spot_img
Wednesday, June 12, 2024
Homeአበይት ዜናየዘመናችን አድዋ ዘመቻ

የዘመናችን አድዋ ዘመቻ

Ethiopian Dam Dispute _ Adwa

የካቲት 19 ቀን 2012(27-02-2020)

የመጀመሪያው ያድዋ ዘመቻችን የተካሄደውና በድል አድራጊነት ያገራችንን ነጻነትና ልዑላዊነት ያስከበርነው የዛሬ መቶ ሃያ አራት ዓመት  ነበር።በዚያን ጊዜ ድንበር ሰብሮ ለመውረር ከውጭ የመጣውን ጠላት እንደ አንድ ሰው መክረን እንደ ንብ ተሰልፈን ካለበት መሬት ድረስ በመሄድ ድባቅ መትተን በመመለሳችን እኛ ብቻ ሳንሆን ሌላው ነጻነቱን ወዳድ ሕዝብ በኩራትና በአድናቆት የሚመለከተውና እንደምሳሌም የሚወስደው ታሪካችን ነው።ያ ያያቶቻችን ገድል አሁን ላለው ትውልድ በነጻነት የመኖር መብቱን አረጋግጦለታል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአድዋ ወዲህ በየጊዜው የሚመጡበትን  የወረራና የትንኮሳ ሙከራዎች ከአባቶቹ በወረሰው ጀግንነት ተባብሮ በመመከት ያገሩን ህልውናና የመኖር መብቱን ሲያረጋግጥ ቆይቱዋል።አሁንም ሆነ ወደፊት ክብርና መብቱን አሳልፎ የሚሰጥ ኢትዮጵያዊ ትውልድ አይኖርም።ይህንን የኢትዮጵያውያኑን ተፈጥሮዋዊ ወኔና አገር ወዳድነት ያላወቁ ጠላቶች ሁኔታ ተጠቅመው ፍላጎታቸውን ለማሙዋላት ያልሞከሩበት ወቅት የለም።አሁንም በመሞከር ላይ ናቸው።

በአባይ ወንዝና በሚገነባው የህዳሴ ግድብ ዙሪያ የተነሳው ያልተገራ የግብጾች የይገባኛል ጥያቄ አገርሽቶበት የኢትዮጵያን ህልውና ከመፈታተን ደረጃ ላይ ደርሱዋል።የአሁኑን ጊዜ ልዩ የሚያደርገው በግብጽ ጀርባ ጥቅማቸውን ለማስከበር ኢትዮጵያን መስዋእት ለማድረግ የተሰለፉ መኖራቸው ነው።ወዳጅና አሳቢ መስለው ጉዳዩ የሚመለከታቸው አገሮች ኢትዮጵያ፣ሱዳንና ግብጽ እንዲደራደሩና እነሱም በታዛቢነት ለመሳተፍ ፈቃደኞች ሆነው በመቅረብ ድርድሩ ከመጀመሩ በፊት ይኖረናል ያሉትን  የታዛቢነት ቦታቸውን በአደራዳሪና በዳኛነት ለውጠው የድርድሩ ውጤት ወደ አንድ ሚዛን ማለትም ወደ ግብጾች እንዲያደላ በኢትዮጵያ ተወካይ ተደራዳሪዎች ላይ ጫና በማስቀመጥ ውሉን እንዲቀበሉና እንዲፈርሙ በማስገደድ ላይ መሳተፋቸው የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ስሜትና ቁጣ ቀስቅሱዋል።

ይህ ኢፍትሃዊና የማንአህሎኝነት ምግባር ከወረራ የተለዬ ተደርጎ አይታይም።ኢትዮጵያ ለሌሎች አገሮች ጥቅም መስዋዕት የምትሆን ጠቦት አይደለችም።የሁለት መቶ ሚሊዮን ጀግና ሕዝብ አገር ነች።ኢትዮጵያውያን በሆነባልሆነው ብንጨቃጨቅም ብሔራዊ መብታችንን አሳልፈን አንሰጥም።ጠላቶቻችን ስህተት ውስጥ እንዲገቡ ያደረጋቸው አሁን የገጠመንን የፖለቲካ ቀውስ ተገን በማድረግና አገሩን የሚወጋ ፣የሚክድ የውስጥ ጠላት አለ ብለው በማመናቸው ነው።ይህ ግን  ዱሮም አልሆነም አሁንም እንደማይሆን ሊያውቁት ይገባል።አባይ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ንብረትና ኩራት ነው።ለጊዜያዊ ጥቅም ብሎ አገሩን የሚከዳ አይኖርም።የከዱ በታሪክና በትውልድ የሚኖራቸውን ቦታ ጠንቅቆ ያውቃል።

 የግብጽ አባይን የመቆጣጠር ሙከራ ከአስር ዓመት ወዲህ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የተከሰተ ሳይሆን ዘመናት ያስቆጠረ ነው፤በጦር ሃይልም ያደረጉት ሙከራ ሳይሳካላቸው ቀርቱዋል።

ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን የትብብር መድረክ(International Ethiopians Solidarity Forum) በአባይ ጥያቄ ላይ ያለው አቋም የሚከተለው ነው

1 የአባይ ወንዝ ማንም የውጭ ሃይል የይገባኛል ጥያቄ የማያቀርብበት የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብት ነው።

2 አትዮጵያ በግዛቱዋ ውስጥ በሚፈስ ወንዝና ጅረት የመጠቀም መብቱዋን ማንም ሊከለክልና ጣልቃ ሊገባበት  አይችልም።

3 ኢትዮጵያ ወንዞችዋን በአግባቡ ተጠቅማ ከድንበሩዋ አልፎ በሚሄደው የውሃ ተፋሰስ ላይ አገሮች ለሚያደርጉት አጠቃቀም ጣልቃ አትገባም።ሱዳኖችም ሆኑ ግብጾች  በመሬታቸው ላይ የሚፈሰውን ውሃ የመጠቀም መብታቸውን ታውቃለች።በአስዋን ግድብና ተመሳሳይ ዕቅዶች ላይ ጥያቄ   እንዳላነሳችና  ችግር እንደማትፈጥር ሁሉ በእሱዋም የህዳሴ ግድብም ሆነ በተመሳሳይ ተግባር ላይ ችግር እንዳይፈጠርባት ትሻለች።ይህ መብቱዋ እንዲከበርላት ድምጻችንን እናሰማለን፤የሚያስፈልገውን ሁሉ ለማበርከት ዝግጁ ነን።

4 የኢትዮጵያ መንግሥት የአገሩን ጥቅም በመደራደር አሳልፎ እንዳይሰጥ፣ከተጀመረውም ድርድር ውስጥ እንዲወጣ እንጠይቃለን። በሆነ ባልሆነው ሰበብ መልሶ እንዳይገባም እናሳስባለን። የአገራችንን ህልውና የማስከበር እንጂ ተደራድሮ አሳልፎ የመስጠት ሥልጣን የለውም።

5 የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን የባዕዳን ሴራ እንደ ጥንት አያት ቅድመአያቶቹ በአንድነት ተሰልፎ እንዲቋቋመው ጥሪ እናደርጋለን።ይህ የፖለቲካ ጥያቄ ብቻ  ሳይሆን የህልውናም ጥያቄ ነውና  ለህልውናችን ለዚህ ዳግማዊ አድዋ ዘመቻ በህብረት እንቁም እንላለን።

6 መንግሥት በብድርና በፖለቲካ ሥልጣን ድጋፍ ምክንያት ከሌሎች አገሮች ጋር ከሚያደርገው ውልና ስምምነት እንዲታቀብ እንጠይቃለን።የሚደረጉ ውሎችና ስምምነቶች ሕዝብ የሚያውቃቸውና ምክር ቤቱ በሚፈቅደው መልክ መሆን አለበት፤አንድ መሪ ወይም አንድ ነጠላ መንግሥት የሚወስነው መሆን የለበትም እንላለን።

    አንድነታችን ሃይላችን ነው! የባዕዳንን ሴራ ተባብረን እናክሽፍ!!

    ኢትዮጵያ ለዘላለም በነጻነት ትኑር!!!

ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን የትብብር መድረክ (International Ethiopian Solidarity Forum)

Email inter.ethiopiansolidarityforum1@gmail.com    

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here