spot_img
Monday, June 24, 2024
Homeነፃ አስተያየትየሚገነፍል ድስት የሚያበላሸዉ እራሱን ነዉ! (ኤፍሬም ማዴቦ)

የሚገነፍል ድስት የሚያበላሸዉ እራሱን ነዉ! (ኤፍሬም ማዴቦ)

 ኤፍሬም ማዴቦ
(emadebo@gmail.com)

አንድ አሜሪካ እያለሁ ብሎገር ከነበርኩበት ግዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ ዉስጥ ሆኖ በኢሜል የሚያገኘኝ ሰዉ በቅርቡ ደዉሎልኝ ሼራተን አዲስ ቀጠረኝ።  ሼራተን አይመቸኝም አልኩትና አምስት ኪሎ ሉሲ ምግብ ቤት ተገናኘን። እሱ ስለሚያዉቀኝ የተቀመጥኩበት ቦታ መጣና ሰላምታ ተለዋዉጠን ማዉራት ጀመርን። ብዙ ካወራን በኋላ ቀና ብሎ አየኝና . . . . . . አቶ ኤፍሬም እኛ ኢትዮጵያዊያን በሃሳብ ባንግባባም በሚያግባቡን ነገሮች ላይ ተከባብረን አብረን መስራት አንችልም እንዴ ሲል ጠየቀኝ።  እንችላለን  . . . . . . እስካሁን ስንችል ግን አላየሁም አልኩት። ከምሳ በኋላ ቡና እየጠጣን ጨዋታችንን ቀጠልን። ለምን ብሎገርነቴን እንደተዉኩ፥ ግንቦት 7 ዉስጥ እንዴት እንደገባሁና ደሞም እንዴትና ለምን ወደ ኤርትራ እንዴሄድኩና ስለ ኤርትራ ቆይታዬ ብዙ ጠየቀኝ። ማወቅ የሚገባዉን አንድ በአንድ ነገርኩት። አሁንም ቀና ብሎ አየኝና አቶ ኤፍሬም መቼ ነዉ ኢትዮጵያዊያን ተግባብተን የምንሰራዉ ብሎ ጠየቀኝ። አንድ ቀን ብዬ መለስኩለት።  እንደገና መገናኘት አለብን መቼ ልምጣ አለኝ። ደዉል አልኩትና ተለያየን። 

አለመግባባት፥ አብሮ አለመስራት፥ አለመተማመንና መጠፋፋት በነገሰበት፥ በወዳጅነትና በጠላትነት መካከል ያለዉ ልዩነት እጅግ በጣም ስስ በሆነበትና የዛሬዉ የቅርብ ወዳጅና አጋር ነገ እንደ ትልቅ ጠላት ሊታይ በሚችልበት ማህበረሰብ ዉስጥ ስለሆነ እኔና ፖለቲካ የተዋወቅነዉ ከዚህ ማህበረሰብ ተነጥዬ ፖለቲካን ከዚህ በተለየ መልኩ በሚያይ ማህበረሰብ ዉስጥ መኖር እስከጀመርኩበት ግዜ ድረስ ለኔም ፖለቲካ ማለት ማህበረሰብ በጠላትነትና ወዳጅነት ተከፋፍሎ የሚጠፋፋበት የአጥፊና ጠፊ ድራማ ነበር የሚመስለኝ።

ከልጅነት ወደ ወጣትነት የተሸጋገርኩት “ወዛደሩ ያሸንፋል” ፥ “ላብ አደሩ ያቸንፋል” ፥  “የዲሞክራሲ መብት ያለገደብ አሁኑኑ”፥ “የዲሞክራሲ መብት ለጭቁኑ አሁኑኑ” ፥“ጊዜያዊ ህዝባዊ መንግሥት ይቋቋም” ፥  “የነቃ የተደራጀና የታጠቀ ህዝብ ያሸንፋል”  . . . . . . የሚሉ መፈክሮች የአገራችንን አየር በሞሉበት ወቅት ነበር። እነዚህ መፈክሮች የመኢሶንና የኢሕአፓ መፈክሮች ነበሩ። መኢሶንና ኢሕአፓ ዉስጥ የነበሩ ታጋዮች ሁሉም ቀደማዊ ኃ/ሥላሤ ዩኒቨርሲቲ ዉስጥ ጎን ለጎን ቁጭ ብለዉ  የተማሩና መሬት ላራሹን አብረዉ የዘመሩ ወጣቶች ነበሩ። መኢሶንም ኢህአፓም ማርክሲስቶች ነበሩ፥ ሁለቱም ኢትዮጵያ ዉስጥ ነጻነት፥ዲሞክራሲና እኩልነት እንዲኖር የሚፈልጉና በወዝ/ላብ አደሩ አምባገነንነት የሚያምኑ ነበሩ። እንግዲህ ይታያችሁ ይህ አንድ ግቢ ዉስጥ የተማረ፥ የፊዉዳሉን ስርአት አብሮ የታገለ፥ አንድ አይነት ርዕዮአተ አለም የሚከተልና ለተመሳሳይ የፖለቲካ ስርአት መመስረት የታገለ ትዉልድ ነዉ  በ”ሸ” እና በ”ቸ” በ”ወዛደር” እና በ”ላብ አደር” ተለያይቶ እርስ በርስ የተላለቀዉ። ይህ እንኳን መገዳደል ሃይለቃል መለዋወጥ የሌለበት ትዉልድ ነዉ ጎራ ለይቶ ቀይ ሽብርን ለመሰለ ፍጹም አረመኔያዊ ወንጀልና የርስበርስ ዕልቂት ኢትዮጵያን የዳረጋት። ጥምረት ፈጥረዉ በጋራ ቢታገሉ ኖሮ ያለምንም ጥርጥር የደርግን ዕድሜ ማሳጠር ይችሉ የነበሩት መኢሶንና ኢሕአፓ አንደኛዉ ከደርግ ጋር ሆኖ ሌላዉን ለማጥፋት በመሞከሩ ሁለቱም ጠፍተዉ ደርግን ግዜያዊ አሸናፊ ኢትዮጵያን አሁንም ድረስ ተሸናፊ አድርገዋታል። የዛሬዉ ትዉልድ ከዚህ ልዩነት ሳይኖረዉ ተለያይቶ እርስ በርሱ ከተላለቀዉ ትዉልድ ምን የተማረዉ ነገር አለ? መለያየት፥ መጠላለፍ፥ አብሮ አለመስራት፥ አለመስማማት፥የቃላት ጦርነት፥ ጽንፈኝነት፥ በሃሳብ ልዕልና አለማመንና ከስህተት አለመማር ዛሬም ድረስ አብሮን ያለ በሽታ ነዉና የዛሬዉ ትዉልድ ካለፈዉ ትዉልድ ምን ተምሯል ለሚለዉ ጥያቄ መልሱ. . . . . ምንም ነዉ።

ባለፉት 18 ወራት የኢትዮጵያ ህዝብ መልካም ዘመን እየመጣ ነዉ የሚያሰኝ ተስፋ አይቷል፥ በአንጻሩ አንገት የሚያስደፉ የጭካኔ ወንጀሎችንም አይቷል፥ አሁንም እያየ ነዉ። ለምሳሌ የአዋሳዉ እልቂት፥ የሻሸመኔዉ ዘቅዝቆ መስቀል፥የቡራዩ ጭፍጨፋ፥ የጌዲኦ መፈናቀል፥ የቤኒሻንጉል ግዲያ፥ በከፍተኛ ትምህርት ተቋሞች ዉስጥ የሚታየዉ የርስ በርስ ግዲያ እና በቅርቡ የ88 ንጹሃን ዜጎችን ህይወት የቀጠፈዉ በአንድ ግለሰብ ዙሪያ ያጠነጠነዉ የፖለቲካ ሸፍጥ ዋና ዋናዎቹ ናችዉ። እነዚህን ዘግናኝ እልቂቶች የተመለከተዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ወደፊት መመልከቱን አቁሞ ፀሎቱና ምህላዉ የባሰ አታምጣ ብቻ ሆኗል። ፈጣሪ ይስማዉ አይስማዉ አላዉቅም። ምድር ላይ ግን የሚሰማዉ ያለም አይመስልም! አልሰማ ያሉት ደግሞ መሪዎቹ ብቻ አይደሉም፥ እንዲያዉም ከመሪዎቹ ይልቅ ጆሮ ዳባ ልበስ ያሉት በስሙ እንታገላለን የሚሉት ፖለቲከኞች፥ ሰብዓዊ መብት ታጋዮችና አክቲቪስት ልጆቹ ናቸዉ።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንኳን ጎራ ለይተን ክብሪት ጭረንበት እንዲሁም አልተቻለም። አፎይ ስንል “ኡኡ” ያሰኘናል፥ እሰይ ብለን ቀና ስንል እግዚኦ ያሰኘናል። ጧትና ማታ ይለዋወጣል፥ ጠራ ስንል ይደፈርሳል፥ሻል አለዉ ስንል ያገረሽበታል። ባለፈዉ ሳምንት አርብ ወደ ቅዳሜ አጥቢያ አዲስ አበባ ላይ የፈነዳዉ የፖለቲካ ቦምብ ግን ሁላችንንም  “ድንቄም መደመር” ያሰኘ ምድር አንቀጥቅጥ ቦምብ ነዉ። ይህ ባላሰብነዉ ግዜና ፍጹም ያልጠበቅነዉ ሰዉ ያፈነዳዉ ቦምብ ባላገር-ሩቅ አገር፥ መሃል አገር-ዳር አገር፥ ዉጭ አገር-ዉስጥ አገር ሳይለይ ደገኛዉን ጋቢ አስለብሶ ጉባኤ ቆለኛዉን ሽርጥ አስገልድሞ ሱባኤ ያሰቀመጠ ክፉ ቦምብ ነዉ። ይህ ቦምብ አንዴ ፈንድቶ የሚቆም ቦምብ አይደለም። መዘዙ ብዙ ነዉ። ይህ ተዋሃድን ሲሉን ዘይትና ዉሃ የሆኑበት፥ በቃ አለቀ ሲባል ገና መቼ የተባለበትና “ሞትም ቢሆን አይለየንም” ያሉን በቁም የተለያዩበት የአዲስ አበባዉ ቦምብ ፍንዳታ ፍንጥርጣሪዉ ቶሎ አይጠፋም። እኚህ ከነአጅሬ ቦምብ ይታደጉናል ያልናቸዉ ሰዉ ያፈነዱት ቦምብ የፈጠረዉ ጫጫታ ቶሎ ጸጥ ካለ አገራችን ኢትዮጵያ ካሁን በፊት አይታዉ የማታዉቀዉን አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ትጀምራለች ደሞም ዘመኑ የብልጽግና ነዉና ትበለጽጋለች። አለዚያም ነገሩ ቀን እስኪያልፍ ያለፋል ነዉና ሌላ ቦምብ ይፈነዳል . . . . ሌላ. . . . . ሌላ . . . . . ሌላ!

“ይህም ትዉልድ ፍም እሳት ነዉ” ተብሎ የተዘፈነለት የዛሬዉ ትዉልድ ይህንን ዛሬ ነገ እያለ የሚፈነዳ ቦምብ አክሽፎ  በኢትዮጵያ የመብትና የነጻነት ትግል ታሪክ ዉስጥ የራሱን አዲስ ምዕራፍ መጻፍ አለበት። የ1950ዎቹ፥ 60ዎቹ እና የ1970ዎቹ ትዉልድ ለእናት አገሩ ኢትዮጵያ ኖሮላት ሞቶላታል፥ እግሩ መንገዱን ብዙ ስህተትም ሰርቷል። ይህ ትዉልድ ወደኋላ ሄዶ ስህተቱን ማረም አይችልም። የዛሬዉ ትዉልድ ግን ከአባቶቹ ስህተት መማር ብቻ ሳይሆን “ያ ትዉልድ” ክፉኛ የተጠናወተዉን ስህተትን ከትዉልድ ትዉልድ የማስተላለፍ አባዜ እምቢ በቃኝ ማለት አለበት። ተለያይቶ ትግል በቃ ማለት አለበት። ይህ ትዉልድ-  እኔ ብቻ ማለት በቃ፥ መጠላለፍ በቃ፥ መሰዳደብ በቃ፥ መገዳደል በቃ ማለት አለበት። ከሁሉም በላይ ደሞ ይህ ትዉልድ እዚም እዛም አገር ዉስጥም ዉጭ አገርም የሚጭረዉን የፖለቲካ እሳት ማቆም አለበት። የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንኳን እሳት ጭረንበት በራሱ እየነደደ አገር የሚያጠፋ ፖለቲካ ነዉ። የዚህ ጽሁፍ ትልቁ መልዕክትም እሳት ባነደድን ቁጥር እሳቱ እኛንም ማቃጠሉ አይቀርም፡ ወይም የሚገነፍል ድስት የሚያበላሸዉ እራሱን ነዉ የሚል ነዉ።

ኢትዮጵያ እንቆቅልሽ ተብሎ “ምናዉቅልሽ” ሲባል መልስ የሌላት  አገር ሆናለች። አዎ የብዙ እንቆቅልሾች ግን ለአንዱም መልስ የሌላት አገር . . . .  አራት ኪሎ አዲስ ፓርቲ እንኳን ደስ አላችሁ፥ቦሌ ጃፓን ኤምባሲ አርቲ ቡርቲ አሃዳዊያን መጡላችሁ። ሜሪላንድ- ቨርጂኒያ ዕብደት፥ አራት ኪሎ ትልቅ ክህደት። መቀሌ ላይ እነ አቦይ ስብሰባ፥ አዋሳ ላይ አዲስ ክልል ጭብጨባ። ሚኒያፖሊስ እንግዳ መጣ “አን ሃዱፉ”፥ ሎስ አንጀልስ አትምጡብን ሂዱ ጥፉ። አዲስ አበባ ወጥ ጣፍጦላት ጎንበስ ቀና፥ ፊንፍኔ ንክች ወጡን የቅመሙ ስም ሚኒልክ ነዉና። መቀሌ ተስፋ ቆርጣ “ጠፍኢናዶ” ፥ ፌዴራሊስቶች ለስብሰባ “ክንመጽእዶ” ዶ. . . ዶ. . . ዶ! ባህር ዳር ልጆቿ ሞተዉ ሃዘን ቁጭ ብላለች፥ ደቡብ እዚህም እዚያም ክልል . . . .ክልል . . . .ክልል  ልሁን አለች። አክቲቪስቱ ገንዘቤን፥ ፖለቲከኛዉ ዉሎ አበሌን፥ ቄሱ መስቀሌን፥ መሪዉ ወንበሬን፥ ጸሃፊዉ ብዕሬን፥ ህዝብ ብቻ አገሬን. . .  አገሬን . . . . አገሬን።  

እኛ ኢትዮጵያዊያን ከጽንፈኝነትና ጎራ ለይቶ ከመተላለቅ ፖለቲካ እስካልተላቀቅን ድረስ አዲስ ፓርቲ ብንመሰርት ባንመሰርት፥ ምርጫ ብናካሄድ ባናካሄድ፥ ባላደራ ብንል በላተራ፥ ካራማራ ብንል ኦሮአማራ፥ ህዳሴ ብንል ዉዳሴ፥ መደመር ብንል መቀነስ፥ የሰላም ጉባኤ ብንል የፀሎት ሱባኤ መቀየር የምንችለዉ ምንም ነገር የለም። ኢትዮጵያን የሁላችንም አገር ማድረግ የምንችለዉ ተቀራርበን በመነጋገር ብቻ ነዉ! በዱሮዉ የኢትዮጵያ ታሪክ ላንስማማ እንችላለን። የወደፊቷ ኢትዮጵያ ምን መምሰል አለባት የሚለዉ ጥያቄ ሲመለስ ግን መልሱ ላይ ሁላችንም አሻራችንን ማሳራፍ እንችላለን። አዎ በአስተሳሰብ ብንለያይም ቁጭ ብለን መነጋገር ከቻልን የወደፊቷን ኢትዮጵያ ሁሉንም ልጆቿን እኩል የምታቅፍ አገር ማድረግ እንችላለን።

የአገር ጉዳይ ነዉና አንድ ነገር ግን ልብ ልንል ይገባል። የአገራችን የፖለቲካ መድረክ የብሄር ፖለቲካን በሚያቀነቅኑና የዜግነት ፖለቲካን በሚያቀነቅኑ ሁለት ተቃራኒ ሃይሎች የተከፈለ ነዉ። ዛሬ በግልፅ እንደምንመለከተዉ የብሄር ፖለቲካ አቀንቃኞች የወደፊቷን ኢትዮጵያ ዕድል በነሱ የፖለቲካ  ቅኝት ብቻ ሊቃኙ ይፈልጋሉ፥ ይህንን ለማድረግ ደሞ ከፍተኛ ዝግጅት አድርገዋል አሁንም እያደረጉ ነዉ። እነሱ የሚቀጥለዉን ምርጫ ዉጤት እያሰሉ ማን ያሸንፋል፥ የትኛዉ ፓርቲ የፓርላማ መቀመጫ ያገኛል፥ማን መንግስት ይመስርታል እና ማን ጥምር መንግስት ዉስጥ ይገባሉ የሚለዉ ጥያቄ መልስ ወደነሱ የሚያደላበትን መንገድ ስትራቴጂ ነድፈዉ እየተንቀሳቀሱ ነዉ። በአንዳንድ ነገሮች ላይ ባይስማሙም እነሱ ይህንን የሚያደርጉት ከያሉበት ተጠራርተዉና ቁጭ ብለዉ እየመከሩ ነዉ። እኛ በብዙ ነገሮች የምንመሳሰል በዜግነት ፖለቲካ የምናምን ሃይሎች ግን በየቀኑ እንደአሜባ እንከፋፈላለን፥ ይህ መከፋፈል ደሞ ዛሬም አገራችን ጭንቋ በዝቶ ድረሱልኝ በምትልበት ግዜም ቢሆን እየባሰበት ሄደ እንጂ አልቆመም። ትናንት የሚበጀን አንድነት ብቻ ነዉ እያሉ የሰበኩ ሃይሎች ዛሬ መከፋፈልን ይሰብካሉ። ትናንት የአገራችን አንድነት ምልክት የነበሩ ሰዎች ዛሬ የጽንፈኝነት ምልክት ሆነዋል። እንደዚህ አንድ አላማ ኖሮን ነገርግን ተከፋፍለንና እርስ በርስ ተላትመን ደሞ አገራችን ኢትዮጵያን ወደምንፈለገዉ ቦታ መወሰድ ቀርቶ ይቺ የምንወዳት አገራችን ጭራሽ ወደማንፈልገዉ አቅጣጫ ስትሄድም ቆመን ከማየት ዉጭ ሌላ ማድረግ የምንችለዉ ምንም ነገር የለም። 

ስለዚህ አገር ዉስጥም ዉጭ አገርም ያለኸዉ ምድረ ፖለቲከኛ፥አክቲቪስትና የመብት ታጋይ ኢትዮጵያዊ ሆይ! . . . . . ልብ በል ደሞም ቆም ብለህ አስብ- ኢትዮጵያ እኛ በፈለግነዉ መንገድ ብቻ ነዉ መሄድ ያለባት የሚሉ ሃይሎች ከላይ በተጠቀሰዉ ደረጃ ሲያስቡና በትረ ስልጣን ጨብጠዉ ያሻቸዉን ለማድረግ ዕቅድ ነድፈዉ ሲንቀሳቀሱ እኔና እናንተ በየቀኑ ከትንሽነት ወደ ትንሽነት እንወርዳለን። እነሱ ዉጭ አገር ሁሉን ነገር ጨርሰዉ ስራ ለመስራት አገር ቤት ገብተዋል፥ እኛ ለመደራጀት ወደ ዉጭ አገር እንሄዳለን። እነሱ አላማቸዉን ለማሳካት የሚታገሉት እኛን ብቻ ነዉ፥ እኛ ግን ትግላችን እርስበርስ፥ ከነሱ ጋር አንዳንዴ ከማይታይ ባላጋራም ጋር ነዉ። ይህንን  ግራ የተጋባ ደንባራ የፖለቲካ ጉዞ በፍጥነት መቀየር ካልቻልን የወደፊቷ ኢትዮጵያ እጃቸዉ ላይ እንጂ እጃችን ላይ አይደለችም!

ባለፉት ሁለት አመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ የለዘብተኛ (Moderate) ድምጾችን አፍ እየዘጋ አየሩ ሁሉ የጽንፈኞችና የአክራሪዎች ድምፅ ብቻ ሆኗል። የአገር ተሰፋ ናቸዉ የተባሉ ሰዎች ፖለቲካችንን ለጽንፈኞች ትተዉ እነሱ የዳር ተመልካቾች ሆነዋል፥አንዳንዶች ደግሞ ለፖለቲካዉ ቁማር የሚያዋጣዉ ከሁለት ዋልታዎች አንዱን መርጦ መቆም ነዉ መሰለኝ እነሱም ዋልታ ረገጥ ሆነዋል። አሁን ከሰሞኑ እንዳየነዉ ደሞ ለአመታት አንድ ላይ ቁጭ ብለዉ የዛሬዋ ቀን እንድትመጣ ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈሉ ወገኖችም ጎራ ለይተዉ ቃላት መወራወር ጀምረዋል። የብዙ አገሮችን ታሪክ ወደኋላ ዞር ብለን ስንመለከት ዲሞክራሲ የሰመረላቸዉ አገሮች በሂደት ሁለቱ ዋልታ ረገጥ ሃይሎች እየሟሙ ለዘብተኛ ሃይሎች እየጎለበቱ የመጡባቸዉ አገሮች ናቸዉ። የኛ አገር ነገር ግን ሁሌም የተገላቢጦሽ ነዉና ለዘብተኛ ድምጾች እየጠፉ ጽንፈኛና አክራሪ ድምጾች እየበዙ መጥተዋል። ከሰሞኑ እንዳየነዉ ደሞ ከአንደኛዉ ዋልታ የተገነጠለ ድምፅ ጭራሽ ሶስተኛ ዋልታ ካልፈጠርኩ እያለ ነዉ። የተገላቢጦሽ ያልኩትም ይህንኑ ነዉ . . . .  ዋልታ ብሎ ሶስት የለማ! የሚገባን ከሆነ እንደ እስራኤል ህዝብ ከግማሽ ምዕተ አመት በላይ አድራሻና መድረሻ የለሽ የፖለቲካ በረሃ ዉስጥ የተንከራተትነዉ የሌለና ፍጹም ሊኖር የማይችል ነገር ካልፈጠርን እያልን ነዉ።

የግራና የቀኝ አክራሪ ሃይሎች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዉስጥ እየተጫወቱ ያለዉን እጅግ በጣም አደገኛና አጥፊ ሚና ለማወቅ ባለፈዉ ሳምንት ቤተስዳ ሜሪላንድና አሌክሳንደሪያ ቨርጂኒያ በዚህ ሳምንት ደሞ መቀሌ ዉስጥ የተደረገዉን ስብሰባና ተሰብሳቢዎቹን መመልከቱ ይበቃል። የሜሪላንዱ ስብሰባ የኦሮሞ ጥቅም መቅደም አለበት የሚል ነዉ። የመቀሌዉ ስብሰባ ደሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ታግሎ የጣለዉን የህወሓትን የስቃይና የመከራ ዘመን እንደገና ሊጭኑበት የሚሞክሩና ማሰብ ያቆሙ አዛዉንቶች ስብስብ ነዉ።የሜሪላንዱና የመቀሌዉ ስብሰባ ኢትዮጵያን የመሰረቱት ብሄር ብሄረሰቦች ናቸዉና እነሱ እስከፈለጉ ድረስ ኢትዮጵያ ትኖራለች እነሱ ካልፈለጉ የየራቸዉን መንገድ መሄድ ይችላሉ ብሎ የሚያምንና በፌዴራሊዝም ሽፋን ኢትዮጵያን ለመበትን ቆርጦ የተነሳ ሃይል ነዉ፥ደሞም መቀሌና ሜሪላንድ በስትራቴጂ ደረጃ አንድ ላይ ይሰራሉ እንጂ አይለያዩም። የቨርጂኒያዉ ስብሰባ በኢትዮጵያ ስም የቆረቡ ሰዎች የተገኙበት ስብሰባ ነዉ። የቨርጂኒያ ስብሰባ አሁን ባለዉ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሃይል አሰላለፍ ዉስጥ ወዳጅና ጠላት የማይለዩ የጥይት አባካኞች ስብሰባ ነዉ። ደግሞም ቨርጂኒያዎች የመቀሌንና የሜሪላንድን ጽንፈኞች አምርረዉ ይቃወሙ እንጂ እነሱ እራሳቸዉም ምንም አይነት የለዘብተኝነት ምልክት የማይታይባቸዉ፥የራሳቸዉን መሰረት የሚንዱና ኢትዮጵያን እየወደዷት የሚጎዷት የዞረባቸዉ የፖለቲካ ሽርጉዶች ናቸዉ።

ሜሪላንድ ዉስጥ ተሰብስቦ የመከረዉ ኢትዮጵያዊ የስብሰባዉ መሪ አድርግ የሚለውን ሁሉ ከማድረግ ወደኋላ እንደማይል ፊቱ ላይ ይነበባል፥ይህ ቁርጠኝነቱ ደግሞ በቅርቡ አገር ዉስጥም  በተግባር ታይቷል። የቨርጂኒያዉ ተሰብሳቢም ተመሳሳይ ቁርጠኝነት አለዉ። የቨርጂኒያዉ ቁርጠኝነት ግን የሜሪላንዱን ሰብሳቢ ለማጥፋት ነዉ። ይህም ቁርጠኝነት አገር ዉስጥ ያለ ቁርጠኝነት ነዉ።  በሁለቱ ሰብሳቢዎች፥ በአላማቸዉና በደጋፊዎቻቸዉ መካከል ያለዉ ልዩነት በጣም ያስደነግጣል። እኔንም ያስደነገጠኝ የዚህ ትልቅ ልዩነት መኖር  ነዉ። ሜሪላንዶች በገንዘብም በሰዉም ተደራጅተዋልና ያሰቡትን የማድረግ አቅም አላቸዉ፥ ቨርጂኒያዎች ግን ከአዳራሽ ዉስጥ ጩኸትና ቁጣ ያለፈ አቅም የላቸዉም።እነዚህ ሁለት ዋልታ ረገጥ ሃይሎች እርስ በርስ ሲላተሙ የምትደማዉ ግን የኔም የነሱም አገር ናት! ለዚህም ነዉ አገሬ ስትደማ እያየሁ በፍጹም ዝም የማልለዉ እንጂ የተለመደዉ የምላስ ብትር እንደሚወረወርብኝማ መች አጣሁት! በኢትዮጵያ ጉዳይ እንኳን የማይጎዳ የሚጎዳም በትር እንደማልፈራ ማን በነገራቸዉ። እነዚህ በየራሳቸዉ መንገድ ቆራጥ የሆኑ ሃይሎች አሜሪካና አዉሮፓ ዉስጥ የሰበሰቡትን ገንዘብ ይዘዉ ኢትዮጵያ ገብተዉ ሲፋጠጡ እሳቱ ከሁለቱ ዝሆኖች አልፎ ሁላችንንም ነዉ የሚያቃጥለዉ። እስከመቼ ነዉ አይናችን እያየ ሌሎች ባነደዱት እሳት እጃችንን አጣጥፈን የምንቃጠለዉ? እስከመቼ ነዉ እርስ በርስ ለመጨራረስ ገንዘብ የምናዋጣዉ? እኔ በቃኝ ብያለሁ!  አንተስ? እንቺስ? እናንተስ? መቼ ነዉ ከመጠፋፋት ፖለቲካ ወደ መነጋገር ፖለቲካ የምንሸጋገረዉ? ለምንድነዉ የግለሰቦችን ተክለሰዉነት መገንባት አቁመን የአላማና የተግባር አንድነት የማንገነባዉ? ለምንስ ነዉ እኛንም አገራችንንም ለማይጠቅም አላማ የምናሳየዉን ቁርጠኝነት ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያ ልጆቼ ከጽንፈኞች ገላግሉኝ ብላ ስትጣራ የማናሳየዉ?

በ1966 ተለያይተን ሞከርን አልሆነም፥ በ1983ትም አልሆነም፥ ዛሬም አይሆንም! ከስህተት አለመማርና መማር አለመፈለግ በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸዉ። የሰዉ ልጆች የተፈጥሮ ባህሪይ ባይሆንም በየግል ህይወታችን ስህተት እየደገምን መኖር እንችላለን።በአገር ላይ ግን ተመሳሳይ ስህተት እየሰራን መኖር አንችልም፥ ሊፈቀድልንም አይገባም። በ1960ዎቹ መኢሶንና ደርግ አንድ ላይ ሆነዉ ኢሕአፓን ለማጥፋት ቆርጠዉ ተነሱ፥ ኢትዮጵያ መኢሶንን፥ ኢሕአፓንና አያሌ ምርጥ ልጆቿን አጣች። ይህንን አሳዛኝ ታሪክ እየሰማ ያደገ አዲሱ ትዉልድ ከዚያ ትዉልድ ጥፋት መማር ነዉ ያለበት እንጂ የዚያን ትወልድ ጥፋት መድገም የለበትም። አዲስ አበባ ዉስጥ መኪና ስንነዳ እኔም የያዝኩት መኪና ነዉ ብለን ቪትስ እየነዳን ከሲኖ ትራክ ጋር ፉክክር አንይዝም. . . . . ቀጨኔ ካልናፈቀን በቀር! ሲኖ ትራክ እንኳን ሄደንበት ሸሽተንም የማይምረን የመንገድ ላይ ቦምብ ነዉ። በጋራ የመስራት ባህልና ድርጅታዊ ዝግጅት እስከሌለን ድረስ የኢትዮጵያ ፖለቲካም ከሲኖ ትራክ አይለይም። ይህ የገባቸዉ ሰዎች ናቸዉ ዛሬ በየአዳራሹና በየአደባባዩ እንደራጅ እያሉ የሚጮኹት። እንስማቸዉና እንደራጅ!

መቼ ነዉ የዛሬዉ ትዉልድ ከጥላቻ፥ ከመጠላለፍና ከመገዳደል ፖለቲካ ተላቅቆ ልዩነቶቹን በዉይይት መፍታት የሚጀምረዉ? ለምንድነዉ በመካከላችን ግድግዳ ሰርተን ከምንለያይ ግድግዳዉን አፍርሰን እና የሜሪላንዱንና የቨርጂኒያዉን ስብሰባ ሰብሳቢዎች እንዲቀራረቡ አድርገን አንዳንድ ልዩነቶቻቸዉ እንዳሉ ሆነዉ በጋራ ጉዳዮች ላይ እንዲወያዩ የማናደርገዉ? የጋራ ጉዳይ የላቸዉም አትበሉኝ! ኢትዮጵያ የምትባል የጋራ አገር አላቻቸዉና የጋራ ጉዳይ አላቸዉ። ችግሩ ጽንፈኝነት በነገሰበት አገር ዉስጥ ስሜታዊነት እንጂ ምክንያታዊነት ቦታ የለዉም፥ ደሞም እንዲህ አይነቱን ፖለቲካችንን ወደመሃል የሚያመጣ ሃሳብ መግደል እንጂ ማዳመጥ የሚፈልግም የለም። መፍትሄዉ ግን መነጋገር ብቻ ነዉ!

 ዛሬ ለፍርድ ይቅረብ፥ይታሰር፥ይሰቀል፥ይገደል እያልን በየሄደበት የምናሳድደዉ ሰዉ ኢትዮጵያ የገባዉ የትግል ስትራቴጂ ነድፎ ነዉ። ይህንን በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ወጣት አደራጅቶ ስትራቴጂዉን ለመተግበር አገር ቤት የገባ ሰዉ እኛ ዉጭ አገር ሄደን በ“ጎ ፈንድ ሚ” እና በአዳራሽ ዉስጥ ቁጣ አናስቆመዉም። ደሞም የኛን የአመት ”ጎ ፈንድ ሚ” ቁጢ ቁጢ  እሱ በግማሽ ቀን ነዉ የሚያፍሰዉ። የገዛ ቤታቸዉን መጠገን ያልቻሉ ስዎችን ከጎናችን አሰልፈን አገር መጠገን አንችልም! ከአካኪ ዘራፍ የማህበራዊ ሜዲያ ተሳዳቢዎች የምናገኘዉ ነገር ቢኖር ተከፍሎ የማያልቅ የፖለቲካ ዕዳ ብቻ ነዉ። እዚያ ማዶ ያሉ ሰዎች እሳት ማንደድ ይችሉ ይሆናል ግን ያነደዱትን እሳት ማጥፋት አይችሉም፥ ደግሞም እሳቱ አያቃጥላቸዉም። ስለዚህ ባይሆን ክብሪቱን ይስጡንና እሳቱን ማንደዱም ማጥፋቱም የኛ አገር ቤት ያለነዉ ሰዎች ስራ ይሁን! ምነዉ አንተም ነበርክበትኮ ትሉኝ ይሆናል፥ አዎ ነበርኩ አሁን ግን እዚህ ነኝ፥ ደሞም ያኔና አሁን ግዜዉ በጣም ይለያያል።

የምናሳድደዉ ሰዉ ግደል ሲሉት ለምን ሂድ ሲሉት ወዴት ብሎ የማይጠይቅ ጽንፈኛ የሆነ ሃይል አደራጅቷል፥ ጽንፈኛን እኛዉ እራሳችን ጽንፈኛ ሆነን አናሸንፈዉም። እኛ ጎጠኛ እሱ ነፍጠኛ ይለናል- የቃላት ጦርነት ተሸናፊ እንጂ አሸናፊ የለዉም። እሱ በእኛ አይን የተሳሳተ አላማ አለዉ፥ እኛም በሱ አይን የተሳሳተ አላማ ነዉ ያለን፥ ግን ስህተት ስህተትን አያሸንፈም። ስለዚህ ይህንን በሃይል የመጣብንን ግለሰብ  ለማስቆም ያለን አማራጭ መደራጅት ብቻ ነዉ። ዛሬ እንዳሻቸዉ እየመጡ አጥራችንን የሚነቀንቁ ሰዎች እኛንም አጥራችንንም የሚያከብሩት እኛም ቤት  የተደራጀ ሃይል እንዳለ ሲያዉቁ ብቻ ነዉ። ተለያይተን ሞከርን፥ ተሰዳድበን ሞከርን፥ ተጠላልፈን ሞከርን፥ተገዳድለን ሞከርን፥ አገር ዉስጥ ሞከርን፥ ዉጭ አገር ሞክርን። ያልሞከርነዉ አንድ ነገር ብቻ ነዉ. . . . .  መደራደር! አዎ እስካሁን ያልሞከርነዉ ቁጭ ብሎ መነጋገርን ነዉ።እስኪ መጀመሪያ እንድንሰማና እንድንከበር እንደራጅ ከዚያ ቁጭ ብለን በአገራችን ጉዳይ ላይ እንደራደርና ፍትህ፥ ነጻነትና እኩልነት የሰፈነባት አገር ፈጥረን ይህንን ብቻዉን አገሬን አገሬን የሚለዉን ህዝብ እንድረስለት።  

ማስታወሻበዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here