spot_img
Sunday, July 21, 2024
Homeነፃ አስተያየትያልነበረን ፌደራሊዝም ሕወሃት እንዴት ሊያድን ይችላል? (ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ)

ያልነበረን ፌደራሊዝም ሕወሃት እንዴት ሊያድን ይችላል? (ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ)

ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ፤
ታህሳስ 25 ቀን 2012 (01/04/2020)

“እውነት እንደ ፀሃይ ናት። ለጊዜው ልትሸፍናት ትችላለህ፤ ግን የትም አትሄድም” ይላል እውቁ ዘፋኝ ኢልቪስ ፕሬስሊ። በሃገራችን የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ፤ ከጀሌ እስከ መሪ፤ ሃሰት ሲናገር እና፤ ለሃሰት ቆሞ ሽንጡን ይዞ ሲከራከር አይተናል። የሌባ ዓይነ ደረቅ ከዓይን ላይ ኩል ይሰርቃል እንደሚባለው፤ የምናውቀውን ሃቅ እንደማናውቅ፤ ይልቅም ሃሰቱ እውነት መስሎ እንዲቀርብ ብዙ ተሰርቷል። በሃስት የታሪክ ፈብራኪዎች በሚፃፉ ብርዝ ታሪኮች፤ ብዙ ሕይወት ሲጠፋ፤ ብዙ ንብረትም ሲወድም አይተናል። “ፖለቲከኛ ወኃ በሌለበት፤ መርከብ አስመጣለሁ ይላል” የሚል የፈረንጆች  ቀልድ አለ። ለዚህም ነው “የልጅ የሽንት ጨርቅ እና ፖለቲከኛ፤ ሲቆይ አስቸጋሪ እና ጥዩፍ ጠረን ስለሚያመጣ፤ በየጊዜው መቀየር አለባቸው” የሚባለው።

         ሕወሃት በኢትዮጵያ በንግስና በኖረበት 27 ዓመታት ውስጥ፤ ልንገምት የማንችላቸው፤ እንደ ሃገር ለዘመናት የምንሸማቀቅባቸው ብዙ ግፎች ተፈጽመዋል። ብዙ ግፎች የተፈፀሙት ደግሞ በሕግ ሽፋን ለመሆሙ፤ ፀሃይ የሞቀው ሃቅ ነው። ምንም እንኳን ሕወሃት ራሱ ጽፎ ባፀደቀው ሕገ መንግሥት፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ብሔር ብሔረሰቦች ራሳቸውን ማስተዳደር የሚችሉበት የፌደራሊዝም ስርዓት አዋቅርያለሁ ቢልም፤ በተለይ በሕወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ መጋቢት 1993 ክፍፍል፤ ተዋቀረ የተባለለት የፌደራል ስርዓት ሃሰት እንደሆነ በገሃድ አጋልጧል፡፡ በመጋቢት 1993 የህወሃት ክፍፍል አንዱ የተማርነው ነገር፤ በእያንዳንዱ የክልል ፕሬዝዳንት ጀርባ፤ አንድ የሕወሃት ባለሥልጣን ተመድቦለት፤ ፕሬዝዳንቶቹ፤ የሕወሃት አሻንጉሊት ሆነው፤ የሕወሃትን መሪዎች ፍላጎት እና ዓላማ ከማስፈጸም ውጭ፤ ቆመንለታል ለሚሉት ብሔር ብሔረሰብ ምንም የፈየዱለት ነገር እንዳልነበረ ነው፡፡

         የዚህ አመራ ዓይን ያወጣ፤ ሕገ ወጥነት በገሃድ ሲጋለጥ፤ ሕወሃት፤ ስልቱን በመቀየር፤ በእያንዳንዱ ክልል ጉዳይ ጣልቃ የሚገባበትን እና፤ የየክልሉን አመራሮች እንደፈለገ የሚዘውርበትን የፊደራል ጉዳዮች ሚኒስትር የሚል መሥርያ ቤት አቋቋሞ አቶ አባይ ፀሃዬን፤ የመስሪያ ቤቱ ሚኒስቴር አድርጎ ሾማቸው። ይህ ሕወሃት፤ ለሕገ ወጥነት ሥራው፤ የተጠቀመበት “ሕጋዊ ጭምብል” ነበር፡፡ ህወሃት ሙሉ በሙሉ ሲቆጣጠረው በነበረ ሃገር ውስጥ፤ ሕገ መንግሥቱን በመጣስ፤ በፈለገው ክልል፤ ያለማንም ጥሪ እና የክልል አስተዳደር ፈቃድ፤ እንደፈለገ እየገባ፤ ፖሊሲ ሲነድፍ፤ ዜጎችን ሲያስር፤ ሲደበደ፤ እና ሲገድል፤ የፌደራሊዝም ስርዓቱ አውቃቀር ቆርቁሮት አያውቅም። በተደጋጋሚ በተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎች እንደተነገርው፤ በሕወሃት የግፍ አገዛዝ ሥር፤ ምንም ዓይነት እውነተኛ የፌደራል ሥርዓት ኖሮ አያውቅም። ዛሬ ከሕወሃት ጋር የሚሞዳሞዱት እንደ አቶ በቀለ ገርባ ዓይነት፤ የከሰሩ ፖለቲከኞች፤ ይህንን ሃቅ በአደባባይ ሲናገሩ ቆይተዋል። ዛሬ ግን መልሰው ይህን ለማየት አይፈልጉም።

         በእያንዳንዱ ክልል፤ የተቀመጡት ፕሬዝዳንት ተብየዎች፤ በሞግዚትነት የተመደቡላቸውን የህወሃት ባለሥልጣናት ፈቃድ ከመሙላት ውጪ፤ ምንም ዓይነት ሥልጣን እንዳልነበራቸው፤ በግልጽ ተናግረዋል። ዛሬ በእስር ቤት ሆነው የፍርድ ጊዜያቸውን የሚጠባበቁት የቀድሞ የሱማሌ ክልል ፕሬዝዳንት፤ በቀድሞው የድህንነት ሹም በጌታቸው አሰፋ ግንባራቸው ላይ ሽጉጥ እየተደቀነባቸው፤ የሕወሃትን ፍላጎት ያሳኩ እንደነበር በአደባባይ ተናግረዋል። ታድያ ያኔ ምነው ከሕወሃት አመራሮች መካክል አንድ እንኳን ብርታት አግኝቶ፤ ሕገ መንግሥቱ ተጣሰ፤ የፌደራል ሥርዓቱም ተጣሰ ሲል አልሰማን?

         ሕወሃት፤ “የፌደራል ሥርዓት መሥርቻለሁ” እያለ የሚኩራራበት ሕገ መንግስት፤ በህወሃት አገዛዝ በሥራ ላይ ውሎ እንደማያውቅ፤ ብዙ የተባለለት ነው፡፡ አላማውም የኢትዮጵያን ሕዝብም ሆነ ማንንም ብሔርም ሆነ ብሄረስብ ለመጥቀም የተቀመረ አልነበረም፡፡ ዓላማው፤ ሕወሃት፤ ከፌደራል ሥርዓቱ የሥልጣን ማማ ላይ ሲወድቅ፤ ትግራይ ውስጥ መሽጎ ንግስናውን ትግራይ ውስጥ ለመቀጠል ነበር፤ አሁንም የምናየው ይህንኑ እውነታ ነው፡፡ ሕወሃት፤ የትግራይን ወጣት ለሥልጣን መወጣጫ አደረገው እንጂ፤ በአንድም ወቅት አስቦ እና ወጥኖ ለትግራይ ሕዝብ ጥቅም የሰራበት ጊዜ አለ ብሎ ለመከራከር የሚያስችል መረጃ የለም፡፡ መረጃ ያለው በመረጃ ይሟገት፡፡ ህወሃት፤ የትግራይን ሕዝብ ተጠቀመበት እንጂ፤ ለትግራይ ሕዝብ አልጠቀመም፡፡ ዛሬም፤ በማያወላዳ ሁኔታ፤ ትግራይ ውስጥ ማንም የህወሃትን ንግስና ሊፈነቅል እንደማይችል፤ የሚቃወሙትን የትግራይ ወጣት ጀግኖች፤ “የመጀመርያ” ጠላት ብሎ ፈርጆ፤ ኢዲሞክራሲያዊ ዘመቻውን በእነዚሁ የትግራይ የቁርጥ ቀን ልጆች ለመጀመር መወሰኑን በአደባባይ ደስኩሯል፡፡

         ይህ በቤተሰብ፤ በጓደኝነት እና፤ በአውራጃ ልጅነት የተጠፈነገው፤ የወንጀለኛ የአመራር ቡድን፤ በትግራይ ሕዝብ ላይ የፈፀመው እና እየፈፀመ ያለውን ክህደት እና ወንጀል ሙሉ ለሙሉ አናውቀውም። እውነቱ ገሃድ ሲሆን ግን፤ ምን ያክል ልብ ሰባሪ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም። ከጥቂት ወራት በፊት፤ ከተለያዩ የዓለም መዓዘናት በመቀሌ ተሰብሰበው የነበሩ የትግራይ ምሁራን፤ አንዱ የተሰማሙበት ነገር፤ ሕወሃት በትግራይ ውስጥ የፖለቲካ መድረኩን እንዲያሰፋ እና፤ ሌሎችንም አሳታፊ ማድረግ እንዳለበት በማያሻማ ሁኔታ ገልጾ ነበር። ሆኖም፤ የሕወሃት መሪ ዶ/ር ደብረጽየን፤ ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ፤ በትግራይ ውስጥ ምንም ዓይነት ሕወሃትን የሚቃወም እንቅስቃሴ እንደማይፈቀድ፤ በማስረገጥ ገልፀዋል። ይህ፤ የትግራይ ሴቶችን አስገድዶ ለሚደፍሩ የሕወሃት ባለሥልጣናት ከለላ የሚሰጥ፤ ጨካኝ አመራር፤ ከራሱ አመራሮች ጥቅም በፊት የትግራይ ሕዝብን ጥቅም ያስቀድማል ብሎ መጠበቅ፤ አባይን በማንኪያ ጨልፎ ለመጨረስ የመመኘትን ያክል ነው።

         ታድያ ሙሉ ለሙሉ በሚቆጣጠረው ክልል ውስጥ፤ ፍፁም አምባገነናዊ የሆነ ሥርዓት የመሰረትን ድርጅት፤ ለሌላው ብሔር ብሄረሰብ ይቆረቆራል ብሎ ማሰብ እንዴት ይቻላል? ለ27 ዓመታት በተቆጣጠረው በትረ መንግስት ሥር፤ ያላከበረውን የፌደራሊዝም ስራዓት፤ ዛሬ ከሥልጣን ማማው ላይ በውርደት ከወደቀ በኋላስ እንዴት ነው ላድነው ብሎ፤ የመናገር ሞራል ሊኖረው የሚችለው? ሕወሃት ሲያነጥስ፤ መሃረብ ሲያቀርቡለት የነበሩ እና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ይህ ነው የሚባል ሚና የሌላቸው እና ያልነበራቸው አበል ተከፋይ “አጋሮቹስ”፤ ትላንት የፌደራል ሥርዓት ተብዬው ሲጣስ የት ነበሩ? እነዚህ እና መሰል ጥያቄዎች መልስ ማግኘት አለባቸው፡፡

         የሕወሃት፤ ይህ የሃሰት “የፌደራል ሥርዓቱን አድናለሁ” የሚል ትርከት አላማው አንድ እና አንድ ብቻ ነው፡፡ ትላንት ያልነበረውን የፌደራል ሥርዓት፤ ምኑን እንደሚያድነውም ግልጽ አይደለም። አንድ ነገር ግን ግልጽ ነው። ሕወሃት በሥልጣን በቆየባቸው ዓመታት ሁሉ፤ እኔ ከሌለሁ “አያ ጅቦ ይመጣል” የሚለውን የሃገር ትፈርሳለች ሰበካውን እውን ለማድረግ፤ የሚያደርገው የሞት እና የሕይወት ጣር ነው። የሕወሃት አመራር፤ ፌደራሊዝምን አድናለሁ በሚል ሰበብም ሆነ፤ ለሕዝብ ተቆርቋሪ የሚመስል ካባ በመደረብ፤ እየፈጠረ ያለው ትርምስ፤ ወደ ነበርበት ሥልጣን ሊመልሰው እንደማይችል ሊገነዘብ ይገባል፡፡ የህወሃትን አገዛዝ ኖርንበታል፤ ተገርፈንበታል፤ ተሰደንበታል፤ አሰቃቂ የስቃይ ገፈት ቀምሰንበታል፤ ከዛም አልፎ ሞተንበታል። ያንን፤ የስቃይ፤ የስደት እና፤ የሞት ዘመን የሚመኝ ካለ፤ አሳዳጅ፤ ገዳይ እና ጥቅሙ የቀረበት አረመኔ ብቻ ነው። ህወሃት እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ወደሚለው የአህያነት አስተሳሰብ ተሸጋግሮ የለኮሰው እሳት፤ ቀድሞ እሱኑ አንድዶ እንደሚጨርሰው ከታሪክ መማር አለበት። በርካታ መረጃዎች እንድሚያሳዩትም፤ የተለያዩ፤ ስግብግብ እና ዓላማ ቢስ ዜጎችን በተለያዩ ክልሎች በመመልመል፤ የሕወሃት አመራሮች በሃገር ውስጥ ከፍተኛ የብሔር ተኮር እና የሃይማኖት ግጭት በመፍጠር በብዙ ሰዎች ሕይወት እና ንብረት ላይ የፖለቲካ ቁማራቸውን የሚጫወቱትም፤ “ሕወሃት ይሻለናል” ነበር የሚል እሳቤ እንፈጥራለን በሚል የሞኝ ቅዠት ነው፡፡ ዛሬ በሥልጣን ላይ ያለው ሃይል መስመሩን ስቶ፤ ሃገሪቱን ወደ ደም ባሕር እንዲቀይር ከፍተኛ ፈታኝ ትንኮሳ እየተደረገ ነው። ብዙዎች፤ ሂደቱን ሳንረዳ፤ መንግሥት፤ በፊት ጥለነው ወደመጣንበት ግድያ እና ግፍ እንዲመለስ ግፊት እናድርጋለን። ወደ በፊቱ አካሄዳችን ከተመለስን ግን መጨረሻው ምን ሊሆን ይችላል ብለን አንጠይቅም።

         የለውጡ ጉዞ ከተጀመረ ጀምሮ፤ ሕወሃት በተደጋጋሚ፤ ሕገ መንግስቱን ከፍ አድርጎ በማውለብለብ፤ ሕግ ተጣሰ ሲል፤ ደጋፊዎቹም ሆነ አባላቱ፤ እስቲ መጀመርያ እናንተ ሕግ አክብሩ ሲሉ አይደመጡም። ትላንት የአረና ትግራይ አባላት በጠላትነት ተፈርጀው፤ ካለሕግ ሲደበድቡ፤ ሲታሰሩ፤ ከተከራዩት ቤት እንዲባረሩ ሲደረጉ፤ ማነው ትግራይ ውስጥ ስለሕግ የበላይነት ሲጠይቅ የሰማነው? ትግራይ ውስጥ የመናገር፤ የመፃፍም ሆነ የመሰብሰብ መብት እንዲሁም የፕረስ ነፃነት ሲገፈፍ፤ የይትኛው የህወሃት አመራር ነው፤ ሕገ መንግሥት ተጥሷል ሲል የሰማነው? ምንም እንኳን ውሸት ተደጋግሞ ሲነገር እውነት ይመስላል ቢባልም፤ የህወሃት ውሽት ከመደጋገሙ ብዛት፤ የመጎምዘዝ ደረጃ ላይ ደረሰ እንጂ፤ ምንም ዓይነት አመኔታ ሊፈጥር አልጋለም አይችልምም፡፡ “አሳማ ላይ ሊፕስቲክ ብታደርግበት፤ አሳማነቱን አይቀይርም፤” ይባላል፡፡ የሕወሃት አመራር በሥልጣን ዘመኑ፤ የአሳማነት ባህሪውን ለመቀየር፤ ‘እራሴን ገምግሜ ማስተካከያ አደርግያለሁ’ ብሎ፤ በተደጋጋሚ ሊፕስቲክ ውስጥ ቢነከርም፤ እራሱን ግን ከአሳማነት ሊቀይር አልቻለም፡፡ የቀድሞው የሕወሃት ሊቀመንበር፤ አቶ መለስ ዜናዊ፤ እንዳሉት፤ ሕወሃት ከአናቱ ጀምሮ በስብሷል፤ ሊታረምም፤ ሊማርም የሚችል አይደለም፡፡ አንዳንዶቻችን፤ ይህ የወንጀለኞች ጥርቅም፤ እራሱን ከወንጀለኞች አጽድቶ፤ አመራሩንም በወጣት እና በበሳል መሪዎች ተክቶ፤ የጥፋት መልዕክተኛ መሆኑን ትቶ ሃገርን ወደ መገንባት ሥራ ይቀየራል የሚል ተስፋ ነበረን። ነገር ግን፤ ሕወሃት ባለፈው ሳምንት በመቀሌ የነበረውን ስብስባ አጠናቆ በሰጠው መግለጫ፤ ጋዜጠኛ አብርሃ በላይ ከዓመታት በፊት እንዳለው፤ ሕወሃት በምንም መልኩ ሊታደስ የሚችል ድርጅት አለመሆኑን አረጋግጧል።

         ለዚህም ነው የህወሃት አመራር፤ ለትግራይ ሕዝብ እና ለተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚበጅ ስራ ላይ ከመወጠር ይልቅ፤ በስብሰባ እና በመግለጫ ጋጋታ ታጅቦ፤ በሞት ጣር ላይ ያለውን የሕወሃት አመራር ለማዳን የሚወራጨው። የሕወሃት አመራር በመጨረሻ የሞት ጣሩ፤ በፖለቲካ አካሄዳቸው በከሰሩ፤ በሃሰት ትርከት ከተወጠሩ የተማሩ መሃይማን ብብት ውስጥ ገብቶ፤ በእነዚህ ድኩማን ሳንባ ለመተንፈስ ቀና ደፋም የሚለው። በባርነት አስተሳሰብ ተገርፎ፤ በሃሳብ የመከነ ባርያ፤ ጌታው ሲያጎነብስ በእንብርክኩ እንደሚሄድ ሁሉ፤ በባርነት አስተሳሰብ የሚዳክሩት፤ እንደ ፀጋዬ አራርሳ እና በቀለ ገርባ አይነት ሰዎች፤ የሕወሃት አመራሮች ሲያጎነብሱ፤ እነሱም ተንበርክከው መሄዳቸው፤ ማንንም ሊያስገርም አይገባም። ሕወሃት ያልነበረውን የፌደራል ስርዓት አድናለሁ ብሎ ሲያጓራ፤ ‘የት የነበረን የፌደራል ስርዓት ነው የምታድኑት ብሎ’ ከመጠየቅ ይልቅ፤ የአስተሳሰብ ድንክዬ የሆኑ ፖለቲከኞች፤ በሃስት ትርከት፤ በአዳራሽ ጭብጨባ ሰክረው፤ አብረው ቢያጓሩ፤ ሊደብቁ የሚሞክሩት እውነት፤ ቦግ ብሎ የሚታይ በመሆኑ፤ ከጥቂት ጊዜ ብኋላ፤ እነሱም፤ በሌሎች ሳንባ ለመተንፈስ ሲንፈራገጡ እናያቸዋለን። እውነት ትቀጥን እንደሆነ እንጂ አትሰበርም፤ ሕወሃትም ያልነበረ የፌደራል ሥርዓትን ሊያድን አይችልም። ይልቅስ፤ ሙሉ በሙሉ እስትንፋሱን እና የሚተነፍስበትን የውሰት ሳንባ አጥቶ፤ ወደ መቃብሩ ከመውረዱ በፊት፤ እራሱን ያስተካክል፤ አመራሩን ከወንጀለኞች ያፅዳ፤ ከ45 ዓመታት በላይ በሥልጣን የቆዩትን አዛውንት መሪዎች ያሰናብት፤ እራሱን በዲሞክራሲያዊ አደረጃጀት እና አስተሳሰብ ያንጽ፤ ያ ሲሆን ብቻ ነው ፤ ህወሃት እንደ ድርጅት፤ ለትግራይም ህዝብም ሆነ ለተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚጠቅም ነገር ሊሰራ እና፤ ለኢትዮጵያ ሕዳሴ እና ብልጽግና አስተዋጽኦ ሊያደርግ የሚችለው።

ቸሩ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ይባርክ።    

 ማስታወሻበዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here