spot_img
Thursday, May 30, 2024
Homeነፃ አስተያየትየአማራ ብሄርተኝነት ስንክሳር እና ያዘለው አደጋ (በመስከረም አበራ)

የአማራ ብሄርተኝነት ስንክሳር እና ያዘለው አደጋ (በመስከረም አበራ)

በመስከረም አበራ
መስከረም 14 2012 ዓ ም

በተማሪዎች እንቅስቃሴ ተፀንሶ የተወለደው የሃገራችን የፓርቲ ፖለቲካ ታሪክ መሰረቱን ያደረገበት ስታሊናዊ ርዕዮተ-ዓለም የዘመኑን ታጋዮች ቀልብ ከሃገራቸው የፖለቲካ አድባር አፋትቶ ከሩሲያ እና ቻይና ጋር ያዋደደ ነበር፡፡ይህ ወደ ራስ ልዩ ሁኔታ በጥልቅ ለመመልከት ፋታ ያልተወሰደበት የፖለቲካ ግልቢያ ነው እስከዛሬ ያላባራ የመከራ ዶፍ በሃገራችን ሰማይ ላይ አዳምኖብን የሄደው፡፡መሰረቱ የተበላሸ ቤት አይፀናምና ከጅምሩ በተንሸዋረረ ትንታኔ ላይ የቆመው የፓርቲ ፖለቲካችን ሁለመና ዛሬ ላይ ሃገራችንን ራሷን ይዟት ሊሄድ በሚችል ህመም ውስጥ ከቷታል፡፡

በዚህ ዘመን ያለን እኛ የፖለቲካችንን ዋነኛ ችግር ተረድተን ለመጭው ትውልድ የምናስረዳበትን ሸውራራ እሳቤ የተረከብነው ከቀደምቶቻችን የፖለቲካ እሳቤ ነው፡፡ሸውራራው የፖለቲካ እሳቤ ከጅምሩ የተቀዳበት ምንጭ  ደግሞ ሰከን ብሎ የታሰበበት፣ሃገራዊ እውነታን ያገናዘበ፣ሙሉ አካል ያለው ትንታኔ አልነበረም፡፡ይልቅስ አንድ አቅጣጫን ይዞ በሚግለበለብ፣ነጥቆ በረርነቱ በበዛ፣ጥራዝ ነጠቅ እውቀት ላይ የቆመ ነበር፡፡ይህ እሳቤ ከወቅቱ ስታሊናዊ የፖለቲካ ፋሽን መምጣት ጋር ውስጥ ለውስጥ ሲብላላ የቆየ ነበር፡፡ቢሆንም ለመጀመሪያ ጊዜ ነፍስ ዘርቶ ስጋ ለብሶ ብቅ ያለው ከአምስት ገፅ በማይበልጥ የዋለልኝ መኮንን ተንታኔ ነው፡፡

ይህ ትንታኔ በኢብሳ ጉተማ “ኢትዮጵያዊው ማን ነው?” በሚል ግጥም ታጅበ፡፡የሩሲያ ቻይና  ማርኪሲስት ድርሳናትን ከማነብነቡ ጋር ተደማመረና ወደ የ1968ቱ የህወሃት ማኒፌስቶነት አደገ፡፡ ትግሉንም ወደ ደደቢት መራው፡፡ይህ ሲባል የዛ ዘመን ትግል ህወሃት ያደረገው የደደቢት ትግል ብቻ ነው ማለት አይደለም፡፡ደደቢት ላይ ማተኮር ያስፈለገው ስሁትነቱ ከስኬት ያላገደው አንድያ ትግል እርሱ ብቻ ስለሆነ ነው፡፡በተጨማሪም አሁን ያለንበትን የፖለቲካ መስመር የመቃኘቱን መልካም ዕድል ያገኘውም ይሄው ስሁት መስመር በመሆኑ ነው፡፡በ1968 የተፃፈው ማኒፌስቶ ውስጥ የተቀመጠው፣ህወሃትን እስከ ዛሬ እየዘወረው ያለው ስሁት መስመር የጀርባ አጥንት ከዋለልኝ መኮንን ጥራዝ ነጠቅ ትንታኔ የሚቀዳ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የአንድ ብሄር(የአማራ) የበላይነት አለ ሲል ያቀረበው ሙሉ አካል የሌለው ስንኩል ትንታኔ ለአንድ ማህበረሰብ ዋና በሆነው የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ረገድ አማራ ሲባል በጅምላ የተጠራው ማህበረሰብ ከበላይነቱ አንፃር የመጠቀሙን ምልክቶች አያሳይም፡፡ፖለቲካዊ አድሎ በሚለው ነገር ላይም ከማለት ባለፈ አማራ መሆን የሚያስኬድበትን እና አማራ አለመሆን የማያስኬድበትን መንገድ አያሳየንም፡፡ከሁሉ በላይ ዘውግ ፖለቲካዊ ህልውና እና ትርጉም ባላገኘበት የሃገራችን የፊውዳል ስርዓት ውስጥ ዘውግን ብቸኛ የትንታኔ መሽከርከሪያ ማድረጉ የዋለልኝ ትንታኔ ዋና ሳንካ ነው፡፡ጡንቻውን ያፈረጠመ ሁሉ ወደ ስልጣን በሚጠጋበት፣ዋናው ጉልበት በሆነበት የፊውዳል ስርዓት ውስጥ ዋናውን (የጉልበተኝነትን ጉዳይ) ግምት ውስጥ ሳያስገባ የሚደረግ ትንታኔ ሙሉ አካል የሌለው ድኩም ሃተታ መሆኑ አይቀርም፡፡ይህን ድኩም ሃተታ ማኒፌስቶው አድርጎ ተጠራርቶ ደደቢት የገባው የአንድ መንደር ጎረምሶች ቡድን ደግሞ የባሰው ድኩም፣ስህተት ደጋሚ፣የሃገር መከራ አስረዛሚ መሆኑ ሳያንስ በለስ ቀንቶት ቤተ-መንግስት መግባቱ የሃገር መከራ እንዳያባራ አድርጓል፡፡ 

የዋለልኝን ድርሳን በልባቸው ፅላት የፃፉት ህዋቶች ብቻ አይደሉም፡፡ይልቅስ ሁሉም የዘውግ ፖለቲከኞች ከህወሃት ባላነሰ ሁኔታ የሚመሩበት ነው፡፡ ህወሃትን እና ሌሎቹን የዘውግ ፖለቲከኞች የሚለያቸው ህወሃቶች ጥርሳቸውን ነክሰው መዋጋት ያስቻለ ብርታታቸው ለቤተ-መንግስት ያበቃቸው ሃሞተ ኮስታሮች መሆናቸው ነው፡፡ይህ ኋለኛው እድፋም ታሪካቸው ሊጋርደው የማይገባው የህወሃት ታጋዮች ውበት ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ኮስታራው ትግላቸውም ሆነ ቅምጥል የስልጣን ዘመናቸው ለኢትዮጵያ የፈየደው በጎ ነገር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም-የሃሪቷን መፀኢ እድል ካለፈችበት የባሰ አስፈሪ ድርጎት ሄደ እንጅ!

የዛሬዋን ኢትዮጵያ በስሁት መንገድ እየነዳ አምጥቶ ገሃነም በር ላይ አስቀምጦ የሄደው የህወሃት ዋና ፈሊጥ አማራ የሚባለውን የኢትዮጵያ ህዝብ በሆነውም ባልሆነውም መክሰስ፣ማክፋፋት፣ቅስም መስበር ነው፡፡ ህገ-መንግስት ሲፅፍ የአማራውን ትምክህት ለመስበር እንደሆነ ለተላላ ሰሚዎቹ ይነግራል፡፡በዘር የተሸነሸነ የአስተዳደር ክልለ ሲመትር አማራው ከተንሰራፋበት የኢትዮጵያ ክልል ተነስቶ ወደጎሬው እንዲገባ፣ከለመደው መግዛት መንዳት እንዲጎድል እንደሆነ ይሰብካል፡፡የመሬትን ባለቤትነት ለብሄር ብሄርሰቦች ሰጠሁ ሲል መሬቱን አማራ እንዳይገዛው እየጠበቅኩላችሁ ነው ሲል እየሰበከ ነው፡፡በዚህ ሁሉ ውስጥ አማራው ንጉስ የጠላው ፍጡር የሚያየውን መከራ ሁሉ አይቷል፡፡የህወሃት የስልጣን ዘመን የተሟሸው አማራው በበደኖ እና አርባጉጉ ባሰማው የሲቃ ድምፅ  ነው፡፡ይህ የሲቃ ድምፅ ለህወሃት የድል ማህተም ነው፤የአማራ አከርካሪ መሰበር፣ላይመለስ ሞቶ ርቆ መቀበር ምልክት ነው፡፡የሰው ልጅ አሰቃቂ ሞት የሰብዓዊ መብት ጉዳይ መሆኑ ቀርቶ የዝቅተኝነት ስሜት ማርገቢያ ሙዚቃ ሆነ፡፡ የአማራው መፈናቀል፣በአንድ ሌሊት ሃብት ንብረት አራግፎ ነፍስ ብቻ ይዞ እግር ወደመራው መትመም አጀብ የማያሰኝ አዘቦታዊ ነገር፣ጆሮ ዳባ ልበስ የሚባል ተገቢ ነገር መሰለ፡፡ ይህ የሆነው ለአጭር ጊዜ አይደለም-ለሩብ ምዕተዓመት እንጅ! 

በሃገራችን መፈናቀል ብርቅ ሆኖ ማነጋገር የጀመረው ከሁለት አመት ወዲህ፣የዘር ፖለቲካው ከአማራው ሌላ ብሄረሰቦችን ቤት ማንኳኳት ሲጀምር ነው፡፡የዘውግ ፖለቲካው ከጨቋኙ የአማር ብሄር በስተቀር ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦችን አስተቃቅፎ የሚያኖር፣ ከአማራ ጭቆና የሚታደግ ድንቅ እድል ተደርጎ ሲሰበክ ኖሯል፡፡የዘውግ ፌደራሊዝሙ ለአማራው ያልተመቸው ደግሞ ሊጨቁን በሃገር ዳርቻ ስለተበተነ ነው የሚል ተረክ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሲተረክ ኖሯል፡፡ይህ ተረክ እውነት አለመሆኑ እየታየ የመጣው በጨቋኝነት የማይታወቁት እንደ ጌዲኦ፣ኦሮሞ ከሶማሌ ክልል፣ከምባታ ከከፋ፣ወላይታ ከሲዳማ በገፍ መፈናቀል ሲጀምሩ ነው፡፡የሆነ ሆኖ ይህ እውነታ የታወቀው እጅግ ዘግይቶ በመሆኑ አማራው ከብዙ አቅጣጫ በሚወረወር ጦር እንዲዋከብ አድርጎት ኖሯል፡፡የዚህ ድምር ውጤት ዛሬ በአስፈሪ ሁኔታ እያደገ የመጣውን የአማራ ብሄርተኝነት ወልዷል፡፡

የአማራ ብሄርተኝነት ጅማሬ?

ባለፉት ሩብ ምዕተ ዓመታት አማራ መሆን ራሱን የቻለ ችግር ሆኖ ኖሯል፡፡በዚህ ዘመን ባለችው ኢትዮጵያ በተለይ ከክልሉ ውጭ የሚኖረው የአማራ ተወላጅ ሰው ቤት እንዳለ ሰው አሳቃቂ ተቆጭው በዝቶ የኖረ ህዝብ ነው፡፡ሆኖም የዚህ ህዝብ እንግልት አደጋውን  በሚመጥን ደረጃ የሚታገልለትነት የአማራ ብሄርተኝነትን ሳይወልድ ቆይቷል፡፡በዚህ ምክንያት የአማራ ህዝብ ብርቱ ጠበቃ በሚያስፈልገው የህወሃት የስልጣን ዘመን ሁነኛ ተሟጋች ሳያገኝ መራራ ፍዳውን በየግሉ ሲጎነጭ ኖሯል፡፡ ይህ ለምን ሆነ ለሚለው ወሳኝ ጥያቄ  ዋነኛው መልስ የህወሃት ጫና ነው፡፡ባለስልጣኑ ህወሃት ከጫካ ጀምሮ የተዋጋለት ዓላማ የአማራውን ቅስም መስበር ነው፡፡ በኋላ ጠቤ ከገዥ እና ነጅው አማራ ጋር ነው እንጅ ከህዝቡ ጋር አይደለም የሚለውን ኢህአዴጋዊ መቀላመድ አምጥቷል፡፡ሆኖም ህወሃት አማራን እንደ ህዝብ እንደ ባለጋራ የሚያይበት ልክፍት እንዳልለቀቀው ማሳያው ብዙ ነው፡፡ ከብዙው አንዱ አፈር ገፊውን አማራ ለዘር ያስቀመጠውን እህል ሳይቀር በቀበሌ ካድሬ እንዲቃጠልበት እያደረገ ሲያፈናቅል፣ይህ ደግሞ ትክክል መሆኑን በፓርላማ ሳይቀር ሊያስረዳ ሲነሳ ነው፡፡

ህወሃት በአንድ በኩል አማራውን በእሾህ ለበቅ እየገረፈም የተበድየ ተረክም ሆነ ተጨባጭ በደል የሚወልደው የዘውግ ብሄርተኝነት በአማራው ዘንድ ብቻ ሲሆን እንዳይበቅልም ወገቡን አስሮ ይሰራ ነበር፡፡ለምን ቢባል የአማራው ብሄርተኝነት ከተወለደና ካደገ አማራን እንደ ጭራቅ እየሳሉ ማስፈራራት አይቻልም፡፡ ይህ ካልሆነ ግንዛቤ የጎደለውን የዘር ፖለቲከኛ በዚሁ አማራ በተባለው ጭራቅ ተፃራሪ አሰልፎ ‘እኔ አማራ ከተባለ ከጭራቅ የማድናችሁ ታዳጊያችሁ ህወሃት እባላለሁ’ እያሉ ስልጣን ማስረዘም አይቻልም፡፡በበኩሌ ህወሃት አማራውን ከኢትዮጵያዊነት ከፍታ አውርዶ ብሄርተኛ አድርጎ ለማሳነስ ሲሰራ ኖሯል በሚለው ሙግት አልስማማም፡፡ይልቅስ ተቃራኒውን አምናለሁ፡፡ ህወሃት የአማራው ብሄርተኝነት አድጎ በህዝቡ ላይ የሚወርደውን በደል ባያስቀር እንኳን በደሉ ስለመድረሱ ሰብዓዊነት ለሚሰማው ሁሉ ክስ እንዳያቀርብ ተግቶ ሲሰራ መኖሩ ትክክለኛ ትንታኔ ሆኖ ይታየኛል፡፡ 

በነገራችን ላይ የማንኛውም ዘውግ ብሄርተኝነት ማደግ የትኛውንም ዘውግ ከመበደል አያድነውም፡፡ለምሳሌ በኢትዮጵያ በአንጋፋቱ ከህወሃትም የሚቀድመው የኦሮሞ ብሄርተኝነት የኦሮሞን ህዝብ ከእስር፣እንግልት፣መፈናቀል መሰደድ፣መሞት ፣መታሰር አላዳነውም፡፡ ያደረገለት ነገር ቢኖር ይህ መከራው ለሰሚ እንዲታወቅ ሪፖርት ማድረግ፣ህዝቡን ለተቀናጀ ትግል ማነሳሳት ነው፡፡ ህዝብን ከፖለቲካዊ በደል የሚታደገው የዘውግ ብሄርተኝነት ማደግ ሳይሆን የዲሞክራሲ ስርዓት መገንባት ብቻ ነው! 

ወደ ቀደመ ጉዳያችን ስንመለስ የአማራ ብሄርተኝነት እንዳያድግ እንቅፋት የሆነው የህወሃት ክርን ነው፡፡ይህ የህወሃት ክርን ለምን አስፈለገ ስንል ሁለት ምክንያት ይኖረዋል፡፡የመጀመሪያውና ዋነኛው የአማራ ብሄርተኝነት ካደገ ህወሃት መወጣጫ አድርጎት ወደ ስልጣን የመጣበትን መሰላል ስለሚያነሳ ነው፡፡ያ መሰላል አማራን እየወቀሱ፣እንዳይመለስባችሁ የምጠብቃችሁ እኔ ነኝ እያሉ ከሌሎች ብሄርሰቦችን የታዳጊነት እምነት አግኝቶ  ስልጣን ላይ መቀመጥ ነው፡፡ ሁለተኛው ጉዳይ የአማራ ብሄርተኝነት ካደገ በአማራው ላይ እየተደፈደፈ ያለውን ለሁሉም የሃገሪቱ ችግር መነሾ የመደረግ የጥፋተኝነት ዳፋ ሃሰትነት ለማስረዳት መነሳቱ፣በሃሪቱ ዳርቻ በአማራው ላይ የሚደረገወውን ግፍ ነቅሶ አውጥቶ ማሳወቁ አይቀርም፡፡

ይህ ሲደረግ ደግሞ በአማራ ክልል ያለው (በመረጃ እጥረት ምክንያት ከክልሉ ውጭ ባሉ ወገኖቹ ላይ የሚደርሰውን በደል ከተባራሪ ወሬ በቀር በተገቢው ሁኔታ ሳያውቅ የኖረው) የአማራ ህዝብ ከሆነበት በደል የተነሳ አዲሱ ወደሆነው የአማራ ማንነት ህብረት መሄዱ አይቀርም፡፡ንዴት የሚቀናው የዘውግ ህብረት ደግሞ ከአማራ ህዝብ  ብረት የማንገት ባህል ጋር ተዳምሮ አማራን ከረዥም ዝምታው ሊያነቃው ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ የአማራውን ነፍስ እንዳለው አካል መንቀሳቀስ የማይወደወን “ገድየ ቀበርኩ” ባዩን ህወሃትን ማስበርገጉ አይቀርም፡፡ስለዚህ ህወሃት የአማራውን መደራጀት በተለየ ትዕግስት ማጣት እንዲያየውና እየተከተለ እንዲያጠፋው አድርጓል፡፡የፕሮፌሰር አስራትን ነፍስ በመብላት ያልተመለሰው የመአድ እና የህወሃት ግብግብ ለዚህ ሁነኛ ምስክር ነው፡፡ መአድ የተደረገበትን ያህል ኦብኮ/ኦፌኮ ያሉ ሌሎች የዘውግ ፓርቲዎች ገና ዳዴ ከማለታቸው የህወሃትን መራራ በቀል አለመቅመሳቸው መአድ በልዩ ሁኔታ ይታይበት የነበረውን የህወሃት ክፉ አይን ለማወቅ ይረዳል፡፡

እንደ መአድ ተወልዶ እንደ መኢአድ ያደገው ፓርቲ ከመነሻው የዘውግ ፓርቲ መሆኑ የግድ እንጅ የውድ እንዳልነበር ማሳያው ብዙ ነው፡፡ አሁንም በየ ድረገፁ የሚገኘው ፕሮፌሰር አስራት በወቅቱ ያደርጉት የነበረው ንግግር ይዘት አንዱ ነው፡፡መሪው የተናገሯቸው የቪዲዮ መዘክሮችም ሆኑ በህይወት ታሪካቸው ዙሪያ የተፃፉ መፅሃፎች የሚያስረዱት የአማራው ብሄርተኝነት መነሻው ከህወሃት የመጣው ክፉ ለበቅ እንደሆ ነው፡፡ የአማራው ትግል መነሻ በአማራው ህዝብ ላይ ያንዣበበውን የህልውና አደጋ መመከት ሲሆን መዳረሻው ደግሞ እኩልነት በሰፈነባት ኢትዮጵያ ከተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በሰላም መኖር ነው፡፡የዚህ ምልክቱ ደግሞ ፓርቲው የአማራን ህዝብ ያንዣበበትን የሞት ጥላ ታግሎ ካስወገደ በኋላ ፓርቲያቸው መኢአድ ወደ ህብረብሄራዊ ፓርቲ እንደሚቀየር በግልፅ ያስቀጡበት መንገድ ነው፡፡ ሆኖም ፕሮፌሰር አስራት የመሰረቱት እና ህይወታቸውን ያጠቱለት መአድ ወደ መኢአድ የተቀየረው አማራውን ከህልውና ስጋት በተግባር መታደግ ችሎ ነው ወይ የሚለው ነገር አጠያያቂ ቢሆንም መአድ ወደ መኢአድ ተቀይሮ አማራውም ሁነኛ ጠበቃ በሚያስፈልገው ጊዜ ምትክ አልቦውን ጠበቃውን ፕሮፌሰር አስራትን ተነጥቆ ክፉውን ጊዜ በየግሉ እንዲጋፈጥ ሆኗል፡፡

ሁለተኛው ዙር የአማራ ብሄርተኝነት እንቅስቃሴ

መአድ በህወሃት ክርን ተደቁሶ ወደ መኢአድ ከተቀየረበት ዘመን ጀምሮ እስከ ህወሃት ለመውደቅ ዘመም ዘመም ማለት ድረስ ባለው ረዥም ዘመን ከየአቅጣጫው እንደ እንጀራ ልጅ ለሚዋከበው የአማራ ህዝብ ጥብቅና የሚቆም ፓርቲም ሆነ ሌላ አይነት ድርጅት በሃገር ውስጥ አልነበረም፡፡ በዚህ ምክንያት አማራው ከአርባጉጉ በደኖ በኋላ ለተከሰተ መንግስት መራሽ ሁለተኛ ዙር ሞት እና መፈናቀል ተዳረገ፡፡ይህ መንግስት መራሽ መፈናቀል በህወሃት መራሹ የአዲስ አበባው መንግስት ቀጭን ትዕዛዝ እንደ ሽፈራው ሽጉጤ እና ያረጋል አይሸሹም ባሉ ተላላኪ አሽከሮቻቸው አጋፋሪነት በጉራ ፈርዳ እና በቤኒሻንጉል የተከወነ ነበር፡፡ህወሃት በአፉ በአልጠላውም የሚለውን የአማራ አርሶ አደር ከገጠር ሲያፈናቅል፣ እንደማይወደው በግልፅ የሚናገረውን የአማራ ምሁር እና የከተማ ልሂቅ ደግሞ ወደ እስርቤት እያጋዘ አስሮ ይገርፍ ነበር፡፡

የሚሰራውን ሲሰራ እንቅፋቱን ሁሉ ቀድሞ ማስወገዱ ላይ የማይሰንፈው ህወሃት የአማራ ብሄርተኝነት እንዳይፀነስ ታጥቆ ይሰራ የነበረው ይህ ሁሉ ግፍ ሲሰራ ለአማራ ህዝብ የሚጮህ እንዳይኖር፣ጠላቴ ያለውን ቤት ዘግቶ ለመደብደብ ነው፡፡ይህ ደግሞ በደምብ ተሳክቶለታል፡፡ማሳያው የአማራን ህዝብ መፈናቀል በተመለከተ ትርጉም ባለው ተቋማዊ መንገድ የሚሞግት አካል አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊነት የሚሰማቸው ግለሰቦች በግላቸው በተለያየ ሚዲያ ነገሩን ለማሳወቅ የሚያደርጉት ጥረት ከጋዜጣ አዘጋጆች ጀምሮ በሚደቀን እንቅፋት ስኬታማ አለመሆኑ ነው፡፡

ሆኖም ተጨባጭ በደል ቀርቶ እውነት እና ውሸትን በዘነቀ ተረክ ለመወለድ የማይቸግረው የዘውግ ብሄርተኝነት ለአማራ ህዝብ ብቻ ሲሆን ከመምጣት አይቀርምና ቢዘገይም የአማራ ብሄርተኝነትም የማታ ማታ መከሰቱ አልቀረም፡፡ይህ ሁለተኛው ዙር የአማራ ብሄርተኝነት ከቀድሞው(ፕሮፌሰር አስራት ይመሩት ከነበረው) የአማራ ብሄርተኝነትነት በብዙ መንገዶች በሚለይ ሁኔታ የተከሰተ ነው፡፡ የመጀመሪያው ልዩነቱ የኋለኛው የአማራ ብሄርተኝነት ያቆጠቆጠው የህወሃት ፈርጣማ ክንድ መዛል በጀመረበት ወቅት መሆኑ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለአማራው ብሄርተኝነት የሁነኛ ባለጋራውን የህወሃትን የቀደመ ክርን ሳይቀምስ በሙሉ አቅሙ እንዲጓዝ  ወለል ያለ መንገድ የሚጠርግ ነውና የብሔርተኝነቱን እድገት ፈጣን አድርጎታል፡፡

ሁለተኛው ልዩነቱ የአሁኑ የአማራ ብሄርተኝነት የተጠነሰሰው ወጣቱ እንደልቡ በማህበራዊ ድረ-ገፅ ተገናኝቶ ከዚህ ቀደም በህወሃት አዝማችነት ከ1968ቱ ማኒፌስቶ ጀምሮ አማራው ላይ የተደረገውን በደል ለማሰላሰል መቻሉ ነው፡፡ይህ ደግሞ ወጣቱ የተበድየ ስነልቦናን በልቡ ማህደር መፃፍ  በቻለበት ሁኔታ ፈጠረ፡፡ለዘውግ ብሄርተኝነት ማደግ ዋና የሆነውን የተበድየ ስነልቦና በተለይ በወጣቱ ዘንድ ማስረፀ መቻሉ ሁለተኛው ዙር የአማራ ብሄርተኝነት ከቀዳሚው በተለየ መልኩ እንዲያብብ አድርጎታል፡፡

በሶስተኝነት ደረጃ የሚጠቀሰው ልዩነት የሁነኛ መሪ ጉዳይ ነው፡፡ቀዳሚው የአማራ ብሄርተኝነት ፕሮፌሰር አስራትን የመሰሉ የሚሞቱለትም የሚቆሙለትም አላማ ያላቸው፣ በቀለም ትምህርት ግንዛቤቸውም አንቱ የተባሉ ሰው የሚመሩት ስብስብ ነበር፡፡ይህ ቀዳሚው የአማራ ብሄርተኝነት ከሁለተኛው ዙር ብሄርተኝነት እጅግ በጣም የሚልቅበትም የሚለይበትም ሁነኛ ልዩነት ነው፡፡ፕ/ሮ አስራት ለአማራው መብት ለመታገል ያበቃቸውን የትግል ምክንያት ጠንቅቀው አውቀው መስህብ ባለው የጨዋ አቀራረብ ማስረዳት የሚችሉ ብቻ ሳይሆኑ ትግላቸው ወደፊት ባሉት አመታት ወዴት እንደሚያመራ ሳይቀር ማስረዳት የሚችሉ ባለግርማ መሪ ነበሩ፡፡በዚህ በእርሳቸው በሳል  ባለ መስህብ መሪነት እና የትግላቸውን ምክንያትን ጠንቅቆ አውቆ እጅግ ጭዋ በሆነ መንገድ ለሌሎች የማስረዳት ፀዳል ሳቢያ ሰብዓዊነት የሚሰማውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ የፓርቲያቸው አባል ካልሆነም ደጋፊ ለማድረግ ችለው ነበር፡፡

በተቃራኒው የሁለተኛው ዙር የአማራ ብሄርተኝነት ባለግርማ መሪ ማግኘቱ ያልሆነለት፣ተረጋግቶ የትግሉን ምክንያት ማስረዳት የተሳነው፣ሊናገር ሲነሳ ቁጣ የሚቀድመው፣ከዘውጉ ውጭ ያሉ ሰብዓዊነት የሚሰማቸውን ሰዎች መሳብ ቀርቶ የትግሉን ምክንያት የሚደግፉ የራሱን ብሄረሰብ ምሁራን ማስጠጋት የተሳነው፣ፖለቲካዊ ብልሃት የጎደለው ደም ፍላታም ንግግር የሚቀድመው፣ወዳጅ ከማበጀት ይልቅ ጠላት የሚያበዛ፣ነጋዴው ከታጋዩ የተደባለቀበት፣አማራነት ሰፍቶበት ገና ከጅምሩ በወሎየ ጎጃሜ፣በተጉለት በቡልጋ፣በደባርቅ ጃናሞራ፣በቆላ በደጋ የሚከፋፈል ሊቀርቡት ቀርቶ ሊሰሙት መስህብ በሌለው ፖለቲካዊ መስተጋብር የተዘፈቀ፣በእርስበርስ ሊፊያ የተመታ፣በመቧካት ፖለቲካ የተጠቃ፣ በአራስ ቤት እንሚሞት ልጅ የመሰለ ነው፡፡     

የመጀመሪውም ሆነ ሁለተኛው የአማራ ብሄርተኝነት እንቅስቃሴ ዋነኛ መነሾ የህወሃት አማራን አይቼ ልጥፋ የሚል ፖለቲካዊ ስሪት መሆኑ ደግሞ ሁለቱን እንቅስቃሴዎች የሚያመሳስላቸው ነገር ነው፡፡የአማራ ብሄርተኛነት መነሾው ይህ የህወሃት ተፈጥሮ ቢሆንም የአማራ የብሄርተኝት ስጋት ግን ህወሃት ብቻ ነው ማለት አይቻልም፡፡እውነት ለመናገር በሃገሪቱ የሚገኙ የዘውግ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉ አማራን ሳይወቅሱ እና ሳይረግሙ የፖለቲካ ትግላቸውን መነሾ ሊያስረዱ ይችላሉ ማለት ዘበት ነው፡፡ስለዚህ የአማራ ብሄርተኝነት ስጋት ሁሉም በሃገሪቱ ያሉት የዘውግ ፓርቲዎች ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ሆኖም በአሁኑ ወቅት ከህወሃት ባላነሰ መጠን ለአማራ ብሄርተኝነት ስጋት ሆኖ ብቅ ያለው የኦሮሞ ብሄርተኝነት ነው፡፡ 

እንደ ህወሃት አማራውን ኢላማ አድርጎ ማኒፌስቶ ባይፅፍም የትኛውም የኦሮሞ ብሄርተኝነት ውድድር ውዝግቡ አማራ ከተባለው አካል ጋር ነው፡፡በኢህአዴግ ወገን የኖረው የኦሮሞ ብሄርተኝነት በኦህዴድ በኩል ስልጣን መያዙ መላውን የኦሮሞ ብሄርተኛ ያስደሰተ ቢሆንም ከኦሮሞ ቀጥሎ በመንግስታዊ ስልጣኑ ላይ በሁለተኝነት የሚታየው አማራ መሆኑ፣ኦሮሞ በያዘው ቤተመንግስት ውስጥ የአማራ አጋፋሪ መታየቱ የሚረብሸው የኦሮሞ ብሄርተኛ ቀላል ቁጥር ያለው አይደለም፡፡በአንፃሩ ኦሮሞ ስልጣን ስለያዘ አማራን ህወሃት ባደረገው መንገድ ይጎዳል ብሎ የሚያስብ የአማራ ብሄርተኛ ቀላል አይደለም፡፡ይህ የጥርጥር እና የፍራቻ እሳቤ መሬት ላይ ካለው የኦሮሞ አክቲቪስቶች እና ፖለቲከኞች ወደ ልቅነት የሚጠጋ እንደልቡ የሆነ ንግግር እና አካሄድ ጋር ሲዳመር አማራው የቀደመ ኢትዮጵያዊ ብሄርኝነቱን ባይተወው እንኳን ችላ ብሎት በአማራነቱ ላይ እንዲያተኩር እያደረገው ይገኛል፡፡

ይህ እያደር እየበረታ የመጣው የአማራ ብሄርተኝነት ታዲያ በቅርቡ የተጀመረውን በዋናነት በአብን በሚመራው የአማራ ብሄርተኝነት ዙሪያ ለመሰባሰብ ሲያመነታ የሚታይበት አጋጣሚ ይበዛል፡፡አብን የሚመራው የአማራ ብሄረተኝነት በዋናነት የሚደገፈው በወጣት አማሮች ሲሆን በእድሜም ሆነ በትምህረት የገፋው አማራ ግን በብሄርተኝነቱ የትግል ምክንያት ላይ ልዩነት ባይኖረውም አብንን ለመቀላቀል ግን ሲያመነታ ይስተዋላል፡፡ ይህ የሆነበት በርካታ ምክንያቶች ሊኖሩ ቢችሉም ከላይ ከፍብለው የተጠቀሱት አዲሱን የአማራ ብሄርተኝነት ተብትበው የያዙ ችግሮች ዋነኞቹ ናቸው፡፡ የአብን የአማራ ብሄርተኝነት ከጅምሩ በዋነኛ መሪዎቹ ሳይቀር የሚነገሩ ፖለቲካዊ ብስለት የሚጎድላቸው ንግግሮች፣ መሪዎቹ በተለያዩ ሚዲያዎች ቀርበው ሲናገሩ የትግላቸውን ምክንያት ጠብሰቅ አድርገው ማስረዳቱ ላይ ላይ  የሚቀራቸው መሆኑ የአማራ ምሁራንን ቀልብ መሳቡ እንዳይሳካላቸው አድርጓል፡፡

በአብን የሚመራው የአማራ ብሄርተኝነት የራሱን ልዩ ፖለቲካዊ ሁኔታ ነቅሶ አውጥቶ በራሱ ቀለም ከመታገል ይልቅ እምብዛም መስህብ የሌለውን የኦሮሞ ብሄርተኞች የትግል ስልት በመድገሙ ላይ የተጠመደ ነው፡፡በአብን የሚመራው የአማራ ብሄርተኝንት ኦነግ ቀመሱን የኦሮሞ ብሄርተኝነት ለመምሰል የሚያደርገው ጉዞዞ ትልቅ ድክመት ያበት ነው፡፡ ይኸውም አምባየ ነው የሚለው የአማራ ህዝብ አንደኛ ከሚያደርገው የኢትዮጵያ ህልውና ጋር የሚላተምበት አጋጠሚም መታየቱ ነው፡፡በማንኛውም ስም የሚጠራ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ኦነግ ወለድ ነው፡፡የኦነግ አንደኛ ደግሞ ኦሮሚያ እንጅ ኢትዮጵያ አለመሆኗን “መጀመሪያ ኦሮሞ ነኝ” በሚለው የትግሉ ዋነኛ መፈክር መረዳት ይቻላል፡፡ይህ ኢትዮጵያዊነቱን አንደኛ አድርጎ ለኖረው እና ቢቸግረው ብቻ አማራነቱን በመለማመድ ላይ ላለው የአማራ ህዝብ ትርጉም ሰጭ አይደለም፡፡በአብን የሚመራው የአማራ ብሄርተኝነት ደግሞ አይኑን የተከለው አርዓያ ባደረገው ኦሮሞ ብሄርተኝነት ላይ እንጅ የአማራን ህዝብ ስነልቦና አገናዝቦ ቆምኩልህ በሚለው ህዝብ ስነልቦና አንፃር አይመስልም፡፡ በዚህ ሳቢያ አብን የአማራ ምሁራንን እና ነፍስ ያወቀውን የዘውጉን ህዝቦች መማረኩ አልሰምር ብሎታል፡፡   

የአማራ ምሁራን እና አዋቂ የዘውጉ ህዝቦች ከህወሃት መሄድ በኋላ ህወሃትን ሊተካ የሚፋትረው የኦሮሞ ብሄርተኝነት አይጠረቄ አካሄድ “ወሎ የእኔ ነው” እስከማለት እንዳደረሰው የሚገነዘቡ ናቸውና እንዲህ ያለውን አካሄድ ለመመከት እንደ አብን ያለ ቁጠኛ የአማራ ብሄርተኝነት መኖሩን ላይጠሉ ይችላሉ፡፡ሆኖም በአብን ስም ለመጠራት የሚወደው የአማራ ምሁር ቁጥር እስከዚህም ነው፡፡የዚህ ምክንያቱ ለአማራ ህዝብ ያለአባት በሆነ መንገድ አብን የሚያሳየው ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን እንደመዋጋትም፣ እንደማጠየቅም የሚቃጣው ኦነግ ቀመስ አካሄድ ነው፡፡ይህ ሄዶ ሄዶ አብንን ከባህር የወጣ አሳ የሚያደርግ ብልሃት አልቦ ጉዞ ነው፡፡የአብን በአማራ ምሁራን ዘንድ ሞገስ ማጣት የኦሮሞ ምሁራንን አግበስብሶ ከያዘው የኦሮሞ ብሄርተኝነት ጋር ለሚያደርገው ውድድር ሚዛን እንዳይመታ ማድረጉ አይቀርም፡፡በዚህ መሃል ከኦሮሞ ብሄርተኝነት መጦዝ የተነሳ የአማራ ብሄርተኝነት እንዲኖር የሚፈልገው የተማረውን ጨምሮ በርካታው የአማራ ብሄር ተወላጅ ወደ አዴፓ እንዲያዘነብል እያደረገ ነው ፡፡

የኢህአዴግ አባል የሆነው አዴፓ ደግሞ በቅርቡ ከእህት ድርጅቶች ጋር ተዋህጄ የሲቪክ ፖለቲካ አራማጅ ፓርቲ እሆናለሁ እያለ ይገኛል፡፡ይህ ውህድ ፓርቲ አማራውን በእጅጉ የሚያስጨንቀውን የኦሮሞ ፖለቲከኞች በአግላይነቱ ህወሃትን የሚያስመኝ፣ለሰብዓዊ መብቶችም ሆነ ለዲሞክራሲያዊ እና ህጋዊ ድንጋጌዎች ቁብ የማይሰጠውን የኬኛ ፖለቲካ ሃይ ማለት መቻል አለበት፡፡ውህዱ ፓርቲ ይህን ማድረግ ከቻለ አማራው ለመልበስም ለማውለቅም የተቸገረበትን የአማራ ብሄርተኝነት ካባ አውልቆ ጥሎ የለመደውን እና የሚያምርበትን የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ለመልበስ የሚያመነታ ህዝብ አይደለም፡፡ ይህ ገቢራዊ ከሆነ በቁጡነቱ ስሙ በክፉ የሚነሳውን አብንንም ሆነ ኮበሌ ደጋፊዎቹን ሳይቀር ማሳመን የሚችል የኢትዮጵያ የመዳኛ መንገድ መሆን ይቻለዋል፡፡ 

ይህ ሳይሆን ቀርቶ ውህዱ ፓርቲ በሲቪክ ፖለቲካ ስም ለተረኛ ነኝ ባዩ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ሸብረክ የሚል ከሆነ የአማራ ምሁራንም ሆኑ ሌላው አብንን ለመቀላቀል እየተሸኮረመመ ያለው አማራ ጓዙን ጠቅልሎ ወደ አክራሪ ብሄርተኝነት መንጎዱ አይቀርም፡፡ይህ ደግሞ የአማራ ክልልን ምናልባትም ታጣቂ ሸማቂዎች ጭምር የሚንቀሳቀሱበት ግልፅ የአመፅ ቀጠና ሊያደርገው ይችላል፡፡የዚህ ምክንያቱ ኢትዮጵያን ከማለት የመነጨው የአማራ ህዝብ ትዕግስት ተሟጦ “ስንት ጊዜ እከዳለሁ?” ወደሚል ቁጭት ሊቀየር መቻሉ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ጫካ እያለም ሆነ ስልጣን ላይ በወጣ ማግስት የአማራን ህዝብ በጠላትነት ፈርጆ ሲንቀሳቀስ የነበረውን ህወሃትን አብልቶ አጠጥቶ፣ደጀን ሆኖ አዲስ አበባ ያስገባው የአማራ ህዝብ ነው፡፡የህወሃት መልስ ግን ምን እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡

ህወሃትን ከአድራጊ ፈጣሪነቱ ያነሳው የአሁኑ ለውጥ እንዲመጣም በውስጠ ፓርቲ ትግሉ ወቅት የአማራው ወኪል ነኝ የሚለው ብአዴን ያደረገው አስተዋፅኦ ከተወራው በላይ ነው፡፡አሁን የመጣው ለውጥም ህወሃት እንዳደረገው የአማራውን አስተዋፅኦ ገደል ወርውሮ የተረኝነት ልግዛ ልንዳ ባይነትን መልሶ ሊያመጣ ከዳዳው የአማራ ብሄርተኝነት ተቀጣጥሎ የሚያመጣው ወላፈን የኢትዮጵያ ብሄርተኝነትን ክፉኛ ሊጎዳ የሚችል ግፋ ካለም የሃገሪቱን ህልውና የሚፈታተን አደጋ ይዞ የሚመጣ ይሆናል፡፡ስለዚህ ኢትዮጵያን ለማዳን የሚሰራ ስራ ሁሉ መጨረሻው እኩልነትን ከማስፈን፣ዲሞክራሲያዊ ስርዓትም ከመገንባት ውጭ በሌላ መንገድ መሄድ ከጀመረ ሃገር ላይ እሳት ለኩሶ መልቀቅ እንደሆነ ሊረዳ ይገባል፡፡ትክክለኛውን የእኩልነት ጉዞ ለመጓዝ፣ሃገርንም እንደጧፍ ከመንደደ ለመታደግ ምን መደረግ አለበት፣ሃገራችን ወደ ዲሞክራሲያዊ የእኩልንት መንገድ እንዳትሄድ ዋነኛ አደጋ የጋረጠውስ ማን ነው? የሚለውን ለመዳሰስ ሳምንት ልመለስ፡፡       

ማስታወሻበዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here