spot_img
Tuesday, November 28, 2023
Homeነፃ አስተያየትህገመንግስታዊ የጎሳ ጥላቻ ፖለቲካ፣ አገር እየፈረሰ ያለው ሰደድ እሳትና የዶ/ር ዐብይ...

ህገመንግስታዊ የጎሳ ጥላቻ ፖለቲካ፣ አገር እየፈረሰ ያለው ሰደድ እሳትና የዶ/ር ዐብይ ትዕግስት (ዶ/ር በድሉ ሙሉአለም)

advertisement

ዶ/ር በድሉ ሙሉአለም
ሰኔ 23፡ 2011 ዓ. ም

የባህርዳርና የአዲስ አበባ አሳዛኙ የመንግስት ሃላፊዎች ህይዎት መጥፋት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ የጎሳ ፖለቲካ ያመጣው ነው። በጎሳ ላይ የተመረኮዘው ህገ መንግሥት፣ የጎሳ ፖለቲካ አደረጃጀት ህዝቡን እርስበእርስ ሊያዋጋና ኢትዮጵያን ሊበታትን ተቃርቧል። ጥላቻ ብዙና የከፋ ጥላቻን እየወለደ፣ አገሪቱን እንደ ሰደድ እሳት እያዳረሰ ነው። የጎሳ ጥላቻ እንደሚያጎላ መስታዎት ነው። ያቀረቡለትንና የሰጡትን መልሶና አጉልቶ ያሳያል። አሁን በአገራች ሲሆን የምንሰማውና የምናየው የብዙ አሥርተ ዓመታት የጎሳ ጥላቻ ፖለቲካ ውጤት ነው።

አሁን ያለንበት አሳዛኝ ደረጃ እንዴት ደረስን?

ጀማሪዎቹ የጎሳ ፖለቲካ አራማጅ የሆኑት ህውሃትና ኦነግ በረጅም ጊዜ ትግላቸው በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ነፍጠኛ፣ ትምክተኛ፣ የሚሉትን አማርኛ ተናጋሪዉን የህብረተሰብ ክፍል፡ ለመጉዳት ዕቅድ አውጥተው፣ በማንፌስቷቸዉ አስፍረዉ፣ ተንቀሳቅሰዋል። ኢትዮጵያዊያን፣ በተለያየ የአገራችን ክፍል፣ በጎሳቸዉ የተነሳ የተፈፀሙባቸዉን ጥቃት፣ ግድያና መፈናቀል ማሰብ ለሚችል ሁሉ፡ የጎሳን ፖለቲካ ጠንቀኝነት ለማሳያት በቂ ትምህርት ይሆን ነበር። የጎሳ ጥላቻ ፖለቲካን አስከፊና አስፈሪ የሚያደርገው እንደ እንፍሌንዛ በቀላሉ ተላለፊ መሆኑ ነው። የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች ነገሮችን ሁሉ የሚያዩት በጎሳ መነፀር ብቻ ነው። ሁሉ ነገር ለእነርሱ ጎሳዊ ነው። የጎሳ ፖለቲከኞች “ድል” የሚያደርጉት ሌሎች ጎሰኞች ሲሆኑላቸው ነው። ምክናያታዊና አርቆ አስተዋይ ሰዎችን እንደማያሸንፉ ያዉቃሉ። ሌሎችም ደግሞ እንደእነረሱ የተንሸዋረረና እንደ ጋሪ ፈረስ ከአንድ አቅጣጫ ውጭ ማየት እንዳይችሉ ለማድረግ ይጥራሉ። መከለያቸዉም የጎሳ አመለካከት ነው። ለዚህም ሲባል ጎሰኝነትን ለማዛመት የመንግስት መዋቅርና የትምህርት ተቋማትን ሳይቀር ይጠቀማሉ። የጎሳ ጥላቻ ፖለቲካን ለማስፋፋት የተሰሩ ሁለት ሁነቶችን ለምሳሌ ልጥቀስ።

አንዱ ህውሃቶች ስልጣን እንደያዙ ኢህዲንን ወደ ብአዲን ሲቀየሩት የተፈጠረው ነው። ህውሃቶች ስልጣን ከያዙ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ፣ አሁን የአማራ ክልል የሚባለውን በወቅቱ ክልል ሶስት አካባቢ በዘር የተደራጀ አልነበረም፡፡ ይወክለዋል የተባለ የፖለቲካ ድርጅት አልነበረውም። በአገሪቱ ሁሉም ነገር የሚሰራዉ በህዉሃትና ኦነግ ነበር። በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ታምራት ላይኔ ባህርዳር በመገኘት ይህን ተናገሩ። ሌላው ሁሉ በብሄር ሲደራጅ፣ የአማራው ህዝብ ፓርቲ ስለሌለው ህብረብሔር ነው ተብሎ የሚጠራውን ኢህድንን የአማራው ህዝብ ድርጅት እንዲሆን ወስነናል በማለት ኢህዲንን ስሙን ወደ ብአዴን በመቀየር የጎሳ አደረጃጀትን ባልተቀበለዉ ክልል ሶስት ህዝብ ላይ ጫኑበት። ሳይወድ በግዱ እናንተ አማራ ናችሁ በማለት የዘር ፖለቲካ እንዲቀበሉ ብዙ የማደንዘዣ ቅስቀሳ ተደረገ። ከዚሁም ጋር ተያይዞ፣ የህዋሃትን ማንፌስቶ መሰረት በማድረግ፣ አማራ የሚባለውን ህዝብ ራሱን በራሱ ወንጀለኛ እንዲያደርግ፡ ገዢ መደብ፣ ነፍጠኛ፣ ትምክህተኛ የሚሉትን፡ ቅጽል እዲለጠፍበት፣ እንዲቀበልና የአጥፊነትና የወንጀለኝነት ስሜት እንዲሰፍርበትና እንዲሳቀቅ አደረጉት። በዚህም አማራዉ በሄደበት ሁሉ የጎሳ ፖለቲከኞች ጥቃት ኢላማ እንዲሆን፣ ከያለበት እንዲባረር እንዲፈናቀልና እንዲጠቃ አደረጉት። ይህም ቀስ በቀስ ስር የሰደደ ቁጭትን እየፈጠረ ሄደ።

ሁለተኛው ማሳያ እነጃዋር መሃመድና ጸጋየ አራርሳ የመሳሰሉ ለኢትዮጵያ አንድነት ጥላቻ ያላቸው ቀስቃሾች፣ ኦሮሞ በአጥንቱና በደሙ ኢትዮጵያን እንዳልገነባ፣ ኦሮሞ በኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ተይዟል፣ “ኢትዮጵያ ከኦሮምያ ትዉጣ”፣ ሰፋሪዎች፣ መጤ፣ “አንገታችሁን በሜጫ እንቆርጠዋለን” እያሉ በአደባባይ በየጊዜዉ የሚዝቱ፣ የዉሸትና የጥላቻ ታሪክ የሚያሰራጩ፣ አክራሪ ኦሮሞ ብሔርተኞችና አሸባሪወች፣ ሌሎች የአገሪቱን ማህበረሰብ በጎሳ ኢንዲደራጁና ከሌላው ጋር ያላቸዉን ግንኙነት እንዲያቋርጡ ያደረጉትን ጥረት ማየት ይገባል። አነዚህና መሰሎቻቸዉ በ OMN እና በማህበራዊ ሚዲያ በመጠቀም የሲዳማን፣ የወላይታን፣ የቅማንት፣ የከሚሴ ኦሮሞወችና ሌሎችንም በጎሳ ለማደራጀትና በሰላም አብረዉ ከኖሩት ህብረተስብ ለመነጠል፣ ለማዋጋትና የኢትዮጵያን አንድነት ለማዳከም ብዙ የተቀነባበረ ዘመቻ አድርገዋል። ብዙ መርዝ ረጭተዋል። በመንግስትም ላይ ብዙ ዉጥረት በመፍጠር አሉታዊ ተጸዕኖ እያደረሱ ነው። ወሎን ጨምረዉ የኦሮሞ ክልል ነዉ ብለዉ ካርታ ሰርተዉ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል። ኦነግ ወሎን ሰሜን ኦሮምያ ነው ብሎ ይፋዊ መግለጫ ሲያወጣ ዝም ብሎ እየታየ ነው። በቅርቡ፣ በከሚሴና አጣየ አካባቢ ሰዉን እንዳዋጉት፣ አሁንም በአማራና በቤንሻንጉል መካከል ጦርነት እንዲፈጠር እየሰሩና እየቀሰቀሱ ነው። የራሳቸዉን ዓላማ ለማሳካት፣ የተሸከሙትን በሽታ ለሌላ ማስተላለፍ፣ ሌሎችን በጎሳ መከፋፈልና ማዋጋት ከህዉሃት የተማሩትን ስልት በተግባር ላይ እያዋሉት ነው። ጃዋር አሁንም ይህን ሁሉንም እጂግ ያሳዘነ የባለስልጣኖች ግድያን እንደአጋጣሚ ተጠቅሞ፣ የመንግስት የቅርብ ሰዉና አማካሪ መስሎ በመቅረብ፣ የበለጠ ክፍፍልና ጥላቻዉን በአማራዉ ክልል ላይ ዘርቷል። መንግስትም ከዚህ ተደጋጋሚ ተግባሩ ሊይስቆመው አለመቻሉ አስገራሚ ነዉ። ይህም ተጨማሪ ቁጭትን በመፍጠር የበለጠ ጥፋትን እንዳያስከትል ይፈራል። ዘረኞችን በመፍጠር ግባችን ይሳካል ብለው በማሰብ፣ ቀደም ብሎ እነጃዋር አክራሪ የአማራ ድርጂትም አንዲፈጠር ድጋፍ ሰጪ መስለው አገሪቱን ይበልጥ በመከፋፈል ለምዳከም ሰርተዋል። በ OMN ብዙ ቀስቅሰዋል። የዘረኝነት መርዝ ለመርጨትና ሰዉን ለማፋጀት ከህዉሃት ቢበልጡ እንጂ አንሰዉ አልታዩም። ይህ በነጃዋርና ኦነግ የሚመራው እንቅስቃሴ፣ ህዝቡን እርስ በእርስ በማባላትና በማዳከም፣ ህዉሃትን መልሶ ወደ ስልጣ እንዲመጣ ዕድል እየሰጡ ነዉ።

የዘርኝነት በሽታ አምጪ ተዉሳክ፣ በወቅቱ ካልታከመና ከስሩ ካልተነቀለ፣ እየጠነከረና መድሃኒት የመቋቋም ሃይሉ እየጨመረ ከአንዱ ጎሳ ወደሌላው ይተላለፋል። የመጨረሻዎቹ የበሽታው ተጠቂዎች ይበልጥ የመረረ የተጠቂነት ስሜትና ጥላቻ ይኖራቸዋል። በይበልጥ ሰቆቃ የተፈጸመባቸው ሰዎች ተጨማሪ በደል የሚሸከሙበት ትዕግስቱ አይኖራቸዉም። የሚወስዱትም ርምጃ የከፋ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም የጎሳ ፖለቲካ መጨረሻዉ የእርስ በእርስ እልቂት ነው። ዛሬ በጎሳችን ብቻ በግፍ ተገድለናል፣ ሰቆቃ ተፈጽሞብናል፣ በገደል ተወርዉረናል፣ በቀስት እየተወጋን ተገድለናል፣ ልጆቻችን ተሰልበዋል፣ ከኖርንበት ቦታ በግፍ ተፈናቅለናል፣ እንደሁለተኛ ዜጋ ታይተናል፣ የሞትንላት አገራችን የመፍረስ አደጋ ላይ ናት፣ የመሳሰሉትን እንደምክንያት በማንሳት ምሬት ያዘሉ ወጣቶች በአገራችን እየበዙ መጥተዋል። በተጨማሪም የጎሳ ፖለቲካና የለዉጡ መሃንዲስ ነን የሚሉት እነ ጃዋርና ሜጫቸዉን አስይዘዉ ህዝብ እያሰለፉ፣ ኦነጎች ባንክ እየዘርፉ፣ ንጹሃንን ገድለዉ እያቃጠሉ፣ የመንግስት መዋቅር እያፈረሱ፣ የሚደረግላቸው የአገር መሪ ደረጃ አያያዝና፣ ለዚህም የዶ/ር አብይ መንግስት ያለዉ ትዕግስት፣ ብዙዎችን አስከፍቷል። ህዝቡ ለዶ/ር አብይና ለለውጡ መሪዎች ያለዉንም ድጋፍ በእጂጉ አውርዶታል። ብዙወች የደስታ እንባ እያነቡ የደገፉት ዜጎች ዛሬ የዶ/ር አብይን ተዓማኝነት መጠራጠር ጀምረዋል። እሾህን በእሾህ ነው በማለት፣ አንዳንድ ተጠቂወችም ይበልጥ ዘረኞች እየሆኑ ነው። ይህም ለዶ/ር ዐብይ መንግስትና ለኢትዮጵያ አንድነት ዋናዉ ፈተና ሆኗል።

የኢትዮጵያ የጎሳ ፖለቲካ ችግር፣ የዘረኞችን ባህሪ ለመቀየር በሚደረግ ንግግር ብቻ አይፈታም። ችግሩ ህገመንግስታዊ፣ መዋቅራዊ፣ ተቋማዊና ስርዓታዊ ነው። ይህ ደግሞ የሚፈታው ህግን፣ መዋቅርንና፣ ስርዓትን በማስተካከል ወይም በመለወጥ ነው። መጀመሪያ ይህን ሃቅ በግልጽ መቀበልና ስምምነት ላይ መድረስ ያስፈልጋል። የችግሩ ምንጭ ላይ ያተኮረ መፍትሄ ያስፈልጋል። ዘረኞችን አንስቶ በሌላ ዘረኞች መተካትም መፍትሄ አይሆንም። ቀደም ሲል ዘረኞች በደል የሚያደርሱት ወይም የሚበቀሉት የተጠቂነት ታሪክ በመጥቀስና መብታችን ተረግጧል በማለት ነበር። አሁን አሁን ደግሞ ዶ/ር ዐብይ ስልጣን ከያዙና የህዉሃት አፈናዉና ግድያዉ ሲቀር፣ ለዘረኝነታቸው የሚጠቅሱት ምክንያት ህገ መንግስቱ ይፈቅድልናል፣ “ህገመንግስቱ ይከበር”፣ ክልሉ የኛ ብቻ መኖሪያ ነው፣ ሌላዉ ይዉጣልን፣ ሌሎች ወደኛ እንዳይመጡ በማለት ነው ።

ስለዚህ መፍትሔው መሆን ያለበት ዘረኛዉን ህገመንግስት መቀየር፣ መዋቅሩን ማስተካከል፣ ተገቢ ተቋማትን ማቋቋምና በተጨማሪም ህዝቡን ወደ ልቦናዉ አንዲመለስና ምክንያታዊ እንዲሆን የውይይት መድረክ በመፍጠር ነው። ይህ እስካልሆነ ድረስ ጥፋቱ ይቀጥላል፣ ኢትዮጵያም አደጋ ላይ ናት። የዉጭ ጠላትም ይህን አጋጣሚ እየተጠቀሙ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ይሰራሉ። ለዚህም ጣልቃገብነት ፍንጭ እየታየ ነው። የጎሳ ቡድን በማጠናከር፣ ትጥቅ በማብዛት ወይንም የክልል ሚሊሻ በመፍጠር ዘላቂ መፍትሄ አይመጣም። ዶ/ር ዐብይ፣ ያላቸዉን ህጋዊና ወታደራዊ ሃይል፣ አስፈላጊም ከሆነ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጨምሮ፣ በመጠቀም፣ በግልጽነት፣ ያለምንም አድሎ በመስራትና የኢትዮጵያን ጥቅም በማስቀደም፣ ከዚህ ስጋትና ጭንቀት ሊያወጡን ይገባል። ህዝቡም ለራሱና ለመጭዉ ትውልድ ዘላቂ ጥቅም ሲል ሊተባበራቸውና ሊረዳቸዉ ይገባል። ካልሆነ የሚተርፉት እንደነጃዋር ያሉት የዉጭ አገር ፓስፖርት ይዘው፣ መርዝ የሚረጩትና ልጆቻቸዉንና ሃብታቸዉን አሽሽተው የሚጠባበቁት የመንግስት ባላስልጣናትና አንዳንድ ሃብታሞች ናቸው። በመሳሪያ ሃይል አይዳንም። የሩዋንዳን እልቂት እናሳትዉስ። ይህ የተፈጸመዉ የባለስልጣናት ግድያ እንደትምህርት ሆኖን ራሳችንንና አስተሳሰባችንን በእርጋታ በመመርመር አገርና ህዝብ እዳይጠፉ መፍትሄ እንፈልግ። ችግሩን የተለያየ ስም መስጠቱ ወይንም በቃላት መጫዋቱ መፍትሄ አይሆንም። ችግሩን እያወቅን ያስመሳይ ስራ አንስራ። ይህን ችግር አያወቁ በጎሳ ፖለቲካ እናተርፋለን ብለው የተሰለፉ፣ ጥላቻንና ሃሳትን የሚዘሩ ሁሉ ኢትዮጵያን ወደ ጥፋት እየወሳዷት ነው። የጎሳ ፖለቲካ እያጠፋን ነው። የባለስልጣኑ ግድያ የማስጠንቀቂያ ደወል ይሁነን። ራሳችንን አናጥፋ። ኢትዮጵያዊያን እንንቃ። ከመሪዎች ብቻ አንጠብቅ። የዜግነት ድርሻችንን በምንችለው መንገድ ሁሉ እንወጣ።

___
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here