ከአማራ ህዝብ ጎን እንቆማለን!
በአማራው ህዝብ ላይ የተፈጸመው ወረራ ግድያና እስራትን አጥብቀን እናወጋዛለን!
የኢትዮጵያ ህዝብ ለለፉት 28 አመታት ያካሄደው ትግል ለነጻነቱ ለመበቱና ለህልውናው እንቅፋትና ጠንቅ የሆነውን የወያኔን የጎሳ ስርአት የማስወገድ እንጂ የህዘባችንን ሰቆቃ የሚያራዝም፣ አንዱን አጥፊ ጎሳ በሌላ አጥፊ ጎሳ ለመተካት አልነበረም። የህዝባችን ትግል ለኢትዮጵያ ህዝብ ደህንነትና አንድነት፣ ለፍትህና ርትእ፣ ለሰብአዊ መብት፣ ለአገራዊ ህልውና እና ብሔራዊ ሉዓላዊነትን ለማስከበር ነበር። ይህ የነጻነት ትግል በዶ/ር አብይና ግብረ አበሮቹ በረቀቀና የህዝብን ንጹህ ቅንነትና ኢትዮጵያዊ ፍቅሩን በማታለያነት በመጠቀም፣ ህዝብ ባላሰበበትና ባልጠረጠበት መንገድ ህዝባዊ ትግሉ እንዲቀለበሰ ሆነ። ዛሬ ለበዙ ዓመታት ያለሙትን የአማራ ማህበረሰብን የማዳከምና የማጥፋት ተግባር በተደራጀና በተቀነባበረ መንገድ ለማካሄድ ዘረፈ ብዙ ጦርነት ተክፍቶበታል። የአገራችንን ሕልውናና የሕዝቧን አንድነት ከምንጊዜውም የበለጠ ስጋት ላይ አድርሶታል። የአማራ ህዝብ ለኢትዮጵያ አገሩ ታማኝነትንና ጀግንነትን ስለ አበረከተ፣ ማንነቴ ኢትዮጵያዊነቴ በማለቱ፣ ኢትዮጵያዊ አብሮነትን በመውደዱ፣ አንድነትና ፍቅርን በመምረጡ፣ጽንፋዊ ልዩነትን፣ የሀሰት ትርክትና ጥላቻን ባነገቡ ጎሰኞች በጠላትነት ተፈርጆ ለጥቃት እንዲዳረግ ሆኖል። የሰሞኑ በባህዳር ከተማ በአማራ ህዝብ መሪዎች ላይ የተፈጸመው ግድያና ጭፍጨፋ የዚሁ የጥቃት ተቀጥያ አንድ ሌላ ገጽታ ነው።
ዛሬ ለሚገደሉትና ለሚሰቃዩት ወገኖቻችን ማዘን ብቻ ሳይሆን፣ ትግላቸውና የፈሰሰው ደማቸው ከንቱ እንዳይሆን፣ለአማራው ህዝብ ህልውናና ደህንነት እንዲሁም ለኢትዮጵያ ትንሳኤ መንፈሳዊ የኃይል ምንጭ ይሆን ዘንድ የጀግኖቻችንን አላማ ህያው ማድረግ ይጠበቅብናል። ስለዚህ በአማራው ማህበረ ሰብ ላይ የሚካሄደው በደልና ጥቃት በሁሉም ኢትዮጵያዊ ላይ የተሰነዘረ ጥቃት መሆኑን በመገንዘብ፣ በአንድ ድምጽ ድርጊቱን ማውገዝና ማስቆም ወቅቱ የሚጠይቀው የጋራ ሃላፊነት ነው። ይህ የጥፋት ሂደት በአፋጣኝ ካልተገታ ግን ለትውልድ የሚተላለፍ ልዩ ማህበራዊ ቀውስ ከፊታችን ተደቅኖ የሚጠብቀን መራራ ሃቅ ይሆናል። ስለዚህም ህዝባችንን ለበለጠ እልቂትና የእርስ በርስ ግጭት ሊጋለጥ እንደሚችል በአፅንኦት ማስተዋልና ይህም ሁኔታ እንዳይከሰት በወቅቱ በስልት፣ በጥበብና በጀግንነት አሰፈላጊውን ሁሉ ማድረግ ተገቢ ነው እንላለን።
ስለዚህ የአማራ ህዝብም ከሌሎች ኢትዮጵውያን ወገኖቹ ጋር በመተባበር የኦነግ/ወያኔን አላማ የሚያራምደው የዶ/ር አብይ ሃሳዊ የጎሳ አስተዳደርን አስወግዶ ኢትዮጵያዊ ህገ መንግስትን መሰረት ያደረገ ህዝብን በአንድነት በእኩልነት የሚያስተዳድር ኢትዮጵያዊ መንግስት መመስረት አገርንና ህዝብን ከጥፋት ያድናል፣ ዘለቄታዊ መፍትሄም ነው ብለን እናስባለን። ይህ አገራዊ የነጻነት መፍትሄ እውን የሚሆነውም ዛሬ በተቀነባበረ መንገድ የኢትዮጵያ ጠላቶች፣ በዶ/ር አብይና ግብረ አበሮቹ መሪነት በአማራ ህዝብ ላይ የሚያደርሱትን ጉዳትና ያወጁትን ጦርነት በአግባቡ ስንታደግ ብቻ ነው።
ይህንንም በመገንዘብ በዚህ ፈታኝ ታሪካዊ ወቅት እኛ፣ በተለያየ አህጉር፣ የምንገኝ፣ የሰብዊ መብት ተቆርቋሪ፣ አገር ወዳድ ፖለቲካ አራማጆች እና፣ ምሁራን ኢትዮጵያውያን ሴቶች፣ ለጥቃት ኢላማ ለተደረገው ለአማራ ህዝብ፣ በተለይ ለሴቶችና ለልጆች ድምጽ ለመሆንና በሚያስፈልገው ሁሉ ለመርዳት ይህንን ትብብር መሰርተን ተነስተናል። በዚህም መሰረት፣
በተራ የማጨበርበሪያ ሽፋን በባህርዳር ከተማ በአማራ አስተዳደር መሪዎች በዶ/ር አምባቸው መኮነን፣ ጄነራል አሳምነው ጽጌ እና ሌሎች የአስተዳደሩ አመራሮች እንዲሁም በአዲስ አበባ በጄነራል ሰአረ መኮነን እና በጄነራል ገዛኢ፣የተፈጸመውን ግድያ በጥብቅ እናወግዛለን፣ትክክለኛና ገለለተኛ ምርመራ እንዲደረግ እንጠይቃለን።
መንግስት ሙሉ በሙሉ በሚቆጣጠረው ሚዲያና በመደመር ስም ከአጥፊው ጋር በተሰለፉ አጋር ሚዲያ በመታገዝ የሚሰራጨው “መንግስት ፍንቀላ” በሚል የሃሰት ትርክት ህዝብን የመወንጀልና በአንድ የአማራ ህዝብ መካከል ልዩነትን ለመፍጠር የሚያሰራጨውን መርዘኛ ቅስቀሳ በአስቸኳይ እንዲቆም፤ ህዝብን ለማደናገር በጀግናው ጄነራል አሳምነው ጽጌ ላይ ከሚካሄደው መሰረት ቢስ ፕሮፖጋንዳ እንዲቆጠብ እንጠይቃለን። በተጨማሪም የውጭ ሃይሎች፣ሚዲያዎች፣ መንግስታት ሆኑ ግለሰቦች፣ ለምሳሌ እንደ ሀርማን ኮሀን አይነት ግለሰብ፣ ይህን ሃላፊነት የጎደለውን ጸረ አማራ የሃሰት ትርክትና የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ ከማስትጋባት እንዲያቆጠቡ አጥብቀን እናሳሰባለን።
አማራን ህዝብ ለመከፋፋልና አስተዳደራዊ መዋቅሩን ለማዳከምና ለመቆጣጠር በአካባቢው የተሰማሩት ጥቅሙን የማያስጠብቁ የፈደራል ልዩ ወታደራዊ ሃይል ከግድያና ከማሰር ተቆጥቦ በአስቸኮይ አካባቢውን ለቆ እንዲወጣ፣ ህዝቡን፣ ማሳደድ፣ ማዋከብ፣ ማሰር እንዲያቆምና በግፍ የታፈኑና በጅምላ የታሰሩት ንፁሀን ዜጎች፣ የአብንና የባለአደራ መሪዎችና አባላት፣ የአስራት ሚዲያ ባልደረቦች ሁሉ በአስቸኳይ እንዲፈቱ እንጠይቃለን።
እንዲሁም በቅርቡ ዶ/ር አብይ ለምክር ቤት ባደረገው ሀሰትና ዘለፋ የተሞላበት ንግግር ህዝብን በማሸበርና በማስፈራራት በጠመንጃ ሃይል እየገደለና እያሰረ እንደሚጋዛ ገልጾል፣ ይህንንም አምባገነናዊ የወንጀል ሂደት ተግባር አጥብቀን እናወግዛለን። ህዝብን በማሸበር ለሚደረሰው የአእምሮና የአካል ጉዳት፣ጥፋትና ሞት መንግስትንና ተባባሬዎቹን ተጣያቂ እናደርጋለን።
የወገኖቻችን የሰማዕታት ደም በከንቱ ፈሶ የማይቀር መሆኑን እያረጋገጥን የበለጠ ተጠናክረን ለዚህ ሰቆቃ የዳረገንን በዶ/ር አብይ የሚመራው ጸረ ኢትዮጵያ፣ ጸረ አማራ፣ የኦነግ/ወያኔ የጎሳ የፖለቲካ ስርአትን ማስወግድ የማንኛውም ህሊና ያለው አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሊያስተውለው የሚገባ ወሳኝ ወቅታዊ ቁልፍ ጉዳይ ነው ብለን እናማናለን።
የዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ የሴቶች ትብብር ለአማራ፣ በዶ/ር አብይ መሪነት በአማራው ህዝብ ላይ የሚፈጸመውን ማንኛውን አይነት ጥቃት አጥብቀን እያወገዝንና የተቃጣውንም የጥፋት ዘመቻ ለማስቆም ማንኛውንም ሰላማዊና ህጋዊ መንገድ በመጠቀም አስፈላጊውን ትብብር ለማድረግ ተነስተናል። ትብብሩ በዋናነት የአማራው ህዝብ በአሁኑ ወቅት ከሚደርስበት ልዩ ልዩ ችግሮችን ለመወጣት አስፍላጊውን ድጋፍ ለማደረግ በሚከተሉት ልዩ ልዩ ተግባሮች ላይ ያተኩራል:
ድህነት በስፋት የሰፈነበትን የአማራ ማህበረ ሰብ ለማጠናከር የቁሳቁስና የገንዘብ (ምግብና መድሃኒት) የመሳሰሉትን እርዳታዎች በማሰባሰብ፣ በአለም ዙሪያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለአማራው ማህበረሰብ አቅሙን እንዲገነባና መሰረታዊ የእለት ኑሮ መደገፊያ እርዳታ እንዲያደርጉ ማስተባበር፣
በአማራው ህዝብ ላይ የሚፈጸመውን ኢሰብአዊ ተግባር፣ እልቂትና የዘር ማጥፋት ወንጀል ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ ማሳወቅና አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ ለመወሰድ፣ ዲፕሎማሲያዊና ህጋዊ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ኢትዮጵያውያን በዶ/ር አብይ ኦነግ/ወያኔ የኢኮኖሚና የዲፕሎማሲ ጥቅሞች ላይ ማእቀብ እንዲደረግ ማደረግ፣
ሴቶች የህብረተሰቡ ዋና አካል እንደመሆናቸው ሁሉ በአገራችን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚ ጉዳይ ውስጥ ወሳኝ ሚና ካልተጫወቱ የአገርም ሆነ የህዝብ ነጻነት አይኖሩምና ሴቶችን ለይስሙላ ሳይሆን በእውነት ሙሉ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ፣ በተጨማሪም የሴቶች ጥያቄ የአገርና የሰብዓዊ መብት ጥያቄ አካል መሆኑን ማስገንዘብና በሴትነታቸው ምክንያት የሚደርሰባቸውን ጉዳት ለማስወገድ፣ መብታቸውን ለማስጠበቅ ማደራጀት ማጠናከር፣
በተለይም በግጭት ወቅት የመከራ ገፈት ቀማሽ ሴቶችና ልጆች በመሆናቸው አስፈላጊውን እርዳታ ሁሉ እንዲያገኙ ማድረግ አጣዳፊ ማህበራዊ ግዴታችን ነው። ባለፈው አንድ አመት በሚሊዮን የሚቆጠሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን በገዛ አገራቸው ተሰደዋል፣ ተፈናቅውል፣ ተግድለዋል። በቡራዮ፣በጌድዮን፣በሶማሌ፣ በሀረር፣ በአጣየ፣በአዲስ አበባ፣ ወዘተ ነፈሰ ጡሮችና ህጻናት ቤታቸው በላያቸው ላይ ፈርሶ መንገድ ላይ ወድቀዋል፣ በርካታ ሴቶች ተደፍረዋል፣ ጭካኔ ለተሞላበ ጥቃትና ሞት ተጋልጠዋል። ይህን አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳት ለመወጣት አስፈላጊውን ሁሉ እንድናደርግ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የትብብር ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፣ ከአማራ ህዝብ ጎን በመቆም ኢትዮጵያን እናድን።
ኢትዮጵያ በቆራጥ ልጆቿ ጀግንነት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኖራለች!!
አለም አቀፍ የኢትዮጵያ ሴቶች ትብብር ለአማራ
አስተባባሪ ኮሚቴ
ሰኔ 2011