spot_img
Monday, May 29, 2023
Homeነፃ አስተያየትየኢትዮጵያ መንግሥት ሥልጣን ምን ድረስ ነው? (ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ)

የኢትዮጵያ መንግሥት ሥልጣን ምን ድረስ ነው? (ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ)

- Advertisement -
Samuel Tibebe Ferenji
ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ

 ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ
 ጷግሜ 2 ቀን 2011 (09/07/2019)                    

ሃገረ አሜሪካንን በመገንባት፤ ታላቅ ሚና የነበረው፤ ፌደራሊስት ተብሎ በሚታውቀው ደብዳቤው በርካታ ጽሁፎችን በጋዜጣ ያሳተመው፤ ጀምስ ማድሰን፤ “ሰዎች መላዕክት ቢሆኑ ኖሮ፤ መንግሥት አያስፈልግም ነበር” ማለቱ ይነገራል። መንግሥት ሲባል ግን የተለያያ ይዘት እና ቅርጽ ያለው ቢሆንም፤ ዋና ሥራው ዜጎችን ከአደጋ መከላከል ነው። በተለይም፤ ዲሞክራሲያዊ በሆኑ የመንግሥት አስተዳደር ውስጥ፤ የመንግስት ሥልጣን የተገደበ በመሆኑ፤ መንግሥት ማድረግ የሚችላቸው እና ማድረግ የማይችላቸው ነገሮች፤ በሕግ የተደነገጉ ናቸው። መንግሥት ሲባልም፤ በተለያየ ደረጃ የስልጣን መዋቅር የተከፋፈለ እና የተለያየ ሥልጣን እና ሃላፊነት ያላቸው ተቋማት እና ግለስቦችም ናቸው፡፡ በበርካታ፤ እንደ እኛ ዓይነት ባሉ ገና የዲሞክራሲ ሥልተ ስርዓት ባልተለመደባቸው ሃገራት፤ ሁሉንም ነገር ከመንግሥት መጠበቅ፤ ለሚከሰቱ ጉዳቶች ሁሉ መንግሥትን መውቀስ፤ የመንግሥት ተቋምና እና የባለሥልጣናትን የሥልጣን ሃላፊነት እና ገደብ ምን እንደሆነ አለመረዳት፤ የፌደራል፤ የክልል፤ የከተማ፤ የክፍለ ከተማ፤ የወረዳና፤ የቀበሌ መንግስታትን፤ የስራ ክፍፍል እና የስልጣን እርከንን አለመረዳት፤ ለበጎ ነገሮች ደግሞ አልፎ አልፎ፤ በጅምላ መንግሥትን ማመስገን የተለመደ ነው። የዚህ ፅሁፍ አላማ አጠቃላይ፤ ስለመንግሥት አሰራር እና ሃላፊነት በዝርዝር ለመከተብ ሳይሆን፤ ዓላማው፤ የፌደራል መንግሥቱ፤ ሥልጣኑ ከምን ድረስ እንደሆነ ለመጠቆም እና፤ ሕግ በጣለበት ገደብ የተነሳ፤ መንግሥት “የፖለቲካ ልሂቃኖቻችን” በሚፈልጉት መልክ፤ ፍጥነት፤ እና ሁኔታ በተለያየ አቅጣጫ የሚነሱት ጉዳዮች ላይ እርምጃ መውሰድ የማይችልበት ሁኔታ እንዳለም ለመግለጽ ነው። 

በተደጋጋሚ እንደተጠቀሰው፤ በአሁኑ ሰዓት ሃገሪቱ የምትተዳደርበት የፌደራል ሥርዓት ሲዋቀር፤ ሆን ተብሎ፤ ታስቦበት፤ እና ታቅዶ፤ የፌደራል መንግሥቱን ደካማ፤ የክልል መንግስታትን ደግሞ፤ ጠንካራ አድርጓል። ሕገ መንግሥቱን አርቅቆ ያፀደቀው የፖለቲካ ሃይል፤ የማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣኑን በሚያጣበት ወቅት፤ “ንግስናውን” በክልል ደረጃ ለመቀጠል እና፤ የፌደራል መንግሥቱም በክልሉ ጉዳይ “ጣልቃ” እንዳይገባ፤ በሕግ አስሮታል። በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 51 ቁጥር 14 መሰረት የፌደራል መንግሥቱ “ከክልል አቅም በላይ የሆነ የጸጥታ መደፍረስ ሲያጋጥም በክልሉ መስተዳድር ጥያቄ መሠረት የሀገሪቱን የመከላከያ ኃይል ያሰማራል፡፡” ይላል፡፡ (መስመር እና ድምቀት የተጨመረ)፡፡ ይህም ማለት፤ የፌደራል መንግሥቱ በክልሎች ውስጥ ሕግ ለማስከበር የሚወስዳቸው እርምጃዎች፤ በመጀመርያ በክልሉ መንግሥት አዎንታዊ ምላሾች ማግኘት አለባቸው ማለት ነው፡፡ 

አሁን ባለው የፌደራል መንግሥት የስልጣን መዋቅር እና ክፍፍል፤ የፌደራል መንግሥት በክልልም ሆነ በከተማ ጉዳዮች ጣልቃ የሚገባበት ሕጋዊ ሥልጣን የተገደበ እና የተወሰነ ነው። እኛ ሃገር፤ ለዓመታት የቆየነው፤ ሥልጣን በአንድ ሰው እጅ ሆኖ፤ ሁሉም ነገር በዛው ሰው “ፈቃድ እና ፍላጎት” ሲተገበር ነው። ምንም እንኳን ላለፉት 24 ዓመታት በሥራ ላይ እንዲውል “የፀደቀው ሕገ መንግሥት” የተለያዩ የመንግስት አካላትን ሥልጣን እና ተግባር የደነገገ ቢሆንም፤ ሕገ መንግሥቱ፤ የጥቂት ግለስቦች እና ቡድን ዓላማና ፍላጎት ማስፈፀምያ ከመሆን ባለፈ፤ በሥራ ላይ አልዋለም፤ በዘፈቀደም ሲጣስ ነበር።  አዲሱ “የለውጥ መራሹ ቡድን” ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ፤ ግን፤ ሕገ መንግሥቱን በማክበር ሥራውን እንድሚሰራ ቃል የገባ በመሆኑ፤ እና የሕግ የበላይነት በሃገሪቱ እንዲሰፍን እየሰራ በመሆኑ፤ ብዙውን ነገር፤ ከሕገ መንግሥቱ ጋር በማጣጣም፤ ለመተግበር ቀና ደፋ እያለ ይገኛል። ይህም በመሆኑ፤ በተደጋጋሚ፤ በተለያዩ ክልሎች ነውጦች ሲነሱ፤ የክልሉ መንግሥታት “ጣልቃ እንዲገባ እስኪጋብዙት” በክልል ጉዳይ “ጣልቃ ባለመግባቱ” በሕዝብ እና በንብረት ላይ ጉዳት ሲደርስ አፋጣኝ ምላሽ አልሰጠም። ምላሽ ሰጥቶ፤ እርምጃ በወሰደባቸው አካባቢዎችም፤ “የእኔን ብሔር አጠቃ” በሚል የፖለቲካ ጡዘት፤ መንግሥት ከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። ከዚህም አልፎ፤ በርካታ ተሟጋች ነን የሚሉ ሃይሎች፤ በቀበሌ፤ በክፍለ ከተማ፤ በወረዳም ይሁን በከተማ ደረጃ ለሚሰሩ ስሕተቶች እና ጥፋቶች፤ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ፤ የፌደራል መንግሥቱን፤ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሲወቅሱ እና ሲያወግዙ አይተናል። 

አንዳንዶች፤ ሆን ብለው እና ለራሳቸው እኩይ የፖለቲካ ዓላማ፤ የቀበሌ ሊቀመንበርም ይሁን፤ የከተማ ከንቲባ ሰራ ብለው ለሚያምኑት ጥፋት ወይም ስሕተት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማጥላላት ሲጠቀሙበት ማየት፤ የተለመደ ሆኗል። ለምሣሌ፤ በለገጣፎ ለተከሰተው የቤቶች መፍረስ ለሚነሱ ጥያቄዎች፤ መልስ መስጠት ያለበት፤ የከተማው ከንቲባ፤ ግፋም ካለ የኦሮምያ ክልላው መንግሥት ሆኖ ሳለ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ተጠያቂ በማድረግ፤ ከፍተኛ ፕሮፖጋንዳ ተሰርቶበታል። በአዲስ አበባ ከተማ በአንድ ወረዳ ውስጥ፤ መታውቂያ በሃስት እየታደለ ነው የሚል ጥቆማ ሲደርስ፤ የወረዳውን አስተዳደር፤ ግፋም ካለ የከተማውን አስተዳደር ተጠያቂ ማድረግ ሲገባ፤ በአንዳንድ “ተሟጋቾች”፤ በዚሁ ጉዳይ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማጥላላት እና፤ አዲስ አበባን “ኦሮሞዋዊ” ለማድረግ፤ “ሴራ” እየተሴረ ነው በሚል፤ ከፍተኛ የፖለቲካ አቧራም ተረጭቷል። ዛሬም እንደምናየው፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የውስጥ ጉዳይ ለተነሳ ውዝግብ፤ የፌደራል መንግሥቱን በቀጥታ ተጠያቂ ለማድረግ ከፍተኛ ፕሮፖጋንዳ እየተሰራ ይገኛል። የፌደራልም ሆነ የክልል መንግሥት፤ በየትኛውም የሃይማኖት ጉዳይ እንዳይገባ፤ ሥልጣኑ በሕግ የተገደበ ነው። አሁን ባለው የቤተ ክርስቲያን የውስጥ ውዝግብ፤ ብዙዊች፤ “መንግሥት፤ ሕግ ተጥሶ ቤተክርስቲያን ላይ ጥቃት ሲፈፀም ዝም አለ” ሲሉ መስማት የተለመደ ሆኗል፤ ግን የትኛው ሕግ እንደተጣሰ የገለፀ ማንም የለም። የቤተ-ክርስቲያኗ የውስጥ ሕግና ደንብ ከተጣሰ፤ ያንን ሕግና ደንብ ማስከበር ያለባት ቤተ-ክርስቲያኗ እንጂ መንግሥት አይደለም። የሃገሪቱ የወንጀለኛ ሕግ ወይም የፍትሃ ብሄር ሕግ ተጥሶ ከሆነ፤ ይህንንም ወደ ሕግ ቦታ ማምጣት የምትችለው ቤተ-ክርስቲያን ነች። ይህ ሆኖ ሳለ፤ መንግሥት በቤተ-ክርስቲያን ጉዳይ “ጣልቃ አልገባም” በማለቱ ሊወቀስም ሆነ ሊወገዝ የሚችልበት ምንም ምክንያት የለም። መንግሥት በቤተ እምነት ጉዳይ ላይም ሆነ፤ በክልል ጉዳይ ጣልቃ እንዲገባ ከተፈለገ፤ ሕጉን መቀየር ያስፈልጋል።     

ሃገረ አሜሪካንን ከመሰረቱት፤ “የአሜሪካን መስራች አባቶች”፤ በተለይ ጀምስ ማድስን እና አሌክሳንደር ሃምልተን፤ የአሜሪካን ሃገር ሲመሰረት፤ አጥብቀው ይከራከሩ የነበረው፤ የፌደራል መንግሥቱ ጠንካራ እንዲሆን ነበር፤ ለዚህም ዋና ምክንያታቸው፤ የማእከላዊው መንግሥት ደካማ ሲሆን፤ በአንድ ሃገር ውስጥ ባሉ የተለያዩ ክልሎች፤ የተለያየ አሰራር የሚፈጥር በመሆኑ፤ በክልሎች ውስጥ የሚፈጠርን ችግር ለመፍታት፤ ማዕከላዊው መንግስትን አቅመ ቢስ ያደርገዋል፤ የክልል መንግሥታት፤ በክልሉ በሚኖሩ ዜጎች ላይ በደል ሲያደርሱ፤ ማእከላዊው መንግሥት በደሉን ለመገደብ የሚችልበት ሥልጣን አይኖረውም የሚል ነበር፡፡ አሜሪካን እንደ ሃገር ከመመስረቱ በፊት የነበሩት 13ቱ እራሳቸውን የቻሉ ክልል መንግሥታትን፤ በአማከለ ጠንካራ አስተዳደር ለመተካት በመፈለጉ ነው፤ 13ቱ ክልሎች፤ የክልል መንግስታት ብቻ መሆናቸው አክትሞ፤ አንድ የተባበረ፤ ጠንካራ የፌደራል መንግሥት ያለው ስርዓት ለመገንባት በመወሰን፤ የተባበሩት የአሜሪካን መንግስትን ማቋቋም የቻሉት፡፡ ምንም እንኳን፤ የአሜሪካን የፌደራል መንግስት እና የክልል መንግሥታት፤ የየራሳቸው የስራ ድርሻ እና ክፍፍል ቢኖራቸውም፤ የስብአዊ መብት ጥሰት ሲኖር እና በሃገር ውስጥ ሁከት ሲኖር፤ የፌደራል መንግስቱ ፖሊስ በቀጥታ በክልል ጉዳይ በመግባት፤ እርምጃዎችን ይወስዳል፡፡ ከዛም አልፎ፤ የክልል መንግስታት በዜጎች ላይ ለሚፈፀሙት የሕግ ጥሰት፤ ዜጎች፤ የክልሉን መንግስት በክልሉ ፍርድ ቤት ወይም በፌደራል ፍርድ ቤት የመክሰስ መብት አላቸው፡፡ 

ከምንም በላይ የአሜሪካንን ዲሞክራሲ ጠንካራ ያደረገው፤ ዜጎች የመንግስትን ሥልጣን እና ሃላፊነት እንዲሁም የሥራ ክፍፍል በሚገባ መገንዘባቸው እና፤ ዜጎች እና ተቋማት ለመብታቸው በመቆም በሚያደርጉት ሙግት ነው። ለዚህም በተለይ የፍትሕ አካላትን በመጠቀም፤ ዜጎች በመንግሥት ለሚደርስባቸው በደል፤ መንግሥትን ይሞግታሉ። ዛሬም ቢሆን፤ አሜሪካን ሃገር ውስጥ፤ የዘር መድልዎ፤ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፤ የመንግሥት የሥልጣን ብልግና አለ፤ ዜጎች ግን፤ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን፤ የዘር መድልዎን፤ እና የመንግሥትን ብልግና የሚታገሉት፤ ተቋማትን በመጠቀም ነው። ለዚህም በተለይ የዜና አውታሮች፤ የሲቪክ ማህበራት እና፤ ፍርድ ቤቶች፤ ያላቸው ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው። በዚህ ፀሃፍ እምነት፤ የመንግሥትን፤ የስልጣን ክፍፍል፤ ሥልጣን እና ተግባር በቅጡ ካለመረዳት በተጨማሪ፤ የእኛ ሃገር አንዱ ጉድለት፤ ሃገሪቱ ውስጥ ያሉትን፤ የሲቪክ፤ የዜና አውታሮች፤ እና የፍትሕ ተቋማት በሚገባ ባለመጠቀማችን፤ ሁሉንም ነገር በአንድ የመንግሥት አካል ላይ ብቻ እንድናነጣጥር አድርጎናል።   

ይህን ንፅፅር ያነሳሁት፤ አሜሪካን ያለፈችበት ውጣ ውረድ፤ ወይም የአሜሪካን ሕዝብ የሚሄድበት መንገድ ሁሉ ለኢትዮጵያ ይመቻል ከሚል እሳቤ ሳይሆን፤ ለአንድ ሃገር ስላም እና ብልጽግና፤ ጠንካራ የፌደራል መንግስት መኖሩ ጥቅም እንዳለው ለማሳየትና፤ ዜጎች፤ በሃገራቸው ጉዳይ በመሳተፍ እና ለመብታቸው በመቆም፤ ለዲሞክራሲ እድገት ሊያበረክቱ የሚችሉትን አስተዋጽኦ ለመጠቆምም ነው። በሃገራችን የዲሞክራሲ ሥልተ ሥርዓት ግንባታ ገና መንገድ እየያዘ ባለበት በዚህ ጊዜ፤ ክልሎችን ጠንካራ ማድረግ እና፤ የፌደራል መንግስቱን ደካማ ማድረግ፤ በክልሎች ተገድበው የሚኖሩ ዜጎች፤ በአምባገነን ሃይሎች ተረግጠው እንዲገዙም፤ መንገድ የሚከፍት በመሆኑ፤ ሕገ መንግሥቱን በማስተካከል ረገድ፤ ገዥው ፓርቲ ሃላፊነት የተመላበት ሥራ መሥራት ይጠበቅበታል ብሎ ይህ ጽሃፍ ያምናል። ቀደም ሲል፤ ሕገ መንግሥቱን አርቀቀው ያፀደቁ ሃይሎች፤ ማዕከላዊው መንግሥት “ደካማ” እንዲሆን በሕግ ያሰሩት፤ ዛሬ እንደምናየው፤ የማዕከላዊውን መንግሥት ሥልጣናቸውን ሲያጡ፤ በክልልላቸው መሽገው፤ “በክልላቸው” የፈቀዳቸውን ለማድረግ እና፤ በሕግ ተጠያቂ ላለመሆንም ነው።    

ባለፉት የትሕነግ መራሹ መንግሥት አገዛዝ፤ መንግሥት፤ ለሕገ መንግስቱ ግድ ያልነበረው እና፤ ለሕገ መንግሥቱ ተገዢ እንዳልነበር ብዙ ተብሎለታል። ትላንት እንደፈለጋቸው ሲጨፈልቁት የነበረውን ሕገ መንግሥት፤ ዛሬ ከቀበሩበት ሳጥን ውስጥ አውጥተው፤ አቧራውን እፍ ብለው፤ “ሕገ መንግሥቱ ይከበር” ሲሉ መስማት አስደማሚ ነው። እስከዛሬ ሕዝባችን የለመደው፤ መንግሥት የፈለገውን ሲያደርግ፤ አምባገነኖች፤ የክልል እና የፌደራል መንግሥት ያላቸውን የሥልጣን መስመር፤ ከቁም ነገር ባለመቁጠር፤ በፈለጉበት ክልል ሰራዊታቸውን እያስገቡ፤ ዜጎችን ሲያስሩ እና ሲገድሉ ስለነበር፤ ዛሬ ሕገ መንግሥቱን ተከትዬ ሃገሪቱን ስርዓት አስይዛለሁ ብሎ ለሚውተረተረው የለውጥ ሃይል እጅግ ፈታኝ ሆኖበታል። ከቀበሌ የመታወቅያ አሰጣጥ ጉድለት “ክስ”፤ እስከ ቤተ ክርስቲያን ቃጠሎ፤ ተወቃሹ ይኽው የለውጥ ሃይል ሆኗል። ሃገሪቱን እየመራ ያለው የለውጥ ሃይል፤ ተገቢ እና አስፈላጊ እርምጃ ለመውስድ እንዳይችል “ሕገ መንግስት” በተባለ ሳንካሰር የእጅ እና እግር ቶርች ታስሯል። 

አሳዛኙ ነገር ይህ ብቻ አይደለም፤ ሕግና ሥርዓት ተከትዬ፤ ሃገሪቱን ወደ ዲሞክራሲያዊ ስልተ ሥርዓት አሻግራለሁ ብሎ እየደከመ ያለውን ሃይል፤ ትላንት ረግጠው ሲገዙን የነበሩ ሃይሎች፤ “በሕግ ሥም” እንዳይንቀሳቀስ “ከማሰራቸው” አልፈው፤ መንግሥት ደካማ ነው፤ የዜጎችን ሕይወት እና ንብረት አልጠበቀም፤ ቤተ ክርስቲያን ሲቃጠል ዝም አለ፤ ዜጎች ሲፈናቀሉ ዝም አለ፤ የሚል ጥሩንባ የሚነፉት እነሱ መሆናቸው እና ይህንንም እንደ እውነት ተቀብሎ የሚያስተጋባ ሃይል መኖሩ ነው። በማህበራዊ ሚድያም ያሰማሩት “ዲጂታል ወታደራቸው” ሌተ ተቀን ተግቶ የሚሰራው፤ ለውጡን ለማጣጣል እና የሕዝብ ድጋፍ ለማሳጣት፤ ሕዝቡ በለውጡ ሂደት ተስፋ ቆርጦ እንዲማረር እና ከዛም፤ “እኛ እንሻልህ ነበር” በሚል ብልጠት፤ ተሽቀንጥረው ከተጣሉበት የአገዛዝ ማማ ላይ ለመውጣት ነው። “ድሃ በሕልሙ ቅቤ ባይጠጣ ኖሮ፤ ንጣት ይገድለው ነበር” የሚል ሃገርኛ አባባል አለ። እነዚህ ተስፈኞች፤ ወደ ሥልጣን ለመመለስ ማሰብ ብቻ ሳይሆን፤ ተግባራዊ እንቅስቃሴም መጀመራቸው፤ ሰሞኑን የተወሰኑ የፖለቲካ ድንክዬዎችን ሰብሰበው፤ “ኢትዮጵያን ለማዳን” የራሳችንን እርምጃ እንወስዳለን ማለታቸው፤ ዲያብሎሳዊ እቅዳቸው ምን እንደሆነ አሳብቆባቸዋል። በትንሹም ይሁን በትልቁ ያኮረፈው “አክቲቪስት” ለእነዚህ ሃይሎች፤ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ፤ ጥርጊያ መንገድ እየከፈተላቸው ይገኛል። በዘረኝነት የተለከፈው፤ እራሱን እንደ ተጽእኖ ፈጣሪ አድርጎ የሚቆጠረው ሃይል ደግሞ፤ “ለለውጡ ሂደት” ትዕግስት ማጣቱን በተደጋጋሚ በሚያደርጋቸው ነገሮች አሳይቷል። 

ከሥልጣን ማማ ላይ ከተወረወሩት፤ የቀድሞ ገዥዎቻችን ጀምሮ፤ “ኦሮም አይመራኝም” በሚል ደዌ የታመመው፤ የለውጡ ጀግና እኔ ብቻ ነኝ በሚል “የትራምፓዊ አስተሳሰብ የሰከረው”፤ በግለሰብ ከልት ታሞ፤ እከሌን ነኩብኝ ብሎ ያኮረፈው፤ የለውጡ ሂደት ያልገባው፤ ለውጡ አዝጋሚ እንጂ፤ አብዮት እንዳልሆነ ያልተረዳው፤ ለሚቀጥለው ምርጫ ሳይዘጋጅ፤ “የእናቴ መቀነት አድናቅፎኝ ነው” ለማለት የተዘጋጀው፤ በጫት ደንዝዞ የፖለቲካ ተንታኝ የሆነው፤ መፃፍ ስለቻለ ብቻ “ካለ እኔ ጋዜጠኛ የለም” የሚለው ግብዝ፤ የዲግሪ መዓት ቆልሎ፤ በአዳራሽ ጭብጨባ በመስከር፤ የሃገሩን መሰረታዊ ታሪክ ሳያውቅ፤ እራሱን እንደ ሊቅ ቆጥሮ የሚቀባጥረው፤ ወዘተ፤ ይህ ሁሉ ሃይል፤ በያዘው የብሽሽቅ ፖለቲካ የገመድ ጉተታ፤ ለውጡን አደጋ ላይ ሲጥል እያየን ነው። በተወሰነ ደረጃም፤ በሃሰት ፕሮፖጋንዳ የታጀለው “ዕለታዊ ዜና” የሃገሩን ሰላም እና እድገት በተስፋ የሚጠባቀቀውን ዜጋ፤ በለውጥ ሃይሉ እምነት እንዲያጣ፤ “ሃገሪቱ የተያዘቸው በሴረኞች ነው” ብሎ እንዲቀበል በሚግቱት ‘ሰበር ዜና” ቀቢጸ ተስፋ እንዲሆንም አድርገውታል። 

የሚድያ ባለሙያዎች፤ ሃላፊነት በጎደለው ሁኔታ የሚያቀርቧቸው፤ ቃለ መጠይቆች፤ የሚዘግቧቸው ዜናዎች እና የሚያትሟቸው መጣጥፎች፤ ስለመንግሥት ስልጣን እና ተግባር፤ አስተማሪ ከመሆን ይልቅ፤ ጠብ አጫሪ እና ሁከት ቀስቃሽ መሆናቸውንም ስናስተውል፤ ከልካይ በሌለበት ሜዳ ላይ እየፈነጠዙ መሆናቸውን እንረዳለን። መንግሥት እነዚህን ለምን አያስቆምም የሚለው የብዙዊች ጥያቄ ቢሆንም፤ መንግስት እነዚህን ሃይሎች ሊያስቆምበት የሚችል ሕጋዊ ሥልጣን እንደሌለው የሚረዱ ጥቂቶች ናቸው። ሌላው አወዛጋቢ የሆነው እና፤ በተለይ በማህበራዊ ሚዲያችን የሚንሸራሸረው፤ እንደ ጃዋር መሃመድ ዓይነት ጽንፈኞች ላይ መንግሥት ለምን እርምጃ አይወስድም የሚል ነው።  ብዙዊች መንግሥት እርምጃ ይውሰድ ሲሉ ግን፤ በምን ሕግ እርምጃ እንደሚወስድ አይነግሩንም። ብዙዊች መንግሥት እርምጃ ይውሰድ ሕግ ያስከብር ሲሉም፤ “እነሱ ጠላት ብለው በፈረጁት ሰው ወይም ተቋም ላይ” እርምጃ እንዲወሰድ እንጂ፤ ሕግ እንዲክበር ካላቸው ፍላጎትም አይደለም።

ብዙዊች፤ መንግሥትን የሚወቅሱት እና የሚያወግዙት፤ በሃገር ሰላም እንዲኖር እና የተጀመረው ለውጥ ከግብ እንዲደርስ ቢሆንም፤ የመንግሥት ሥልጣን ከምን ድረስ እንደሆነ፤ የትኛው የመንግሥት አካል፤ ለየትኛው ጉዳይ ተጠያቂ እንደሆነ፤ በግልጽ አያስቀምጡም። የፌደራል፤ የክልል፤ የከተማ እና የቀበሌ የመንግስት አካላትን ሥልጣን እና ተግባር በሚገባ ማወቅ እና መገንዘብ፤ ለምናነሳው ጥያቄም አቅጣጫ ጠቋሚ ይሆናል ብዬ አምናለሁ። አሁን ባለው ሕግ፤ የፌደራል መንግሥቱ፤ እንደፈለገ፤ የፈለገው ክልል ውስጥ ገብቶ፤ ሕግ የማስከበር ሥልጣን የለውም። በየትኛውም የእምነት ጉዳይ ጣልቃ ገብቶም፤ በማንም ላይ እርምጃ ሊወስድበት የሚችል ሥልጣን የለውም። ስለዚህ፤ በክልሎች ለሚፈጠረው ሥርዓተ አልበኝነት ተጠያቂ፤ መሆን ያለበት የክልሉ አስተዳደር እራሱ ነው። በቤተክርስቲያንም ሆነ በማንኛውም የእምነት ተቋማት ውስጥ ለሚፈጠር የውስጥ ሕግና ደንብ ጥሰት፤ መፍትሔ መፈለግ ያለባቸው፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የእምነት ተቋማቱ ናቸው። ሌላው ደግሞ በመናገር መብት ላይ ያለው ብዥታ ነው። ዜጎች፤ የመናገር መብታቸው ይከበር ሲባል፤ የተውሰኑ ሰዎች፤ የንግግር መብት ይገደብ ማለት አይደለም። መንግሥት፤ የተወሰኑ ሰዎችን መብት ማክበር፤ የሌሎችን ደግሞ የመጣስ ሥልጣን የለውም። እንደ ጃዋር ዓይነት ጽንፈኞች፤ የመናገር መብት አላቸው። እነሱ ባነጠሱ ቁጥር ግን፤ ጉንፋን የሚይዘው ሰው ካለ፤ “ለጉንፋኑ”፤ መንግሥትን ተጠያቂ ሊያደርግ አይገባም። በማንኛውም ወቅት፤ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የሚያጋጭ ቅስቀሳ ካደረጉ፤ የሚመለከተው አካል እርምጃ እንዲወስድ መረጃውን በማቀበል መተባበር፤ እንዲሁም በእነዚህ ሃይሎች ቅስቀሳ፤ ጉዳት የደረሰበት ወገን፤ በራሱ አነሳሽነት ፍርድ ቤት በመክሰስ ማስቀጣት፤ ይችላል።

ማዕከላዊ መንግሥቱ አቅም እንዲያጣ ያደረገው የሃገሪቱ ሕግ ቢሆንም፤ በተለይም፤ የቀድሞ ገዢዎቻችን “ዲጂታል ወታደሮች”፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከጽንፈኞች ጋር በማስተሳሰር፤ በለውጡ ላይ ተስፋ እንድንቆርጥ ተግተው ቢሰሩም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ማንም ጽንፈኛ ባነጠሰ ቁጥር፤ “መሃረብ የማያቀብሉ”፤ በራሳቸው የሚተማመኑ መሪ መሆናቸውን በተደጋጋሚ አሳይተዋል። ዛሬ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የተፈጠረውን ውዝግብ፤ ከሚገባው በላይ በመለጠጠ፤ ያበጠችውን ሜዳ፤ እንደ ተራራ አግዘፈው፤ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ፤ የፖለቲካ ካባ ለማልበስ የሚደረገው ሩጫ አደጋው ለሁሉም ነው። የቤተክርስቲያን መሪዎች፤ በመግለጫቸው፤ የመንግሥት ባለሥልጣናት፤ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመከፋፈል፤ እየሰሩ ነው ቢሉም፤ ማነኛው የመንግሥት ባለሥልጣን መሆኑን አለመጥቀሳቸው፤ ወቀሳቸውን ጭብጥ የለሽ ያደረገዋል። ሲጀመርም፤ ቤተ ክርስቲያን በራሷ ጉዳይ፤ መንግሥትን ጣልቃ እንዲገባ ጋብዛ፤ በሶሻል ሚድያ ግን፤ ምዕመናን “መንግሥት ከቤተ ክርስቲያን ጉዳይ እጁን ያንሳ” ብለው ሲያስተጋቡ ማየት እና መስማት፤ በምዕመናኑ እና በቤተ ክርስቲያን መሪዎች መካክል ያለውን ልዩነት ያሳያል። የኦርቶዶክስ ቢተክርስቲያን የውስጧን ሕግ የሚጥሱ አገለጋዮችንም ይሁን ምእመናን፤ ሕጓ በሚፈቅደው መሰረት እርምጃ መውሰድ ይኖርባታል። መንግሥት በቤተክርስቲያን ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ምንም ሕጋዊ ሥልጣን የለውም። ይህንንም ለምእመናኑ በግልጽ ማሳወቅ ያስፈልጋል። ከዚህም አልፎ፤ በቤተክርስቲያኒቱ ላይ ጉዳት አደረሱ የሚባሉ ባለሥልጣናት ሥም እና ያደረሱት ጉዳት በግልጽ ለሕዝብ ይፋ መሆን አለበት። ይህ ሲሆን ብቻ ነው፤ የሕግ የበላይነት ሊኖር የሚችለው እና ለወደፊትም ማንም በቤተ እምነት ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገባ ትምህርት የሚሆነው።  የቤተ ከርስቲያኒቱ አመራር፤ በጉዳዩ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያላቸውን አገልጋዮቹን በማነጋገር፤ እና ገፍቶም ከሄደ አስፈላጊውን ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ ማስቆም የሚችልበትን ሕጋዊ መንገድ ሁሉ ቢጠቀም፤ አሁን ያለውን የፖለቲካ ትኩሳት ያበርደዋል። ለዚህች ሃገር፤ ሃላፊነት እና ግዴታ ያለበት መንግሥት ብቻ ሳይሆን ሁላችንም ነን። ሁላችንም የድርሻችንን እንወጣ፤ የእያንዳንዱን የመንግሥት ተቋም ሕጋዊ ሥልጣን እና ሃላፊነት ምን እንደሆነ እንገንዘብ፤ በተለይ ደግሞ አሁን ያለው ሕገ መንግሥት የማዕከላዊ መንግስቱን ያዳከመ በመሆኑ፤ ሕገ መንግሥቱ፤ በሃገራችን ላይ፤ እስካሁን ያደረሰውን ጉዳት ተገንዝበን፤ ሊቀየር የሚችልበትን መንገድ በቅንነት እንነጋገር። 

ቸሩ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ይባርክ።

መልካም አዲስ ዓመት ለሁላችንም። ዘመኑን፤ የይቅርታ፤ የመተሳሰብ፤ እና የመተባበር ያድርግልን።            

ማስታወሻበዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
12,864FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here