spot_img
Wednesday, March 22, 2023
Homeነፃ አስተያየትግልጽ ደብዳቤ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ሥልጣናቸውን ይልቀቁ። (ከጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ)

ግልጽ ደብዳቤ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ሥልጣናቸውን ይልቀቁ። (ከጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ)

- Advertisement -

ከጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ
መስከረም 24 ቀን 2012 (10/05/2019)

” …የኦሮሞ ህዝብ እዚህ ከተማ ነው የተሰበረው እዚሁ ነው መገፋት የጀመረው በዛ ዘመን የነበሩት እነ ቱፋ ሙናን የነፍጠኛ ስርዓት እዚሁ ነው የሰበራቸው፤ ዛሬ የሰበረንን ስርዓት ሰብረን ኦሮሞ በተዋረደበት ከተማ ከብሯልና እንኳን ደስ አለን ….”

 አቶ ሽመልስ አብዲሳ በኢሬቻ በዓል ከተናገሩት የተወሰደ፡፡

“መንግሥት የብሔሮችን፤ የብሔረሰቦችን፤ የሕዝቦችን ማንነት የማክበርና በዚሁ ላይ በመመርኮዝ በመካከላቸው እኩልነትን፤ አንድነትንና ወንድማማችነትን የማጠናከር ግዴታ አለበት”  (ስርዝ እና ድምቀት የተጨመረ)፡፡

የኦሮምያ ክልላዊ መንግስት ሕገ መንግሥት አንቀጽ 103 ቁጥር 2፤

በመስከረም 23 ቀን 2012 በአዲስ አበባ የኢሬቻ የአከባበር በዓል ላይ፤ ፍፁም ሃላፊነት በጎደለው መልክ፤ አንድን ሕዝብ ሆን ብሎ ለማዋረድ እና አላስፈላጊ “የፖለቲካ ትርፍ” ለማግኘት ሲሉ፤ የኦርምያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ ከላይ የተጠቀሰውን ፀያፍ ንግግር አድርገዋል። አቶ ሽመልስ፤ ከታሪክ ጋር የተጣረዘ፤ ምንም ዓይነት ጭብጥ የሌለው ንግግር ሲያደርጉ ይህ የመጀመርያቸው ባይሆንም፤ በዚህ ይቅርታ በሚጠየቅበት እና ስለ ሰላም መነገር በሚገባው፤ የኦሮሞ ሕዝብ ባሕላዊ ዝግጅት ላይ ያደረጉት ንግግር፤ የኦሮሞ ክልላዊ መንግሥትን ሕገ መንግሥት አንቀጽ 103 ቁጥር 2 የጣሰ ከመሆኑም በላይ፤ የኦሮሞን ሕዝብ የማይወክል እና የማይመጥን፤ እንዲሁም፤ አሁን ሃገሪቱ እየመራ ያለውን የኦዴፓ የኅዳሴ ለውጥ መርህ የማይከተል በመሆኑ፤ አቶ ሽመልስ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ በመጠየቅ ከሥልጣናቸው ሊለቁ ይገባል። ይህ ካልሆነ ግን፤ ከዚህ የሃላፊነት ቦታ ያስቀመጣቸው፤ ጨፌ ኦሮምያ፤ ከሥልጣናቸው እንዲያነሳቸው፤ የበኩሌን ጥሪ አቀርባለሁ፡፡  

አቶ ሽመልስ ከዚህ ቀደም፤ ኢሬቻ አዲስ አበባ እንዲከበር መታቀዱን ለሕዝብ ይፋ ሲያደርጉ፤ “የኦሮሞ ሕዝብ፤ የኢሬቻ በዓልን አዲስ አበባ እንዳያከብር ከ150 ዓመታት በፊት ተከልክሎ ነበር” ሲሉ፤ እንደ ብዙዎች፤ ይህ ፀሃፍ በትዝብት አዳምጦ አልፏል። የሚያሳዝነው ግን፤ ይህንን የ “150 ዓመት” የሃሰት ትርክት በርካታ ሰዎች እየደገሙት ነው። አዲስ አበባ ከተቆረቆረች ያስቆጠረችው ዕድሜ ገና 133 ዓመታት ሆኖ ሳለ፤ “የኦሮሞ ሕዝብ” ከ150 ዓመት በፊት ኢሬቻን አዲስ አበባ እንዳያከብር ተከልክሏል ሲባል፤ የኦሮሞ ልሂቃንም ሆኑ፤ የታሪክ ተማሪ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ምላሽ አለመስጠታቸው፤ ለአቶ ሽመልስ የመስከረም 23 ንግግር ጡንቻ እንደጨመረላቸው ግልጽ ነው፡፡ ባለፉት 28 ዓመታት፤ ከአቶ አሊ አብዶ ጀምሮ፤ በርካታ የኦሕዴድ አመራር አባላት የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆነው ተሹመዋል፤ በየትኛው ወቅት ነው፤ ኢሬቻ አዲስ አበባ እንዲከበር ተጠይቆ የተከለከለው? ኢሬቻ አዲስ አበባ እንዲከበር የተጠየቀበት ወቅት እንዳለ የሚያሳይ ምንም ጭብጥ መረጃ የለም፡፡ አቶ ሽመልስ፤ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ “የተበዳይነት ስሜት” እንዲጎለብት “ተጎጂነትን” ለመኮርኮር የተጠቀሙበት መነሻ ሃሳብ ነበር። አቶ ሽመልስ መስከረም 23 ያደረጉት ንግግር ሕገ መንግሥቱን የጣሰ ብቻ ሳይሆን፤ ምንም ታሪካዊ ጭብጥ የሌለው፤ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ለማጋጨት በጥቂት ጽንፈኛ ሃይሎች የሚቀነቀን አመለካከት ነው፡፡ አቶ ሽመልስ የተሰጣቸውን ሥልጣን እና ሃላፊነት እንደማይመጥኑ፤ በተጨባጭ ያሳዩ በመሆናቸው፤ በራሳቸው ፍቃድ፤ ከሥልጣናቸው ቢለቁ፤ ለቆሰቆሱት ቁስል፤ የማዳኛ የመጀመሪያ እርምጃ ይሆናል፡፡ 

የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በተለያዩ ገዥዎች፤ በደል ደርሶበታል፤ አንዱ ብሔር ከሌላው የበለጠ፤ የተበደለ ብሔር ነው የሚለው ትርከት፤ ሕዝብን ለመከፋፈል፤ ጽንፈኞች የሚጠቅሙበት የወደቀ አስተሳሰብ መሆኑን ለመገንዘብ ሊቅ መሆን አያስፈልግም፡፡ አቶ ሽመልስ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ማስተሳሰር ሲገባቸው፤ የዚህ የወደቀ ሃሳብ ተገዥ መሆናቸው፤ ለተሰጣቸው የሃላፊነት ቦታ ብቃት እንደሌላቸው ማረጋገጫ ነው፡፡ ኦሮሞው አያቴ፤ ማይጨው የዘመቱት ኢትዮጵያዊነትን አንግበው ነበር፤ ኦሮሞው አባቴ፤ የደከመው እና የሰራው ኢትዮጵያውያንን በሚያስተባብር ቁም ነገር ላይ እና ለኢትዮጵያ አንድነት ነው፡፡ ማንም ሃላፊነት የሚሰማው ዜጋ፤ ብሔሩ ምንም ይሁን ሊሰራ የሚገባው ሕዝብን ማስተባብር ላይ እንጂ፤ ሕዝብን መከፋፍል ላይ ሊሆን አይገባውም፡፡ 

አቶ ሽመልስ፤ እንደ አንድ ዜጋ፤ የፈለጉትን የማመን እና የመናገር መብት ቢኖራቸውም፤ እንደ አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን፤ ያውም የክልል መሪ፤ የሚናገሩት ሁሉ፤ ሕገ መንግሥቱን የማይፃረር፤ እወክለዋለሁ የሚሉትን ሕዝብ የሚመጥን እና፤ አንድን ሕዝብ ከሌላ ሕዝብ ጋር የማያጋጭ መሆን አለበት።  የኦሮሞ ክልላዊ መንግሥትም ሕገ መንግስት  “መንግሥት የብሔሮችን፤ የብሔረሰቦችን፤ የሕዝቦችን ማንነት የማክበርና በዚሁ ላይ በመመርኮዝ በመካከላቸው እኩልነትን፤ አንድነትንና ወንድማማችነትን የማጠናከር ግዴታ አለበት”  (ስርዝ እና ድምቀት የተጨመረ)፤ ሲል ሕገ መንግሥቱን በማክበር ለመስራት ቃል የገቡ ሰዎች፤ አቶ ሽመልስ ያደረጉትን ዓይነት ጠብ አጫሪ ንግግር መጠየፍ አለባቸው ማለት ነው፡፡ በጣም የሚያሳዝነው እና የሚያሳፍረው፤ አቶ ሽመልስ፤ የአማራን ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጋብዘው፤ እነዚህ ባለሥልጣናት በተገኙበት፤ የአማራን ሕዝብ መዝለፋቸው ነው፡፡ ይህ አንድን እንግዳ እቤት ጋብዞ ከመስደብ ያልተለየ ነውር ነው፡፡ በእንዲህ ዓይነት፤ ኢትዮጵያውያን በሚጠየፉት የነውር ባሕል የጨቀየ ሰው፤ ታላቁን የኦሮም ሕዝብ ሊመራ የሚችልበት፤ ሞራልም፤ ራዕይም፤ ብቃትም የለውም፡፡ ስለዚህ ለሁሉም እንዲበጅ እና፤ ከዚህ ከደረሰብን የሕሊና ቁስል መዳን እንድንጀምር፤ መላው የኢትዮጵያን ሕዝብ በአደባባይ ያዋረዱት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ሥልጣናቸውን ይልቀቁ፡፡ 

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ይባርክ፡፡    

ማስታወሻበዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
12,440FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here