spot_img
Sunday, May 26, 2024
Homeነፃ አስተያየትየዲያስፖራ ተሳትፎ በከፍተኛ ትምህርት - እድሎችና ፈተናዎቹ (በ አየናቸው አሰፋ )

የዲያስፖራ ተሳትፎ በከፍተኛ ትምህርት – እድሎችና ፈተናዎቹ (በ አየናቸው አሰፋ )

በ አየናቸው አሰፋ1
ሚያዝያ 10 2011 ዓ .ም

በጥናት የተደገፈ ቁርጥ ያለ መረጃ አይኑር እንጂ በኢትዮጵያ ዲያስፖራ ዘንድ መጠነ ሰፊ የእውቀት ሀብት ያለ መሆኑ ከሞላ ጎደል ሁሉም የሚስማማበት ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ እ.ኤ.አ. በ2014 የወጣ ጥናት እንደሚያሳይው እድሜያቸው 25 አመት እና ከዛ በላይ የሆነ በአሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መካከል 32% የሚሆኑት ቢያንስ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ናቸው፡፡ ይህም ከአሜሪካውያን አማካይ አገራዊ የትምህርት ደረጃ ከፍ ያለ ነው፡፡ በተመሳሳይ እ.ኤ.አ. በ2012 የወጣ አንድ የተባበሩት መንግስታት ሪፖርት በአሜሪካ እና በካናዳ ብቻ ቢያንስ 1600 በሶስተኛ ዲግሪ ደረጃ የሰለጠኑ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩ ግምት አስቀምጧል፡፡ ይህ ሪፖርት ከወጣበት ጊዜ ወዲህ ባሉት አመታት የነበረው የተማረ የሰው ሃይል ፍሰት ሲታይ ይህ ቁጥር ሊንር እንደሚችል ይገመታል፡፡ በሌላ በኩል በአሜሪካ ካለው ጋር ተመጣጣኝ ባይሆንም እንኳን እንደ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ጀርመን፣ አውስትራሊያ እና ኖርዌይ ባሉ ዋና ዋና የኢትዮጵያውያን መዳረሻዎች በተመሳሳይ የሰው ሃይል ሀብት ክምችት የሚገኝባቸው ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ ዲያስፖራው በእውቀት ዘርፎች እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ ከሚጠበቀውና ካለው አቅም በታች ነው፡፡ ለዚህም ሊነሱ ከሚችሉት በርካታ ምክንያቶች መካከል ዋና ዋና የሆኑትን ሁለቱን መጥቀስ ይገባል፡፡ አንደኛው በመንግስት እና በዲያስፖራው መካከል (በአብዛኛው) ጸንቶ የቆየው የመረረ ፖለቲካዊ ልዩነት ሲሆን ሁለተኛው የእውቀት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ያተኮረ የጠራ የዲያስፖራ እስትራቴጂ ያለመኖር ናቸው፡፡ ከጥቂት አመታት በፊት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል የተዘጋጀው የዲያስፖራ ፖሊሲም ቢሆን እውቀት ተኮር በሆኑ ዘርፎች ላይ በቅጡ የታሰበበት፣ የተቀናጀ እና የተሰነደ አይደለም፡ስለሆነም ፖለቲካው የሚፈጥረውን መሰናክል አልፈው የትምህርት ተቋማትን ለመደገፍ የሚሞክሩትም እንኳን ድጋፋቸው ያልተቀናጀ እና በግለስብ ደረጃ የተገደበ እንዲሆን ግድ ሆኗል፡፡

ሰሞንኛ ለውጦች

ባለፈው አመት የጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣት በመንግስት እና በዲያስፖራው መካከል የነበረውን ግንኙነት በከፍተኛ ሁኔታ ለውጦታል፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስተር ዲያስፖራውን አካታች የሆነ ፖለቲካዊ ማሻሻያ ከማድረጋቸው በተጨማሪ ዋና ዋና ወደ ሆኑ የዲያስፖራው መቀመጫዎች በማቅናት ዲያስፖራው በአገር ግምባታ እንዲሳተፍ፣ በተለይም የተማረው እና ሙያተኛው ዲያስፖራ በእውቀቱ እና በሙያው ሀገሩን እንዲያገለግል ግልጽ ጥሪ አድርገዋል፡፡

ምላሹም አዎንታዊ እና ደማቅ ነበር፡፡ ዲያስፖራው በሰፊው ድጋፉን ከመግለጽ በተጨማሪ በመራር ተቃዋሚነታቸው የሚታወቁ ጉምቱ ምሁራን ሳይቀር የመንግስትን ጥሪ ተቀብለው በተለያየ መንገድ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ይህንን በቅርቡ እየታየ ያለውን አዎንታዊ ግንኙነት ለማመላክት ልዩ ልዩ ማሳያዎች መጥቅስ ይቻላል፡፡

በታህሳስ ወር ራእይ ለኢትዮጵያ (Vision Ethiopia) የተባለው በዋናነት መቀመጫቸውን በአሜሪካ ያደረጉ ኢትዮጰያውያን ምሁራንን ያቀፈው የድርጅት ጉባኤውን በአዲስ አበባ አካሂዷል፡፡ ይህ ቢያንስ በሁለት ምክንያቶች በዲያስፖራው እና በመንግስት መካከል እያቆጠቆጠ ያለው በጎ ግንኙንት ተምሳሌታዊ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ የራእይ ለኢትዮጵያ መሪዎች ለበርካታ አመታት መንግስትን በጽኑ በመተቸት የሚታወቁ በመሆናቸው ባለፉት አመታት ይህንን ጉባኤ አዲስ አበባ ላይ ማካሄድ የሚታሰብ አልነበረም። ብዙዎቹ የጉባኤው አዘጋጆችና ተሳታፊዎች ለአስርት አመታት ከዘለቀ የስደት ኑሮ በሁዋላ ነው ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት፡፡ ሁለተኛ አዘጋጆቹ በኋላ እንዳስታወቁት ከነእንከኑም ቢሆን መንግስት አበረታች የሆነ ድጋፍ ለጉባኤው መሳካት አድርጓል። አልፎ ተርፎም የሳይንስና ከፍትኛ ትምህርት እና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሮች በጉባኤው ላይ በመግኘት ንግግር አድርግዋል፡፡

ባለፉት ወራት በርካታ የዲያስፖራ ድርጅቶች፣ ማህበራትና ጥምረቶች ተወካዮች ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል፤ ከመንግስትና የትምህርት ተቋማት ሃላፊዎች ጋርም ተወያይተዋል። ከነዚህም የተወሰኑት ከሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር የወደፊት አብሮ የመስራት አቅጣጫ የሚያስቀምጡ የመግባቢያ ሰነዶችን ተፈራርመዋል።

በሌላ በኩል መንግስት ቀደም ሲል በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ እንደ አንድ የስራ ዘርፍ የነበረውን የዲያስፖራ ጉዳይ ለብቻ በማውጣት የዲያስፖራ ኤጀንሲን አቋቁሟል፡፡ በትምህርት ዘርፉም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የአማካሪ ቦርድ ያቋቋመ ሲሆን ፣ በቦርዱ ውስጥ መቀመጫቸውን በውጭ ያደረጉ ምሁራን በሰፊው ተካተውበታል። ከዚህም በተጨማሪ በአማካሪ ቦርዱ ውስጥ ካሉት አስር ልዩ ልዩ ንዑስ ቡድኖች ውስጥ የዲያስፖራ ተሳትፎን የሚመለከት ይገኝበታል።

ተግዳሮቶች

ከላይ የተዘረዘሩት አዎንታዊ ለውጦች ፈተና አልባዎች አይደሉም። ይህን ሰሞንኛውን መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም እና ዲያስፖራው በሙሉ አቅሙ ሀገሩን የሚያገለግልበትን እድል ለመፍጠር ችግሮችን መለየትና ፈጣን ምላሽ መስጠት ያሻል። ለምሳሌ በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ያለው የዲያፖራ ተሳትፎ አንዱ ተግዳሮት ከፍተኛ እጥረት ባለባቸው የትምህርት አይነቶች ላይ ያለው ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆን ነው። የኢትዮጵያ ትምህርት ተቋማት ያለባቸው ከፍተኛ የተማረ ሰው ሃይል እጥረት በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ በተለይም በቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና እና ሂሳብ የትምህርት መስኮች ሲሆን በአብዛኛው ከዲያስፖራው የሚገኘው ደጋፍ በማህበራዊ ሳይንስ የትምህርት ዘርፎች ነው። ተፈላጊ በሆኑት የተፈጠሮ ሳይንስ ትምህርት ዘርፎች ካለው አቅም አኳያ እስካሁን ያለው ተሳትፎ እጀግ ውሱን ነው። ስለሆነም በነዚህ የትምህርት ዘርፎች ያለው የዲያስፖራ ተሳትፎ ማጠናከር እና ማስፋፋት የሚቻልበትን መላ መሻት ያስፈልጋል። ለዚህም መሰረቱን በአሜሪካ ኒው ዮርክ ግዛት ያደረገው እና በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ የተሻለ እንቅስቃሴ እያደረገ ያለውን የምሁራን ቡድን ተሞክሮ እንደመነሻ መውሰድ ይቻላል።

ግልጽ የሆነ ተቋማዊ ይዘት ያለው የዲያስፖራ ተሳትፎን አካታች በሆነ መልኩ የሚያስተባብር አካል ያለመኖር ሌላው ወቅታዊ ፈተና ነው። በቅርቡ የተቋቋመው የዲያስፖራ ኤጀንሲ ለዚህ የቀረበ ስልጣን የስራ ድርሻ መዘርዝር ያለው ቢሆንም ድርጅቱ አዲስ እንደመሆኑ ገና የራሱን መዋቅር፣ የስው ሃይል እና የቢሮ ቁሳዊ ዝግጅት በማደራጀት ላይ ነው። ስለሆነም ወቅቱ የሚጠይቀውን ፈጣን እና የተቀናጀ ምላሽ ለመስጠት ውሱንነት ሊኖርበት ይችላል።

በዚህ ላይ ዩኒቨርሲቲዎች በቅጡ የተቀናጀ የዲያስፖራ ተሳትፎ እቅድ የሌላቸው በመሆኑ እስካሁን አብዛኛው የዲያስፖራ ተሳትፎ በግል ተነሳሽነትና በተናጠል፣ ከተቋማዊ መስመሮች ይልቅ በግል ትውውቅና ግንኙነት ላይ የተመሰረተ አካሄድ እንዲይዝ ግድ ሆኗል። በመሆኑም ለጉዳዩ የተሻለ ቅርበትና አቅም ያለው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዩኒቨርሲቲዎችን እና ባለፉት አመታት በጉዳዩ ላይ ሲታትሩ የነበሩ በሃገር ውስጥ እና በውጭ ያሉ ግለሰቦችና ድርጅቶችን በማስተባበር በእውቀት ተኮር ዘርፎች የዲያስፖራን አስተዋጽኦ ሊያሳድግ የሚችል ፖሊሲ እና የተቋማዊ ማዕቀፍ ሊያሰናዳ ይገባዋል።

እዚህ ላይ በዩኒቨርሲቲዎች የሚነሳው አለመረጋጋት እና ሰላም እጦት የሚያስከትለው ዘርፈ ብዙ ፈተና የማይካድ ነው። ያለመረጋጋቱ መደበኛ የሆነውን የትምህርት ሂደት እና በዛም ውስጥ ዲያስፖራው ሊያደርግ የሚችለውን ተሳትፎ ከመገደቡ ባሻገር የዩኒቨርሲቲዎቹ አመራሮችና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከዘላቂ እና ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ይልቅ የእለት ከእለት ችግሮችን የመቆጣጠር እና መረጋጋትን የመመለስ ስራ ላይ እንዲጠመዱ ያስገድዳል።

ሌላው ሊጠቀስ የሚችለው ተገዳሮት የዜግነት ጉዳይ ነው። በተለይ ረዘም ላለ ጊዜ በቅጥር መልክ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የሚያገለግሉ የሌላ ሃገር ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊያን መታየት ያለባቸው እንደ ኢትዮጵያዊ ነው ወይንስ እንደ ውጭ ሀገር ዜጋ የሚለው መልስ ያላገኘ ጥያቄ ነው። በርግጥ በአዋጅ ቁጥር 270 መሰረት የትውልደ ኢትዮጵያዊ ማስረጃ ያላቸው የውጭ ሀገር ዜግነት የያዙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ውሱን ከሆኑ ፖለቲካዊ ተሳትፎዎች ውጭ እንደ ኢትዮጵያዊ እንደሚቆጠሩ ተደንግጓል። ይህም ከመግቢያ ቪዛ እና የስራ ፍቃድ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የሚያቀል (የሚያስወግድ) ነው። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ የትምህርት ተቋማት የውጭ ሐገር ዜጎች ከኢትዮጵያውያን ባልደረቦቻቸው ቢያንስ አምስት እጥፍ ክፍያ ሊያገኙ የሚችሉ በመሆኑ እኒህ የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን በየትኛው የደሞዝ ምጣኔ ይከፈላቸው፤ ክፍያውስ በብር ይሁን ወይስ በውጭ ሀገር ገንዘብ የሚለው ንትርኮችን አልፎም እስከ ፍርድ ቤት ክርክር የደረሰ አለመግባባትን አስከትሏል።

ባጠቃላይ በዲያስፖራው ዘንድ ያለው ተነሳሽነትም ሆነ የመንግስት የማሻሻያ እርምጃዎች በዲያስፖራው ዘንድ ያለውን ከፍተኛ የሰው ሀብት የከፍተኛ ትምህርት ዘርፉን ለመደገፍና ለማሳደግ እና ለማሻሻል መጠቀም የሚያስችል ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። ነገር ግን ይህ መልካም አጋጣም ከመቀዛቀዙ በፊት በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል ተቋማዊ ይዘት ያለው የህግ እና የአደረጃጀት እርምጃዎችን መውሰድን ይጠይቃል።

____
1 ፀሃፊው በቦስተን ኮሌጅ የአለም አቀፍ ከፍተኛ ትምህርት ጥናት ማእከል ውስጥ ተመራማሪ እና የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው ayenachew@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ

ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here