አክሎግ ቢራራ -ዶር
ታህሳስ 30 2012 ዓ ም
እትዮጵያና የእርዳታ ታሪኳ
ኢትዮጵያ የጣልያንን ፋሽስት ኃይል እንደገና አሸንፋ ነጻነቷን ከተጎናጸፈች በኋላ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አጋር የነበረችው ዩናይትድ ኪንግደም ለኢትዮጵያ እርዳታ መስጠት ጀመረች። እንግሊዝ እርዳታዋን በ 1952 አቋረጠች፤ አሜሪካ ተካቻት።
ከ 1950-1970 ባለው ጊዜ መካከል ኢትዮጵያ ከአሜሪካ፤ ከዓለም ባንክና ከሌሎች ለጋሶች ያገኘችው የእርዳታ መጠን $600 ሚሊየን ይገመታል። አንድ ሶስተኛ የሚሆነውን የለገሱት አሜሪካኖች ናቸው። የሶቭየት ህብረት $100 ሚሊየን፤ ዓለም ባንክ $121 ሚሊየን ለግሰዋል። የእርዳታው መጠን በዓመት ሶስት ሚሊየን ዶላር ይገመታል።
ኢትዮጵያ የግል የብድር አገልግሎት የሚሰጠው የ International Finance Corporation (IFC) አባል የሆነችው በ 1956 ሲሆን በዝቅተኛ ወለድ እስከ አርባ ዓመት ድረስ የሚከፈል ብድር ወይንም የማይከፈል ድጎማ የሚሰጠው የ International Development Association (IDA) አባል የሆነችው በ1961 ነው። ስለሆነም፤ በሁለቱም መንገዶች እርዳታ የምታገኝበት መንገድ አለ።
እርዳታ ሲባል በገንዘብ ብቻ የሚሰጠው አይደለም። ስዊድን የንጉሱን ክቡር ዘበኛ አሰልጥናለች። ህንድ ለኢትዮጵያዊያን የከፍተኛ ትምህርት አገልግሎትና ድጋፍ ሰጥታለች፤ አስተማሪዎች ወደ ኢትዮጵያ ልካለች። በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አንዱ አስተማሪየ ህንድ ነበር። በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አብዛኛዎቹ አስተማሪዎቸ “የሰላም ልኡካን” ተብለው የሚጠሩ አሜሪካኖች ነበሩ። አሜሪካ ብዙዎቹን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ደግፋለች፤ የትምህርት እድል ሰጥታለች።
በደርግ መንግሥት የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ተለውጦ፤ አገሪቱ አብዛኛውን ድጋፍ ታገኝ የነበረው ከሶቭየት ህብረት አገሮች ነበር፤ ከምስራቅ ጀርመን፤ ከቸኮስሎቫክያ፤ ከራሽያና ከሌሎች፤ የመንንና የኩባን ድጋፍ ጨምሮ። እርዳታው መሳሪያና ስልጠናን ያካተተ ስለሆነ በገንዘብ አልተተመነም። ግን ግዙፍ ነው። ብዙ ሽህ ኢትዮጵያዊያን በሶቭየት ህብረት የትምህርት እድል አግኝተዋል። የሶቭየት ህብረት አገሮች አብዛኛዎቹን የደርግ ካድሬዎች አሰልጥነዋል። በልዩ ልዩ የሳይንስና የቴክኖሎጅ ትምህርት ለተሳተፉ ኢትዮጵያዊያን እድል ሰጥተዋል። በገንዘብ ቢተመን ኖሮ ግዙፍ ነው። በቀውጢ ቀን ለኢትዮጵያ ድጋፍ የሰጡትን ወዳጆቻችን ባንረሳቸው መልካም ነው።
ትምህርትና እውቀት የስልጣኔ መሰረት ስለሆነ፤ በዚህ ዘርፍ ለኢትዮጵያዊያን እርዳታ የሰጡ አገሮች ሁሉ የገንዘብ ድጎማና ብድር ከሰጡት የበለጠ ሊመሰገኑ ይገባቸዋል። ምክንያቱም፤ ትምህርትና እውቀት አይሰረቅም፤ አይነጠቅም። አንድ አባባል አለ። “አንድን ሰው አሳ ብትመግበው፤ ለአንድ ቀን ብቻ” ትረዳዋለህ። “ይህን ሰው አሳ እንዴት እነሚያጠምድ ወይንም እንደሚይዝ ብታስተምረው ግን ህይወቱን ሙሉ ትመግበዋለህ።” ትምህርት ድህነትን ለመቅረፍ ወሳኝ ነው።
ታዳሚው እንዲያጤነው የፈልግሁት፤ በደርግ መንግሥት አሜሪካኖችና ዓለም ባንክ፤ አይ ኤም ኤፍ እርዳታቸውን አቁመው ነበር ። እርዳታው የቀጠለው ለተራቡ ወገኖቻችን የምግብ ድጋፍ በመስጠት ዙሪያ ነው፡፡
በአጭሩ ለማለት የምፈልገው እርዳታና የውጭ ግንኙነት ወይንም ፖለቲካ የተያያዙ መሆናቸውን ነው። የደርግ መንግሥት ከወደቀ በኋላ የምእራብ አገሮች ለኢትዮጵያ መንግሥት የሚሰጡት እርዳታ እየጨመረ ሄዷል። በዚህም መሰረት ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው የእርዳታ መጠን ከፍ እያለ ሄዷል። እዳው እየጨምረ የሄደበት ዋና ምክንያት ለዚህ ነው።
ኢትዮጵያ እርዳታውን፤ ድጎማውን፤ ብድሩን ለልማትና የስራ እድል ለመፍጠር ብትጠቀምበት ኖሮ ችግር ወራሽ፤ እዳ ተሸካሚ እና እዳን ለመክፈል ሌላ የውጭ ምንዛሬ ተበዳሪና ለተከታታይ ትውልድ የእዳ ሸክም አሸጋጋሪ አገር ባልሆነችም ነበር። ሌብነቱ፤ ምዝበራው፤ ሙስናው፤ ግዙፍ ኃብት እየተሸሸገ ከአገር መሸሹ ሁኔታውን አባብሶታል።
ይህን ሃተታ ግልጽ ለማድረግ በአምስት መሰረታዊ ሃሳቦች ዙሪያ እከፍለዋለሁ፤
አንድ፤ ብድርና እዳ አዲስ ነው ወይንስ የቆየና የተወረሰ ክስተት?
ብድር፤ ድጎማና እዳ የቆየና ተከታታይ ታሪክ አለው፤
- ከታች በመረጃ እንዳሳየሁት፤ ህወሓት መራሹ “ፈጣን እድገት” ለማሳየት የቻለበት ዋና ምክንያት ለጋስ አገሮችና አበዳሪ ድርጅቶች ግዙፍ ድጎማና ብድር ስለሰጡ ነው፤
- የኢትዮጵያ ሕዝብ ገቢ ዝቅተኛ ስለሆነ፤ ከታክስና ከቀረጥ የሚገኘው ገቢ ከካፒታል ባጀቱ ፍላጎት ጋር ሊመጣጠን ስለማይችል፤ ለእድገቱ ወሳኝ ግብአት የሆነው እርዳታው (Foreign aid) ነው፤
- እድገቱ የተካሄደው በድጎማ ነው፤—ለምሳሌ መሰረተ ልማት፤ ግድቦች፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፤ ስታዲየሞች፤ የሃዲድ ስራዎች፤ ህንጻዎች፤ መሰብሰቢያ አዳራሾች ወዘተ፤
- የግሉ ክፍል ሳይሆን፤ የፓርቲ፤ የፌደራልና የክልል መንግሥታት፤ ከገዢው ፓርቲ ጋር የተቆራኙ ኩባንያዎችና የግል ተቋማት የውጭ ምንዛሬውን ይሻሙት ነበር፤
- የረባና ሃላፊነት የሚያሳይ ተቆጣጣሪ ድርጅት ወይንም ተቋም አልነበረም፤
- እጂግ በሚዘገንን ደረጃና በተከታታይ የውጭ ምንዛሬው ተሰርቅቋል፤ ከአገርና ከሕዝብ ሸሽቷል፤
- የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ መዋቅር አልተቀየረም፤ ኢንዱስትሪ አልተሳፋፋም፤ የገጠሩ ኢኮኖሚ ዘመናዊ አልሆነም።
ሁለት፤ ብድር ለምን አስፈለገ?
- ማንኛውም ድሃና ኋላ ቀር አገር ብድር ያስፈልገዋል፤
- ኢንዱስትሪውን ለመስራትና ለማስፋፋት መሳሪያ ክውጭ መሸመት አለበት፤
- የገጠሩን ኢኮኖሚ ዘመናዊ ለማድረግ መሰረተ ልማት መስፋፋት አለበት፤
- የተገዛው መሳሪያ ለምርት ካልዋለ ግን፤ የሚከብረው ኮሚሺን የሚያገኘውን አካልና ሻጩን ይሆናል፤
- ድጎማና ብድር የሚሰጠው ተደጓሚው ወይንም ተበዳሪው አገር ራሱን ችሎ ከብድር ነጻ እንዲወጣ ነው፤
- ለምሳሌ፤ ደቡብ ኮሪያና ሌሎች የምስራቅ ኤዢያ አገሮች ለጥቂት አመታት ብቻ፤ በአማካይ ከሰላሳ ዓመታት በታች ባለ ወቅት፤ ድጎማና ብድር አግኝተው የራሳቸውን ኢኮኖሚ ዘመናዊ ለማድረግ ችለዋል፤
- ድጎማንና ብድርን በሃላፊነት የመጠቀም ግዴታው የተጠቃሚው ወይንም የተበዳሪው አገር እንጅ የደጓሚው ወይንም የአበዳሪው አይደለም፤
- ጥናቶች የሚያሳዩት አበዳሪዎች የኢትዮጵያ ብድር “እንዲቀንስ የሚፈልጉ አይመስልም” የሚል ነው። ምክንያቱም፤ የራሳቸው ጥቅም ጥገኝነትን ይጠይቃል፤ ተበዳሪ ከሌለ አበዳሪ አይኖርም፤
- የምእራብ አገሮች፤ ዓለም ባንክ፤ አይኤም ኤፍ፤ ሳውዲ አረብያ፤ ኩዌይት፤ ቻይናና ሌሎች አበዳሪዎች የራሳቸው የዲፕሎማሲ፤ የራሳቸው መርህና ስትራተጂ፤ የራሳቸው የንግድና የገቢ ፍላጎት አላቸው፤
- ስለሆነም፤ እያንዳንዱ ተበዳሪ አገር የራሱ የልማት ፍላጎት እንዲሟላ ከፈለገ ብሄራዊ ግዴታውን መወጣት አለበት።
ሶስት፤ ብድሩና እዳው ምን ፋይዳ አለው?
- ላወቀበት ድጎማውና ብድሩ ማህበረሰባዊና ብሄራዊ ጥቅም እንዲኖረው እያንዳንዱ ዶላር ምርትን ለማሳደግ፤ የስራ እድልን ለመፍጠርና የልማት መሰረቱ ስር እንዲሰድ ሊያደርግ ይችላል፤ ደቡብ ኮሪያ እንዳደረገችው፤
- ባለሞያውች የሚሉት እያንዳንዱ ዶላር እንዳይባክን፤ እንዳይሰረቅ፤ ኢንዱስትሪዎችን እንዲያሥፋፋና ለልማት እንዲውል ከተደረገ የሚያስገኘው ጥቅም ከአራት እስከ አምስት እጅ አያንስም፤ ከባከነ ግን ዜሮ በዜሮ ነው፤
- እንዲያውም፤ ብድሩ መከፈል ስላለበት፤ እዳው ለተከታታይ ትውልድ ሸክም ይሆናል የሚባለው ለዚህ ነው፤
- ብድሩ ሳይከፈል ቀርቶ እዳው እየጨመረ፤ እዳውን ለመክፈል ሌላ ብድር ከተጨመረበት፤ ችግሩ ይባባሳል፤
- አብዛኛው የኢትዮጵያ ብድር በልዩ ልዩ ዘዴ “በቀን ጅቦች፤ በሙሰኞች፤ አሁንም እንደ በፊቱ የእኛ ተራ ነው” ባዮች ከተሰረቀ፤ በተለይ፤ ከአገር ከሸሸ ብድርና እዳው ተደማምሮ ጥገኝነትን ያስከትላል፤
- እዳ በእዳ ሲተካ፤ የእርስ በእርስ ግጭት፤ ጽንፈኝነት፤ አገር ወለድ ሽብርተኝነት፤ የሞራል ውድቀት ያስከትላል፤ የዋጋ ግሽፈት አይቀርም፤
- የእዳ ሸክም ለኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶች ወንፊቶች ይፈጥራል፤ ወጣቱ ትውልድ በራሱ መንግሥት ላይ የሚኖረው እምነት እየቀነሰ ይሄዳል፤ ተቃውሞ ይባባሳል።
አራት፤ ኢትዮጵያ ምን ታድርግ?
- የኢትዮጵያ መንግሥት ካለፈው የማፍያ-አይነት ድርጅታዊ ምዝበራ ታሪክ መማር አለበት። “የቀን ጅቦች” ማለቱ ብቻ መርህ ሊሆን አይችልም። አዲስና ተተኪ “ጅቦች” የአገሪቱን ባጀት፤ በተለይ የውጭ ምንዛሬውን እንዳያባክኑት ጠንካራ፤ ነጻና ብሄራዊ ተቆጣጣሪ ተቋማት ያስፈልጋሉ፤
- ኢትዮጵያን በብድርና በውጭ ድጎማ ተማምኖ ህብረተሰቧን ዘመናዊ ለማድረግ አይቻልም፤
- የወቅቱን የተወረሰ የውጭ ምንዛሬ ተግዳሮት ለመወጣት መበደር አማራጭ ነው ከተባለ፤ እኔ አማራጭ አይመስለኝም፤ ኢትዮጵያ የራሷን ብሄራዊ ጥቅም ማስቀደም አለባት፤
- ማንኛውም ብድርና ድጎማ የአገሪቱን የማምረትና ስራ የመፍጠር አቅም ማጠናከር መስፈርት ማንጸባረቅ አለበት፤
- የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም ባንክ፤ ከአፍሪካ ልማት ባንክ እና ከአይ ኤም ኤፍ የተበደረችው እዳ ሁሉ እንዲሰረዝላት ድርድር መጀመር አለባት፤ ትችላለች፤
- ጥናቶች የሚያሳዩት፤ ከአፍሪካ አገሮች መካከል ግማሾቹ የውጭ ብድር እዳቸው እየጨመረ ሄዶ፤ ከጠቅላላ ገቢያቸው 50 በመቶ አልፏል፤ የኢትዮጵያ ዛሬ 60 በመቶ ደርሷል፤ ዘላቂነት የለውም፤ ሸክም ነው፤
- የአፍሪካ አገሮች ጠቅላላ የእዳ መጠን በ 2017, $417 ቢሊየን አልፏል፤ የኢትዮጵያ “በዝቅተኛ $30 ቢሊየን፤ በከፍተኛ $53 ቢሊየን ደርሷል” ይባላል፤
- ከጥቂት አመታት በፊት የአይ ኤም ኤፍ የበላይ ሃላፊ አዲስ አበባ ሄደው የኢትዮጵያ እዳ መጠን “አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል” ብለው አስጠንቅቀው ነበር፤
- ከጠቅላላው የአፍሪካ እዳ መካከል ቻይና $132 ቢሊየን የሚሆነውን የንግድ ብድር ሰጥታለች፤ እዳው ካልተከፈለ የተበዳሪውን ግዙፍና አትራፊ ኩባንያዎች የመውረስ እድል አላት፤ ቻይናዎች ሲወስዱ እየመረጡ አትራፊዎቹን ነው፤
- ቻይና ለኢትዮጵያ ያበደረችው መጠን $12 ቢሊየን ይገመታል፤ የአፍሪካን አስር በመቶ ቢሆን አያስገርምም፤
- የአፍሪካ አገሮች፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተበደሩት ግዙፍ ብድር መካከል 35 በመቶ የሚሆነውን ያበደሩት እንደ ዓለም ባንክ ያሉ ተቋማት ናቸው፤
- ሰላሳ ሁለት በመቶ (32 %) የሚገመተው ብድር የተሰጠው በግል ባለ ኃብቶች፤ ባንኮች፤ የጡሮታ ድርጂቶች ወዘተ ነው፤
- የዓለም ባንክ የአገሮችን የእዳ መጠንን ዘገባ አድርጎ የሚያሳየው መረጃ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የእዳ መጠን በ 2010 $7.3 እንደ ነበረና በአሁኑ ወቅት በአራት እጅ ወይንም አራት ጊዜ ጨምሮ $28 ቢሊየን እንደ ደረሰ ነው፤
- ከዚህ ግዙፍ ብድርና የሚከፈል እዳ መካከል፤ የዓለም ባንክ ድርሻ ለተለያዩ 35 የልማት ስራዎች (Projects) $8.36 ቢሊየን ፈሰስ አድርጓል፤
- በቅርቡ ለኢትዮጵያ ተሰጠ ከተባለው $9 ቢሊየን መካከል $3 ቢሊየን ከዓለም ባንክ፤ $2.8 ከአይ ኤም ኤፍ፤ ሌላው ከሳውዲ አረብያና ከሌሎች አገሮች ነው ተብሎ ተወርቷል፤
- ይህ ተጨማሪ ብድር ካለፈው እዳ ጋር ሲጨማመር የኢትዮጵያን የውጭ እዳ መጠን ያባብሰዋል እንጅ አይቀንሰውም፤
ለዚህ ነው፤ ከላይ እንደ ጠቀስኩት፤ ቢያንስ ቢያንስ፤ ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክና ከተመሳሳይ ድርጅቶች የተበደረችውን ብድርና እዳ ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዝላት ድርድር መጀመር አለባት ያልኩት። ይቻላል፤ ከዚህ በፊት ተደርጓል። አበዳሪዎቹ አቅም አላቸው።
አምስት፤ ብድሩና እዳው ከኢትዮጵያ ልማት አቅድ ጋር እንዴት ይዛመዳል?
የኢትዮጵያ መንግስት የልማት ራእይ እንዲህ የሚል ነው፤
“ዋናው የአገሪቱ ራእይ መሰረታዊ ዓላማ በ 2025 ኢትዮጵያን ወደ ዝቅተኛ የመካከለኛ ገቢ ያላት አገር ማሸጋገር ነው።” ይህም፤ “የህዝቡን ተሳትፎና አቅም በማጠናከር ወይንም በማጎልመስ፤ ዲሞክራሲን፤ መልካም አስተዳደርንና አገዛዝን፤ ማህበረሰባዊ ፍትሃዊነትንን” መቀዳጀትን ኢላማ ያደርጋል።
በፍጥነት የበለጸጉና በመበልጸግ ላይ የሚገኙ አገሮች—ደቡብ ኮሪያ፤ ቻይና፤ ቬትናም፤ ታይላንድ ወዘተ ኢኮኖሚዎቻቸውን ያሳደጉት ከዝቅተኛ አምራችነት ወደ ከፍተኛ አምራችነት በመለወጥ ነው። ከእርሻው ክፍል ወደ መፈብረኩ ወይንም ኢንዱስትሪው ክፍል በመሸጋገርና ለዜጎቻቸውና ለውጩ ገበያ የቁሳቁስ ምርቶችን በማምረትና በማቅረብ። ትምህርና የስራ እድል ከዚህ መዋቅራዊ ለውጥ ጋር አብሮ ይሄድና የሰራተኞች ገቢ ከፍ ይላል፤ ኑራቸው ይሻሻላል። የገጠሩ ህዝብ የተሻለ የስራና የኑሮ አማራጮች ይኖሩታል። በትንሽ መሬት ብዙ ይመረታል።
እሳክሁን የሚታየው የኢትዮጵያ እድገት፤ አብዛኛው በመንግሥትና በተመሳሳይ የግንባታ ስራና በአገልግሎት (ሆቴል፤ ምግብ ቤት) ዙሪያ የተመሰረተ ነው። የፋብሪካና የሌላው የኢንዱስትሪ ስራ ገና አልተስፋፋም። መዋቅራዊ ለውጥ የለም የሚባለው ለዚህ ነው። የፋብሪካ ስራዎችን ለማስፋፋትና የሥራ እድል ለመፍጠር እምቅ አቅም ያለው የግሉ ክፍል ገና ጫጩት ነው። አንድ የዓለም ባንክ ጥናት እንደጠቆመው፤ የኢትዮጵያ የግል ክፍል ከሌሎቹ የአፍሪካ አገሮች ጋር እንኳን ሲነጻጸር “ከአገሪቱ ጠቅላላ ገቢ የሚሸፍነው 9 በመቶውን ብቻ ነው።” የሌሎቹ የአፍሪካ አገሮች የሚሸፍነው “20 በመቶውን ነው።”
ማን ጫጩት አደረገው፤ ፓርቲውና መንግሥት። ብድሩን የሚሻሙት እነዚህ ክፍሎች ናቸው።
በተጨማሪ፤ ሌላ የማይካድ ሃቅ አለ። ይኼውም ብሄር–ተኮሩ የፌደራል ስርዓት ለልማት ማንቆ ሆኗል። ሰላምና እርጋታ የለም። ኢንቬስተሩ እንደ ልቡ ለመንቀሳቀስ አይችልም። ኢንቬትመንት ይፈርሳል።
የኢኮኖሚውን መዋቅር ለመቀየር ምን ያስፈልጋል?
- የሕግ የበላይንት፤ ሰላም፤ እርጋታና የዜጎች ደህንነት እንዲከበር ማድረግ፤
- የእትዮጵያ የዘውግ ፌደራል የፈጠረው አድሏዊይና አግላይነት ገጽታ ያለው የልማት ግብዓቶች አስተዳደር፤ ለምሳሌ፤ የፌደራል ባጀት፤ የውጭ እርዳታና ዳጎማ አመዳደብና ስርጭት እንዲስተካከልና በግልጽነት እንዲመራ ማድረግ፤
- የግሉን ክፍል የኢኮኖሚ ውድድር፤ የመፈብረክና የኢንዱስትሪ ልማት ትኩርት እንዲሰጠው በተግባር ማሳየት፤
- ጉቦን፤ ሙስናን፤ ሌብነትንና የኃብት ሽሽትን ሙሉ በሙሉ ማቆም፤
- ባለሥልጣናትና ሌሎች ኃላፊዎች ግልጽነትና ሃላፊነት የሚያንጸባርቅ ሞያተኛነት እንዲያሳዩ ማድረግ፤
- ለወጣቱ ትውልድና ለሴቶች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የስራ እድል መክፈት፤ የግል ተቋም መስርተው ስራ እንዲፈጥሩ አቅማቸውን ማጎልመስ፤ ብድር በዝቅተኛ ወለድና ያለመያዢያ (collateral) እንዲያገኙ ማመቻቸት፤
- የውጭ ምንዛሬ ምርትን ለማሳደግ፤ መዋቅሩን ለመለወጥ እንዲውል መስፈርቶች መዋጣትና ስራ ላይ ማዋል፤
- ለውጭ ምንዛሬውና ለእዳው አስቸኳይ መፍትሄ መፈለግ፤
- ለፖለቲካው አመራር ሁከትና ማነቆ የሆኑትን ተግዳሮቶች በውይይትና በድርድር በአስቸኳይ መፍታት።
እዳ ቢሰረዝ ሌላ እዳ እንዳይከሰት ምን ይደረግ? የሚለው ጥያቄ አግባባ አለው። ለዚህ መልሱ፤ ኢትዮጵያ ትኩረት ማድረግ ያለባት ከኢንቬስትመንትና ከንግድ ላይ ይሁን እላለሁ፤ ብድር ማቆም አለበት። ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ያለፈው የሰባ ዓመታት የብድር ታሪካችን ዋና ምስክር ነው። ዓለም ባንክና አይ ኤም ኤፍ የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የመላውን የጥቁር አፍሪካን ችግሮች አባብሰውታል።
ይህን ክፍል ለማጠቃለል፤ እነዚህ ተቋማት ባላቸው ዓለም አቀፍ ተሰሚነትና ተቀባይነት መሰረት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ተሰርቆ በውጭ ባንኮችና በሌሎች ተቋማት በልዩ ልዩ ስሞችና መንገዶች የተደበቀው ከአርባ ቢሊየን ዶላር በላይ የሚገመት ኃብት እንዲመለስ ዘመቻ ቢደረግ አስተዋጾ ሊያደርጉ ይችላሉ። ብድር ከመስጠት ይልቅ የኢትዮጵያ አንጡራ ኃብት እንዲመለስ ቢያደርጉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያመሰግናቸዋል። ጥሪውን የማቅረብ ዘመቻ መጀመር ያለበት በኢትዮጵያ መንግሥት ነው። ዲያስፖራው ግን በያለበት ቅስቀሳ ሊያደርግ ይችላል።
ከዚህ በታች የማቀርበው ትንተና፤ ከላይ ያቀረብኩትን መሰረተ ሃሳብ ለማብራራት ይጠቅማል የሚለውን መረጃ ነው።
በትርጉም ላይ እንስማማ። ኢትዮጵያ ከውጭ የምታገኘውን የድጋፍ አይነት መለየት አስፈላጊ ነው።
የውጭ እርዳታ ምን ማለት ነው?
የውጭ እርዳታ ማለት የውጭ መንግሥታት፤ ዓለም አቀፍና የግል ተቋማት፤ በጎ አድራጊ ድርጅቶችና ግለሰቦች ለተጠቃሚ አገሮች ወይንም የህዝብ አካላት የሚያስተላልፉት የካፒታል ጥሬ እቃ፤ መዋእለንዋይ፤ ገንዘብ፤ የጦር መሳሪያ፤ ምግብ፤ መድሃኒት፤ እውቀት፤ አገልግሎት፤ አስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፍ ማለት ነው። ይህ አጠቃላይ ትርጉም ነው። በዝርዝር ሲታይ ግን ዋና ዋናዎቹ ክፍሎች የሚከተሉት ናቸው፤
አንድ፤ በድጎማ– ያለምንም ወለድና ክፍያ የሚሰጠው ድጎማ (Grant) የሚባለው ነው፤ ድጎማው የተለያዩ መልኮች አሉት፤ ስልጠናን፤ የአቅም ግንባታን ያካትታል፤
ሁለት፤ ዓለም ባንክ ለድሃ አገሮች ለረዢም ጊዜ በዝቅተኛ ወለድ (የማስተዳደሪያ ወጭውን ብቻ የሚሸፍን) Soft loan ተብሎ የሚሰጠው ነው፤
ለምሳሌ በ October 30, 2018 ዓለም ባንክ የ $1.2 ቢሊየን ድጋፍ ሰጠ፤ $600 ሚሊየን በስጦታና $600 ሚሊየን በክሬዲት ( እስከ አርባ ዓመታት ጊዜ ወስዶ የሚከፈል)፤
የዚህ አይነቱ ድጋፍ የሚሰጠው እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ድሃ ለሆኑ አገሮች ነው፤ ይህ ከንግድ አይነቱ ብድር ይለያል፤
ሶስት፤ ብድር (Loans) ተብሎ የሚጠራው ነው፤ ለሃተታየ መሰረት የሆነው፡፡ ብድሩ በውጭ ምንዛሬ የሚከፈል ከሆነ ጣጣ ነው። ለምስሌ፤ ዓለም ባንክ ወይንም ሌላ አካል ያበደረው ብድር በውጭ ምንዛሬ መከፈል አለበት ካለ የኢትዮጵያን ብር አትሞ ለመክፈል አይቻልም። ኢትዮጵያ እዳውን ለመክፈል የውጭ ምንዛሬ ያስፈልጋታል ማለት ነው።
የውጭ ምንዛሬ ከሌላትስ?
በብድር እዳ የተበከሉ፤ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ድሃ አገሮች ታሪክ የሚያስተምረን ወይ አበዳሪዎች “ይቅር” ይላሉ ወይንም ለዚህ ችግር መፍትሄ ያቀርባሉ ተብለው የሚገመቱት ዓለም ባንክና አይ ኤም ኤፍ በጋራ ተመካክረው ችግሩን ለመፍታት ይሞክራሉ።
በዚህም መሰረት፤ ከዚህ በፊት በ 2001 ዓ.ም. ኢትዮጵያና ሌሎች በድህነትና በብድር እዳ የተበከሉ አገሮች ዓለም ባንክና አይ ኤም ኤፍ በጋራ በመሰረቱት “ከፍተኛ ብድር ያለባቸው ድሃ አገሮች” በተባለው ፕሮግራም መሰረት የኢትዮጵያ የብድር እዳ ቅነሳ ተደረገላት። ይህ የብድር እዳ ቅነሳ ከሃብታም አገሮችና እንደ ዓለም ባንክ ካሉ ዓለም አቀፍ አበዳሪ ድርጅቶች የተገኘውን የብድር እዳ ጨምሮ ነበር። ይህ ቅነሳ የተዛባውን የኢትዮጵያን የንግድ ሚዛን ለማሻሻልና የአገሪቱን የኢኮኖሜ እንቅስቃሴ ለማረጋጋት እንዲረዳ የታቀደ ነበር። አይ ኤም ኤፍ ትኩረት የሰጠው ለሚዛኑ (balance of payments ) ሲሆን ዓለም ባንክ ደግሞ ለልማቱ ነበር። ግን፤ የተሰጠው ድጋፍ መዋቅሩን አልቀየረውም።
በዚህ ወቅት በ 1999, ፤ የቀድሞው የሶቭየት ህብረት አካል የነበሩ አገሮች፤ በተለይ ሩሲያ፤ $5 ቢሊየን የተገመተ እዳ ሰርዘዋል፤ ግዙፍ እዳ። የኢትዮጵያ የውጭ እዳ መጠን በግማሽ የቀነሰው ለዚህ ነው። የምእራብ አገር አበዳሪዎች የቀነሱት $2 ቢሊየን ነው።
ከዚያ ወዲህ የኢትዮጵያ የውጭ እዳ መጠን በአይነትም፤ በስርጭትም፤ በመጠንም ከመቸውም በላይ ጨምሯል። ሙዲስ (Moody’s) የተባለው የአሜሪካው የእዳ መጠንን ገምጋሚ ድርጅት እንዲህ ብሏል። የኢትዮጵያ መንግሥት በየአመቱ ለውጭ እዳ የሚከፍለው መጠን $1.4 ቢሊየን (ከጠቅላላ የአገሪቱ ገቢ 1.8%) ሲሆን፤ ይህ መጠን ከ 2017/18 እና ከ 2020/21 ላሉት አመታት ይሆናል። www.moodys.com/research/Moodys-affirms-Ethiopias…
የንግዱ ሁኔታ አሳሳቢ ነው የሚሉ ታዛቢዎች ብዙ ናቸው። ኢትዮጵያ ከውጭ የምትሸምተው መጠን ባለፉት አስር ዓመታት በያመቱ በአማካይ 12.5% አድጓል። የወጭው መጠን በ2010 $3.6 ቢሊየን የነበረው በ 2016/2017 ወደ $14 ቢሊየን ጨምሯል። በ 2017/2018 ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የላከችው መጠን $2.84 ቢሊየን ሲሆን በተመሳሳዩ ወቅት የሸመተችው ግን $15.28 ቢሊየን ነበር። የኢኮኖሚው መዋቅር ካልተለወጠ ችግሩ ይባባሳል።
ሚዛኑ ተዛብቷል የሚለው ዘገባ የመጣውና አይ ኤም ኤፍና ዓለም ባንክ ብድር የሰጡበት መሰረታዊ ምክንያት ይኼው ነው።
እነዚህ ሁለት አበዳሪ ድርጅቶች ለብዙ ዓመታት የኢትዮጵያ የፓርቲ፤ የግልና የመንግሥት ድርጅቶች ብድር እየጨመረ ሄዷል፤ መሰረታዊ የፖሊሲና መዋቅራዊ ለውጦች ያስፈልጋሉ፤ የግሉ ክፍል ማደግ አለበት፤ ግልጽነትና ሃላፊነት ያለው የማክሮኢኮኖሚክ ፖሊሲ ያስፈልጋል ወዘተ ሲሉ ከርመዋል። በተግባር የታየ ውጤት የለም።
ኢትዮጵያ ምን ያህል እርዳታ አግኝታለች?
የኢትዮጵያ የመገናኛ ሚንስትር የነበረው ጌታቸው ረዳ ለሮይተር ሲናገር ያለው ትዝ ይለኛል። “እኛ በቀኝም በግራም እንዋሽ ነበር” ያለውን ማስታወስ ጠቃሚ ነው። በእድገትና በብድርም መጠን ተዋሽቷል። ስለዚህ ሃቁን ለማግኘት አይቻልም፤ ግን፤ ህወሓት መራሹን ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘበት ጀምሮ በኦፊሴል ደረጃ የተገኘው የእርዳታ መጠን ተጨማምሮ ሲታይ ግዙፍ ድጋፍ ተሰጥቷል።
በዝቅተኛ መጠን በ 1991 $1.7 ቢሊየን፤ ከዚያ በኋላ በየዓመቱ በአማካይ ከሁሉም ለጋሶች $3.5 ቢሊየን እስከ 2014፤ በ2015 ምርጫ ክርክር ዝቅ አለ፤ እንደገና በ2016 $ 4 ቢሊየን፤ አሜሪካ ብቻ በዚህ አመት $818 ሚሊየን ለግሳለች። በጠቅላላ ሲደመር የተለገሰው “ወደ $53.6 ቢሊየን” ይገመታል (J. Bonas, Ph.D. Economic Commentary, Special to Addis Standard, July 19, 2016። ይህ መጠን ብዙ ነው የሚሉ እንዳሉ አውቃለሁ፤ ግን የተለገሰው የውጭ ምንዛሬ መጠን በዝቅተኛ አርባ አምስት ቢሊየን ዶላር እንደነበር ከዚህ በፊት በጻፍኳቸው ትንተናዎችና ዘገባዎች በመረጃ ተደግፊ አቅርቤ ስለነበር ዶር ቦናስ ካቀረበው ዘገባ ጋር ይቀራረባል።
በተጨማሪ፤ ቻይና ከ 2000 ወዲህ ለኢትዮጵያ የሰጠችው፤ አብዛኛው የንግድ ብድር (ለሃዲድና ሌላ መሰረተ ልማት) $12 ቢሊየን አልፏል። የተሰረዘም ብድር አለ።
በአጭሩ የውጭ እርዳታ ግዙፍ ሆኖ ይታያል። እንቆቅልሽ የሆነው ጉዳይ ግን፤ ኢትዮጵያን ከድህነት አሮንቃ ነጻ አውጥቶ ራሷን የቻለች አገር ለማድረግ አልተቻለም። ለወጣቱ ትውልድ ብዙ የስራ እድል አልፈጠረም። የግሉ ክፍል አሁንም ጫጩት ነው። የእዳው መጠን እየጨመረ ሄዶ ከአገሪቱ ጠቅላላ ገቢ በ 2018 ወደ 60 በመቶ ደርሷል፤ በ 1997 ሃያ አምስት በመቶ የነበረው።
እኔን ያስጨነቅኝ ይህ ግዙፍ እርዳታ ከምርትና ከስራ እድል ፈጠራ ጋር ሊመጣጠን አለመቻሉ ነው። ማን ተጠቃሚ ሆነ የሚለውን ጥያቄ በተደጋጋሚ አቀርባለሁ። በመሬት ላይ የሚታየው ሃቅ ሌላ ነው፤ ከተገኘው ግዙፍ እርዳታ ጋር አይዛመድም።
ለምሳሌ፤ ኢትዮጵያ ሰሊጥ አምርታ ለምግብ ዘይት ብቻ በየዓመቱ $600 ሚሊየን ወጭ አድርጋ ትሸምታለች። በእርሻ የምትመካው አገር ለስንዴ በየአመቱ $700 ሚሊየን ወጭ ታደርጋለች።
የኢትዮጵያ የውጭ የብድር መጠን በትክክል አይታወቅም፤ በዝቅተኛ ግምት $30 ቢሊየን ይባላል:: አንዳንድ ተመልካቾች ወደ $53 ቢሊየን ይጠጋል ይላሉ። ሃቁ በሁለቱ መካከል ሊሆን ይችላል።
ለማጠቃለል፤ በቅርቡ የተለገሰው $9 ቢሊየን ሲጨመርበት እዳውን ማን ይከፍለዋል?
ይህ የውጭ ምንዛሬ አግባብ ላለው፤ በእቅድ ለተደገፈ፤ ግልጽነትና ሃላፊነት ላለው ለምርትና ለስራ እድል ፈጠራ ቢውል (ለመዋቅራዊ ለውጥ) እያንዳንዱ ዶላር ሊያስገኘው የሚችለው ጥቅም አምስት እጅ ሊሆን ይችላል። ባለሞያዎች፤ ዓለም ባንክን ጨምሮ ድርብርብ (multiplier effect) ይኖረዋል የሚሉት ለዚህ ነው። ብድርና እርዳታ ኢትዮጵያን ዘመናዊ ቢያደርጋት ኖሮ ዛሬ የመካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ መሆን ነበረባት።
የውጭ እርዳታ ድጎማና ብድር በኢትዮጵያ ቢሰራ ኖሮ (ማለትም ገንዘቡ ባይባክን፤ ባይሰረቅና ከአገር ባይሸሺ ኖሮ) ለኢትዮጵያ እስካሁን የተሰጠው ብድርና ሌላ ድጎማ የምርት ኃይሉን ጨምሮ፤ የስራ እድልን በብዛት ፈጥሮ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ጠቅላላ ገቢ ቢያንስ ቢያንስ እጥፍ ያደርገው ነበር። የተማረው ወጣት ትውልድ የስራ እድል ይኖረው ነበር።
መዋቅራዊ ለውጥ ስለሚኖር የኑሮ ውድነት አይባባስም ነበር። የግሉ ክፍል ተወዳዳሪ ሆኖ ለውጭ ገበያ የሚሆኑ ምርቶችን ለማቅረብ የሚችልበት እድል ይፈጠር ነበር። በዜጎች መካከል ያለው የገቢና የኑሮ ልዩነት እየጠበበ ይሄድ ነበር። የገጠሩ ኢኮኖሚ ዘመናዊ የሚሆንበት እድል ይፈጠር ነበር። ግጭት ይቀንስ ነበር። ስደት ይቀንስ ነበር።
በኦፊሴል ሆነ በሌላ መንገድ የሚሰጥ ብድር ዋናው ሚናው የአገሪቱን የማምረትና የስራ እድል ለማሻሻል የሚለገስ እንጅ የጥቂቶችን ኪስ የሚሞላ መሆን የለበትም። አለያ፤ የብድር እዳ ተሸካሚው ተከታታይ ትውልድ መሆኑ የማይቀር ነው።
በተከታታይ ብድሩ ይስረዝ ወይንም ይቀነስ የሚለው መርህ መፍትሄ ሊሆን አይችልም። ብድርን በብድር መክፈልም ጎጅ ፖሊሲ ነው።
ከዚህ በፊት ድህነትን ለመቅረፍ ይበደሩ የነበሩ አገሮች፤ ደቡብ ኮሪያ፤ ታይዋን፤ ቻይና፤ ታይላንድ፤ ቬትናም ወዘተ የተበደሩትን የውጭ ምንዛሬ አግባብ ባለው ሁኔታ፤ እቅድ አውጥተው፤ የምርት ኃይላቸውን በማጎልመስ፤ የሰራ እድል በመፍጠር፤ በአስርት ዓመታት ዘመናዊ ኢኮኖሚ ለመመሰረት ችለዋል፤ ቢያንስ እየቻሉ ይታያሉ።
ኢትዮጵያ የሰባ ዓመታት የእርዳታና የብድር ታሪክ አላት። ባለፉት ሃያ ሰምንት ዓመታት ኢትዮጵያ ያስገኘችው የእድገት ውጤት መልካም ነው ቢባልም ካገኘችው ድጋፍ ጋር ሲመጣጠን ግን አብዛኛው የውጭ እርዳታ ባክኗል፤ ተሰርቋል፤ ከአገር ሸሽቷል። ይህ ሁኔታ ሊቅጥልና ሊደገም አይችልም።
ኢትዮጵያ የእርዳታ ጥገኛ አገር ሆና ከመቀጠል ይልቅ፤ በበለጠ መመካት የሚኖርባት፤ የሕዝቧን የማመረት አቅም፤ በተለይ የወጣቱን ትውልድ የማምረትና የመፍጠር አቅም በፍጥነት ማጠናከር፤ እያንዳንዱን ከውጭ የሚገኝ እርዳታ እንዳይባክን አድርጎ ለምርትና ለስራ እድል ፈጠራ መጠቀም፤ የኢኮኖሚው ፖሊሲ ለአገር በቀል እድገት ደጋፊ እንዲሆን ማድረግ ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት የረዢም ጊዜ ራእይ አገሪቱ በተወሰኑ አመታት ከእርዳታ ነጻ ሆና ራሷን የምትችልበትን የልማት ፍኖተ ካርታ በመቀየስ–ትኩረት የሚሰጣቸውን ሴክተሮች በመለየት የምርት ኃይሎችን፤ መፈብረክ፤ ኢንዱስትሪንና የገጠር ኢኮኖሚ ዘመናዊነትን ማሳደግ፤ ለብዙ ሚሊየን ወጣቶችና ሴቶች የስራ እድል መፍጠር አግባብ አለው።
ለማጠቃለል፤ ካለው የውጭ እርዳታና ብድር ልምድ የሚታየው ቁም ነገር፤ ይህ ሁሉ ግዙፍ እርዳታ ተገኝቶ የስራ እድል ለምን አልተፈጠረም? የኢንዱስትሪ ልማት በሰፊው ለምን አልተካሄደም? ኢትዮጵያ በምግብ ሆነ በሌሎች አስፈላጊ የፍጆት እቃዎች መስፈርቶች እስካሁን ለምን ራሷን አልቻለችም? የኑሮ ውድነት ለምን ተባባሰ? የገጠሩ ኢኮኖሚ ለምን ዘመናዊ ለመሆን አልቻለም? ብድር ሲጨምር የውጭ ምንዛሬ እንደ ገና እንዳይባክን ምን የተቋማት ለውጥ ታስቧል ወይንም ተመቻችቷል?
እነዚህን ጥያቄዎች እንመካከርባቸው፤ መንግሥትም ያስብባቸውና ወደ ፖሊሲ ይቀይራቸው።
በብዙ ቢሊየን ዶላር የሚታሰበው የተሰረቀውና ከአገር የሸሸው ኃብት እንዲመለስ ምን እቅድ አለ? የሚሉት ጥያቄዎችም ቢታሰብባቸው መልካም ነው።
የእርዳታና የብድር ታሪክ በኢትዮጵያ ከ70 ዓመታት በላይ እንደሆነው አሳይቻለሁ። ከአሁን በኋላ ኢትዮጵያ ከእርዳታ ይልቅ ኢንቬስትመንትንና ንግድን መመሪያ ብታደርግ የተሻል የልማት ውጤት ትቀዳጃለች የሚል እምነት አለኝ።
January 5, 3030