spot_img
Friday, June 14, 2024
Homeነፃ አስተያየትታላቁ የኢትዮጵያ ግድብ ስኬታማ የሚሆነው በተቆርቋሪ መንግሥት ብልሃት ነው

ታላቁ የኢትዮጵያ ግድብ ስኬታማ የሚሆነው በተቆርቋሪ መንግሥት ብልሃት ነው

አክሎግ ቢራራ (ዶር)
የካቲት 2 , 2012

“Fierce competition for fresh water may well become a source of conflict and wars in the future, “Kofi Annan, Secretary General of the U.N. 2001

“Contention over water has created a high risk of violent conflict by 2025,” Ban Ki-Moon, Secretary General of the U.N. 2008

እነዚህ የተባበሩት መንግሥታት መሪዎች ያቀርቧቸው ማስጠንቀቂያዎች ትክክል ናቸው። ወደፊት ብቻ ሳይሆን፤ ዛሬ ባለንበት ዓለም በተፈጥሮ ኃብት የይገባኛልነት ምክንያት በየአካባቢው ግጭቶች ይካሄዳሉ። የዓለም ሕዝብ ቁጥርና ፍላጎት እየጨመረና እየተለወጠ ሲሄድ ግጭቶችም እየተባባሱ ይሄዳሉ። ይህ አስጊ ሁኔታ በሃገራችን ከማንነት ጥያቄ ጋር እየተቆራኘ ለፖለቲካ ልሂቃን፤ ለአክራሪ ብሄርተኞች፤ ለጽንፈኞች፤ ለእስልምና ኃይማኖት አክራሪዎችና ለኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶች ቀስቃሽና መጋቢ ሆኗል። የውክልናው ጦርነት በኢትዮጵያ ላይ ከመቸውም ጊዜ በባሰ እየተካሄደ ነው። የማንነትን ጥያቄ እየዘለጠጡ ለሥልጣንና ለግል/ለቡድን ጥቅም የሚያውሉ ኃይሎች ያልተገነዘቡት ሃቅ፤ ቆምንለት ለሚሉትም ሕዝብ አጥፊ መሆኑን ነው።

ኢትዮጵያ ሃገራችን ካፈራቻቸው ምሁራንና ደራሲያን መካከል ለዘላለም የሚጠቀሱ ምክሮችንና አስተያየቶችን አብርክቶን ወደማይቀረው ዓለም ያለፈው ሎሬት ፀጋየ ገብረመድህን አንዱ ነው። እሱ ያለው ለትንተናየ አግባብ አለው።

“አህያ ሁን አለኝ፤ አህያ ሆንኩለት፤

አሰሱን ገሰሱን እንድሸከምለት።

መጓዡ ሁን ብሎ ፈረስ አደረገኝ፤

በየዳገቱ ላይ ወስዶ እሚጋልበኝ።

እንጃ ግን ሰሞኑን በግ ነህ ተብያለሁ፤

ሊያርደኝ ነው መሰለኝ አሁን ፈርቻለሁ። “

ኢትዮጵያ የተከበበች አገር መሆኗን ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ በድህረገጾች አሳስቤ ነበር። እንደ ዛሬ ግን ለአገሬ ሰግቸ አላውቅም። ወገኖቸ እንደ በግ እየታረዱ፤ እህቶቸ እየተነጠቁ፤ የአገሬ አንጡራ ኃብት እየተነጠቁ ሳይ ከስጋት በላይ ስጋት አደረብኝ። ሌላ አገር እንፍጠር፤ እንገንጠል ወይንም የራሳችን የበላይነት እናጠንክር ወይንም “ተረኛነታችን ይከበር” ወይንም ወደ ሥልጣን እንመለስ የሚሉ ኃይሎች ኢትዮጵያ የነገዋ ዩጎስላቭያ ወይንም ሩዋንዳ ወይንም የመን ወይንም ሊቢያ ብትሆን ምን ሊያገኙ ነው?

ዛሬ የምንኮራባት ኢትዮጵያ በቀደምትነት የሚያስፈልጋት ክብሯን፤ ግዛታዊ አንድነቷንና ሉዐላዊነቷን የሚያስከብርላት አመራርና መንግሥት ነው። ከፖለቲካ ፉክክርና ከምርጫ በፊት ይህች ታላቅ አገር በራሷ ልጆች ንትርክና የእርስ በእርስ ጦርነት እንዳትጠፋ ማድረግ የሁላችንም፤ በተለይ በድሃው ሕዝብ ድጋፍ የተማርነው ልጆቿ ነው። ይህች አገር ከጠፋች በኋላ ብናለቅስ ፋይዳ የለውም። በማንነት ሆነ በሌላ የግልና የቡድን ዝናና ጥቅም ምክንያት ዛሬ ኢትዮጵያን ወደ ገደል አፋፍ የሚገፏት እብሪተኞች፤ ጠባብ ብሄርተኞች፤ አክራሪ ኃይሎች ያልተገነዘቡትን ክስተት አስቀድሜ ለመናገር እገደዳለሁ። 

እነሱንም ሆነ ንጹሁን የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚጠብቃቸው ተከታታይ የእርስ በእርስ ግጭትና እልቂት እንደሚሆን መገመት አለባቸው። እንዴት ከመቶ አስራ አምስት ሚሊየን ሕዝብ ተቆርቋሪ፤ ብልሃተኛ፤ ለነገው ትውልድ የሚያስብ ይጠፋል? ወገን ወገኑን እንደ በግ ሲያርደው እያየን እንዴት እንቅልፍ ይይዘናል? እንዴት በልተን አናድራለን?

የታላቁ የኢትዮጵያ ግድብ ጉዳይ ከእነዚህ ከአገር ውስጥና ከውጭ ጠላቶች ፍላጎት፤ ጥቅምና “የኔ ተራ ነው” ባይነት ጋር ተያይዟል። የዛሬ ሰላሳ አምስት ዓመት የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሃፊ ሆኖ ያገለግል የነበረው ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ እንዲህ ብሎ እንደነበር አስታውሳለሁ። “በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት የሚካሄደው በውሃ የበላይነት ምክንያት ነው።” ይህ የአረብ ብሄርተኛ የድርጅቱ መሪ ከመሆኑ በፊትና ከሆነ በኋላ ጸረ-ኢትዮጵያ አቋም ነበረው። ሻብያንና ሌሎችን የብሄር እንቅስቃሴዎች ደግፎ ኢትዮጵያ የባህር በሯን እንድታጣ ካደረጉት ባለሥልጣናት መካከል አንዱ ነበር። በዐባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይ ጦርነት የማይቀር መሆኑን ቡትሮስ ቡትሮ ጋሊ ያውቅ ነበር።

የአረብ ሊግ የተባለው ድርጅት በኢትዮጵያ ላይ ያካሄደው ተከታታይ ጥቃት አሁንም አልቆመም። ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል ከጀርባ ሆኖ የሰራው ሴረኛ አንዱ ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ ሲሆን፤ በድርጅት ደረጃ ሌላው ጫና ያደረገው ስብስብ የአረብ ሊግ ነው። ከህወሓት፤ ከሻብያ እና ከኦነግ ጋር ሆኖ ሁኔታዎችን አመቻችቷል፤ ተመሳጥሯል። ይህ ሴረኛነት አሁንም በአዲስ መልክ ይታያል። በኢትዮጵያ ሰላምና እርጋታ የውሃ ሺታ የሆነበት ዋና ምክንያት፤ አንዱ የአገር ውስጥ የዘውግ ጽንፈኞችና አክራሪዎች ሲሆኑ፤ ሌላው ከጀርባ ሆኖ የገንዘብ፤ የመረጃ፤ የአቅም ግንባታ ድጋፍ የሚሰጡት ግብጽ፤ ኢራንና ተመሳሳይ ኃይሎች ናቸው።

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በዚህ ወር መጨረሻ በአዲስ አበባ ሰለ ሰላም፤ ስለ ደህንነትና ስለቭእርጋታ ውይይት ሲያደርግ ለአገራችን ሰላም ከነሱት ኃይሎች መካከል የግብጹ አል ሲሲ የሚያካሂደውን የውክልና ጦርነት እንዲያቆም ሹክ ያለው የኢትዮጵያ ባለሥልጣን ወይንም ሌላ ተቆርቋሪ ያለ አይመስለኝም። የሚነገረው ሌላ የሚሰራው ሌላ ነው።

ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ “በመካለለኛው ምስራቅ” ጦርነት አይቀርም ብሎ ሲናገር ሰሜን አፍሪካንም ይጨምራል፤ ግብጽን። ግን በቲግሪስ ኤፍራትስ ወንዝ አጠቃቀም ዙሪያ ስመለከተው፤ እስካሁን ድረስ ንትርክ ቢኖርም፤ ተርኪ፤ ኢራክ፤ ሶሪያና ሌሎች አገሮች ወደ ጦርነት አልሄዱም። ተርኪ ብዙ የመብራትና የመስኖ ግድቦችን ሰርታለች። የኔቶ አባል በመሆኗ ብቻ ሳይሆን በዚህች አገር ላይ አረቦች ጦርነት አላወጁም። እስራኤል አስደናቂና የተለየ የውሃ አጠቃቀም ዘዴዎችን ፈጥራ ለሌሎች አገሮች ምሳሌ ሆናለች። በመካከለኛው ምስራቅ፤ ዋናውና ወሳኙ የወንዝ አጠቃቀም ስኬት ምክንያት፤ ተርኪ አገር ወዳድ አመራር፤ ጠንካራና አገር ወዳድ መከላከያ ኃይል ስላላት ነው።

ከአፍሪካ አገሮች በባሰ ሁኔታ የውሓ እጥረት ያለው በመካከለኛው ምስራቅ ነው። የውሓ እጥረት ለጦርነት መንስኤ መሆኑን እየተቀበልኩ፤ ግን ይህ ሁኔታ ብቻውን ጦርነት አይቀሰቅስም። ብዙ አገሮች፤ በአውሮፓ ራይን፤ ሮንና ሌሎች ወንዞች፤ በኤዥያ ሜኮንግ፤ በላቲን አሜሪካ አማዞን፤ በአሜሪካ ሪዮግራንዲ እና በደቡባዊ አፍሪካ ሌሶቶና ደቡብ አፍሪካ ተዋውለው ስራ ላይ ያዋሉት የውሓ አቅርቦትና ፍጆት ውል ወዘተ ያለ ጦርነት ስኬታማ ሆነዋል። ስምምነት፤ ሰጥቶ መቀበልና መቻቻልም ሚና አላቸው። ይህ ከሆነ የአፍሪካ አገሮች የናይል ወንዝ ድርድር አድርገው (Nile Basin Initiative) ወንዙን ለጋራ ጥቅም አናውለው ካሉ በኋላ ግብጽ ለምን አሻፈረኝ አለች? ማንን ተማምና? ምን አይነት የዲፕሎማቲክ ድጋፍ አግኝታና ከማን? በኢትዮጵያ ውስጥ ምን አይነት ክስተት አይታና ተማምና?

የዐባይን ወንዝ በሚመለከት የሚታየው የአገር ውስጥና የዲፖሎማሲ የኃይል አሰላለፍና ጫና ነው። በዚህ ትንተና የማቀርበው በፖለቲካ አመራር ያለውን ጥንካሬና ድክመት ነው (hydro politics and power balance). በአሁኗ ኢትዮጵያ የኃይል አሰላለፉ እና የዲፕሎማሲ ጫናው ፍትሃዊና ሚዛናዊ አይደለም። የሚያደላው ለግብጽ ነው። ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ የውክልና ጦርነት እየተካሄደባት ነው። ይህን ክስተት ልንክደው አንችልም። ይህን የሚያደርገው ህወሓት ብቻ አይደለም፤ የኦሮሞ ብሄርተኞችና ጽንፈኞች፤ የእስልምና አክራሪዎች የአንበሳውን ክፍል ይዘውታል።

ኢላማው ምንድን ነው? እኔ ስከታተለውና ስገመግመው ኢትዮጵያን ለማዳከም፤ ቢቻል በሙሉ እንድትበታተን ለማድረግ ነው። ይህ አፍራሽነት የጀመረው ዛሬ አይደለም። ሕገ መንግሥቱ “እኛ የኢትዮጵያ ሕዝብ” በማለት ፋንታ፤ “እኛ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች” በሚል መሰረታዊ ሃረግ ሲጀምርና ኢትዮጵያን በዘውግና በቋንቋ ሲሸነሽኗት ነው ችግሩ የተፈጠረው። ይኼን የጣሊያኖችን እቅድ ስራ ላይ ያዋሉት የብሄር ልሂቃን ናቸው። ከጀርባ ሆነው ድጋፍ የሰጡት ግን እነ ኽርማን ኮህን እና አረቦች ናቸው። የዓባይ መዘዝ አለበት ማለት ነው።

ህወሕት መራሹ ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘበት ጀምሮ፤ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የሚሉት እሴቶች እየተወገዱ፤ በግልጽ የሚካሄዱትና እየጠነከሩ እንዲሄዱ የተደረጉት እሴቶች ጠባብ ብሄርተኝነትና ጽንፈኛነት፤ ህወሓት ተወግዶ በተራው “የእኛ፤ ኬኛ” የሚሉት ኃይሎች ስብስቦች ናቸው። ይህ  ጠባብ ብሄርተኛነት፤ ጽንፈኛነትና “ኬኛነት” ለማን ያደላል? ለግብጽ ነው የሚያደላው። የውክልና ጦርነት ስር እየሰደደ ሄዷል ማለት ይኼው ነው። እነዚህ የአገር ውስጥ ኃይሎች ለአገርና ለመላው ሕዝብ በመቆም ፋንታ ተወካይ ሆነው ለውጭ ኃይሎች እያገለገሉ ነው። ውክልና ማለት መሳሪያ ይዞ መተኮስና መግደል ብቻ አይደለም። እንደ ኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ያሉትን ተቋማትን ማፍረስ አንዱና ዋናው አካል ነው። የዘውግና የኃይማኖት አክራሪነትን እያስተጋቡ ኢትዮጵያዊነት እና አብሮና ተከባብሮ ይኖር የነበረውን የእስልምናና የክርስትና ወንድማማች ሕዝብ እንዲለያዩ ማድረግና ተቋማት እንዲፈርሱ መጎትጎት ሌላው ስልት ነው።

እርግጥ ነው ግብጽ የውሃ እጥረት እንዳለባት አልክድም፤ ማንም አይክድም። እኔ የምከራከረው ኢትዮጵያ ሉዐላዊነቷ በዓለም ታውቆ በነጻነቷ የቆየች አገር እንደ መሆኗ መጠን፤ የራሷ የሆነውን ዐባይን ገድባ ለራሷ ብሄራዊ ልማት ለመጠቀም ሙሉ መብት አላት ነው።  በድርድር ዙሪያ የኢትዮጵያ ሕዝብ በጨለማ እየኖረና እየተራበ ይኑር፤ የግብጽ ሕዝብ ግን የውሃና የምግብ ዋስትናው ይጠበቅ የሚል ሶተኛ አካል ወይንም ኃይል ሊኖር አይችልም።

አሜሪካ ከጎረቤቷ ከሜክሲኮ ጋር የምትጋራው ሪዮግራንዴ አለ፤ ብዙ ግድቦች ስርታ ትጠቀማለች። ተርኪ የቲግሪስ ኤፍራትስን ወንዝ ለኃይል ማመንጫና ለመስኖ ስራ ገድባለች። በአፍሪካ አህጉር በስምምነት ስኬታማ የሆነውና ሊጠቀስ የሚገባው ምሳሌና አማራጭ በሌሶቶና በደቡብ አፍሪካ መካከል የተደረገው ውል ነው። የሌሶቶ ሃይላንድ የውሃ ፕሮጀክት (The Lesotho Highlands Water Project (LHWP) ተብሎ የሚታወቀው ስምምነት፤ በአንድ በኩል ሌሶቶ የኃይል ማመንጫ ግድብ ያለበትን ውሃዋን ለደቡብ አፍሪካ እያቀረበች ደቡብ አፍሪካ ለሌሶቶ ግብር እንድትከፍል ያደረገ ውል ነው።

በውሉ መሰረት ሌሶቶና ደቡብ አፍሪካ በጋራ የሰሩት ድርጅት ብዙ ትልልቅ ግድቦችን የያዘ ሲሆን፤ እነዚህ ግድቦች በመላው ሌሶቶ ቦዮች ተከፍቶላቸው ውሃው ተሰብስቦ ቫል በተባለው በደቡብ አፍሪካ ወንዝ አጠራቃሚነት ለደቡብ አፍሪካ ህብረተሰብ የውሃ አገልግሎት ይሰጣል። በሌሶቶ መጋቢ ከሆኑት ወንዞች መካከል ማሊባማትሶ፤ ማትሶኩ እና ሴንኩ ይገኙበታል። እነዚህ ሁለት የጥቁር አፍሪካ አገሮች በጋራና በመተባበር የፈጠሩት የወንዝ አጠቃቀም ፕሮጀክት በአፍሪካ ከፍተኛ ቦታ የያዘ ነው። ሞዴል ነው።

ይኼን ምሳሌ የጠቀስኩብት መሰረታዊ ምክንያት ከዐባይ ጋር ይመሳሰላል ለማለት ሳይሆን፤ ለሁለት ምክንያቶች ነው።

አንደኛ፤ ፈቃደኛነት ካለ ለኢትዮጵያ ሌላው አማራጭ ግብጽ ከዐባይ ለምታገኘው ውሃ መጠን በስምምነት ኪራይ እንድትከፍል እንዲታሰብበት ለማሳየትና፤

ሁለተኛ፤ በደቡብ አፍሪካና በሌሶቶ መካከል የተደረገው ውል የሚያሳየው በውሉ መሰረት ሌሶቶ በራሷ ክልል ወይንም ወሰን ለሚገኘው ተቋም የሉዐላዊነት መብቷን ለመጠቀም እንደቻለች ለማሳየት ነው። በ 24 October 1986 የተፈረመው ውል አንቀጽ 7 (1) እንዲህ ይላል፤ “The Lesotho Highlands Development Authority shall have the responsibility for the implementation, operation and maintenance of that part of the Project situated in the Kingdom of Lesotho, in accordance with the provisions of this Treaty and shall be vested with all powers necessary for the discharge of such responsibilities. የሌሶቶ ልማት ባለሥልጣን በሌሶቶ ለሚገኘው የውሃ ፕሮጀክት የስራ አፈጻጸም ሂደት ደህንነት፤ ጥገናና ሃላፊነት ሙሉ ስልጣን ይኖረዋል” ይላል።

በተመሳሳይ፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ግድብ ባለቤት፤ ሉዐላዊነትና ባለሙሉ ስልጣን ኢትዮጵያ እንጅ ግብጽ ልትሆን አትችልም። ኢትዮጵያ በአስዋን ግድብ ላይ እንደማያገባት ሁሉ፤ ግብጽም ሆነ ሌላ ሶስተኛ አካል በታላቁ የኢትዮጵያ ግድብ አስተዳደር፤ ጤናማነት፤ ጥበቃ፤ ጥገናና አመራር ጣልቃ መግባት የለበትም። የኢትዮጵያ መንግሥት መሪዎች ዋና ሃላፊነት ይኼው ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከገቢው አውጥቶ በሰራው ግድብ ላይ ኢትዮጵያ ሉዐላዊ መብት የላትም፤ ግብጽ ወይንም ሌላ ሶስተኛ አካል ያገባዋል የሚል ካለ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት መከራከር ያለበት፤ ይህ አዲስ ክስተት፤ የዓለም መንግሥታት ከሚከተሉት ደንብ፤ ልምድ፤ ውልና ሕግ ውጭ ነው ብሎ ደፋር አቋም መውሰድ አስፈላጊ ነው። ይህን የግብጾችን ተንኮልና ሴራ የሚያስተጋቡ አካላት፤ ዓለም ባንክንና የአሜሪካን መንግሥት ጨምሮ ካሉ በይፋ ለኢትዮጵያና ለመላው የአፍሪካ ሕዝብ በግልጽ ይንገሩን፤ አይሸውዱን። ግልጽነት ይኑር። ሌሶቶ ሉዐላዊ መብቷን ካስከበረች ኢትዮጵያም የማታስከብረበት ምክንያት የለም። ግብጽ በሲዝ ካናል ሉዐላዊነት ተከራክራ መብቷን አስከብራለች። እኛስ?

ዓለም ባንክ፤ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት፤ የናየል ተፋሰስ አገሮች ድርድርና ውል በስምምነት ወንዙን እንጠቀም ብለው ቃል ከገቡና ተቋም ከፈጠሩ በኋላ ግብጽ እሚበተኛነት አሳይታለች። ግብጽ ከፈርዖኖች ዘመን ጀምራ ኢትዮጵያ ወንዞቿን እንዳትጠቀም ስታስፈራራን ኖራለች። ወረራዎችም አካሂዳለች። ጠ/ሚንስትር መለስ ዜናዊ አንድ ጊዜ ይህን የእብሪተኛነት ባህል እንዲህ በሚል ድፍረት አሰምቶ ነበር። “ኢትዮጵያን ለመውረር የመጣ ግብጻዊ ወደ አገሩ ተመልሶ ታሪኩን የተናገረበት ጊዜ የለም።” ግድቡን በሚመለከት፤ጠ/ሚንስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝም የወሰደው ተመሳሳይ አቋም ነበር። አገርን የሚመራ ማንኛውም ግለሰብ ታማኝነቱ ለኢትዮጵያና ለመላው ሕዝቧ ብቻ ነው፤ ለፓርቲው ወይንም ለዘውጉ ወይንም ለሥልጣኑ አይደለም።

የግድቡ ክርክር የወንዙ ውሃ መቀነስ ብቻ አይደለም። ግድቡ ሲሞላ ለተወሰነ ጊዜ የግብጽ የውሃ መጠን ሊቀንስ ይችላል። ግን መጠኑ ለግብጽ አስጊ እንደማይሆን ጥናቶች ያሳያሉ። ችግሩ ግብጽ አንዲትም ጠብታ እንዲቀንስ ፈቃደኛ አይደለሁም ማለቷ ነው። ይህ ግትር አቋም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁልጊዜም ቢሆን ረሃብተኛ ሆኖ እንዲማቅቅ፤ በጨለማ እንዲኖር ከመፍረድ ልዩነት የለውም። ደንታ ማሳየት ያለበት ግትሩ የአልሲሲ መንግሥት አይደለም። በሃላፊነት የሚጠየቀው ጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ የሚመራው መንግሥት ነው። በዚህ ዙሪያ ኢትዮጵያን ተጠቂና አጎብዳጅ እንድትሆን ያስገደዷትን ክስተቶች በአጭሩ ላቅርብ፤

 1. ህወሓት የኢትዮጵያን መንግሥት ተቃውሞ መቀሌ መመሸጉና በየአካባቢው ግጭቶችን መቀስቀሱ፤ በቅርቡ ልክ ትግራይ የተለየ አገር በሚመስል ሁኔታ፤ ህወሓት በመቀሌ ያሳየው የመከላከያ ኃይል ትእይንት—ልዩ ልዩ ከባድ መሳሪያዎችን የያዘ–ህወሓት አገር ወዳዱን የትግራይን ሕዝብ ለጦርነት የሚያዘጋጀው ይመስላል።

እንደ ግብጽ ላለ የውጭ ተመልካች በኢትዮጵያ አንድ መንግሥት የለም። ሁለት ወይንም ከሁለት በላይ መንግሥታት አሉ ወደሚል ድምዳሜ ያመራቸዋል። ኢትዮጵያን በቀላሉ ለማንበርከክ ይቻላል ወደሚል የተሳሳተ አቅጣጫ። የኢትዮጵያ የፌደራል መንግሥት በአስቸኳይ ከሚያደርጋቸው ውሳኔዎች መካከል በየክልሉ የተቋቋሙትን ልዩ የጦር ኃይሎችና የመሳሪያ ክምችቶች ብሂራዊ ወይን ኢትዮጵያዊ ማድረግ ነው። ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት አንድ ለአገር ሉዐላዊነትና ግዛታዊ አንድነት ታዛዢና ታማኝ የሆነ የመከላከያ ኃይል ብቻ ነው።

 • በጃዋር ሞሃመድ ቀስቃሽነት፤ ጠባብ ብሄርተኛውና ጽንፈኛው የቄሮ አካል፤ አክራሪ የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮችና ሽኔ ኦነግ የተባለው አሸባሪ እንቅስቃሴ በድሬ ዳዋ፤ በሃረር፤ በአዲስ አበባ፤ በኦሮምያ፤ በቤኒ-ሻንጉል ጉሙዝና በሌሎች ክልሎች የሚያካሂዱት አመጽ እየተባባሰ መሄዱ። ጃዋርንና ጠባብ ብሄርተኞችን ያደፋፈራቸው ክስተት የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ለጃዋር ልዩ ክብር በመስጠት ጥበቃ እንዲደረግለት ማድረጉ ነው። ይህ ሁኔታ ብዙ የአረብ አገሮችን፤ ግብጽን ጨምሮ አስደስቷቸዋል። አድልዎ ከፋፋይ አስተሳሰብ ነው።
 • በየአካባቢው በሰላም ወጥቶ መግባት አለመቻሉ፤ የመሳሪያ ክምች መብዛቱ፤ የንግድና የሌላው ክፍል የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መበከሉ።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በፍጥነት ከሚያድጉ አገሮች መካከል የመጀመሪያውን ደረጃ ይዞ እንደ ነበር ዓለም ባንክና ሌሎች ድርጅቶች ዘግበውታል። የኢትዮጵያ ልማት እንቅስቃሴ እነ ጃዋራና ሌሎች ጠባብ ብሄርተኞች፤ ጽንፈኞችና የእስልምና ኃይማኖት አክራሪዎች፤ ራሳቸውን “ፌደራሊስት” ነን የሚሉ አካሎችና የውክልና የጦር እንቅስቃሴዎች በሚያካሂዱት የተቀነባበረ አመፅ ምክንያት እየተጎዳና እየተበከለ ሄዷል። እድገትና ልማት ከአገር ዘላቂነነትና ከሕዝብ ደህንነት ጋር የተያያዙ ናቸው። በመውደቅ ላይ ያለ አገር ወይንም የወደቀ አገር ሊለማ አይችልም። ሶማልያ ምሳሌ ናት።

የፌደራልና የክልል ባለሥልጣናት ነፍሰ ገዳዮችን፤ የእምነት ተቋማት አውዳሚዎችን፤ አቃጣዮችን፤ የኢንዱስትሪና የመሰረተ ልማት አፍራሾችን፤ የወጣት ተማሪዎች አፋኞችን፤ የባንክ ዘራፊዎችን፤ የመሳሪያ ነጋዴዎችንና ሌሎች ወንጀለኞችን ተከታትሎ ለፍርድ ለማቅረብ አለመቻሉ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ ጎድቶታል። ኃይልን አንጠቀምም ባይነት ደህንነትን ከማስከበር ጋር አብረው አይሄዱም። አለያ መንግሥት ለምን አስፈለገ

የኢትዮጵያ ውድቀት መሰረታዊ ምክንያት የመንግሥት ባለሥልጣናት አግባብ ያለውን እርምጃ በፍጥነት ለመውሰድ ካለመቻላቸው ጋር የተያያዘ ክስተት ነው። ሕገወጥን ግለሰብና ቡድን እያባበሉ ሕግ ይከበር ማለት ዘበት ነው።

የፌደራሉ መንግሥት የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅና ለማስጠበቅ አለመቻሉ፤ የሕግ የበላይነት እንዲከበር ለማድረግ ቆራጠኛነትና ድፍረት አለማሳየቱ፤ በድምራቸው ሲታዩ ለአገሪቱ ልማት እየቀነሰ መሄድ ብቻ ሳይሆን፤ ለኢትዮጵያ ጠላቶች፤ በተለይ ለግብጽ አመች ሁኔታዎችን ፈጥሯል። ችግሩ የኢትዮጵያ ህልውና ጉዳይ ሆኗል።

ዳን ኮፕፍ (Dan Kopf) የተባለ የኢኮኖሚና ፋይናንስ ተመራማሪ Quartz Africa, በተባለው መጽሄት በ February 4, 2020 ባወጣው ዘገባ ዓለም ባንክን ጠቅሶ እንዲህ ብሏል። “The World Bank recently revised Ethiopia’s growth projection for 2020 growth down to 6.3 percent from 8.2 percent and down to 6.4 percent for 2021 from 8.2 percent… የኢትዮጵያ እድገት በተከታታይ ሁለት አመታት እየቀነሰ ይሄዳል” የሚል ዘገባ ነው። ይህ አያስገርመኝም። እርጋታ የሌለበት አገር የእድገት መጠኑ እንደሚቀንስ ከሌሎች አገሮች ልምዶች ተምረናል።

ከዚህ በፊት በጻፍኩት ትንተና የኢትዮጵያ የውጭ እዳ መጠን አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን በመረጃ በመደገፍ አሳስቤ አማራጮችን አቅርቤ ነበር። ምክሬን የሚያስተናግድ ባለሥልጣን አለ የሚል እምነት ባይኖረኝም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይስማው፤ ታሪክ ይመዝግበው በሚል ግንዛቤ ነው።

ዳን ክፕፍ “ኢኮኖሚስቶች እንደሚሉት ከሆነ የኢትዮጵያ የእድገት መጠን” በልዩ ልዩ ምክንያቶች እየቀነሰ ይሄዳል” በሚል ደምድሟል። በኔ ጥናትና ምርምር ከሁሉ በላይ አስጊ ሁኔታ የፈጠረው ዜጎች በሰላም ወጥቶ ለመግባት፤ ለመንቀሳቀስ፤ ለመነገድ ወዘተ አለመቻላቸው፤ የሕግ የበላይነት አለመከበሩ ለልማቱ መጠን ከፍተኛ ጫና አድርጓል።

 • አልካይዳ፤ አል-ሸባብ፤ ቦኮሃራም መሰል ድርጅቶች የውጭ፤ ለምሳሌ ከግብጽ መንግሥት፤ ድጋፍ እየተሰጣቸው ስር መስደዳቸው ኢትዮጵያን አጥፊነታቸው በግልጽ የሚታይ መሆኑ፤
 • በቀንና በይፋ ከአስራ ሰባት በላይ የሚሆኑ የባንክ ቅርንጫቾች መዘረፋቸው፤ የአካባቢ ፖሊሶች እርምጃ አለመውሰዳቸ፤ የተባበረና የተቀናጀ የኢኮኖሚ ሌብነት፤ ውድመትና ስርቆት መካሄዱ፤
 • ኢትዮጵያ በቀን ጅቦች ብቻ ሳይሆን፤ በሃሰተኞች፤ በፖለቲካ ነጋዴዎች፤ በአክራሪ የእስልምና ተከታዮች፤ በሕገወጠኞች፤ በውጭ ተቀጣሪዎች ወዘተ መበከሏ፤
 • የአገሪቱ ወሳኝ የሆኑ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች በልማት ስም ከኢትዮጵያዊያን እጅ እየተነጠቁ መሆናቸው፤ የአረብና ሌሎች የውጭ ኢንቬስተሮች እድሉን እየተጠቀሙበት መሆኑ፤
 • የኢትዮጵያ የደህነት ምስጢር ከአገር ወዳዶች እጅ እየወጣ መሆኑ፤
 •  የኃይማኖት ጦርነት እንዲከፈት ቅስቀሳዎችና እልቂቶች መካሄዳቸው፤
 1.  አብያተ ክርስቲያናትና መስጊዶች ሆነ ተብሎ መቃጠላቸው፤ ሕዝቡ የተቃጠሉትን ለመተካት ትኩርት እንዲሰጥ መገደዱ፤ የስራ እድል፤ የምርት እገት ለመፍጠር የሚችል ግዙፍ ኃብት መተኪያ መሆኑ፤
 1. ንጹህ ወገኖቻችን መገደላቸው፤ አስራ ሰባት ወጣት የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ተጠልፈው መወሰዳቸው፤ አርባ ሽህ የሚሆኑ የኮሌጅ ተማሪዎች ክክልሎች መባረራቸው፤
 1. የፌደራሉ መንግሥት የመከላከያ፤ የደህንነትና የፌደራል ፖሊስ ኃይሎችን አጣምሮ የማያዳግም ወታደራዊ እርምጃዎች ለመውሰድ አለመቻሉና፤
 1. የብሄር ተኮሩ ሕገመንግሥትና የክልሉ አስተዳደር የኢትዮጵያን ብሄራዊና ዘላቂ አቅም መበረዛቸውና ማዳከማቸው ይገኙበታል።

እነዚህ ሁኔታዎች (variables) በድምራቸው ሳያቸው የግብጽ መንግሥት የኢትዮጵያን የውስጥ የአስተዳደር ድክመቶችና ብልሽቶች ተጠቃሚ ሆኗል ለማለት እደፍራለሁ። ታላቋን ኢትዮጵያን በራሳችን በውስጥ የዘውግ ንትርክና አክራሪ በሆኑ፤ በተወሰኑ የእስልምና ኃይማኖት ከፋፋይ ሁከቶች አድክመናታል። ለጥቃት ዳርገናታል። የኢትዮጵያዊነት አገር ፍቅር ጠፍቷል። ምንም እንኳን የአምባገነን መንግሥት ቢመራትም፤ አገራችን ኢትዮጵያ የዚህ አይነት ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች አልገጠሟትም። የአገር ፍቅርና የሕዝብ ህብረት ከውጭ አደጋ እንደሚያድነን የአድዋ ታሪካችን አረጋግጧል።

ከግብጾችና ከሌሎች ለኢትዮጵያ ደህንነት፤ ብሄራዊ አንድነት፤ ብልጽግናና ዲሞክራሳዊ ስርአት ግንባታ ደንታ ከሌላቸው አካላት አንጻር ሁኔታውን ላሳየው።

 1. የኢትዮጵያ ሕዝብ በየቀኑ በሚደርስበት ግድያ፤ አፈናና ሌላ ግፍና በደል ሰላማዊ ሰልፍ እንዲወጣ፤ የሞቱትን እንዲቀብር፤ የጠፉትን እንዲፈልግ፤ የፈረሰውን እንዲተካ፤ እንዲያለቅስና እንዲተክዝ ተገዷል፤ ይህ ሁኔታ ተደጋጋሚ ሲሆን የረባ የልማት እንቅስቃሴ ለማድረግ አይቻልም።
 • እኔን የሚያሳፍረኝ፤ ሕዝቡ በገፍ ሲያለቅስና ሰላማዊ ሰልፍ ሲወጣ እንኳን በዘውግ አጥር ተለያይቶ ነው። ታፍነው የት እንደደረሱ የማይታወቁት ወጣት ተማሪዎች የአንድ ዘውግ አባላት በመሆናቸው ይሆን ሌላ፤ በሰብእነታቸው መስፈርት ብቻ አብሮ መጮህ፤ አብሮ ማዘንና ሰላማዊ ሰልፍ መውጣት አይታይም። “ይህች የኔም ልጅ ትሆናልች፤ ይኼ የኔም ልጅ ይሆናል” ማለት እንዴት ተሳነን? ጎንደሬው በገፍ ወጥቶ “ የኦሮሞ ደም ደማችን ነው” ማለቱ ከመቸው ተረሳ?
 • የሰው ህይወትና ደህንነት በዘውግና በኃይማኖት እንደተለያየ የውጭ ታዛቢዎች፤ በተለይ ግብጾች ጉዳችን ያውቁታል፤ ይጠቀሙበታል። ይህ ሁኔታ የውርደት ውርደት ነው!!
 • ራሱን በራሱ ዝቅ ያደረገን ህብረተሰብና አገር ጠላቱ ብቻ ሳይሆን ወዳጁም ይንቀዋል።
 • ለኔ ኢትዮጵያ ቆራጥ፤ ደፋርና አገር ወዳድ፤ ሕዝብ አፍቃሪ የሆነ መንግሥት የላትም እንድል ያስገደደኝ፤ ከሁለት ወራት በፊት በኦሮምያ ክልል ታፍነው የት እንደደረሱ የማይታወቁት ወጣት ተማሪዎች ሁኔታ ነው። ጉራጌ፤ አማራ፤ ኦሮሞ፤ ትግሬ፤ ሶማሌ ወይንም ሌላ ወላጅ ልጁን ከድህነት አሮንቃ ለማውጣት ትምህርት ቤት ሲልክ ልክ ናይጀሪያ እንደሆነው በቦኮሃራም መሰል ድርጅት ልጅ ሲነጠቅ፤ “ይህ ልጅ ወይንም ይህች ልጅ የኔም ልጅ ናት/ነው” ብሎ በአብሮነት መጮህ አለመቻላችን ከውድቀት በታች መቀበራችን ያመለክታል። ይህ ኢ-ሰብአዊነትና ጨካኝነት የተለመደ ሁኔታ መከሰቱን ያሳያል (The normalization of atrocities).

በኢትዮጵያ እንደዚህ አሳፋሪ እልቂት፤ አፈና በተደጋጋሚ ሲታይ የመጀመሪያ መሆኑ ነው። ነገ በኔ ላይ ይደርስ ይሆናል የሚል ስሌት እንዴት አይታይም?

 • እኛ ኢትዮጵያዊያን በማንኛም ዓለም ራሳችን ከፍ አድርገን፤ በራሳችን ተማምነን፤ ተከብረን በየትኛውም ዓለም ለመኖር መቻላችንን የዓለምን ሕዝብ ሲያስደንቅ ቆይቷል። ከአርጀንቲና እስከ ራሺያ፤ ከኢንዶኔዢያ እስከ ኖርዌይ፤ ከቻይና እስከ አላስካ፤ ከህንድ አገር እስከ ካናዳ ወዘተ ነጭ ላልሆኑ ሕዝቦች ሁሉ ለነጻነትና ለሉዐላዊነት ፈር የከፈተችው ኢትዮጵያ ለውጥን ተቀብላ ወደፊት በመሄድ ፋንታ ተጠቂ ያደረግናት እራሳችን ነን። የሌለ ታሪክ እየተረክን፤ አብሮ ችግሮችን ከመፍታትና ከልማት ላይ በማተኮር ፋንታ ቀን በቀን የሲዖል አለምን እየፈጠርንላትና እየቀበርናት ነው። ይህ ሁኔታ የተከሰተበት ጊዜ በግራኝ ሞሃመድ እና በዮዲት ጉዲት ዘመናት ነው። የጠፋውን ሕዝብና ኃብት ብናስበው ኖሮ ከእነዚህ እልቂቶች እንማር ነበር፤ አልተማርነም።
 • ኢትዮጵያ ሃገራችን ለጥቁር አፍሪካ ህብረት (Pan-Africanism) ከፍተኛ አስተዋጾ አድርጋ ነበር። አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ሌላ ሳይቀር ሰንደቅ ዓላማዋን ኰርጀዋል። ብዙ ፈረንጆች ልጆቻቸውን “ምኒሊክ፤ ቴዎድሮስ” ብለው የሚጠሩት ኢትዮጵያ የጀግኖች አገር ስለሆነች ነው። የታወቀችው አርቲስት አሽሌ ግራሃም ልጇን ምኒልክ ብላ ጠርታለች። ጠባብ ብሄርተኞች ግን አጼ ምኒልክን በማድነቅና በማክበር ፋንታ፤ በተገላቢጦሽ “ጡት ቆራጭ” ብለው የአኖሌን ኃውልት ገንብተዋል። ይህ ኃውልት መፍረስ አለበት። ምክንያቱም የጥላቻና የእልቂት ምልክት ኃውልት ነው።
 • የማንነት ጥያቄ ፈር ለቋል፤ ድንበር የለውም። የበላይነት የሚፈልግ አካል የማንኛውን መብት ጥሶ መሬቱም፤ ታሪኩም፤ ስልጣኑም የኔ ብቻ ነው ማለቱ አይቀርም። ነግ በኔ  እንበል የምለው ለዚህ ነው።
 • እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች ኢትዮጵያን ደካማና የተከፋፈለች አገር ናት ለሚል ግምገማና ድምዳሜ ዳርገዋታል።
 • ግብጽ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየገባች እያዩ፤ ተፎካካሪ ነን የሚሉ ፓርቲዎች ጠንካራ ብሄራዊ አቋም ሲወስዱ አይታይም። አብዛኛዎቹ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚታገሉት ለወንበር እንጅ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅምና ደህንነት አለመሆኑን የግብጽ ታዛቢዎች በሚገባ ያውቁታል። ግብጽ የሚጋበዘው ማንን ነው? ለውክልና አመች የሆኑትን ግለሰቦችና ስብስቦች።
 1. ጠንካራና አገር አቀፍ የሆነ ብሄራዊ ተፎካካሪ ፓርቲ በቀላሉ ለመመስረት አስቸጋሪ መሆኑን ግብጾች ያውቃሉ፤ የሚፈልጉት ብሄርተኮርና የእስልምና ኃይማኖት ፓርቲ እንዲመሰረት ነው። ይኼ ኢትዮጵያን ያደክማል፤ ያፈርሳታል።
 1. ህወሓት የበላይ ሆኖ አገሪቱን ይገዛ በነበረበት ወቅት ይታይ የነበረው የአገር ውስጥና የውጭ ወኔና እምቢተኛነት ዖዴፓ ህወሓትን ከተካ ወዲህ ድምጥማጡ እንደጠፋና ህብረተሰቡ እንደተከፋፈለ ታዛቢዎቹ ያውቁታል።
 1. ግብጾችና ሌሎች ኃይሎች በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ለጠባብ ብሄርተኝነት፤ ለጽንፈኛነትና ለእስልምና ኃይማኖት አክራሪነት ገበያ አለው የሚል እምነት አላቸው፤ ዶሃ ለጉባኤ አለጀዚራ ጋብዞኝ ሄጀ አይቸዋለሁ፤ ይህ ሁኔታ በዐብይ መንግሥት ተባብሷል። ልቅ ሁኔታ እንደተፈጠረ ግብጾች ያውቁታል፤ እየተጠቀሙበት ነው።

ግብጾችና ሌሎች የውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያ አንድ መንግሥት ሳይሆን ዘጠኝ ወይንም ከዚህ በላይ መንግሥታት አሉ የሚለውን ብሂል በማጠናከር ላይ ናቸው። “ኢህአዴግ ወደ ብልጽግና ፓርቲ ተለውጧል” ቢባልም በአስተሳሰቡ፤ በመንፈሱ፤ በሕገ መንግሥቱና በአደረጃጀቱ መሰረታዊ ለውጥ አይታይም። አሁንም ዘውጋዊ ነው።  

ለማጠቃለል፤

 • የዐብይ መንግሥት ታላቁን የኢትዮጵያን ግድብ ስኬታማ የማድረግ ግዴታ አለበት፤ ይህም ማለት መለስ ዜናዊና ኃይለማሪያም ደሳለኝ ይዘውት ከነበረው ብሄራዊ አቋም ዝንፍ ማለት የለበትም ነው።
 • ከላይ የሌሶቶን ምሳሌ ጠቅሸ እንዳቀረብኩት ታላቁ ግድብ የኢትዮጵያ አንጡራ ኃብት እንደመሆኑ መጠን፤ በበላይነት የማስተዳደሩ ስልጣን የኢትዮጵያ ብቻ ነው፤ ግብጽን ሆነ ሌላውን አካል አይመለከተውም፤ ሉአላዊ መብት ማለትም ይኼው ነው።
 • የወደፊቱን የድርቅና የውሃ መጠን አስቀድሞ ለመተንበይ አይቻልም፤ ጥንቃቄ መደረግ ያለበት ኢትዮጵያ ለመቆጣጠር በማትችልበት ሁኔታ የራሷን መብት፤ ነጻነትና ሉዐላዊነት መነገድ አደገኛ ነው።
 • አሜሪካና ዓለም ባንክ አሉበትም ቢባል፤ ድርድር ማለት የአገርን ብሄራዊ ጥቅም አሳልፎ መስጠት አይደለም። ማንም አገር የማያደርገውን የአሜሪካ ሆነ የዓለም ባንክ ባለሥጣናት በኢትዮጵያ ላይ እንዲጭኑባት መፍቀድ ብሄራዊ ክብርን ማሳነስና ከክህደት ጋር የሚያያዝ ድርጊት ነው። ለሉዐላዊነት ለንግድ አይቀርብም።
 • የግብጽ ኢኮኖሚና የመከላከያ ኃይል ጠንካራ ነው ተብሎ ቢገመትም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በግብጾች ሆነ በሌሎች የውጭ ጠላቶች ተሸንፎ አያውቅም። በኢህአዴግ (በብልጽግና) ፓርቲ አመራር ቢሸነፍ ሃላፊነቱን መሸከም ያለበት ሕዝቡ ሳይሆን የሚመራው መንግሥት ነው።
 • የማይካደው ክስተት የኢትዮጵያን ሕዝብና ኢትዮጵያዊነትን ያዳከመው፤ በዘውግ እንዲከፋፈል ሆነ ተብሎ የተጫነበት ሕገመንግሥትና የክልል አስተዳደር ነው። ለዚህ ተጠያቂዎች የዘውግ የፖለቲካ ልሂቃን ናቸው።
 • ታላቁን የኢትዮጵያን ግድብ ግጭት ለመፍታት በበላይ ሆኖ የሚያስታርቅ ገለልተኛ ዓለም አቀፍ አካል ስለሌለ (የተፋሰሰ አገሮች የሞከሩትን እቅድ ግብጽ ስላልተቀበለችው)፤ ግብጽና ኢትዮጵያ በጋራ ሆነው የአሜሪካን መንግሥትና ታዛቢ ነኝ የሚለውን ዓለም ባንክን ሙጥኝ በማለት አስታርቁኝ ብለዋል።
 • የኔ ግንዛቤና ስጋት የአሜሪካ መንግሥት ፍትሃዊና ሚዛናዊ የሆነ አቋም የለውም የሚል ነው። ግብጽ የአሜሪካ ስትራተጂክ ወዳጅ ናት። አሜሪካ የሚያዳላው ኃይል ላለውና ስትራተጂክ ወዳጅ ለሆነው አካል ስለሆነ፤ ኢትዮጵያ በውስጥ ክፍፍል ተበክላለች፤ ግብጽ ከእስራኤል ጋር ያላት ግንኙነት ለአሜሪካ ጠቃሚ ነው በሚሉ ስሌቶች የድርድሩ አድሏዊ እንደሚሆን እገምታለሁ።
 • የውሃ እጥረትን ችግር የፈታች አገር ኢስራኤል ናት። ይህች አገር የምተጠቀማቸው ብልሃቶች አሉ፤ ከእነዚህ መካከል፤
 • ሕዝብ የሚጠቀምበትን የውሃ ፈሰስ መልሶ ማጣራትና መጠቀም፤ ግብጽ ይህን አማራጭ አትጠቀምም፤ ብዙ ውሃ ታባክናለች፤ ግብጽ ባባከነች ኢትዮጵያ መቀጣት የለባትም፤
 • ስድሳ በመቶ የእስራኤል አገር በረሃና ደረቅ ነው፤ ይህች አገር ችግሩን የፈታችው ጥልቀት ያላቸውን የውሃ ጉድጓች በመቆፈርና ከውቅያኖስ ውሃ እየሰበሰበች በማጣራት ነው (Desalination plants). እስራኤል ብዙ ወጭ እያደረገች ቴክኖሎጅ ተጠቅማ ውሃዋን ለእርሻ ምርቶች ትጠቀማለች፤ ግብጽ የምተመካው በናየል ወንዝ ብቻ ነው፤ እያባከነች፤
 • ኢስራኤል ከላይ የቀረቡትን ዘዴዎች ተጠቅማ ባለፉት ሰባ አመታት ጠናካራ ኢኮኖሚ ፈጥራለች፤
 • ዓለም ባንክ ሊያድርጋቸው ከሚችለው አማራጮች መካከል በኢትዮጵያ ላይ ጫና ከማድረግ ይልቅ ግብጽ የእስራኤልን ሞዴል እንድትጠቀም ጫና ማድረግ ነው፤
 • የኢትዮጵያ መንግሥት ከግብጽ ጋር ሲደራደር፤ የምታገኙትን ውሃ አታባክኑ፤ ዲሳሊንኔሽን ተጠቀሙ፤ ቆሻሻውን ውሃ መልሳችሁ፤ አጣርታችሁ ተጠቀሙ ሊል ይችላል፤ እናንተም እስኪ ድሙ ሊል ይችላል፤
 • ኢትዮጵያን እንደ ዓባይ እናት አገር ብናያት፤ እናት ልጇ እየተራበና በጨለማ እየኖረ ያላትን ኃብት ለሌላ ቤተሰብ አትሰጥም የሚለውን መሰረተ ሃሳብ ከተጋራን፤ ኢትዮጱያም እንደ እናት አገር ታላቁን ግድብ የመጠቀም ሉዐላዊ መብት አላት ብሎ መከራከር ተገቢ ነው፤ ይህን ሃስብ እናሰር
 • ኢትዮጵያን ከድህነትና ክኋላ ቀርነት አሮንቃ ካላወጣናት ህገ ወጥነት፤ የእርስ በእርስ እልቂት፤ ሕገ ወጥነት፤ ረሃብና ስደት ይቀጥላል፤ ግድቡን ስኬታማ ማድረግ የህልውና ጉዳይ ነው፤
 • የኢትዮጵያ ሕዝብ በጨለማ እየኖረና እየተራበ፤ ኃብትና ጥሪቱን ለግብጽ ስጡ የሚል አማካሪና አስታራቂ አካል ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፤
 • ግብጽ ሃላፊነቷን ትወጣ፤ ሌሎችን አማራጮች ወጭ አድርጋ ትጠቀምና የሌሶቶውን ሞዴል አማራጮች ከግንዛቤ ውስጥ አናስገባቸው እያልኩ እመክራለሁ።

ከጠንካራ ጎን ሆኖ ለመከራከር፤ መፍትሄው የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም ጥንካሬና የአገሬን ብሄራዊ ጥቅም ማስከበር ግዴታየ ነው የሚል አቋም መውሰድ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት ግድቡን በሚመለከት የጥቁር አፍሪካ አገሮችን ድጋፍ መጠየቅና ከኢትዮጵያ ጋር አብረው እንዲቆሙ ማድረግ አለበት።

በመጨረሻ፤ የዓባይ ወንዝ ጉዳይ በአንድ ግድቡ አይቆምም።

ስለሆነም፤ ኢትዮጵያ የሌሶቶን ሞዴል ተጠቅማ፤ ግብጽ ከዓባይ ወንዝ በያመቱ ለምታገኘው ውሃ ኪራይ እንድትከፍል ለማድረግ ጥናት ማካሄድ እንዳለባት እንደ አማራጭ አቀርባለሁ። ያልተሞከረን ሃሳብ መሞከር አስፈላጊ ነው። አገር ወዳድ ኢዮጵያዊያን ልናደርገው የምንችለው አማራጭ ከላይ ያልቱን አማራጮች የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲመክርባቸው ጫና ማድረግ ነው።

እኛ ከተባበርና በአንድ ድምጽ ለአንዲት ታሪካዊ አገር ከቆምን፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም እና ሉዐላዊነቷን የሚያስከብርበትን ሁኔታ ለመፍጠር እንችላለን።

February 10, 2020

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here