
መስከረም 16 ቀን 2012 ዓም(25-09-2019)
የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የኢትዮጵያ የነጻነትና የአንድነት ምሰሶ ናት
አገራችን ኢትዮጵያ ባስመዘገበችውና ባለፈችበት የረጅም ዘመን ታሪኳ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለአገራዊ ምስረታ፣ለሕዝብ ሰላምና አንድነት ከፍተኛውን ድርሻ አበርክታለች።የቦታ እርቀት፣የተፈጥሮ ውጣ ውረድ፣የጎሳና የቋንቋ መሰናክል ሳያግዳት አቅም በፈቀደው መጠን ከዳር እስከዳር ተንቀሳቅሳ ለኢትዮጵያውያን በሙሉ ብቻ ሳይሆን በፋሲፊክ ዳርቻ ለሚገኙ አገሮች ምእመናን ጭምር የፈጣሪን ቃልና ትእዛዝ፣የብሉይና የአዲስ ኪዳንን መልእክቶች ስታደርስ፣ፈሪሃ እግዚአብሔርን፣ ስነምግባርን፣ሰብአዊነትን፣ከማስተማሩዋም በላይ መሃይምነትን ለመቅረፍ ኢትዮጵያውያን ፈላስፋዎች የፈጠሩትን ፊደል ተረክባ አስቆጥራለች።
የውጭ ጠላት አገር ለመውረር በመጣ ጊዜም ከመንፈሳዊ አግልግሎት በተጨማሪ እንደ አንድ የወታደር ተቋም በጦር ሜዳ ታቦት ይዛ ዘምታለች።በሰላም ጊዜ እንደምምህር፣ በጦርነት ወቅትም እንደ ወታደር ሆና የኢትዮጵያን ነጻነትና ዳር ድንበር አስከብራለች።በዚህም ተጋድሎዋ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጥርሳቸውን ነክሰው የምትጠፋበትን መንገድ ሲያወጡና ሲያወርዱ ኖረዋል።
በዚህ መንፈሳዊና የዜግነት ግዳጅ ከዃላ የመጣውና የተስፋፋው የእስልምና እምነት ተቋም ከጎኑዋ ተሰልፎ ብሔራዊ ግዳጁን ፈጽሞዋል።የሁለቱም ሃይማኖቶች መሪዎችና ተከታዮች በአንድ አገር ልጅነት እጅ ለእጅ ተያይዘው የመጣባቸውን የጋራ ጠላትና የገጠማቸውን የጋራ ችግር በጋራ በማሶገድ የአገራቸውን ነጻነትና ህልውና አስከብረዋል።በአድዋና በማይጨው ጦር ሜዳ ጎን ለጎን ሆነው ጠላትን ሲዋጉ ምትክ የሌለው ህይወታቸውን ገብረዋል።
የውጭ ሃይሎች ሕዝቡን በቋንቋና በሃይማኖት ከፋፍለው እርስ በርሱ እንዲጋጭና በድክመቱ አገሪቱን ለመያዝ ያደረጉት ሙከራ በሁለቱም የእምነት ተከታዮች እምቢባይነት ሳይሳካ ቀርቶ ኢትዮጵያ የባርነት ቀንበር ሳያርፍባት ነጻነትዋን አስከብራ እንድትኖር አብቅቶዋታል።ዛሬም የነዚሁ የውጭ ሃይሎች መሰሪ ተግባር አልቆመም።በተለይም ላለፉት አርባ ዓመታት በብሔር ነጻነትና እኩልነት ስም የሚንቀሳቀሱ የውስጥ አርበኞቻቸውን በማደራጀትና በመርዳት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ከመቸውም ጊዜ በላይ ተጠናክረው የአገራችን አንድነትና ሰላም ከፈተና ላይ ወድቆ ይገኛል።በተለይም ለአንድነት ፊታውራሪ በሆነችው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይና በአማራው ማህበረሰብ ላይ ጥቃቱ ገዝፎ ይገኛል።በዚህ የተወጠነ የጥፋት ዘመቻ አያሌ ቤተክርስቲያንና ገዳማት ተቃጥለዋል፣ንብረቶች ወድመዋል፣ተዘርፈዋል።መነኮሳት፣ቀሳውስትና ምእመናን በጠራራ ጸሃይ በሚዘገንን ሁኔታ ተጨፍጭፈዋል፤በድንጋይ ዘመን የጥቃት መሳሪያ ተደብድበዋል፤ክቡር ሰብአዊ አካላቸው እንደ እንጨት በእሳት ተቃጥሎ አመድ ሆኑዋል።አሁንም ጥቃቱ አልቆመም።መንግስት ተብየውም ሥልጣን ላይ የተቀመጠው ቡድን የነውጠኞቹንና የጸረ አንድነቱን እኩይ ተግባር አይቶ እንዳላዬ ሰምቶ እንዳልሰማ አልፎታል።ወንጀለኞቹን አሳዶ በመያዝ ለሕግ ማቅረብ፣ለተጠቂው ወገን የመከላከያ አቅም መፍጠር ሲገባው የአዞ እምባ እዬረጨ ሰልፉን ከወንጀለኞቹ ጋር አድርጉዋል።
በደልና ግፍ የተፈጸመበት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ተከታይ ሕዝብ ግን ለሰላምና ለይቅርታ ያለውን ስነልቦና እየተፈታተነው በመምጣቱ ዝምታውን ሰብሮ በአደባባይና በደጀሰላም ወጥቶ ድምጹን በማሰማት ላይ ይገኛል።በዚህ ሰላማዊ ትግሉ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ የሆኑት ኢትዮጵያውያን ወገኖቹም አብረውት በመሰለፍ የኦርቶዶክስ ተዋህዶን መንካትና ማጥቃት እኛን መንካትና ማጥቃት ነው፤የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ማለት የአገራችን አንድነት ምሰሶ ማለት ነው፤ምሰሶው ከፈረሰ ሁላችንም አገር አልባ እንሆናለን!ለሃይማኖታችን ከለላና ጣራ ሆና የኖረችው ኢትዮጵያ አገራችን በነውጠኞችና በውጭ ጠላቶች ሴራ አትፈራርስም!በማለት አረንጉዋዴ፣ቢጫና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለቡ በወሎ እራያና አዘቦ፣በወረኢሉና ቦረና፣በአፋር፣በጎጃም፣በጎንደር፣በሸዋ፣በአዲስ አበባና በተለያዩ የክፍላተሃገር ከተሞች አደባባይ ላይ ወጥተው አንድነታቸውን አሳይተዋል፤በማሳዬትም ላይ ናቸው።የደመራ በዓል የሚከበርበትንም ቦታ በማጽዳትና በማዘጋጀት ከክርስቲያን ወገኖቻቸው ጋር ተሰልፈዋል።
ይህንን የሕዝብ አንድነትና አብሮነት የኢትዮጵያ ክፍላተ ሃገር ህብረት ከልብ እያደነቀ፤በጠላቶች ሰርጎ ገቦች ተንኮል እንዳይቦረቦር በተደራጀ መልክ በቀጣይነት እንዲመራ ለማሳሰብ ይወዳል።የአፍራሽና የነውጠኞች የጉልበት ጥቃት በሰላማዊ ሰልፍ ብቻ ሊገታ ስለማይችል ተመሳሳይ የመከላከያ ዘዴ መፈጠርም እንዳለበት ለማሳሰብ ይወዳል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንና የእስልምና ሃይማኖት ተቋማትና ተከታዮች ለአገራቸው ነጻነትና አንድነት፣ለሰላምና ለሕዝብ አብሮነት የሚያደርጉትን መደጋገፍና የተባበረ ትግል ያደንቃል።
አገሪቱን እመራለሁ የሚለው በሥልጣን ላይ ያለው ቡድንም በሕዝብ ላይ ለሚደርሰው ጉዳትና በአገሪቱ ላይ ለሚደርሰው ጥፋት ተጠያቂ መሆኑን እያስገነዘበ፣እንደ መንግሥትም ሕግና ፍትህ እንዳይጓደል ፣ወንጀለኞች በሰሩት ወንጀል እንዲጠየቁ፣የተበደሉት ወገኖች የሚካሱበት ደንብና መመሪያ በመከተል ሃላፊነቱን እንዲወጣ ይጠይቃል።ሕዝብ በዬአቅጣጫው ለሚያነሳው ጥያቄ ተገቢ መልስ መሰጠት እንዳለበት ያምናል።
ለወደፊቱ የአገርን አንድነት ፣የሕዝብን ሰላምና አብሮነት የሚፈታተን ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይከሰት በሃይማኖትና በጎሳ ስም የፖለቲካ ድርጅት መፍጠርና መንቀሳቀስ በሕግ እንዲታገድ ይጠይቃል።አገራችንን ለውድቀት ሕዝቡንም ለእርስ በርስ ግጭት፣መፈናቀልና ስደት ያበቃው ጎሳና ቋንቋን መሰረት ያደረገው የክልል አወቃቀር ስለሆነ በአስቸኳይ ተወግዶ በክፍላተሃገር የአስተዳደር መዋቅር እንዲተካና የፌዴራል ትስስሩም በዚያው መልክ እንዲሆን ያሳስባል፤ለዚያም ይታገላል።ለትግሉ ቀጣይነት ከዚህ በታች ባለው የግጥም ስንኞች ጥሪውን ያስተላልፋል።
ስማኝ ያገሬ ሰው ባንድ ላይ ተነሳ ፣
ድር ከተባበረ ይጥላል አምበሳ።
እስላም ወይ ክርስቲያን ሳይባል በሙሉ፣
የጎሳ ልዩነት ሳይኖር በመሃሉ፣
ያገርን ነቀርሳ መንቅላችሁ ጣሉ።
እስላም ክርስቲያን ባንድ ተሰለፍ፣
አገር ለማዳን ሕዝብ ለማትረፍ።
ተያያዝና እጅ ለእጅ፣
አገር አቆዬው ለልጅህ ልጅ፣
ክልልና ዘር ይጎዳል እንጂ ምንም አይበጅ።
ከሃይማኖት ፊት የኖረች አገር፣
እናት ኢትዮጵያ ዘላለም ትኑር።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ና የሙስሊሙ የህብረት ትግል ይለምልም!
ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የሚቅበዘበዙ ሃይሎች በሕዝብ ትግል ይደመሰሳሉ!!
የኢትዮጵያ ክፍላተ ሃገር ህብረት