spot_img
Saturday, September 23, 2023
Homeነፃ አስተያየትምርጫ ወይስ ተቋም ግንባታ . . . . . . የቱ ይቀድማል?...

ምርጫ ወይስ ተቋም ግንባታ . . . . . . የቱ ይቀድማል? (ኤፍሬም ማዴቦ)

advertisement

ኤፍሬም ማዴቦ 
ነሃሴ 20 2011 ዓ. ም.

የጠ/ሚኒስትር አቢይ አህመድ መንግስት አገር ዉስጥና ከአገር ዉጭ የሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችን ጋብዞ የአገራችንን ችግሮች አብረን እንፍታ የሚል ጥያቄ ካቀረበ በኋላ በነበሩት 16 ወራት ኢትዮጵያ ዉስጥ በአዳራሾች፥ በማህበራዊ ሜዲያ፥ በቴሌቭዥንና እንዲሁም በፖለቲካ ፓርቲዎችና በምርጫ ቦርድ መካከል በተደረጉ ዉይይቶች ዉስጥ ጉልህ ቦታ ከነበራቸዉ የዉይይት አርዕስቶች ዉስጥ አንዱና ዋነኛዉ የ2012ቱ ምርጫ ይራዘም ወይስ አይራዘም የሚለዉ ጥያቄ ነበር። ይህ ጥያቄ የዚህ ጽሁፍ ጸሃፊ በሁለት ሺ አስር ዓም ሐምሌ ወር ማለቂያ ላይ ከትግል አጋሮቹ ጋር ሆኖ አሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ ዉስጥ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በተገናኘበት ወቅት ካነሳቸዉ ጥያቄዎች ዉስጥ አንዱ ነበር። በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግስት ለዚህ ጥያቄ የሰጠዉ መልስ ምርጫዉ በተያዘለት የግዜ ሰሌዳ መካሄድ የለበትም የሚል አሳማኝ ሃሳብ የሚመጣ ከሆነ ምርጫዉ የማይራዘምበት ምንም ምክንያት የለም የሚል ነበር።ጠ/ሚኒስትር አቢይ አህመድ ከዋሽንግተን ከተመለሱ በኋላ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በተገናኙባቸዉ አጋጣሚዎች ሁሉ የምርጫዉ መራዘም አገርን የሚጠቅም እስከሆነ ድረስ የ2012ቱ ምርጫ ሊራዘም እንደሚችል ፍንጭ መስጠታቸዉ የሚዘነጋ አይደለም። 

በቅርቡ ጠ/ሚኒስትር አቢይ አህመድ በወቅታዊ የአገራችን ጉዳዮች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ ምርጫዉ ይራዘም እና መራዘም የለበትም የሚሉ የየራሳቸዉ ምክንያት ያላቸው የፖለቲካ ኃይሎች እንዳሉ ገልጸዉ የሳቸዉ ድርጅት ኢህአዴግ ግን ምርጫዉ ይራዘም የሚል አቋም እንደሌለዉ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፓሬሺን አስደምጦናል። አገራችን ኢትዮጵያ ዛሬ ለምትገኝበት እጅግ በጣም አሳሳቢ ሁኔታ አያሌ ኩነቶችን አንደ ምክንያት መጥቀስ ይቻላል። ባለፉት ሰማንያ አምስት አመታት ኢትዮጵያ ዉስጥ የነበሩት መንግስታት የገነቡት የፖለቲካ ስርአት አግላይ የሆነ የጥቂቶች ስርአት መሆኑና እነዚሁ መንግስታት የዘረጉት የኤኮኖሚ መዋቅር አብዛኛዉን ህዝብ ድሃ ያደረገ ነጣቂ የኤኮኖሚ መዋቅር መሆኑ ኢትዮጵያ ዛሬ ለገባችበት አዘቅት ዋነኛዉ ምክንያት ነዉ። ከዜህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ዉስጥ በሶስቱም መንግስታት ዘመን የተወሰኑት ትላልቅ አገራዊ ዉሳኔዎች ሁሉ የተወሰኑት በጥቂት ግለሰቦችና ቡድኖች ብቻ መሆኑ ለዛሬዉ ችግራችን ምክንያት ነዉ። 

ባለፉት ሃምሳ አመታት ዉስጥ አገራችን ኢትዮጵያ ለሶስተኛ ግዜ ምናልባትም ለመጨረሻ ግዜ ወሳኝ የሆነ የታሪክ መታጠፊያ ላይ ቆማለች። ይህ የታሪክ መታጠፊያ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባለድርሻዎች በሚቀጥሉት ሃምሳና መቶ አመታት አገራቸዉ ኢትዮጵያ የምትጓዝበትን አቅጣጫ የሚያመለክቱ ትላልቅ ዉሳኔዎችን የሚወስኑበትና ለዘመናት ላጨቃጨቁን የፖለቲካ ጥያቄዎች መልስ ሰጥተው የአዲሲቱን ኢትዮጵያ መሰረት የሚጥሉበት አጋጣሚ ነዉ እንጂ ሁላችንንም ተሸናፊ ሊያደርግ ወደሚችል ምርጫ ሮጠዉ የሚገቡበት አጋጣሚ አይደም። እንደዚህ አይነቶቹን በዛሬዉ ትዉልድ ላይ ብቻ ሳይሆን በተከታታይ ትዉልድ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ትላልቅ አገራዊ ዉሳኔዎችን እንደትናንቱ ዛሬም አንድ ቡድን ብቻዉን የሚወስን ከሆነ ይህ ብዙዎችን ያገለለ የአንድ ወገን ዉሳኔ ይቺን በነጋ በጠባ ለዘላለም ትኑር እያልን ረጂም ዕድሜ የምንመኝላትን አገር ማፍረስ እንደሚችል ልንገነዘብ ይገባል። እርግጠኛ ነኝ ማናችንም አይናችን እያየ ኢትዮጵያ ትፍረስ ወይም አትፍረስ የሚል ዉሳኔ ለመወሰን ጠረቤዛ ዙሪያ የምንቀመጥ አይመስለኝም። በአገራችን የወደፊት ዕድል ላይ የጋራ ዉሳኔ ስንወስን ከባዱ ነገር አገራችን ትፍረስና አትፍረስ ከሚል ዉሳኔ አንዱን መምረጥ አይደለም። በጣም ከባዱ ዉሳኔ አገራችን ለዘላለም የምትኖርበትን መንገድ ከሚጠቁሙ ሁለት አማራጮች ዉስጥ አንዱን መምረጥ ነዉ። ከነዚህ ሁለት አማራጮች አንዱን መምረጥ አቅቶን እርስ በርስ ስንባላ ነዉ አገራችን የመፍረስ አደጋ ዉስጥ የምትገባዉ። አገራችን ኢትዮጵያን ከጥፋት የምናድነዉ በእኛም በኢትዮጵያም ህይወት ዉስጥ እጅግ በጣም ከባድ ነዉ የሚባለዉን ዉሳኔ በድፍረት፥ በብልሃትና በአርቆ አሳቢነት መወሰን ከቻልን ብቻ ነዉ። በአገር ላይ የሚወሰን ከባድ ዉሳኔ ደግሞ ከሌሎች ጋር መምከርንና በጥሞና ማሰብን ይፈልጋል እንጂ ለብቻ አይወሰንም። ይህ በታሪክ መታጠፊያ ላይ ቆመን የምንወስነዉ ታሪካዊ ዉሳኔ ድፍረት፥ብልሃት፥ማሰብና መምከር ብቻ ሳይሆን ሰፊ ግዜም ይፈልጋል።

የአንድ አገር ዲሞክራሲ ጥንካሬና ዘላቂነት አገሪቱ ከገነባቻቸዉ ዋና ዋናዎቹ የዲሞክራሲ ተቋማት አይነትና ጥንካሬ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነዉ። ዲሞክራሲ ዛሬ አለማችን ዉስጥ ካሉት ስርአቶች ሁሉ የተሻለዉ ስርአት ነዉ እንጂ እንከን የለሽ ስርአት አይደለም። ስለሆነም አገሮች ዲሞክራሲን ሲገነቡ ከአገራቸዉ ተጨባጭ ሁኔታዎች (ባህል፥ ታሪክ፥የፖለቲካ ልምድና ማህበራዊ አደረጃጀት) ጋር እያዛመዱ ነዉ መገንባት ያለባቸዉ እንጂ ሁሉም አገር  ዉስጥ የሚሰራ ወይም ለሁሉም አገር የሚመች አንድ ወጥ የሆነ ዲሞክራሲ የለም። ስለዚህ እኛም አገር ዉስጥ ምን አይነት ዲሞክራሲ ነው የሚያስፈልገን የሚለዉን ጥያቄ ለመመለስ፥አገራችን ዉስጥ ያለዉን ተጨባጭ ሁኔታ፥ የፓለቲካ ታሪካችንን፥ የዲሞክራሲ ባህላችንን፥ ማህበረሰባቸን ዉስጥ ያለዉን ፖለቲካዊ አሰላለፍና የማህበረሰባችንን የዕድገት ደረጃ በሚገባ መመርመርና መፈተሽ አለብን። የዚህ ምርመራና ፍተሻ ዉጤት ነዉ ምን አይነት ዲሞክራሲ ያስፈልገናል የሚለዉን ጥያቄ የሚመልስልን፥ ደግሞም ምን አይነት ዲሞክራሲ ያስፈልገናል ለሚለዉ ጥያቄ መልስ ካገኘን በኋላ ነዉ ወደ ምርጫ መሄድ ያለብን። ካለዚያ ከፈረሱ ጋሪዉ ይቀድምና መሄጃዉም መድረሻዉም ይጠፋናል።

ዲሞክራሲ ልምዱም ባህሉም በሌለባቸዉ አገሮች ዉስጥ ሊገነባ ይችላል (ጋና ቦትስዋና) ፥ ዲሞክራሲ ተገንብቶ በፈረሰባቸዉ አገሮች ዉስጥ እንደገና ሊገነባ ይችላል (ስፔን ጀርመን)፥ ዲሞክራሲ ለአመታት የእርስ በርስ ጦርነት በተካሄደባቸዉ አገሮች ዉስጥ ሊገነባ ይችላል (ቦስኒያ ሰርቢያ) ፥ ዲሞክራሲ የረጂም አመት የመብትና የነጻነት ትግል በተደረገባቸዉ አገሮች ዉስጥ ሊገነባ ይችላል። ዲሞክራሲ በአንድ በኩል ብዙ ማንነቶች እና የባህልና የሃይማኖት ስብስቦች ባሉባቸዉ አገሮች ዉስጥ፥በሌላ በኩል ደግሞ እራስን በራስ የማስተዳደር እና የመገንጠል ጥያቄ በተነሳባቸዉ አገሮች ዉስጥ ሊገነባ ይችላል።     አንዳንድ አገሮች ከሞላ ጎደል አንድ ወጥ ቋንቋና ባህል ያለባቸዉ አገሮች ናቸዉ፥ አንዳንድ አገሮች ደግሞ ብዛት ያላቸዉ የተለያዩ ማንነቶች፥ ቋንቋዎች፥ ባህልና ሀይማኖት ያለባቸዉ አገሮች ናቸዉ። አንድ አገር ዉስጥ የዲሞክራሲ ግንባታ መሰረት ከመጣሉ በፊት እነዚህ በአገሮች መካከል ያሉ ልዩነቶች በሚገባ መጤን አለባቸው። 

ኢትዮጵያ የፈላጭ ቆራጭ የንጉስ አገዛዝ፥ ወታደራዊ አምባገነን አገዛዝ እና ብሄር ተኮር ፖለቲካ የተፈራረቁባትና ሁለት ስር ነቀል አብዮቶች በተከታታይ የተካሄዱባት አገር ናት። ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ለረጂም አመታት በመሳሪያ የታገዘ የመብትና የዲሞክራሲ ትግል የተካሄደባት ብቻ ሳትሆን የብሄር ጥያቄ፥ እራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄና የመገንጠል ጥያቄ የተነሳባት አገር ናት። እነዚህ እዉነቶች እና የዛሬዉ የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የሚነግረን አንድ ትልቅ ሀቅ አለ፥ እሱም ኢትዮጵያ እነዚህን ለዘመናት የተነሱ ጥያቄዎች ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ሊመልስ በሚችል አገረ-ግንባታ ሂደት ዉስጥ ማለፍ እንዳለባት ነዉ። የዚህ አገረ-ግንባታ ሂደት አላማ ዛሬ የአገራችንን የተለያዩ ማንነቶች እና የወል ስብስቦች በእኩልነት ማስተናገድ የሚችልና የግለሰብንና የቡድንን መብት የሚያከብር ዲሞክራሲያዊ ስርአት መሰረት መጣል ከሆነ ዉጤቱን እናዉቀዋለንና የሚያሰጋን ነገር አይኖርም። በዚህ ለአገራችን እጅግ በጣም  አስፈላጊ በሆነ ሂደት ዉስጥ ከማለፋችን በፊት ምርጫ ችግራችንን ይፈታል በሚል ምርጫ ዉስጥ ብንገባ ግን የምርጫዉን ዉጤት ተከትሎ ምን ሊመጣ ይችላል የሚለዉን ጥያቄ መልስ ከወዲሁ ማውቅ አንችልም። የምናስባቸዉና የምንሰራቸዉ ስራዎች ሁሉ በግለሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በአገር ደረጃም ነዉና ዉጤቱን የምናዉቀው የተሻለ አማራጭ እያለ ዉጤቱን የማናወቀዉ አማራጭ ዉስጥ መግባት ያለብን አይመስለኝም።  

የዚህ ጽሁፍ ዋነኛ አላማ እንደ አገር አንድነታችንን አስጠብቀዉ የሚያስቀጥሉንን እና ሁላችንንም አቅፈዉ በእኩልነት የሚያኖሩንን ተቋሞች በጠንካራ መሰረት ላይ አቁመን ወደ ምርጫ ብንሄድ ይሻላል እንጂ የእነዚህ ተቋሞች መሰረት ሳይጣል ከምርጫዉ ሰሌዳ ጋር ሙጭጭ ማለት አደጋ አለዉ የሚል ነዉ። ገዢዉ ፓርቲ ኢህአዴግ እና ምርጫዉ በተያዘለት ሰሌዳ ካልተካሄደ ኢትዮጵያ ትበተናለች የሚሉ ሀይሎች ሊረዱት የሚገባ ነገር ቢኖር፥ በአገራችን የወደፊት ጉዳዮችም ሆነ በምርጫዉ ሰሌዳ ላይ ተቀራርበን መነጋገር ነዉ አገራችንን ከመበታተን የሚያድናት እንጁ በራችንን ቅርቅር አድርገን ዘግተን “ምርጫ ወይም ሞት”እያልን ብንጮህ ጩኸቱ ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ መፈክሮች ያሰሙንን አምባገነኖች ያስታዉሰን ይሆናል እንጂ ሌላ ምንም የሚፈይደዉ ፋይዳ የለም። ዛሬ ሁላችንም የምንቆጨዉ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሤ እንዲህ አድርገዉ ቢሆን ኖሮ፥ ደርግ እንዲህ አድርጎ ቢሆን ኖሮ፥ ህወሓት/ኢህአዴግ እንዲህ አድርጎ ቢሆን ኖሮ እያልን ነዉ። ለመሆኑ እኛ ዛሬ ያለንበት ቦታ ምን አይነት ቦታ እንደሆነ ገብቶናል?  እኛኮ ያለነዉ ትናንት እነዚህ ሰዎች በነበሩበት ቦታ ምናልባትም በተሻለና ከነሱም በላይ እጅግ በጣም ወሳኝ በሆነና ቆራጥ ዉሳኔ በሚፈልግ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ነዉ። የቀኃስ፥ የደርግና የህወሓት/ኢህአዴግ ስርአቶች ያጠፉት ጥፋት ደካማና የተከፋፈለች ኢትዮጵያን አስረክቦናል። እኛ የምናጠፋዉ ጥፋት ግን ለሚቀጥለው ትዉልድ የሚያስረክበዉ አገር አይኖርም!

ምርጫ ምትክ የማይገኝለትና የአንድ አገር ህዝብ ሉዓላዊነቱን የሚያረጋግጥበት ወይም ህዝብ ብቸኛ የፖለቲካ ስልጣን ምንጭና ባለቤት ለመሆኑ ማረጋገጫ መሳሪያ ነዉ። ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ ምርጫዉ ይገፋ ወይም አይገፋ የሚሉ የፖለቲካ ኃይሎችን እያጨቃጨቀ ያለዉ ይህንን እዉነት ማወቅና አለማወቅ አይደለም።  ኢትዮጵያ የምትገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ ለምርጫ አመቺ ነዉ ወይስ አይደለም? ነጻና ገለልተኛ የሆኑ ዲሞክራሲያዊ ተቋሞች ሳይኖሩን ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ እንችላለን ወይ? ጡዘቱ እንኳን እኛን ጎረቤቶቻችንን ያስጨነቀ ብሄረተኝነት በነገሰበት አገር ዉስጥ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ ይቻላል ወይ? አንደ አገር የሚያስተሳስሩን ማህበራዊ እሴቶች በተናዱበትና ሌላ ቢቀር በሰንደቅ አላማዉ እንኳን የማይግባባ ህዝብ ባለበት አገር ዉስጥ በምርጫ ያሸነፈዉ ፓርቲ ምን አይነት አገር ነዉ የሚረከበዉ?በፌዴራል ስርአቱ ዉስጥ የፌዴራሉን ከፍተኛ ፍርድ ቤት  ትዕዛዝ የሚጥሱ፥የፌዴራሉ ፓርላማ የወሰነዉን ዉሳኔ አንቀበልም የሚሉና የኢትዮጵያን ህዝብ ቀርቶ እንመራዋለን የሚሉትን የራሳቸዉን ክልል ህዝብ የማይወክልም የማይመጥንም መግለጫ በየቀኑ የሚሰጡ የክልል መሪዎች ባሉበት አገር ዉስጥ ምን አይነት ምርጫ ነዉ የምናካሄደዉ? አገራችንን አላነቃንቅ ብለዉ ቀስፈዉ የያዙን ትላቅል ችግሮች ፊት ለፊታችን ላይ ተደቅነዉ፥ የባሰ ሊያበጣብጠን ወደሚችል ምርጫ ዉስጥ ካልገባን እያልን አፋችንን ሞልተን የምንናገር የፖለቲካ ሰዎች ከምርጫዉ የምንጠብቀዉ የራሳችን ጥቅም አለ፥ የችግሩ ስፋትና ጥልቀት አልገባንም ወይም ለወደፊቱ ትዉልድ ያለን አመለካከት ዝቅተኛ ነዉ። እነዚህን ከላይ  የተጠየቁትን አምስት ጥያቄዎች የዛሬዉን የራሳችንን የፖለቲካ ጥቅም እያሰብን ሳይሆን የነገዉን የአገራችንን ጥቅም ተመልክተን አግባብ ባለዉ መልኩ ሳንመልስ ህገ መንግስቱ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በየአምስት አመቱ በህዝብ ይመረጣሉ ተብሎ ስለተጻፈ ብቻ ሮጠን ወደ ምርጫ የምንገባ ከሆነ ሊመጣ የሚችለዉን ጥፋት ህገ መንግስቱ ላይ የተጻፉት 106 አንቀጾች አያቆሙትም። 

ከረጂም ግዜ የርስበርስ ጦርነትና ግጭት የተላቀቁ አገሮች ሰላምና መረጋጋት ያመጣልናል በሚል ተቻኩለዉ ወደ ምርጫ እንደገቡና የምርጫዉ ዉጤት የባሰ ትልቅ ቀዉስ ዉስጥ ይዟቸዉ እንደገባ ከሶቭየት ህብረት መፈራረስ በኋላ ዲሞክራሲን የገነቡ አገሮች ታሪክ በግልፅ ያሳየናል።ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ቅቡልነት ያለዉ መንግስት አንዲፈጠር ስለሚያደርግ ለሰላምና መረጋጋት አስፈላጊ ስለመሆኑ ጥርጥር የለዉም። ነገር ግን ምርጫዉን ነጻና ፍትሃዊ ማድረግ የሚችሉ ተቋሞች ሳይኖሩ ምርጫዉ እንዴት ነጻና ፍትሃዊ ሊሆን ይችላል? በብዙ አገሮች ዉስጥ የተደረጉ ሳይንሳዊ ጥናቶች የሚነግሩን እዉነት ቢኖር፥ ጎራ ለይተዉ በታገሉ የፖለቲካ ባለድርሻዎች መካከል መግባባት ሳይፈጠር፥አገርን እንደ ሙጫ አጣብቀዉ የሚይዙ የዲሞክራሲ ተቋሞች ግንባታ ሳይጀመርና የዜጎች መብት፥ ነጻነትና እኩልነት መከበራቸውን የሚያረጋግጡ ተቋሞች ሳይኖሩ ወደ ምርጫ የገቡ አገሮች በቀላሉ ወደማይወጡት ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀዉስ ዉስጥ እንደገቡ ነዉ። በተለይ ኢትዮጵያን በመሳሰሉ የብሄር ማንነት የሁሉም ነገር መለኪያ በሆነባቸዉ አገሮች ዉስጥ ምርጫን ማሸነፍና መሸነፍ ቀርቶ የብሄራዊ ፈተና ውጤትም ከብሄር ማንነት ጋር በቀጥታ ስለሚያያዝ የብሄር ፖለቲካ ተቋማዊ ልጓም ሳይበጅለት ምርጫ ዉስጥ ቸኩሎ መግባት መዘዙ ብዙ ነዉ። 

ካምቦዲያ፥ቦስኒያ፥ ኮሶቮ፥ ኢራቅና አፍጋኒስታን ዉስጥ በግልጽ እንደታየዉ፥ በድህረ-ግጭት ማህበረሰቦች ዉስጥ ምርጫ የርስ በርስ ጦርነቶችን ያቆማል፥የታጠቁ ኃይሎችን ወደ ሰላማዊ ፓርቲ ፖለቲካ ይስባል ደግሞም የፖለቲካ ቅቡልነትን ይፈጥራል በሚል ሰላምና መረጋጋት ሳይኖር፥ ምን አይነት ዲሞክራሲያዊ ስርአት መገንባት እንዳለበት በፖለቲካ ባለድርሻዎች መካከል ስምምነት ሳይፈጠር፥ብሄረተኝነት በገነነበት እና የምርጫዉን ነጻና ፍትሃዊ መሆን የሚያረጋግጡ ተቋሞች ሳይኖሩ አገሮች ወደ ምርጫ እንዲገቡ የሚገፋፋዉ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ነዉ። ይህ የሚያሳየን አለም አቀፉ ማህበረሰብ በድህረ-ግጭት ማህበረሰቦች ዉስጥ ምርጫን የሚመለከተዉ የአገረ-ግንባታ ሂደቱ መልክ ከያዘ በኋላ ግዜዉን ጠብቆ መምጣት እንዳለበት አንድ ምዕራፍ ሳይሆን የአገረ-ግንባታዉ ሂደት መጀመሪያና መጨረሻ ቁልፍ አካል አንደሆነ አድርጎ ነዉ። በእርግጥ ምርጫ ቁልፍና ወሳኝ የሆነ የዲሞክራሲ ሂደት አካል ነዉ፥ ሆኖም ግን ምርጫ በአገረ-ግንባታ ሂደት ዉስጥ እንዴት፥ በማንና ለምን መካሄድ አለበት የሚሉ ጥያቄዎችን የሚመልሱ ተቋሞች ጥንስስ ከተጣለ በኋላ መምጣት ያለበት በአገረ-ግንባታ ሂደት ዉስጥ የአንድ ትልቅ ምዕራፍ (Milestone) መቋጫ ነዉ እንጂ የአገረ-ግንባታ ሂደት መጀምሪያ አይደለም፥ መሆንም አይችልም። በድህረ-ግጭት ማህበረሰቦች ዉስጥ የአገረ-ግንባታዉ ሂደት የሚፈለግበት ደረጃ ላይ ሳይደርስ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ግፊት ተቻኩለዉ ምርጫ ያካሄዱ ኢራቅና አፍጋኒስታንን የመሳሰሉ አገሮች ዛሬም ድረስ የተረጋጋ ማህበረሰብ መፍጠር አልቻሉም። 

የጠ/ሚኒስትር አቢይ አህመድ መንግስት ወደ ሥልጣን ከመጣበት ግዜ ጀምሮ የህወሓት/ኢህአዴግን መንግስት በሙሉ ኃይላቸዉ ሲረዱ የነበሩት ትላልቆቹ መንግስታትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ ሌሎችም  አለም አቀፍ ተቋማት በሚቀጥለው የአገራችን ምርጫ ላይ አሻራቸዉን ለማሳረፍ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው በተለያየ መልኩ ገልጸዋል። ሆኖም እነዚህ አካላት ከፍተኛ ትኩረት የሰጡት ኢትዮጵያ ምን አይነት ዲሞክራሲ ያስፈልጋታል ወይም ኢትዮጵያ የጀመረችዉን የአገረ-ግንባታ ሂደት እንዴትና በምን መልኩ ብንረዳ ነዉ የኢትዮጵያን ሰላምና ብልጽግና ማረጋገጥ የምንችለዉ በሚሉ ወሳኝ የረጂም ግዜ አገራዊ ግቦች ላይ አይደለም። ይልቁንም የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ትኩረት የሚቀጥለውን ምርጫ እንዴት ነዉ የምንረዳዉ በሚል የአጭር ግዜ ግቦች ላይ ነዉ። ይህ ነዉ ተብሎ ሊነገር የሚችል የዲሞክራሲ ልምድ በሌለባትና ከ100 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በሚኖርባት ደሃ አገር ዉስጥ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ ቀርቶ ዉጤቱ ከወዲሁ የታወቀ የይስሙላ ምርጫ ማካሄድም እጅግ በጣም ያስቸግራል። ስለዚህ አለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚቀጥለውን ምርጫ አስመልክቶ ሊረዳን በማሰቡ ልናመሰግነዉ ይገባል። ሆኖም ምርጫዉን ማካሄድ የምንችልበት ሁኔታ ሲፈጠር  ነዉ ማካሄድ ያለብን እንጂ ለምርጫዉ ስንል የረጂም ግዜ ጥቆሞቻችንን ትተን በአጭር ግዜ ጥቅሞቻችን ላይ ማተኮር የለብንም፥ ከትክክለኛ  ውክልና ይልቅ ብልጭ ብሎ ድርግም የሚል መረጋጋት ላይ ማተኮር የለብንም፥ የፖለቲካ ስምምነት ከሚፈጥረዉ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ይልቅ ታይቶ ወዲያዉ ሊጠፋ በሚችል የፖለቲካ ቅቡልነት (Political Legitimacy) ላይ ማተኮር የለብንም።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባለድርሻዎች ባለፈዉ ታሪካችን ላይ የሚያደርጉትን ማለቂያ የሌለዉ እሰጥ አገባ አቁመዉ የልጅ ልጆቻችን ባጠቃላይ መጪዉ ትውልድ የኔ ነዉ ብሎ የሚቀበለውን አዲስ ታሪክ መጻፍ መጀመር አለባቸዉ። የዚህ አዲስ ታሪክ የመጀመሪያዉ ምዕራፍ በፍትህ፥ በዲሞክራሲና በፖለቲካ ተቋሞች  ግንባታ መጀመር አለበት።ምን አይነት የፌዴራል አወቃቀር ነዉ የሚበጀን፥ምን አይነት የመንግስት ቅርፅ ነዉ የሚያስፈልገን (ፓርላማዊ፥ ፕሬዚደንታዊ፥ ግማሽ ፕሬዚደንታዊ) ምን አይነት የምርጫ ስርአት ነው የሚያስፈልገን (አብላጫ ድምጽ፥ተመጣጣኝ ) በሚሉ የአገራችንን የወደፊት አቅጣጫ በሚወስኑ ትላልቅ ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባለድርሻዎች ዉይይት መጀመር አለባቸዉ፥ የኢትዮጵያ ህዝብም በዉይይቱ ላይ የራሱን ድምጽ የሚያሰማበትን መንገድ መፍጠር አለባቸዉ። በእነዚህ ትልልቅ የአገራችንን የወደፊት አቅጣጫ በሚወስኑ ተቋሞች ላይ የሚደረጉ ዉይይቶች ለነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ቅርፅና ይዘት የሚሰጡ ዉይይቶች ስለሆኑ፥ እነዚህ ዉይይቶች መጠናቀቅ ያለባቸው ወደ ምርጫ ከመግባቻችን በፊት ነዉ። የእነዚህ ትላልቅ ተቋሞች መሰረት ከተጣለ በኋላ ምርጫ ዉስጥ የመግባት ትዕግስቱ ቢኖረን መልካም ነዉ። ነገር ግን ይህ ሂደት ብዙ ግዜ ስለሚወስድ አደጋ አለዉ የሚሉ ኃይሎችን ስጋት እንጋራ ብንል እንኳን በእነዚህ ትላልቅ ጉዳዮች ላይ ሁላችንንም የሚያግባባ ስምምነት ላይ ደርሰን ወደ ምርጫ ብንሄድ የምርጫዉን ዉጤት ባንወደዉም ውጤቱን ተቀብለንና አክብረን ለሚቀጥለው ምርጫ እንዘጋጃለን እንጂ እርስ በርስ  የሚያናክስ ሁኔታ ዉስጥ አንገባም።

አገራችን ኢትዮጵያ ተደጋጋሚ የአገረ-ግንባታ ሂደቶች ተጀምረዉ ፍጻሜ ያላገኙባት አገር ናት፥ ኢትዮጵያ አክራሪ ብሄረተኝነት የነገሰባትና እንዲሁም ሰላምና መረጋጋት ያጣች አገር ናት። ኢትዮጵያ የማይግባቡና አንዳንዴም  የሚቃረን የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸዉ የፖለቲካ ባለድርሻዎች ያሉባት አገር ናት።ኢትዮጵያ የርስ በርስ ጦርነት የተካሄደባትና በአለማችን ዉስጥ መገንጠል በተግባር ከታየባቸዉ በጣት ከሚቆጠሩ አገሮች ዉስጥ አንዷ ናት። ኢትዮጵያ አሁንም መገንጠልን ያለ ምንም ቅደመ ሁኔታ እንደ ትልቅ መብት ህገ መንግስቷ ዉስጥ ያስቀመጠች “እኛ ያልነው ካልሆነ እንገነጠላለን” የሚሉ “ሃይለኞች” ያሉባት አገር ናት። ኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስቱን የሚገዳደር የታጠቀ ልዩ ሃይልና የራሳቸዉ የሆነ ሜዲያ ያላቸዉ በብሄር የተደራጁ ክልሎች የሚገኙባት አገር ናት።እነዚህ የኢትዮጵያን ህልዉና የሚገዳደሩ እጅግ በጣም አሳሳቢ ሁኔታዎች የመርገብ ምልክት ሳይታይባቸዉና በትልልቆቹ የአገራችን ጉዳዮች ላይ ምንም አይነት አገራዊ ስምምነት ላይ ሳይየደረስ ህገ መንግስታዊ ግዴታ ነው በሚል መርህና በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ግፊት ምርጫ ዉስጥ ብንገባ ከምርጫዉ በኋላ ሊመጣ የሚችለዉን ጥፋት ሀገ መንግስቱም አለም አቀፉ ማህበረሰብም ሊያቆሙት አይችሉም። ኢትዮጵያን ከጥፋት ለማዳንና የዚችን ትልቅና ታሪካዊ አገር ቀጣይነት ለማረጋገጥ፥ህገ መንግስቱን ማሻሻል፥ እንደገና መጻፍ፥ ይህ ሁሉ የማይቻል ከሆነ ደግሞ አገር ለማዳን ሲባል ህገ መንግስቱን በከፊል ወይም በሙሉ እስከማገድ ድረስም መሄድ አለብን ብሎ የዚህ ጽሁፍ ጸሃፊ ያምናል። የኢትዮጵያን ህልዉና በተመለከተ ህገ መንግስቱ ለኢትዮጵያ መኖር ይኖራል እንጂ ኢትዮጵያ ለህገ መንግስቱ መኖር አትኖርምና የ2012ቱን ምርጫ ሰሌዳ በተመለከተ የምንወስነዉ ዉሳኔ ከኢትዮጵያ ህልዉና ጋር በቀጥታ የተያያዘ መሆኑን ሁላችንም ልንገነዘብ ይገባል። ኢህአዴግ ባለፉት ሃያ ሰባት አመታት ብቻ ሳይሆን አገራችን በለዉጥ እንቅስቃሴ ዉስጥ በቆየችባቸዉ ባለፉት 16 ወራት ዉስጥም የወሰናቸዉንና መወስን ሲገባዉ ያልወሰናቸዉን ዉሳኔዎች ስንመለከት በዚህ በአገራችን ታሪክ ዉስጥ እጅግ በጣም ወሳኝ በሆነ የሽግግር  ወቅት ትልልቆቹን አገራዊ ዉሳኔዎች ኢህአዴግ ብቻዉን እንዲወስን መፍቀድ 1966ን እና 1983ን መድገም ይሆናል። ይህንን የብቻ ዉሳኔ የኢህአዴግ ሰዎችም የሚፈልጉት አይመስለኝም፥ ደግሞም እንዲህ አይነቱን ከትዉልድ ወደ ትዉልድ የሚተላለፍ ታሪካዊ ዉሳኔ አንድ ወገን ብቻ እንዲወስነዉ መፍቀድ ኢህአዴግን ብቻ ሳይሆን ሁላችንንም ከታሪክም እኛዉ እራሳችን ደግመን ደጋግመን ካጠፋነዉ ስህተትም የማንማር የፖለቲካ ገለባዎች ያደርገናል። እኛ በአባቶቻችን እንደምንኮራ በእኛ መኩራት የሚገባዉና እኛን አባቶቼ ብሎ የሚጠራዉ መጪዉ ትዉልድ ታሪካችንን ሲጽፍ የመጽሀፉ መግቢያ ላይ የሚጽፈዉ “አባቶቻችን ከታሪክ የተማሩት ጥፋትን መድገም ነዉ” የሚል አሳፋሪ ሀረግ ይሆናል።

emadebo@gmail.com    እዚህ ጽሁፍ ዉስጥ ያለዉ ሃሳብ ሁሉ የኔ የኔና የኔ ብቻ ነዉ!
___

ማስታወሻበዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
13,672FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here