spot_img
Sunday, July 21, 2024
Homeነፃ አስተያየትበሳይንስና በፍልስፍና መነፅር መታየት ያለባቸውና መልስ የሚያስፈልጋቸው የብሄረሰብ፣ የጭቆናና የማንነት ጥያቄዎች !!...

በሳይንስና በፍልስፍና መነፅር መታየት ያለባቸውና መልስ የሚያስፈልጋቸው የብሄረሰብ፣ የጭቆናና የማንነት ጥያቄዎች !! (ፈቃዱ በቀለ -ዶ/ር)

ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)
መስከረም 21 2012 ዓ ም (ጥቅምት 02 ፣  2019)

መግቢያ

እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ ወደ ኋላ በቀሩ አገሮች ውስጥ በሃይማኖትና በብሄረሰብ ስም ተሳቦ በየጊዜው የሚነሳው መጋጨትና እንዲያም ሲል መገዳደል ዋናው ምክንያት ሌላ ነገር ሳይሆን በእነዚህ አገሮች ውስጥ መካሄድና መደረግ ያለበት መንፈሳዊ ተሃድሶ ከቁም ነገር ውስጥ ስለማይገባና ስላልተካሄደም ነው። በተለይም የፖለቲካ ስልጣንን የጨበጡና ሀብትን አካብተው የተንደላቀቀ ኑሮ የሚኖሩና፣ ወይም ደግሞ ስልጣን ላይ ለመውጣት የሚታገሉና በውጭ ኃይሎች የሚደገፉ አንዳንድ የነፃ አውጭ ድርጅት ነን ባዮች ጥቃቅን ልዩነቶችን እየፈለጉና ከሌላው በልጠው ለመገኘት ሲሉ የማያስፈልግና ሳይንሳዊ መሰረቶች የሌላቸውን ቃላቶችን በመወርወር አንደኛው የህብረተሰብ ክፍል በሌላው ላይ እንዲነሳ በማድረግ በቀላሉ ሊገታ የማይችል ግጭት ወይም የወንድማማቾች መተላለቅ እንዲፈጠር ለማድረግ ይበቃሉ። 

በተለይም የህብረተሰብን ታሪክና ውጣ ውረድነትን በተጣመመ መልክ በመተርጎምና፣ የሚኖሩበትን ህብረተሰብ ከሌሎች አደጉ ከሚባሉት አገሮች ጋር ሳያነፃፅሩ፣ ጭቆናና በደል ደርሶብናል፣ ወይም የአንድ ጎሳ የበላይነት የሰፈነበት ነው በማለት ከሀቁ የራቀ ነገር በማውራት ልዩነቱ እንዲሰፋ፣ መጠራጠር እንዲኖርና የመጨረሻ መጨረሻ በቀላሉ እልባት የማያገኝ ጦርነት እንዲቀሰቀስ የማይጭሩት እሳት የለም። ጭቆና የሚባለው ነገር በእኛ አገር ብቻ ያለ ነገር አድርገው በማቅረብና በማናፈስ መሰረታዊ ከሆኑ ጥያቄዎች በመሸሸ አንድ ምስኪን ህዝብ በቀላሉ ሊወጣ የማይችለው ማጥ ውስጥ እንዲገባ ሁኔታውን ያመቻቻሉ። በዚህም ምክንያት የተነሳ የሰው አስተሳሰብ፣  በተለይም ደግሞ የወጣቱ ጭንቅላት በማያስፈልግ አስተሳሰብ በመጠመድ ተግባሩ ወደ ጠብ ጫሪነት እንዲያመራ ይደረጋል። ለዕውነተኛ ነፃነት መሰረት ከሆነውና በራስ ላይ ዕምነት ከሚያሳድረው ሳይንሳዊ ዕውቀት እንዲሸሽ በማድረግ ደሃና ኋላ ቀርቶ እንዲኖር ያደርጋሉ። 

ይህ ብቻ ሳይሆን፣ አንዳንድ አገዛዞች በደንብ ሳያገናዝቡ ተግባራዊ የሚያደርጓቸው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎች፣ እንዲሁም ካለአግባብ ሀብት ማካበት ለድህነትና በራሳቸው ለሃይማኖትና ለብሄረሰብ ግጭት ምክንያት ይሆናሉ። ምክንያቱም ከውጭ የሚመጡ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ዕውነተኛና የተስተካከለ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ዕድገት ስለማያመጡ ሆድ የባሰው ወጣት መሸሸጊያ የሚያደርገው የብሄረሰብንና የሃይማኖትን ጥያቄዎች በማንገብ ነው። የአገራችን ታሪክ እንደሚያረጋግጠው መንግስታቶቻችን በውጭ ኃይሎች እየተመከሩ ተግባራዊ የሚያደርጓቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሙሉ የስራ-አጥነትን ወይም ፈትነትን የሚቀንሱ ሳይሆኑ በራሳቸው ለችግሩ ተጨማሪ ምክንያት በመሆንና በአንድ አገር ውስጥ የተዛባ ሁኔታ በመፍጠር ህብረተሰብአዊ ቅራኔ እንዲከሰትና እንዲሰፋ ለማድረግ በቅተዋል። በዚህ መልክ ካለብዙ ግንዛቤና ንቃተ-ህሊና መዳበር ጉድለት የተነሳ የሚወሰዱ እርምጃዎች አንዱን ብሄረሰብ የሚጠቅሙ፣ ሌላውን ደግሞ የሚጎዱ ተደርገው በመተርጎም የራሳቸውን አጀንዳ ዕውን ለማድረግ ለሚፈልጉ ጥቂት ኃይሎች ወይም ኤሊት ነን ለሚሉት አመቺ ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል።

ዛሬ በአገራችን ምድር በብሄረሰብና አልፎ አልፎ በሃይማኖት ስም ተሳቦ በወንድማማቾች መሀከል የሚከሰተው አለመግባባትና ደም መፋሰስ በውጭ ኃይሎችና፣ የዚህም ሆነ የዚያኛው ብሄረሰብ ኤሊቶችና እኛ ነን መሪህ በሚሉ የተጠነሰሰና የተስፋፋ ነው። የጭቆናና የመበደል ጉዳዮች የሚነሱትና እንደልዩነት የሚራገቡት በእርግጥም በድህነት ዓለም ውስጥ ከሚኖረው ምስኪን ህዝባችን ሳይሆን፣ ጥያቄዎች የሚነሱት የተንደላቀቀ ኑሮ ከሚኖረውና ራሱ ሳይገባው ከውጭ የሚመጡ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ በማድረግ የራሱን ህዝብ ወደ ድህነት ዓለም ውስጥ ከሚገፈትረው ይኽኛውን ወይም ያኛውን ብሄረሰብ እወክላለሁ ከሚለው ኢሊት ነው። እንደዚህ ዐይነቱ ኤሊት በእርግጥም የሚታገለው እወክለዋለሁ ለሚለው ብሄረሰብ ሳይሆን የውጭ ኃይሎችን ጥቅም ለማስጠበቅ ነው።  የውጭ ኃይሎች ደግሞ እንደዚህ ዐይነቱን ግራ የተጋባና ያልተገለጸለትን ኤሊት በጥቅም በመግዛት ልዩነቱ እንዲሰፋና የድህነቱም ዘመን እንዲራዘም ያደርጋሉ። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያለች የረጅም ጊዜ ታሪክ፣ የተሟላ ቋንቋና ልዩ ልዩ የሚያማምሩ ባህሎችና እጅግ የሚያምር መልከዓ-ምድር ያላት አገር በሳይንስና በቴክኖሎጂ ማደጓን ስለማይፈልጉ አለ የሚባለውን የብሄረሰብ ልዩነት ተገን በማድረግ ህዝባችን ተንሳፎና ግራ ተጋብቶ እንዲኖር የማይፈጥሩት ተንኮል የለም። መሳሪያ የሚሆናቸውም ከዚህ ወይም ከዚያኛው ብሄረሰብ የተውጣጣና ግራ የገባው ኤሊት ነኝ የሚለው ኃይል ነው። ከጥቅሙ በስተቀር አርቆ ማሰብ የማይችልና በውጭ ኃይሎች ቡራኬ የሚኖረውና የሚጠመዘዘው ዋናው ተግባሩም ሳይንስን፣ ፍልስፍናና ልዩ ልዩ የዕውቀት ዘርፎችን በማዳበር የዕድገት ኃይል ከመሆን ይልቅ ጥቁር ወንድሙንና እህቱን ሰላም መንሳት ነው። ኃይላቸውን ሰብሰብ አድርገው በአንድነት አገራቸውን እንዳይገነቡና በዓለም ህዝብ ፊት ተከብረው እንዳይኖሩ ማድረግ ነው።   

ከዚህ አደገኛና አገራችንን ወደ ዲንጋይ ዘመን ሊለውጣት ከሚችለው ሁኔታ በመነሳት፣ ለምን በእንደዚህ ዐይነቱ ኤሊት በተለይ፣ በአጠቃላይ ደግሞ በጠቅላላው ኤሊት ነኝ በሚለው ዘንድ  የሃሳብ መዘበራረቅ በመፈጠር አንድን አገር የጦርነት አውድማ አድርጎ የታሪክ ቅርስን ለማጥፋት የሚደረገውን አደገኛ አካሄድ ለማሳየት እሞክራለሁ። ክዚህ በመነሳት ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ ባልሆነ አስተሳሰብ ያልታነፀ ጭንቅላት ለምን ለጦርነትና ለአገር ውድመት ምክንያት እንደሆነ በንፅፅራዊ አገላለጽ ለማረጋገጥ እሞክራለሁ። ለዚህ ዐይነቱ ንፅፅር ሊጠቅመን የሚችለው የአውሮፓው የህብረ-ብሄር አወቃቀርና የካፒታሊዝም በአሸናፊነት መውጣትና ዛሬ የዓለምን ህዝብ የመኖርና ያለመኖር ዕድል መወሰንን እንደመነሻ በመውሰድ ነው። ስለሆነም ከአገራችን ይልቅ በአውሮፓ ምድር የበለጠ ደም መፋሰስና ጭቆና እንደነበርና የአውሮፖው ህዝብ ከብዙ መቶ ዓመታት ጦርነትና መፈናቀል በኋላ ራሱን በራሱ በማግኘት አነሰም በዛም ውስጠ-ኃይሉ ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚና ማህበረሰብ እንደገነባ መገንዘብ ይቻላል። ለዚህ ደግሞ ኃይልና የማያቋርጥ ጦርትነት ሳይሆን  የመጨረሻ መጨረሻ ዋናው የዕድገት አንቀሳቃሽ ኃይል፣ የሃሳብ ጥራትና በሃሳብ ዙሪያ የተደረገ ምርምርና ክርክር ለህብረተሰብ ዕድገት ወሳኝ ሚናን እንደተጫውቱ መገንዘብ ይቻላል። ክዚህ ስንነሳ እንዴት የአውሮፓው ህብረተሰብ የፍልስፍና፣ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ የማቲማቲክስ፣ የሊትሬቸርና የድራማ፣ እንዲሁም ከጭንቅላት ውስጥ የሚፈልቁ የልዩ ልዩ ዕውቀቶች ባለቤት በመሆን የበላይነትን ሊቀዳጅ እንደቻለ በተቻለ መጠን ማየት ይቻላል። በዚህም መሰረት ተንኮል፣ አጉል ጥላቻ፣ መናናቅ፣ ስራን አለማክበር፣ በዲስፕሊን አለመስራትና ኃላፊነት አለመሰማት እንዳሉ ተወግደው የእውሮፓው ማህበረሰብ በካፒታሊዝም የሚገለጽ ዕድገት ባለቤት ለመሆን እንደበቃና ዓለምን እንደሚያሽከረክራት መረዳት ይቻላል።

ሙሉውን በፒዲኤፍ ፋይል ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

___

ማስታወሻበዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here