spot_img
Monday, June 24, 2024
Homeነፃ አስተያየትየአቶ ለማ መገርሳ "ልዩነት" ሰምና ወርቅ (በመስከረም አበራ)

የአቶ ለማ መገርሳ “ልዩነት” ሰምና ወርቅ (በመስከረም አበራ)

(በመስከረም አበራ)
ታህሳስ 10 , 2012 ዓ. ም.

“የለማ ቡድን” የሚባለው ስብስብ የህወሃትን የበላይነት የማስወገዱ ታላቅ ትግል በሚዘከርበት ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ ይዞ ሲወሳ የሚኖር ቡድን ነው፡፡ይህ ቡድን ሃገራችን በለውጥ ወሊድ እንዳትሞት ያደረገ ባለውለታ ነው፡፡የለማ ቡድን በስተመጨረሻው የህዝብን ትግል ባይቀላቀል ኖሮ የሃገራችን እጣ ፋንታ እንደ ሊቢያ ላለመሆኑ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡የዚህ ቡድን መጠሪያ በስማቸው የተሰየመላቸው አቶ ለማ መገርሳ ኢትዮጵያዊነትን አንግበው ለውጥ እንደሻቱ ሲናገሩ የብዙውን ኢትዮጵያዊ ልብ በሃሴት ሞልተዋል፡፡ ኢትዮጵያን አጀንዳ አድርጎ መነሳቱ ከወደ ኦሮሞ ብሄርተኝት ፖለቲከኞች መንደር እምብዛም የተለመደ ስላልሆነ ነበር ደስታው፡፡

የሆነ ሆኖ የአቶ ለማ የድንገቴ ኢትዮጰያዊነት መንፈስ እና ይህን ጉዳይ ከሱስ ጋር አናፅረው ያቀረቡበት መንገድ እኔን ጨምሮ አንዳንዶቻችንን ጥርጣሬ ላይ ጥሎን ነበር፡፡ባህር ዳር ላይ “ኢትዮጵያዊነት ሱሴ ነው” ያሉት አቶ ለማ ከባህርዳር ሲመለሱ አዲስ አበባ ላይ ከአራቱ ፓርቲዎች ሊቃነመናብርት ጋር መግለጫ ለመስጠት በተቀመጡበት ደግሞ “ኢትዮጵያዊነት በግድ የተጫነብን ስለሆነ ለመለማመድ ጊዜ ያስፈልገናል”ሲሉ መሰማታቸው በግሌ ግራ አጋብቶኝ “በለማ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው?” በሚል ርዕስ በከተብኩት ፅሁፍ ነገሩን በጥንቃቄ ማየት እንደሚገባ በገባኝ መጠን ለማሳየት ሞክሬ ነበር፡፡አቶ ለማ ከዚች ቀን ንግግራቸው ሌላ ጥርጣሬ ላይ የሚጥል ንግግር አለመድገማቸው ኢትዮጵያን የሚለው ሰው እያደር እንዲያምናቸው ሆነ፡፡    

ለውጡ ከተዋለደ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ ከኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድርነት ወደ መከላከያ ሚኒስትርነት የመጡት አቶ ለማ ታዲያ ከህወሃት መባረር በኋላ ስለኢትዮጵያ ቀድሞ በሚናገሩበት ሁኔታ ሲናገሩ የተደመጡት ሚኖሶታ ላይ ከዶ/ር አብይ ጋር ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ብቻ ነው፡፡ኋላ ላይ “የከተማ ፖለቲካን መቆጣጠር ወሳኝ ነገር በመሆኑ ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ኦሮሞዎችን አዲስ አበባ መሃል እና ዳር ዳር ማስፈር ይዣለሁ” ሲሉ የሚናገሩበት ቪዲዮ በዶ/ር አብረሃም አለሙ ከኦሮምኛ ወደ አማርኛ ተመልሶ መውጣቱ፣በዚህ ቪዲዮ የሚናገሩት ደግሞ ዶ/ር አብይም ጭምር መሆናቸው “ያለን ኢትዮጵያዊ አጀንዳ ነው” ሲሉ እጅግ አምኗቸው ለነበረው ህዝብ ትልቅ ግራ መጋባትን የፈጠረ ነበር፡፡

ከዛ ወዲህ ለማ ከአደባባይ ጠፉ!ከዕይታ በመጥፋታቸው ብቻ ሳይሆን ከኦሮሚያ ክልል ርዕሰ-መስተዳድርነት መነሳታቸውን እና በአደባባይ መታየት በመቀነሳቸው “እስከ ሞት እከተለዋለሁ” ካሉት ባልንጀራቸው ዶ/ር አብይ ጋር እንደ ወትሮው እንዳልሆኑ መወራት ያዘ፡፡በሌላ በኩል አብይ እና ለማ እጅ እና ጓንት ሆነው በኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ስም ለኦሮሞ የበላይነት የሚሰሩ ተደርጎም ይወሰድ ነበር፡፡

እውነት እና ንጋት እያደር ጠርቶ የዶ/ር አብይ እና የአቶ ለማ የሃሳብ ልዩነት በራሳቸው በአቶ ለማ አንደበት ይፋ ሆነ፡፡ ይህ ልዩነት መከሰቱ ተፈጥሯዊ ቢሆንም ልዩነቱ የተከሰተበትን ምክንያት መመርመሩም አስፈላጊ ነው፡፡ሃገራችን ተቋማዊ ዲሞክራሲን ያልገነባች በመሆኗ የፖለቲካዋ እጣ ፋንታ ስልጣን በተቆናጠጡ ሰዎች ፍላጎት፣ስነ-ልቦናዊ ሁኔታ፣የግል ማንነት በእጅጉ የሚላጋ ነውና የአቶ ለማ ልዩነት ዲሞክራሲያዊ የሃሳብ ልዩነት ነው ተብሎ ብቻ የሚታለፍ ሳይሆን በትኩረት መተንተን ያለበት ጉዳይ ነው፡፡

አቶ ለማ ለቪኦኤ በሰጡት ቃለ-ምልልስ ያስቀመጧቸው ሃሳቦች ለልዩነታቸው ዋነኛ የሆኑ ምክንያቶችን ያስረዳሉ፡፡በዚህ ቃለ ምልልሱ አቶ ለማ ያነሱት አንደኛው ነጥብ “ከሆነ ጊዜ ወዲህ ተሰሚነቴ ቀንሷል” የሚል ነው፡፡ይህ ተሰሚነቴ ቀንሷል የሚለው ነገር ህወሃትን ለመጣል በሚደረገው ትግል አቶ ለማ ዶ/ር አብይ የኦህዴድ ሊቀመንበር እንዲሆኑ የፈለጉበትን ምክንያት የሚጠቁም ጭላንጭል አለው፡፡አቶ ለማ ለዶ/ር አብይ የኦህዴድ ሊቀመንበርነታቸውን የለቀቁላቸው እርሳቸው የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት መቀመጫ ወንበር ስለሌላቸው ነበር እንጅ ይህ ቅድመ ሁኔታ ቢሟላላቸው ኖሮ ወንበራቸውን አሳልፈው ለሌላ ይሰጡ ነበር ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡አብይ በወቅቱ የኦህዴድ ምክትል ሊቀመንበር መሆናቸው ደግሞ አቶ ለማ የሊቀመንበርነቱን ቦታ ለሌላ የኦህዴድ ሰው የመስጠታቸውን ሁኔታ ሩቅ ያደርገዋል፡፡

ከዚህ ቀጥሎ የሚመጣው ነገር ደግሞ አቶ ለማ እና ዶ/ር አብይ ጓደኝነት ነው፡፡አቶ ለማ ዶ/ር አብይን ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ያበቃውን የኦህዴድ ሊቀመንበርነት ወንበር የመልቀቃቸው “ውለታ”፣ሁለቱ ሰዎች ያላቸው ጓደኝነት እና የዶ/ር አብይ የፓርቲ ጓዶቻቸውን በተቻለ መጠን እንደፀባያቸው አባብሎ ለመያዝ የሚያደርጉት ጥረት(የለማ ልብ መሻከር ከገፃቸው ላይ እየተነበበም አብይ “የኖቤል ሽልማቴን ለድህነት ጓዴ ለለማ ሰጥቻለሁ” ማለታቸውን ልብ ይሏል) ወዘተ ለለማ የሚሰጠው መልዕክት ይኖራል፡፡ይህ መልዕክት ጠ/ሚ አብይ የለማ ሌላኛው እጃቸው እንደሚሆኑ፣ለማ አድርግ የሚሏቸውን የሚያደርጉ እሽ ባይ እንደሚሆኑ የማሰብ ሳይሆን አልቀረም፡፡አቶ ለማ የጠ/ሚነቱን መንገድ መጥረጊያ የሆነውን የኦህዴድ ሊቀመንበርነት ለአብይ አመቻችተው የማቅረባቸው ውለታም በለማ በኩል ለተጠበቀው የአብይ እሽ ባይነት እንደ አንድ ምክንያት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

“ተሰሚነቴ ቀንሷል” የሚለው አባባል አቶ ለማ ባሰቡት ልክ አብይን መዘወር ያለመቻልን ቅሬታ ያዘለ ነገር አለው፡፡ነገሩ የመዘወር ፍላጎት ባይሆን ኖሮ አቶ ለማ አለኝ የሚሉት የሃሳብ ልዩነት በአብላጫ ድምፅ ከተሸነፈ ማድረግ የነበረባቸው በዲሞክራሲያዊ አካሄድ ሃሳባቸው ብዙሃኑን ማሳመን ስላልቻለ በድምፅ መበለጣቸውን ተቀብለው መቀጠል እንጅ “ተሰሚነት አጣሁ” ብሎ ለክስ መነሳት አልነበረም፤በዲሞክራሲያዊ የድምፅ ብልጫ መሸነፍ ማለት ተደማጭነት ማጣት አይደለምና፡፡በዲሞክራሲያዊ የድምፅ ብልጫ የተሸነፈ ሃሳብ ገዥ ያልሆነው የእኔ ተደማጭነት ስለቀነሰ ነው ማለት “ህግ መሆን ያለበት የኔ ሃሳብ ነው” የማለት የመዘወር ፍላጎት የማያጣው ዝንባሌ ነው፡፡  

ለማ በምን መልኩ ነው አብይን ሊዘውሩ የሚፈልጉት የሚለው ተገቢ ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም፡፡የዚህጥያቄ መልስ የሚገኘው ደግሞ “የኦሮሞ ህዝብ ቆጥሮ ያስረከበንን ጥየቄ ሳንመልስ ቀረን” የሚለው የአቶ ለማ ንግግር ውስጥ ነው፡፡ 

የኦሮሞ ልሂቃን “ስም አይጠሩ” ጥያቄዎች

የኦሮሞ ህዝብ እንደሰው የሰው ልጆች ሁሉ የሚጠይቁት የሰብዓዊ መብት፣የዲሞክራሲ፣የኢኮኖሚ ጥያቄዎች ይኖሩታል፡፡በታዳጊ ሃገር እንደሚኖር፣ መብቱ ተረግጦ አንደኖረ ህዝብ ደግሞ ከማኛውም ኢትዮጵያዊ ጋር የሚጋራው በርካታ ጥያቄ ይኖረዋል፡፡እንደ ኦሮሞነቱ ደግሞ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ይኖራሉ፡፡የኦሮሞ ህዝብ እንደ ሰውነቱም፣እንደ ኢትዮጵያዊነቱም ሆነ እንደ ኦሮሞነቱ  የሚያነሳቸው ጥያቄዎችን አንግቦ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን የህወሃትን የበላይነት ለማስወገድ ታግሏል፡፡

በህዝባዊ ትግሉ ውስጥ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ግልፅ ነበረ፡፡ከቀየው ያለመፈናቀል፣ያለመታሰር ፣ያለመሳደድ፣በማንነቱ የመከበር፣በክልሉ ሃብት ተጠቃሚ የመሆን ጥያቄዎች ናቸው የኦሮሞን ህዝብ ለትግል ያሰለፉት፡፡ከዚህ በተጓዳኝ ሲነሳ የሚሰማው ኦሮምኛን የኢትዮጵያ የስራ ቋንቋ የማድረግ ጥያቄ ነው፡፡ከዚህ ባለፈ የኦሮሞ ህዝብ ከሰው ፍጥረት፣ከኢትዮጵያዊያን ወገኖቹ የተለየ ረቂቅ ጥያቄ ሊኖረው አይችልም፡፡ሆኖም በግልፅ እንዳይናገሩት አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ የደረሰበት ደረጃ የማይፈቅድላቸው በኦሮሞ ህዝብ ስም የራሳቸውን ረቂቅ ጥያቄ አንግበው የሚንቀሳቀሱት የኦሮሞ ልሂቃን አይጠፉም፡፡በየደረሱበት “የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ” እያሉ የሚያመሳጥሩትም የራሳቸው ልቦና የሚጠይቃቸውን ጥያቄ ነው፡፡ይህን ጥያቄ መመርመር የፖለቲካችንን ፈር የሚያሳይ ነውና ወደዛው ልለፍ፡፡

ጥያቄ አንድ

እነዚህ የኦሮሞ ልሂቃን የሚያነሷቸው ጥያቄዎች በርካታ ናቸው፡፡የመጀመሪያው ማንኛውም የበለጠ ታግያለሁ ባይ የሚያነሳው ይበልጥ በመታገሌ በሃገሩ ፖለቲካ ላይ በለጥ ብየ ልታይ የሚል የውለታ አስቆጣሪነት፣የልብለጣችሁ ባይነት ጥያቄ ነው፡፡በርካታ የኦሮሞ ልሂቃን አሁን በኢትዮጵያ የመጣው ለውጥ እንዲመጣ የታገለው ኦሮሞ ነው ብለው ያስባሉ፡፡አስበውም ህወሃት ያደርገው እንደነበረው የኦሮሞ የበላይነት በሃገሪቱ እንደሚጣ አጥብቀው ይሻሉ፡፡ይህ ፍላጎት ኦሮሞ ከዚህ በፊት ስልጣን ላይ እንዳይወጣ ተደርጎ ሲናቅ፣ሲጨቆን ኖሯል የሚል ከስነ-ልቦናዊ ነገር ጋርም ተያያዥነት አለው፡፡አሁን ተጠራርቶ ስልጣን ላይ መቀመጡ የሚፈለገውም ሲንቀኝ፣ሲጨቁነኝ ነበር ተብሎ የሚታሰበውን አካል ከዋነኛ የፖለቲካ ጨዋታ ውጭ አድርጎ ለመበቀል ያለመ ህወሃት ሲጓዝበት በነበረው መንገድ ለመጓዝ የመፈለግ ዝንባሌ ነው፡፡ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተወሰኑ የኦሮሞ ብሄርተኞች ወደ ህወሃቶች መለስ ቀለስ ማለታቸው፣በግልፅ ህወሃት ስትራቴጃዊ አጋራችን ነው ሲሉ መደመጣቸው የዚህ ዝንባሌ ምልክት ነው፡፡

ሆኖም ከአዘቦታዊው የኦሮሞ ብሄርተኝነት ትርክት ከፍ ብለው የመጡት ዶ/ር አብይ እና በጣም ጥቂት የኦህዴድ ጓዶቻቸው ይህ አካሄድ እንደማያዋጣ፣ለኦሮሞ ህዝብም የሚጠቅመው በእኩልነት እንጅ በመብለጥ መኖር እንዳልሆነ ተረድተው በልጦ ለመታየት ከሚሹ የኦሮሞ ብሄርተኞች የተለየ መንገድ ያዙ፡፡በግልፅ የማይነገረው ግን ደግሞ ቀላል የማይባሉ የኦሮሞ ልሂቃን የሚጋሩት በህወሃት መንገድ የመጓዝ እሳቤ ነው በኦህዴድ ውስጥ ያሉትንም ሆኑ የሌሉትን አክራሪ ኦሮሞ ልሂቃን ከዶ/ር አብይ ጋር ሆድ እና ጀርባ ያደረጋቸው፡፡ሌሎች ምክንያቶች ከዚሁ ምክንያት የሚመዘዙ ዘለላዎች ናቸው፡፡ የሚገርመው ነገር ግን አቶ ለማ መገርሳም የዚህ እሳቤ ተጋሪ መሆናቸው ነው፡፡”የኦሮሞ ህዝብ ቆጥሮ ያስረከበኝ ጥያቄ አለ” ሲሉ በኦሮሞ ህዝብ ስም ያነሱት ስም አይጠሩ ጥያቄ ይሄው ጎላ ብሎ የመታየት ምኞት ካልሆነ እንደ ጀመሩት ወደ ሚዲያ ቀርበው ተሰጠኝ ያሉትን ጥያቄ ቢያስረዱ ለመስማት የሚጓጓው ብዙ ነው፡፡

ጥያቄ ሁለት

ሌላው ስም አይጠሩ የኦሮሞ ልሂቃን ጥያቄ እነሱ “አባ ቢዩማ” የሚሉት ወደ አማርኛው ሲመለስ “የሃገር ባለቤት” የመሆን ጥያቄ ነው፡፡ይህ ጥያቄ ሳይድበሰበስ እንቅጩን ሲቀመጥ ኦሮሚያ ውስጥ ያለውን ኦሮሞ ያልሆነ ኢትዮጵያዊ ከኦሮሚያ ነቅሎ የማስወጣት ፍላጎት ነው፡፡የጥያቄው ዋነኛ አቀንቃኝ ደግሞ በአሁኑ ወቅት የአክራሪው የኦሮሞ ብሄርተኝነት መሪው አቶ ጃዋር መሃመድ  ነው፡፡ጃዋርና ሰልፈኞቹ የኦሮሞ ህዝብ ዋነኛ ችግር ኦሮሞ ያልሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ በኦሮሚያ ክልል መኖሩ ይመስላቸዋል፡፡

በጃዋር እና በሰልፈኞቹ እሳቤ ኦሮሚያ ክልል የሚኖረው ኦሮሞ ያልሆነ ኢትዮጵያዊ አማራ ከሆነ ለጭቆና የሄደ ነው፤አማራ ካልሆነ ደግሞ የኦሮሚያን ተፈጥሮ ሃብት ሊቀራመት፣ሊያራቁት የሄደ ጥገኛ እንጅ ለኦሮሚያ ማደግም የሚያዋጣው እውቀት፣ሙያ፣ገንዘብ እና ጉልበት ይዞ የሚሄድ አይደለም፡፡ስለዚህ ኦሮሞ ያልሆነ ኢትዮጵያዊ ኦሮሚያን መልቀቅ አለበት፡፡በቅርቡ በባሌ በግልጽ በአደባባይ የሌሎች ብሄረሰቦች ስም እየተጠራ ከእነሱ ጋር የሚደረግ ግንኑነት እንዲቋረጥ እንዳለበት፣ ከኦሮሚያም ለቀው እንዲወጡ የሚያስፈራራ ስማበለው ሲለፈፍ መሰማቱ አንድ አስረጅ ነው፡፡በቡራዩ የተደረገው ግድያ እና ሌሎች በርካታ አጋጣሚዎች ሁሉ የዚህ እሳቤን ስር መስደድ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ይህ መጤ የማስለቀቁ ስራ ሲተገበርና ኦሮሚያ ውስጥ የሚኖረው፣የሚነግደው፣ተቀጥሮ  የሚሰራው  ሁሉ ኦሮሞ ብቻ የማድረጉን አካሄድ ነው በነጃዋር የፖለቲካዊ መዝገበ ቃላት “አባ ቢዩማ”፤በአማርኛው ሲመለስ ደግሞ “የሃገር ባለቤት” የሚባለው፡፡ጃዋር ከለማ ወግኖ አብይን የሚያብጠለጥለው አብይ ይህ እሳቤ ሃገር የማዳን መንገድ እንዳልሆነ ስለተረዱ፤ሃሳቡንም ሃሳባቸው ስላላደረጉ ነው፡፡በአንፃሩ ጃዋር እና አቶ ለማ በዚህ ጉዳይ ላይ ተቀራራቢ እሳቤ ሳይኖራቸው አልቀረም፡፡ባይሆን ኖሮ ጃዋር የለማን ስም እንደ ማስቲካ ከአፉ የማይነጥልበት ምክንያት አይኖርም፡፡

አቶ ጃዋር መሃመድ ከዛሬ ስንት አመት በፊት “Ethiopia out of Oromiya” ወደ አማርኛው ሲመለስ “ኢትዮጵያ ከኦሮሚያ ትውጣ” የሚለው ስሜታዊ የቪዲዮ ንግግሩን የዚህ እሳቤ ተሸካሚነቱ ምስክር ነው፡፡”ያ የቆየ ንግግሩ ነው፤ ዛሬ የእሳቤ ለውጥ አምጥቶ ይሆናል” የሚል አንባቢ ካለ ደግሞ ጃዋር ከዛሬ አምስት ወር ባልበለጠ ጊዜ ወደ ሲዳማ ዞን ተጉዞ፣በሲዳማ ኮበሌዎች ተከቦ “ክልላችሁን በህግም በጉልበትም የራሳችሁ ካደረጋችሁ የክልላችሁ ሃብት ባለቤቶች ትሆናላችሁ፤የክልላችሁ ሃብት የትምክህተኞች እና የዘራፊዎች መፈንጫ መሆኑ ያበቃል፤ኦሮሚያም የኦሮሞ፣ሲዳማም የሲዳማ ብሄረሰብ ትሆናለች” ሲል የተናገረውን ማድመጥ ይቻላል፡፡በዚህ ንግግር ውስጥ ጃዋር “ዘራፊ” እና “ትምክህተኛ” ሲል የሚገልፀው በሲዳማ ዞን የሚኖር ሲዳማ ያልሆነን ኢትዮጵያዊ እንደሆነ ክርክር ያለው ነገር አይደለም፡፡                           

ይህን የሚለው አቶ ጃዋር ደግሞ ገና ከመነሻው ዶ/ር አብይን ስሙን ለመጥራት ሳይቀር ሲቸገር የነበረ በአንፃሩ ደግሞ አቶ ለማን ለማሞገስ ጊዜ የማይበቃው፣በአቶ ለማ ጠ/ሚ መሆን አለመቻል ሲብሰለሰል የኖረ ሰው መሆኑ የአቶ ለማ ዘመም ዘመም ወደ አቶ ጃዋር ጎራ ለመሆኑ ፍንጭ ሰጭ ነው፡፡አቶ ጃዋር ከዶ/ር አብይ ጋር አይን እና ናጫ፣ ከአቶ ለማ ጋር ደግሞ ወዳጅ እንደሆነ የሚጠቁሙ ዝንባሌዎችን በተደጋጋሚ ማሳየቱ ሳያንስ አቶ ለማ ከዶ/ር አብይ ጎራ ጋር ያላቸውን ልዩነት በቪኦኤ ወጥተው የተናገሩበት ንግግር ሳይታገድ ጭምር “ታግዷል” እያለ ደረት ሲመታ መሰንበቱ የአብይን እና የለማን፣እንዲሁም የአብይን እና የጃዋርን አሰላለፍ ልዩነት ሲጠራጠር ለነበረ ሁሉ ውዥንብሩን የገፈፈ ነበር፡፡ዋናው ጉዳይ ግን ጃዋር የለማ ልዩነት ታማኝ ምንጭ በሆነው ቪኦኤ ይፋ እንዲሆን ለምን ፋታ አጥቶ ሰራ የሚለው ጥያቄ ነው፡፡

ጃዋር ይህን ያደረገው በኦሮሞ ብሄርተኞች ዘንድ የለማ ሚዛን ከአብይ ሚዛን ከብዶ የሚታይ መስሎት፣በለማ በኩል የራሱን የጃዋርን ሚዛንም በማከል የአብይን ፖለቲካዊ ሚዛን ለማቅለል ነበር፡፡ይህ ቢሳካ ኖሮ በተዋሃደው ፓርቲ ውስጥ ያሉ የኦሮሞ ብሄርተኞች በውህደቱ ማግስት ንትርክ አንስተው አንድ አንድ እያሉ  በለማ ጎራ ተሰልፈው ‘የብልፅግና ፓርቲ የኦሮሞ ህልውና የሌለው የነፍጠኞች ፓርቲ ነው’ የሚለውን ዘፈን ጮክ አድርጎ ለማዘፈን ነበር፤አልተሳካም፡፡ይህ የጃዋር እሳቤ ቢሰምር ኖሮ ሃገራችን ከወደ ኦሮሚያ በሚነሳ ፖለቲካዊ ድብልቅልቅ ተመትታ በቋፍ ላይ ያለው መረጋጋቷ አደጋ ላይ በወደቀ ነበር፡፡ይህ እንዳይሆን አብይ ያደረጉትን መለኛነት፣ብስለት፣ አስገራሚ ብልሃት የተሞላበት፣ እጅግ ድፍረት የሚጠይቅ እርምጃ አለማድነቅ አይቻልም፡፡

አብይ ለማን እና ጃዋርን የመሰሉ በኦሮሞ ብሄርተኞች ዘንድ እጅግ ግዙፍ ቦታ ያላቸውን ሰዎች አሸንፈው፣ኦህዴድን ሙሉ በሙሉ ይዘው ወደ ብልፅግና ፓርቲ መጓዛቸው በግሌ ተዓምር የሚመስለኝ ድል ነው፡፡እዚህ ላይ ላስመዘገቡት ባለድልነታቸው ለዶ/ር አብይ ትልቅ አድናቆት አለኝ! አድናቆቴ የሚመነጨው ደግሞ ከውስጥ አቶ ለማን የመሰሉ ምርኩዝ ባፈነገጡበት፣ከውጭ ጃዋርን የመሰለ አጯጯሂ በር ላይ ባለበት ሁኔታ የኦሮሞ ብሄርተኞችን ወደ ሲቪክ ፖለቲካ ጎትቶ ማምጣት ምን ያህል አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን አደገኛ ሙከራ መሆኑን ስለምረዳ ጭምር ነው፡፡ነገሩን ተዓምር የሚያስመስለው ሌላ ጉዳይ በብዙ ያመንናቸውን አቶ ለማን ሳይቀር የፈተነውን የኦሮሞ ብሄርተኝነት እድገት ደረጃ ምን ላይ እንደደረሰ ስለምገነዘብ ነው፡፡

የሆነው ሆኖ በውስጥ ውስጥ ጉም ጉም ሲባልበት የሰነበተው የአብይ እና ለማ ልዩነት በጃዋር አጋፋሪነት በቪኦኤ እንዲለቀቅ የተፈለገበት የአብይን ሚዛን የማቅለል ዘመቻ ጃዋር እንዳሰበው አብይን አቅልሎ በለማ ላይ ሞገስ ደርቧል ወይ? የሚለው ሲመረመር ነገሩ አቶ ጃዋር ካሰበው በተቃራኒ ነው፡፡እንደውም ለአብይ ከሁለት በኩል ድል ሲያስመዘግብለት አቶ ለማን ደግሞ ወደ ጃዋር ቀጠና በመውረዱ የቁልቁሊት ጉዞ እንዲያዘግሙ አድርጓል፡፡

አብይ ከሁለት ጎራ የሰበሰቡት የፖለቲካ ትርፍ ከየት እና ከየት ነው? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ስለሚችል ግልፅ ማድረጉ ተገቢ ነው፡፡አንዱ ጎራ በተለያዩ ጊዜያት በታዩ ምልክቶች (ለምሳሌ የአዲስ አበባ የኦሮሞ ባለቤትነት ላይ ፓርቲያቸው ባወጣው መግለጫ፣ከአቶ ለማ ጋር ስለ ዲሞግራፊ ለውጥ ሲያወሩ በታዩበት ቪዲዮ፣አዲስ አበባ ላይ ሰልፍ መከልከላቸውን፣ከባላደራው ጋር በገቡበት እሰጣ ገባ ሳቢያ)የተነሳ ከለማ እና ጃዋር ያልተለዩ አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኛ አድርጎ ያያቸው የነበረውን እና የቀደመ ፍቅሩን እየቀነሰ የመጣውን የኢትዮጵያ ብሄርተኛውን ጎራ ልብ በተወሰነ ደረጃ ለመመለስ መቻላቸው ነው፡፡የለማ ማፈንገጥ እና ይህን ተከትሎ ጃዋር በግልፅ ከለማ ጎን መቆሙን የሚያሳዩ ዲስኩሮች ማድረጉን ተከትሎ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛው አብይ  ከላይ የተጠቀሱትን በአክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኝነት የሚያስጠረጥሩትን ነገሮች ሲያደርግ የነበረው በለማ መሪነት ከፓርቲው በሚመጣበት ጫና እንደነበረ ለመገንዘብ የቻለበት ነገር በተወሰነ ደረጃ የተፈጠረ ይመስላል፡፡ይህ ለአብይ ቡድን እጅግ ጉልበት ሰጭ ነገር ሲሆን ለለማ እና ለጃዋር ጎራ የሚጎዳው እንጅ የሚጠቅመው ነገር የለም፡፡

ሁለተኛው አብይ የፖለቲካ ትርፍ የሰበሰቡበት ጎራ ከሌለው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር በእኩልነት እና በሰላም መኖርን እንጅ የህወሃትን መንገድ የማይደግፈውን ሰከን ያለውን ኦሮሞ ህዝብ ከፍል ነው፡፡ለኦሮሞ ህዝብ ይበልጥ ተቆርቋሪ እንደሆነ የሚያወሳው የአቶ ለማ/ጃዋር ቡድን ኦህዴድ ውስጥ ጉልበት እንደሌለው፣ ማንንም የኦህዴድ አባል የብልፅግና ፓርቲ አባል ከመሆን ማስቀረት አለመቻሉን ያሳጣ ነው ይህ አጋጣሚ፡፡ይህ ደግሞ ቢያንስ በኦህዴድ ውስጥ ቢበዛ ሰከን ባለው የኦሮሞ ፖለቲከኛ ዘንድ የአብይ ፖለቲካዊ ሚዛን ከለማ/ጃዋር ከበድ እንደሚል ያመላክታል፡፡ የአብይ ለዘብተኛ የኦሮሞ ብሄርተኝነትን የማስኬድ መንገድ  ከጃዋር/ለማ መንገድ በተሻለ በኦሮሞ ብሄርተኞች ዘንድም ተቀባይነት እንዳለው በአንፃሩ የጃዋር/ለማ ቡድን “የአባ ቢዩማ” እሳቤ እምብዛም ሩቅ የሚያስኬድ እንዳልሆነ ግልፅ ምስክር ነው፡፡የአብይ መንገድ ከኦሮሙማ ጠባብ እሳቤ አለፍ ብሎ ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ከገባችበት ቅርቃር የመታደግ ሰፊ እሳቤ በመሆኑ በሰፊው የኦሮሞ ህዝብ ዘንድም የሃገር አዳኝነትን የከፍታ ስነ-ልቦና የሚያሰርፅ ትልቅ ምዕራፍ ነው፡፡

ጥያቄ ሶስት

 ሶስተኛው የጃዋር/ለማ ሰልፈኞች ጥያቄ በልዩ ጥቅም ጥያቄ የተጠቀለለው አዲስ አበባን በጨፌ ኦሮሚያ ስር የማስተዳደር ፋታ አልቦ አምሮት ነው፡፡ይህ ህገ-መግስታዊ ካለመሆኑ ባሻገር የአዲስ አበባን ህዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት የሚቀማ የጉልበተኝት ጥያቄ ሃገራችን ለምትሻው የህገ-መንግስታዊነትነት እና ዲሞክራሲያዊ የአስተዳደር ዘይቤ ትልቅ ተግዳሮት የሚደቅን ፈተና ነው፡፡ሆኖም ከዲሞክራሲም ሆነ ከህግ የበላይነት ጋር ትውውቅ የሌላቸው ግን ደግሞ ዲሞክራሲንም ሆነ የህግ የበላይነትን በማነሳሳቱ ማስመሰል ወደር የሌላቸው የዘውግ ፖለቲካው ጎራ ቀሳውስት ጥያቄው ተገፍቶበታል፡፡አዲሱ የብልፅግና ፓርቲ ለአዲስ አበባ የራሷን መቀመጫ የሰጠ መሆኑ ለአዲስ አበባ ህዝብ ጥሩ ምልክት ቢሆንም የኦሮሞ ብሄርተኞች በአዲሱ ፓርቲ ላይ ዋገምት የሚተክሉበት አቅጣጫ መሆኑም መረሳት የለበትም፡፡

አቶ ለማ አዲስ አበባን የኦሮሚያ የማድረጉ የማይሆን ጉዞ መንገደኛ መሆናቸውን ያኔ የዲሞግራፊ ለውጥ ለማምጣት እየሰራሁ ነው ያሉበትን ንግግር አስተባበልኩ ብለው በተናገሩት ንግግር ውስጥ “ኦሮሞ አዲስ አበባ አምጥቼ ባሰፍርስ እኔ የኦሮሚያ አስተዳዳሪ አይደለሁም እንዴ?ይህን ማድረግ መብቴ አይደለም እንዴ?” ባሉት ንግግር ውስጥ ፍንጭ ማግኘት ይቻላል፡፡ለማ “የኦሮሞ ህዝብ የሰጠንን ጥያቄ ሳንመልስ ወደ ውህደት መሄድ የለብንም” ሲሉ እንደ ማኛውም አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲከኛ  በግልፅ የማይናገሯቸው ግን ከላይ የተነሱ ሶስት ጥያቄዎችን ሳንመልስ ከብሄርተኝነታችን ፈቀቅ ማለት የለብንም ማለታቸው ነው፡፡

ይህን ሲሉ የረሱት መሰረታዊ ነገር ግን እነሱ አሉን የሚሏቸው ጥያቄዎች ኦሮሞ ላልሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ምን ማለት ናቸው የሚለውን ነው፡፡ይህን መሰረታዊ ነገር ጨርሰው እንዳልረሱ የሚያሳየው ደግሞ ጥያቄዎቹን በግልፅ ሲያስቀምጡ አለመታየቱ ነው፡፡ይልቅስ እነዚህን ልባቸውን የሞሉ ጥያቄዎች ሌላ ስም ሰጥተው ነው የሚያቀርቧቸው፡፡”ኦሮሞ የበለጠ ስለታገለ የበለጠ ይግዛ” የሚለውን የልባቸውን ጥያቄ “የኦሮሞ ህዝብ ትግል ተካደ” የሚል የኮድ ስም ሰጥተውታል፡፡በኦሮሚያ ክልል ኦሮሞ ማየት ያለመፈለግ መጤ ጠል ጥያቄያቸውን “የኦሮሞ ህዝብ የሃገር ባለቤትነት ጥያቄ” በሚል የአደባባይ ስም ይጠሩታል፡፡አዲስ አበባን በጨፌ ኦሮሚያ ስር የማስገባቱን ኢ-ህገመግስታዊ፣ኢዲሞክራሲያዊ የጉልበተኝት ጥያቄያቸውን “በአዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም አለን” የሚል የዳቦ ስም ሰጥተውታል፡፡ስሙን ለመጥራት ራሳቸውም የሚሽኮረመሙበት ጥያቄ እንዴት ሆኖ እውን እንደሚሆን ጊዜ የሚፈታው ይሆናል፡፡ 

ማስታወሻበዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።                                       

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here