spot_img
Saturday, July 13, 2024
Homeነፃ አስተያየትእራስን በራስ የማስተዳደር መብትና የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም

እራስን በራስ የማስተዳደር መብትና የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም

ኤፍሬም ማዴቦ
ህዳር 12 2012 ዓ ም

ከአለማችን ህዝብ 40 በመቶ የሚሆነዉ የሚኖረዉ ፌዴራል የመንግስት መዋቅርን በሚከተሉ አገሮች ዉስጥ ነዉ። ይህ ማለት ግን ፌዴራሊዝም ብዙ አገሮች ዉስጥ አለ ማለት አይደለም፥ እንዲያዉም 150 የአለም አገሮች አሃዳዊ የመንግስት መዋቅርን ነዉ የሚከተሉት። አሃዳዊ የመንግስት መዋቅር ዛሬ አዳዲሶቹ የአገራችን ጥራዝ ነጠቆች እንደሚነግሩን ፀረ ዲሞክራሲ ወይም ፀረ አንድነት አይደለም። ዲሞክራሲ  አሃዳዊ ወይም ፌዴራሊዝም ብሎ ነገር አያዉቅም። በሁለቱም ዉስጥ ያለ ምንም ችግር እራሱን መግለጽ ይችላል። ለምሳሌ ጃፓን፥ ፈረንሳይና እንግሊዝ አሃዳዊ የመንግስት መዋቅር ያለባቸዉ አገሮች ሲሆኑ አሜሪካ፥ ጀርመንንና ካናዳ ደግሞ ፌዴራል የመንግስት ስርአትን የሚከተሉ አገሮች ናችዉ። እነዚህ ስድስት አገሮች ጠንካራ አንድነት አላቸዉ፥ ሁሉም የአለማችን ሃብታም አገሮች ናቸዉ፥ ሁሉም የአለማችን የዲሞክራሲ ምልክቶች እና የG 8 ቡድን አባላት ናቸዉ።

አገሮች ፌዴራሊዝምን የመረጡበት የየራሳቸዉ የሆነ ምክንያት አላቸዉ። ፌዴራሊዝም አንዳንድ አገሮች ዉስጥ “ራስን በራስ የማስተዳደር” ጥያቄ መልስ ነዉ፥ አንዳንድ አገሮች ዉስጥ ትልቅ የጋራ ገበያና ጠንካራ ኢኮኖሚ የመፍጠር ፍላጎት ዉጤት ነዉ። አንዳንድ አገሮች ዉስጥ ደግሞ ፌዴራሊዝም በተለያዩ ቡድኖች መካከል ለሚነሱ ግጭቶችና አለመግባባቶች ዕልባት ለመስጠት የሚወሰን አገራዊ ዉሳኔ ዉጤት ነዉ። አንዴትም ተፈጠረ እንዴት ፌዴራሊዝም በፍጹም የማይለዩት  ሁለት ትልልቅ መታወቂያ ካርዶቹ አሉት- አንደኛዉ የጋራ አስተዳደር (Shared-rule) ሲሆን ሁለተኛዉ ራስን በራስ ማስተዳደር (Slef-rule) ናቸዉ። እነዚህ ሁለት እሴቶች በሌሉበት ቦታ ስለ ፌዴራሊዝም ማዉራት አይቻልም። አሃዳዊ የመንግስት መዋቅር ኖሯቸዉ ከዲሞክራሲ ጋር የማይተዋወቁ አገሮች አሉ፥ ፌዴራሊዝምና ድሞክራሲ ግን ተነጣጥለዉ መኖር አይችሉም። 

ኢትዮጵያ ፌዴራል የመንግስት መዋቅርን ከሚከተሉ 25 የአለማችን አገሮች ዉስጥ አንዷ ናት። ፌዴራሊዝም የተለያዩ ሉዓላዊ አገሮች አብረን እንኑር ብለዉ ተደራድረዉ የሚፈጥሩት ወይም የአንድ ሉዓላዊ አገር ልህቃን በአካባቢ እራሳችንን እናስተዳድር ብለዉ ተደራድረዉ የሚፈጥሩት ስርአት ነዉ። ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉ ፌዴራሊዝም የተፈጠረዉ ከሁለቱም መንገዶች በተለየ መንገድ ነዉ። በ1980ዎቹ አጋማሽ ኢትዮጵያ ዉስጥ ህገ መንግስት የጻፈዉ፥ የፌዴራል ስርአቱን የፈጠረዉና ፌዴራል ስርአቱን ለመፍጠር የተደራደሩትን አካላትንም በራሱ አምሳል የፈጠረዉ ህወሓት ነዉ። ፌዴራሊዝም ኢትዮጵያን ለመሳሰሉ ብዙ ብሄር ብሄረሰቦች፥ ሃይማኖት፥ ቋንቋና የባህል ስብስቦች ለሚገኝባቸዉ አገሮች ሁነኛ የመንግስት መዋቅር ነዉ። ሆኖም ፌዴራሊዝም የአንድ አገር ህዝብና የተለያዩ የፖለቲካ ባለድርሻዎች ተስማምተዉ የሚፈጥሩት ስርአት ነዉ እንጂ አንድ ቡድን በሌሎች ላይ የሚጭነዉ ጭነት መሆን የለበትም። የኢትዮጵያ ፌዲራሊዝም አንደኛ -ሲመሰረት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ ፌዴራሊዝም አይደለም፥ሁለተኛ- ዲሞክራሲ አልባ ፌዴራሊዝም ነዉ፥ሶስተኛ-በአካባቢም በማዕከልም የፖለቲካ ስልጣንን ጠቅልሎ የያዘና በፌዴራሊዝም የተለበደ አሃዳዊ ስርአት ነዉ። ለምሳሌ ህወሓት የበላይ በነበረበት ዘመን በተለይ አቶ መለስ ዜናዊ በህይወት በነበሩበት ግዜ የክልል ፕሬዚደንትና የደኢህዴን፥ የብአዴንና የኦህዴድ ሊ/መንበር ሆነዉ የሚሾሙት ሰዎች የግድ የህወሓትን እዉቅና ማግኘት ነበረባቸዉ። 

 የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ኢትዮጵያ ፌዴራል የመንግስት መዋቅርን የምትከተል አገር መሆኗን በግልጽ ይናገራል፥ ሆኖም ዛሬ በተግባር እንደሚታየዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ኮንፌዴሬሺን እንጂ ፌዴራሊዝም የሚባል ነገር ያለም አይመስልም። ክልሎች ከፌዴራል መንግስቱ ጋር የሚገዳደር፥ ታማኝነታቸዉ ለፍትህና ለህግ የበላይነት ሳይሆን የኛ ነዉ ለሚሉት ክልል ብቻ የሆነ የታጠቀ ልዩ ሃይልና ፖሊስ አላቸዉ። በክልሎችና በፌዴራሉ መንግስት መካከል ያለዉ ግኑኝነት የላላ ነዉ፥ አንዳንድ ክልሎች ጭራሽ ለፌዴራሉ መንግስት አይታዘዙም። የፌዴራሉ መንግስት በተለይ የመከላከያ ሰራዊታችን በክልሎች ዉስጥ እንደ ባዕድ አካል የሚታይበትና አንዳንዴም ይዉጣልን የሚባልበት ግዜ አለ። እንዲህ አይነቱ ህግ የማይገዛዉ ዕብጠት ሊፈጠር የቻለዉ ህገ መንግስቱ ሲጻፍና ፌዴራል ስርአቱ ሲዋቀር ትልቅ ትኩረት የተሰጠዉ ለብሄር ብሄረሰቦች መብት ብቻ እንጂ ይህ መብት በተግባር እንዴት እንደሚገለጽ ምንም የተባለ ነገር ባለመኖሩ ነው። ለምሳሌ ህገ መንግስቱ ብሄር ብሄረሰቦች እንዴት አብረዉ በሰላም ይኖራሉ፥ እያንዳንዱ ክልል አካባቢዉን ለማስተዳደር የሚያስችል የቆዳ ስፋት፥ በቂ ሀብትና የሰዉ ሃይል አለዉ ወይ፥ ክልሎችና የፌዴራል ስርአቱ የሚኖራቸዉ ግኑኝነት ምን መምሰል አለበት፥ አገሪቱ ዉስጥ ከፍተኛዉ ስልጣን የማነው? የፌዴራሉ መንግስት ወይስ የክልሎች፥ ኢትዮጵያ ዉስጥ የዜጎች መሰረታዊ መብት ሲጣስ ማነዉ የሚደርስላቸዉ፥ የፌዴራሉና የክልል ህገ መንግስት ሲጋጭ የትኛዉ ህገ መንግስት ነው ተፈጻሚ የሚሆነዉ ለሚሉና ለሌሎችም መሰረታዊ ጥያቄዎች ምንም ትኩረት አልሰጠም። ዛሬ አገራችንን የባህር ላይ ሞገድ እንደመታዉ መርከብ የሚያናዉጣት የእነዚሁ ትኩረት ሳይሰጣቸዉ የታለፉ ጥያቄዎች መዘዝ ነዉ።  

ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረዉ የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ለብሄር ብሄረሰቦች ከፍተኛ መብት ይሰጣል፥ ለምሳሌ አንቀጽ 8 ንዑስ አንቀጽ አንድ – የኢትዮጵያ ብሄሮች፥ ብሄረሰቦች፥ ህዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ናቸዉ ይላል። ኢትዮጵያ ዉስጥ ብዙዎቹ ክልሎች እስከነስያሜያቸዉ በአንድ ብሄር ዙሪያ የተገነቡ ስለሆነ በእነዚህ ክሎች ዉስጥ የሚኖር ከሌላ ክልል የመጣ ኢትዮጵያዊ እንደሁለተኛ ዜጋ ነው የሚታየዉ። ይህ ደሞ የዚህ ጽሁፍ ጸሃፊ የፈጠረዉ ተራ ወሬ አይደለም። በከተማ ደረጃ ድሬደዋ፥ ሐረርና አዋሳ ዉስጥ የየአካባቢዉ ተወላጅ ባልሆኑ ዜጎች ላይ የሚደርሰዉን በደል መመልከት ይበቃል። በአካባቢ ደረጃ ደግሞ ከሶማሌ ክልል፥ ከጉጂ፥ ከጉራ ፈርዳና ከሌሎችም አካባቢዎች ቦታዉ የእናንተ አይደለምና ዉጡ ተብለዉ የተፈናቀሉ ሰላማዊ ዜጎችን መመልከቱ ይበቃል። ኢትዮጵያ ዉስጥ የብሄር ፖለቲከኞች ስለኢትዮጵያ ፌዴራል ስርአት ሲያወሩ የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ከዲሞክራሲ ጋር አለመተዋወቁ ነዉ እንጂ ሌላ ችግር የለበትም ይላሉ። ሌሎቻችንም ብንሆን ትኩረት ሰጥተን የምናወራዉ ስለዲሞክራሲና እሱን ተከትሎ ስለሚመጣዉ ምርጫ ነዉ። ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ በየክልሉ የሚታየው ትልቅ ችግር ግን የፍትና የእኩልነት አለመኖር እና የህግ የበላይነት አለመከበር ነዉ።   

ኢትዮጵያ ዉስጥ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ሊካሄድ ይችላል፥ ግን ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ስለተካሄደ ብቻ ኢትዮጵያ ዉስጥ መልካም የዲሞክራሲ ጅምር አለ ሊባል አይችልም። ለዚህ ዋና ሁለት ምክንያቶች አሉ። አንደኛ- የኢትዮጵያ ፌዴራል ስርአት የራስን ጉዳይ በራስ የመወሰን መብት የሚሰጠዉ በክልል ደረጃ ብቻ ነዉ እንጂ በተለያያዩ የአስተዳደር እርከኖች ለሚኖረዉ ህዝብ “እራስን በራስ የማስተዳደር” መብት አይሰጥም። ሁለተኛ- ኢትዮጵያ ዉስጥ በህዝብ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ የአጭርና የረጂም ግዜ ዉሳኔዎችን የሚወስኑ የክልል ፕሬዚደንቶች እና የከተማ ከንቲባዎች ተሿሚዎች ናቸዉ እንጂ በቀጥታ በህዝብ አይመረጡም። ስለዚህ እነዚህ ሁለት መዋቅራዊ ችግሮች ሳይፈቱ ምርጫ ስለተካሄደ ብቻ የኢትዮጵያን ፌዴራላዊ ስርአት ዲሞክራሲያዊ ነዉ ማለት አይቻልም። ዲሞክራሲ ለህብረተሰብ ያበረከተዉ ትልቁ ገጸበረከት የፖለቲካ ሥልጣንን ከፈላጭ ቆራጭ አምባገነኖች መዳፍ ዉስጥ አዉጥቶ የህዝብ ንብረት እንዲሆኑ ማድረጉ ነዉ። ፌዴራሊዝም ለህብረተሰብ ያበረከተዉ ትልቅ ስጦታ ደግሞ ህዝብ የፓለቲካ ሥልጣንን በሚኖርበት አካባቢና በማዕከል እኩል እንዲጋራዉ ማድረጉ ነዉ። 

ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚገኙ የብሄር ፖለቲካ አራማጆች ብረት አንስተን የታገልነዉ የህዝብን የ”ራስን ጉዳይ በራስ የመወሰን” መብት (Self-determination) ለማስከበር ነዉ ይላሉ። እነሱ ህዝብ የሚሉት ግን ብሄር ብሄረሰብ ብለዉ የሚጠሩትን የህብረተሰብ ክፍል ብቻ ነዉ። ከዚህ ዉጭ ያለዉ ከተለያዩ ብሄሮች የሚወለድና እራሱን ከአንድ ብሄር የማይቆጥር በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዜጋና ከራሱ ክልል ወጥቶ ሌላ ክልል ዉስጥ የሚኖር ህዝብ የራሱን ዕድል በራሱ መወሰን ቀርቶ የኔ ነዉ የሚለዉን ተወካዩን መምረጥም አይችልም። ለምሳሌ ኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ዉስጥ ቁጥሩ እጅግ በጣም ብዙ የሆነ እራሱን አማራ ብሎ የሚጠራ ህዝብ በገጠርም በከተማም ይኖራል፥ ሆኖም ይህ ህዝብ የፌዴራል መዋቅሩና የምርጫ ስርአቱ በጣምራ በፈጠሩበት ችግር የተነሳ ቁጥሩን በሚመጥን መልክ ጨፌ ኦሮሚያ ዉስጥም ሆነ በአገራዊዉ ፓርላማ ዉስጥ ጥቅሜንና ፍላጎቴን ይወክሉልኛል የሚላቸዉን የራሱን ተወካዮች መምረጥ አይችልም። 

የ”ራስን ጉዳይ በራስ መወሰን” የሚለዉ መርህ አንድ ዉሳኔ የሚወስን አካል ዉሳኔዉን እንዴት መወሰን እንዳለበት ወይም የዉሳኔዉ ዉጤት ምን መሆን እንዳለበት ምንም የሚለዉ ነገር የለም፥ ደግሞም የ”ራስን ጉዳይ በራስ የመወሰን” መብት ለህዝብ የተሰጠ መብት መሆኑን ይናገራል እንጂ “ህዝብ” ማለት እንዲህ ማለት ነዉ ብሎ ትንታኔ ዉስጥ አይገባም። አንድ በግልጽ የሚናገዉ ነገር ግን አለ፥ እሱም የ”ራስን ጉዳይ በራስ መወሰን” ማለት ዉሳኔዉን የሚወስነዉ አካል ግለሰብ ይሁን ቤተሰብ ወይም ማህበረሰብ የራሱን ጉዳይ በተመለከተ ማንም ጣልቃ ሳይገባበት እራሱ ይወስናል ማለት ነዉ- ይህ ማለት ደግሞ የራስን ዕድል በራስ መወሰን የሚባለዉ መብት የአገራችን የብሄር ፖለቲካ አቀንቃኞች እንደሚነግሩን ለብሄሮች ብቻ የተሰጠ መብት አይደለም ማለት ነዉ። ግለሰቦችም የራሳቸዉን ጉዳይ በራሳቸዉ የመወሰን መብት አላቸዉ።  ለምሳሌ አንድ ግለሰብ የት መኖር እንደሚገባዉ፥ ምን አይነት ሃይማኖት መከተል እንደሚገባዉ፥ ምን አይነት ትምህርት መማር እንደሚገባዉ፥ ምን መስራትና የት መስራት እንደሚገባዉ፥ መሪዉ ማን መሆን እንደሚገባዉና በምርጫ ወቅት ማንን መምረጥ እንደሚገባዉ የሚወስነዉ እሱ እራሱ ነዉ ማለት ነዉ። ታዲያ ኢትዮጵያ ዉስጥ በዞን፥ በከተማዎችና በወረዳዎች ዉስጥ የሚኖረዉ ህዝብ ለምንድነዉ የራሱን ጉዳይ በራሱ እንዲወስን የማይፈቀድለት? መቼ ነዉ በከተማዎች የሚኖረዉ ህዝብ ልጆቹ በምን ቋንቋ መማር እንዳለባቸዉ እሱ እራሱ የሚወስነዉ? መቼ ነዉ በአዲስ አበባና በሌሎቹም የኢትዮጵያ ከተማዎች የሚኖረዉ ህዝብ ከንቲባዉንና የምክር ቤት አባላትን የሚመርጠዉ? ለምንድነዉ አዳማን፥ አዋሳንና ቢሾፍቱን በመሳሰሉ ህብረብሄር የአገራችን ከተማዎች ዉስጥ ያለዉ የፖሊስ ሃይል የሚያገለግለዉን ህዝብ የማይመስለዉ? 

ኢትዮጵያ ዉስጥ ሉዓላዊነት፥ ማንነትና የመሬት ባለቤትነት የተቆራኙ ነገሮች ስለሆኑ ብሄር ብሄረሰቦች ከተማን በተለይ ህብረብሄር ከተማዎችን ማስተዳደር እንደማይችሉ አዋሳ ዉስጥ በተግባር ታይቷል።አዋሳን የመሰለች የአገር ዉስጥና የአለም አቀፍ ጎብኚዎች ማግኔት የነበረች ዉብ ከተማ ዛሬ ዉበቷን ጥላቻ ጋርዶት ማግኔትነቷን ክፋትና ጭካኔ አድብዝዞት አዋሳ ህይወት የሌለባት ከተማ መስላለች። ህብረ ብሄር በሆኑ የተለያዩ የአገራችን ከተማዎች ዉስጥ በግልጽ እንደሚታየዉ ከተማዎችን የሚያስተዳድሩ ሰዎችና በከተማዎች ዉስጥ ያለዉ የፖሊስ ሀይል ከከተማዉ ነዋሪ ህዝብ ጋር አለመመሳሰላቸዉ ብቻ ሳይሆን ሆድና ጀርባ ናቸዉ። በከተማዎች ዉስጥ የሚኖረዉ ህዝብ ከተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች የመጣ ህዝብ ነዉ።በክልል እየተሾሙ ከተማዎችን የሚያስተዳድሩ ሰዎች ግን የክልሉ ባለቤት ነኝ የሚለዉ ብሄር አባላት ናቸዉ። ለምሳሌ ከ1997 ዓም ጀምሮ የአዋሳ ከንቲባና የከተማዋ ምክር ቤት አባላት በአዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ያልተመረጡ የሲዳማ ብሄር ተወላጆች ናቸዉ። ይህ ከዲሞክራሲ ጋር የማይተዋወቅና የከተማ ነዋሪዎችን የዜግነት መብት የገፈፈ ወገናዊ አሰራር መቆም አለበት። ኢትዮጵያ ዉስጥ በወረዳ ደረጃ ካለዉ የአስተዳደር እርከን ጀምሮ እስከ ክልል ድረስ ባሉ የአስተዳደር እርከኖች ዉስጥ የሚኖረዉ ህዝብ መመራት ያለበት በክልል ደረጃ በሚሾሙ ሰዎች ሳይሆን እራሱ በመረጣቸዉ መሪዎች ብቻ መሆን አለበት።

አዲስ አበባን ጨምሮ አንዳንድ ትላልቅ ህብረብሄር ከተማዎችን “የኛ ናቸዉና” ክልላችን ዉስጥ መካተት አለባቸዉ የሚልና ህዝብን ለግጭት የሚጋብዝ ኢ-ምክንያታዊ ድምፅ ከቅርብ ግዜ ወዲህ እየበረከተ መጥቷል።ለምንድነዉ ብሄር ብሄረሰቦች ህብረብሄር ህዝብ የሚኖርባችዉን ከተማዎች ካላስተዳደርን የሚሉት? ለምንድነዉ በከተማዎች የሚኖረዉ ህዝብ ከሱ ጋር በማይኖሩና በማያዉቃቸዉ ተሿሚዎች የሚመራዉ? ለምንድነዉ ብሄር ብሄረሰቦች እነሱ በትግላችን አገኘን የሚሉትን እራስን በራስ የማስተዳደር መብት ከከተማዉ ህዝብ ላይ መቀማት የሚፈልጉት? ላለፉት አርባና ሃምሳ አመታት ጫካ ገብተን የታገልነዉ ህዝብ የራሱን ጉዳይ በራሱ የመወሰን መብቱ እንዲከበር ነዉ ብለዉ አፋቸዉን ሞልተዉ የሚነገሩን የብሄር ልህቃን ለምንድነዉ የአዲስ አበባ፥የመቀሌ፡ የድሬደዋ፥ የጂማ፥ የሐረር፥ የባህርዳር፥የደሴ፥ የአዳማ፥ የአዋሳ ወዘተ ህዝብ የራሱን ጉዳይ በራሱ መወሰን እንድችል የማይተዉት ወይም ዕድል የማይሰጡት? ተምቤንን፥አንደርታንና ዕሮብን የሚያስተዳድሩ አስተዳዳሪዎችን ለምንድነዉ ህወሓት ብቻ የሚሾመዉ? ለምንድነዉ የእነዚሁ አካባቢ ህዝብ የራሱን መሪዎች ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እየመረጠ እራሱ ላይ መሾም እንድችል ዕድል የማይሰጠዉ? ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ ቆርጫለሁ እያለ የሚነግረን የኢትዮጵያ መንግስት  መቼ ነዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ በዞን፥ በወረዳና በየከተማዉ የሚኖረዉ ህዝብ መሪዎቹን እንዲመርጥ መንገድ የሚያመቻቸዉ? በሚቀጥለዉ ምርጫ ይህ የማይሆን ከሆነ የትኛዉ ምርጫ ነዉ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ይሆናል እየተባለ የሚነገረን? ለመሆኑ ሲጀመር መሪዎቹን መምረጥ የማይችል የዞን፥ የከተማና የወረዳ ህዝብ ስለነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ማዉራትስ ይችላል? 

ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉን ፌዴራል ስርአት ከዉጭ ሆኖ የሚመለከት ሰዉ የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም እንደማንኛዉም አገር ፌዴራሊዝም በየአካባቢዉ ለሚኖር ህዝብ እራስን በራስ የማስተዳደር መብት የሚሰጥ ይመስለዋል። ጉዳዩ ግን ወዲህ ነዉ። የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ለህዝብ የሚሰጠዉ “እራስን በራስ የማስተዳደር” መብት የሚጀምረዉም የሚያበቃዉም ክልል ላይ ነዉ። ከክልል በኋላ በዞን፥ በከተማና በወረዳ ደረጃ ያለዉ አሰራር በሙሉ አሃዳዊ አሰራር ነዉ። ይህ ማለት ደግሞ ኢትዮጵያ ዉስጥ በዞን፥ በከተማና በወረዳ ደረጃ የሚኖረዉን ህዝብ እላዩ ላይ ቁጭ ብለዉ አድርግ አታድርግ የሚሉት በቀዳማዊ ኃ/ሥላሤና በደርግ ዘመን እንደሚደረገዉ ከማዕከል እየተሾሙ የሚመጡ ሹሞች ናቸዉ። ይህ ደግሞ ከዋና ዋናዎቹ የፌዴራሊዝም መሰረተ ሃሳቦች ጋር የሚጻረር አሰራር ነዉ። ለምሳሌ የአዳማና የሐረር ከተማ ህዝብ፥ የሃዲያና የወላይታ ዞን ህዝብ፥ ወይም በየትኛዉም የአገራችን አካባቢ በወረዳዎች የሚኖረዉ ህዝብ ክልል እየሾመ በሚልካቸዉ ሹሞች ነዉ የሚመራዉ እንጂ ይመሩኛል ብሎ የሚተማመንባቸዉን የራሱን መሪዎች የመምረጥ ዕድል የለዉም። ይህ የሚነግረን ኢትዮጵያ ዉስጥ ”የራስን ጉዳይ በራስ መወሰን” የሚባለዉ መሰራታዊ የሰዉ ልጆች መብት በህገ መንግስት ደረጃ ይቀመጥ እንጂ ይህንን መብት በህገ መንግስቱ ዉስጥ ያስቀመጡ ሰዎችም ሆኑ ዛሬ መብቱን እየጠየቁ ያሉ ሰዎች ከራሳቸዉ የግል ጥቅምና ፍላጎት ዉጭ ለዜጎች መብትና ነጻነት ምንም ግድ እንደሌላቸዉ ነዉ። ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ እራሳቸዉን የፌዴራሊዝም አባት አድርገዉ የሾሙና ፌዴራል ስርአቱ መሻሻል አለበት የሚሉ ሃይሎችን “አሃዳዉያን” እያሉ የሚጠሩት እንዲህ አይነቶቹ ህዝብን የትም ሆንክ የት የምናስተዳድርህ እኛ ብቻ ነን የሚሉና በፌዴራሊዝም ካባ ህዝብን ጨፍልቀዉ የሚገገዙ “ፌዝ-ራሊስቶች” ናቸዉ። 

የኢትዮጵያ ህዝብ የክልልና የፌዴራል ፓርላማ ተወካዮቹን ስለመረጠ ብቻ እራሱን በራሱ ያስተዳድራል ሊባል አይቻልም። አንድ ህዝብ እራሱን በራሱ ያስተዳድራል የሚባለዉ በእያንዳንዱ የአስተዳደር እርከን ደረጃ የሚኖር ህዝብ መሪዎቹን ያለምንም ተፅዕኖ እሱ እራሱ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መምረጥ ሲችል ብቻ ነዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉ ፌዴራል ስርአት ይህንን አይፈቅድም። አገራችን ኢትዮጵያ ዉስጥ የዲሞክራሲ መሰረት እየጣልን ነዉ የምንል ከሆነ ይህ መሰረት መጣል ያለበት ከወረዳ ጀምሮ ነዉና ወረዳዎችና ዞኖች መሪዎቻቸዉን፥ከተማዎች የምክር ቤት አባላቶቻቸዉንና ከንቲባቸዉን ክልሎች ደግሞ ፕሬዚደንቶቻቸዉን በቀጥታ በሚሰጥ ድምፅ  መምረጥ መቻል አለባቸዉ። እርግጠኛ ነኝ ከግማሽ ምዕተ አመት በላይ ለህዝብ ታገልኩ የሚል የፖለቲካ ልህቅ የህዝብን ምርጫ የሚፈራ አይመስለኝም! ደግሞም በንጉሱና በወታደራዊዉ በደርግ ዘመን ያልወደድናቸዉን የማዕከል ተሿሚዎች ዛሬ የምንወድበት ምንም ምክንያት የለም!!!

ኢትዮጵያ ዉስጥ በዞን፥ በከተማና በወረዳ ደረጃ የሚኖረዉ ዜጋ የዜግነት መብቱ ተከብሯል ማለት የሚቻለዉ ይህ ዜጋ በሚኖርበት አካባቢ የራሱን ጉዳይ እራሱ መወሰን ሲችል ብቻ ነዉ።በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ዉስጥ እራሳቸዉን በአንድ ብሄር መነጽር የማይመለከቱና ከክልላቸዉ ወጥተዉ በሌሎች ክልሎች ዉስጥ የሚኖሩ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ሰብዓዊ፥ ዲሞክራሲያዊና የሲቪክ መብት ሊከበር የሚችለዉ እነዚህ ዜጎች በሚኖሩበት አካባቢ ሁሉ በመረጧቸዉ መሪዎች ሲመሩ ነዉ። ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግስት ከሚቀጥለዉ ምርጫ በፊት በተለያዩ የአስተዳደር እርከኖች የሚኖረዉ ኢትዮጵያዊ ሁሉ የራሱን ጉዳይ በራሱ መወሰን የሚችልበትን መንገድ ማመቻቸት አለበት። የ2012ቱ ምርጫ በተያዘለት የግዜ ሰሌዳ ካልተካሄደ አገር ይበጠበጣል እያሉ የሚያስፈራሩን የፖለቲካ ልህቃኖቻችንም የኢትዮጵያ ህዝብ “እራስን በራስ የማስተዳደር” መብት በክልል ደረጃ ብቻ በተገደበበት አገር ዉስጥ ምርጫ ማካሄድ ማለት በፌዴራሊዝምና በዲሞክራሲ መቀለድ ወይም ሁለቱንም አለማወቅ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል። ምርጫ ከመካሄዱ በፊት የዜጎች በየእርከኑ እራስን በራስ የማስተዳደር መብት መከበሩ፥ ነጻና ገለልተኛ የምርጫ ሂደት መኖሩና ምርጫዉ ነጻና ፍትሃዊ መሆኑን የሚያረጋግጡ ተቋማት መኖራቸዉ መረጋገጥ አለበት።

ማስታወሻበዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here