spot_img
Friday, June 21, 2024
Homeነፃ አስተያየትተደራድረን የጋራ አገር መፍጠር ካልቻልን አማራጩ ደም እየተፋሰስን መኖር ነዉ!

ተደራድረን የጋራ አገር መፍጠር ካልቻልን አማራጩ ደም እየተፋሰስን መኖር ነዉ!

ኤፍሬም ማዴቦ (emadebo@gmail.com)
ህዳር 4 , 2012 ዓ. ም.

አገራችን ኢትዮጵያ ዉስጥ የብሄር እኩልነትና እራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ የፖለቲካ ቅርፅ ይዞ የአደባባይ መፈክር ከሆነ ብዙ አስርተ አመታት ተቆጥረዋል። መሬት ለአራሹ የሚል ሁሉን አቀፍ መፈክር አንግቦ የቀዳማዊ ኃ/ሥላሴን ስርአት ከስር መሰረቱ ያናጋዉ የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ የኋላ ኋላ ለሁለት ሲከፈል በአንደኛዉ ተርታ የተሰለፉት ሃይሎች ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉ ጭቆና የብሄር ጭቆና ነዉ የሚሉና ብዙም ሳይቆዩ መሳሪያ አንስተዉ ጫካ የገቡ ሃይሎች ነበሩ። ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለሚታየዉ አለመረጋጋት፥ የብሄረተኝነት ስሜት መነሳሳትና መግነን ዋነኛ ተጠያቂዎችም እነዚሁ ሃይሎች ናቸዉ። አገራችን ኢትዮጵያ የምትገኘዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን አለም አቀፉ ማህበረሰብም ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶት በየቀኑ በሚከታተለዉ የለዉጥ ሂደት ዉስጥ ነዉ። ሆኖም ይህ የለዉጥ ሂደት ተስፋ ብቻ ሳይሆን “ምን እሆናለሁ” በሚል ፍርሃትም የተሞላ ነዉ። ፍርሃቱ ብዙ ምክንያት አለዉ። የወደፊቷን ኢትዮጵያ ይረከባል ተብሎ የሚጠበቀዉ ወጣት ትዉልድ በየዩኒቨርሲቲዉ ዘር ቆጥሮ እርስ በርስ እየተጋደለ አገራችን ኢትዮጵያን ተረካቢ አልባ እያደረጋት ነዉ። ለዘመናት ዕቁብ፥ዕድር፥ደቦና በቅዱስ ታቦታት የተሰየሙ ማህበራት እያስተባብሩት ወገኔ እየተባባለና ቡና እየተጣጣ በጉርብትና የኖረ ህዝብ ዛሬ በአንድ ወቅት ቡና የጋበዘዉን ወገኑን ክልሌን ለቅቀህ ሂድ እያለ ነዉ። ከተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች መጥቶ በከተሞች የሚኖረዉ ህዝብ እሱ የገነባቸዉን ከተሞች “የኔ ናቸዉ” የሚል ድምፅ እየበረከተ በመምጣቱ የከተማ ነዋሪዉ ህዝብ ሶስትና አራት ትዉልድ የኖርኩበት ቦታ የኔ ካልሆነ እኔ ማነኝ ቦታዬስ የት ነዉ የሚል ጥያቄ እራሱን እየጠየቀ መልስ ማግኘት ባለመቻሉ ከፍተኛ ስጋት ዉስጥ ወድቋል። ለወትሮዉ ጦርነት የሚባል ቃል ሲሰማ ከያለበት ተጠራርቶ በጋራ የዉጭ ወራሪዎችን አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶና አሳፍሮ የሚመልስ ህዝብ ዛሬ በሚያሳፍር መልኩ “የኔ ክልል” “ያንተ ክልል” እየተባባለ የጦርነት ነጋሪት ይጎስማል። 

ምንድነዉ ለዚህ በታሪካችን አይተነዉም ሰምተነዉም ለማናዉቀዉ የእርስ በርስ መተላለቅ የዳረገን? አንደአበሻ ቀሚስ ጥለት አምሮና ደምቆ ሊያሳምረን የሚገባን ብዝሃነታችን ለምንድነዉ እንድንጣላና ደም እንድንፋሰስ የሚያደርገን? ሁለትና ሶስት ሚለንየም ወደኋላ ስንሄድ የራሱ ፊደልና ስልጣኔ የነበረዉ ህዝብ፥ የአክሱምን ሃዉልት ያቆመ ህዝብ፥ ዕጹብ ድንቅ የላሊበላ አብያተ ክርስትያናትን የሰራና ጂማ አባጅፋር እና ጎንደር ፋሲለደስ ቤተ መንግስቶችን የገነባ ህዝብ ከሱ እጅግ በጣም ወደኋላ ቆይተዉ የመጡ ስልጣኔዎች የመሬቱ አልበቃ ብሏቸዉ ማርስና ጨረቃን ሲመኙ እሱ ምን ነክቶት ነዉ መሬት ላይ ተስማምቶ መኖር ያቃተዉ? ንጉስ ኤዛና ክርስትናን የመንግስታቸዉ ሐይማኖት አድርገዉ ሲያዉጁ መንግስትም ሃይማኖትም ያልነበራቸዉ ህዝቦች ዛሬ እነሱ ጠንካራ መንግስት፥ የተረጋጋ አገር፥ ያደገ ኤኮኖሚና ቴክኖሎጂ ባለቤቶች ሆነዉ አለምን ሲያዝዙ እኛ ካለነሱ እርዳታ መኖር ያቃተን ለምንድነዉ? 

ለመሆኑ ለምንድነዉ ይህ እንደ ኮሶ ሊመረንና ሊያሳፍረን የሚገባ ንጽጽራዊ ኋላ ቀርነት የማይመረንና የማይቆጨን? ለምንድነዉ ከትልቅነት ወደ ትንሽነት በመዉረዳችን ልንቆጭ ሲገባን ጭራሽ የባሰ ትንሽነት የሚያምረን? ለምንድነዉ አሳምረን የመገንባት ሙሉ ችሎታዉ እያለን ሌሎች አሳምረዉ የገነቡትን “የኔ ነዉ” ማለት የሚቀናን? ለምንድነዉ ለምለም መሬት ባየን ቁጥር “የኛ ነዉ” በሚል እዉርነት ተነሳስተን መሬት እየተቀማማን እኛም መሬቱም ጦማችንን የምናድረዉ? 

የኢትዮጵያ ልህቅ ለምንድነዉ የሌላዉ አለም ልህቅ  አላምጦ የጣለዉን የፖለቲካ ማስቲካ እሱ ከተጣለበት እየለቀመ ጣፍጦት እንደገና የሚያኝከዉ? መቼ ነዉ የኢትዮጵያ ምሁር “ዶክተር” የሚባል የትምህርት ደረጃ መለኪያን እንደ ስም ማሳመሪያ ጌጥ መጠቀሙን ትቶ አገርን የሚያድን የጥናትና ምርምር ስራ የሚሰራበት? መቼ ነዉ ምሁሮቻችን “ቆይ ገና ነዉ አልለየለትም” የሚል የፈሪ ምክንያት መደርደራቸዉን ትተዉ ለዚህ እዉነትና እዉቀት ለራበዉ ወገናቸዉ እዉነትና እዉቀት የሚመግቡት?

አገራችን ኢትዮጵያ ዛሬ የምትገኝበት የታሪክ ምዕራፍ አያሌ የአዉሮፓ አገሮች ከመቶ ሃምሳ አመታት  በፊት ያለፉበት የታሪክ ምዕራፍ ነዉ። የአገረ-ግንባታ ሂደት (Nation Building Process) በብዙ አገሮች ዉስጥ ልህቃኑን አጨቃጭቋል፥ ህዝብን ከህዝብ አጋድሏል፥ ንብረት አዉድሟል። ይህ የራሱን አገር በሚገነባ ማህበረሰብ መካከል መከሰት የማይገባዉ ክስተት የሚከሰተዉ በአገር ግንባታ ሂደት ዉስጥ ማን፥ ምን፥ የት፥ መቼና እንዴት በሚሉ ጥያቄዎች ላይ እኛ ሰዎች ስለማንስማማ ነዉ። ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚታየዉ ሁኔታ ግን ካለመስማማትም አልፎ ላለመስማማት የተማማልን ነዉ የሚመስለዉ። ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፈን እየላላ የመጣዉን አገራዊ አንድነታችንን ማጠናከር ሲገባን ጭራሽ ላልቶ ሊፈታ በቀረበ  አንድነት ዉስጥ ትናንሽ የጎንዮሽ አንድነት ለመፍጠር እንሯሯጣለን። ከሩብ ምዕተ አመት በላይ ህገ መንግስቱን እንዳሰኘዉ ሲደፈጥጥ የከረመ ሀይል ዛሬ ህገ መንግስቱ ካልተከበረ ሞቼ አገኛለሁ እያለ ብቻዉን ታንጎ ይጨፍራል። ከፌዴራሊዚም ዉጭ ሌላ የሚያዋጣን የመንግስት መዋቅር የለም ተብሎ በሚሰበክበት አገር ዉስጥ ከራሱ ዉጭ ማንንም ላለመስማት ጆሮዉን የዘጋ ሀይል ከሱ በላይ ፌዴራሊት የሆኑ ሀይሎችን “አሃዳዊ ስርአት ናፋቂዎች” እያለ የሞኝ ጩኸት ይጮሃል። ያሁኑ ይባስ እንዲሉ አሁንማ ጭራሽ ምርጫዉ ካልተካሄደ ብቻችንን መንግስት እንመሰርታለን የሚል ፈረንጆቹ ለልጆቻቸዉ የሚነግሩት አፈታሪክ (Fairytale) የተገላቢጦሽ በትናንሽ ሰዎች ለአዋቂዎች እየተነገረ ነዉ። አገራችን ኢትዮጵያ እነዚህ ሁሉ ምስቅልቅሎች እንደ ክረምትና በጋ የሚፈራረቁባት በአንድ በኩል ማርክሲዝም፥ሊብራሊዚምና አብዮታዊ ዲሞክራሲ ተቀላቅለዉበት የራሱን ወጥ የሆነ አገራዊ ፍልስፍና መቀመር ያልቻለ የፖለቲካ ልህቅ በሌላ በኩል ደግሞ ከብሄር ዉጭ ሌላ ምንም እዉነት የለም ብለዉ አይናቸዉን በጨርቅ ያሰሩ የብሄር ልህቃን ጎራ ለይተዉ የአገራችንን የፖለቲካ መድረክ ስለተቆጣጠሩት ነዉ። አገራችን ኢትዮጵያ ከዚህ ለዘመናት ቀስፎ ከያዛት ክፉ የፖለቲካ በሽታ ድና ልጆቿን አይዟችሁ አለሁላችሁ የሚትልበት ግዜ መምጣቱ አይቀርም። ይህ ግዜ የሚመጣዉ ግን እኛ ልጆቿ ወደ ዉስጥም ወደ ዉጭም መመልከት ስንጀምርና ችግራችን የአገራችን ድህነት ብቻ ሳይሆን የኛም ተማርን የምንል ልጆቿ የአዕምሮ ድህነት መሆኑን በዉል ስንረዳ ነዉ። 

አገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ብሄር ብሄረሰቦች አገር ናት- ይህ ማንም ምንም ሊለዉጠዉ የማይችል አብሮን የኖረና አብሮን የሚኖር እዉነት ነዉ። ተጋብተናል? አዎ ተጋብተናል። ተዋልደናል? አዎ ተዋልደናል። ግን ይህ መጋባታችንና መዋለዳችን የጋራ አድማሳችንን ያሰፋዋል እንጂ ማንነታችንን ጨፍልቆ አንድ ማንነት ዉስጥ አይከተዉም። ኦሮሞነት፥ አማራነት፥ ሶማሌነት፥ ሲዳማነት፥ሃድያነት፥አፋርነት ወዘተ ሁሉም ክቡር ማንነቶች ናቸዉ። እነዚህ ክቡር ማንነቶች ግን የማይተዋወቁ፥ የጋራ ታሪክ የሌላቸዉና ለየብቻቸዉ የቆሙ ነጠላ ማንነቶች አይደሉም። ይተዋወቃሉ፥ የሚጋሩት አገር፥ ታሪክና ባህል አላቸዉ። ኢትዮጵያን “ኢትዮጵያ” ያሰኟት አያሌ ብሄር ብሄረሰቦች መብትና ነጻነታችዉ ሳይከበርና በእኩልነት ሳይታዩ ለብዙ አመታት አብረዉ ኖረዋል። የዉጭ ወራሪ ሲመጣ በጋራ ተዋግተዉና የኢትዮጵያን ዳር ድንበር አስከብረዉ “በቅኝ ገዥዎች ያልተገዛ ህዝብ” የሚል አኩሪ ስም እንዲኖረን አድርገዋል። ዶጋሌ፥ መተማ፥ አድዋ፥ ወልወል፥ ካራማራና ባድሜ ላይ አገሬ ብለዉ ተቃቅፈዉ ተዋግተዉ ተቃቅፈዉ ወድቀዋል። ስለዚህ እነዚህ ቁጥራቸዉ ወደ ሰማኒያ የሚደርስ የተለያዩ ማንነቶች የጋራ መታወቂያችን ነዉ ብለዉ በአላማቸዉ ያጸኑት፥ በደማቸዉ የጻፉት፥በአጥንታቸዉ ያጠነከሩት ኢትዮጵያዊ የሚባል ከትዉልድ ወደ ትዉልድ የሚተላለፍ ክቡር ማንነት አለ።

አገራችን ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የአገረ-ግንባታ (Nation Building) ሂደቶች ዉስጥ አልፋለች። ዳግማዊ ሚኒልክ በ1880ዎቹ አጋማሽ አካባቢ የጀመሩት የአገረ-ግንባታ ሂደት የዛሬዋን ትልቅ ኢትዮጵያ ሰጥቶናል። ሆኖም ከሳቸዉ በኋላ ኢትዮጵያን ለረጂም አመታት የመሩት ቀዳማዊ ኃ/ሥላሤና(43 አመት) ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማሪያም (17 አመት) ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት የሚያቅፍ የፖለቲካ ስርአት መፍጠር ባለመቻላቸዉ ዳግማዊ ሚኒልክ የጀመሩት አገረ-ግንባታ ሂዳት ከፍጻሜ መድረስ አልቻለም። በ1983 ዓም የብሄር ሀይሎች የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስልጣን ሲጨብጡ የዛሬዋን ምስቅልቅሏ የወጣ ኢትዮጵያ የፈጠረ አዲስ የአገረ-ግንባታ ሂደት ተጀመረ። ይህ በህወሓት የተመራዉ፥ የብሄር ማንነትን የፖለቲካ መሰረቱ ያደረገና ባጠቃላይ የቡድን መብትን አስቀድማለሁ በሚል ባዶ ጩኸት የክልልንም የማዕከልንም ስልጣን ብቻዉን ተቆጣጥሮ የቡድንንም የግለሰቦችንም መብት የረገጠ የአገረ-ግንባታ ሂደት ኢትዮጵያዊ ማንነትን ለማጥፋት ሃያ ሰባት አመት ከታገለ በኋላ ሳይሳካለት ቀርቶ ከሱ ቀደም እንደነበሩት ሁለት ስርአቶች በህዝባዊ ትግል ከስልጣን ተወግዷል። እነዚህ በአንድ በኩል የተለያዩ ማንነቶችን ጨፍልቀዉ አንድ ወጥ ማንነት ለመፍጠር የተደረጉ ሙከራዎች እና በሌላ በኩል ደግሞ አገረ ኢትዮጵያን በብሄር ማንነት ላይ ለመመስረትና የሁላችንም የጋራ ማንነት የሆነዉን “ኢትዮጵያዊ ማንነት” ለማደብዘዝ የተሞከሩ ተከታታይ ሙከራዎች በአገራችን ኢትዮጵያ የኤኮኖሚና ማሀበራዊ ዕድገት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ ከማድረግ ባሻገር አንዱ ሌላዉን ማሸነፍ እንዳልቻለና ለወደፊትም እንደማይችል በተግባር አሳይተዉናል። በእነዚህ በሁለት በተለያየ መልኩ በተደረጉ የአገረ-ግንባታ ሙከራዎች ዉስጥ እንዲጨፈለቁ የተደረጉ ማንነቶች (የብሄር ማንነት እና ኢትዮጵያዊ ማንነት) ላለመጨፍለቅ ባደረጉት መራራ ትግል የአገረ-ግንባታዉ ሂደት ፍጻሜ ላይ እንዳይደርስ አድርገዋል። ይህ የሚያሳየን እኛ ኢትዮጵያዊያን አንደቀድሞዉ የአገረ-ግንባታ ሂደቶች ማንም ሳይጫነን እኛዉ እራሳችን ቁጭ ብለን ተደራድረን ይህንን ከብዙ አመታት በፊት የተጀመረዉን የአገር-ግንባታ ሂደት ከፍጻሜ ማድረስ እንዳለብን ነዉ።

ኢትዮጵያ ዉስጥ ብሄሮች አሉ፥ የብሄር ማንነት አለ፥ ብሄረተኞች አሉ፥የብሄር ፖለቲካም አለ። በአንፃሩ ኢትዮጵያዊ ብሄረተኝነትና ለኢትዮጵያ የሚበጃት የዜግነት ፓለቲካ ነዉ ብሎ የሚሞግት ሃይልም አለ። የአገራችን ኢትዮጵያን ያለፉት ሰማንያ አምስት አመታት የፖለቲካ ታሪክ ስንመለከት በመንግስት ደረጃ የብሄር ማንነትን ለማደብዘዝ ለዘመናት የተደረገዉ ሙከራ የተቋጨዉ የብሄር ሀይሎችን ስልጣን ላይ በማዉጣት ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ በጠመንጃ ሀይል ስልጣን የጨበጡ የብሄር ሀይሎች ኢትዮጵያዊ ብሄረተኝነትን ለማጥፋትና የብሄር ማንነትን ለማንገስ ያደረጉት የ27 አመት ሙከራ የተጠናቀቀዉ ኢትዮጵያዊ ብሄረተኝነት የሚለመልም እንጂ የማይጠፋ ጠንካራ መሰረት ያለዉ ብሄረተኝነት መሆኑን በማረጋገጥ ነዉ። ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ ፊትለፊት የተፋጠጡትም እነዚሁ ሁለት ሀይሎች ናቸዉ። እነዚህ ሁለት ሃይሎች ከታሪክ የሚማሩ ከሆነ የሁለቱም ታሪክ የሚነግረን አንድ ትልቅ ሃቅ አለ- እሱም የብሄር ፖለቲካ አራማጆች በምንም መልኩ ከእነሱ መሰረታዊ ጥቅም ጋር የማይጻረረዉን እና የወል ስብስቦች መብት፥ ነጻነትና እኩልነት በተለይ ለ”እራስን በራስ የማስተዳደር” መብት መከበር ሌት ከቀን ከሚሰራዉ ኢትዮጵያዊ ብሄረተኝነት ጋር መፋለም እንደሌለባቸዉ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ብሄረተኝነትም ካቀፈዉና ካከበረዉ መልሶ የሚያቅፈዉንና የሚያከብረዉን የብሄር ማንነትን ለመጨፍለቅ ሙከራ ማድረግ እንደሌለበት ነዉ። ይልቁንም ለሁለቱም ሃይሎች የሚበጀዉ የኔ ከሚሉት ከየራሳቸዉ ጎጥ ወጣ ብለዉና ጠረቤዛ ዙሪያ ቁጭ ብለዉ ምን አይነት ህገመንግስት ይኑረን? ምን አይነት የምርጫ ስርአት ይኑረን? ምን አይነት የመንግስት ቅርፅ ይኑረን? ምን አይነት የፖለቲካ ስርአት እንመስርት? ኢትዮጵያዊ ማንነትና የብሄር ማንነት እንዴት አንዱ በሌላዉ አዉድ ዉስጥ መኖር ይችላል በሚሉ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ መደራደርና የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ነዉ። የዚህ ድርድር ዉጤት ለሁላችንም እኩል የሆነች፥ የህግ የበላይነት የተረጋገጠባት፥ የግለሰብና የቡድንን መብት የሚከበርባት እና እንዲሁም ፍትህ፥ ነጻነት እኩልነትና ዲሞክራሲ የሰፈነባት ኢትዮጵያ መሆን አለባት። አንዴት?

 “እንዴት” . . . .  እኛ ኢትዮጵያዊያን በ1966 እና በ1983 ዓም ሁለት መልካም አጋጣሚዎችን አግኝተን ያልመለስነዉ፥ ዛሬ ለምናያቸዉ የፖለቲካ ዉጣዉረዶችና የተለያዩ ችግሮች የዳረገን እና ዛሬም ሌላ ዕድል ምናልባትም የመጨረሻ ዕድል አግኝተን የሚገባዉን አጽንኦት ያልሰጠነዉ ጥያቄ ነዉ። የዚህ ጽሁፍ መሰረታዊ አላማም እባካችሁ በተለያየ ጎራ የተሰለፋችሁ ኢትዮጵያዊያን ኑ አንድ ላይ ሆነን እንምከርና ለዚህ ከላይ “እንዴት” ብሎ ለቀረበዉ ጥያቄ የማያዳግም መልስ እንስጥ የሚል ነዉ። ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያ እጅግ በጣም ወሳኝ በሆነ የሽግግር ወቅት ላይ ትገኛለች። ይህ የሽግግር ወቅት ባለፉት ሃምሳ አመታት ኢትዮጵያ ዉስጥ የተነሳዉን የሰብዓዊ መብት መከበር ጥያቄ፥ እራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ፥ የኤኮኖሚ ነጻነት ጥያቄና እንዲሁም የፍትህና የእኩልነት ጥያቄ ላንዴና ለመጨረሻ ግዜ መመለስ አለበት፥ ወይም የተለያዩ ማንነቶች የሚያነሱትን የቋንቋችን፥ የባህላችንና የታሪካችን ይከበር ጥያቄ፥ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ጥያቄና የእኩልነት ጥያቄ መመለስ ለሚችል ዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ጠንካራ መሰረት መጣል አለበት። ምን አይነት ዲሞክራሲያዊ ስርአት ብንገነባ ነዉ የተረጋጋ አገር ፈጥረን በሰላም መኖር የምንችለዉ የሚለዉን ጥያቄ አሉታዊ በሆነ መልኩ መመለስ የሚያስችሉን ብዙ የቅርብና የሩቅ አገሮች ልምዶች አሉን፥ ከከሸፉ የአገራችን ተሞክሮዎችም ብዙ የምንማረዉ አለ።  

ይህ ሁሉ እንዳለ ሆኖ ግን በአንድ በኩል ቋንቋንና ብሄርን  መሰረት ያደረገዉን ፌዴራሊዚም ትነኩና እቺ አገር ትፈርሳለች እያሉ የሚዝቱ የብሄር ልህቃን በሌላ በኩል ደግም የብሄር ፖለቲካ በህግ መከለከል አለበት እያለ የሚጮህ የ“አንድነት ሀይል” ነኝ ባይ ልህቅ ባለባት ኢትዮጵያ ዉስጥ እንዴት አድርገን ነዉ ሁሉን አቀፍ ዲሞክራሲያዊ ስርአት የምንገነባዉ? ለመሆኑ ከክልሌ ዉጣልኝ ወይም ወደ ክልሌ አትድረስብኝ የሚለዉን የብሄር አለቃና ኢትዮጵያ ዉስጥ በየትኛዉም ክልል፥ ዞንና ወረዳ ዉስጥ እንዳሰኘኝ የመንቀሳቀስ ሙሉ መብት አለኝ የሚለዉን የዜግነት ፖለቲካ አቀንቃኝ ማቀራረብና እነዚህ ሀይሎች ተደራድረዉ ጠንካራ አንድነት ያለዉ አገር እንዲፈጥሩ ማድረግ ይቻላል? ምንድነዉ የብሄር ፖለቲካ አራማጆች የሚፈልጉት? ጥያቄያቸዉስ ምንድነዉ? የዜግነት ፖለቲካ አራማጆችስ ምንድነዉ የሚፈልጉት? ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚታየዉ  የእርስ በርስ ግጭትና የፖለቲካ አለመረጋጋት ከብሄር ወይም ከቡድን መብት ጥያቄ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነዉ። ታዲያ አንድ ኢትዮጵያዊ እንደዜጋ የግለሰብ መብቱ፥ በቡድን አባልነቱ ደግሞ የቡድን መብቱ ሳይሸራረፍ የሚከበርባትን ወይም ጠቅለል ባለ አነጋገር የቡድን መብትና የግለስብ መብት ሙሉ በሙሉ የሚከበርባትን ኢትዮጵያን ገንብተን ሙሉ ሀይላችንን ድህነትና ኋላ ቀርነት ላይ ማሳረፍ የምንጀምረዉ መቼ ነዉ? 

አገራችን ኢትዮጵያ በሃምሳ አመት ለሶስተኛ ግዜ እጅግ በጣም ወሳኝ በሆነ የታሪክ መታጠፊያ ምዕራፍ ላይ ቆማለች። እኛ ኢትዮጵያዊያን ይህንን ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ የምንጽፈበት መንገድ እንደ አገር መቀጠል መቻላችንና አለመቻላችን ላይ ትልቅ አንድምታ አለዉ። በዚህ ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ መደምደሚያ ላይ በወርቅ ቀለም መጻፍ ካለባቸዉ ቁምነገሮች ዉስጥ አንዱና ዋነኛዉ  . . . . . የዘመናት አብሮ መኖር ልምድ ያለዉ የኢትዮጵያ ህዝብ በአካባቢ እራሱን በራሱ እያስተዳደረ በማዕክል የፖለቲካ ስልጣን ተጋርቶ የሚኖርበትንና ፍትህ፥ ነጻነትና እኩልነት የሚረጋገጥበትን ዲሞክራሲያዊ ስርአት ፈጠረ የሚል መሆን አለበት። 

ኢትዮጵያ ዉስጥ በሽግግሩ መንግስት ወቅት ተረቅቆ የጸደቀዉ ህገ መንግስት የዛሬዋን ኢትዮጵያን እንደ አገር አዋቅረዉ ያቆሙ እጅግ በጣም መሰረታዊና በአገረ-መንግስት ግንባታ ሂደት ወቅት መዘለል የሌለባቸዉን ሶስት ህገ መንግስታዊ ጥያቄዎች መልሷል። እነዚህ ሶስት መሰረታዊ ጥያቄዎች የምርጫ ስርአት (አብላጫ ድምፅ)፥ የመንግስት ቅርፅ (ፓርላማ ስርአት) እና የመንግስት መዋቅር (ፌዴራሊዝም) ናቸዉ። እነዚህ ሶስት ተቋሞች የአንድን የፖለቲካ ማህበረሰብ ማንነት የሚቀርጹና በማህበረሰቡ የፖለቲካ፥ የኤኮኖሚና ማህበራዊ ህይወት ላይ የረጂም ግዜ አሻራ የሚያሳርፉ ተቋሞች ስለሆኑ የተቋማቱ ምርጫ ሲደረግና የተመረጡት ተቋማት ዲዛይን ሲደረጉ ልህቃኑንና ምሁራኑን ብቻ ሳይሆን የህዝብ ተወካዮችንና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ህዝብንም በቀጥታ የሚያሳትፉ መሆን አለባቸዉ። በ1980ዎቹ ኢትዮጵያ ዉስጥ የነበረዉ የሽግግር መንግስት ሁሉንም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባለድርሻዎች በእኩልነት ያላሳተፈና አንዳንዶቹን ደግሞ ጭራሹንም ያላሳተፈ በመሆኑ በሽግግሩ ወቅቱ የተወሰኑት ትልልቆቹ ዉሳኔዎች የህዝብን ይሁንታ ያገኙ ዉሳኔዎች አልነበሩም። ለዚህም ይመስላል ባለፉት ሃያ ሰባት አመታትና ዛሬም ጭምር አንዳንዶቹን ተቋሞች ይቀየሩልን አንዳንዶቹን ደግሞ እንደገና በአዲስ መልክ ይዋቀሩልን የሚል ህዝባዊ ጥያቄ በየአደባባዩ የሚሰማዉ።

የዚህ ጽሁፍ ጸሃፊ አገራችን ኢትዮጵያ ዛሬ በተለይ አሁን የምትገኝበት ታሪካዊ ወቅት ከላይ የተዘረዘሩትን አምስት ዋና ዋና ህገ መንግስታዊ ጥያቄዎችና ሌሎችንም ህዝባዊ ጥያቄዎች መልሰን አገራችንን በጠንካራ የዲሞክራሲ መሰረቶች ላይ ማቆም ያለብን ግዜ ነዉ ብሎ ያምናል። እነዚህ ጥያቄዎች እንደ ከዚህ ቀደሙ በሃይለኛ ግለሰቦች፥ በጥቂት እኛ ነን መወሰን ያለብን በሚሉ ቡድኖች ወይም የህዝብና የአገር አደራን ባልተሸከሙ ሰዎች መመለስ የለባቸዉም። ዛሬ በአንድ በኩል የወደፊቷን ኢትዮጵያ በብሄር መነጽር ብቻ የሚመለከቱ የተደራጁ ሃይሎች አሉ፥ በሌላ በኩል ደግሞ የወደደፊቷን ኢትዮጵያ በዜግነት መነጽር የሚመለከቱ ሃይሎች አሉ። ኢትዮጵያ ሁለቱንም መሆን አትችልም፥ ወይም የአገራችንን የፖለቲካ መሰረት ዜግነትም ማንነትም መሆን አይችልም። ስለዚህ ወደድንም ጠላን የወደፊቷ ኢትዮጵያ ዜግነትንና ማንነትን አዛምደዉ እነዚህ ሁለት ማንነቶች ተቃቅፈዉ አንድ ላይ በሰላም እንዲኖሩ የማድረግ ሃላፊነት የተጣለባቸዉ የማንነት ፖለቲካና የዜግነት ፖለቲካ አራማጆች ድርድር ዉጤት መሆን አለባት። 

ዛሬ ኢትዮጵያን በመምራት ላይ የሚገኘዉ በጠ/ሚ አቢይ አህመድ የሚመራዉ የሽግግር መንግስት ታሪክ የጣለበት አንድ እጅግ በጣም ትልቅ ሃላፊነት አለበት። ይህ ታሪካዊ ሃላፊነት ደግሞ በአንድ ሰዉና በአንድ መንግስት ዘመን ዉስጥ ቀርቶ በአንድ አገርና ህዝብ ታሪክ ዉስጥም በሺና ሁለት ሺ አመታት አንድ ግዜ ብቻ የሚገኝ በጣም ትልቅ አገራዊ ሃላፊነት ነዉ። ይህ ሃላፊነት አገር የማዳን ሃላፊነት ነዉ። ይህ ሃላፊነት የራሱ መብትና ነጻነት ሳይከበርለት የአገሩንና የጎረቤቶቹን ነጻነት ያስከበረ ህዝብ መብቱና ነጻነቱ ተከብሮ በእኩልነት እንዲኖር የማድረግ ሃላፊነት ነዉ። ይህ ሃላፊነት ኢትዮጵያ የሚባል ስም በአለም ካርታ ላይ ዘለአለማዊነቱ እንዲረጋገጥ የማድረግ ሃላፊነት ነዉ። 

የኢትዮጵያ ህዝብ ከጠ/ሚ አቢይ አህመድ መንግስት በጉጉት ከሚጠብቃቸዉ ስራዎች ዉስጥ  አንዱና ትልቁ “ማንነት” እና “ዜግነት” በሚል ጎራ ተለያይተዉ ሆድና ጀርባ የሆኑትን ሁለት ጎራዎች ወደ ድርድር ጠረቤዛ በማምጣት የወደፊቷን ኢትዮጵያ ቅርፅና ይዘት የሚወስኑ ትልልቅ ጥያቄዎችን እንዲመልሱ ማድረግ ነዉ። ዛሬ የኢትዮጵያ መንግስት ጎንበስ ቀና የሚልለት ትልቁ ግብ የ2012ቱን ምርጫ በሰላም ማገባደድ ይመስላል። ኢትዮጵያ የምትገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ ግን አገር አቀፍ ምርጫ ቀርቶ ተራ የእግር ኳስ ጨዋታም በሰላም ተጀምሮ በሰላም ለማለቁ ዋስትና የሚሰጥ አይደለም። ደግሞም ምርጫ ወደዋናዉ ግባችን የሚወስደን መሳሪያ ነዉ እንጂ ምርጫዉ በራሱ ግብ አይደለም። የ2012ቱ ምርጫ ነጻና ፍትሃዊ ሆኖ ቢካሄድም ዛሬ አገራችን ዉስጥ በ“ማንነት” እና በ“ዜግነት” ጎራዎች መካከል ያለዉን ሽኩቻና ዉጥረት አያቆምም፥ ወይም ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ስለተካሄደ ብቻ ዛሬ የምናያቸዉ የብሄር ግጭቶችና ግድያዎች አይቆሙም። እነዚህ ግጭቶችና ግድያዎች የሚቆሙት ከግጭቶቹ ጀርባ ያሉት ጥያቄዎች መልስ ሲያገኙ ብቻ ነዉ። ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግስት ከምርጫዉ በፊት መሰራት ላለባቸዉ ትልልቅ አገር አድን ስራዎች መንገድ ማመቻቸት አለበት። ምንድናቸዉ እነዚህ አገር አድን ስራዎች? 

ኢትዮጵያ ብዙ ብሄር ብሄረሰቦች የሚኖሩባት አገር ናት፥ እነዚህ ብሄር ብሄረሰቦች አንዳንዶቹ ብዙ ህዝብ ያላቸዉ ትላልቅ ብሄር ብሄረሰቦች ናቸዉ፥ አንዳንዶቹ ደሞ አናሳ ብሄር ብሄረሰቦች ናቸዉ። በሌላ በኩል ደግሞ በአንዳንድ ብሄር ብሄረሰቦች ክልል ዉስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸዉ የሌላ ብሄር አባላት ይኖራሉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚካሄድ ምርጫ አንዱና ትልቁ ስራ ለአናሳ ብሄር ብሄረሰቦችና ተሰበጣጥረዉ ለሚኖሩ ህዝቦች ቁጥራቸዉን በሚመጥን መልኩ ፓርላማ ዉስጥ ዉክልና ማግኘታቸዉን ማረጋገጥ ነዉ። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ዛሬ በስራ ላይ ያለዉን አብላጫ ድምፅ የምርጫ ስርአት መፈተሽ አለብን። የኢትዮጵያ ፓርላማ ሶስት ትልልቅ ችግሮች ያሉበት ፓርላማ ነዉ- አንደኛ-ፓርላማዉ የህግ አስፈጻሚዉ አካል አገልጋይ እንዲሆን ተደርጎ የተዋቀረ ፓርላማ ነዉ፥ ሁለተኛ- ዉክልናዉ ለክልል የሆነና የክልሎችን ጥቅም የሚያስጠብቅ አካል የሌለዉ ፓርላማ ነዉ፥ ሶስተኛ- ኢትዮጵያ ውስጥ ህግ የሚተረጉመዉ የፓርላማዉ አንድ ክፍል የሆነዉ “ፌዴሬሺን ምክር ቤት” የተባለዉ አካል ነዉ። ይህ ማለት ደግሞ የህግ አዉጭዉ አካል ህግ ያወጣልም ይተረጉማልም ወደሚል እጅግ በጣም አደገኛ ድምዳሜ ይወስደናል። እንዲህ አይነቱ የፓርላማ አወቃቀር በሶስቱ የመንግስት አካላት መካከል መኖር የሚገባዉ የስራ ነጻነትና ገለልተኝነት እንዳይኖር ያደርጋል፥ ደግሞም ሶስቱ የመንግስት አካላት በሁሉም ነገር እንዲስማሙ መንገድ በመክፈት አንዱ አካል ሌላዉን መቆጣጠር እንዳይችል ያደርጋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ “ህግ ተርጓሚ” የሚል ስም በተሰጠዉ ፌዴሬሺን ምክር ቤት ዉስጥ ህግ የተማሩ ሰዎች የሉም ማለት ይቻላል፥ ቢኖሩም በጣት የሚቆጠሩ ናቸዉ። ይህ ማለት ደግሞ ኢትዮጵያ ዉስጥ በተቋም ደረጃ ህግ የሚተረጉሙ ሰዎች ህግ የማያዉቁ ሰዎች ናቸዉ ማለት ነዉ። 

የሚቀጥለዉ ምርጫ በታሪካቸን ዉስጥ እጅግ በጣም ወሳኝ የሆነ ምርጫ ነዉ፥ ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግስት ይህ የዲሞክራሲ ጅምራችንን ብቻ ሳይሆን የወደፊት አቅጣጫችንን ጭምር የሚወስነዉ ምርጫ ነጻና ፍትሃዊ ሆኖ በሰላም ለመጠናቀቁ ዋስትና የሚሰጡ ነጻና ገለልተኛ አካላት መኖራቸዉ ማረጋገጥ አለበት (ሜዲያ፥ ፍትህ ተቋማት፥ ፖሊስና መከላከያ፥ ደህንነት፥ ክልል ልዩ ሃይል)። እስካፍንጫዉ የታጠቀ ልዩ የክልል ሃይልና በክልል የሚታዘዝ ሜዲያ ባለበት አገር ዉስጥ (በተለይ የዲሞክራሲ ልምድ በሌለዉና በዘር ተከፋፈለ  አገር ዉስጥ) ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ እጅግ በጣም ከባድ ነዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ የክልል ፖሊስና ልዩ ሃይል አባላት ታማኝነት ለፍትህና ለህግ የበላይነት ሳይሆን በሚኖሩበት ክልል ዉስጥ “የኛ” ለሚሉት ህዝብ ብቻ እነደሆነ በተደጋጋሚ በተግባር ታይቷል። ስለዚህ እነዚህ ጉዳዮች አዎንታዊ መሻሻል ሳይታይባቸዉ ምርጫ ዉስጥ መግባት የኋላ ኋላ እንዉጣ ብንልም መውጣት የማንችለዉ አዘቅት ዉስጥ ሊከትተን ይችላል። 

የጠ/ሚ አቢይ አህመድ መንግስት ስልጣን ላይ በቆየባቸዉ ባለፉት 20 ወራት ህገ መንግስቱ መሻሻል አለበት፥ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ፕሬዚደንታዊ ስርአት ነዉ የሚሉና የፌዴራል ክልሎች አወቃቀር እንደገና መታየት አለበት የሚሉ ትልልቅ አገራዊ ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ሲጠየቁ ተደምጠዋል። ፕሬዚደንታዊ ስርአት ይሻለናል ወይስ የፓርላማ ስርአት ወይስ የሁለቱ ቅይጥ የሆነዉ ግማሽ ፕሬዚደንታዊ ስርአት የሚለዉ ጥያቄና የፌዴራል አወቃቀራችን እንዴት ቢሆን ይሻላል የሚሉ ጥያቄዎች በምሁር ደረጃ መጠናት ያለባቸዉ ጥያቄዎች ናቸዉ፥ የኢትዮጵያ ህዝብም በእነዚህ የወደፊት ዕድሉን በሚወስኑ ትላልቅ ጥያቄዎች ላይ መወያየት መጀመር አለበት። የምንታገለዉ ለህዝብ መብት መከበር ነው የሚሉ ወገኖች ሁሉ በእርግጥም ለህዝብ የሚታገሉ ከሆነ ከላይ በተጠቀሱት ትላልቅ ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ላይ እጅ አጣጥፎ መቀበል ብቻ ሳይሆን እየሰጡ መቀበል እንዳለ አዉቀዉ ለድርድር መዘጋጀት አለባቸዉ። ሰጥቶ መቀበል ባለበት የድርድር ሂደት ዉስጥ አሸናፊ እንጂ ተሸናፊ ሊኖር አይችልምና የማንስማማባቸዉ ዉሳኔዎች ካሉ እነሱን ለህዝብ እንተዉና ህዝብ የወሰነዉን ዉሳኔ የመቀበል ድፍረቱና ችሎታው ግን ሁላችንም ሊኖረን ይገባል። ይህ የፖለቲካ ባለድርሻዎች ሊኖራቸዉ የሚገባ ህዝበ ዉሳኔን የማክበር ድፍረትና ችሎታ የጠ/ሚ አቢይ አህመድ መንግስትም ሊኖረዉ ይገባል። የተለያዩ የፖለቲካ ባለድርሻዎችን፥ ምሁራንን፥ የአገር ሽማግሌዎችንና የሃይማኖት መሪዎችን የማሰባሰብና በትልልቆቹ የኢትዮጵያ የወደፊት ጉዳዮች ላይ እንዲወስኑ ማድረግ የኢትዮጵያ ህዝብ ከሽግግሩ መንግስት የሚጠብቀዉ አቢይ ዉሳኔ ነዉ። ይህ ዉሳኔ ምርጫ የማካሄድ ዉሳኔ አይደለም! ይህ ዉሳኔ አገራችን ኢትዮጵያ በ1966 እና በ1983 ዓም አግኝታ ያጣቻቸዉን ዕድሎች አሁንም ለሶስተኛ ግዜ እንዳታጣ የማድረግ ዉሳኔ ነዉ። ይህ ዉሳኔ ኢትዮጵያን እንደ አገር የማስቀጠል ትልቅ ዉሳኔ ነዉ። ይህ ዉሳኔ የአገራችንን የፖለቲካ መድረክ ለሁለት የከፈሉትን የብሄር ፖለቲካ አራማጆችንና ኢትዮጵያዊ ብሄረተኞችን ወይም የማንነትና የዜግነት ፖለቲካ አራማጆችን ወደ ድርድር ጠረቤዛ በማምጣት ኢትዮጵያ የብሄር ማንነትን እና ኢትዮጵያዊ ማንነትን ወይም “ዜግነትን” እና “ማንነትን” አጣምራ መሄድ የምትችል አገር መሆኗን የሚያረጋግጥ ዉሳኔ ነዉ።   

ማስታወሻበዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here