spot_img
Saturday, September 30, 2023
Homeነፃ አስተያየትዶ/ር ዐብይም ሆኑ ኢንጂነር ታከለ ኡማ፤ ሊወቀሱም ሊወገዙም ይገባል።

ዶ/ር ዐብይም ሆኑ ኢንጂነር ታከለ ኡማ፤ ሊወቀሱም ሊወገዙም ይገባል።

advertisement
Samuel Tibebe Ferenji
ጸሃፊው – ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ

ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ
ጥቅምት 18 ቀን 2012 ዓ.ም

“የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚጀመረው በአንድ ሰው ግድያ ነው– ባደረገው ድርጊት ሳይሆን፤ በማንነቱ። የ “ዘር ማጽዳት ዘመቻ” ከአንድ ሰፈር ጀምሮ፤ ወደ ሌላው ሰፈር ይዛመታል። የአንዱን የሰው ሕይወት ክቡርነት መጠበቅ ሲያቅተን፤ ብዙውን ጊዜ፤ መጨረሻው፤ መላውን ሃገር ከፍተኛ ጥፋት ውስጥ የሚከት ይሆናል”። ኮፊ አነን ከተናገሩት በግርድፉ የተተረጎመ። 

ኢትዮጵያ ውስጥ፤ ዲሞክራሲያዊ ስልተ ስርዓት ለመገንባት፤ ከ45 ዓመታት በላይ ከፍተኛ ትግል ተካሂዷል፡፡ ሃገራችን ውስጥ፤ ፍትሃዊ እና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት ተደጋጋሚ እድል ብናገኘም፤ ልንጠቀምበት አልቻልንም፡፡ “የባለታክሲው የመጨረሻ ደንበኛ” በሚል ርዕስ; ከአምስት ዓመታት በፊት ለንባብ የበቃው መጽሐፌ ላይ እንደገለጽኩት፤ የኢትዮጵያ ትልቁ ችግር፤ ዜጎች ከሃገር ጥቅም ይልቅ፤ ለግለሰብ እና ለድርጅት ጥቅም የሚሰሩ መሆናቸው ነው። ሃገራችን ዛሬ የጀመረችው የለውጥ ሂደት ሊገኝ የቻለው፤ በአንድ ወይም በጥቂት ቡድን ትግል ነው ብሎ ማመን እና ማሰብ፤ ይህ ለውጥ እንዲመጣ ከፍተኛ ዋጋ የከፈሉ፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን፤ የሕይወት መስዋዕትነት መናቅና፤ እነዚህን ብርቅዬ የኢዮጵያ ልጆች በድጋሚ መግደል ነው። ቄሮም ይሁን ፋኖ የሚባል ቡድን ከመታለሙ በፊት፤ የኢትዮጵያ አንድነት ፀንቶ እንዲቆይ እና፤ የዘር ፖለቲካ የፈጠረውን አድልዎ፤ ኢፍትሃዊነትን እና የሰብዓዊ መብት ረገጣን በመቃወም ፋና ወጊ የሆኑ እና የህይወት መስዋዕትነት የከፈሉ ብዙ ኢትዮጵያውያን አሉ። የእነዚህ ብርቅዬ ዜጎች ድምር የትግል ውጤት እና ከፍተኛ መስዋዕትነት ነው፤ ቄሮንም፤ ፋኖንም ሆነ፤ በኢሕአዲግ ውስጥ የተፈጠረውን “የለውጥ” ሃይል ያስነሳው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለፍትህ እና ለመልካም አስተዳደር ትግል የጀመረው በህዳር 2007 አይደለም፤ አልነበረምም፡፡ አሁን ላለንበት የለውጥ ውጤት፤ ባለቤቱ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ፤ ጥቂት ግለሰቦች አይደሉም። በአሁኑ ስዓት፤ የስልጣን መንበሩን የተረከበው ሃይል፤ በብአዴን እና ደሕዴን አጋርነት፤ እንዲሁም ሕወሃት ውስጥ ባሉ፤ ለውጡ አስፈላጊ መሆኑን በተገነዘቡ ሃይሎች ጥረት ነው፤ ወደ ሥልጣን የመጣው እንጂ ቄሮ በተባለ ቡድን፤ ወይም ጃዋር በተባለ ጽንፈኛ አይደለም። ይህ በጽኑ ሊሰመርበት ይገባል። 

ዶ/ር ዐብይ እና የሚመሩት የለውጥ ሃይል፤ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍተኛ ድጋፍ የተቸራቸው እና፤ አንዳንዶቻችንም፤ መጀመርያ “ለውጡን የተረከቡ መሪዎች” በጥርጣሬ አይተን፤ በኋላ ግን የለውጡን ሂደት በጽናት የደገፍነው፤ በሃገራችን የሕግ የበላይነት እና የሕዝባችን ሰብዓዊ መብት ይከበራል፤ የዘር አድልዎም ይቀራል፤ ከምንም በላይ ደግሞ ሥልጣን የሕዝብ የሚሆንበት መንገድ መሰረት ይይዛል ከሚል እምነት ነው። ምንም እንኳን የዶ/ር ዐብይ አመራር፤ ለውጡን፤ ከግብ ለማድረስ፤ የሃገራችንን የይቅርታ ባሕላዊ እሴት፤ በፖለቲካው “ጨርቅ” ውስጥ ሸምኖ ሊያዋህደው ቢሞክርም፤ በተለይ በአንዳንድ አካባቢዎች ይህ ሙከራ እንደ ፍርሃት በመቆጠሩ፤ ጽንፈኛ ሃይሎች፤ በዜጎቻችን ላይ እና በሃገራችን ውስጥ ከፍተኛ ጥፋት እንዲያደርሱ አድርጓል። ጥፋቱም ከደረሰ በኋላ አጥፊዎች ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ፤ “ክልል በመምረጥ” የሚመስልበት ሁኔታ በገሃድ እየታየ ነው። በአማራ ክልል እና በሲዳማ ዞን፤ ብቃት ያለው ፈጣን እርምጃ መውሰድ የቻለ የመከላከያ ሃይል፤ በኦሮምያ ክልል የንፁሃንን ሕይወት በቀጠፉ እና ንብረት ባወደሙ፤ ጽንፈኛ ወጣቶች እና፤ ለዚህ ሁሉ ጥፋት ምክንያት በሆነው ግለሰብ ላይ ለምን እርምጃ እንዳልወሰደ፤ ብዙዎቻችንን ግራ አጋብቷል።

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት፤ የፌደራል መንግሥት በክልሎች ጣልቃ ሊገባ የሚችለው ክልሉ ሲጠራው እንደሆነ ይገልፃል። በዚህም ሊሆን ይችላል የፌደራል ፖሊስም ይሁን መከላከያው በአስቸኳይ ኦሮምያ ክልል ገብቶ ሕግ የማስከበር ሥራውን ያልሰራው። ነገር ግን፤ የኦሮምያ ክልል የፌደራል መንግሥቱን ጣልቃ ገብነት ከጠየቀ በኋላ፤ በፌደራል ፖሊስም ሆነ በመከላከያ ሰራዊቱ የተወሰዱ እርምጃዎች፤ በቂ ያልሆኑ እና አድልዎ የታየባቸው ለመሆኑ፤ በርካታ ዘገባዎች ያሳያሉ። ከሁሉም በላይ ደግሞ፤ ዶ/ር ዐብይ አሕመድ፤ “ጭንቅላታቸውን አሽዋ ውስጥ በመቅበር” ይህ የችግር ማዕበል እስኪያልፍ የሚጠብቁ መምሰላቸው፤ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ጥያቄን አጭሯል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የታሉ ሲሉም የአለም የዜና አውታሮች ዘግበዋል። እስከዛሬ ድረስ፤ አንድ ጽሁፍ ከመልቀቅ በስተቀር፤ አደባባይ ወጥተው፤ ሕዝቡን የማረጋጋት ሥራ ሲሰሩ አላየንም። ዶ/ር ዐብይ በርካታ በጎ ስራዎችን ሲሰሩ መደገፍ ብቻ ሳይሆን፤ አላስፈላጊ ወቀሳ እና ውግዘት ሲንሳባቸውም በአደባባይ ተሟግቻለሁ። ሲያጠፉ እና ሲሳሳቱ ደግሞ ሊወቀሱም እንደሚገባ በተደጋጋሚ ገልጫለሁ። ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንደገለጽኩት፤ ለእኔ ማንም ከሃገር በላይ አይደለም።

ታከለ ኡማም በርካታ በጎ ስራዎችን ለአዲስ አበባ ከተማ ሰርተዋል። አሁን ግን አዲስ አበባ በዚህ ሁሉ ትርምስ ውስጥ እያለች፤ ምነው ድምፃቸው ጠፋ? በአዲስ አበባ ሕግና ስርዓት ማስከበር፤ የአዲስ አበባ መስተዳድር ሃላፊነት ነው። ይህ ሁሉ ወጣት፤ በጃዋር ቤት አካባቢ ድንኳን ተክሎ ሲሰበሰብም ሆነ ሰላማዊው እና ሕግ አክባሪው ዜጋ ላይ ከፍተኛ ስጋት ሲፈጥር፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ምን ሰራ? ለዚህ ታከለ ኡማ ተጠያቂ ናቸው፡፡ ማንም ይሁን ማን፤ በሃላፊነት ቦታ ላይ ሲቀመጥ፤ ሃላፊነቱን የሚረከበው ትክክለኛ ሥራ ለመስራት ነው፡፡ ሥራውን የሚሰራው ለሕዝብ ውለታ ብሎ ሳይሆን ሥራው ስለሆነ ነው፡፡ ሥራቸውን በአግባብ ሲሰሩ መመስገን ሲገባቸው፤ ሲያጠፋ እና ሲሳሳቱ ደግሞ፤ ሊወቀሱ እና ሊወገዙም ይገባቸዋል፡፡ ቡራዩ ላይ በጽንፈኛ ወጣት ኦሮምዎች፤ በተፈፀመ “የዘር ማፅዳት” ግድያ፤ የአዲስ አበባ ወጣቶች ዋጋ ሲከፍሉ አይተናል። ይህ እንዴትስ ፍትሃዊ ሊሆን ይችላል? የአዲስ አበባ ወጣቶችን ሰላማዊ ሰልፍ የከለከለ መስተዳድር፤ እንዴት ነው በቦሌ አካባቢ ከመስተዳድሩ ፈቃድ ሳያገኙ፤ በነዋሪዎች ላይ ሥጋት እየፈጠሩ ያሉትን ወጣት ኦሮሞዎች ዝም የሚለው? እነዚህ ጥያቄዎች ተድበስብሰው የሚያልፉ ሊሆኑ አይችሉም፤ መልስ ያስፈልጋቸዋል፡፡ 

ባለፉት ጥቂት ቀናት በኦሮምያ ክልል እና ሌሎች አካባቢዎች፤ በጽንፈኛ ወጣት ኦሮሞዎች አሰቃቂ እርምጃ፤ ለጠፋው ሕይወት እና ንብረት ተጠያቂው፤ ዶ/ር ዐብይ እና ኢንጂነር ታከለ ብቻ አይደሉም፡፡ የኦሮምያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሽመልስ አብዲሳ፤ የችግሩ አካል ናቸው። እኝህ ሰው፤ በተለይም በኢሬቻ በዓል ላይ፤ አዲስ አበባ ያደረጉት ንግግር፤ ለእነዚህ ጽንፈኛ ወጣቶች “ጉልበት” የሰጠ ለመሆኑ፤ አልጠራጠርም። ብዙ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ጃዋር መሐመድ ይህንን ነገር ያቀድው ቀደም ብሎ ነው። አቶ ሽመልስ ከጃዋር እና ከኦሮሞ አክቲቪስቶች ጋር አላቸው ከሚባለው ቅርበት አንፃር፤ ይህንን ቀደም ብለው ለማወቅ የሚቸገሩ አልመሰለኝም። ችግሩ ከመከሰቱ ከአንድ ቀን በፊት፤ በተለያዩ የኦሮሞ ማህበራዊ ድሕረ ገፆች ላይ፤ ቄሮ ይህን አመጽ ለማቀዱ ሲንሸራሸር የነበረ ሃሳብ ነው። አሜሪካ ያለን ሰዎች እንኳ ቄሮ ለዓመጽ እየተዘጋጀ መሆኑን ሰምተናል። ታድያ የኦሮሞ ክልላዊ መንግሥት በቂ ፖሊስ ቀድሞ እንዴት አላሰማራም? ቄሮ የተባለው ቡድን፤ ወደ አመፀኛ እና ሕግን የማይፈራ ቡድን እየሆነ መምጣቱን፤ በተደጋጋሚ አሳይቷል፤ ይህ ቡድን ማን ፈቃድ ሰጥቶት ነው፤ ሰልፍስ ያደረግው? ሰልፉንስ ሰበብ አድርጎ የስንት ንጹሃንን ሕይወት የቀጠፈው በማን አይዞህ ባይነት ነው? የኦሮምያ ፖሊስ ኮሚሽንም ሆነ የክልሉ መንግሥት ንጹሃን ላይ ግድያ ሲፈጸም እና ንብረት ሲወድም፤ ተመጣጣኝ እርምጃ ያልወሰዱበት ምክንያት ምንድነው? በአስቸኳይስ ለፌደራል መንግስቱ ጥሪ ያላቀረበው ለምንድነው? እነዚህ ሁሉ መልስ ማግኘት አለባቸው፡፡ 

የመከላከያ ሰራዊትም ሆነ፤ የፌደራል ፖሊስስ፤ በክልሉ መንግሥት ጥሪ ከተደረገለት በኋላ፤ በቂ ሰራዊት እና የፖሊስ ኃይል ያላሰማራበት ምክንያት ምንድነው? በአማራ ክልል፤ ያውም፤ የጦር መሳሪያን የታጠቅን ኃይል፤ በአጭር ሰዓታት ተቆጣጠርኩ ያለው የመከላከያ ሰራዊት፤ ዱላ እና ስለት የያዘን ጽንፈኛ የወጣት ቡድን በአጭር ስዓታት ውስጥ መቆጣጠር እንዴት አልቻለም? ይህ፤ አቶ ለማ መገርሳንም፤ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንንም ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ በመንግሥት የፀጥታ ሃይሎች ጥበቃ የሚደረግለት ግለሰብ፤ ‘መንግሥት የግድያ ሙከራ አደረገብኝ’ ሲል “የጮኸው የሃሰት ጩኸት” ለዚህ ሁሉ ሰላማዊ ሰው ሕይወት መቀጠፍ እና ንብረት መውደም ምክንያት ሆኖ ሳለ፤ ግለሰቡ ተጠያቂ የማይሆንበት ምክንያት ምንድነው? ዛሬም ይህ ግለሰብ “ማንንም አልፈራም” እያለ በራሱ የቴሌቪዥን መስኮት ላይ ብቅ ብሎ አሁንም ይደነፋል፡፡ ማንንም አልፈራም ብሎ የሚፎክረው ግን የበርካታ የደሃ ኦሮሞ ወጣቶችን ደረት መከላከያ አድርጎ እንጂ፤ እራሱን ፊት ለፊት አውጥቶ እና የሚመጣውን ገፈት ለመቀበል ተዘጋጅቶ አይደለም። ትላንት ድረሱልኝ ብሎ ኡኡታውን ሲያቀልጥ ሰምተን፤ ዛሬ ማንንም አልፈራም ሲል ስሰማ “ፈሪ ፍርሃቱን ሲሸፍን ደረቱን ይነፋል” የሚለው ሃገራዊ ብሂል ይታወሰኛል፡፡

ትላንት ሲዳማ ዞን ኢጀቶ የተባለውን ጽንፈኛ ቡድንን ያንበረከከ የፌደራል መንግሥት፤ ኦሮምያ ክልል የበቀለውን ይህን አደገኛ ቡድን ማንበርከክ እንዴት አቃተው? ትላንት የሲዳማ ዞን የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጆች እና ሃላፊዎች ላይ እርምጃ የወሰደ የፌደራል መንግሥት፤ ዛሬ መሃል አዲስ አበባ ተቀምጦ፤ ከሕዝብ በተለመነ ገንዘብ እና በአሜሪካን ታክስ ከፋዮች የገንዘብ እርዳታ፤ እየተደጎመ የተንደላቀቀ ኑሮ የሚኖር ግለሰብ መርዝ የሚረጭበት እና ሃገር የሚያምስበት ቴሌቪዝን ፕሮግራም አዘጋጆች እና መሪዎች ላይስ ለምን እርምጃ አልተወሰደም? ወይስ “አንዳንድ ኢትዮጵያኖች እና ትውልደ ኢትዮጵያኖች፤ በዘራቸው የተነሳ፤ ከሌላው ኢትዮጵያዊ የበለጠ እኩል ናቸው”? የፍትሕ ስርዓቱ ሁሉንም በእኩል የማያይበት ምክንያቱ ምንድነው? ትላንት የጠላነው እና የታገልነው የዘር መድልዎ፤ ዛሬ ገኖ ሲወጣ፤ የለውጡ መሪዎች ከምን ቀርቀሃ ውስጥ ነው እራሳቸውን “የቀበሩት”? ጃዋር አሜሪካዊ ነው፤ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እንደፈለግ እንዲንቦጫረቅ ለምንድነው መብት የሚሰጠው? ሕዝብንስ ሲያተራምስ ለምንድ ነው፤ ቢያንስ ከሃገር እንዲባረር የማይደረገው? 

“የለውጥ ሃይሉ” ወደ ሥልጣን የመጣሁት በቄሮ ትግል ነው ብሎ የሚያምን ከሆነ፤ ከታሪክ አልተማረም ማለት ነው፡፡ “የስልጣን መሰረቴ፤ የኦሮሞ ሕዝብ ነው” ከሚል እሳቤም ከሆነ፤ ይህም ስሕተት ነው፡፡ እውነት ነው እንኳን ተብሎ ቢታመን፤ ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ የተፈፀመው አረመኔያዊ ድርጊት፤ የኦሮሞን ሕዝብ ሥም ያጎደፈ፤ በአብዛኛው የኦሮሞ ሕዝብ የማይደገፍ እና የኦሮሞን ሕዝብ ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ጋር የሚያቃቅር እና፤ በሚሊዮን የሚቆጠር ንፁሃን ኦሮሞዎችንም አደጋ ላይ የሚጥል ነው። የለውጥ አመራሩ ይህን በጽኑ ሊገነዘብ እና፤ ከመግለጫ ጋጋታ ይልቅ፤ ተመጣጣኝ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል። አንድን መሪ፤ መሪ የሚያደርገው፤ ቁርጠኝነት በሚያስፈልጋቸው ነገሮች ላይ ቁርጠኛ እርምጃ ሲወስድ ብቻ ነው። የሕግ የበላይነት የማይከበርባት ሃገር ውስጥ፤ በምንም መልኩ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ሊገነባ አይቻልም። የአንድ ሃገር መሪም የመሪነት ብቃቱ የሚለካው፤ የዜጎችን ሕይወት በመጠበቅ በሚወስደው ቁርጠኛ እርምጃ ነው ብዬ አምናለሁ። ‘የምወስደው እርምጃ፤ ምን ዓይነት የፖለቲካ ዋጋ ያስከፍለኛል’ በሚል ቀመር፤ በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚወሰድ የግድያ እርምጃን በዝምታ ማለፍ፤ ከተጠያቂነት ሊያድን አይችልም። የሚከተለውን መንጋ ተጠቅሞ፤ “የዘር ማፅዳት ዘመቻን” መሳሪያ በማድረግ “የዜጎች ጉሮሮ ላይ ስለት የደገነን” አረመኔ፤ ሙሉ ትጥቅ የያዘ ሰራዊት እና የፖሊስ ኃይል ያለው መንግሥት፤ ሕጋዊ እርምጃ ወስዶ ማስቆም ካልቻለ፤ ስለሕግ የበላይነት መኖር ቢደሰኮር፤ ትርጉም የለውም።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ትላንትና፤ “ዐብይ ምነው ዝም አሉ?” ስትል ጠይቃለች፤ እኔም እንደ አንድ ተራ ዜጋ፤ ጽንፈኛ ወጣት ኦሮሞዎች፤ የንፁሃን ኢትዮጵያውያንን ሕይወት በአሰቃቂ ሁኔታ ሲቀጩ፤ ልቤ ስለተሰበረ፤ ልባቸው ደም ያነባ እናቶች፤ “አለሁላችሁ የሚል” መሪ እና መንግሥት ባለማግኘታቸው፤ ዐብይ ምን ነው ዝም አሉ? ብዬ ለመጠየቅ እገደዳለሁ፡፡ በተደጋጋሚ እንደተገለፀው፤ ሃላፊነት የተጣለባቸው አመራሮች ዝም ሲሉ፤ የድርጊቱ ተባባሪ እንደሆኑ ይቆጠራሉ። ስለዚህ፤ ዶ/ር ዐብይም፤ ኢንጂነር ታከለ ኡማም፤ አቶ ለማ መገርሳም እና አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ በጽንፈኛ ወጣት ኦሮሞዎች ለተቀጠፈው ሕይወት ተጠያቂ ናቸው። በዚህ ፀሃፍ እምነት፤ የሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት፤ የዐብይ መራሹ መንግስት የሚወስዳቸው እርምጃዎች፤ በሃገራችን ለሚኖረው የሕግ የበላይነት ወይም ስርዓተ አልበኝነት ወሳኝ የሆነ ተጽእኖ ይኖረዋል። 

በዚህ አጋጣሚ፤ ዶ/ር ዐብይን ከመደገፍ ውጪ አማራጭ የለም የምትሉ፤ ቆም ብላችሁ አስቡ። አማራጭ የሌለው ሞት ብቻ ነው። ሁሉም ነገር አማራጭ አለው። ዐብይ በጎ ሲሰሩ ሊደገፉ፤ መስራት ያለባቸውን ካልሰሩ ደግሞ ድጋፍ ሊነፈጋቸው ይገባል። እኔ በበኩሌ ድጋፌም ሆነ ተቃወሞዌ ለሚሰሩት ሥራ እንጂ፤ ለግለሰቡ አይደለም። በዙ ሰርተዋል፤ ብዙ ጥረዋል፤ ብዙም ደከመዋል፤ ለለውጡም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ያለአግባባም ተወግዘዋል፤ ተወቅሰዋልም። አሁን ግን የሚጠበቅባቸውን ሥራ አልሰሩም ብዬ ስለማምን፤ በዝምታቸው፤ ሊወቀሱም ሊወገዙም ይገባል እላለሁ።

ሕይወታቸውን ላጡ ንፁሃን ዜጎች፤ ነፍሳቸውን በገነት ያኑርልን። በአካላቸውም ሆነ በሕሊናቸው ጉዳት ለደረሰባቸው፤ እግዚአብሔር ብርታቱን ይሰጣቸው። ጥቂት ጽንፈኞች፤ የኢትዮጵያውያንን የአብሮ መኖር እሴት እንዳይሸረሸሩ ሁላችንም ተግተን እንስራ።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ይባርክ።        

ማስታወሻበዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
13,705FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here