spot_img
Sunday, May 19, 2024
Homeነፃ አስተያየትወደ ህወሃት ሽማግሌ የሚልክ ለኢትዮጵያ ህዝብ ምን ይልካል? (በመስከረም አበራ)

ወደ ህወሃት ሽማግሌ የሚልክ ለኢትዮጵያ ህዝብ ምን ይልካል? (በመስከረም አበራ)

በመስከረም አበራ
ጥቅምት 12, 2012 ዓ. ም.

በተለያየ አጋጣሚ ከሚያጋጥሙኝ አስተያየቶች አንዱ አቶ ጃዋር መሃመድን መነጋገሪያችን ማድረጉን እንተው፤ግለሰቡ የሚሰጠንን አጀንዳ አንስተን በመተንተን ሰውየው የሚፈልገውን ክብር በመስጠት ተፅኖ ፈጣሪነት እንዲሰማው አናድርግ የሚል ነው፡፡በግሌ ስራየ ብሎ ሰውን ማጉላትንም ሆነ ሆን ብሎ ሰውን ማሳነስን ብቻ አላማ አድርጎ መጓዙ የብልህ መንገድ አይመስለኝም፡፡ጠቃሚው ነገር የሰው ስራ የሚያመጣው ተፅዕኖ ላይ ትኩረት አድርጎ መነጋገሩ ይመስለኛል፡፡በዚህ ሁኔታ ግባችን ግለሰቦች ሳይሆኑ የግለሰቦች ሃሳብ እና አካሄድ የሚያመጣው በጎ ወይ መጥፎ ተፅዕኖ ነው፡፡በጎ ወይም መጥፎ ተፀዕኖ ያመጣውን የሰዎችን ስራ በተመለከተ ስንነጋገር የሰዎችን ስም ማንሳታችን ደግሞ አይቀርም፡፡በጎውን ስራ ስናወድስ፤መጥፎው ስራ ወደ ባሰ መጥፎ እንዳያድግ ልንነጋገርበት ስናነሳሳው ከግለሰቦች ጋር የተለየ ፀብ ወይም ፍቅር ስላለን አይደለም፡፡

ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ ዝም ብሎ ለማለፍ ሞክሬ ያልቻልኩት የአቶ ጃዋር ንግግር ነው፡፡ንግግሩን ሰምቼ ዝም ብሎ ማለፉ ያቃተኝ ደግሞ ግለሰቡ በርካታ ስሜታዊነት የበዛው ተከታይ ያለው ሰው በመሆኑ ንግግሩ የሚያመጣው ተፅዕኖ በጎ ስላልመሰለኝ ነው፡፡የዚህ ንግግር አንድ በጎ ጎን አቶ ጃዋር መስመሩ ከህወሃት ጋር መሆኑን በግልፅ ማሳወቁ ብቻ ነው፡፡ለዛሬው ፅሁፌ መነሻ የሆነኝ የግለሰቡ ንግግር የተደረገው  በኦሮምኛ ቋንቋ “OMN” በተባለው ሚዲያ ላይ ነው፡፡ንግግሩ ከኦሮምኛ ወደ አማርኛ ሲተረጎም ይህን ይመስላል፤

“በደቡብም በምስራቅም ሄጃለሁ፡፡ብዙ ሰዎች ፈርተው አይናሩትም እንጅ አቋማቸው ከህወሃት የተለየ አይደለም፡፡ፖለቲካ ያስተማሩኝም የብዙ ፓርቲዎች አመራር፣ምሁራን፣ወጣቶችም ጭምር በተለያየ ዘዴ አዋርቻቸዋለሁኝ፡፡ በይዘት ህወሃት የሚያራምደውን ፌደራላዊ ፖለቲካ ይደግፋሉ፡፡ እኛም አሁን ከህወሃት ጋር የሚያጣላን የታክቲክም ሆነ የእስትራቴጅ ልዩነት የለም፡፡ ህወሃቶች ፌደራሊስቶች መሆናቸውን በተደጋጋሚ በተግባርም በአቋምም አሳይተዋል፡፡ድሮ ብዙ ተባብለናል፡፡ያለፈው አልፏል፡፡ እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው ግን በአብይ ዙሪያ ካሉት ሰዎች መካከል አብይን ከልብ የሚደግፉ በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ናቸው፡፡በስም ሁሉ ልጠራቸው እችልላለሁ፡፡አሁን ኦሮሞ ማድረግ ያለበት ለእስትራቴጅክ  አጋሮቹ አጋርነቱን ማሳየት ነው፡፡ ሽማግሌም ቢሆን ልከን  ዋናውን እስትራቴጅያዊ ወዳጅ አብሮን እንዲሰራ እንሞክር፡፡ አብይ ብቻውን ነው እየሄደ ያለው፡፡እንደተናገርት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው አጠገቡ ያሉት፡፡” (መስመር የእኔ)

ይህን ንግግር በፍጥነት ወደ አማርኛ መልሰው ለህዝብ ይፋ ያደረጉት የተለያዩ የትግራይ ሚዲያዎች ናቸው፡፡ተናጋሪው ወደ  ምስራቅ እና ምዕራብ መጓዙን ሲናገር የተጓዘው ወደ ደቡብ/ምስራቅ ኦሮሚያ ይሁን ወደ ደቡብ/ምስራቅ ኢትዮጵያ ግልፅ አይደለም፡፡ከተናጋሪው የቆየ በሚዲያ ለሚደረግ ንግግር ጥንቃቄ ያለማድረግ፣ተረጋግቶ እና አስቦ ያለማውራት ባህሪ ተነስቶ ለገመገመ ደግሞ ደቡብ/ምስራቅ የሚለው አባባል ደቡብ/ምስራቅ የሚለውን አቅጣጫ ለመጠቆም ሳይሆን  ወደ ብዙ ቦታ ተዘዋውሬ ሰዎች አነጋግሬያለሁ ለማት ሲሆን ይችላል፡፡

ተናጋሪው ኦሮሚያ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ፖለቲከኛ በመሆኑ እያወራ ያለው በኦሮሚያ ስላነጋገራቸው ሰዎች ነው ብለን ብንነሳ እየተባለ ያለው በኦሮሚያ ውስጥ ህወሃት ያራምደው የነበረው የፌደራሊዝም ፖለቲካ በእጅጉ ይወደዳል ነው፡፡ይህ ማለት ኦሮሚያ ክልል በህወሃት ምርጫ ይሰየም የነበረ ርዕሰ መስተዳደር በመናፈቅ እየዋተተች ነው ማለት ነው፡፡የኦሮሞ ፖለቲከኞች የኦሮሚያ ክልል ህወሃት በሚያሰማራቸው ህወሃታዊ ዘራፊዎች መዘረፉ ስለቀረበት አዝናነው ሊሞቱ ነው ማለት ነው፡፡    

ምስራቅ የተባለው በምስራቅ ኢትዮጵያ ነው ከተባለ ደግሞ የሶማሌ ክልል ምሁር፣ፖለቲከኛ ወጣት ህወሃት ያደርገው የነበረውን ፌደራላዊ ፖለቲካ ይደግፋል ማለት ነው፡፡ በሌላ አባባል የሶማሌ ምሁር፣ፖለቲከኛ እና ወጣት አብዲ ኢሌ እና ህወሃት እጅ ለእጅ ተያይዘው ያነበሩትን የፌደራሊዝም ፖለቲካ የሚደግፍ ነው ማለት ነው፡፡ይህ ማለት የሶማሌ ፖለቲከኛ፣ወጣት እና ምሁር የጄል ኦጋዴንን ሲኦል በመናፈቅ መዋተት ውስጥ ነው ማለት ነው፡፡የሶማሌ ህዝብ በህወሃት ጀነራሎች የኮንትሮባንድ ንግድ ዘረፋ ናፍቆት እየተቸገረ ነው ማለት ነው፡፡የሶማሌ ሴቶች በቀን በብርሃን በመሃል ከተማ መደፈርን የመሰለን “አክብሮት”ያመጣላቸውን ፌደራሊዝም እየናፈቁ ነው ማለት ነው፡፡

ሕወሃት ያነበረው ፌደራላዊ ፖለቲካ ተናጋሪው እንደሚያስበው የደቡብ/ምስራቅ ጉዳይ ስላልሆነ ሰፋ አድርገን ስናየው በጋንቤላ በህወሃት ጀነራል እና ደራሽ ኢንቨስተር መሬትን መዘረፍ፣የሲጋራ መግዣ የማያክል ገንዘብ ከፍሎ ለሚመጣ የውጭ ኢንቨስተር መሬትን አስረክቦ መፈናቀል፣ህወሃት በሾመው አሻንጉሊት አስተዳዳሪ መተዳደር ባጠቃላይ የህወሃት የገንዘብ ሳጥን መሆን ነው፡፡ለጋንቤላዎች ህወሃት ያነበረው የፌደራል ፖለቲካ ለኑዌር ወግኖ አኙዋክን መቸፍጨፈ፤አለያም ኑዌር እና አኙዋክ ወንድማማችነቱን ረስቶ ለደመኝነት እንዲፈላለግ ማድረግ ነው፡፡

የህወሃት የፌራሊዝም ፖለቲካ በአማራ ክልል ሁኔታ እንየው ከተባለ ለምለም መሬትን ለህወሃት አስረክቦ፣የማልቀሻ እና መዝፈኛ ቋንቋን ሳይቀር ህወሃት የሚመርጥበት የባርነት አለም ውስጥ ቋንጃን ተቆርጦ መንፏቀቅ ነው፡፡የህወሃት ፌደራላዊ ፖለቲካ ለአማራ ህዝብ በረከት ስምኦን በተባለ ኤርትራዊ ገዥ እግር ስር ተደፍቶ ውርደት መጋት አለያም አለምነው መኮንን በተባለ የአሽከር አሽከር አሻንጉሊት አስተዳዳሪ ያልተገራ አፍ መሰደብ ነው፡፡የህወሃት ፌደራሊዝም በአማራ ክልል መዲና ባህርዳር ከተማ ህወሃት በቀለሰው እስርቤት በህወሃት ገራፊ በፌሮ መገረፍ ነው፡፡የህወሃት ፌደራላዊ ፖለቲካ በአማራ ክልል በተቀለሰ እስርቤት አማራ ሱሪውን አወልቆ ራቁቱን እንደቀረ፣አከርካሪው የተሰበሰ ሽባ እንደሆነ እየተነገረው የበላው በአፉ እስኪመጣ በህወሃት መኳንንት ተዘቅዝቆ የሚሰቀልበት ማለትነው፡፡የህወሃት ፌደራላዊ ፖለቲካ ለደቡብ ክልል ፖለቲከኛ በአንድ ህወሃት ቀላጤ ደብዳቤ መሾር፤የህወሃት ባስልጣናትን ዘመድ አዝማድ በአንድ ሌሊት ከበርቴ የሚሆንበትን መንገድ ከፍቶ ዳርቆሞ ማየት ነው፡፡

የህወሃት ፌደራሊዝም ዘጠኙም ክልል ጀግናው ህወሃት በትግርኛ ፅፎ ያሰናዳውን መመሪያ በየቋንቋው ተርጉሞ ህወሃት እንደወደደ ለማስፈፀም ሽር ጉድ ማለት፤ለባርነት መታጠቅ ነው!የህወሃት ፌደራሊዝም ማለት የሶስት አባል እና የአምስት አጋር ፓርቲዎች  ካድሬዎች የህወሃትን መንበር ተሸክመው “አሜን አሜን” ሲሉ ማለት ነው፡፡የህወሃት ፌደራሊዝም ማለት መለስ ዜናዊ የእግዜር ታናሽ ተደርጎ ተቆጥሮ የተናገረው ቃል በዘጠኙም ክልል ካድሬዎች እንደወረደ ሲነገር ማለት ነው፡፡ የህወሃት ፌደራሊዝም ማለት ህወሃት የጠላውን ዜጋ በሌሊት ይሁን በቀን፣በእግር ይሁን በፈረስ ከፈለገው ክልል አምጥቶ ማዕከላዊ አስገብቶ ጥፍሩን ሲነቅል፣በፌሮ ጀርባውን ሲተለትል፣ዘር እንዳይተካ ሲያኮላሽ፣ግብረ ሰዶም ሲፈፅም፣ሴት በርብርብ ስትደፈር ማለት ነው፡፡ህወሃት ፌደራሊስትነቱን በተግባር አስመስክሯል ሲባል “ይህ አረመኔያዊ ተግባር ስሙ የፌደራሊዝም ፖለቲካ ይባላል” ብሎ መናገር ነው፤ይህ ደግሞ ለእብደት መዋሰን ነው! ከህወሃት ጋር ስትራቴጃዊ አጋር ነኝ ማለት የዘረፋ፣የአይን አውጣነት፣የሰብዓ መብት ጥሰት አጋር ነኝ ማለት ነው፡፡

በርግጥ የህዋትን አረመኔነት ለመገንዘብ ከኢትዮጵያ ህዝብ አጠገብ ተቀምጦ ህወሃት ባሳረረው ማሳረረር ሳቢያ ከእትንፋሱ የሚወጣውን የምሬት ጭስ ማየት ይጠይቃል፡፡በህወሃት ዘመን ወደ ኢትዮጵያ ዝር ለማለት ቀርቶ ለማሰብ የማይደፍር ራሱን ጠባቂ “ታጋይ” ህወሃት በኢትዮጵያ ህዝብ አካል እና አእምሮ ውስጥ ስላስቀመጠው የማይሽር ጠባሳ ሊያውቅ አይችልም፡፡እንዲህ ያለው “ታጋይ” ትናንት ህወሃትን ሲታገል የነበረው ከአትላንቲክ ማዶ ነፍሱን በጨርቅ ቋጥሮ በተቀመጠ፣መራራ በደል ባልቀመሰ ማንነቱ ስለነበረ ያለፈውን እንደዋዛ ለመተው አይቸገርም፡፡

በመሆኑም አቶ ጃዋር በምድረ-አሜሪካ ሆኖ ህወሃትን ታገልኩ ባለበት ዘመን ስለ ህወሃት ስላለው ነገር ሁሉ እንደ መፀፀት በሚቃጣው መልኩ እንደ አለፈ ውሃ እንዲተለው ይፈልጋል፡፡እኛ የህወሃትን አረመኔያዊ ገፅታ ሁሉ እዚችው ቁጭ ብለን ያየን ኢትዮጵያዊያን ግን ህወሃትን መታገላችን ከበቂ በላይ በሆነ ምክንያት የተነሳ የተደረገ ነበርና የሚያፀፅተን፣እንደ አለፈ ውሃ እንዲረሳልን የምንፈልገው ታሪክ አይደለም፡፡ይልቅስ ባሰብነው ቁጥር የምንኮራበት የታሪካችን ገፅ ነው! ወደፊትም ህወሃታዊነት የሚያንሰራራ በመሰለን ጊዜ ሁሉ ከቀድሞ በበረታ ጥንካሬ ለመታገል እጅ ለእጅ የምንያያዝ ባለምክንያት እምቢ ባዮች  ነን እንጅ “የትናንቱን እርሱልን እና እንታረቅ” የምንል አጥነተ-ቢስ ልፋጭ ስጋዎች አይደለንም፡፡ትላንት ያለ ምክንያት የጮኽ ብቻ “የትናነትቱን እርሱልኝ” ይላል፤ትናንት በበቂ ምክንያት የታገለ ባለ አእምሮ በታገለው ባላጋራው ፊት አይሽረከረክም፡፡

ከሁሉም በላይ የባላጋራችንን የህዋትን ማንነት አሳምረን  እናውቃለን፡፡ህወሃት ስልጣኑን ካስቀማው ባለጋራው  ጋር  አይደለም አንድ አጭር  የትችት አርቲክል ከፃፈበት ሰው ጋር የእውነት እርቅ አይታረቅም፡፡በህወሃት እልፍኝ የእውነት እርቅ የለም! ህወሃት ከነገሩ ሁሉ አጥንት አለው! ጠላቱ እንታረቅ ባለው ሰዓት ሁሉ የሚታረቅ ደጅ ወጥቶ የተቀመጠ ልብ የለውም፡፡የሆነ ሆኖ የህወሃት እግር ስር ተንከባሎ ማሩኝ ማለት፣አመድ ነስንሶ ማቅ ለብሶ፣ድንጋይም ተሸክሞ  ለእርቅ የህወሃትን ደጅ ማንኳኳት ይቻላል፡፡ መታወቅ ያለበት አበይት ጉዳይ ግን ህወሃት ጥፋቱን አምኖ ለመስተካከል ባልሞከረበት፣ጭራሽ ሃገሪቱን ለባሰ ብጥብጥ ለመዳረግ ታጥቆ በሚሰራበት በዚህ ወቅት  “ሽማግሌ ልኬም ቢሆን ከህወሃት ጋር እታረቃለሁ” ማለት ለኢትዮጵያ ህዝብ የጠብ ደብዳቤ መፃፍ ነው!

ማስታወሻበዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here