spot_img
Wednesday, May 29, 2024
Homeነፃ አስተያየትየደቡብ ኢትዮጵያ ፖለቲካ እንቆቅልሽ እንዴት ይፈታ? (በቦጋለ ታከለ)

የደቡብ ኢትዮጵያ ፖለቲካ እንቆቅልሽ እንዴት ይፈታ? (በቦጋለ ታከለ)

(በቦጋለ ታከለ)
ነሃሴ 3 2011 ዓ ም

በሲዳማ ልሂቃን የተጀመረው የክልል እንሁን ጥያቄ ዘጠኝ ሌሎች ክልሎችን አስከትሎ በመምጣት የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዘቦች ክልል በመባል የሚታወቀውን ክልል የፖለቲካ ሙቀት ውስጥ ከቶታል፡፡ክልል ጠያቂዎቹ የሲዳማ ልሂቃን የክልሉን ዋና ከተማ አዋሳን ይዞ ክልል ከመመስረት ውጭ ሌላ ነገር መስማት የማይፈልጉ መሆናቸው ደግሞ ነገሩ አወሳስቦታል፡፡የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ከዞን ጀምሮ ወደ ክልል ምርቤት  በሚያዘግምበት ጊዜ የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ህገመንግስታዊ ቢሆንም ክልል ጠያቂዎቹ የሲዳማ ፖለቲከኞች የአዋሳ ከተማን እጣ ፋንታ በጥያቄያቸው ውስጥ እንዴት እንደሚመለከቱት በጥብቅ መጣራት ነበረበት፡፡ ይህ አልሆነም፡፡ የሲዳማ ዞን ምክርቤት በሙሉ ድምፅ አፀደቅኩት ያለውን የክልልነት ጥያቄ ወደ ክልሉ ምክርቤት ይዞ ሲመጣ የክልሉ ምክርቤት የክልሉ ብሄረሰብ ሁሉ ያለማት አዋሳ ጉዳይ ጥርት ባለ መንገድ እንዲቀርብለት ጠይቆ ጉዳዩን ለማብራሪያ ወደ ዞኑ መመለስ ነበረበት፡፡ 

የአዋሳ ነገር ሾላ በድፍን በሆነበት ሁኔታ የክልሉ ምክርቤት ጉዳዩን ወደ ምርጫ ቦርድ መግፋቱ ትልቅ ስህተት ከመሆኑም ባሻገር ምርጫ ቦርድን ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ጭምር ውሳኔ እንዲሰጥ የማስገደድ አጣብቂኝ ውስጥ ከቶታል፡፡የክልሉ ምክርቤት የአዋሳን ነገር እንዲህ እንደዋዛ በተድበሰበሰ ሁኔታ ወደ ምርጫቦርድ ያሳለፈበተት አጉል መዘናጋት አሁን ክልሉን የሚመራውን ደኢህዴንን ዋጋ እያስከፈለው ይገኛል – በኤጄቶ ጎረምሳ እስከመደብደብ ያደረሰውም ይሄው መዘናጋቱ ነው፡፡ 

የደቡብ ክልል ምክርቤት በወቅቱ እልህ በሚመስል ሁኔታ ተሯሩጦ አዋሳን ጨምሮ ክልል ለመሆን የሚጠየቀውን ልክ ያልሆነ ጥያቄ ጭምር አግበስብሶ ወደ ምርጫ ቦርድ ከማስተላለፉ በፊት  የአዋሳ ከተማ ነገር ተብራርቶ እንዲቀርብለት ቢጠይቅ ኖሮ የሲዳማ ልሂቃን አዋሳን ጨምረው ወስደው ክልል መመስረት እንደሚፈልጉ ግልፅ ማድረጋቸው አይቀርም ነበር፡፡ይሄን ጊዜ የክልል ምክርቤቱ የሲዳማን ክልል የመሆን ህገመንግስታዊ መብት እያከበረ ነገር ግን የአዋሳን ጉዳይ በተመለከ በቀረበው ጉዳይ ላይ እንደማይስማማ አስረግጦ መከራከርና አዋሳን ሸጉጦ የተነሳውን ልክ ያልሆነ ጥያቄ በአብላጫ ድምፅ ውድቅ ማድረግ ሁሉ ይችል ነበር፡፡

ሁለተኛው አማራጭ የክልሉ ምክርቤት መነጋገር የሚችለው የሲዳማ ክልል ከአዋሳ ውጭ ባሉት ከተሞች ዋና ከተማውን አድርጎ መመስረት ይችላል አይችልም በሚለው ጉዳይ ላይ ብቻ መሆኑን አስረግጦ አሳውቆ ጥርት ባለው፣ህገ-መግስቱም በሚደግፈው የሲዳማ የክልልነት  ጥያቄ ላይ ብቻ ተወያይቶ ውሳኔውን ወደ ምርጫ ቦርድ ማስተላለፍ ነበር፡፡ይህ ህጋዊም ተገቢም አካሄድ ነው፡፡ 

ምክንያቱም አዋሳ ከተማ በሲዳማ ዞን ውስጥ ያለች ከተማ አይደለችም፡፡ ስለዚህ ሲዳማ ክልል ይሁን የሚለው ጥያቄ የሚያመለክተው የሲዳማ ዞን የተባለውን የግዛት ወሰን  የሲዳማ ክልል ብሎ ከዞን ወደ ክልል የማሳደግን ጥያቄ ነው፡፡ በዚህ ግዛት ውስጥ ደግሞ አዋሳ የለችም!አዋሳ በራሷ ከተማ አስተዳደር የምትተዳደር እንደሆነች እና ከሲዳማ ዞን የተነጠለች እንደሆነች የሲዳማ ልሂቃን ቁጭ ባሉበት በክልሉ ምክርቤት በ1995 በወጣ አዋጅ ተደንግጓል፡፡

ሆኖም አዋሳ ከተማ  በሲዳማ ክልል ውስጥ የምትገኝ ከተማ ባልሆነችበት ሁኔታ የዞኑ መቀመጫ እንድትሆን ተርጓል፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ በደቡብ ክልልም ሆነ በአአዋሳ ከተማ አስተዳደር የሲዳማ ልሂቃን ተፅዕኖ ከፍ ያለ በመሆኑ ነው፡፡ይህ ለምን ሆነ የሚለውን ከመለስ ዜናዊ ውጭ የሚያውቅ የለም፡፡ሊሆን የሚችለው ግን ከተሞችን በዙሪያቸው ባሉ ብሄረሰቦች የገጠር ልሂቃን እጅ የመጣል ኢህአዴጋዊ የፖለቲካ ዘይቤ ምክንያት ነው፡፡ ይህ ራሱ የሚነሳው ደግሞ የቆምኩት ለገጠሩ ህዝብ ነው ከሚለው በዘረኝነት ላይ የቆመው የኢህአዴግ የፖለቲካ ዘይቤ ነው፡፡ 

የሲዳማ ፖለቲከኞች አዋሳን ማዕከል ያላደረገች የሲዳማ ዞን በህልማቸውም አስበዋት ስለማያውቁ የክልሉ ምክርቤት የአዋሳን ነገር በተለይ በ1995 ከወጣው አዋሳን ከሲዳማ ዞን ለይቶ የራሷ አስተዳደር ያላት ከተማ መሆኗን ጠቅሶ አጥብቆ ቢከራከር  ኖሮ ጥያቄውን በአጭሩ ማስቆም ይቻል ነበር፡፡

አሁን ማድረግ የሚቻለው አንደኛ አማራጭ ሪፈረንደም አስፈፅማለሁ የሚለው ምርጫ ቦርድ እና የክልሉ ምክርቤት የአዋሳ ከተማ በክልሉ ህገመንግስት የደቡብ ክልል ዋና ከተማ መሆኗን እና ይህችን ከተማ ለሲዳማ ዞን በመስጠቱ ዙሪያ የክልሉ ህዝብ እና ስብጥሩ የአዋሳ ከተማ ህዝብ  ድምፅ የሚሰማበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው፡፡ የሲዳማ ዞን ህዝብ ክልል ለመሆን ሪፈረንደም እንዲያደርግ መብት ሲሰጠው የአዋሳ ህዝብም ወደ ሲዳማ ክልልል ወይስ ወደተቀረው የደቡብ ክልል መካለል እንደሚፈልግ ሪፈረንደም የማድረግ መብት ሊሰጠው ይገባል፡፡ በሁለተኛ አማራጭነት የተቀረው የደቡብ ክልል ህዝብም አዋሳን መዲናው አድርጎ በደቡብ ክልል ውስጥ መቀጠል ነው ወይስ በየቋንቋው ክልል መመስረትን ነው የሚሻው የሚለው ነገርም ለመላው የደቡብ ህዝብ በአማራጭነት ቀርቦለት በሪፈረንደም መወሰን አለበት፡፡ 

ሶስተኛው አማራጭ የደቡብ ክልል ህዝቦች በየቋንቋቸው ክልል የመመስረት ፍላጎት እንዳላቸው በሪፈረንደም ካሳወቁ የአዋሳ ህዝብ በፌደራል መንግስት ስር የሚተዳደር የፌደራል ከተማ ወይም ከደቡብ ክልል በአንዱ (ምናልባትም በሲዳማ ክልል) ውስጥ ለመግባት እንዲመርጥ ለክልሉ ህዝቦች ሁሉ የተሰጠው ሪፈረንደም የማድረግ መብት ሊሰጠው ይገባል፡፡

ከላይ የተጠቀሱት አማራጮች ሊሆኑ የሚችሉት መቼ ነው ብሎ መጠየቅ እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ እንደሚታወቀው የሲዳማ ልሂቃን መላው የደቡብ ህዝብ የደከመባትን አዋሳን ጨምሮ በመውሰድ ክልል የመመስረት ጥድፊያቸው 11/11/11 በሚል ቀመር ታጅቦ የማዕከላዊውን መንግስት፣የደቡብ ክልልን የሚመራውን ደኢህዴንን እና የምርጫ ቦርድን ፋታ ነስቶ፤ከሲዳማ የማይወለደውን በአዋሳ እና በሲዳማ ዞን የሚኖር ህዝብ በህይወት ጭምር የሚተመን ከባድ ዋጋ ሲያስከፍል ከርሟል፡፡ 

የሲዳማ ልሂቃን በሪፈረንደም ክልል የመሆን መብታችን ይከበርልን ሲሉ ለሚያነሱ ጥያቄ ይህንን የማስፈፀም ስልጣን የተሰጠው የምርጫ ቦርድ ነው፡፡ ሆኖም ምርጫ ቦርዱ አሁን ባለበት የሰው ሃይል እና ድርጅታዊ ቁመና የሲዳማ ልሂቃን 11/11/11 ሲሉ ባስቀመጡት የጊዜ ገደብ ውስጠጥ ይህን ማስፈፀም እንደሚቸገር ሲገልፅ ከርሟል፡፡ 

ከምርጫ ቦርድ ጎን ለጎን ሪፈረንደሙን በማስፈፀሙ እና አዲሱን ክልል በማቋቋሙ ረገድ ባለ ሙሉ ስልጣን የሆነው በደኢህዴን የሚመራው የደቡብ ክልል ምክር ቤት ነው፡፡ይህ ምክርቤት ደግሞ በክልሉ የተነሱ የእርስበርስ ግጭቶችን እና መፈናቀሎችን (መስቃን እና ማረቆ፣ከፋ እና ከምባታ፣ጋሞ እና ጎፋ፣ጌዲኦ እና ጉጅ፣ጉራጌ እና ቀቤና) በማቀዛቀዝ እና በሃገሪቱ የታየውን ለውጥ እንዳይቀለበስ በማርጋቱ አጣዳፊ ስራ ላይ በተወጠረበት ሁኔታ የሲዳማ ልሂቃ ባስቀመጡት የ11/11/11 የጊዜ ወሰን የሲዳማ ክልልነትን ጉዳይ እልባት መስጠት አይችልም፡፡ 

ህገ-መንግስቱ ብሄረሰቦች ክልል የመሆን መብት እንዳላቸው ሲደነግግ እንደምርጫ ቦርድ እና የክልል ምክርቤቶች ባሉበት ተቋማዊ ቁመና ይህን ማድረግ ሲችሉ፣ከሁሉም በላይ ሃገሪቱ ህልውናዋን አደጋ ላይ በማይጥል የፖለቲካ መረጋጋት ውስጥ ስትሆን ነው፡፡ይህ ባልሆነበት ሁኔታ የክልል ጥያቄ ዕለቱኑ ካልተመለሰ ብሎ የሲዳማ ልሂቃን እና ጎረምሶች እንዳደረጉት ያለ የሰው ህይወት እና ንብረት የሚያጠፋ ብጥብጥ ውስጥ መግባት  የሃገሪቱን ፌደራሊዝም ህልውና አደጋ ላይ መጣል ነው፡፡ ስለዚህ በአንቀፅ 48 የተሰጠው ክልል የመሆን ህገመንግስትዊ መብት የሚከበረው ሃገር ስትኖር መሆኑ መረሳት የለበትም፡፡ 

የሲዳማ ልሂቃን ጥያቄ የሃገሪቱን ፌደራላዊ ስርዓት አደጋ ላይ የሚጥለው እንዴት ነው የሚለውን ወሳኝ ጥያቄ ማንሳት አስፈላጊ ነውና ወደዛ ልለፍ፡፡የሲዳማ ልሂቃን አዋሳን ይዘን ክልል እንመሰርታለን ሲሉ በሚመጣው ምርጫ የሚወከሉበት፣ “ክልል አሁኑኑ” የሚሉትን የተጣደፈ ጥያቄያቸውንም የሚያስተናብር “ሲዓን” የሚባል በምርጫ ቦርድ የተመዘገበ ፓርቲ ስላላቸው በመጭው ሃገራዊ ምርጫ ሊወከሉ ይችሉ ይሆናል፡፡ በአንፃሩ እነሱ አሳዋን ይዘን ክልል እንመሰርታለን ሲሉ የለፋባትን አዋሳ ከተማን በቀን በብርሃን መዘረፉ ያስቆጣው ሌላው የደቡብ ክልል ዞን የራሱን ክልል መመስረት እንደሚፈልግ ቁጣ ወለድ ጥያቄውን እያሰማ ይገኛል፡፡ የሃገሪቱን ፌደራላዊ ስርዓት አደጋ ላይ የሚጥለው ችግር የሚመጣው እዚህ ላይ ነው፡፡ 

ከሲዳማ ክልል በተጨማሪ ክልል ለመሆን የጠየቁ ዘጠኝ የደቡብ ክልል ዞኖች ክልል የሚሆኑት ከሃገራዊ ምርጫ በፊት ነው፡፡ ምክንያቱም ጥያቄያቸው ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ በደቡብ ክልል ምክርቤት ታፍኖ ቢያዝም ጥያቄያቸውን ከዞናቸው ወደ ክልል ምክርቤት የላኩበት ቀን ቆጥረው እነሱም የሲዳማ ልሂቃን እንዳደረጉት  የፌደራል መንግስትን እና የምርጫ ቦርድን ይሁንታ ሳንጠብቅ የራሳችንን ክልል እንመሰርታለን ብለው ሊነሱ ይችላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ የሚፈጠረው ትርምስ በደኢህዴን እውቀት እና ጉልበት ይፈታል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ 

ተዓምር ተፈጥሮ ክልል ጠያቂዎቹ የደቡብ ዞኖች ክልል መሆን ቢችሉ በመጭው ሃገራዊ ምርጫ የሚወከሉበት ፓርቲ የላቸውም፤ደኢህዴንንም አንፈልግም ብለው ነው ክልል መመስረት የተመኙት፡፡

በዚህ መሃል እነዚህ ህዝቦች በሃገራዊ ምርጫ የሚወከል የህዝብ ተወካይም ሆነ ክልሎቻቸውን የሚያስተዳድር ህጋዊ ፓርቲ ላይኖራቸው ነው፡፡በውል የማይታወቅ አታጋይ ፓርቲ አላቸው ከተባለም ይህ ፓርቲ በምርጫ ቦርድ ተመዝግቦ በተቃረበው ሃገራዊ ምርጫ ለመወዳደር ህጉ የሚጠይቀው በቂ ጊዜ አይኖረውም፡፡ በዚህ መሃል የአስተዳደር እና የስልጣን ክፍተት በመፈጠሩ የዞኖቹ ህዝቦች ህልውናም ሆነ የአጠቃላይ የፌደራል ስርዓቱ ህልውና አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ስለዚህ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጠያቂ ልሂቃን ጉዳይ የሚያዝበት መንገድ እጅግ በጥንቃቄ የተሞላ መሆን አለበት፡፡ 

ይህ ካልሆነ አደጋው ብዙ ነው፡፡የመጀመሪያው አደጋ ደኢህዴን በደቡብ ክልል የተነሱትን ጥያቄዎች በተመለከ ያሳያል የሚባለው ወጥ ያልሆነ አቋም ነው፡፡ባለፈው የድርጅቱ ጉባኤ የተሳተፉ የአይን እማኞች እንደሚናገሩት ደኢህዴን የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ በሪፈረንደም ለመፍታት እና የሌሎችን ዞኖች ተመሳሳይ ጥያቄ በጥናት እፈታለሁ ሲል በግልፅ በጉባኤው ላይ እንዳስቀመጠ ነው፡፡ደኢህዴን ይህን ሊያደርግ እንደሚችል ጥርጣሬ ላይ የሚጥለው ተጨማሪ መረጃ ፓርቲው የሲዳማን ጥያቄ እስከ ምርጫ ቦርድ እንዲደርስ አድርጎ ሲያበቃ የሌሎችን ዞኖች ጥያቄ ከክልል ምክርቤት ማሳለፍ አለመቻሉ ነው፡፡ ይህ ልክ ያልሆነ አካሄድ ክልል ጠያቂዎችን ዞኖች ቁጣውስጥ ከትቶ የደቡብ ክልል ዞኖች በአመፅ ሲታመሱ እንዲከርሙ አድርጓል፡፡ ደኢህዴን ነገሩን መፍታት ካለበት ሁሉንም በአንድ አይን አይቶ እንጅ ይበልጥ ለረበሸ የበለጠ ጥቅም የሚያስገኝ የፈሪ ውሳኔ መወሰን የለበትም፡፡  

ሁለተኛው አደጋ ክልል የጠየቁት አስሩ ዞኖች ተኣምር ተፈጥሮ በፈለጉት ሰዓት ክልልነትን ህልውና ቢያገኙ እንኳን በመጭው ሃገራዊ ምርጫ በየትኛው ፓርቲ ተወክለው የህግአውጭ የሆነው ፓርላማ ውስጥ ሊገቡ እና አዲስ በፈጠሩ ክልል መንግስት ሊመሰርቱ እንደሆነ የታሰበበት አይመስልም፡፡ይህ በቅጡ ያልታሰበበት ትልቅ አደጋ የደቡብ ክልልን ህዝብ ከመላው ከሃገሪቱ የመንግስት ስርዓት የሚነጥል እጅግ አደገኛ ነገር ነው፡፡የሃገሪቱን የፌደራል ስርዓትም ሆነ ሃገራዊ አንድነት የማፍረስ አቅም ያለው ግን ደግሞ በውል ያልተጤነ አደጋ ነው፡፡ይህን አደጋ ለማስቀረት የደቡብ ክልል ምክርቤት መጭው ሃገራዊ ምርጫ አስኪደረግ ድረስ  በክልሉ በሚነሱ የክልልነት ጥያቄዎች ላይ አጠቃላይ እግድ መጣል ይኖርበታል፡፡   

ሶስተኛው  ችግር ክልል የጠየቁቱ የደቡብ ክልል ዞኖች በተዓምር የክልልነት ህልውና ቢያገኙ ክልልነት ያልጠየቁት የደቡብ ክልል ህዝቦች እጣ ፋንታ ምን ሊሆን ነው የሚለው ነገር የታሰበበት አይመስልም፡፡ ክልሉን ለረዥም ጊዜ ሲያስተዳድር የነበረው ደኢህዴን አስር ዞኖችን ካሰናበተ በኋላ ባለው ቅሪት አካሉ ያስተዳድራቸዋል ከተባለም ከወዲሁ ግልፅ መሆን አለበት፡፡

የደቡብ ክልል ለብዙ ክልሎች የሚሸሸን ከሆነ በአዲሶቹ ክልሎች መካከል የሚነሱ የድንበር ውዝግቦች የማይቀሩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በሲዳማ እና በወላይታ ዞን መካከል ሎክ አባያ በሚባለው አካባቢ ላይ የቆየ የይገባኛል ጥያቄ አለ፡፡ ይህ የይገባኛል ጥያቄ በአቶ ኃ/ማርያም ደሳሰኝ አጋፋሪነት ወላይቶች የእኛነው የሚሉት ወደ አስራ ሶስት የሚጠጋ ወረዳ ለሲዳማ ተሰጥቷል ሲሉ ያማርራሉ፡፡ ይህ ለምሳሌ ተጠቀሰ እንጅ ሌሎች ዞኖችም ከአጎራባች ዞኖቻቸው ጋር የድንበር እና የተፈጥሮ ሃብት ውዝግብ ውስጥ መግባታቸው አይቀርም፡፡ 

ይህ ውዝግብ የሃገሪቱን ፖለቲካ ሳይፈትን መፍትሄ እንዲያገኝ ደግሞ ሃገራችን በተረጋጋ ፖለቲካ እና በጠንካራ መንግስት ስር መገኘት አለባት፡፡በብዙ ችግር የሚላጋው የዶ/ር አብይ መንግስት ደግሞ ተጠናክሮ የሃገሪቱን ፖለቲካ ያረጋጋ ዘንድ ጊዜ ያስፈልገዋልና ዛሬውኑ የክልል ጥያቄያችን መልስ ያግኝ የሚለውን ጥድፊያ በይደር ማቆየቱ አስፈላጊ ነው፡፡ይህን ለማለት ማዕከላዊው መንግስት በቂ ምክንያት አለው፤ክልል ጠያቂው የፖለቲካ ልሂቅም የጠየቅኩት ዛሬ ካልተፈፀመ ሞቼ እገኛለሁ ማለቱ ሃገር ፈርሳ ካላየሁ ከማለት ጋር እንደሚቀራረብ መረዳት አለበት፡፡
____ 

ማስታወሻበዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here