spot_img
Wednesday, May 29, 2024
Homeነፃ አስተያየትየአብይ/ለማ "አብረቅራቂ" ድል (በመስከረም አበራ)

የአብይ/ለማ “አብረቅራቂ” ድል (በመስከረም አበራ)

(በመስከረም አበራ)
መጋቢት 30 ቀን 2011 ዓ .ም.

ባለፉት ሳምንታት ፅሁፎቼ የሃገራችንን ፖለቲካ ወደ አስፈሪ ገደል እየነዳ ባለው የኬኛ ፖለቲካ ዙሪያ ሃሳቦችን ሳነሳ ሰንብቻለሁ፡፡ያለፈውን ሳምንት ፅሁፌን ስቋጭም የኬኛ ፖለቲካን ልጓም ለማስያዝ ማን ምን ማድረግ አለበት በሚለው ወሳኝ ጉዳይ ዙሪያ ሃሳቦችን እንደምሰነዝር ቀጠሮ ይዤ ነበር፡፡ሆኖም ሰሞኑን አቶ ለማ መገርሳ እና ዶ/ር አብይ የተናገሯቸው ንግግሮች እና ተያያዥ ጉዳዮች ለከረምኩበት የኬኛ ፖለቲካ ምርመራ ግብዓት የሚሆኑ ስለመሰለኝ በዚህ ሳምንት ጣልቃ አስገብቼ ልቃኛቸው ወደድኩ፡፡

አቶ ለማ መገርሳ እና ዶ/ር አብይ አህመድ የለውጥ አመራር ነን በማለታቸው የኢትዮጵያን ህዝብ ቀልብ የሳቡ ሰዎች ናቸው፡፡በዚህ ላይ እድሜ ጠገቦቹ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲከኞች “ኦሮሞ በቁመቱ ልክ ስልጣን ያላገኘባትን ኢትዮጵያን አንፈልግም” ሲሉ የኖሩ መሆናቸው ግልፅ ነው፡፡እንዲህ ባለ የኩርፊያ ሁኔታ ለነበረው የኢትዮጵያ እና የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲከኞች ግንኙነት የለማ/አብይ ኢትዮጵያን እየጠሩ ወደ ፖለቲካው ሜዳ መምጣት እንዳች እርቅ የሚያመጣ ነገር ተደርጎ ነበር በብዙ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ የተወሰደው፡፡እውነት ለመናገር እንደ ኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲከኞች ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ከባድ የቤትስራ የሆነ ብሄርተኝነት የለም፡፡የሃገራችን ፖለቲካ ከዘር ቁርቁስ ወጥቶ ወደ ተራማጅ ዲሞክራሲያዊ ፖለቲካ እንዳይራመድ በማዘግየት የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲከኞችን የሚወዳደር የለም፡፡

የኦሮሞዎቹ ለማ/አብይ ወደ ስልጣ መምጣት የኦሮሞ ብሄርተኝነት ልሂቃን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዝመና ላይ የጣሉትን ከባድ ቀንበር ይቀንሰዋል የሚል እምነት ነበረ፡፡ሆኖም የተራማጅ ወጣቶች ስብስብ ነኝ ባዩ ኦዴፓ ወደ ስልጣን ላይ መምጣት ነገሩን ሊቀይረው አልቻለም፡፡ይልቅስ አስቻይ ሁኔታን ፈጠረለት፡፡ይህ አስቻይ ሁኔታ በምን ይገለፃል ከተባለ በቀዳሚነት የሚመጣው የአብይ/ለማ ቡድን አማላይ ንግግር ነው፡፡የነዚህ ሰዎች ንግግር አብዛኛው የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲከኞች የማይታወቁበትን የኢትዮጵያን ጉዳይ ቀዳሚ አድርጎ ሌሎች ጉዳዮችን ተከታይ የማድረግ ነው፡፡ይህ ንግግራቸው ከልባቸው ይሁን አይሁን እርግጠኛ መሆን ለመለኮት ብቻ የተቻለ እውቀት ስለሆነ ሃገሩን የሚወድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ቃላቸውን አምኖ ለተግባራቸው አጋርነቱን ከማሳየት ውጭ አማራጭ የለውምና ያደረገው ይህንኑ ነው፡፡

ወደተግባር ሲገባ ግን አብይ/ለማ እያሳዩ ያለው ነገር የተጠበቀውን ያህል አልሆነም፡፡ እንዲያም ሆኖ ህዝቡ ከጎናቸው አልተለየም፡፡አብይ/ለማ ያሉበትን የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲካን ውስብስብነት ሁሉም ሰው የሚረዳው ስለሆነ እነዚህን ሰዎች እየደገፉ “አክራሪዎችን” እንዲከላከሉ ጉልበት ወደ መሆኑ ነው የሌላው ኢትዮጵያዊ ዝንባሌ፡፡ይህ ነገር ግን እንደተጠበቀው የአክራሪ ብሄርተኞችን ጉልብ ከማዛል ይልቅ እያበረታቸው ነው የሄደው፡፡ኦነግን የመሰሉ ታጣቂ አክራሪ ዘረኞች በሃገሪቱ ላይ እየፈፀሙ ያለውን ጥቃት፣የተለያዩ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ሚዲያዎች እና ምሁራን ቅንጣት ያህል ሃላፊነት በማይሰማው መንገድ ዘረኝነትን ያለከልካይ ያራግቡ ይዘዋል፡፡በአደባባይ ከሌላ ዘር ጋር ጋብቻ እና ንገግግር እንዲቆም የሚናገሩ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲከኞችን አብይ የሚመሩት መንግስት በህግ አልጠየቃቸውም፡፡

ሃገሩ ኢትዮጵያ እንድትኖርለት የሚፈልገው የዜግነት ፖለቲካ ጎራውም መንግስት ለነዚህ አካላት የሚያሳየውን አላስፈላጊ ትዕግስት በመቃወም ጮክ ብሎ ለመናገር ቀድሞ ስለ ለማ/አብይ በተናገረው መልካም ንግግር ይሉኝታ ተተብትቦ አፉን ይዟል፡፡ይሉኝታውን ጥሎ ስለ እውነት የሚናገረው የዜግነት ፖለቲካ ደጋፊ ከራሱ ከዜግነት ፖለቲካው ጎራ የጨለምተኝነት፣የለውጥ አደናቃፊነት ስም ተለጥፎበት ውግዘት ይዘንብበታል፡፡ይህን ውግዝ የፈራው ሌላው የዜግነት ፖለቲካ ደጋፊ ቡድን ክፉም ደግም የማይናገር ዝምተኛ ሆኗል፡፡

ሲጠቃለል የአብይ/ለማ ቡድን ወደስልጣን መምጣት የዜግነት ፖለቲካ ጎራውን ክፉኛ ከፋፍሎ አዳክሞታል፡፡የክፍልፋዩ አንድ ቡድን ከላይ እንደተቀመጠው የአብይን እና የለማን የቀደመ ንግግር ሰምቶ እዛው ላይ የዕምነት አለት ሰርቶ መኖርን የመረጠ፣ቃል ከተግባር ለማመሳከር የማይፈልግ፣እውነትን መሸሽን የመረጠው ነው፡፡ይህ ቡድን የራሱ እውነትን መሸሽ ሳይበቃው እንደ እርሱ እምነት ብቻ ታቅፈው ያልተቀመጡትን ዜጎች በጨለምተኝነት፣በለውጥ አደናቃፊነት የሚከስ፣ አድርባይነትም የማያጣው ጎራ ነው፡፡በጣም የሚገርመው ለዜግነት ፖለቲካ ጠመንጃ አንግተው ሲታገሉ የነበሩ ወገኖችም በዚህ ጎራ ውስጥ ሰተት ብለው የገቡ መሆናቸው ነው፡፡

ይህኛው ጎራ በአሁኑ ወቅት በሃገራችን ስልጣን በያዙም ባልያዙም የኦሮሞ ብሄርተኞች ስራ ሳቢያ በሃገራችን እያንዣበበ ያለውን ችግር የማያውቅ አይደለም፡፡ይልቅስ አብይ/ለማን ከደሙ ንፁህ ለማድረግ የሚፋትር ዓላማው ምን እንደሆነ ግራ የሚያጋባ ቡድን ነው፡፡ይህ ቡድን አብይን/ለማን ተራማጅ ፖለቲከኞች ለማድረግ ካለው መፋተር የተነሳ እነሱው ዋና እና ምክትል ሊቀመናብርት ሆነው በሚመሩት ኦዴፓ በመግለጫ ሳይቀር የሚያወጣውን እጅግ አደገኛ አካሄድ “የአክራሪዎች ስራ ነው” ሲል የማይታወቅ የጦስ ዶሮ ያርዳል፡፡በበኩሌ የኦዴፓን መግለጫዎች፣የሹማምንቱን ንግግሮች ካየሁ በኋላ “በአክራሪው” እና “በለዘብተኛው” ኦህዴድ መሃል ያለው መስመር ሊገባኝ ተቸግሬያለሁ፡፡የኦሮሞ ፖለቲከኛ ማክረሩ የሚታወቀው “ፊንፊኔ ኬኛ” ሲል ነው፡፡ይህ ደግሞ ለማ እና አብይ ሊቀመናብርት ሆነው ማህተም ባሰፈሩበት የኦዴፓ መግለጫ በግልፅ አማርኛ የተነገረ ነገረ ነው፡፡በዚህ ሁኔታ አክራሪ ከለዘብተኛ የተለየ ተደርጎ የሚወራው የለበጣ አካሄድ አላማው ምን እንደሆነ ግልፅ አይደለም፡፡

ሁለተኛው ቡድን ቃል ከተግባር መርምሮ እውነት ወዴት እያዘነበለች እንደሆነ መረዳት ባያዳግተውም ቀድሞ ስለለማ/አብይ ስለተናገረው በጎ እምነት የተነሳ ይሉኝታ የያዘው ነው፡፡ይህ ጎራ እውነቱን ተረድቶ ሃገሪቱ ስለገባችበት ችግር በግልፅ መነጋገሩን የሚሸሽው ነው፡፡ሶስተኛው ጎራ አብይ/ለማም ቃል ከተግባር ለማሰናሰል አቅም ሊያንሳቸው የሚችሉ የሰው ፍጡራን መሆናቸውን፣ ግፋ ሲልም የዘር ፖለቲከኞች መሆናቸውን የተረዳ ነው፡፡ይህኛው ጎራ አብይ/ለማን ጨምሮ የኦሮሞ ፖለቲከኞች እየተጓዙበት ያሉትን አካሄድ መርምሮ በጎ የሚባሉትን በማበረታታት አደገኛ የሚመስሉት ደግሞ በፍጥነት ሃይ ሊባሉ እንደሚገባ የሚወተውተው፣ለዚህም የሚሰራው ነው፡፡ በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ እየሰራ ያለው የባልደራስ ምክርቤት ከዚህ ወገን የሚመደብ ነው፡፡አራተኛው ቡድን ቀደም ሲል በለማ/አብይ ቡድን በሰፊው ተስፋ አድርጎ የነበረ ከመሆኑ የተነሳ አሁን ኦዴፓ በሚያደርገው ከንግግሩ ያፈነገጠ ተግባር ተስፋ ቆርጦ፣በሃገሩም ተስፋው ተሟጦ በኩርፊያ ዝምታ ውስጥ ያለው ነው፡፡ይህ ተስፋ የቆረጠው ቡድን እድሉን ከሃገሩ ለማሰናሰል የሚቸገር፣ ባገኘው አጋጣሚም ስደትን የሚመርጥ ነው፡፡
ህወሃትን ለመቃወም በአንድነት ተሰልፎ ጠንካራ የፖለቲካ ሃይል ሆኖ የኖረው የዜግነት ፖለቲካ አራማጁን ጎራ እንዲህ እርስ በርሱ የማይደማመጥ፣እንደ ውሃላይ ኩበት የሚዋልል፣ግራ የገባው ያደረገው የለማ/አብይ በተግባር የማይተረጎም ንግግር ነው፡፡ይህ የለማ/አብይ ቡድን ወደ ስልጣን መምጣት ለብሄር ፖለቲካው ያስመዘገበው አብረቅራቂ ድል ነው፡፡የለማ/አብይን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ የዜግነት ፖለቲካው ጎራ በመርህ ላይ ቆሞ ታግሎ የሚያታግል፣አሰባሳቢ ጠንካራ ፓርቲ የሌለው የሙትልጅ ሆኗል፡፡ያለ አሳባሳቢ የቀረው ይሄው ጎራ ቢቸግረው ግለሰቦች በሚያቋቁሙት የሲቪክ ማህበር ስር ሆኖ መታገል ጀምሯል፡፡ይህም ቢሆን አዲስ አበባ የእኛ ነች ለሚለው አንድ ተግዳሮት ብቻ የሚሰራ መሰባሰብ ነው፡፡ በመላ ሃገሪቱ ዜግነቱን ብቻ ይዞ የተበተነው ኢትዮጵያዊ የክልል ባለቤት ነኝ በሚል የዘር ፖለቲከኛ ለሚመጣበት ተግዳሮት አለሁ የሚለው ፓርቲ የለም፡፡

ይህን ይሰራሉ የተባሉ አርበኞች ግንቦት ሰባትን የመሰሉ ፓርቲዎች ጭራሽ እነሱ ሊሰሩት የሚገባውን ስራ እየሰሩ ያሉ ግለሰቦችን እና ሚድያዎችን በማውገዝ ተጠምደዋል፡፡ይህ የዜግነት ፖለቲካውን ጎራ የገጠመው የቋንቋ እና የሚና መደበላለቅ ለዘር ፖለቲከኞች ትልቅ ድል ነው፡፡ ለዚህ ምስክሩ “አቶ እስክንድር ነጋ ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳይሰጥ ከመከልከል ይልቅ በዜግነት ፖለቲካ አቀንቃኞች ማስወገዙ የተሻለ ትርፋማ ያደርግ እንደነበር” አቶ ጃዋር ለኦዴፓ መራሹ መንግስት ምክር መለገሱ ነው፡፡ጃዋር ይህን ያለው ከምድር ተነስቶ አይደለም፤የዜግነት ፖለቲካ አራማጁ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ባልደራስ የሚል ነገር ልክ እንዳልሆነ ሲያወግዙ፣ባልንጀራቸው አቶ ኤፍሬም ማዴቦ እና አቶ አበበ ቦጋለ ኦዴፓን በተመለከተ እውነትን እየገለፁ ያሉ የኢሳት ጋዜጠኞችን በጨለምተኝነት እና ተንኮለኝነት ሲከሱ ስለሰማ እንጅ!

የዜግነት ፖለቲካው ጎራ እንዲህ ባለ ከፍተኛ ግራ መጋባት፣ትርምስ፣ድንግርግር እና ለጎሳ ፖለቲካ የመገበር አድርባይነት ውስጥ እንደገባ፤ክፉኛ እንደተከፋፈለ ያወቁት የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲከኞች ወቅቱን ያለ ሃይ ባይ የበላይነታቸውን ለማፅናት፣የዜግነት ፖለቲካን ወደ ማያንሰራራበት ማጥ ውስጥ ለመክተት እየተሟሟቱ ነው፡፡ይህን ለማድረግ ሚዲያን ፣የመንግስት ስልጣንን፣ቄሮ የተባለውን ስብስብ ይጠቀማሉ፡፡በሚዲያ በኩል እንደ አቶ በቀለ ገርባ አይነት ሰዎችን አሰልፈው የኦሮሞ ብሄርተኝነት በኦሮሚያ የሚኖርን ሌላውን ሰው ገበያ ወጥቶ በገዛ ገንዘቡ ገዝቶ እንዳይበላ እስከማድረግ የሚደርስ ጉልበት እንዳፈረጠመ ሊያሳውቁን ይጥራሉ፡፡የOMN ባለቤቶች እና መሰሎቻቸው የዜግነት ፖለቲካ በተሻለ ሁኔታ ባለባቸው ክልሎች የዘር ፖለቲከኞች እንዲጎለብቱ አዳዲስ የዘር ፖለቲከኞችን በመኮትኮት ላይ ሲሟሟቱ አዛውነቱ ኦነግ በማንነታቸው ሳቢያ ስለሚያፈናቅላቸው ፣ስለሚያስርባቸው ብሄሮች በስህተት አይዘግቡም፡፡
የመንግስት ስልጣንን የያዘው ኦዴፓ አንድቀን ኮስተር አንድቀን ለዘብ እያለ የኬኛ ፖለቲካውን የሚያግዝ ስራ እየሰራ ነው፡፡መግለጫ አውጥቶ አዲስ አበባን የኦሮሚያ እንደሚያደርግ ባወራ በሳምንቱ በጠ/ሚው አንደበት አዲስ አበባ የሁሉም ሰው እንደሆነች ይናገራል፡፡ ዶ/ር አብይ እንደውም ነውር(በእሳቸው አገላለፅ አሳፋሪ) የሆነው አዲስ አበባ የማን ነች ብሎ መጠየቁ እንጅ አዲስ አበባ የእኔ ነች ሲባል እንዳልሆነ ለሃገር ውስጥ ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫቸው ተናግረዋል፡፡አብይ ሲቀጥሉ “አዲስ አበባ የእኔ ነች ማለት የአንተ አይደለችም ማለት አይደለም” ሲሉ ኦዴፓ ለአዲስ አበባ ባለቤትነት እንደሚሰራ በመግለጫው የነገረን ነገር ስህተት እንዳልሆነ በገደምዳሜ ተናግረዋል፡፡

እዚህ ላይ ልብ መባል ያለበት ሁለት ነገር አለ፡፡አንደኛው በዶ/ር አብይ እይታ ህገመንግስ ጥሶ አዲስ አበባ የእኔ ነች ከሚለው ኦዴፓ ይልቅ የኦዴፓ ነገር ግር ብሎት አዲስ አበባ የማን ነች ብሎ የሚጠይቀው አካል ጥፋተኛ ነው፡፡ሁለተኛ አዲስ አበባ የእኔ ነች ማለት የአንተ አይደለችም ማለት አይደለም ሲሉ ኦዴፓ አዲስ አበባ የእኔ ነች ሲል በጨፌ ኦሮሚያ ስር አድርጌ ላስተዳድራት ማለቱ ነው፤ ይህ ደግሞ እናንተ አዲስ አበባ እንዳትኖሩ አይከለክልምና አዲስ አበባ የእናንተም ነች ማለታቸው ነው፡፡በዚህ የባለቤትነት ሁኔታ ኦዴፓ እያስተዳደረ፣የአዲስ አበባ ህዝብ ኦዴፓ በወደዳቸው ኦሮሞዎች ብቻ እየተዳደረ፤ አዲስ አበባ ደግሞ የሁሉም ነች ተብላ ይቀጥላል ማለት ነው፡፡ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ጃዋር አዲስ አበባ የኦሮሞ ንብረት መሆኗን ከሚናገርበት ንግግር የሚለየው ጃዋር የኢህአዴግ ካድሬ ባለመሆኑ ፍላጎቱን በግልፅነት በመናገሩ ብቻ ነው፡፡በተግባር ግን ጃዋርም አብይም እየተናገሩ ያሉት የአዲስ አበባን ህዝብ ራስን የማስተዳደር መብት በመንፈጋቸው የመቀጠል እቅድ እንዳላቸው ነው፡፡

ይብስ የሚገርመው የእርሳቸውን ፓርቲ ኦዴፓን ጨምሮ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲከኞች በአዲስ አበባ ላይ የሚያነሱት ጥያቄ ህገ-መንግስቱ ይከበር የማለት ነው ያሉት ነገር ነው፡፡ አብይ ይህን ሲያብራሩ ጥያቄው አዲስ አበባ በኦሮሚያ እምብርት ላይ የምትገኝ በመሆኑ የፋብሪካ ውጋጅን በኦሮሚያ ክልል ላይ የምትጥል ከመሆኑ እና ኦሮሚያ ለአዲስ አበባ ከምታስገኘው ግብዓት ጋር የተያያዘ እንደሆነ እንጅ ሌላ ነገር እንዳልሆነ ሊነግሩን ሞክረዋል በመግለጫቸው፡፡ይህን የሚሉት አብይ አዲስ አበባ የኦሮሚያ እንድትሆን እሰራለሁ ያለው ኦዴፓ ሊቀመንበር ናቸው፡፡

የህገ-መንግስቱ መከበር ጥያቄ እና የባለቤት ልሁን ጥያቄ አንድ ናቸው የሚለውን የጨፍኑ ላሞኛችሁ ነገር እዚህ ላይ ልተወውና ኦሮሚያ ለአዲስ አበባ የምታስገባው ግብዓት ልዩ ጥቅም እንድታገኝ ያደርጋታል ያሉትን ነገር ላንሳ፡፡ ወደ አዲስ አበባ የተለያዩ የግብርና ግብዓት ማስገባት ባለ ልዩ ጥቅም የሚደርግ ከሆነ ፍራፍሬውን ፣ቅመማቅመሙን ፣አትክልቱን ፣ቡናውን ወደ አዲስ አበባ የሚጭነው የደቡብ ክልልም፣እህሉን የሚጭነው የአማራ ክልልም፣ጨውን የሚልከው የአፋር ክልልም፣ፍየሉን የሚያበላው የሶማሌ ክልልም ሌሎች ክልሎችም ወደ አዲስ አበባ በሚልኩት የግበዓት ድርሻቸው መጠን በአዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም ያስፈልጋቸዋል ማለት ነው፡፡

ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም ይኑራት እየተባለ ከሚነገረው ነገር ሁሉ የሚያስኬደው በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ የአዲስ አበባን ውጋጅ የሚቀበሉ እና በመስፋፋቷ የተፈናቀሉ አርሶ አደሮችን በተመለከተ የሚነሳው ነገር ብቻ ነው፡፡እነዚህ ሰዎች ተገቢው ካሳ ሊሰጣቸው፣የተመሳቀለው ህይወታቸው እንዲስተካከል እንዲሰራ የሁላችንም ጥያቄ ነው፡፡ በእነሱ አስታኮ ከኦሮሚያ ዳርቻ ለመጣ ካድሬ አዲስ አበባን የማስተዳደር ወንበር ላይ ቂብ እንዲል መስራት ግን የሚያስማማም የሚያስኬድም ነገር አይደለም፡፡

እንደ አብይ ሁሉ አዲስ አበባን በተመለከተ በማይጨበጥ እጅግ ሙልጭልጭ ንግግር ውስጥ የሰነበቱት አቶ ለማ መገርሳ ከንግግራቸው መረዳት የሚቻለው አዲስ አበባ የኦሮሚያ ነች የሚለውን መግለጫ አምነውበት ያደረጉት እንጅ አንዳንድ የድንገቴ የዋህ ፖለቲከኞች እንደሚሉት አክራሪ ኦዴፓዎች አስገድደዋቸው እንዳልሆነ ነው፡፡የሶማሌ ክልል ተፈናቃዮችን አዲስ አበባ አላሰፈርኩም ብለው የሸመጠጡበት ንግግራቸው ከአፋቸው ሳይወጣ “ባሰፍርስ ምን አለበት እኔ የኦሮሚያ አዛዥ አይደለሁም እንዴ?” ማለታቸው ብቻ በቂ ምስክር ነው፡፡
ለማ ኢትዮጵያ ወደ ዘር እልቂት እንዳትሄድ በማድረጋቸው የውለታቸው ባለ ዕዳ እንደሆንን እየነገሩን የሰነበቱት ከኦሮሚያ ዳርቻ ለመጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ላልሆኑ ኦሮሞዎች የአዲስ አበባ መታወቂያ አላደልንም ማለታቸውን የምናምን ተላሎች ስለምንመስላቸው ነው፡፡’እነዚህ ባለ መታወቂያዎች አዲስ አበባ የሰፈሩት የጎሳ ግጭትን ለማስወገድ ዘብ ሊቆሙ ነው’ መባላችንም አይቀርም አንድቀን ደግሞ! በብዙ ያመንናቸው ዶ/ር አብይ ጭራሽ አዲስ አበባ ለማንም ከኦሮሚያ ለመጣ ኦሮሞ መታወቂያ አልተሰጠም ሲሉ በእርሳቸው ብቻ ሳይሆን በሃገራችን ፖለቲካም ተስፋ የሚያስቆርጥ ንግግር ተናግረዋል፡፡

አብይ በመግለጫቸው የህግ የበላይነትን እያስከበሩ እንደሆነ ለማስረገጥ መንግስታቸው በሱማሌ ክልል ያደረገውን፣በአዋሳም ህግ የጣሱ ሰዎችን ለፍርድ እንዳቀረቡ፣በሻሸመኔ ሰው ዘቅዝቀው የሰቀሉ ሰዎች እድሜ ልክ እንደተፈረደባቸው ገልፀው ይህ ሁሉ የህግ ማስከበር ስራ ተሰርቶ እያለ መንግስታቸው ህግን በማስከበር ክፍተት ስሙ የሚነሳው በጅምላ ስላላሰረ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡በዚህ ንግግር አንዳዘንኩ ሳልናገር ማለፍ አልፈልግም!

ያሳዘነኝ ዋና ነገር የኢህአዴግ ባለስልጣናት የኢትዮጵያን ህዝብ ግንዛቤ እንዴት አሳንሰው እንደሚገምቱ ማየቴ ነው፡፡የህግ የበላይነትን ማስከበር ሰውን ሰብስቦ ማሰር ነው ብለን የምናስብ ቢሆን ኖሮ አብይ ስልጣን ላይ እንደመጡ የአዲስ አበባን ወጣቶች ያለ አንዳች ምክንያት በጅምላ ሲያስሩ ህግ አስከበሩ ብለን እናሞግሳቸው ነበር፡፡ባጭሩ የአብይ መንግስት ህግ አላስከበረም የምንለው እትብታችን ባልተቀበረበት ሃገር ስንኖር ወጥተን መግባት አስጊ ስለሆነብን፣ በነፍስ ማጥፋት የተከሰሱ ሰዎች ፋይላቸው እንኳን ሳይዘጋ በትልቅ ሹመት ላይ ተቀምጠው ብናይ፣ኦነግ የተባለ ቡድን የኦህዴድ ባለስልጣናትን ተተግኖ ምስኪኖችን ሲየፈናቅል ብናይ፣የኦህዴድ ባለስልጣናት በግልፅ ባደባባይ ዘር እየለዩ እንደሚያፈናቅሉ በገዛ ንደበታቸው ሲናገሩ ብንሰማ ነው፡፡

ጠ/ሚ አብይ በመግለጫቸው ኦነግ በጌዲኦ ህዝቦች ላይ ያደረገውን ጥፋት ላለመናገር ያደረጉት መተጣጠፍ እኩል ያሳዘነኝ ነገር ነው፡፡ጠ/ሚው የጌዲኦዎችን ችግር በማንሳት ወደ ችግር ፈጣሪው ኦነግ ላለመሄድ ችግሩን ወደ ማሳነስ አስገማች ነገር ገብተዋል፡፡ሰው አልተራበም ሊሉም ይቃጣቸዋል፤”ሚዲያዎች ያልተራበ ሰው ፎቶ እያወጡ ነው እንጅ ሰው አልተራበም፤ ፣በርሃብ ሰው አልሞተም፣የሞተውም አንድ ሰው ነው እሱም በህመም ነው” ብለዋል፡፡ “ጌዲኦ እና ጉጅ እኔ እና አንተ ከምናስብላቸው በላይ የሚተሳሰቡ አብረው የኖሩ በትውልድም የወንድማማች ልጆች ናቸው” ሲሉ ስለጉዳዩ የጠየቃቸውን ጋዜጠኛ “ምን አገባህ?” በሚል ነገር ሸንቆጥ ሊያደርጉም ሞክረዋል፡፡

ከሽንቆጣቸው መለስ ሲሉም የጌዲኦን እና ጉጅን ችግር የአየር ፀባይ ችግር፣የመንግስት ክትትል ማነስ፣ሌሎች የማይታወቁ ሰዎች ተፈናቃይ ነን ብለው በመምጣታቸው እና በመለስተኛ የፀጥታ ችግር የተከሰተ ነገር አድርገው ኦነግን ላለመንካት ሲሉ ብቻ ነገሩን እጅግ ባቃለለ መንገድ ሊያልፉት ሞክረዋል፡፡ ጭራሽ “የጉጅ ሽማግሌዎች ጎረቤቶቻችን ጌዲኦዎች ምንነክቷቸው ነው የሄዱት ብለው ምክንያቱ ጠፍቷቸው እየተቸገሩ ነው” ሲሉ ጌዲኦዎች እንዲሁ መንገድ መንገድ ብሏቸው እንደተፈናቀሉ ሊያስመስሉ ሞክሯቸዋል፡፡

አብይ እንዲህ በአስገማች መንገድ እውነታውን ሊክዱ የሚፍጨረጨሩት ለኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲካ ተገን ሲሰጡ ነው፡፡አብይ ኦነግ ባጠፋው መጠየቅ ቀርቶ ያጠፋው ጥፋት እንኳን እንዳይወራ ማለባበሳቸው ለኢትዮጵያ መስራት ነው ብሎ ማመን የአድርባይነት ልምድ ይጠይቃል፡፡የዜግነት ፖለቲካ አራማጁ ጎራ ወደደም ጠላ፣ነቃ አልነቃ አብይ እና ለማ ኦነግን ጨምሮ የተለያዩ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ቡድኖች እያመጡ ያለውን ጥፋት ጆሮ ዳባ ባሉ ቁጥር የዜግነት ፖለቲካ ወደ ማያሰራራበት ገደል ይወርዳል፤የኢትዮጵያ እጣ ፋንታም መኖር ያለመኖሯ በማያሳስባቸው የጎጥ ፖለቲካ ካህናት እጅ ይወድቃል፡፡በነዚህ ሰዎች እጅ የወደቀች ኢትዮጵያ ይጎዝላቪያን ወይ ሩዋንዳን ትሆን ዘንድ ግድ ነው፡፡ ይህ ፅዋ ከሃገራችን ያልፍ ዘንደ መስራት ግድ ነው፡፡ እንዴት? ለሚለው ሳምንት እንድረስ፡፡
__
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here