ ጠብታ አለትን እንደሚበሳ ሁሉ ከዚህም በላይ መጎዳታችን ለጥገና አስቸጋሪ ያደርገዋልና የባሰው ከመምጣቱ በፊት በቶሎ መላ እንፈልግ፡፡…

__
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
13,682FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here