–የመንፈስ ነፃነትና ተጨባጭ ሁኔታዎችን በትክክል የማንበብ አስፈላጊነት! – II
ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)
ጥቅምት 29፣ 2019
መግቢያ
አብዮቱ ከፈነዳና ብዙ ትርምስ ከተፈጠረ በኋላ ደጋግሞ የሚነሳው ጥያቄና ክርክር አገራችን እንደዚህ ዐይነት ምስቅልቅል ውስጥ ልትገባ የቻለችው ከታሪካችንና ከአስተሳሰባችን ጋር ሊጣጣም የማይችል ርዕዮተ-ዓለም በማስገባታችን ነው የሚል ነው። በሌላ ወገን ማርክሲዝም ሌኒንዝም ከመግባቱ በፊት ከባህላችን ጋር „የማይጣጣሙ“ አስተሳሰቦችና የአኗኗር ስልቶች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ አገራችን ውስጥ ሰተት ብለው በመግባት የህይወታችን አካል ለመሆን በቅተዋል። እራሳችን ያልፈጠርናቸው አያሌ ነገሮች በመግባት እንድንጠቀምባቸው ተደርጓል። ጥያቄው የውጭ ርዕዮተ-ዓለምን መዋሱ ላይ ሳይሆን እንዴት እንጠቀምበታለን ነው። በትክክል ገብቶናል ወይ? በማርክሲዝም ሌኒንዝም ቲዎሪ አማካይነት የኢትዮጵያን ህብረተሰብ አወቃቀር ማጥናትና ማወቅ ይቻላል ወይ? በጊዜው ይታይ የነበረውን ድህነት፣ የስራ-አጥነትና ረሃብ ምክንያቶችን ለማወቅ ማርክሲዝምንና ሌኒንዝምን እንደመመርመሪያ መሳሪያ ሊያገለግሉን ይችላሉ ወይ? ባጭሩ የኢትዮጵያን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የባህልና የስነ-ልቦና ሁኔታ በቲዎሪው አማካይነት ማወቅ ይቻላል ወይ? በተጨማሪም የማርክስና የሌኒን ቲዎሪዎች አገራችንን ወደ ዘመናዊነት ለማሸጋገር ያስችሉናል ወይ? እነዚህንና ሌሎች አያሌ ጥያቄዎችን ያቀረብን እንደሆን ብቻ ሚዛናዊ ፍርድ ለመሰጠት እንችል ይሆናል።
ለማንኛውም በአብዮቱ ወቅት የተፈጠረውን አሳዛኝ ሁኔታ አስመልክቶ የሚወነጀለው የተማሪው እንቅስቃሴና „ኮሙኒዝምን ተግባራዊ አደርጋለሁ“ ብሎ የተነሳውን የደርግን አገዛዝ ነው። ይሁንና ግን ዛሬ አገራችንና ህዝባችን ለገቡበት ፈታኝ ሁኔታ ተጠያቂው የማርክሲዝምና የሌኒንዝም ቲዎሪ ለመሆኑ በቴዎሪም ሆነ በኢምፔሪካል ደረጃ የተረጋገጠ ነገር የለም፤ በጊዜው በአብዮቱ ውስጥ የተሳተፉትና አሁንም በህይወት የሚገኙ አንዳንድ መሪዎች ማርክሲዝምን-ሌኒንዝምን ተጠያቂ ሲያደርጉ አልተሰማም። አብዮቱ ለምን እንደዚህ ዐይነት ምስቅልቅል ሁኔታዎችን አስከተለ? ለምንስ ሺህ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲገደሉ ተደረገ? ለሚሉት ጥያቄዎች በቂ ምክንያት ሲሰጡ አልተሰማም። ይሁንና የቀድሞ የኢህአፓ አባል የነበረው፣ በኋላ የብአዴን አባል አመራር የነበረውና ከነመለስ ዜናዊ ጋር ስልጣን ላይ የወጣው ታምራት ላይኔ „ማርክሲዝም ሌኒንዝም አሳስቶት“ እንደዚያ ዐይነቱን ወንጀል እንደፈጸመ እየደጋገመ ነግሮናል።
በእርግጥ በአብዮት ስምና በማርክሲዝም ሌኒንዝም ስም እንደዚያ ዐይነት ውርጅብኝና ግድያ ሲፈጸም በጊዜው ይህንን ሁኔታ የተመለከቱ ሰዎች፣ ወይም ደግሞ የዘመድ አዝማድ የተገደለባቸውን ሰዎች ዋናው ምክንያት ማርክሲዝም ሌኒንዝም አይደለም ብሎ ማሳመን በፍጹም አይቻልም። ማንኛውም ሰው ፍርድ የሚሰጠው ድርጊቱን የፈጸሙ ሰዎችን አስተሳሰብ በመመርመር፣ ያደጉበትን ህብረተሰባዊ ሁኔታ በማጥናት፣ እንደዚህ ዐይነቱ ርዕዮተ-ዓለም ከመግባቱ በፊት የአብዮቱ ተዋንያን የተኮተኮቱበትን ርዕዮተ-ዓለም በመመርመር አይደለም። ከዚህም በላይ ፍርድ በጅምላ ሲሰጥ ማን በመጀመሪያ ደረጃ ተኩስ እንደከፈተና፣ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ እንዲወጣ ለማድረግ እንደበቃ በፍጹም የሚጠይቅ የለም። ከዚህም ባሻገር በአብዮቱ ውስጥ የተደረገው ትንቅንቅ በውስጥ ኃይሎች ብቻ ሳይሆን የውጭ ኃይሎችም እጃቸው እንዳለበትና፣ በቀይና በነጭ ሽብር ውስጥ የማይናቅ እርኩስ ሚና እንደተጫወቱ ሊያወጣና ሊያወርድ የሚሞክር ሰው በፍጹም የለም። ኮሙኒዝምን ወይም ደግሞ የማርክሲዝምን ሌኒንዝም ርዕዮተ-ዓለም በጭፍን የሚጠላው ሰው ተጠያቂ የሚያደርገው ይህንኑ ርዕዮተ-ዓለም ነው። ይሁንና ግን ተደጋግሞ የሚዘነጋ ጉዳይ አለ። በመጀመሪያ ደረጃ የጊዜ ጉዳይ(Timing) አለ። ይህም ማለት አብዮቱ ሲፈነዳ ጊዜው አመቺ የሆነውን ያህል፣ በሌላ ወገን ደግሞ ኢምፔሪያሊዝምና ሌሎች አጎራባች አገሮች እንደዚህ ዐይነቱን መሰረታዊ ለውጥ አጥብቀው ለመዋጋት የሚያስችላቸው ኃይልና፣ ይህንን ፍላጎታቸውንም ተግባራዊ ለማድረግ የሚችል የውስጥ ኃይል እንደነበረ ነው። በሁለተኛ ደረጃ፣ አብዮቱ የፈነዳው በግብታዊ መንግድ ወይም ሳይታሰብ በመሆኑ የተሰበጣጠረውንና „የተለያየ ዓላማ“ የነበረውን ኃይል በአንድ መሰረተ-ሃሳብ ዙሪያ በማሰባሰብ እንዲታገልና አገር ለመገንባት እንዲነሳ ማድረግ በፍጹም አይቻልም ነበር። በሶስተኛ ደረጃ፣ የህዝቡ አስተሳሰብና፣ በተለይም ደግሞ የተማረው የህብረተሰብ ክፍል ይህንን ርዕዮተ-ዓለም የመቀበልና የአገር መገንቢያ መመሪያ የማድረግ አቅም አልነበረውም። የአገራችን የማቴሪያል ወይም ደግሞ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ግኑኝነት በጣም ደካማ ስለነበር የነቃና ለውጥን የሚፈልግ ኃይል ሊፈጥር አልቻልም። ለተወሰነ ጊዜ ካልሆነ በስተቀር በቆራጥነትና በተከታታይነት በአብዮቱ ጎራ ሊሰለፍ የሚችል ኃይል ማፍራት በፍጹም አይቻልም ነበር። በአራተኛ ደረጃ፣ ተራማጅ ነኝ በሚለው ሰፈር የተፈጠረው የእርስ በእርስ ሹከቻና ጥላቻ አብዮቱን አደጋ ውስጥ መጣሉ ብቻ ሳይሆን ተተኪ የማይገኝላቸውን በጊዜው ተማሩ የሚባሉ ምሁሮች እንዲያልቁ ተደረገ። በተጨማሪም በብዙ ሺህ የሚቆጠር ህዝብና ወጣት አለቀ። አብዛኛው በማያውቀው መንገድ የዚህኛው ወይም የዚያኛው ፓርቲ አባል በመሆን የእሳት እራት ሊሆን በቃ። በአምስተኛ ደረጃ፣ ካለምንም ሳይንሳዊ ጥናትና ካለበቂ ኢምፔሪካል መረጃ „አብዮት ሊሳካ የሚችለው ደም በማፍሰስ ብቻ ነው“ የሚለው አስተሳሰብ በብዛት ስለተስፋፋ፣ በተለይም በቂ ዕውቀትና ግንዛቤ ሳይኖረው አብዮቱ ውስጥ የተቀላቀለውና አልፎ አልፎም ብሶት የነበረው አጋጣሚ አገኘሁ በማለት በወንድሞቹና በእህቶቹ ላይ እንደዚህ ዐይነቱን አሰቃቂ ድርጊት እንዲፈጽም አደረገው። ባጭሩ አብዮቱ የቂም በቀል መወጣጫ ጊዜም ሊሆን በቃ።
ከዚህ ስንነሳ መጠየቅ ያለብን ጉዳይ እንዲያው በቁንጽልና ፊት ለፊት የሚታየውን ነገር እንደዋና ምክንያት አድርገን በመውሰድ ሳይሆን ከዚህ ባሻገር ያሉትን ምክንያቶች በመመርመር ነው። በተለይም አሁን በቅርቡ የቀድሞ የመኢሶን መሪ የነበረውን የአቶ አንዳርጋቸው አሰግድን የቃለ-መጠይቅ ምልልስ ከተመለከትኩኝና ካዳመጥኩኝ በኋላ ጠያቂው አቶ ደረጀ ኃይሌ በደርግ ወታደሮች በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉትንና ያቀረባቸውን የአብዮቱ ተዋንያንን ፎቶዎች ስመለከት ነገሩ እንደዚህ በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ አይደለም። በሌላ አነጋገር፣ ጠለቅ ብለን በመሄድ በተለይም በአብዮቱ ውስጥ የተሳተፈውንና በእልቂት ውስጥ ዋና አቀነባባሪ የሆኑትን ሰዎች ስነ-ልቦና መመርመር ያለብን ይመስለኛል። አሁንም በሌላ አነጋገር መጠየቅና መመርመር ያለብን ጉዳይ አንድን ርዕዮተ-ዓለም በጭፍን ከመወንጀል ይልቅ የራሳችንን ስነ-ልቦናና እንደዚህ ዐይነቱን ህብረተሰብአዊ ፕሮጀክት ወይም አብዮት ካለደም መፋሰስና ሳንወነጃጀል ማስተናገድ እንችላለን ወይ? ብለን ነው መጠየቅ ያለብን። በእኔ ዕምነት አንችልም የሚል ነው። ለዚህ ዋናው ምክንያት መንፈሳችን ለዚህ የተዘጋጀ አልነበረም፤ በአንድ አስተሳሰብ ዙሪያ በመሰባሰብ ለአንድ ዓላማ የመታገል ሞራላዊ ብቃት አልነበረንም የሚል ነው። ዞሮ ዞሮ ባህርያችን በጣም አስቸጋሪ ነው ማለት ነው። ከዚህ በመነሳት ፖለቲካን እንደ ዓላማ ወይንም የመታገያ መሳሪያ አድርገን ከመውሰዳችን በፊት መጓዝ ያለብንን ክንውናዊ ሂደት የተረዳን አልነበርንም። በሌላ አነጋገር ካለመንፈሳዊ አብዮት በፊት ፖለቲካዊና ማህበራዊ ለውጥ ማምጣት በፍጹም አይቻልም። ይህም ማለት የግዴታ መንፈስን ከማንኛውም እቡይ ተግባር ማጽዳት ያስፈልጋል። የህብረተሰብን ጥያቄ በአርቆ-አስተዋይነት መነፅር በበቂው ማጥናትና መመርመር የሚያስፈልግ ይመስለኛል። በተለይም በዛሬው ወቅት በአገራችን ምድር የሚታየውን አደገኛ ሁኔታ ለመወጣትና ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የምንፈልግ ከሆነ ከመንፈስ አብዮትና ጠለቅ ካለ ምሁራዊ ዝግጅት ውጭ ሌላ አማራጭ ነገር በፍጹም ሊኖር አይችልም።
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።